Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 382

“እናቴ ልጆች እንዲማሩ የነበራት ፍላጎት ትልቅ ስንቅ ሆነኛል ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ፤ የፍሬሽ ኤንድ ግሪን አካዳሚ መስራችና ስራ አስኪያጅ

Saturday, 12 October 2013 15:18

“ለህፃናት ምቹ የትምህርት አጋጣሚን መፍጠር ያስፈልጋል” የሚል ፅኑ እምነት ያላት ምግባረሰናይ ሰው ናት፤ የዛሬዋ የህይወት አምድ እንግዳችን ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ። ከአመታት በፊት የኮሌጅ ትምህርቷን አጠናቃ ስትመረቅ መተዳደሪያዋ እንዲሆን በተከራየችው ግቢ ውስጥ ህፃናትን በክፍያ በማስተማር ስለመጀመሯ የምትናገረው እንግዳችን፣ ዳሩ ግን በርካታ ህጻናት በመማሪያና ወደትምህርት ቤት መሄጃ ዕድሜያቸው ከወላጆቻቸው ጋር በጎዳና ላይ ሲንከራተቱ ማየቷ የንግድ ሃሳቧን ሊያስለውጣት የሚያስችል አጋጣሚ ስለመፍጠሩ ታስታውሳለች።

“ዋናው መነሻ አንድ እናት መንገድ ዳር ስትለምን ልጇንም ይዛ ነው። ታዲያ ይህን ሳይ እነርሱ ቢለምኑም ነገር ግን ልጆቻቸውን ለምን ወደትምህርት ቤት እንደማይልኩ ስጠይቅ የማገኘው መልስ ተመሳሳይ ነው፤ የትኛው ትምህርት ቤት ነው ልጄን በነፃ የሚያስተምርልኝ የሚል ነው።” የምትለው ወይዘሮ ሙዳይ ይህ የበርካታ ችግረኛ ወላጆች እሮሮ የወ/ሮ ሙዳይን ለትርፍ የተቋቋመ ትምህርት ቤት ወደበጎ አድራጎት የትምህርት መስጫ እንደለወጠው ተናግራለች።

ለህፃናት የነገ ህይወት ተስፋን ስለማስጨበጥ እሰራለሁ የምትለው ወ/ሮ ሙዳይ፤ በ1992 ዓ.ም የተመሰረተውን “ፍሬሽ ኤንድ ግሪን” አካዳሚ ከትርፋማ ድርጅትነት ወደ ምግባረ ሰናይ ተቋም ስትለውጠው ፈታኝ አጋጣሚዎች እንደነበሯት ታስታውሳለች። አንደኛውና የመጀመሪያው ፈተና ከፍለው ልጆቻቸውን ማስተማር የሚችሉ ወላጆች ሃሳቧን ሊረዱና ሊደግፏት አለመቻላቸው ነው። “ከጎዳና ተዳዳሪዎቹና ከችግረኛ ወላጆች ያመጣኋቸውን ህፃናት ሙሉ የትምህርት ወጪና አስፈላጊውን ነገር ሁሉ አሟልቼ ነበር እንዲማሩ የምረዳቸው። ይህም በመሆኑ የችግረኞቹ ልጆች የትምህርት ቤታችንን ዩኒፎርም ለብሰው ከትምህርት ቤት ከወጡ በኋላ ከወላጆቻቸው ጋር በጎዳና ላይ ሲታዩ ሌሎቹ ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸው ጎዳና ላይ ከሚውሉ ልጆች ጋር እንደሚማሩ ሲያውቁ አካሄዴን ሊደግፉት አልቻሉም። ወይ ልጆቹን መርዳት እንድተው ወይ ደግሞ እነርሱ ትምህርት ቤቱን ለቀው ሌላ ቦታ እንደሚሄዱ ነበር ያስጠነቀቁኝ” ትላለች። ምንም እንኳን የመጨረሻ ምርጫዋ ዋጋ እንደሚያስከፍል ብታውቅም፤ ህፃናቱንና የህፃናቱን ችግረኛ ወላጆች ለመርዳት ትወስናለች።

