አማራጭ የቱሪዝም መስህቦች፤ በሰቆጣ

Wednesday, 03 September 2014 14:26

ከቅርቡ የሻዳይ በዓል በዋግምኽራ ዞን በሰቆጣ ከተማ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል። የዋግምኽምራ ዞን በአማራ ክልል ከሚገኙ አስር ዞኖች አንዱ ሲሆን፤ በተለይም የደርግ አገዛዝን ለመጣል የትጥቅ ትግል ከተካሄደባቸው እና ብዙ ውጣ ውረዶችን ካዩ ዞኖች አንዱ ነው።

ዞኑ ከመሰረተ ልማት አንጻር ወደ ኋላ የቀረ ቢሆንም በውስጡ ግን ከሰባት የማያንሱ የቱሪስት መስህብነት ያላቸው ቅርሶች አሉት። የሻዳይ በዓል አከባበርና እርሱን ተከትሎ የዋግምኽራ ልማት ማህበር (ዋልማ) ባዘጋጀው በዚህ ፕሮግራም ወቅት፤ ከዞኑን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘመኑ ታደሰ ጋር በዞኑ የቱሪዝም ሀብትና ቀጣይ ሁኔታ ላይ ተናግረናል።

ሰንደቅበዋግምኽራ ዞን ምን ያህል የቱሪስት መስህቦች አሉ?

አቶ ዘመኑበዞናችን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መስህቦች አሉ። በዋናነት መጥቀስ ከተፈለገ “የውቅር መስቀል ክርስቶስ ቤተ ክርስትያን” አንዱ ነው። ይህ ቤተክርስትያን ከአንድ አለት ተፈልፍሎ የታነፀ ህንፃ ነው። ረጅም እድሜ ያለውና በአፄ ካሌብ ዘመነ -መንግስት የተገነባ ነው። እንደውም ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያን ሁሉ በ500 ዓመታት ዕድሜ የላቀ ነው። በውስጡም የግሪክና የላቲን መስቀሎች አሉ። ሌላው “ነፍስ አድን ዋሻ የሚባለው ነው። ይህ ዋሻ ከትጥቅ ትግሉ ጋር የሚያያዝ ታሪክ ያለው ነው። በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከደርግ ጋር ኢህአዴግ ሲዋጋ በብዛት ትግሉ የተካሄደበት አካባቢ ነው። ከትግሉ ወቅት ይህቺ ከተማ (ሰቆጣ) ቢያንስ ለዘጠኝ ጊዜ ያህል በጦር ጀቶች ተደብድባለች። ይህ ድብደባ ሲፈፀም የአካባቢው ህዝብ “ነፍስ- አድን ዋሻ” ውስጥ ይሸሸግ ነበር። ለዛም ነው ነፍስ አደን ዋሻ የተባለው። ሌላው ደግሞ “ባል ኪዳነ ማሪያም” የምትሰኝ ገደማ አለች። ይህቺ ገዳም በ1870 አካባቢ የተገነባች ነው። በዚህች ገዳም ውስጥ የአፄ ምኒልክ ደብዳቤ፣ የአፄ ኃይለስላሴ ደብዳቤና የበርካታ ጳጳሳት ደብዳቤዎች ይገኛሉ። ገዳሟ ከሃይማኖታዊነቷ በተጨማሪ ከማዕከላዊ መንግስትም ጋር የጠበቀ ቁርኝት ነበራት።

ወደዝቋላ ከሄድን ደግሞ የሚወልድ ድንጋይ አለ። ይህ ድንጋይ ሳይንሱን ጠብቀህ እውነት ነው ማለት ሊከብድ ይችላል። ነገር ግን በዚህ ተራራማ ሥፍራ ድንጋዮች ይወልዳሉ የሚል አፈ ታሪክ አለ። የሚወልዱትም ዘመኑ መልካም ከሆነ ብቻ ነው። ይህም ዘመኑን የሚያመላክት ነው። ለምሳሌ በ77 እና 85 ዓ.ም ድርቅ ሲኖር ይሄ ድንጋይ አልወለደም። ይህ ተዓምር ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን በየዓመቱ ድንጋዩ ሲያረግዝና ሲወልድ ታየዋለህ። ሌላው የድንጋይ ሙሽሮች የሚባለው ቦታ ነው። በእኛ አካባቢ በዓል ሙሽራ አምስት ሰው ሆኖ ነው የሚሄደው። ይህም የድንጋይ ሙሽሮች አፈ-ታሪክ የተፈጠረው ሙሽሮቹ እየሄዱ ሳለ ዝናብ ይመጣል፤ ዝናቡ ሙሽሮቹን ሲያበሰብሳቸው ክፉ በመናገራቸው ፈጣሪ አድርቆ አስቀራቸው ነው የሚባለው። ለዛም ስታየው ትክክለኛ የሙሽሮች ምስል ነው የሚታየው። ይሄን በአካል ሄዶ በማየት ብቻ የሚደንቅ ነገር ነው። ሌላው የቱሪስት መስህባችን “የግራኝ አህመድ እመቤት” የምትባል ቤተ-ክርስትያን አለች። ይህቺ ቸርች ታሪኳ በጣም ሰፊ ነው፤ የሚባለው ምንድነው ግራኝ አህመድ ቤተክርስትያኖችን በሚያቃጥሉበት ወቅት ወደዚያ ቸርች (ቤተክርስትያን) ሲመጡ ግን አንድ ጊዜ ጎርፍ ዘጋባቸው። በሌላ ጊዜ ደግሞ የንብ መንጋ ያጋጥማቸዋል፤ በዚህ ምክንያት ወደዚያ ቸርች ባለመግባታቸው ቤተክርስቲያኗ “የግራኝ አህመድ እመቤት” ተባለች ማለት ነው። ከነዚህ ታሪካዊ ቅርፆች በተጨማሪ የተለያዩ የቤት እስረኞችዋ በዞናችን መስህብ ናቸው ማለት ይቻላል።

