ዋግኽምራ- በፈተና የተከበበች ዞን

Wednesday, 23 July 2014 17:19

 

 

በተለያዩ አካባቢዎች በተለያየ ስያሜ ከነሐሴ 16 እስከ 18 ቀን በየአመቱ የሚከበረው የሻዳይ በዓል ዘንድሮም በዋግኽምራ ዞን በድምቀት ይከበራል። በዓሉ “ህብረት ለዋግ ልማት” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ሲሆን፤ የአካባቢውን ችግር ለመቅረፍ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር በዋግ ልማት ማህበር፤ አማካይነት ለመሰብሰብም ታቅዷል። የበዓሉን አከባበር እና በዋግኽምራ ዞን ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር አስመልክቶ የዘንድሮ የሻዳይ በዓል ልማታዊ ህብረት (ቴሌቶን) አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ከሆኑት አቶ መዝሙር ፈንቴ ጋር ቆይታ አድርገናል።               ሰንደቅ፡- የሻዳይ በዓል አከባበር መነሻው ምን ይመስላል?

አቶ መዝሙር፡- የሻዳይ በዓል አከባበር እንግዲህ የዛሬ 500 ሺህ ዓመት ገደማ እንደጀመረ ይነገራል። ከኖህ ዘመን ጀምሮ በዚያ አካባቢ ይከበር እንደነበረ ይነገራል። እኛ ግን እንደ ትልቅ አጀንዳ ይዘን እና አቅደን ማክበር የጀመርነው ከ1999 ዓ.ም ጀምረን ነው። ባህሉ እንዳይረሳ ተናፋቂ በሆነ መንገድ ለቱሪስቶችም በሀገር አቀፍ እና በአለም አቀፍ ደረጃ እያሳወቅን ተወዳጅ ለማድረግ እየሞከርን ነው።

ሰንደቅ፡- ይህ የሻዳይ በዓል በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ስያሜዎች ይከበራል። የዘንድሮ በዋግ ኽምራ ሲከበር በምን አይነት መልኩ ለማክበር ታስቧል?

አቶ መዝሙር፡- እኛም በዋግ ኽምራ ዞን በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ተዘጋጅተናል። በዓሉን ከየአካባቢው የሚመጡ ልጃገረዶች ያከብሩታል። በበዓሉ ዕለት ሰብሰብ ብሎ በአንድ ቦታ እንዲከበር እናደርጋለን። ይህን የምናደርገው ለሚዲያም ለበዓሉ አክባሪም እንዲመች በማለት ነው። ከዚያ በኋላ በሚኖሩት ሁለት ቀናት ግን ልጃገረዶቹ በየመንገዱ ላይ እና በየመንደሩ እየተዘዋወሩ ጨዋታውን እንዲያሳዩ እናደርጋለን። በየቤቱ እየዞሩ ጨዋታውን እንዲያሳዩ የምናደርገው በዓሉ ወደ ኮንስርትነት እንዳይቀየር ነው። በዓሉ ወደ ኮንስርትነት ከተቀየረ አደጋ አለው። እገሌ እንደሚባለው ድምጻዊ ያንን የሚጫወቱ ልጆች ብቻ ተጫዋች ይሆኑና ህብረተሰቡ ተመልካች ይሆናል። በዚህም የማህበረሰቡ ባህል መሆኑን እንረሳዋለን።

በዓሉ የህዝብ ስለሆነ በየዓመቱ ይከበራል። ነገር ግን በአንድነት ብናከብረው የተለየ ድምቀት ይኖረዋል በሚል ነው ተሰብስበን የምናከብረው። በ2004 ዓ.ም ላሊበላ ላይ፣ 2003 ሰቆጣ ላይ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ተከብሯል። ዞሮ ዞሮ ግን በጋራ የምንጋራው ባህል ስለሆነ እና የትግራይ ማህበረሰብ፣ በአማራ ማህበረሰብ እና በአገው ማህበረሰብ ውስጥ ያለው ህዝብ በአንድ ታሪካዊ አጋጣሚ የተሳሰረ በመሆኑ ባህሉን በጋራ ለመጠበቅ በጋራ መስራታችንን ያሳያል።

ሰንደቅ፡- የዋግኽምራ ማህበረሰብ ዋና መገለጫው ምንድን ነው?

