በቆሎ እሸት - የከተማችን የክረምት መድመቂያ

Wednesday, 30 July 2014 12:37

 

የየወቅቶችን መቃረብ አስመልክቶ በርካታ ወቅታዊ የሆኑ ነገሮች እንቅስቃሴ ጎልቶ ይታያል። በተለይ እንዲህ ያለው የክረምት ወቅት ሲመጣ ደግሞ የራሱ የሆኑ በርካታ መገለጫዎች አሉት። በየመኖሪያ ቤቱ ከሚከናወኑ ተግባራት በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በየጎዳናው ላይ የምናያቸው እንቅስቃሴዎች የበለጠ የሁሉንም ቀልብ እየሳቡት ይገኛሉ። በየመንገዱ ጥጋጥግ በተለይ የሰዎች እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው መንገዶች ላይ የድንች ቅቅል፣ የድንች ጥብስ (ቺፕስ) እንዲሁም የተቀቀለ እንቁላል አልያም የሽንብራ እና የገብስ ቆሎ ይዘው የተቀመጡ እናቶችን መመልከት ረዘም ያለ ጊዜን ያስቆጠረ ልማድ ነው።

አጭር እድሜ ቢኖረውም በስፋት ተቀባይነት እያገኘ የመጣው ግን በቆሎ እሸት ነው። በቆሎ እሸትን በጥብስ እና በቅቅል መልክ በየትኛውም የከተማችን መንገድ ላይ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። ከምሳ ሰዓት በኋላ ባሉት ጊዜያት በርካታ ቁጥር ያላቸው ነጋዴዎች በከሰል የተሞላ የከሰል ምድጃቸውን እና በቆሏቸውን ይዘው በአንድ የመንገድ ጥግ ይቀመጣሉ። ፈላጊ እስኪመጣ ድረስ በቆሏቸውን እየጠበሱ ይጠባበቃሉ። ዝናብ እና ብርድ ሳይበግራቸው ደንበኞቻቸውን ያስተናግዳሉ። ሥራው የሚሰራው (በቆሎው የሚጠበሰው) በከስል መሆኑ እነዚህ በቆሎ ጠባሾች ብርዱንም እግረመንገዳቸውን እንደቋቋሙት አድርጓቸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዋናው ካምፓስ በተለምዶ አንደኛ በር ወይም ድድ ማስጫ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በዚህ በቀሎ በመጥበስ ስራ ላይ ተሰማርተው ብርድ ባረፈበት ምሽት ከሰላቸውን እያራገቡ በቆሎ ሲጠብሱ ያገኘናቸው እናትም የገለፁልን ይህንኑ ነው። እኚህ እናት ወይዘሮ ታደለች ይባላሉ። ቀን ቀን በሰው ቤት እንጀራ እየጋገሩ እና ልብስ እያጠቡ ይተዳደራሉ። ከዚያ ሲመለሱ ደግሞ ከሰል እና በቀሏቸውን ይዘው ዘወትር ወደማይጠፉበት ቦታ በመሄድ በቆሎ ጠብሰው ይሸጣሉ። የቀኑን ድካማቸውን እና ብርዱን ደግሞ በከሰሉ ሙቀት ይቋቋሙታል።

በሰው ቤት እንጀራ ሲጋግሩ ከሚከፈላቸው ገንዘብ በተጨማሪ ከአንዳንዶቹ ቤት እንጀራ እንደሚበረከትላቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ታደለች፤ በዚህ በበቆሎ እሸት መጥበስ ሥራ ላይ መሰማራታቸው ደግሞ ልጆቼ ምን በልተው ያድራሉ ከሚል ስጋት ነፃ አድርጓቸዋል። የተሸጠውን ሸጠው የተረፈውን ይዘው ወደ ቤታቸው ይገባሉ። ልጆቻቸው ደግሞ ያንን ጠብሰው ወይም ፈልፍለው በመቁላት ከፈለጉ ደግሞ ቀቅለው ይመገባሉ።