ሰንደቅእነዚህን የቱሪስት መስህቦች ከማስተዋወቅ አንፃር ብዙ የተሰራ ስራ የለም። የውጪዎቹ አይደሉም የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እንኳን እነዚህን ስፍራዎች አያውቋቸውም። ይህን ለማስተዋወቅ የናንተ ቢሮ ምን እየሰራ ነው?

አቶ ዘመኑቢሯችን ሙሉ በሙሉ ስራዎችን አልሰራም ብለን አናምንም። በተለያዩ አጋጣሚዎች የተለያዩ መፅሔቶችን እያዘጋጀን እንበትናለን፤ በሚዲያዎችም ለማስተዋወቅ ሞክረናል። እርሱ ብቻ አይደለም ቱሪዝም ለሚመለከታቸው ኤጀንሲዎችም ያሳወቅንባቸው ሁኔታዎች አሉ። ነገር ግን አሁንም ቢሆን መስራት የሚገባንን ያህል ሰርተናል ማለት አያስደፍርም። አንደኛ ኢኮኖሚካል ችግር ሲሆን፤ ሁለተኛ ደግሞ የመሰረተ ልማት አለመሟላቶች ናቸው። ሌላውና ዋነኛው መገናኛ ብዙሃንን በሚገባ መጠቀም አለመቻላችን ነው።  

ከዘንድሮው የሻደይ በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ በርካታ ጋዜጠኞች እዚህ ተገኝተዋል ብዙዎቹ የመጎብኘት አጋጣሚውን ስላገኙ በሚዲያቸው ያስተዋውቁልናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በቀጣይም የምንሰራው ስራ ይኖራል።

ሰንደቅየዞኑ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ በ2006 ዓ.ም ስራው ምን ያህል ጎብኚዎችን አስተናገደ?

አቶ ዘመኑበርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ ቱሪስቶች ወደዞኑ መጥተዋል። ቢያንስ ወደ 5000 የሚጠጉ የውጪ ቱሪስቶች በዚህ ዓመት ብቻ ጎብኝተውናል። በተለይ የኛ አካባቢ ከአክሱምና ከላሊበላ መካከል በመገኘቱ ቱሪስቶች ሊመጡ ችለዋል። ከላሊበላ ያለው ርቀት 125 ኪሎ ሜትር ሲሆን፤ ከአክሱም ደግሞ 230 ኪሎ ሜትር ነው ርቀታቸው። ከዚህ በዘለለ ግን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ 160 ሺህ አካባቢ የሚጠጋ ነው። ይህም ከዓመት ወደአመት እየተሻሻለ የመጣ የጎብኚዎች ቁጥር ነው።

ሰንደቅቀላል የማይባል የጎብኚዎች ፍሰት ካለ ከሆቴለች ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

አቶዘመኑእንዳየኸው አካባቢችን በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮም የተጎዳ ነው። ያም በመሆኑ የአካባቢያችን ባለሀብቶች የኢኮኖሚ አቅም የጎለበተ ባለመሆኑ ባለኮከብ ሆቴሎች አሉ ብለን አንናገርም። ነገር ግን ይብዛም ይነስም ከከተማችን አቅም አንፃር የተጀመሩ ሆቴሎች አሉ። እነዚህ ሆቴሎችም ንፅህናቸውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል አብረን እየሰራንበት ነው። በዚህም ቢሯችን በወረዳም ሆነ በዞን ደረጃ ክትትል ያደርጋል። ጥሩ የሰሩትን እናበረታታለን፤ መስተካከል ያለባቸውንም በመደገፍ እንዲሻሻሉ እየሰራን እንገኛለን።

ሰንደቅዞናችሁ ከ2000 ዓ.ም ወዲህ የሻደይ በዓል በድምቀት እያከበራችሁ ነው። ይህን በዓል ከቱሪስት መስህብነት አንጻር ምን ያህል እየተጠቀማችሁበት ነው?

