ማህበራዊ ተጠያቂነታችን ምን ያህል ነው

Wednesday, 03 September 2014 14:29

          

የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ዓላማውን አድርጎ የተነሳው ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎት ለመስጠት እና ለማግኘት በማህበረሰብ፣ በቡድኖች እና በመንግስት መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከርን ነው። ይህ ፕሮግራም በትምህርት፣ በጤና፣ በውሃ እና ፍሳሽ እንዲሁም በግብርና እና የገጠር መንገድ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሁሉም ዜጋ በተጠያቂነት አገልግሎት እንዲሰጥ እና እንዲቀበል የማድረግ አላማን ይዞ ነበር እ.ኤ.አ በ2011 ወደ ስራ የገባው። ከዚህ ጎን ለጎንም መንግስት እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች የህዝብን ሀብት በአግባቡ እና ግልፅ በሆነ መንገድ መጠቀም እንዲችሉ ተጠያቂነት እንዲሰፍን የማህበረሰቡ ተሳትፎ እንዲኖር የማድረግ አላማ አለው።

ማህበራዊ ተጠያቂነት ተራው ዜጋ የህዝብ አገልግሎቶችን ለማግኘት ድምጻቸውን የሚያሰሙበት፣ ከፖሊሲ አውጪዎች እና አገልግሎት ሰጪዎች ጋር በጠንካራ እና በደካማ ጎኖች ላይ ውይይት በማድረግ አገልግሎት ሰጪዎች ተጠያቂ የሚሆኑበት መንገድ መፍጠርን ያስችላል ተብሏል።

ይህ ፕሮግራም የእንቅስቃሴውን ውጤት ለማየትም በየአካባቢው እየተሰሩ ያሉትን ስራዎች በማቅረብ አሸናፊዎችን የመለየት ስራ ተሰርቷል። በዚህም መሰረት የዚህን ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም በሚካሄድበት በአፋር፣ በኦሮሚያ እንዲሁም የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ሁለት ወረዳዎች ሪዲም ጀነሬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መላኩ ስብሀቱ ተሸላሚ ሆነዋል። ይህም ውጤት የተገኘው በኦሮሚያ ክልል መተሀራ ከተማ ላይ በተደረገ አሳታፊ የቪዲዮ ፕሮግራም ነው።

አቶ መላኩ እንደገለፁት ይህ አሳታፊ የቪዲዮ ፕሮግራም ከስድስት እስከ ሰባት ወራትን የፈጀ ነበር። በመጀመሪያ ባለሞያዎች ስለ አሳታፊ ቪዲዮ ፕሮግራም ምንነት እና አሰራር ስልጠና ተሰጥቷል። አንዱ የአሸናፊነት መስፈርት የነበረውና ይህ ቡድን ያሸነፈበትም ማህበራዊ ተጠያቂነት ምን ያህል ወደ ማህበረሰቡ ሰርፆ ገብቷል የሚለው ነበር። በዚህም አገልግሎት ተቀባዩ ማህበረሰብ ይህን አገልግሎት ለማግኘት ያለውን የመጠየቅ አቅም እንዴት ማሳደግ ይቻላል? የሚሉት ጉዳዮች ላይ በስፋት መስራታቸውን ገልፀውልናል።

በመተሀራ ከተማ የተሰራው ስራ በጤናው ዘርፍ ላይ በመሆኑ በዚሁ ዘርፍ በተሰራ ስራ ነው አሸናፊ መሆን የተቻለው። በዚህ አጋጣሚም ዳይሬክተሩ እንደገለፁት ህብረተሰቡ ውስጥ የጠያቂነት ፍላጎት እንዳለ ተገልጿል። «ይሄ አሳታፊ የቪዲዮ ፕሮግራም ደግሞ ለህዝቡ የበለጠ የጠያቂነት አቅም ፈጥሮለታል፤ መንገዱንም አሳይቷል። እኛም ያንን አቅም በስልጠናዎች በማዳበር አውጥተን አሳይተናል” ብለዋል አቶ መላኩ። በዚህም መሰረት ህብረተሰቡ በተለይ በግልጽነት እርስ በራሱ በመወያየት ለችግሮች መፍትሄ ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በስፋት መስራት ችለዋል።