በህይወት ውስጥ ራስን በመልካም ነገር ለሌሎች መግለጥ የራሱ የሆነ የመንፈስ እርካታ እንዳለው አምናለሁ የምትለው ወ/ሮ ሙዳይ፤ ህፃናቱን በትምህርት ገበታቸው አቆይታ ለማስተማር የግቢው ኪራይ፣ የመምህራኖቹ ደሞዝ እና ለተማሪዎቹ መዘጋጀት ያለባቸው የቁርስና የምሳ አቅርቦትን ለማሟላት ከአቅሟ በላይ የሆነባት ጊዜ መጣ። ይህም ሆኖ ወደምታውቃቸውና ወደሚያውቋት ሰዎች ጋር ሁሉ በመዞር ያሰበችውን በማስረዳት ድጋፍ እንዲያደርጉላት ስትጠይቅ ብዙዎቹ አላሳፈሯትም ነበር። “የምረዳቸው ህጻናት እንዳሉና የእነርሱንም የትምህርት ወጪና አስፈላጊ ነገሮች ለማሟላት የሚያስፈልገኝን ነገር ጠቃቅሼ ቢያንስ በአንድ ልጅ የ40 ብር ክፍያን እንዲያግዙኝ ስጠይቃቸው አንዳንዶቹ ሁለትም ሶስትም እስከ አምስት ተማሪዎች እንወስድልሻለን ብለው ቃል ገቡልኝ። ይህም ብቻ አይደለም አንድ ወዳጄ ኑሮዋ አሜሪካ ነው። ለተማሪዎቹ ምሳ የሚሆን ወጪን እኔ እችልልሻለሁ አለችኝ። ይህ ሲሆን በዚሁ በግቢያችን ውስጥ ለተማሪዎቹ ምግብ የሚዘጋጅበትን ሁኔታ በማመቻቸት ስራ አጥተውና ተቸግረው የተቀመጡትን የተማሪዎቹን ወላጆች በምግብ ስራ በማሰማራት ለራሳቸውም የስራ እድል እንዲያገኙ አመቻችተናል” ስትል ትገልጻለች።

ሲጀምር ሃያ ሁለት ወላጆች ለልጆቹ ምግብ በማብሰል ስራ ሲተባበሯት እራሷ ደግሞ ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ በግቢው ውስጥ የፈለጉትን እንዲሰሩና የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ እንደተመቻቸላቸው የምትገልፀው ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ፤ በአሁኑ ወቅት እነዚህ የተማሪዎቹ ወላጆች የጥጥ ምርትን በተለያዩ ቅርፆች በማዘጋጀት ግቢውን ሊጎበኙ ለመጡ እንግዶች በመሸጥ ራሳቸውን የሚደጉሙበትን አማራጭ እየሰሩበት ይገኛሉ።

 

የ“ሙዳይ አሶሴሽን” በአሁኑ ወቅት ከ150 በላይ ህፃናትን ከመዋለ ህፃናት እስከ ስድስተኛ ክፍል በማስተማር ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ከ65 ላላነሱ ችግረኛ ወላጆችም የስራ ዕድልን ፈጥሮ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። ወይዘሮ ሙዳይም ከተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ግለሰቦች ከምታገኛቸው የሚጠረቃቀሙ የወጪ መሸፈኛ ገንዘቦች በተጨማሪ በግሏ “ጆ-ኬሽ” የተሰኘ የኮምፒዩተር ጨዋታን በአለም ከሚገኙ ተወዳዳሪዎች ጋር በመጫወት የምታገኘውን ሽልማትም ለትምህርት ቤቱ ትገለገልበታለች። ይህም ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ የዚህን “ጌም” የሚጫወት ሰው ት/ቤቱን እንዲጎበኝ በመቀስቀስ የስፖንሰር ድጋፍ እንዲሰጥ ማስቻል ሌላኛው የገቢ ምንጯ እንደሆነ ትናገራለች።

