ሰው ማትረፍ መቻል በራሱ ትርፍ ነው

Wednesday, 27 August 2014 11:20

 

አቶ ዳዊት ኃይሉ

 

ውዳሴ ዳያግኖስቲክ ማእከል ከተቋቋመ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም በዚህ አጭር እድሜው ለህብረተሰቡ ያበረከተው አስተዋፅኦ ግን ከፍተኛ ነው።ይህ ማእከል የተለያዩ የሶቲስካን ፣ የራጅ፣ የአልትራሳውንድ እና መሳሰሉትን የጤና አገልግሎቶች በመስጠት በሀገሪቱ የመጀመሪያው ማዕከል ነው። ማዕከሉ በአብዛኛው ከላይ የተጠቀሱትን አገልግሎቶች የሚሰጥ ሲሆን፤ ከዚህ ጎን ለጎንም የአምቡላንስ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ያቀርባል። ማዕከሉ እነዚህን የጤና አገልግሎቶች ለህብረተሰቡ ለማቅረብ የተቋቋመ ቢሆንም፣ ከዚህ በተጨማሪ ግን በሚያደርጋቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ይታወቃል።

ማዕከሉ በተለይ በየዓመቱ መጨረሻ ወር ወይም በጳጉሜ ወር “ጳጉሜን ለጤና” በሚል መሪ ቃል የሲቲ ስካን ምርመራ እንዲያገኙ በሀኪም ታዞላቸው ነገር ግን ምርመራውን ለማግኘት የገንዘብ አቅም የሌላቸው ሰዎች ምርመራውን በነፃ እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፣ ምርመራውንም በነፃ ይሰጣል። ማዕከሉ ይህን አይነቱን አገልግሎት በመስጠቱ ረገድ አራት አመታትን ያሳለፈ ሲሆን ዘንድሮም ለአምስተኛ ጊዜ ይህንኑ አገልግሎት ከጳጉሜ አንድ ጀምሮ እስከ ጳጉሜ አምስት ቀን 2006 ዓ•ም ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ተገልጿል።

የማዕከሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ኃይሉ የዘንድሮውን ዝግጅት አስመልክቶ እንደገለፁትም ማዕከሉ “ጳጉሜን ለጤና” በሚለው መርህ በየዓመቱ ምርመራውን እንዲያደርጉ ታዘው ነገር ግን ገንዘብ ለሌላቸው ሰዎች ነፃ ምርመራ ይሰጣል። ይህን ነፃ የሲቲ ስካን ምርመራ አገልግሎት የሚወስዱት ህሙማን በመንግስት ሆስፒታሎች ምርመራ ተደርጎላቸው በሀኪም የታዘዙ እና ይህን የሲቲ ስካን ምርመራ ገንዘብ ከፍለው ማድረግ የማይችሉ እንደሆኑ የገለፁት አቶ ዳዊት፤ እነዚህ ህሙማን በእርግጥ ከፍለው አገልግሎቱን ማግኘት የማይችሉ እና ምርመራው የሚያስፈልጋቸው እንደሆነ ሲረጋገጥም ምርመራው እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።

ማዕከሉ ለህብረተሰቡ ይህን የነፃ አገልግሎት ለመስጠት የተነሳሳው የተቋቋመበትን ቢዝነስ ከማራመድ ጎን ለጎንም ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ስላለበት መሆኑን የገለፁት አቶ ዳዊት፤ የጳጉሜ ወር ለዚህ የነፃ ሲቲስካን ምርመራ የተመረጠችውም በማህበረሰቡ ውስጥ ተስፋን ለመፈንጠቅ መሆኑን ገልጸዋል። “ጳጉሜ በአመቱ ውስጥ የመጨረሻዋ ወር እንዲሁም ወደ አዲስ አመት የመሸጋገሪያ ድልድይ በመሆኗ ሁላችንም አዲሱን አመት በአዲስ በተስፋ፣ ራእይ እና ጤና እንድንቀበለው ካለን ፅኑ ፍላጎት በመነሳት ነው ይህ አገልግሎት በዚህች ወር ለመስጠት የመረጥነው” ሲሉ አቶ ዳዊት አስረድተዋል።

