የሴቶቹ ራስን ፍለጋ

Wednesday, 06 August 2014 14:33

ወይዘሮ ወርቅነሽ ገብረ መድህን የአስር ዓመት እና የአራት ዓመት ልጆች እናት ሲሆኑ፣ እነዚህን ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት እና ቤተሰባቸውን የሚመሩት ባለቤታቸው ሰርተው በሚያመጡት ገቢ ነበር። እርሳቸው ቤት ውስጥ ቁጭ ብለው የባለቤታቸውን እጅ ከመጠበቅ ውጭ ይሄ ነው የሚሉት ስራም ሆነ የራሳቸው ገቢ አልነበራቸውም። የቤታቸውን ስራ አጠናቀው በምትተርፋቸው ጊዜ ወደ ቀበሌ ብቅ እያሉ አንዳንድ ነገሮች ውስጥ ይሳተፉ ነበር።

በዚህ አጋጣሚም ስራ አጥ የሆኑ ሴቶች በፀጉር ስራ እና በስራ ፈጠራ ሞያ ስልጠና እንዲወስዱ ምዝገባ ሲካሄድ እርሳቸውም ተመዘገቡ። ስልጠናው ለሶስት ወራት የተካሄደ ሲሆን በቆይታቸውም በርካታ የሞያ ክህሎቶችን በመቅሰም በቀጣይ በዚህ በሰለጠኑበት ሞያ ለመስራት እቅድ እንዲይዙና ተስፋም እንዲሰንቁ አድርጓቸዋል።

የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተለያዩ ሙያዊ ክህሎት ማዳበሪያ ስልጠና ሰጥቷል። ይህ ስልጠና ከዚህ ቀደም በሁለት ዙር ተሰጥቶ የነበረ ሲሆን በሶስተኛው ዙር የሰለጠኑት 670 ሴቶችም ባለፈው እሁድ በግሎባል ሆቴል ተመርቀዋል። እነዚህ ስራ አጥ ሴቶች በፀጉር ስራ ሞያ እና በስራ ፈጠራ (entrepreneur Ship) መስክ ለሶስት ወራት ያህል ስልጠናውን ወስደዋል። በፀጉር ስራው የፀጉር አጠባ፣ የፀጉር ጥቅለላ፣ የካውያ ስራ፣ የፓይስትራ ስራ እና ሌሎች ተጓዳኝ የሆኑ ስልጠናዎችን ወስደዋል፤ ሰልጣኖቹ።

በማስዋቡ ረገድ ደግሞ ቅንድብ መቀንደብ፣ ጥፍር ማሳመር፣ ሜክአፕ አጠቃቀም እና የመሳሰሉትን ኮርሶች ወስደዋል። ከእነዚህ በዚህ ዘርፍ ከሰለጠኑ ሴቶች መካከል ታዲያ ከላይ የጠቀስናቸው ወይዘሮ ወርቅነሽ ገብረመድህን አንዷ ናቸው። ነዋሪነታቸው በልደታ ክፍለ ከተማ የሆነው እኚህ ሴት ከስልጠናው ምን እንዳገኙ እና የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ሲሉ ገልፀውልናል።

“በስልጠናው እኔ ብዙ ትምህርት እና ሙያ አግኝቼበታለሁ። በሶስት ወር ውስጥ የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስጃለሁ። በፊት ያልነበረኝን ብዙ ሙያ ቀስሜበታለሁ። በፊት ምንም የማላውቀውን አሁን ግን ስራውን የትም ብሄድ እንደምወጣው እርግጠኛ ነኝ” ይላሉ። ወይዘሮ ወርቅነሽ እንደገለፁልን ከሆነ ይህን አይነቱ ለስራ አጥ ሴቶች እየተሰጠ ያለው ስልጠና እንደ እርሳቸው ያሉ በርካታ ሴቶች የባሎቻቸውን እጅ ከመጠበቅ ይልቅ ጊዜያቸውን በስራ ላይ እንዲያሳልፉ እና የራሳቸውንም ገቢ እንዲፈጥሩ ይረዳቸዋል።

