የወጣት በጎፈቃደኞች

Wednesday, 09 July 2014 13:36

የክረምት ወቅት መቃረብን አስመልክቶ ተማሪዎችን እና ወጣቶችን በበጎ ፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተ ስራ ለማሰማራት የተለያዩ አካላት በርካታ ስራዎችን ይሰራሉ። ከነዚህ አካላት መካከልም የአዲስ አበባ ወጣቶች ፎረም አንዱ ነው። ፎረሙ ከአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ጋር በመተባበር በ2005 ዓ.ም የተካሄዱትን የበጎ ፈቃደኝነት ስራዎች ክንውን እና በ2006 ዓ.ም ሊሰሩ የታቀዱ ስራዎችን አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት የግንዘባ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። እኛም ይህን የበጎ ፈቃደኝነት እንቅስቃሴ አስመልክቶ የአዲስ አበባ ወጣቶች ፎረም ሰብሳቢ እና የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑትን አቶ ፀጋዬ ገብረ ጻዲቅን አነጋግረናቸዋል።

ሰንደቅ፡- የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎትን የጀመራችሁት መቼ ነው? ውጤቱስ ምን ይመስላል?

አቶ ፀጋዬ፡- የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎትን ፎረማችን ሲያካሂድ ለ11ኛ ጊዜ ነው። በእነዚህ አመታት በጎ ፈቃደኞችን አፍርተናል። ባለፈው ዓመት ቀድሞ ከነበሩ ዓመታት የተሻለ ውጤታማ ስራ ስርተናል። በዘንድሮው ዓመትም እቅድ አውጥተን ውይይት ካደረግን በኋላ ወጣቶቹ ወደ ስራ ዓለም ገብተዋል። ባለፈው ዓመት በዚህ መልኩ አቅደን በመስራታችን መንግሥት ሊያወጣው የነበረውን 27 ሚሊዮን ብር ለማዳን ችለናል።

ሰንደቅ፡- ወጣቶቹ በጎ ፈቃደኞች በምን በምን የአገልግሎት ዘርፎች እንዲሰማሩ ይደረጋል?

አቶ ፀጋዬ፡- ወጣቶች ከትምህርት ገበታ እረፍት በሚሆኑበት በዚህ በክረምት ወቅት ሊሳተፉባቸው የሚችሉ የተለያዩ መስኮች ተዘጋጅተዋል። እነዚህም ችግኝ ተከላ፣ ለአቅመ ደካሞች አልባሳትን መሰብሰብ፣ ለታዳጊዎችና ለወጣቶች የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣ እንዲሁም የኮምፒውተር የክህሎት ትምህርት መስጠት፣ ሰብዓዊ አገልግሎት፣ ጽዳት እና ስፖርትና መዝናኛ ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪም በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኤች አይ ቪ ምርመራንና የስነ ተዋልዶ ትምህርት፣ በደም ለገሳ እና በመሳሰሉት ተግባራት ላይ ይሳተፋሉ። በአጠቃላይ ለወጣቶቹ የተዘጋጁት ወደ 15 የሚደርስ ዝርዝር ተግባራት ናቸው። የክረምቱ ወቅት የገባ በመሆኑ ስራውን ቀደም ብለን ጀምረነዋል። ወጣቶቹ እየሰሩ ቢሆንም በይፋ መክፈቻ እናደርጋለን ብለን አስበናል።

ሰንደቅ፡- ወጣቶች ስራውን ሊሰሩ ሲመጡ በፍላጎታቸው እንዲሰማሩ የማድረጉ ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ ፀጋዬ፡- ሁሉም አደረጃጀቶች በፌዴሬሽኑ ጥላ ስር ነው የሚታቀፉት። ወደ አራት የሚሆኑ የክልል እና ሶስት የከተማ አደረጃጀቶች አሉ። አማራ ወጣቶች ፌዴሬሽን አዲስ አበባ ቅርጫፍ፣ ደቡብ ወጣቶች ፌዴሬሽን አዲስ አበባ ቅርንጫፍ እና ትግራይ ወጣቶች ፌዴሬሽን አዲስ አበባ ቅርንጫፍ እንዲሁም ኦሮሚያ ወጣቶች ፌዴሬሽን አዲስ አበባ ቅርንጫፍ አሉን። በተጨማሪም አዲስ አበባ ወጣቶች ሊግ፣ አዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን እና አዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር የሚባሉትን ጨምሮ ሰባት አደረጃጀቶች በፈዴሬሽኑ ጥላ ስር የታቀፉ ናቸው። ስለዚህ ይህን የክረምት በጎ ፈቃደኛ ፕሮግራም የሚያወጣው የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን ነው። በዚህም መሠረት ማን ምን መስራት እንዳለበት ክፍፍል ይደረጋል። የስራ ክፍፍል ቢደረግም ስራው ግን በጋራ ነው የሚሰራው። ኃላፊነት ለመስጠት ያህል ማን ምን ይስራ ይባላል እንጂ ስራዎቹ ሁሉም በጋራ ነው የሚሰሩት። ማን ምን እንደሚያስተባብር ታውቆ ድልድል ይደረጋል። ይሄንን የማስተባበር ስራ እያንዳንዱ አደረጃጀት ኃላፊነት ይወስዳል። ለምሳሌ አንድ አደረጃጀት የችግርኝ ተከላውን ዘርፍ ሊወስድ ይችላል።