አቶ መዝሙር፡- ከሁሉም በላይ በዚያ አካባቢ ያለው እንግዳ ተቀባይነት አስደንጋጭ ነው። ምንም እንኳ በርካታ ችግሮች ቢኖሩበትም ያለውን ነገር ለመስጠት አይሳሳም። አንድ ቅል እርጎ ካለው ቀንሶ እንኳን ሳያስቀር ነው ለእንግዳ የሚሰጠው። አንዲት ግልገል ብትኖረው እርሷን ለእንግዳ ያርዳል። የዋግኽምራ ሰው የሚሰጥህ ቢያጣ እጁን ቆርጦያበላሃል የሚል ተረት አለ። ይህን ስናይ ማህበረሰቡ የሞላው እና የተትረፈረፈው ይመስላል። ሀገሩ የወተት እና የማር ሀገር ይመስላል። በመንገድ እያስቆሙ ያስተናግዳሉ። እንግዳ ፀጋ ነው፣ በረከት ነው የሚል እምነት አለው ማህበረሰቡ። ይሄ ደግሞ ተነግሮት ሳይሆን ከደም እና አጥንቱ ጋር የተያያዘ ነው። ኢትዮጵያ የመስተንግዶ እና እንግዳ ተቀባይ ሀገር የሚባል የተለመደ ነገር አለ። የዚያ አካባቢ መስተንግዶ ግን ከዚህም በላይ ነው። መንገድ ላይ አቁሞ ብሉልኝ ብሎ ሲለምን አልፈሸው ስትሄጂ ምን በድዬ ይሆን እያለ ይረበሻል።

ሰንደቅ፡- አከባቢው ካለው የመሬት አቀማመጥ ጋር በተያያዘ ማህበረሰቡ በችግር ውስጥ እንደሚገኝ ይገለፃልና የዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው?

አቶ መዝሙር፡- ይህ አካባቢ በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዳ እና ኋላ ቀር የሆነ አካባቢ ነው። ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ጀምሮ በአካባቢው እርሻ ይታረሳል። ነገር ግን እርሻው በኋላ ቀር ዘዴ ነው የሚታረሰው። በኋላ ቀር አስተራረስ ወቅት ደግሞ ደን ይመነጠራል። ወንዝና ጅረቶችም ጉዳት ይደርስባቸዋል። አፈርም ይሸረሸራል። በዚህ ምክንያት አካባቢው በአሁኑ ወቅት ለእርሻ የሚውለው መሬት 110ሺ ሄክታር ብቻ ነው። የዋግኽምራ ቆዳ ስፋቷ 878ሺ ሄክታር ሲሆን፣ የህዝቡ ቁጥር ደግሞ ግማሽ ሚሊዮን ይሆናል። አካባቢው በጣም ተራራማ ነው። ምናልባትም በአንድ አካባቢ ላይ በርካታ ተራሮች የተከማቹበት የአለማችን የመጀመሪያዋ አካባቢ ልትሆን ትችላለች ዋግኽምራ። ይህም ሆኖ ግን መታረስ የሌለበት መሬት እየታረሰ ነው። ከአካባቢው መሬት 50 ሺ ሄክታር ብቻ ነበር መታረስ የነበረበት። ነገር ግን ሰዎች ወገባቸው ላይ መጫኛ ታስሮ ተንጠልጥለው በተለያየ ዘዴ 110ሺ ሄክታር ታርሷል። ቀሪው ደግሞ የወሰለተ (ጥቅም ላይ ያልዋል) መሬት ነው። በግብርና ባለሞያዎች ምክር መሰረት ተዳፋትነቱ ከ17 በመቶ በላይ የሆነ መሬት መታረስ የለበትም ይባላል። ነገር ግን በአካባቢው እየታረሰ ነው።