ሌላው ለወጣቶቹ የተሰጠው ስልጠና የስራ ፈጠራ (entrepreneurship) ስልጠና ነው። በዚህ የስልጠና ዘርፍ የተለያዩ ስራ ፈጠራ ክህሎቶች፣ አመቺ አጋጣዎች እንዴት መጠቀም እንደሚቻል፣ የገንዘብ አያያዝ፣ ኃላፊነትን መወጣት፣ ጥሩ ተግባቦትን መፍጠር እና ሌሎችም ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ስልጠናውን እንዲወስዱ ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪም ሴቶቹ በአካባቢያቸው ባሉት ጥቂት እና ተጨባጭ ነገሮች ተጠቅመው እንዴት መለወጥ እንደሚችሉ የግንዛቤ ማዳበሪያ ስልጠና መውሰዳቸውን የቀረበው የስልጠና ሂደት ሪፖርት አመልክቷል።

ከሰልጣኞቹ አንዷ የሆነችው ወጣት ፍሬህይወት ጉርሙ በዚህ በስራ ፈጠራ መስክ ያገኘችው እውቀት በተስፋ እንድትኖር እያደረጋት እንደሆነ ትናገራለች። “10ኛ ክፍል የማትሪክ ፈተና ተፈትኜ ውጤት ሳይመጣልኝ በመቅረቱ ቤት ውስጥ ነበር የምውለው። አንዳንድ ጊዜ እናቴን ቤት ውስጥ አግዛታለሁ እንጂ ሌላ ምንም ስራ አልሰራም ነበር። እንደ አጋጣሚ እናቴ ቀበሌ ስራ አጥ ወጣቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ስትነግረኝ ሄጄ ተመዘገብኩ። ስልጠናውን ለመውሰድ ክፍያ አለመጠየቁ ደግሞ በጣም ነው ያስደሰተኝ። ከፍዬ መማር ባለመቻሌ እንጂ ውጤት ሳጣ የሆነ ነገር መማር ፈልጌ ነበር። ግን ወደዚህ ስልጠና በነፃ ስገባ በጣም ነው ደስ ያለኝ። በፊት ስለራሴ ሳስብ በጣም ይከፋኝ ነበር። እናቴን ማገዝ ባለመቻሌ የእኔ መጨረሻ ምን ይሆን የሚለው ዋናው ጭንቀቴ ነበር። አሁን ግን ለእናቴም ለራሴም እየደረስኩኝ እንደሆነ ተስፋ አለኝ” ትላለች ወጣት ፍሬህይወት።

ለሰልጣኞች ስልጠናው እንዲሰጥ የተደረገው ሳክ በተባለ ተቋም እና በኦሪዮን የውበት ማሰልጠኛ ማእከል አማካይነት ነው። በገንዘብ በኩል ያለውን የአውሮፓ ህብረት የሰልጣኞቹን ወጪ የሸፈነ ሲሆን፤ ስልጠናውንም ከተለያዩ ቦታዎች የተውጣጡ ባለሞያዎች እንዲሰጡ ተደርጓል። ሰልጣኞቹ ሴቶች ስልጠናውን መውሰዳቸው ከራሳቸው አልፈው ለሀገር እና ለወገንም ጭምር ጠቃሚ ዜጋ እንዲሆኑ በማሰብ የተከናወነ መሆኑም ተገልጿል።

በሰልጣኞቹ የምርቃት ስነሥርዓት ላይ የተገኙት የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ እንደገለፁትም ሰልጣኞቹ ከስልጠናው በኋላ የግል ኪሳቸውን መሙላት ብቻም ሳይሆን ከስራ ጠባቂነት አስተሳሰብ ተላቀው ወደ ስራ ፈጣሪ የአመለካከት ባለቤትነት እንደሚገቡ እና ሌሎች በርካታ ሴቶችንም እንደሚስቡ ገልጸዋል። ሚኒስትሯ አያይዘውም የሰልጣኞቹ ግላዊ ጥረትና ተነሳሽነት ለበለጠ ውጤት እንዲያበቃቸው ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ይህ አይነቱ ለስራ አጥ ሴቶች የሚሰጥ ስልጠና ከዚህ ቀደምም በተለያዩ መንገዶች እና አካባቢዎች ሲሰጥ እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ። ባለፈው ጥር ወር 2006 ዓ.ም 600 ያህል ቁጥር ያላቸው ሴቶች በጅግጅጋ፣ በድሬዳዋ እና በአዲስ አበባ ለሶስት ወራት ያህል ስልጠና መውሰዳቸው ተገልጿል። በዚህ ስልጠናም ሴቶቹ በተለየዩ የጣውላ ስራ፣ በቀለም ቅብ እንዲሁም በጀሶ ስራ ስልጠና ወስደዋል። ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የስራ ፈጠራ ክህሎቶች ላይ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። በዚህም እነዚህ ስራ ፈትተው የሚቀመጡ ሴቶች በቀጣይ ህይወታቸው ጥሩ አጋጣሚዎችን ተጠቅመው የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውን ህይወት እንዲለውጡ ያግዛቸዋል ተብሏል። ይህም ሴቶቹ ቤታቸው ውስጥ ተቀምጠው የሌላውን እጅ ከመጠበቅ ይልቅ የራሳቸውን ገቢ በመፍጠር የተሻለ ነገር እንዲኖራቸው ያደርጋል ተብሏል።

