“ከተረፈ ብቻ ነው ሴት ወደ ት/ቤት የምትላከው”

Thursday, 03 July 2014 12:45

 

ወ/ሮ ዘርትሁን ተፈራ የሲቄ

የሴቶች ልማት ማህበር መስራች

 

እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊት ወጣት ለአቅመ ሄዋን ሲደርሱ በወግ ማዕረግ ጋብቻ ፈፅመዋል። በትዳራቸው ሁለት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፤ ትዳራቸው ዘለቄታ ሳይኖረው ቀረና በፍቺ ተጠናቀቀ። እኚህ እናትም ሁለት ልጆቻቸውን በብቸኝነት በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፈው አሳደጉ። ነገር ግን እርሳቸው ላይ የደረሰውን ፈተና አብዛኞቹ የሀገራችን ሴቶች እንደሚጋሩት ስለገባቸው ቀጣዩ ትውልድ የዚህ ችግር ሰለባ እንዳይሆን ለመስራት ቆርጠው ተነሱ። የሲቄ ሴቶች ልማት ማህበር መስራቿ ወይዘሮ ዘርትሁን ተፈራ።

ወይዘሮ ዘርትሁን ተወልደው ያደጉት ምዕራብ ሸዋ ዞን በሚገኘው ወለጋ አካባቢ ነው። በላይብረሪ ሳይንስ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም በዴቨሎፕመንት ማኔጅመንት ሁለተኛ ድግሪያቸውን የያዙ ሲሆን፤ ካናዳን ጨምሮ በተለያዩ የውጭ ሀገራት ተምረዋል። እድገታቸው እና ኑሯቸው አዲስ አበባ ቢሆንም በተለይ በትውልድ አካባቢያቸው በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና ያውቁት ስለነበረ እነዚህን ሴቶች የሚረዳ ማህበር ለማቋቋም በማሰብ ከጥቂት ጓደኞቻቸው ጋር ሆነው ሲቄ የሴቶች ልማት ማህበር የተባለውን እና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰውን ማህበር መሰረቱ። በወቅቱ በማህበሩ የሚታገዙት 20 ሴቶች ብቻ ነበሩ። ይህ ማህበር ከተመሰረተ 16 ያህል ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ያሉት አባላት ቁጥርም ከ50ሺህ በላይ እንደደረሰ ወይዘሮ ዘርትሁን ይገልጻሉ። ለአምስት ዓመታት ያህል ማህበሩን በትርፍ ጊዜያቸው ሲያንቀሳቀሱ ቢቆዩም አባላት ቁጥር ሲጨምር ግን የሙሉ ጊዜ ስራቸው አደረጉት። ወይዘሮ ዘርትሁንን በድርጅቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ አነጋግረናቸዋል።

ሰንደቅ፡- ማህበሩ የተቋቋመበት ዓላማ ምንድን ነበር?

ወ/ሮ ዘርትሁን፡- የማህበሩ ዓላማ ችግረኛ የሆኑ እናቶችን እና ሴት ተማሪዎችን መርዳት ነው። ለእነዚህ ሴቶች የሚጠቅም ስራን መፍጠር፣ የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ እገዛ ማድረግ እንዲሁም የሚደርሱባቸውን ጥቃቶችና ችግሮች መከላከል የሚችሉበትን አቅጣጫ ማሳየት ነው። በተጨማሪም ስልጠናዎች ይሰጣሉ።