ሌላው የአካባቢውን ችግር ያባባሰው የተከሰተበት ተደጋጋሚ ድርቅ ነው። በሀገሪቱ የተከሰቱ ድርቆች በአጠቃላይ አካባቢውን ሳይነኩት አላለፉም። ዝናብ አጠር አካባቢ በመሆኑ በተደጋጋሚ በድርቅ ተመትቷል። በ1977 ዓ.ም ድርቅ ወቅትም ሆነ በሌሎች የድርቅ ወቅቶች አካባቢው በጣም በድርቅ የተጠቃ አካባቢ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ አካባቢ ተደጋጋሚ ጦርነቶች ተካሂደዋል። ብአዴን የትጥቅ ትግል የጀመረበት የጦር አውድማ ነበር። ሌሎች በርካታ ጦርነቶችም በአካባቢው ተካሂደዋል። እነዚህ ሁሉ ችግሮች ታዲያ ተደራርበው አካባቢው በቀላሉ እንዳያንሰራራ አድርገውታል።

ሰንደቅ፡- በአካባቢው በአሁኑ ወቅት እየተስተዋሉ ያሉት ችግሮች ምንምን ናቸው?

አቶ መዝሙር፡- ከላይ እደጠቀስኩልሽ ከ550ሺ ሄክታር በላይ የሚሆነው ዳገታማ መሬት ጥቅም ላይ ያልዋለ የወሰለተ መሬት ነው። አሁን ባለንበት ሁኔታ ትልቁ ሀብት የህዝብ ጉልበትና መሬት ነው። ይሄ መሬት እያለ በአካባቢው ከ20ሺ እስከ 30ሺ የሚሆኑ ወጣቶች መሬት አልባ ናቸው። ስራ አጦች ናቸው። መሬት የለም ይባላል። መሬት ጠቦ አይደለም። በዚህ አስተሳሰብ መሬት የሚባለው ተራራማ ያልሆነው ብቻ ነው። ተራራው እንደመሬት ተደርጎ አይታሰብም፣ እንደ ትልቅ ሀብት አይቆጠርም።

በተጨማሪም አካባቢው ትምህርትም ሆነ በጤና በጣም ኋላ ቀር ነው። በዚህም ሳቢያ በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችም ኋላ ቀር ማህበረሰብ ነው። መንግስት ብዙ ጥረት አድርጓል። ደርግ ሲወድቅ ከ6 እና ከ7 የማይበልጡት ትምህርት ቤቶች ቁጥር አሁን በ7 ወረዳዎች 200 ያህል ደርሷል። 29 ጤና ጣቢያዎች አሉ። በርካታ ጤና ኬላዎችም አሉ። ከዚያን ጊዜ ጋር ሲነፃፀር ለውጥ አለ። ነገር ግን ወቅቱ ከሚፈቅደው ነገር እና ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ስናነፃፅረው እጅግ ኋላ ቀር ነው። ችግሩ ምን ያህል ስር የሰደደ እንደሆነ የሚያሳየው የሚደረገው ጥረት ችግሩን መቅረፍ ሲያቅተው ነው። ችግሩን ለመፍታት የመንግስት ጥረት ብቻ ጊዜ ይፈጃል። ጊዜው በረዘመ ቁጥር ህዝቡ ተስፋ ይቆርጣል። ምናልባትም ይህ አካባቢ የሚሊኒየሙን የልማት ግብ ከማሳካት አኳያ ትልቅ ችግር ያለበት፣ ትልቅ ጥያቄ ላይ የወደቀ የሀገራችን አንድ ደካማ ነጥብ ሊሆን ይችላል። የዚህ አካባቢ አለመልማት የክልሉ ብሎም የሀገራችን አለመልማት ነው። ኢትዮጵያ የልማት ግቡን አሳካች የሚባለው እያንዳንዱ ክልል፣ ወረዳ እና ቀበሌዎች የለሙ መሆናቸው እንጂ አንዱ የተሻለ ሄዶ ሌላው ወደኋላ ቀርቶ በማጣፋት እና በማካካስ አይደለም። ስለዚህ ይህ አካባቢ የሀገራችን አንድ ደካማ ጎን የመሆን አደጋ ሁሉ አለ።