ብዙዎቻችን በመንገዳችን እንደምንመለከተው አንዳንድ በቆሎ ጠባሾች የበሰለ ሶስት አራት በቆሎ ጥብስ አድርሰው መንገደኞችን ይጠባበቃሉ። ያ የበሰለው ገዢ እንደማያጣ እርግጠኛ በመሆንም ሌላ ከስር ሲያበስሉ ይታያሉ። እነዚህ በቆሎ ጠባሾች እንደገለፁልን ከሆነ በተለይ የበቆሎ ጥብስ ገበያ ምሽቱ እየገፋ ሲሄድ ይደራል። ወደቤት ለመግባት በጥድፊያ ላይ ያለ ሰው የተጠበሰውን በቆሎ በፍጥነት ገዝቶ እየበላ ስለሚሄድ ተጠብሰው የሚቀመጡት በቆሎዎች አማራጮች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ልክ እንደቋሚ ደንበኛ የተወሰኑ ሰዎች የሚመጡበትን ሰዓት በመገመትም በቆሏቸውን አዘጋጅተው የሚጠብቁ ገጥመውናል።

አንዳንድ በቆሎ ጠባሾችም ልክ እንደደንበኛ የሚቆጥሯቸው ሰዎች ሲመጡ ከተጠበሱት ውስጥ ለአንተ (ለአንቺ) ይሄ ነው የሚሻለው እያሉ የመመረጥ ሀኔታ መኖሩንም ተገንዝበናል። በጣም የሚቀርቧቸው ደግሞ ሌላ ተጠብሶ እንዲሰጣቸው ይደረጋል። ሶስት ሆነው እየተሳሳቁና የተጠበሰ በቆሎ እየበሉ ሲሄዱ ካገኘናቸው ወጣቶች አንዱ የሆነው ወጣት ዮሴፍም የገለፀልን ይሄንኑ ነው። “እኔና ጓደኞቼ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቆሎ ጥብስ ሱስ ሆኖብናል። እንደምንም ብለን ወደቤታችን ስንገባ ግማሽ እራስ በቆሎ መግዛታችን አይቀርም። ብርዱን እና ክረምቱን ልንረሳው የምንችለው በዚህ ነው” ይላል ወጣት ዮሴፍ።

ዮሴፍ እና ጓደኞቹ ተወልደው ያደጉት ክፍለ ሀገር በመሆኑ እና የገበሬ ልጆች በመሆናቸው ስለበቆሎ እሸት ጥሩ እውቀት እንዳላቸው በመግለፅ እንደሌላው የከተማ ሰው እንደማይሸወዱ ይናገራሉ። ገና ከጥሬነቱ ጀምረው የትኛው መጥፎ የትኛው ደግሞ ሲበሉት ጣእሙ ጥሩ እንደሚሆን ጭምር እንደሚያውቅ የሚናገረው ወጣቱ ዮሴፍ ይሄንን ለማድረግ ግን እንደደንበኛ ወደ ሚመለከቱት አንድ ጠባሽ ጋር ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ጎራ ይላል። ለእርሳቸው ሰላምታ ካቀረበ በኋላ ልክ እንደተለመደው ያለችውን ብሎ በማዘዝ ቀልቡ ያረፈበትን ገዝቶ እንደሚሄድ ገልፆልናል።

ከክፍለ ሀገር ከሚመጡ ሰዎች ይልቅ ከተማ ተወልደው ያደጉ እና ስለበቆሎ እሸት ብዙም እውቀቱ የሌላቸው ሰዎች ብዙም ሲያማርጡ አይታዩም የሚለውን ሃሳብ የሚስማማበት ወጣት ዮሴፍ፣ በተለይ እንደርሱ ላሉ የገበሬ ልጆች ከገበሬው እርሻ ላይ ተቆርጦ የሚቀርበውን ትኩስ በቆሎ እሸት እያየ አድጎ እዚህ ያሉትን ለመመገብ በተለይ በመጀመሪያ አካባቢ ከባድ ነው። ከእርሻ ላይ የተቆረጠውን ትኩስ በቆሎ እሸት ለሚያውቅ ሰው በትራንስፖርት እና በተለያዩ እንግልቶች ከማሳ እስከ ገበያ ያለውን ሂደት አልፈው የሚመጡ በቆሎዎች ተፈጥሯዊ ይዘታቸው እንደሚቀንስ እና ሲያዩዋቸውም የመጠውለግ ባህሪይ እንዳለባቸው ነው ተጠቃሚዎች የሚናገሩት።