በዚህ በሶስተኛ ዙር የሰልጣኞች ምርቃት ፕሮግራም ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሚስ ቻንታል ሄብረቼት በበኩላቸው ሰልጣኞቹ በስልጠናው ወቅት ያገኙትን እውቀት እና ክህሎት ወደ ስራ በመቀየር ህይወታቸውን የመለወጥ እና በሀገራቸው እድገት ውስጥም ከፍተኛ ተሳታፊ የመሆን ተስፋ መሰነቅ እንዳለባቸው ገልፀዋል። ሴቶቹ ኑሮን ለማሸነፍ እና በራሳቸው ላይ ለውጥ ለማምጣት በራሳቸው ተነሳሽነት ታግዘው ወደ ስራ በመግባት አሁን ያሉባቸውን እንቅፋቶች በቅርብ ቀናት ውስጥ ማስወገድ እንደሚችሉም አምባሳደሯ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ስራ ከመፈለግ ይልቅ የራስን ስራ ፈጥሮ መስራት ከምንም ነገር በላይ አዋጭ ነገር እና አማራጭ የሌለው በመሆኑ ሴቶቹ በዚህ የሰራ ፈጠራ ላይ መሰማራታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ በራሳቸው ላይ ለውጥ እንዲያመጡ ያግዛል ተብሏል። ሰልጣኞቹም ከስልጠናው ካገኙት እውቀትና ክህሎት በተጨማሪ ያሉትን የስራ አማራጮች ተጠቅመው የየራሳቸውን ስራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ይናገራሉ።

“አሁን ያለኝ እውቀት ስራውን እንድሰራ በቂዬ ነው። ከቻልኩኝ የራሴን ፀጉር ቤት ከፍቼ የመስራት ሀሳብ አለኝ። አቅሜ ካልቻለ ደግሞ በሰው ፀጉር ቤት ተቀጥሬ ትንሽ እሰራለሁ። ነገሮችን ሳስተካክል ደግሞ የራሴን ፀጉር ቤት ከፍቼ መስራት እፈልጋለሁ። እኔ ብቻም ሳልሆን ሌሎች ሰዎችንም ቀጥሬ የመስራት ሰፊ ሃሳብ ነው ያለኝ” የሚሉት ወይዘሮ ወርቅነሽ፣ ከእንግዲህ በኋላ እንደቀድሞ የቤት እመቤት ሆነው የባለቤታቸውን እጅ የሚጠብቁበት ሁኔታ እንደሌለ ይናገራሉ።

ወጣት ፍሬይህወት በበኩሏ አሁን የገንዘብ አቅሟ የራሷን ስራ ለመስራት ብዙም የማይፈቅደላት ቢሆንም፣ ባላት ነገር ተጠቅማ ራሷን ለመለወጥ ማቀዷን ትናገራለች። “እስከ አሁን ዝም ብዬ በመቀመጤ በጣም ቆጭቶኛል። ቤቴ ውስጥ ቁጭ ብዬ ብዙ ነገር መስራት እችል ነበር። ስልጠናውን እየወሰድኩ እያለሁ ቤቴ ሆኜ የጎረቤቶቼን ፀጉር እየሰራሁ ገንዘብ ማግኘት ችያለሁ። አሁን ደግሞ ጥሩ እውቀት አለኝ። በዚህ እውቀቴ ከዚህ የበለጠ ስራ ለመስራት አስባለሁ” ትላለች ወጣት ፍሬህይወት።

በሰልጣኞቹ የምርቃት ስነሥርዓት ላይ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት እንዲሁም በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሚስ ቻንታል ሄብረቼት እና ሌሎች እንግዶችም ታዳሚ የነበሩ ሲሆን፣ ዝግጅቱም ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በመጡ የኪነ ጥበብ ወጣቶች ደምቆ ውሏል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1859 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 764 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us