የአእምሮ ጤና ትኩረት ያልተሰጠው፤ ግን ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ

Thursday, 14 August 2014 12:42

ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሀገራችን ያለውን የአእምሮ ጤና ህክምና ለማጠናከር ስትራቴጂ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ስትራቴጂው እ.ኤ.አ. ከ2012/13 እስከ 2015/16 ባሉት ጊዜያት ውስጥ በቀላሉ ተደራሽ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገኝ እና ተቀባይነት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት የተቀመጠ ነው። ይህን የተቀመጠ ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግም የተወሰኑ እንቅስቃሴዎች የተጀመሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች መካከልም አንድ ሀገራዊ የአእምሮ ጤና ተቋምን ማቋቋም እና በተለያዩ የጤና ተቋማት የአእምሮ ጤና ባለሞያዎች ሰልጥነው እንዲወጡ ተደርጓል።

በተጨማሪም ለመስኩ የተመደበውን በጀት በአግባቡ እና ለተፈለገው ዓላማ በመጠቀም እንዲሁም የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች በየአካባቢያቸው ህክምና እንዲያገኙ የህክምና ጣቢያዎችን የማስፋፋት ሥራዎች ተሰርተዋል።

ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት ለመፈጸም የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ የመሠረተ ልማት እና የጤና ተቋማትን ማስፋፋት እንዲሁም አገልግሎቶቹን በተከፋፈለ መንገድ ለመስጠት የሚያስችሉ መልካም አጋጣሚዎችም እንዳሉ ተገልጿል። ይህም ሆኖ በእንቅስቃሴው ላይ እንደድክመት የተቀመጡ ነገሮች አልጠፉም። ከእነዚህም ውስጥ ውስን ሀብት ብቻ በመኖሩ አገልግሎቱን ተደራሽ የማድረግ ችግር፣ አብዛኛው በጀት በሆስፒታሎች አገልግሎ ላይ እንዲውል መደረጉ፣ ከህክምና ውጭ ላሉ እንደ ማገገሚያ እና የስነልቦና አገልግሎቶች የተወሰነ ሀብት መመደብ ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪም የተቀናጀ የሪፈራል ሲስተም እጥረትና እየተሰጡ ላሉ ስልጠናዎች ክትትል እና ድጋፍ አለማድረግ የሚሉት እንደ ደካማ ጎን ተቀምጠዋል።

ሌላው ይህ ስትራቴጂ በተያዘለት መንገድ እንዳይሄድ ካደረጉት ችግሮች መካከል የበጀት እና የሌሎች ሀብት እጥረት፣ አማራጭ አገልግሎቶች አለመኖር እንዲሁም የአእምሮ ችግር ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚደርሰው የመገለል ችግር ተጠቃሾች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ደካማ የሆነ ተጨባጭ የጥናት ውጤቶችን አጠቃቀም እና የጤና አገልግሎቱን እድገት ለመለካት ያለው የመረጃ እጥረት ለዚህ ስትራቴጂ ተግባራዊነት እንደ ችግር የተጠቀሱ ናቸው።

ይህን ስትራቴጂ እውን ለማድረግ እና ስለ አእምሮ ጤና በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ግንዛቤ እጥረት ለማጥራት ያግዛል የተባለ ሀገር አቀፍ ሲምፖዚየም ባለፈው ነሐሴ 5 እና 6 ቀን 2006 ዓ.ም በደሳለኝ ሆቴል ተካሂዶ ነበር።

የአእምሮ ጤና ችግር በሀገራችን ቀዳሚ ከሆኑት የማይተላለፉ በሽታዎች አንዱ ነው። በተለይ በገጠር የሀገሪቱ አካባቢ ይህ በሽታ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ ከሚገኙ በሽታዎች 11 በመቶውን ይይዛል። የአእምሮ ጤና ችግር በተለይ ከድብርት ጋር በመያያዝ ከኤች አይ ቪ በመቅደም እጅግ አሰቃቂው በሽታ ነው። በዚህም ሳቢያ ይህ የአእምሮ ጤና ችግር በሀገራችን በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እየተገለፀ ይገኛል። ምንም እንኳ ይህ የአእምሮ ጤና ችግር በሀገራችን ሰፊውን ድርሻ ቢይዝም የተሰጠው ትኩረት ግን እጅግ ዝቅተኛ ነው።

