ከችግር ያልተላቀቁት ወጣቶች

Wednesday, 20 August 2014 13:33

የዓለም ወጣቶች ቀን በየዓመቱ ነሐሴ 6 ቀን በመላው ዓለም ላይ ተከብሮ ይውላል። የዘንድሮም በተለያዩ ዝግጅቶች ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ተከብሯል። እለቱ ሲከበርም የወጣቶች ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሁንም ድረስ በቂ መፍትሔ እንዳላገኙ ተገልጿል።

የዘንድሮው የወጣቶች ቀንም «ወጣቶች እና የአእምሮ ጤንነት» በሚል መሪ ቃል ነበር የተከበረው። ይህ አለም አቀፉ የወጣቶች ቀን ወንድ እና ሴት ወጣቶች በአለም ላይ ለሚፈለገው ለውጥ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ፣ ወጣቶችን የሚገጥሟቸው ውጣ ውረዶችን አስመልክቶ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ታስቦ ነው የሚከበረው። በእለቱም ሀገራት የሚመለከታቸው አካላት የወጣቶችን ፍላጎት ተገንዝበው ከችግሮቻቸው የሚያመልጡባቸውን ፖሊሲዎች እንዲያወጡ እና ተግባራዊ እንዲያደርጉ እንዲሁም ወጣቶችን በውሳኔ ሰጪነት ሃላፊነት ውስጥ እንዲያሳትፉ የማደረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው በማሳሰብ ይከበራል።

በኢትዮጰያ ከህዝቡ ቁጥር ከግማሽ በላይ የሚሆነው ወጣት ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወጣት የሚባለው ትውልድ እድሜው ከ15 እስከ 24 ዓመት ያለው እንደሆነ ያስቀምጣል። በኢትዮጵያም በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች የህዝቡን ግማሽ ያህል ቢኖቸውም ህይወታቸውን በተሳካ ሁኔታ የሚመሩት ግን የተወሰኑት ናቸው።

እ.ኤ.አ በ2012 ኢምፓክት ኢትዮጵያ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው በአዲስ አበባ ብቻ 100ሺ ያህል የጎዳና ተዳዳሪዎች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ከግማሽ በላዮቹ ወጣቶች ናቸው። ይህ ቁጥር በየቀኑ ከገጠራማ የሀገሪቱ ክፍል በሚመጡ ወጣቶች እያሻቀበ ይገኛል። እነዚህ ወደ ከተማ የሚገቡ ወጣቶችም ስራ ፈተው ከመቀመጣቸው የተነሳ አላስፈላጊ በሆኑ እንደ እፅ ተጠቃሚነት፣ በአልኮሆል ጠጪነትና የመሳሰሉት ድርጊቶች ላይ ይሳተፋሉ። ከዚህ በመቀጠልም በዝርፊያ፣ በቅሚያ፣ እና በመሳሰሉት ወንጀሎች ውስጥ በመሳተፍ ወጣት ጥፋተኛ ይሆናሉ። በየጊዜው ይፋ የሚሆነው የፖሊስ ሪፖርት እንደሚያመለክተውም ከእነዚህ አይነት ወንጀሎች ጋር በተያዘ በቁጥጥር ስር ከሚውሉ ሰዎች መካከል ከግማሽ በላዮቹ ወጣቶች ናቸው።

ሌላው ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል የተባለው የትርፍ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ቦታ እና እንቅስቃሴ አለመኖሩ ነው። በዚህም ሳቢያ እነዚህ ወጣቶች ወደተለያዩ የፊልም እና ሲኒማ ቤቶች አምርተው ጊዜያቸውን ማሳለፍን እንደ ብቸኛ አማራጭ ይወስዱታል። አብዛኞቹ እነዚህ ወጣቶች የሚመለከቷቸው ፊልሞች ደግሞ ጥፋተኝነትን፣ ልቅ ወሲብን እና ኢ-ሰብአዊ የሆኑ ድርጊቶች የሚታዩባቸው በመሆናቸው ወጣቶቹ ስለራሳቸው ባህል፣ ህዝብ እና ሀገር አሉታዊ አመለካከት እንዲኖራቸው እና ሌላውን አለም እንዲናፍቁ ያደርጋቸዋል።