በዚህ በመተሃራ በተደረገው የአሳታፊ የቪዲዮ ፕሮግራም ተጠቃሚ ከሆኑት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከልም አንዷ ልምዳቸውን እንዲካፍሉን አነጋግረናቸው ነበር።

ወይዘሮ ፌሩዝ መሀመድ ይባላሉ። የመጡት ከመተሀራ ከተማ ሲሆን፤ በአካባቢያቸው ያለውን ማህበራዊ ተጠያቂነትን በማስፋፋት እና መልሶ በማልማት ሞዴል ናቸው። ወይዘሮ ፌሩዝ የከተማዋን ሴቶች ወክለው ወደ አዲስ አበባ እንደመጡ ገልፀውልናል። የእነ ፌራዝ ቡድን በተለይ በጤናው ዘርፍ ባመጡት ተጨባጭ ለውጥ ለዚህ ሽልማት በቅቷል።

ይህ ፕሮጀክት ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በከተማዋ በርካታ ችግሮች እንደነበሩ የገለፁት ወይዘሮ ፌሩዝ ይህን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት አድርገው ውጤታማ መሆናቸውን ይገልፃሉ። “ከተማችን ከዚህ በፊት ጤና ጣቢያ አልነበራትም። አንድ ጤና ጣቢያ ቢኖራት እርሱም በተፈጥሮ ውሃ ተበላ። በዚህም ሳቢያ ህክምናው ይሰጥ የነበረው በግለሰብ ቤት ውስጥ ነበር። ይህም ሆኖ ጤና ጣቢያው በቂ ነገሮች የተሟሉለት ባለመሆኑ መድሃኒት በአግባቡ ለተጠቃሚ አይደርስም ነበር” የሚሉት ወይዘሮ ፌሩዝ፣ ከዚህ ውጪም በዚያ በግለሰብ ቤት ውስጥ መድሃኒቶች በእርጥበት እና በሙቀት እንደሚበላሹ እና በአይጥ ጭምር ይበሉ እንደነበር ገልጸዋል።

ጤና ጣቢያው ፈራርሶ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው በግለሰብ ቤት ውስጥ በመሆኑ ሰራተኞች እንደልባቸው ስራቸውን ማከናወን አለመቻላቸውንም ወይዘሮ ፌሩዝ ገልፀውልናል። ከዚህ በተጨማሪም እንኳን ለታካሚዎች ቀርቶ ለማንም የማያመች መፀዳጃ ቤት ይጠቀሙ ነበር። ታዲያ እነዚህን ችግር መቅረፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለእነዚህ ሴቶች ስልጠናውን በመስጠት ማህበራዊ ተጠያቂነትን እያንዳንዱ ሰው እንዴት አድርጎ ወደ ራሱ መውሰድ እንደሚችል የማስገንዘብ ስራ ተሰርቷል።

ሴቶቹ ስልጠናውን እንዳገኙም ቀጥታ ወደ ተግባር የገቡ ሲሆን፤ በመጀመሪያ ያደረጉትም በጅምር ላይ የነበረው ጤና ጣቢያ ተጠናቆ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ነበር። እናም ሆስፒታሉን ለመጨረስ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት በተጠያቂነት መንፈስ ወደስራው እንዲገቡ እና ሆስፒታሉ እንዲጠናቀቅ ተደርጓል። በመሆኑም ቀድሞ በግለሰብ ቤት ውስጥ ይሰጥ የነበረው የህክምና አገልግሎት በአዲሱ ጤና ጣቢያ ውስጥ እንዲሰጥ ተደርጓል።

ወይዘሮ ፌሩዝ እና ሌሎች የቡድኑ አባላት የተጀመሩ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎች እንዲጠናቀቁ ከማድረግ በተጨማሪም በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ መሻሻል እንዲመጣ እና ሰራተኞችም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የማድረግ ስልጠናም ወስደዋል። በዚህ ስልጠና ተጠቅመውም ሰራተኞች ተጠቃሚው የተቀላጠፈ እና ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ስራ መስራት ነበረባቸው። “እኛ ማህበራዊ ተጠያቂ ሆነን የተመረጥን በመሆናችን ፊት ለፊት በግልጽ ነው እየተነጋገርን የምንሄደው። ስለዚህ ሰራተኞች መልካም ባህሪይ እንዲኖራቸው መነጋገር ጀመርን። ይሄንን ስናደርግም ነጥቦችን ለይተን እዚህ ጋር ጥሩ ሰርታችኋል፣ እዚህ ጋር ያለው ደግሞ ይስተካከል በማለት በግልፅ ድክመቶች እንዲሻሻሉ አድርገናል” ይላሉ ወይዘሮ ፌሩዝ። እንደ ወይዘሮ ፌሩዝ ገለፃ ትልቁ እና ዋናው ነገር እነዚህ ስልጠናውን የወሰዱት እና ማህበራዊ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች በግልፅ ከአገልግሎት ሰጪዎች ጋር በመወያየት ለህብረተሰቡ ተገቢ አገሎግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ነው።