አቶ ዘመኑሻዳይ በዞናችን ተወዳጅ እና ብዙዎች አመቱ መቼ በደረሰ ብለው የሚጠብቁት በዓል ነው። በዓሉ ህዝባዊ በዓል ነው። ነገር ግን ከ1999 ጀምሮ ዓለም በኋላ እንደመንግስት ቁጭብለን ይሄን በዓል ማሳደግ አለብን ብለን ከህዝቡ ጋር በትኩረት እየሰራን ነው። ይህም ብቻ አይደለም እስካሁን ድረስ በዓሉ ሃይማኖታዊ በዓል ነበር፤ አሁን ግን ከዚያም አልፎ ለአካባቢያችን ገንዘብ ማስገኛ እንዲሆን እየሰራን ነው። ለምሳሌ አምና “መረጃ ለልማት” በሚል የማህበረሰብ ሬዲዮ ቁሳቁሶችን ለማሟላት የገቢ ማሰባሰቢያ አድርገናል። በዚህ ዓመትም “ሻዳይ 2006 ህብረት ለዋግ ልማት” በሚል መሪ ቃል ገንዘብ የማሰባሰብ ስራን እየሰራን ነው። በዚህ አጋጣሚ በዓሉን አጠንክረን በመያዝ ከሀገር ውጪም ከሀገር ውስጥም የሚመጡ ጎብኚዎችን መያዝ የምንችልበት ሁኔታ እንዳለ እናምናለን። ይሄ ነገር ተጠናክሮ በየዓመቱ የሚቀጥል ይሆናል።

ሰንደቅእንደሚታወቀው የሻደይ በዓል አከባበር የሴቶች ማዕከላዊነትን የተላበሰ ነው። በርካታ ወጣት ሴቶችም በበዓሉ አከባበር ላይ ሲሳተፉ አይተናል። ነገር ግን በተለይ በሰቆጣ ከተማ ውስጥ በምሽት በነበረኝ ምልከታችን በርካታ ወጣት ሴቶች ራሳቸውን ለወሲብ ንግድ አቅርበው አይተናል። ምናልባትም ሻደይን ተከትሎ “ሴክስ ቱሪዝም” ከተማችሁን አያሳስባትም?

አቶ ዘመኑበአሁኑ ወቀት ምናልባት እነዚህ ወጣት ሴቶች ከጥገኝነት ለመውጣት ሲሉ አድርገውት ሊሆን ይችላል። የምትለው ነገር በፍፁም የለም ለማለት አልችልም። የተለያዩ ሴቶች ካለባቸው ችግር አኳያ ወደዚህ ተግባር ሊገቡ ይችላሉ። ነገር ግን ይህን ለመቅረፍ የሚችልበት ብዙ መንገድ አለ፤ አንደኛው ለምሳሌ የሻደይ በዓል በራሱ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚ ወጣቶቹ በስራ ተሰማርተው ተጠቃሚ የሚሆንበትን ነገር ማመቻቸት ነው። ሁለተኛው መንግስት የቀረፃቸው ፖሊስና ስትራቴጂዎች አሉ፤ ከጥቃቅንና አነስተኛ ጋር ተያይዞ በዚያ በመሳተፍ ከዚህ የድህነት ህይወት እንዲወጡ መስራት ይገባል የሚል እምነት አለኝ።

ሰንደቅበዘንድሮ የሻደይ በዓል ላይ ክቡር ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ የኢፊዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ እና ሌሎች ባለስልጣናትም ተገኝተዋል። የዞኑን የቱሪዝም ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከፌዴራል መንግስት የምትጠብቁት ድጋፍ ምንድነው?

አቶ ዘመኑየፌዴራሉና የክልል መንግስት ዞኑን ማገዝ ያለባቸው። አንደኛ የአካባቢውን ህብረተሰብ የትምህርት ደረጃ ማሻሻል ነው። በተለይም ከቱሪዝም ጋር ተያይዞ ያለውን አስተሳሰብ ለማዳበር የሚረዱ ስራዎች በጋራ መሰራት አለባቸው። ከዛ በዘለለ ግን በዞናችን ውስጥ ያሉ የቱሪስት መስህቦችን በመጠበቅ ረገድ ድጋፍ ሊደረግ ይገባል። አንዳንዶቹ ቅርሶቻችን እድሜያቸው የገፋ ከመሆኑ አንጻር ጥገና የሚያስፈልጋቸው ናቸው። ይህ የግንባታ ወጪ በዞንና በወረዳ አቅም የሚፈታ አይደለም። በዚህ ላይ የተሻለ ድጋፍ ቢደረግልን አካባቢችንን ለቱሪስት ገቢ መደገፍ እንችላለን የሚል እምነት አለን።   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1407 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 928 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us