ወጣት ሴቶች ደግሞ ከላይ ከተጠቀሱት አጣብቂኞች በተጨማሪም ለውስብስብ ችግሮች እየተዳረጉ መሆኑን ነው ሪፖርቱ የሚያመለክተው። ትምህርታቸውን ያቋረጡ፣ እስከ አስረኛ ክፍል ወይም እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሴት ወጣቶች በሀገሪቱ ውስጥ ሰርተው መኖር ባለመቻላቸው ተስፋ በመቁረጥ ወደሴተኛ አዳሪነት ሕይወት እንደሚገቡ ያተተው ሪፖርቱ ፤ይህን ተከትሎም ለኤችአይቪ እና ለመሳሰሉት የአባላዘር በሽታዎች የሚዳረጉ በርካቶች ናቸው ይላል።

የስራ አጥነት ጉዳይ ከተነሳ በኢትዮጵያ ያለው የስራ አጥነት ምጣኔ አሁንም ድረስ ከሁለት አሀዝ እንዳልወረደ ከማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ለአብነት ያህልም ዝቅተኛ የተባለው እና እ.ኤ.አ. በ2012 የተመዘገበው የስራ አጥነት ምጣኔ 17 ነጥብ 5 በመቶ ነው። ይህ ቁጥር በ2012 ዓ•ም 18 በመቶ ነበረ። ከፍተኛውን ደረጃ የያዘው እና እ.ኤ.አ በ1999 ዓ.ም የተመዘገበው የስራ አጥነት ምጣኔ ደግሞ 26 ነጥብ 4 በመቶ እንደነበረ መረጃው ያመለክታል።

ታዲያ የዘንድሮው አለም አቀፉ የወጣቶች ቀን ልክ እንደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ሁሉ በበርካታ ችግር ተተብትበው የሚገኙ ወጣቶችን ሊያጠቃ ከሚችለው የአእምሮ ጤና ችግር ለመታደግ ታስቦ የተከበረ ነው። የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳይም እንደገለፀው ወጣቶች ሰላም እና መረጋጋትን ሊያመጣ የሚችል እምቅ ችሎታ ባለቤቶች በመሆናቸው ቀጣይ ህይወታቸውን መስመር ማስያዝ ያስፈልጋል። ቀኑ ሲከበርም በፖሊሲዎች እና አመለካከቶች ላይ የወጣቶችን ተሳትፎ ማካተት እና ለወጣቶችም እድሉን በመስጠት መሆን እንዳለበት ተገልጿል።

ወጣትነት ተአምራዊ የሆኑ ለውጦች የሚከሰቱበት እና ከህፃንነት ወደ ጎልማሳነት ለመሸጋገር የሚያገለግል የእድሜ ደረጃ በመሆኑ እጅግ ውስብስብ እና ከአእምሮ ጤና ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች የሚከሰቱበት እንደሆነም ተገልጿል። የዘንድሮው የወጣቶች ቀን መሪ ቃልም ሊመረጥ የቻለው በወጣቶች ላይ የሚከሰቱ የወጣጥነት እድሜ አስቸጋሪ ነገሮችን አስመልክቶ ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው እንዲሁም ወጣቶች በሚያሳዩት ያልተጠበቀ ባህሪይ ምክንያት ከማህበረሰቡ የሚደርስባቸው መድሎ እና መገለል እንዲቆም እንዲሁም ወጣቶች ሃሳባቸውን እንዲያሳኩ ከጎናቸው እንዲቆም ለማድረግ ታስቦ ነው ይላል የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣የሳይንስ እና ባህልና ድርጅት (ዩኔስኮ)።