ማዕከሉ ነፃ የሲቲ ስካን ምርመራውን ላለፉት አራት ዓመታት ሲሰጥ የቆየ በመሆኑ እስከ አሁን ድረስ ከአምስት ሺህ በላይ የሆኑ ሰዎች ነፃ የሲቲስካን ምርመራ አግኝተዋል። ማእከሉ ምርመራውን ከውጭ በሚመጡ ብቁ ባለሞያዎች ጭምር የሚሰጥ ሲሆን፣ ይህ ምርመራ ዓመትን ጠብቆ ብቻም ሳይሆን፤ በየእለቱም የሚከናወን ምርመራ መሆኑን አቶ ዳዊት ገልጸዋል። “ይህን ነፃ የምርመራ አገልግሎት የምንሰጠው በአመት አንድ ጊዜ በዘመቻ ቢሆንም በየቀኑ ግን ብዙ ሥራዎችን እንሰራለን። በቀን ቢያንስ በተለያየ አጋጣሚ ጉዳት ለደረሰባቸው ከአራትና አምስት ሰዎች በላይ ነፃ ምርመራ እናደርጋለን” ብለዋል አቶ ዳዊት። ከዚህ በተጨማሪም በትራፊክ አደጋ እና በተለያዩ አጋጣሚዎች አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ሲኖሩ ስልክ እየተደወለ ጭምር ነፃ ምርመራውን እንዲሰጥ ማዕከሉ እንደሚጠየቅ ተገልጿል።

ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ይህን ነፃ የሲቲስካን ምርመራ ለመስጠት ካነሳሱት ምክንያቶች መካከል ዋናው በጤናው ዘርፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ካለው ፍላጎት በመነሳት ቢሆንም፣ ከዚህ ጎን ለጎን ግን መንግስታዊ የሆኑ የጤና ተቋማት ብቻቸውን በሀገራችን በጤናው ዘርፍ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የማይችሉ በመሆኑ ማዕከሉ በበጎ ፈቃደኝነት የራሱን ኃላፊነት ለመወጣት ካለው አቋም በመነሳት ነው ተብሏል። እንዲህ አይነቱን በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የሲቲስካን ምርመራ ከዚህ በፊት የትኛውም ማዕከል አድርጎት እንደማያውቅ የተገለፀ ሲሆን፤ ይህም ማዕከሉን በዚህ ረገድ የመጀመሪያው ያደርገዋል ተብሏል።

በማዕከሉ ነፃ የሲቲ ስካን ምርመራ የሚያገኙ ሰዎችን ለመለየት መጠነኛ ፈታኝ ሁኔታዎች እንደሚስተዋሉም ከዚህ አገልግሎት ጎን ለጎን ተነስቷል። የትኛው ሰው ነው ከፍሎ ምርመራውን ማግኘት የሚችለው? የማይችለውስ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በድህነት ውስጥ የሚኖር በመሆኑ አስቸጋሪ እንደሆነ ተገልጿል። ይህን ችግር ለመቅረፍም የነፃ ምርመራ አገልግሎቱን ለመስጠት ከመንግስት ሆስፒታሎች ጋር በመስራት ነፃ አገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን ህሙማን ማስረጃ የመሰብሰብ ስራ ይሰራል። ከዚህ በተጨማሪም የኦቲስቲክ ችግር ያለባቸው ልጆች ማእከላት፣ ወላጅ አልባ የሆኑ ህጻናት መረጃ ማህበራት እንዲሁም የአረጋውያን መረጃ ማእከላትን የማእከሉ ችግረኛ ህሙማንን የመለየት ስራ እየተሰራ እንደሆነ ተገልጿል።

ማዕከሉ በነፃ የሚሰጠው የሲቲ ስካን ምርመራ በገንዘብ ሲሰራ ለአንድ ሰው ከአንድ ሺህ እስከ ሁለት ሺህ ብር ዋጋ አለው። ማዕከሉ ለትርፍ የተቋቋመ ድርጅት እንደመሆኑ በየዓመቱ ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣ ይገኛል። ታዲያ ይህን ያህል ገንዘብ ማውጣቱ በማእከሉ ላይ ኪሳራ አያስከትልም ወይ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ለዚህ ጥያቄ መልስ የሰጡት የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማእከል ማርኬቲንግ እና ህዝብ ግንኙነት ማናጀሯ ወይዘሮ ሰብለ ኃይሉ ናቸው። “ሰው ማትረፍ መቻል በራሱ ትርፍ ነው” ያሉት ወይዘሮ ሰብለ፣ ምንም እንኳን ማእከሉ ለትርፍ የተቋቋመ ማዕከል ቢሆንም፣ ለሰዎች መልካም ነገርን ማድረግ በራሱ አያከስርም። የኛ አገልግሎት ሰዎችን መጥቀም እስከቻለ እና የሰው ህይወት ማትረፍ ከቻለ አይከስርም” የሚሉት ወይዘሮ ሰብለ በርግጥ አገልግሎቱን በነፃ መስጠቱ ዋጋ የሚያሰከፍል እንደሆነም ገልጸዋል።

