ለሴቶች ተስፋን የሰነቀው እቅድ

Wednesday, 16 July 2014 12:12

 

ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሀገራችን እየተስተዋለ ያለውን የፊስቱላ ችግር ለመቅረፍ እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በተራዘመ ምጥ ምክንያት የሚከሰት ፌስቱላ አሳሳቢና ጉዳቱ ከባድ ቢሆንም መከላከል የሚቻል እና በህክምና ሊድን የሚችል መሆኑን በማስረዳት የችግሩን ተጠቂዎች መታደግ እና ወደ ቀድሞ ህይወታቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራው ብዙ ሊሰራበት እንደሚገባ ነው የተጠቆመው። “በ2020 ፊስቱላን ከኢትዮጵያ በማጥፋት ህይወትን እናድስ” በሚል መርህም ይህን ለውጥ ለማምጣት የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቷል። ይህ የድርጊት መርሃ ግብርም በሀገራችን በእናቶች እና ሴቶች ላይ እየተከሰቱ ያሉት ችግሮችን እና ፌስቱላን በተመለከተ ጥናት የተደረገባቸውን መረጃዎች ይዟል።

በዓለማችን ላይ በእናቶች ላይ በሚደርስ ሞት 99 በመቶውን የሚይዙት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ናቸው። ከእነዚህ በማደግ ላይ ካሉ ሀገራት ደግሞ 62 በመቶውን የሚይዙት ከሰሀራ በታች ያሉ ሀገራት ናቸው። በእነዚህ በ2013 ብቻ 58 በመቶ የሚሆኑትን የእናቶች ሞት አስተናግደዋል የተባሉት ሀገራትም ህንድ፣ ናይጄሪያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ፓኪስታን፣ ታንዛኒያ፣ ኬኒያ፣ ቻይና እና ዩጋንዳ ናቸው። በኢትዮጵያ 13ሺ እናቶች የሞቱ ሲሆን፣ ይህም 4 በመቶውን ይይዛል።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ 2ነጥብ6 ሚሊዮን ያህል ውልደቶች እንደሚካሄዱ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት። ከነፍሰ ጡር እናቶች መካከል ደግሞ 15 በመቶዎቹ በህይወት ዘመናቸው ሁሉ ለሚሰቃዩበት ውስብስብ ችግሮች ተጋላጮች ናቸው። በዚህ ቀጥተኛ የሆነ ውስብስብ ችግር ምክንያትም 85 በመቶ የሚሆነው ሞት ይከሰታል። ከዚህ በተወሳሰበ ችግር ውስጥም 13 በመቶው ሞት የሚከሰተው በተራዘመ ምጥ ምክንያት ሲሆን፣ 12 በመቶው ደግሞ ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ራስን በመሳት ይከሰታሉ። ከዚህ በተጨማሪም 6 በመቶው ከውርጃ ጋር በተያያዘ ውስብስብ ችግር ምክንያት ይከሰታል።

ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ነፍሰ ጡር እናቶች ሞት ቀጥተኛ ምክንያቶች ቢሆኑም፣ ጥናቱ ያስቀመጣቸው ሌሎች ከእርግዝና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸው ምክንያቶችም አሉ። እነዚህም ኤች አይ ቪ ኤድስ እና የደም ማነስ 4 በመቶ የሚሆነውን የሞት ድርሻ ሲይዙ፣ ወባ 9 በመቶውን ይይዛሉ። እነዚህ ቀጥተኛ ያልሆኑ ምክንያቶች በአጠቃላይ 21 በመቶውን የነፍሰ ጡር እናቶች ሞት ያጠቃልላሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ሴቶች ላይ በስፋት እየተከሰቱ የሚገኙ እነዚህ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ ችግሮች ታዲያ ሲደማመሩ ውጤታቸው ከምጥ ጋር ለተያያዘ የፊስቱላ ችግር መጋለጥ ነው። ለፊስቱላ ከሚያጋልጡ ችግሮች 95 በመቶውን የሚይዘውም የተራዘመ ምጥ ነው። ይህ በተራዘመ ምጥ ምክንያት የሚከሰት የፊስቱላ ችግር ምጡ በተራዘመ ቁጥር የህፃኑ ጭንቅላት በማህፀን በር ለመውጣት በሚያደርገው ግፊት ምክንያት የፊኛ ከረጢትና የሰገራ መውጫ (ደንዳኔ) ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር የደም ዝውውር እንዲቋረጥና በአካባቢው የሚገኙ ስስ የስጋ ክፍሎች እንዲጎዱ እና እንዲበሱ ያደርጋቸዋል። ይህ ችግር በዋናነት የሚከሰተው ደግሞ ሴቷ ያለ እድሜ ጋብቻ በመፈፀሟ እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ባለመቻሏ ነው። እነዚህ ያለ እድሜያቸው የሚያገቡ እና የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት የማይችሉ ህፃናት እድገታቸውን ሳይጨርሱ ቁመታቸው የማጠር እና ዳሌያቸው ሳያድግ (ሳይሰፋ) እርግዝናን ያስተናግዳሉ። በዚህ ወቅት በሚመጣ ምጥም የህፃኑ ጭንቅላት በቀላሉ ለመውጣት አስቸጋሪ ይሆንበታል። በዚህም ምክንያት ከላይ የተጠቀሰውን አይነት የፊስቱላ ችግር ማስተናገድ ግዴታቸው ይሆናል ማለት ነው።

ዩኤስ ኤይድ ባለፈው በፈረንጆች ዓመት ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ የቀረበው ጥናት እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ በየአመቱ ከ3ሺ 500 እስከ 3ሺ 700 የሚደርሱ አዳዲስ የፊስቱላ ተጠቂዎች ይመዘገባሉ። በዚህ ስሌት መሰረት ሲሰራም ኢትዮጵያ ውስጥ ቁጥራቸው ከ36ሺህ እስከ 39ሺህ የሚደርሱ ሴቶች የፊስቱላ ችግር እንዳለባቸው ተገልጿል። እነዚህ የፊስቱላ ችግር የገጠማቸው ሴቶች በድህነት፣ ትምህርት ባለማግኘት እና በቂ የሆነ የጤና አገልግሎት ሳያገኙ የገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ በመሆናቸው ለችግሩ ከፍተኛ ተገላጭነት እንዳላቸው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያስረዳል። ሆኖም ግን እነዚህ ሴቶች ከህመሙ በተጨማሪም ለበርካታ ችግሮች እየተዳረጉ መሆናቸውን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባደረገው ጥናት አረጋግጧል።

በአብዛኛው በችግሩ መንስኤ ዙሪያ ያሉት የተሳሳቱ ግንዛቤዎች በእነዚህ የችግሩ ተጠቂ ሴቶች ላይ የስነ ልቦና፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን በማድረስ ከትዳር አጋሮቻቸው፣ ከቤተሰቦቻቸው እና በማህበረሰቡም ጭምር መገለል እንዲደርስባቸው ያደርጋል። በዚህም መሰረት 92 በመቶ የሚሆኑት የዚህ ችግር ተጠቂዎች በፊስቱላ ችግር ምክንያት ሽንትና አይነ ምድራቸውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው በሚፈጠር መጥፎ ጠረን ምክንያት ከማህበረሰቡ በሚደርስባቸው መገለል ለድብርት ወይም ለድባቴ ህመም ይጋለጣሉ ይላል ጥናቱ። ከዚህ በተጨማሪ 70 በመቶዎቹ ይህንኑ ችግር በማሰብ ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር ተለያይተዋል። በሚያሳዝን ሁኔታ ደግሞ 19 በመቶ የሚሆኑት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንኳ እንድ ማእድ እንዳይቆርሱ የመገለል አደጋ ደርሶባቸዋል።

