ማን ከማን ይማራል?

Friday, 04 October 2013 19:09

በመስከረም አያሌው

በየአመቱ ከአዲስ አበባ ብቻ ከ15ሺህ በላይ ዜጐች በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት ይሰደዳሉ ይላል ከአዲስ አበባ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮ የተገኘ መረጃ። ከአዲስ አበባ ብቻ በህጋዊ መንገድ የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር ይሄን ያህል ይሁን እንጂ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ መገመት ከሚቻለው በላይ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮም በተለይ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት በተለያየ መልኩ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ቢሮው ባለፈው ሳምንት በከተማችን የሚገኙ ኤጀንሲዎችን ሰብስቦ አወያይቶ ነበር። በውይይት መድረኩ ላይ ከ400 በላይ የሚሆኑ ኤጀንሲ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም መደረግ ባለበት ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

ከሁሉም በላይ በውይይቱ ወቅት ትኩረት የተሰጠው ወደ ውጭ ሀገራት የሚሰደዱ ዜጐችን በሚሄዱበት ሀገር ሊገጥሟቸው ከሚችሉ ችግሮች ለመታደግ የተለያዩ ስልጠናዎች መስጠት አለበት የሚለው ነበር። አብዛኞቹ ወደ ውጭ ሀገራት የሚሄዱ ሰራተኞች በሚሄዱበት ሀገር የሚጠብቃቸውን ነገር የማያውቁ እና ዝም ብለው በድፍረት የሚጓዙ በመሆናቸው ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ ነው። በመሆኑም በቢሮው አማካኝነት እነዚህ ችግሮች በተመለከተ ሠራተኞቹ ከመሄዳቸው በፊት በባለሙያዎች ስልጠና እንዲሰጣቸው እየተደረገ ይገኛል። በዚህም መሠረት ለ18ሺ ዜጐች በተለያየ ጊዜ ስልጠና ለመስጠት ታቅዷል።

ቢሮው ይሄንን አላማውን ለማሳካትም ለጊዜው በሰባት አብይ ማዕከላት ስልጠናውን ለመስጠት አስቧል። በስልጠናውም ሄደው በቤት ሰራተኛነት ለመቀጠር የሚያስቡ እና ስልጠናውን ለመውሰድ ፈቃደኛ ለሚሆኑ 3ሺ ያህል ሰዎች ስልጠናውን ለመስጠት ታቅዷል።

ከየኤጀንሲዎች የተገኙ ተወካዮች እንደገለፁትም ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች በሰው ሀገር ሄደው ላልጠበቁት አደጋ እና ችግር እየተጋለጡ ያሉት በሀገር ውስጥ በቂ የሆነ ስልጠና ተሰጥቷቸው እና ዝግጅት አድርገው ባለመሄዳቸው ነው። በእኛ ሀገር ያለው እና ዜጐቻችን በሚሄዱበት ሀገር ያለው ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ እና አስተሳሰብ በጣም የተራራቁ በመሆናቸው ኢትዮጵያውያኑ እዚያ ሲሄዱ ከሁኔታው ጋር መላመድ እያቃታቸው ላልታሰበ አደጋ ይጋለጣሉ። ግራ በመጋባትም ላልተፈለገ እና ለተዘበራረቀ ህይወት ይዳረጋሉ። በመሆኑም ይህን ክፍተት ማስቀረት ባይቻል እንኳን ለማጥበብ እንዲህ አይነቱ ስልጠና ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ነው ሀላፊዎቹ የገለፁት።

ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ ብቻ 459ሺ 810 ዜጐች በህጋዊ መንገድ ወደተለያዩ አረብ ሀገራት ለስራ ፍለጋ የተሰደዱ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥም 76ሺ 562ቱ ከአዲስ አበባ ከተማ እንደሚሄዱ ነው የአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው በመድረኩ ላይ የተናገሩት። በመሆኑም ከከተማ አካባቢ የሚሄዱ ዜጐች ጭምር ስለሚሄዱበት አካባቢ ሁኔታ በቂ የሆነ እውቀት የላቸውም። እነዚህን ዜጐች ከችግር ለመታደግ እና በሄዱበት ሀገር በሰላም ሰርተው እንዲመለሱ ለማድረግም ስልጠናውን መስጠቱ አስፈልጓል።

በአሁኑ ወቅት በተለይ በህገወጥ መንገድ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ የተገለፀ ሲሆን፤ ይሄንን ችግር ለመቅረፍም የተለያዩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ ነው የተገለፀው። በዚህም ምክንያት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን ኤጀንሲዎች ማወያየት አስፈልጓል።

ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ሰው ሀገር ሄደው የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ግምት ውስጥ ሳያስገቡ በተስፋ ብቻ በመሰደድ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች መቋቋም እያቃታቸው ለከፋ ችግር ብሎም ለህልፈተ ህይወት እየተዳረጉ እንደሆነ ነው የተገለፀው። በአብዛኛው ኢትዮጵያውያኑ ሴቶች ለከፍተኛ የጉልበት ብዝበዛ፣ ለወሲብ ንግድ እና ለሌሎች አፀያፊ ድርጊቶች እየተዳረጉ ይገኛሉ። ወንዶች ስደተኞች በበኩላቸው በተለይ በጅቡቲ እና በመሳሰሉት ሀገራት ከአቅማቸው በላይ የሆነ የጉልበት ስራ እንዲሰሩ፣ የሽመና ስራ እንዲሁም የግብርና ስራ ላይ እንዲሰማሩ ይገደዳሉ። ከዚህ በተጨማሪም ለጤና እና ለስነ ልቦና ተስማሚ ባልሆኑ ቦታዎች ላይ ከብቶችን እንዲያረቡ እንዲሁም በጐዳና ላይ ንግድ እንዲሰማሩ እየተዳረጉ ነው ይላል ከቢሮው የተገኘ መረጃ።

ኢትዮጵያውያኑ ሴቶች በዋናነት በሱዳን አቅጣጫ ወደ ጅቡቲ፣ ግብፅ፣ ሊቢያ፣ ሱማሊያ እና የመን የሚተላለፉ ሲሆን በሄዱበት አካባቢም ሰብአዊ መብታቸውን የሚነኩ ድርጊቶች ይፈፀሙባቸዋል። አብዛኞቹ የሰሩበትን ደመወዝ የሚከለከሉ ሲሆን፤ የስነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ጉዳቶችም ይደርስባቸዋል። ቀኑን ሙሉ ሲሰሩ ውለው የሌሊት እንቅልፍ እንዳያገኙ የሚደረጉ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞችም እንዳሉ የተገለፁ ሲሆን፤ በአሰሪዎቻቸው በየጊዜው ማስፈራሪያ የሚደርስባቸው፣ የሚደበደቡ እና ባስም ሲል እስከ ግድያ ለሚደርስ አደጋ ተጋላጭ ናቸው። በርካታ ሴቶችም በሱዳን ነዳጅ ማውጫ አካባቢ ሲደርሱ ለወሲብ ንግድ ተላልፈው ይሰጣሉ ይላል መረጃው።

በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችም በሚደርሱባቸው ያልጠበቁት ችግሮች ምክንያት አእምሯቸው እየተነካ እና ራሳቸውን እየሳቱ ራሳቸውን በራሳቸው እስከማጥፋት ይደርሳሉ። የቀሩት ደግሞ ወደ ሀገራቸው እንኳን ሳይመለሱ እዚያ ሰው ሀገር ጐዳና ላይ ወድቀው ይቀራሉ።

እንዲህ አይነቱን በዜጐች ላይ እየደረሰ ያለ ችግር ለመቅረፍ ህገወጥ ስደትን በማስቀረት ህጋዊውን ማበረታታት ያስፈልጋል ተብሏል። በዚህ ስራ ውስጥ ደግሞ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስዱት ኤጀንሲዎች እና ደላላዎች እንደሆኑ ነው አቶ ኤፍሬም የገለፁት። በመሆኑም ኤጀንሲዎች እና ደላሎች ዜጐችን ከመላክ በተጨማሪ የሄዱት ሰዎች በሄዱበት ሀገር ያሉበትን ሁኔታ፣ እየገጠማቸው ያለውን ችግር እና ሊወሰድ የሚገባውን የመፍትሄ እርምጃ በተመለከተ ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው ገልፀዋል።

በተለይ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቀረት ህብረተሰቡን እና ከስደተኞቹ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው አካላት ማነቃቃቱን እንደ አማራጭ የወሰደው ቢሮው፤ ከኤጀንሲዎች በተጨማሪም የስደተኞች ወላጆች እና አዛውንቶችን በጉዳዩ አሳትፏል። ለእነዚህ አዋቂ ወላጆች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክም አዘጋጅቶ ነበር። መድረኩ ባለፈው ረቡዕ ‘‘ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን በመከላከል የዜጐቻችንን ክብር፣ ደህንነት፣ ሞራል፣ ተጠቃሚነት ብሎም የሀገራችንን መልካም ገፅታ ለመገንባት በሚደረገው ተግባራዊ እንቅስቃሴ የአረጋውያን ሚና’’ በሚል ርእስ ተካሂዷል።