ሰንደቅ፡- ማህበሩ ስራ ሲጀምር የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

ወ/ሮ ዘርትሁን፡- ሲጀምር በ20 ሴቶች ነው የጀመርነው። በጣም በችግር ላይ ያሉ እና ማገዶ ተሸክመው ከሰበታ አካባቢ ወደ አዲስ አበባ እያመጡ የሚሸጡ እናቶችን በማገዝ ነው ስራውን የጀመረው። ሲጀመር መንግሥታዊ እንዳልሆነ ድርጅት ሳይሆን፣ በራስ ተነሳሽነት እኔ ራሴ ጓደኞቼን አስተባብሬ ነው የጀመርኩት። ከኪሳችን ገንዘብ አውጥተን አንዳንድ የእጅ ስራ ሰርተው እንዲሸጡ እና ገቢ አግኝተው እንዲቆጥቡ በማድረግ ነው የጀመርነው። ስንጀምር አለም ገና አካባቢ ነበር የጀመርነው። ከዚያም አስፋፍተን የምዕራብ ሸዋ ዞንን እስከ ወሊሶ ድረስ፤ ወደ ምስራቅ ወለጋ ነቀምት እና ነቀምት ዙሪያ እየሰራን ነው። አሁን በቅርቡ አምቦ ላይም ጀምረናል። በዚህም በአሁኑ ወቅት ከ50ሺ በላይ ሴት አባላት አሉን።

ሰንደቅ፡- ከሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለየት ያሉ ፕሮግራሞቻችሁ ምንድን ናቸው?

ወ/ሮ ዘርትሁን፡- እንደፕሮግራም እኛ በልጃገረዶች ትምህርት ላይ እንሰራለን። ከ20 በላይ በሆኑ ትምህርት ቤቶች ይሄንን ስራ እንሰራለን። ይሄ ማለት ህብረተሰቡ በሴት ልጅ ትምህርት ላይ ያለው አመለካከት እንዲቀየር እና ወደ ት/ቤት እንዲልክ፤ ትምህርት ቤት ውስጥ ያለው ሁኔታም ለሴት ልጆች ምቹ እንዲሆን ለምሳሌ የሴት መፀዳጃ ቤቶችን በመገንባት፣ የሴቶች ክበባትን በማቋቋም እና በጣም ችግረኛ ለሆኑ ሴት ተማሪዎች ዩኒፎርም እና ደብተሮችን በመግዛት እገዛ እናደርጋለን።

እናቶች ደግሞ የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስደው በራስ አገዝ ቡድን ተደራጅተው የራሳቸውን ገቢ እንዲያገኙ፣ ስራዎችን እንዲፈጥሩ እደርጋለን። ሰርተው ያገኙትን እየቆጠቡ የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲገነቡ እናደርጋለን። ለዚህም እነዚህ እናቶች የራሳቸው የሆነ ነገር ይኖራቸዋል። እርዳታ የሚለውን ነገር ወደ ጎን ትተው በሚሰጣቸው ስልጠና የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ እና የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ እያደረግን ነው። ሴቶቹ በግልም በጋራም በጥቃቅን ንግዶች፣ በከብት እና ዶሮ እርባታ፣ በጓሮ አትክልት ልማት እና በመሳሰሉት ስራዎች ላይ ይሰማራሉ።

ሰንደቅ፡- ሲቄ የሴቶች ልማት ማህበር በአብዛኛው የሚታወቀው በኦሮሚያ ክልል ነው። እንቅስቃሴያችሁን በዚሁ የገደባችሁት ለምንድን ነው?

ወ/ሮ ዘርትሁን፡- ብዙ ምክንያቶች አሉን። በመጀመሪያ ስቄ ማለት በኦሮሚያ ሴቶች የሚይዟት ቀጭን ዱላ ማለት ነው። ያቺ ዱላ የምታሳየው ሴቶችን በትብብር ስለመብታቸው የሚናገሩበት መሆኗን ነው። በተለይ በባሌ አካባቢ ሲቄ ስለምትታወቅ ይሄንን ስም ይዘን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ብንሰራ ውጤታማ ያደርገናል ከሚለው የተነሳ ነው። ስራውን የጀመርነውም በዚህ ክልል ውስጥ ነው። በተጨማሪም በክልሉ ብዙ ለችግር የተጋለጡ ሴቶች አሉ። የእኛ አቅም የሚችለው በዚህ ክልል ውስጥ መንቀሳቀስን ብቻ ነው። በአዲስ አበባ ደግሞ በርካታ ተመሳሳይ ስራ የሚሰሩ ድርጅቶች አሉ። በአንድ ቦታ መደራረቡ ምን ይጠቅማል? ብዙ ሊሰራባቸው የሚገባ ቦታዎች አሉ። እኛ አቅማችን የቻለውን ያህል ያልተሰራባቸውን ቦታዎች እያደረስን ነው።