በቆሎ እሸት ከጥብስ በተጨማሪ በቅቅል መልክ በየጎዳናው ይገኛል። ለበርካታ ወጣቶች እንደ አዲስ የስራ እድል ሆኖ ብቅ ያለው ይህ የቅቅል በቆሎ ንግድ እንደ በቆሎ ጥብስ ረጅም እድሜ ባያስቆጥርም ያለው ተጠቃሚ ቁጥር ግን እንደ እድሜው አይደለም። በበርካታ አጠናዎች በቅርፅ በተሰራ ጋሪ ላይ በትልቅ የብረት ከሰል ማንደጃ የተቀጣጠለ ከሰል ላይ በትልቅ ብረት ድስት ውስጥ እና በብረት ድስቱ አፍ አልፎ የተከመረ የበቆሎ እሸት በላስቲክ ከረጢት እየቋጠሩ በከሰሉ ላይ በመጣድ የሚጓዙ በርካታ ወጣቶችን በተለይ ወደ አመሻሹ ላይ እናያለን። ከእነዚህ ወጣቶች መካከል አንዱ የሆነው ወጣት አድማሱ ኃይሉ የዘወትር ስራው ይሄ ነው። ቀን ቀን በትምህርት እና በሌሎች ስራዎች ሲሯሯጥ ቢውልም በአማካይ ከቀኑ አስር ሰዓት ገደማ ጀምሮ ግን ከሰሉን አቀጣጥሎ በጋሪው ላይ ካስቀመጠ በኋላ የሚያስፈልጉትን እንደ ተጨማሪ ከሰል እና ውሃ፣ የከሰል ማራገቢያ፣ የበቆሎ ቅጠል እንዲሁም የበቆሎ ማውጫ መቆንጠጫ አዘጋጅቶ በቆሎው ወደመብሰል ሲቃረብ ጉዞውን ይጀምራል። በየመንገዱ ለጠየቀው ሰው ሁሉ እየሸጠም መንገዱን ይቀጥላል።

ከፒያሳ በተለምዶ በእሪበከንቱ ወደአራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት የሚያስወጣውን ዳገት በመውጣት ላይ ሳለ ያገኘነው ወጣት አድማሱ የመንገዱ ዳገተማነት ከሚገፋው ጋሪ ጋር ተደማምሮ በላብ አጥምቆታል። በየእለቱ ምሽት ላይ በዚህ አይነት መልኩ ለገበያ እንደሚወጣ የገለፀልን ወጣት አድማሱ፣ ስራው የሚከብደው በቆሎውን እና አስፈላጊ እቃዎቹን ጭኖ በሚሄድበት ወቅት ቢሆንም በቆሎውን ሸጦ ሲመለስ ግን ሸክሙ እንደሚቀልለት ነግሮናል።