እነዚህ በፊስቱላ እና ከፊስቱላ ጋር በተያያዘ ችግር የሚጠቁ ሴቶች በገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች እና አዲስ እየበቀሉ በመጡ ክልሎች ውስጥ መገኘታቸው ደግሞ ችግሩ እንዲባባስ እንዳደረገው ነው ጥናቱ የሚገልጸው። በዚህም ሳቢያ ስራውን ውስብስብ እና አድካሚ ቢያደርገውም ብዙ ነገር መስራት እንዳለበት ተቀምጧል። በተለይ ደግሞ ችግሩ ሳይከሰት በመከላከሉ እና የችግሩ ተጠቂ የሆኑትን ሴቶች መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት ብዙ መስራትን ጠይቋል። በዚህ ችግር ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው እና ከማህበረሰቡ መገለል የደረሰባቸው ሴቶች የስነልቦና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እና መልሶ ለማቋቋም ብዙ ስራዎችን መስራት አስፈላጊ ሆኗል።

በተራዘመ ምጥ ምክንያት የሚከሰተው ፊስቱላ በአሁኑ ጊዜ ከጤና ችግርነትም በላይ ስር የሰደደ የማህበራዊ እና ባህላዊ ችግር እየሆነ መምጣቱን የጠቀሱት ባለሞያዎች፣ በመሆኑም ጉዳዩ ከፖሊሲ ጀምሮ በችግሩ ተጠቂዎች፣ በሚኖሩበት ማህበረሰብ እና በዙሪያቸው ባሉ አካላት ላይ ሁሉ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪም የችግሩ ተጠቂዎች አቅማቸው በሚችለው ስራ ላይ በመሰማራት ገቢ የሚያገኙበትን መንገድ እንዲፈጥሩ፣ ስለ ፊስቱላ ችግር መንስኤ ግልፅ የሆነ እውቀት ኖሯቸው ሌላውንም ማህበረሰብ ለመለወጥ እንቅስቃሴው ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረጉም የግዴታ መሆኑ ተቀምጧል። ከሁሉም በላይ ግን የስነ ልቦና ምክር አገልግሎት አግኝተው የተረጋጋ ህይወት እንዲመሩ፣ ሙሉ አምራች ሃይል እንዲሆኑ የማድረጉ ስራም ወሳኝ ነው ተብሏል።

በህክምናው ዘርፍም ቢሆን በኢትዮጵያ ባሉ የፊስቱላ ህክምና በሚሰጡ ጣቢያዎች ለሴቶቹ በቀዶ ህክምና አገልግሎት መሰጠቱ ተገልጿል። በዚህም መሰረት በተለያዩ አካባቢዎች ቅርንጫፍ የህክምና ማእከላትን በመክፈት የሚንቀሳቀሰው ሀምሊን ኢትዮጵያ የፊስቱላ ሆስፒታል በአምስር ዓመታት ውስጥ የበርካቶችን ህይወት መለወጥ ችሏል።

    ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እ.ኤ.አ በ2020 በተራዘመ ምጥ ምክንያት የሚከሰተውን የፊስቱላ ችግር ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ለማጥፋት የሚያግዙትን ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልጿል። በዚህም እስከ ታህሳስ 2005 ዓ.ም ድረስ 6ሺ 900 አዋላጅ ነርሶችን በማሰልጠን ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል። በተጨማሪም 158 የሚሆኑ የተቀናጀ ቀዶ ህክምና መኮንኖች ተመርቀው በስራ ላይ ይገኛሉ። በጤና ተቋማት ረገድ ተጨማሪ ስምንት የፊስቱላ ተቋማትን በመክፈት በአመት ተጨማሪ 200 ሰዎችን ማገልገል የሚችል ማዕከል ለመገንባት ታቅዷል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1432 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 744 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us