በአካባቢው ያለው የትምህርት ጥራትም እጅግ አሳሳቢ ነው። የትምህርት ጥራትን ያረጋገጡ ትምህርት ቤቶች የሚሰጣቸው ደረጃ አለ። በዋግ ማህበረሰብ ውስጥ አንድም ትምህርት ቤት ይሄንን ደረጃ አላሟላም። ከ200 ምናምን ትምህርት ቤቶች ደረጃ 4 የደረሰ አንድም ትምህርት ቤት የለም። ደረጃ 3 የገቡት 10 ምናምን ትምህርት ቤቶች ናቸው። 500 ያህል ክፍሎች በዳስ እና በዛፍ ጥላ ስር ሆነው ነው የሚማሩት። መዋእለ ህፃናት የለም ማለት ይቻላል። የግል አንድ ሶስት- አራት ናቸው ያሉት። ቅድመ መደበኛ ትምህርት ስለሌለ ከስር ኮትኩቶ ጥሩ ተማሪዎችን መፍጠር አልተቻለም። መደበኛ ትምህርት ቤት ሲገቡ ገና ሀ ሁ ብለው ፊደል ይቆጥራሉ። ይሄ ችግር በጣም አሳሳቢ ነው።

ጤና ጣቢያን ስንመለከት ከ29 ጤና ጣቢያዎች 10 ያህሎቹ የጤና ጣቢያነትን ደረጃ የማያሟሉ እና ስሙን ብቻ የያዙ ናቸው። ራሱ የክልሉ ጤና ቢሮ የጤና ጣቢያን ደረጃ ስለማያሟሉ ወደ ጤና ኬላነት ደረጃ እናወርዳቸዋለን ብሎ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል። ከ125 ቀበሌዎች መካከል 32 ቀበሌዎች ጭራሹኑ ጤና ኬላ የላቸውም። ስለዚህ ሌላው ቢቀር የእናቶችና ህጻናትን ሞት መቀነስ የሚለው ግብ በነዚህ አካባቢ የሚሰራ አይደለም። ከክልል አንፃር ሲታይ በአካባቢው የእናቶችና ህጻናት ሞት ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል። ይሄ ደግሞ ፋታ የማይሰጥ ነገር ነው። ወደ 25 ጤና ኬላዎች ጣሪያ እና ግድግዳ ብቻ ይዘው ውስጣቸው ምንም የላቸውም።

በአካባቢው የአይን ህመም ከፍተኛ ችግር ነው። ቁጥራቸው ያልታወቀ አይነስውራን ወጣቶች አሉ። ከ6ሺ እስከ 6ሺ 500 የሚደርሱ አስቸኳይ የአይን ቀዶ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ወጣቶችና ጉልማሶች አሉ። እነዚህ አምራች ሃይሎች ይህን ህክምና ካላገኙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አይነስውርነት ይሄዳሉ። ችግሩ በጣም ተያይዥ ነው። በአካባቢው ያለው የውሃ ችግር እጅግ እጅግ ከፍተኛ ነው። ውሃ የለም ማለት ንፁህ የመጠጥ ውሃ የለም። ንፅህና ስለማይኖር በሽታ ይኖራል ማለት ነው። የተፈጥሮ ሀብት ካልለማ ደግሞ ውሃ ለአካባቢው ከየትም አይመጣም። የተፈጥሮ ልማት ከጤናም ከምግብ ዋስትናም ጋር የተያያዘ ነው።

ሰንደቅ፡- ማህበሩ እነዚህን በአካባቢው የሚስተዋሉ ችግሮች ከመቅረፍ አንፃር ምን አይነት እቅዶችን ይዟል?