“በገንዘብም ሆነ በህሊና ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል። ገንዘቡ ብቻ አይደለም። ሰዎቹ በጣም ተጎድተው የሚመጡ ስለሆኑ ለእነርሱ ምርመራ በሚደረግበት ወቅት ከባድ የሆነ ስሜት ሊሰማ ይችላል። ነገር ግን ይሄ ኃላፊነታችን በመሆኑ በደስታ ነው የምንሰራው” ብለዋል።

ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ሲሰጥ ይሄ የመጀመሪያው አይደለም። ማዕከሉ የሚገኘው በአራዳ ክፍለ ከተማ ውስጥ እንደመሆኑ በክፍለ ከተማው ውስጥ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ከዚህ ከማዕከሉ የተለየ ጥቅም እንዲያገኙ በማድረግ ይታወቃል። ይኸውም ለምርመራ ወደ ማዕከሉ የሚመጣ የክፍለ ከተማው ነዋሪ ከሚከፍለው ክፍያ ላይ የ20 በመቶ ቅናሽ እንዲደረግለት ተወስኗል። በተጨማሪም ለዚህ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች የአምቡላንስ አገልግሎት ያለ ምንም ክፍያ እንዲሰጥ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል።

ወደ ማዕከሉ የሚመጡት ተጎጂዎች አብዛኞቹ በትራፊክ አደጋ የተጎዱ እንደሆኑ የተገለፁ ሲሆን፣ እነዚህ ሰዎችም ያለምንም ክፍያ የሲቲ ስካን ምርመራ እንዲያደርጉ ይፈቀድላቸዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ህብረተሰቡ ስለትራፊክ አደጋ ግንዛቤ እንዲኖረው እና ከአደጋ ራሱን እንዲከላከል ከአራዳ ክፍለ ከተማ ትራፊክ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ትምህርት ይሰጣል። በአካባቢው የሚገኙ እና ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች የተገኙ ልጆች የትምህርት እድል እንዲያገኙ እና የሚያስፈልጋቸው ነገርም እንዲሟላላቸው በመስራት ላይ እንደሆነ አቶ ዳዊት ገልፀውልናል።

ማዕከሉ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከተነሳበት አላማ ጎን ለጎን ማህበረሰቡን ለማገልገል በርካታ ስራዎች እስከ አሁን የሰራ ሲሆን፤ በቀጣይም አገልግሎቱን በስፋት ለመስጠት አቅድ አለው። በአዲስ አበባ እና በክልሎች እስከ አሁን ድረስ ከ3ሺህ በላይ የሆኑ ሰዎች ህክምና አግኝተዋል። ህክምናው ከቀዶህክምና ጋር የተያያዘ በመሆኑ ዝግጅት እየተደረገበት መሆኑም ተገልጿል።

    ይህ ማዕከል በየዓመቱ ችግረኛ ህሙማንን በነፃ ለማከም የሚይዘው ኮታ አምስት መቶ ቢሆንም የሚመዘገበው እና የነፃ ምርመራ አገልግሎትን የሚፈልገው ሰው ቁጥር ግን ከፍተኛ ነው ብለዋል አቶ ዳዊት። “ባለፈው ዓመት 500 ያህል ሰዎች በነፃ ምርመራ ያደርጋሉ ብለን ነበር ያሰብነው። ነገር ግን 950 ሰው ነው የመጣው። እኛ የቻልነውን ሁሉ አድርገናል። ለአምስት ቀናት ምርመራውን ለመስጠት አስበን የነበረ ሲሆን፤ እስከ መስከረም 28 ቀን የፈጀ ዘመቻ ነበር ያደረግነው” ያሉት አቶ ዳዊት፤ ዘንድሮም እስከ አንድ ሺህ ሰዎች ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀውልናል። በመሆኑም ማእከሉ እስከ አንድ ሺህ ሰዎችን በነፃ ለመመርመር ዝግጁ ነው ብለዋል። ነገር ግን ነጻ ምርመራው የሚሰራው ከ ጳጉሜ አንድ እስከ አምስት ባለው ጊዜ ውስጥ ለተመዘገቡ ብቻ ነው ። ሆኖም ግን የሲቲ ስካን ምርመራ ዝም ብሎ የጤንነት ሁኔታን ለማየት ሳይሆን በሀኪም ትእዛዝ ብቻ የሚሰጥ ምርመራ በመሆኑ እና ምርመራው ጨረር አመንጪ በሆነ መሳሪያ የሚጠቀም በመሆኑ ሰዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም ተገልጿል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1571 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 597 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us