እንዲህ አይነቱን እየተንቀሳቀሱ የመነገድ ስልት አብዛኞቹ ወጣቶች ሲጠቀሙበት ይታያል። እነዚህ ወጣቶች ቋሚ የሆነ ተቀምጠው የሚሸጡበት ቦታ ሳይኖራቸው መንገድ ላይ በመንቀሳቀስ ሽያጫቸውን ያካሂዳሉ። መነሻቸውን እንጂ መድረሻቸውን ባለመገመት የያዙት በቆሎ ተሸጦ እስከሚያልቅ ድረስ ይጓዛሉ። በመሀሉ ትንሽ ቆም በማለት በቆሏቸውን ከሸጡ በኋላ ደግሞ ሌላ ጉዞ። በዚህ አይነቱ ንግድ ውስጥ ያሉት ታዲያ ሌሎች አንድ ቦታ ተቀምጠው ከሚሸጡ ሰዎች በተሻለ መልኩ የያዙትን ሸጠው በመጨረስ ይታወቃሉ። ወጣት አድማሱም እንዲህ ይገልፀዋል። “አንድ ቦታ ተቀምጦ መሸጥ ማለት ገዢው ወደ አንቺ እንዲመጣ መጠበቅ ማለት ነው። ገዢ ደግሞ ለራሱ በሚመቸው መንገድ ይሄዳል እንጂ ላንቺ ብሎ አይመጣም። ስለዚህ እንዲህ ወደ እርሱ ስትሄጂ በቀላሉ ትገናኛላችሁ። እንደምንም ብለን እዚህም እዚያም ተሯሩጠን የያዝናትን ሳንጨርስ አንገባም” ይላል።

ምንም እንኳን እንዲህ አይነቱ ስራ አድካሚ ቢሆንም በቆሏቸውን ይዘው በተንቀሳቀሱ ቁጥር የሚያገኟቸው ደንበኞች በርካቶች በመሆናቸው ብዙ መሸጥ ይችላሉ። ሸጠው ጥቂት በቆሎዎች ሲቀሯቸውም መግዛት የሚፈልግ ሰው እንዳለ እነዚህ ሻጮች ያውቃሉ። ከብረት ድስት አፍ ላይ የሚገኘው በቆሎ ብዙም ያልበሰለ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ወደመጨረሻው የቀረው ለረጅም ጊዜ ውሃ ውስጥ ሆኖ እሳት ያገኘው በመሆኑ የመብሰሉ መጠንም ያንኑ ያህል ነው።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ያለውን የጥብስ እና ቅቅል በቆሎ ዋጋ በማየት ይህ ስራ አዋጭነቱ እንዴት ነው? የሚለውን መመልከት ይቻላል። የአንድ ራስ ጥብስ በቆሎ አማካይ ዋጋ አምስት ብር ሲሆን አንዱ ራስ ቅቅል በቆሎ ደግሞ በአማካይ 6 ብር ዋጋ አለው። ሶስቱ ራስ ጥሬ በቆሎ እሸት ደግሞ በአስር ብር ይሸጣል። በሌላ በኩል ደግሞ ደርቆ እና ተፈልፍሎ ለገበያ የሚቀርበውን የበቆሎ ዋጋ ስንመለከት የአንድ ኪሎ በቆሎ ዋጋ በአማካይ ስምንት ብር ነው። በዚህ መልኩ ስንመለከተው ስራው አዋጭነት ያለው ይመስላል። ወይዘሮ ታደለችም ምንም እንኳን ስራው አድካሚ ቢሆንም በስፋት ለሚሰሩበት ሰው አዋጭነቱ የተሻለ መሆኑን ይናገራሉ።

ሥራውን ቤት ውስጥ ሆኖ መስራት ባለመቻሉ እና የስራው ወቅት የክረምት ወቅት መሆኑ የሥራውን ክብደት እንደሚያጎላው ነው ወይዘሮ ታደለች የሚገልፁት። በተለይ እንደ እርሳቸው በአንድ ቦታ ተቀምጦ ለሚጠብስ ሰው ከዝናብ እና ከብርድ ጋር እየታገሉ መስራትን ይጠይቃል። አቅም ያላቸው እና በስፋት በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች የአዲስ አበባ መግቢያዎች ድረስ በመሄድ ቀጥታ ከገበሬው በመግዛት ጠብሰው ወይም ቀቅለው ሲሸጡ ጥሩ ትርፍ እንደሚያገኙበት ነው ወይዘሮ ታደለች የገለፁልን። እንደ እርሳቸው በጥቂቱ የሚሰሩት ግን ከዚሁ ከአትክልት ተራ በጭነት መኪና እያመጡ ከሚያከፋፍሉ ነጋዴዎች ስለሚረከቡ ትርፉ ያን ያህል አለመሆኑንም አያይዘው ገልጸውልናል።