አቶ መዝሙር፡- አካባቢውን ለማልማት ተራራው ሀብት መሆኑን እና ይህን እምቅ ሀብት ወደ ጥቅም በመለወጥ ሀብት ማፍራት እንደሚቻል አስተሳሰብ መፍጠር ያስፈልጋል። ማንኛውም ሰው የየአካባቢውን ሀብት እና ችግር መገንዘብ ይኖርበታል። ሜዳ ላይ ላለ ሰው ተራራ ጭኖ አይወሰድም። ተራራ ላይ ላለውም ሜዳውን ጭኖ መውሰድ አይቻልም። ሁሉም በየአካባቢው የየራሱን ሀብት ወደ ጥቅም መለወጥ አለበት። በአካባቢው የሚገኘው የተከዜ ግድብ ወደ 80 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ሀይቅ አለ። ያ ሃይቅ 75 ኪሎ ሜትር የሚገኘው በዋግ ውስጥ ነው። ዞኑ ከግድቡ ወደ ላይ ነው። ሁሉም ተፋሰሱ የሚሄደው ወደዚያው ስለሆነ አካባቢው ካልለማ ግድቡ በደለል ተሞልቶ ከጥቅም ውጪ ሊሆን የሚችልበት አደጋ አለ።

እኚህን የመሰሉትን አደጋዎች ለማስቆም ስራ አጥ ወጣቶች ተራሮችን አልምቶ ሀብት መፍጠር እንደሚቻል ተገንዝበው ወደ ስራ እንዲገቡ የማድረግ እቅድ አለን። በዝግጅቱ ላይ በሚዘጋጀው ልማታዊ ህብረት (ቴሌቶን) ከ400 እስከ 500 ሚሊዮን ብር ድረስ ሰብስበን ለልማት የማዋል አላማ አለን። በዚህም በ7 ወረዳዎች እያንዳንዱ 250 አባላት ያሉትን ሶስት የስራ አጥ ወጣቶች ማህበር የማቋቋም ሃሳብ አለን። ለማህበራቱ መነሻ ገንዘብ ሰጥተን በእንስሳት መኖ፣ በማር እና በተለያዩ ልማቶች ላይ እንዲሰማሩ እናደርጋለን። እነዚህ ወጣቶች ተፈጥሮን በመንከባከብ በተራሮቹ ላይ ሲሰሩ ተራሮቹ ይለማሉ። ተራራ ሲለማ ደግሞ ስራቸው ውሃ ያወጣል። በዚህ መልኩ አካባቢው ተመልሶ ይለማል ማለት ነው። በዚህም ከ5 እስከ 6ሺህ ስራ አጥ ወጣቶችን ለመለወጥ ብናስብም የዋግ ችግር በዚህ ብቻ ይፈታል ተብሎ አይታሰብም።

በዝግጅቱ ላይ ከቴሌቶኑ በተጨማሪ የፓናል ውይይት ለማድረግ አስበናል። የተወሰነ መነሻ ሃሳብ በማንሳት ስትራቴጅካዊ በሆነ መንገድ የአካባቢውን ችግር መፍታት እና አካባቢውን መለወጥ የሚቻለው በምን መልኩ እንደሆነ ሰዎች የሚያነሱትን ሃሳብ ማሰባሰብ እንፈልጋለን። አካባቢው የክልሉ በጣም ደካማ አካባቢ ስለሆነ ችግሩን በተለየ መልኩ ለመፍታት እንፈልጋለን። የፌዴራል መንግስትም ሆነ የተለያዩ የልማት ተቋማት አካባቢው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ እንፈልጋለን። በቀጣዩ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥም አካባቢው በተለየ ትኩረት ካልተሰራበት የሀገሪቱ ደካማ ጎን ሆኖ መቀጠሉ የማይቀር ነው።  

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
1551 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 506 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us