ሰንደቅ፡- በስራ አጋጣሚ ስትመለከቱት በክልሉ ከሴቶች ላይ ያለው ችግር ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ዘርትሁን፡- እኛ በስራ አጋጣሚ እንደተገነዘብነው አንዱ የሴቶች ችግር አለመማር ነው። በገጠር አካባቢ ቅድሚያ የሚሰጠው ለወንድ ነው። ከተረፈ እና አቅም ከቻለ ብቻ ነው ሴቷ ትምህርት ቤት የምትላከው። ይህ ደግሞ ጉዳቱ ከግለሰቧ አልፎ ለቤተሰብም ለሀገርም ነው። ሌላው ያየነው ነገር እርዳታ የሚለውን አስተሳሰብ አስወግደን ሴቶች በራሳቸው መንቀሳቀስ እንዲችሉ እገዛ ማድረግ እና መንገድ ማሳየት እንዳለብን ነው። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ልጃገረዶችን ማስተማር እንዳለብን እና ሁለንተናዊ ጥቅሙን ማሳወቅ እንዳለብን ተገንዝበን በፕሮግራማችን ውስጥ አካተናል።

በተለይ በወጣት ሴቶች ላይ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራን ነው። በፀጉር ስራ፣ በልብስ ስፌት ሞያ፣ በማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ምርት ስራ ላይ ተሰማርተው የራሳቸውን ገቢ እንዲያገኙ እያደረግን ነው።

ሰንደቅ፡- በእነዚህ ሴቶች ላይ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት በምትሰሩበት ወቅት የየአካባቢዎቹ ባህል ያሳደረባችሁ ተፅእኖ ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ዘርትሁን፡- ብዙ ባይባልም ያስቸግራል። ቢያስቸግርም ግን እየሰራንበት ነው። ይሄንን ችግር ለመቅረፍ ማህበረሰቡን እናሳትፋን። በማህበረሰቡ ውስጥ ድምፅ ያላቸውን የኃይማኖት መሪዎች፣ በእድር አካባቢ ያሉ ትላልቅ ሰዎችን እናሳትፋለን። በተጨማሪም ከሴቶች ጉዳይ ጋር አብረን ነው የምንሰራው። በዚህ መልኩ የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንቀርፋለን። በእርግጥ የትም ሲኬድ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል ማለት አይደለም። ነገር ግን በሂደት ነገሮች እየተስተካከሉ ይሄዳሉ።

ሰንደቅ፡- በማህበሩ እገዛ ተደርጎላቸው ራሳቸውን የቻሉ ሴቶች ተመልሰው ማህበሩን እንዲያግዙ የሚደረገው ጥረት ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ዘርትሁን፡- በማህበራችን 65 ያህል ልጃገረዶችን አዶለሰንት ገርልስ ስኮላርሺፕ በሚል ዩኒቨርስቲ እስከሚደርሱ ድረስ የኢኮኖሚ ችግራቸውን ሁሉ እየፈታን በትምህርታቸው እንዲገፉ አድርገናል። ከእነዚህ ውስጥ 30 ያህሉ ትምህርታቸውን አጠናቀው ተመልሰው ማህበሩን በመርዳት ላይ ናቸው። በህግ አማካሪነት፣ እናቶችን በማደራጀት፣ በማስተማር እና በመሳሰሉት ስራዎች እያገዙን ያሉ ልጃገረዶች አሉ።