ከ13 ዓመታት በፊት “ፍሬሽ ኤንድ ግሪን አካዳሚ” ሲመሰረት ለትርፍ ቢሆንም ከአመታት በኋላ ግን ሙሉ በሙሉ ወደበጎ አድራጎት ስራ ተለውጦ በማገልገል ላይ ቆይቷል። ያም ሆኖ በበጎ አድራጎት ድርጅትነት ከመንግስት ፍቃድ ካገኘ ገና አንድ አመቱ ነው። ከዚያ በፊት ለመንግስት ያልተቋረጠ ግብርም ትከፍል እንደነበር የማህበሩ መስራችና ስራ አስኪያጅ የሆነችው ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ ትገልፃለች።

“ጎበዝ ተበዳሪ ነኝ” የምትለው ወ/ሮ ሙዳይ፤ የትምህርት ቤቱን የኪራይ ወጪ፣ የመምህራን ደሞዝ፣ የዩኒፎርምና የምግብ አቅርቦቱን ሁሉ በግሏለ ለማሟላት ከአመት አመት እየተፍጨረጨረች ስለመሆኑ ታስረዳለች።

ኑሮዋ ያን ያህልም የተቀናጣ ሳይሆን በእናቷ እጅ ያደገችው ሙዳይ ግን አንዳችም ነገር ሳይጎድልባት ያለችግር የኖረች ናት። ይህም በልጅነት ዕድሜዋ ከእናቷ የወሰደችው መልካምነት ለዛሬ ዘመን ትጋቷ እንደእርሾ ሳይሆናት እንደማይቀር ትናገራለች። “እናቴ ልጆች ትምህርት ቤት እንዲሄዱ በጣም ትሟገት ነበር። አንዳንዶቹንም የመማሪያ እየከፈለች ሁሉ ታስተምራቸው ነበር። ይህ ለኔ ትልቅ ስንቅ የሆነኝ ይመስለኛል” ባይ ናት።

ስለህጻናት ሁሌም አስባለሁ የምትለው ወ/ሮ ሙዳይ እናቷ ያሳደሩባት ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ አድጋ ትምህርቷን ስታጠናቅቅም ዲፕሎማዋን ያገኘችው በህፃናት እንክብካቤ ዙሪያ እንደነበር ትናገራለች። ቀጥላም ዲግሪዋን በቢዝነስ ማኔጅመንት ያገኘችው ወ/ሮ ሙዳይ፤ ለወደፊቱም የምታስተምራቸው ህፃናት የተሻለ ቦታ ደርሰው ማየት ትልቁ ህልሟ መሆኑን ታስረዳለች።

“የራሴ የምለው ቤተሰብ አለኝ። ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ነኝ” የምትለው ወ/ሮ ሙዳይ፤ ከቤተሰቦቿ ጋር በምታስተምርበት ግቢ ውስጥ ካለች አንዲት ቤት ውስጥ በመኖር ላይ ትገኛለች። “ባለቤቴ ሃሳቤን ተረድቶኝ እሺ ብሎ የሚደግፈኝ በመሆኑ በጣም አመሰግነዋለሁ” የምትለው ሙዳይ፤ የራሷን ሁለት ልጆች ጨምሮ በጉዲፈቻነት የምታሳድጋቸው 12 ህፃናት አብረዋት ቢኖሩም አንድ ቀን ግን ችግር ቢገጥማትና እርሷ አንድ ነገር ብትሆን ትምህርት ቤቱ የመዘጋት አደጋ ሊደርስበት ይችል ይሆናል የሚል ስጋት እንዳላት ትገልጻለች። የሚረዷት ሰዎችና የመንግስት አካላት ብታገኝ እንዲሁም በኪራይ የምትኖርበትን ጊቢ የሚተካላት ነፃ ቦታ ቢገኝ ወጪውን ከመቀነሱም ባሻገር ሌሎች መረዳት ያለባቸውን ህፃናት ከማስገባቱም በላይ ትምህርት ቤቱን ከ6ኛ ክፍል በላይ አድርጎ የመስራት ፍላጎት እንዳላት አስታውቃለች።

Last modified on Saturday, 12 October 2013 15:25
ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1522 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 689 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us