በዚህ ቢሮው ባዘጋጀው መድረክ ላይ ከ1ሺ 500 በላይ ከየክፍለ ከተማው የተውጣጡ አረጋውያን እንዲሁም በአረብ ሀገራት ቆይተው የተመለሱ ወጣቶች እና ሌሎችም ተገኝተዋል። በመድረኩ ላይ የየራሳቸውን ገጠመኝ ለታዳሚው ያካፈሉት በአረብ ሀገር ቆይተው የመጡ ወጣቶችም የችግሩን አሳሳቢነት አመልክተዋል። ወጣቶቹ ያለ ምንም ዝግጅት እና ስልጠና በሀገራቸው ያለውን ነገር ንቀው ወደ ሰው ሀገር በመሰደዳቸው ከፍተኛ ቁጭት ያደረባቸው እዚያ ከደረሱ በኋላ እንደሆነ እንባ እየተናነቃቸው ገልፀዋል። ‘‘ይህ ትውልድ ከእኛ መማር አለበት። ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው…’’ እያሉም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። በእነዚህ ወጣቶች ሁኔታ ልቡ የተነካው ወላጅም ከንፈር ከመምጠጥ አልፎ እንባ እስከመራጨት ደርሶ ነበር።

ተሞክሯቸውን ያካፈሉት ወጣቶች በተለይ ህገወጥ ደላሎች በሰጧቸው ያልተጨበጠ ተስፋ ተሳስተው ከሀገራቸው እንደወጡ ተናግረዋል። እዚህ ሀገራቸው ላይ የተነገራቸውን ተስፋ ግን ገና እዚያ እንደደረሱ እንዳጡትም በቁጭት ተናግረዋል።

በሀገራቸው ላይ ሰርተው መለወጥ ሲችሉ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ባህር ተሻግረው ቢሄዱም እንዳሰቡት የራሳቸውንም ሆነ የቤተሰቦቻቸውን ህይወት ከመለወጥ ይልቅ በመላ ቤተሰብ ላይ ጠባሳ ለሚጥል አደጋ መጋለጣቸውን ተናግረዋል። አብዛኞቹ እንደገለፁትም በሰው ሀገር ደም ተፍተው ከሚያገኙት ነገር ይልቅ በሀገራቸው ፆማቸውን ማደርን እንደሚመርጡ ገልፀዋል። አረብ ሀገር ሄደው የሚሳካላቸው በጣም ጥቂቶቹ ብቻ እንደሆኑ የተናገሩት እነዚህ ወጣቶች ከዚያ ስኬት ጀርባ ግን መጠኑን ለመግለፅ የሚያስቸግር መስዋእትነት እንደተከፈለበት ተናግረዋል። ‘‘በዜጐች ላይ እየደረሰ ያለው ሰቆቃ በእኛ ማብቃት አለበት’’ ያሉት ወጣቶቹ ወላጆችም ልጆቻቸውን መምከር እና ማስተማር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙ አረጋውያን በበኩላቸው እነርሱ ወጣት በነበሩበት ወቅት ሁሉም ወጣት በሀገሩ ላይ ለመሞት እንጂ ወደ ሰው ሀገር መሰደድን አስቦት እንደማያውቅ ነው የተናገሩት። የአሁን ጊዜ ትውልድ ለሀገሩ ያለው ፍቅር በጣም አነስተኛ እንደሆነም ገልፀዋል። አንድ ሰው ከሀብት እና ከብልፅግና በላይ የሀገሩን ክብር ማስቀደም እንዳለበት የተናገሩት አረጋውያኑ፤ ሀብትና ብልፅግናም በሀገር ላይ ሲሆን ውበት አለው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በወጣቱ ዘንድ እየተስተዋለ ያለው ሀገርን ጥሎ የመሸሽ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የገለፁት አንዳንድ አረጋውያን፣ እነርሱም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ሀላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በእኛ ባይደርስ እንኳን በየጐረቤታችን የደረሰው ችግር የሁላችንንም ልብ የነካ ነው ያሉት አንዲት እናት፤ የስደት ችግሩ በአንድ ግለሰብ ብቻ የሚያቆም ሳይሆን ጐረቤት እና መላውን ሀገር የሚጐዳ ነው ብለዋል። በመሆኑም አረጋውያን ልክ እንደነርሱ ወጣቶች ለሀገራቸው ክብር እንዲኖራቸው፣ ከፍተኛ የስራ ፍቅር እንዲኖራቸው እና በሀገራቸው ላይ ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ ማስተማር እና መምከር አለባቸው ብለዋል።

በአብዛኛው መገናኛቸው የእድር፣ የማህበር እና የእቁብ ቦታ መሆኑን የገለፁት አረጋውያኑ፣ በእነዚህ አጋጣሚዎች ሁሉ በመመካከረ እና እርስ በርስ በመማማር ችግሩን ለመቅረፍ ብሎም ትውልድን ለመታደግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ወላጆችም ልጆቻቸው ወደ ውጭ ሀገር በመሄድ እንዲረዷቸው ከመገፋፋት እና ከማበረታታት ይልቅ በሀገራቸው ላይ ሆነው እንዲለወጡ መምከር እንዳለባቸው አመልክተዋል።

Last modified on Friday, 04 October 2013 19:17
ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
2002 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 940 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us