ሰንደቅ፡- በበጎ ፈቃደኞች የሚከናወኑት ተግባራት ከሌላው ተግባር የሚለዩባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? የተለየ መስፈርትስ ያስፈልገው ይሆን?

አቶ ፀጋዬ፡- በመጀመሪያ ደረጃ የበጎ ፈቃደኝነት ስራን ለመስራት እምነት ያስፈልጋል። ስራው የሚሰራው በመጀመሪያ የሚሰራው ሰው ሲያምንበት ነው። ሲሰራው አስደስቶት እና ጠቀሜታውም የጋራ ነው ብሎ ያሰበ ሰው ነው የሚሰራው። መልካም ስራ መስራት ከገንዘብም በላይ የሚሰጠው ጠቀሜታ የላቀ መሆኑን ያወቀ እና ያመነበት ብቻ ነው የሚሰራው። በዚህ ስራ ላይ የሚሳተፉ ወጣቶች እውቀታቸውንም፣ ገንዘባቸውን እና ጊዜያቸውንም ጭምር ነው ኢንቨስት የሚያደርጉት። ስለዚህ በክፍያ ወይም በግዳጅ ከሚሰራ ስራ ይለያል። ጠቀሜታውንም ስታዩ የተወሰኑ አባላትን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ማህበረሰብ ነው ተጠቃሚ የሚያደርገው። ለምሳሌ ለአረጋውያን እና ለአቅመ ደካሞች አልባሳትን የማሰባሰብ ስራ የሚሰሩ አባላት አሉ። በዚህ የሚጠቀሙት በችግር ውስጥ ያሉ አረጋውያን ናቸው።

የማጠናከሪያ ትምህርትን ስንመለከትም ተጠቃሚዎቹ ወጣቶች ናቸው። የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እውቀታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ፣ በክረምት ወቅት ስራ አጥተው በአልባሌ ቦታ ጊዜያቸውን እንዳያሳልፉ ያግዛቸዋል። እነዚህ ነገሮች በአጠቃላይ ጠቀሜታቸው በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን በማህበረሰብ ደረጃ የሚቀመጥ ነው። የበጎ ፈቃደኝነት ስራዎቹ እየተሰጡባቸው ያሉት ዘርፎች ራሳቸው ጠቃሚ በመሆናቸው የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ሁሉንም አካላት የሚጠቅም እንቅስቃሴ ነው። ስራውም በበጎ ፈቃደኛው ብቻ የሚሰራ ስራ ስላልሆነ የማህበረሰቡን ሙሉ ተሳትፎም ይጠይቃል።

ሰንደቅ፡- ለዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበረሰብ ያለው አመለካከት ምን ይመስላል? የመተባበር ሁኔታውስ?

አቶ ፀጋዬ፡- ማህበረሰቡ ጥሩ አመለካከት ነው ያለው። አልፎ ተርፎም ተባባሪ ነው። ለምሳሌ ጽዳትን ብንመለከት እኛ ስናጸዳ አብረውን የሚያፀዱ አሉ። በሌላውም ስራ ላይ እንዲሁ ተሳትፎ ያደርጋሉ። ያበረታቱናል። በሌሎቹ መስኮችም ስንሰማራ የማበረታታት እና የመደገፍ ነገር አለ። ምክንያቱም የበጎ ፈቃደኝነት ስራ ላይ የሚሰማሩ ወጣቶች በክረምት ወቅት ጥሩ ማሳለፊያ ጊዜ በማግኘታቸው ማህበረሰቡ ይደግፈዋል።