የመተሀራ ከተማ ትልቅ ችግር ነበር የተባለው የአምቡላንስ ችግር ነው። በከተማዋ የአምቡላንስ አገልግሎት ባለመኖሩ በምጥ የተያዙ እናት እንዲሁም ህፃናት ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጡ እንደነበረ ወይዘሮ ፌሩዝም ገልፀዋል። በርካታ እናቶች ህክምና ፍለጋ ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ በሚያደርጉት እንግልት ብዙ ደም ይፈሳቸው እንደነበር እና ህይወትም ያልፍ እንደነበር ገልፀውልናል። ሆኖም ሴቶቹ ማህበራዊ ተጠያቂነትን በተመለከተ ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ባደረጉት ግፊት አማካይነት ከተማዋ የአምቡላንስ አገልግሎት እንድታገኝ ተደርጓል። “በፊት በርካታ እናቶች በአምቡላንስ እጥረት ምክንያት ደም ይፈሳቸው እና ሕይወታቸውን ያጡ ነበር። ነገር ግን ይሄ ማህበራዊ ተጠያቂነት ከመጣ በኋላ ከዛሬ አራት ወራት በፊት በአንድ ሚሊዮን አራት መቶ ሺህ ብር አምቡላንስ ተገዝቶ በማገልገል ላይ ይገኛል” ብለዋል ወይዘሮ ፌሩዝ።

ከዚህም በተጨማሪ በከተማዋ የተገነባው ጤና ጣቢያ ያሉት የመኝታ ክፍሎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ እናቶች በቂ ጊዜ በጤና ጣቢያው ማሳለፍ አይችሉ እንደነረም መረጃዎች ያመለክታሉ። «እናቶች ወልደው እዚያው ብዙ መቆየት አይችሉም። ሌላ ሴት ስትመጣ በደንብ ሳያገግሙ ክፍሎቹን ለቀው ለመውጣት ይገደዳሉ። በዚህም አስፈላጊውን ህክምና ሳያገኙ የሚቀሩ ነበሩ። ነገር ግን እኛ ማህበራዊ ተጠያቂዎች ግፊት በማድረጋችን ከከተማው መስተዳድር አምስት መቶ ሺህ ብር ተመድቦልን ተጨማሪ ክፍሎች ሊሰሩልን በእንቅስቃሴ ላይ ነው” ብለውናል ወይዘሮ ፌሩዝ።

እነ ወይዘሮ ፌሩዝ ከጤናው ዘርፍ በተጨማሪም አንዳንድ ባህላዊ አሰራሮች በተሻለ መንገድ ለመተግበር የሚያግዙ ስራዎችን ሰርተዋል። በተለይ በእድር አሰራር ላይ ያለውን አስተሳሰብ ወደ ተሻለ መንገድ ለመተግበር እየሰሩ ይገኛሉ። “እድሮች በፊት ጡሩንባ የሚነፉት ሰው ሲሞት ብቻ ነበር። ነገር ግን አሁን ሁሉም ቡድኖች የየራሳቸውን አባላት በማስተባበር በየሳምንቱ በጡሩንባ የፅዳት ዘመቻ ያደርጋሉ” ብለውናል። ከእነዚህ ማህበራዊ ተጠያቂዎች የወጣቶች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የሴቶች፣ የአዛውንቶች እና ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያሉ ሰዎችን ቡድን ያካተተ ነው። ከአዛውንቶች ቡድን አብዛኛዎቹ የእድር ተጠሪዎች በመሆናቸው የዚህን የዘመቻ እንቅስቃሴ በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይም ተግባራዊ ለማድረግ ሰፊ እቅድ እንዳለ ተገልጿል።

ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በየቢሮው እየሄዱ ከመንግስት አካላት ጋር በመነጋገር ለችግሮች ባለቤት በማድረግ መፍትሄ እንዲያፈላልጉ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ማህበረሰቡ ይህን ማህበራዊ ተጠያቂነት ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሆነ ተገልጿል።

ማህበራዊ ተጠያቂነት በግለሰብ ደረጃም ሆነ በማህበረሰብ ደረጃ ያለው ጠቀሜታ ከምንም በላይ እንደሆነም ወይዘሮ ፌሩዝ ከራሳቸው ተሞክሮ ተነስተው ይናገራሉ። “ስልጠናውን የሰጠን እና ኮሚቴውን ያቋቋመው ሪደም ጀነሬሽን ነው። እኔ በዚህ እንቅስቃሴ ያገኘሁት ትልቅ ነገር ግልፅነት ነው። አንድን ሰው ቤቴ ቁጭ ብዬ ቡና እየጠጣሁ ከማማው ችግሩን ብነግረው ያ ሰው ራሱን ቆም ብሎ ያያል፤ መፍትሄም ይገኛል። ብቻዬን ብከስል ግን ራሴን ነው እየጎዳሁ ያለሁት። ሰው ሊያጠፋ አይደለም የሚሰራው። እሰራለሁ ብሎ ነው ሰው የሚሳሳተው። የጤና ጣቢያውን ሰናይ አገልግሎት የሚሰጡት ሰዎች ሊደክማቸው ይችላል። ሰልችቷቸውም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እዚህ ጋር እኮ እንዲህ ተሳስተሻል ብለን በግልፅ ስንነግራት ቆም ብላ ራሷን የምታይበት ጊዜ አለ” የሚለት ወይዘሮ ፌሩዝ፣ የእነሱ ተግባርም በዚህ ቅኝት የተነሳ መሆኑን ገልጸውልናል።

ለአብነት ያህልም ከተማዋ አምቡላንስ ይኑራት አይኑራት የከተማው መስተዳድሩ መረጃ ላይኖረው ይችላል ያሉት ወይዘሮ ፌሩዝ፣ እነሱ ችግሩን ወደ ከተማው መስተዳድር በማቅረባቸው መፍትሄ እንዳገኙት ሁሉ ማንኛውም ችግር በመነጋገር እና እርስ በእርስ በመረዳዳት መፍትሔ እንደሚገኝለት ገልጸዋል።

      ታዲያ እነወይዘሮ ፌሩዝ በማህበረሰቡ ውስጥ ማህበራዊ ተጠያቂነት እንዲሰፍን በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጉዟቸው አልጋ በአልጋ አልነበረም። ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈው ነው ለዚህ ደረጃ የበቁት። መጀመሪያ ላይ ችግሩን ከማውራት በዘለለ መፍትሄ አይገኝለትም የሚል ስጋት ነበር። ብዙ ጊዜ ችግር መኖሩን ከማውራት ውጭ መፍትሄ አለመገኘቱን የገለፁት ወይዘሮ ፌሩዝ አያይዘውም ያለውን ስጋት ይገልፃሉ። “ያለውን ችግር ብናገር ነገ ሌላ ችግር ይዞብኝ ይመጣል ተብሎ ይፈራ ነበር። ነገ ጤና ጣቢያ ልታከም ሄጄ ያልሆነ መርፌ ብትወጋኝስ፣ የከተማው መስተዳደር ቢያስረኝስ የሚሉ ፍርሃቶች ነበሩ። አንድን ጉዳይ አንስተን እንዲህ ልናደርግ አስበን ነበር እኮ ስንላቸው ደግሞ ሰው ያጥላላብን ነበር። ሁላችንም የምንሰራው ያለምንም ክፍያ በበጎ ፈቃደኝነት ነበር። ማህበረሰቡን ለማሳመን ጥረት እናደርጋለን። የሰው ፊት ገርፎን፣ ፀሐይና ዝናብ ተፈራርቆብን ነበር ይሄንን ስራ ስንሰራ የነበረው” የሚሉት ወይዘሮ ፌሩዝ ይሄንን ሁሉ ውጣ ውረድ አልፈው ለዚህ ደረጃ መብቃታቸውንም ገልጸውልናል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1343 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1061 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us