ሰንደቅ፡- ማህበሩ የ16 ዓመታት እድሜ እንደማስቆጠሩ የተሰሩት ስራዎች የታሰበውን ያህል ውጤታማ ናቸው? የህብረተሰቡ ምላሽስ ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ዘርትሁን፡- እኛ እንግዲህ በሰራናቸው ስራዎች ውጤታማ ነን ብለን እናስባለን። ህብረተሰቡ ግን የተሰራው ስራ በቂ አለመሆኑን ነው የሚነግረን። ብዙ ስራ ብንሰራም እንዲህ አይነት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሌሎች ቀበሌዎች እና ወረዳዎች እንዳሉ እየነገሩን እና ተመሳሳይ ስራ ብታስፋፉልን እያሉን ነው። እኛም በህዝቡ ጥያቄ መሰረት ድጋፋችንን ለማስፋት እና ያልተዳረሱትን አካባቢዎች ለማዳረስ፣ የማዳረስ እቅድ አለን።

ከሴቶች እገዛ ጎን ለጎን ደግሞ ለህፃናትም ድጋፍ እናደርጋለን። በወሊሶ አካባቢ 50 ያህል እናትና አባት የሌላቸው ህጻናትን እየረዳን እንገኛለን። ማህበሩ በተለይ በልጃገረዶች ትምህርት ላይ በስፋት የመስራት እቅድ ነው ያለው። ጎበዝ ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ወደፊት እንዲገፉ የማበረታታት ስራን ለመስራት በስፋት አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው። ለወደፊት ደግሞ ከዚህ በላይ የመስራት ሰፊ እቅድ ይዘናል።

ሰንደቅ፡- ማህበሩ ከረጂ አባላት ከሚያገኘው ገቢ በተጨማሪ ያሉት የገቢ ምንጮች ምንድን ናቸው?

ወ/ሮ ዘርትሁን፡- የእኛ ገቢ የሚገኘው ከውጪ ነው። ከአባላት የሚገኝ ገቢም ይኖራል። ጥሩው ነገር እነዚህ 50 ሺህ ያህል ሴቶች ራሳቸውን የቻሉ እና የራሳቸውን ገቢ የሚያገኙ መሆናቸው ነው። እኛ የቴክኒክ እና የክህሎት ስልጠና ነው የምንሰጣቸው። ሊሰሩ የሚችሉበትን መንገድ የማሳየት እና የእገዛ ስራ ነው እንጂ የምንሰራው፤ በአብዛኛው በራሳቸው ነው ሰርተው ተጠቃሚ የሚሆኑት።

ሰንደቅ፡- ወንዶች በሴቶች ላይ ለውጥ እንዲመጣ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚደረግበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ዘርትሁን፡- ስንነሳ በወንዶች እና በሴቶች መካከል እኩል የሆነ የትምህርት እና የሀብት እድል እንዲኖር ለማድረግ ነው። በሴቶች እና በወንዶች መካከል ያለውን የተራራቀ ክፍተት ለማቀራረብ ነው የሁሉም በሴቶች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ዓላማ። ሆኖም ግን የወንዶችን ተሳትፎ ይጠይቃል። ለዚህም ሲባል ወንዶችን በማህበረሰብ ውይይት ውስጥ እናሳትፋን። የሴቶችን ችግር ለመቅረፍ እገዛ እንዲያደርጉ እናደርጋለን። ባል ያላቸው ሴቶችን ስናሰለጥንም የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ እናሳትፋለን።

በትምህርት ቤት ውስጥ ደግሞ ወንድ ተማሪዎች ሴት ተማሪዎችን እንዲያግዟቸው፤ የአቻ ለአቻ በሚለው ትምህርት እንዲሳተፉ እናደርጋለን። ወንዶች በቀጥታ ተጠቃሚ እና አጋዥ ባይሆኑም በተዘዋዋሪ ግን ተሳታፊዎች ናቸው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1426 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 754 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us