የአእምሮ ጤና ችግር በሀገራችን በአብዛኛው ከመለኮታዊ ችግሮች ጋር ስለሚያያዝ ብዙም በግልፅ እንዲታወቅ እና እውቅና እንዲያገኝ አይደረግም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ እነዚህ የአእምሮ ጤና ችግሮች ከመጥፎ የሰው አይን (ቡዳ)፣ ልክፍት እና ከመሳሰሉት ነገሮች ጋር እንደሚያያዝ በማህበረሰቡ ዘንድ የተደረጉ ጥናቶችን ጠቅሶ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል። ለእነዚህ የአእምሮ ጤና ችግሮች የሚሰጠው ምክንያት ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እንደመሆኑ መጠን፤ ህመሙን ለማዳንም ወደ ጤና ተቋማት ከመሄድ ይልቅ በሃይማኖት እና በባህል መድሃኒቶች መጠቀሙ ደግሞ በሽታው እንዲባባስ ያደርገዋል ይላል ጥናቱ።

ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ የአእምሮ ጤና ችግሮች ለምሳሌ ጭንቀትን የመሰሰሉት ህመሞች ከድህነት አሊያም ከከባድ ሃዘን ጋር የሚያያዙ በመሆናቸው ብዙም ትኩረት እንደማይሰጣቸው ተገልጿል።

የዓለም ጤና ድርጅት የአእምሮ ጤና ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንዲህ ያስቀምጣል፤ አንድ ሰው የራሱን ችሎታ ማገናዘብ ሲችል፣ ከሌሎች ጋር አዎንታዊ የሆነ ተግባቦትን መፍጠር ሲችል፣ የህይወትን ውጣ ውረዶች መቋቋም ሲችል፣ በምርታማነት መልኩ መስራት ሲችል እና ውጤታማ ሲሆን እንዲሁም ለቤተሰቡ እና ለማህበረሰቡ አስተዋፅኦ ማበርከት ሲችል የአእምሮ ጤና አለው ይባላል።

በተቃራኒው ደግሞ የአእምሮ ጤና ችግር ያለበት ነው በአስተሳሰቡ ላይ፣ በስሜቱ ላይ፣ አሊያም ደግሞ በባህሪው ላይ ችግር ይኖርበታል። እነዚህ በአስተሳሰቡ እና በስሜቱ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች ደግሞ ከእለት ተእለት እንቅስቃሴው ጋር በመጋጨት ህይወቱ እንዲመሰቃቀል ያደርጉታል። በዚህም ሳቢያ ከቤተሰብ፣ ከጓደኞቹ እና ከማህበረሰቡ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲበላሽ ያደርገዋል።

ለአንድ ሰው አእምሮ ጤና መቃወስ የማንም ሰው ስህተት አይደለም። ኤክስፖርቶች እንደሚገልፁትም ለአእምሮ ጤና ችግር ራሱን የቻለ መንስኤ አለው። ይኸውም ከዘር የሚተላለፍ ተገላጭነት፣ በጭንቅላት ውስጥ ያለው የኬሚካሎች አለመመጣጠን፣ ጭንቀት እና ለተለያዩ አእምሮን ለሚያስቱ ድንጋጤዎች (trauma) መጋለጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በእነዚህ ችግሮች ምክንያትም የተለያየ አይነት የአእምሮ ጤና ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላልሉ። እነዚህ ችግሮችም ከፍተኛ ጭንቀት፣ ድብርት፣ መደበት፣ የመዘንጋት በሽታ (schizophrenia) እንዲሁም የአእምሮ መቃወስ (bipolar disorder) ናቸው።

ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪም የወደዱትን ማጣት፣ ፍቺ መፈፀም፣ ለአደጋ መጋለጥ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ሱስ አስያዥ ነገሮችን መጠቀም ለችግሩ የበለጠ ተጋላጭ የሚያደርጉ ምክንያቶች ናቸው። እነዚህ ነገሮች በሚከሰቱበት ወቅት የእንቅልፍ መዛባት እና የእንቅልፍ ማጣት፣ የአመጋገብ ችግር፣ እንዲሁም አቅም ማጣት እና አስተሳሰብን የመቀየር ችግር ይፈጠራል።

በዚህም ሳቢያ በርካቶች ወዳልታሰበ የህይወት አቅጣጫ ያመራሉ። በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም ራሳቸውን ለማጥፋት አደጋ ይዳረጋሉ። ከዚህ ስሜት ለመውጣት የተወሰኑት አደንዛዥ እፆችን እና አልኮልን ሲጠቀሙ፣ ሌሎች ደግሞ ይህን ብስጭታቸውን ለመቋቋም ተደባዳቢ፣ ጠብ አጫሪ እና ጉልበተኛ ይሆናሉ። እነዚህ ችግሮች ታዲያ ፍቺ፣ ቤት ውስጥ ጥቃት፣ በወላጆች እና በልጆች መካከል ብጥብጥ እንዲፈጠር እንዲሁም በህፃናት ላይ የሚደርሱ ወንጀሎች እንዲስፋፉ ያደርጋሉ።