ዩኔስኮ ይዞ በተነሳው አላማም ወጣቶች ተሳታፊነታቸው ጨምሮ በሀገራቸው እና በመላው አለም ላይ በሚከሰተው ለውጥ ላይ ሙሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ ገልጿል። ለዚህ ደግሞ ወጣቶችን ለፖሊስ ማስፈፀሚያ ቁስ አድርጎ ሳይሆን የፖሊሲ ለውጥ ሀይል አድርጎ መቀበልን ይጠይቃል ብሏል ድርጅቱ። ይህ ደግሞ በትውልዶች መካከል ያውን መግባባት እና ትብብር በማጠናከር ወጣቶች በማህበረሰቡ ውስጥ እና በኢኮኖሚው ላይ ተሳትፈው ለውጥ እንዲያመጡ በማድረግ የሚሳካ ነው ይላል ድርጅቱ። ሀገራት አዳዲስ ፖሊሲዎችን ሲያወጡም ካለፉት ስህተቶች በመማር እና የወጣቶችን ፍላጎት በማዳመጥ ቢሆን ችግሮቻቸውን በቀላሉ መቅረፍ እንደሚችሉም ተገልጿል።

የወጣቶች የአእምሮ ጤና ለአጠቃላይ የማህበረሰብ ጤናማነት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ነው የተገለፀው። ወጣቶች የፈጠራ ምንጮች እና የአወንታዊ ለውጥ መሰረቶች በመሆናቸው እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ጤናማ ሆነው ጤናማ ማህበረሰብ እንዲገነቡ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ሲልም አሳስቧል።

እንደተበባሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ በአለማችን ላይ ካሉ ወጣቶች 20 በመቶዎቹ የአእምሮ ጤና ችግር ተጠቂዎች ናቸው። ከአእምሮ ጤና ችግር ጋር የሚኖሩ ወጣቶች ታዲያ በሚደርስባቸው መድሎ እና መገለል ምክንያትም ብዙዎች እርዳታ ማግኘት አይችሉም። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለውም እነዚህ በችግሩ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ባላስፈላጊ እፍረት ከህዝቡ ተገልለው እንዳይኖሩ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ቀኑንም ስናከብር የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ወጣቶች ተሰጥኦዋቸውን እንዲያውቁ እና የአእምሮ ጤና ችግር ሁላችንንም እንደሚመለከተን እናሳያቸው ብሏል ድርጅቱ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ባንኪሙን በበኩላቸው ይህን የአእምሮ ጤና ችግር ባለባቸው ወጣቶች ላይ የሚደርስ አድሎ እና የመገለል ችግር ለማስቀረት ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ ገልፀዋል። አያይዘውም ትምህርት ይህን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫወት እንዲሁም የአእምሮ ጤናን አስመልክቶ እንዴት ማውራት እንዳለብን ጭምር ለመረዳት እና ለመገንዘብ ትምህረት እጅግ ያግዛል ብለዋል። በተለይ የአእምሮ ጤና ችግር ችላ በተባለባቸው እና በዚህ ችግር ላይ ብዙም ኢንቨስት እየተደረገባቸው ባልሆኑ ሀገራት ያሉ የአእምሮ ችግር ያለባቸው ወጣቶች ለድህነት፣ ለፆታዊ ጥቃት እና ለመሳሰሉት ችግሮች የበለጠ ተጋላጮች በመሆናቸው በማህበረሰቡ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራሉ፡፤

ለእዚህ የአእምሮ ጤና ችግረ ተጋላጭ የሆኑ ቤት አልባ ወጣቶች፣ በጥፋተኝነት የተጠረጠሩ ወጣቶች፣ ወላጅ ያጡ ወጣቶች እና የመሳሰሉት ደግሞ ለእዚህ መድሎ እና መገለል በይበልጥ የተጋለጡ ናቸው። የሚሊኒየሙን የልማት ጎሎች ለማጠናቀቅ አምስት መቶ ያህል ቀናት እንደቀሩ የገለፁት ዋና ፀሀፊው፣ ሁላችንም እነዚህን ለችግሩ ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶች በመርዳት ታሪካዊ የሆነው ዘመቻ እንዲሳካ የድርሻችንን እንወጣ ሲሉ ጠሪ አቅርበዋል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1408 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 479 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us