ሰንደቅ፡- የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎትን በአሁኑ ወቅት እያከናወናችሁ ያላችሁት ተማሪዎች እረፍት በሚሆኑበት በክረምት ወቅት ነው። ነገር ግን በበጋውም ወቅት ከትምህርት ገበታ እና ከስራ አለም ተገለልለው በየመንደሩ የሚውሉ ወጣቶች አሉ። እነዚህን ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት ስራ ላይ ለማሳተፍ የምታደርጉት እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ ፀጋዬ፡- በአሁኑ ሰዓት ያለን መረጃ በበጋ ወቅት ሁሉም እድሜው ለትምህርት የደረሰ ዜጋ መማር አለበት በሚለው የመንግሥት አቋም መሠረት ወጣቶች ሰፊ የትምህርት እድል አላቸው። ስለዚህ መማር የማይችሉ ወጣቶች መማር እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ አለ። እኛ እንደገመገምነው ማለት ነው። ከዚህ ውጨ በመንግሥትም በግልም መማር የማይችሉ ወጣቶች እኛ አላጋጠሙንም። ነገር ግን በትምህርታቸው የሰነፉ ተማሪዎችን ከማብቃት አኳያ በክረምት ብቻ ሳይሆን በበጋም ወቅት ነፃ የትምህርት እድል የሚያገኙበትን ሁኔታም እንፈጥራን።

በተለያየ ምክንያት ውጤት ያልመጣላቸው እና በግል ከፍለው መማር የማይችሉ ነፃ የትምህርት እድል በተለያዩ ተቋማት እንዲያገኙ በየአደረጃጀቱ ይደረጋል። ነገር ግን የበጎ ፈቃደኝነት ስራው በክረምት ብቻ የሚሰራ አይደለም። አንዳንዶቹ በክረምት ብቻ ይሰራሉ። ሌሎቹ ደግሞ አመቱን ሙሉ ይሰራሉ። ስለዚህ እንነዚህ አንቺ እንደጠቀሻቸው አይነት ወጣቶች ካሉ የመሳተፍ እድሉ አላቸው።

ሰንደቅ፡- በስፋትና በጥልቀት ሊሰራባቸው ይገባል የሚባሉት የበጎ ፈቃደኝነት ስራዎች የትኞቹ ናቸው?

አቶ ፀጋዬ፡- እኛ ሁሉም ዘርፎች ሊሰራባቸው ይገባል ብለን ነው የምናምነው። በዋነኛነት ግን በችግኝ ተከላ ላይ በደንብ መስራት አለበት።የፅዳት እና የትምህርት ዘርፍም ብዙ ሊሰራባቸው ይገባል። የኤች አይ ቪ እና የደም ልገሳም ብዙ መስራትን ይጠይቃሉ። ደም ልገሳን በተመለከተ ብዙ መስራት ያለበት የግንዛቤ እጥረት ስላለ ነው። ደም ለምን እንደሚለግስ እና እንደማይለግስ የማያውቅ ሰውም አለ። ደም መለገስ ህይወትን የማዳን የዜግነት ኃላፊነት በመሆኑ በዚህ ላይ በደንብ መስራት አለበት። ኤች አይ ቪን በተመለከተ ደግሞ ቅድሚያ ራሳቸውን አድነው እንዴት ሌሎችንም እንደሚያድኑ ምክር መስጠትን ይጠይቃል። በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሰራት ይገባዋል።

ሰንደቅ፡- በዘንድሮ ዝግጅታችሁ ከቀድሞዎቹ የተለየ የተያዘ ዕቅድ አለ?

        አቶ ፀጋዬ፡- በዘንድሮው ሰፊ ዕቅድ ነው የያዝነው። ወጣቱን በአጠቃላይ በማንቀሳቀስ በበርካታ ፕሮግራሞች ላይ ለማሳተፍ ዕቅድ አለን። ዘንድሮ በተሻለ ሁኔታ ሰርተን ከቀድሞው የተሻለ ውጤት ለማምጣት ነው ያሰብነው። ባለፈው ዓመት 800 ሺህ ወጣቶችን እናሳትፋለን ብለን አቅደን ከ600ሺ እስከ 700ሺ ወጣቶችን ነው ያሳተፍነው። በዚህም 27 ሚሊዮን ብር ገደማ ማዳን ችለናል። ዘንድሮም 800ሺ ወጣቶችን ለማሳተፍ ነው ያቀድነው። በዚህም በመንግሥት ይወጣ የነበረው 30 ሚሊዮን ብር እናስቀራለን ብለን እናስባለን።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1668 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 767 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us