ከጭንቀት ለመገላገል ተብሎ ጥቅም ላይ የሚውሉ እንደ ጫት፣ አልኮል እና ካናቢስ ያሉት ነገሮች በሌላ በኩል ለእዚህ የአእምሮ ጤና ችግር እንደምክንያት እንደሚጠቀሱም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል።

በ2000 እ.ኤ.አ የአእምሮ ጤና ችግር በአለማችን ላይ አደገኛ ናቸው ተብለው በተቀመጡ በሽታዎች ውስጥ 13 በመቶውን እንደሚይዝ የአለም ጤና ድርጅት ይፋ አድርጎ ነበር። ይህ አሃዝ አሁን ባለበት ሁኔታ ከቀጠለም በ2020 ይህ የአእምሮ ጤና ችግር 15 በመቶ ድርሻ ይይዛል ተብሎ ይገመታል ይላል ድርጅቱ። ለዚህ የአእምሮ ጤና ችግር እንደመንስኤ ከተቀመጡት ምክንያቶች ውስጥም ጭንቀት በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ነበር። በዚህ አያያዝ ጭንቀት በ2020 ለአእምሮ ጤና ችግር ከሆኑ ምክንያቶች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሊቀመጥ ይችላል ተብሏል።

በኢትዮጵያ በርካታ የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ቢገኙም ስለጉዳዩ ያለው አመለካከት ግን አነስተኛ እንደሆነ ይገለፃል። የአእምሮ ጤና ችግርን አንስቶ መነጋገር እንዳልተለመደ፤ መነጋገር ቢቻል እንኳ ችግሩ ያለባቸውን ሰዎች “እብድ” ከማለት በተረፈ ሰዎችን እንደማንኛውም ህመምተኛ ያለመመልከት ችግር እንዳለ ይነገራል። ከዚህ በተጨማሪም የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ሁልጊዜ ጉዳት የሚያደርሱ ተደርገው ከመታየታቸውም በላይ ችግራቸው እንደማይድን ተደርጎ ይወዳል።

በኢትዮጵያ ካሉ ህፃናት ከ17 እስከ 23 በመቶ የሚሆኑት የአእምሮ ጤና ችግር እንዳለባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። በህጻናት ላይ ለሚከሰቱ የአእምሮ ጤና ችግር እንደምክንያት የተቀመጡትም በወሊድ ወቅት እና በእርግዝና ወቅት የሚፈጠሩ ውስብስብ ችግሮች ናቸው።

ሌላው በአእምሮ ጤና ችግር ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት አለው የተባለው ኤች አይ ቪ ኤድስ ነው። ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ እንደ ጭንቀት፣ ድብርት እና ለመሳሰሉት የአእምሮ ጤና ችግሮች ተጋላጭ በመሆናቸው በሽታውን የመቋቋም አቅማቸው ይወርዳል። በተጨማሪም የአኗኗር ዘይቤያቸውን በመለወጥ ለረጅም ጊዜ በህይወት የመኖር እድላቸውን ያሳጣቸዋል ይላል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከቫይረሱ ጋር ከሚኖሩ እና መድሃኒት ከሚወስዱ ሰዎች 38 በመቶዎቹ የጭንቀት ችግር አለባቸው። ከቫይረሱ ጋር እየኖሩ በቲቢ በሽታ ጋር ከተያዙ ሰዎች መካከል ደግሞ 64 በመቶዎች ለጭንቀት ተዳርገዋል።

በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች ሌሎቹ የአእምሮ ጤና ችግር ተጠቂዎች ናቸው። በእስር ላይ ያሉ ሰዎች ካለው የእስረኞች ብዛት፣ እስረኞች ከፈፀሟቸው ወንጀሎች አይነት እንዲሁም ነፃነትን ከማጣት እና ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ ካለማድረግ የተነሳ፣ ከማህበረሰቡ በመገለላቸው፣ ተስፋ ከማጣታቸው እና በቂ የሆነ የጤና አገልግሎት ካለማግኘታቸው የተነሳ አብዛኞቹ ለአእምሮ ጤና ችግር ተጋላጮች ናቸው። ምንም እንኳን በቂ የሆነ መረጃ ባይኖርም በአዲስ አበባ ፌዴራል ማረሚያ ቤት እና በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በሚገኙ ታራሚዎች መካከል 61 ነጥብ 9 በመቶዎቹ ለከፍተኛ የአእምሮ ጤና ችግር የተጋለጡ ሆነው ተገኝተዋል ሲል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስቀምጧል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
2085 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 476 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us