ወጣት አድማሱ በበኩሉ ሥራው የክብደቱን ያህል አዋጭነቱ (አትራፊነቱ) እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ገልፆልናል። ከበቆሎ ጥብስ ይልቅ ቅቅሉ ለረጅም ሰዓት እሳት ላይ መቆየት ስላለበት ከፍተኛ መጠን ያለውን ከሰል እንደሚወስድ የሚገልፀው ወጣት አድማሱ፣ የከሰሉ ወጪ፣ የሚያወጡት ጉልበት እና የሚወስደው ጊዜ ቢደማመሩ ከእለት ገቢነት ያለፈ ትርፍ እንደሌለው ገልፆልናል።

ከእዚህ የበቆሎ እሸት ጋር በተያያዘ ሊታሰብ የሚገባው አንድ ነገር አለ። ይኸውም ከበቆሎው የሚወጡት እንደ ቅጠል እና ቆረቆንዳ ያሉት ተረፈ ምርቶች አወጋገድ ነው። የተወሰኑት በዚህ ስራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች እነዚህን ተረፈ ምርቶች በአግባቡ ቢያስወግዱም አንዳንዶቹ ግን በማን አለብኝነት እዚያም የሰሩበት ቦታ ላይ ጥለው ሲሄዱ ይታያሉ። ቀደም ባሉት ዓመታት በመንገድ እና በመንገድ ዳር ትላልቅ የድንጋይ ጉልቻዎችን እየጎለቱ በትልቅ ጎላ ድስት በቆሎ የሚቀቅሉ ግለሰቦች ነበሩ። በተለያዩ የመንገድ ዳርቻዎችና ጥጋጥግ ስር ይሄንን ሥራ በሚሰሩበት ወቅት አካባቢውን ከማቆሸሽም በተጨማሪ የእሳት አደጋ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ይህ አይነቱ ስራ ተከልክሏል። አሁን በተለያየ መንገድ እየሰሩ ያሉትም በዚህ በንፅህና ጉዳይ ላይ ሊያስቡበት ይገባል። ተጠቃሚዎችም ቢሆኑ በቆሎውን ከበሉ በኋላ ተረፈ ምርቶቹን በማስወገዱ ረገድ ጥንቃቄን ይጠይቃል።

    ሌላው በዚህ በበቆሎ እሸት ንገድ ላይ ሊነሳ የሚገባው በቆሎዎቹ የሚበስሉበት ሁኔታ ምን ያህል ንፀህናውን የጠበቀ ነው? የሚለው ጉዳይ ነው። አብዛኞቹ በቆሎ ጠባሾች አጥሮችን እና ግንቦችን ተደግፈው እና ለእነርሱ አመቺ ነው ያሉት ቦታ ላይ ነው ተቀምጠው ነውየሚጠብሱት። እነዚህ የአጥር ጥጎች ደግሞ ጨለምለም ሲል እና ብዙም የሰው ግርግር ሳይኖር ሲቀር እንደመፀዳጃነት የሚያገለግሉ ናቸው። በዚህ መልኩ ሲታይ ስራው የሚሰራበት ቦታ ፅዳት ምን ያህል አስተማማኝ እንደሆነጥርጣሬ ያስነሳል። በቅቅል በቆሎ አቅራቢዎች በኩልም የሚታዩ አንዳንድ ነገሮች አሉ። በቆሎው ከሚጠቀለልበት የላስቲክ ከረጢት አንስቶ በቆሎ የሚቀቀልበት ውሃ፣ ብረት ድስት እና በቆሎ ማውጫ (መቆንጠጫዎች) ያላቸው ንፅህና አሳሳቢ ነው። ይህም ሆኖ ግን በቆሎ እሸት የከተማችን የክረምት ወር መድመቂያ ሆኗል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
2549 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 736 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us