የዓውደ ዓመት ገበያ

Wednesday, 10 September 2014 10:57

የክረምት ወራትን አገባደን እነሆ ለቀጣዩ ዓመት የመጀመሪያችን የሆነውን የመስከረም ወር ልንቀበል ነው። አንዱ ዓመት ከሌላው ዓመት የሚለዩት የራሱ የሆኑ ነገሮች ቢኖሩትም፤ ከዓመት ዓመት ሂደታቸው የማይቋረጥ አንዳንድ ነገሮች ግን እንደተጠበቁ ናቸው። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የሚመጡት የአውዳዓመት አከባበር ባህላችን፣ ልጆች የሚያስፈልጋቸው ነገር አሟልቶ ወደ ትምህርት ቤት መላክ እንዲሁም ከትምህርት ዓለም ወጥቶ የስራውን ዓለም መቀላቀል ሂደታቸው የማያቋርጥ ኡደቶች ናው።

እንደተለመደው ዘንድሮም ከተማችን ከግራ እና ከቀኝ ወጥሮ በያዛት የኑሮ ውድነት ውስጥ ሆና የአዲስ ዓመት በዓልን እንዴት ልታስተናግድልን ተዘጋጅታለች? የሚለውን ልናስቃኛችሁ ወደድን።

በመጀመሪያ ያመራነው የከተማችን ዋና የአትክልትና ፍራፍሬ መሸጫ ወደሆነው የፒያሣው አትክልት ተራ ነበር። በአብዛኛው በአትክልትና ፍራፍሬ ትርፍራፊዎች ምክንያት በሚፈጠረው ጭቃ እና ከመጠን ያለፈ ሽታ የሚታወቀው አትክልት ተራ በአሁኑ ወቅት በተወሰነ ደረጃ መሻሻል እየተስተዋለበት ይገኛል። በቦታው ላይ ያለውን ዝርክርክነት ለማስወገድ ያግዛል የተባለው ህንፃ በግንባታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ሁኔታው ተስፋ ሰጪ ነው። ሆኖም ግን በግንባታ ላይ ካሉት ጅምር ህንፃዎች ዙሪያ የሚከናወነው ንግድ በአካባቢው ፅዳት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖን ፈጥሯል።

ይህን የፒያሣውን አትክልት ተራ አስቸጋሪ ሁኔታ አልፎ ወደ አትክልት መደብሮች ያመራ ሰው ታዲያ የፈረንጁን ቀይ ሽንኩርት በኪሎ ከ8 ብር እስከ 11 ብር፣ የአበሻ ቀይ ሽንኩርት ከ13 ብር እስከ 15 ብር የሚያገኝ ሲሆን፣ ነጭ ሽንኩርት ከ40 ብር እስከ 43 ብር፣ ቲማቲምም በዚህ በፒያሣ አትክልት ተራ በኪሎ ከ10 ብር እስከ 13 ብር፣ ቃሪያ በኪሎ ከ22 ብር እስከ 25 ብር፣ እንዲሁም ድንች በኪሎ ከ4 ብር እስከ 5 ብር መግዛት ይችላል።

በሌላ በኩል ደግሞ ለቅቤ ማንጠሪያ እና ለሌሎች ምግቦችም እንደቅመም የሚጠቅመው አንድ ኪሎ ያልተፈለፈለ ኮረሪማ ከ105 ብር እስከ 110 ብር ዋጋ ያለው ሲሆን፤ አንድ ኪሎ ዝንጅብል ደግሞ ከ11 ብር እስከ 13 ብር ይገኛል።

በዘንድሮ የአዲስ ዓመት መባቻ የቅቤ እና የዘይት ዋጋስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል የሚለውን ለመቃኘትም ሙከራ አድርገናል። የቅቤ ዋጋን ለመቃኘት በጐጃም በረንዳ የሚገኙ የቅቤ መደብሮችን እና በመገናኛ ሾላ ገበያ የሚገኙ የቅቤ መደብሮችን ለመቃኘት ሞክረናል። በዚህም መሠረት በእነዚህ ሁለት የገበያ ቦታዎች የቅቤ ዋጋ እንደ ቅቤው በሳልነት እና ለጋነት የሚወሰን መሆኑን ተገንዝበናል። በመሆኑም አንድ ኪሎ ለጋ ቅቤ ከ165 ብር እስከ 175 ብር፣ በመካከለኛ የመብሰል ደረጃ ላይ ያለ አንድ ኪሎ ቅቤ ከ160 ብር ጀምሮ፣ በሳል የተባለው እና ብዙዎች አብዝተው የማይፈልጉት ቅቤ ደግሞ ከ155 ብር ጀምሮ በመሸጥ ላይ ይገኛል። በተያያዘም አንድ ኪሎ አይብ ከ45 ብር እስከ 50 ብር በኪሎ በመሸጥ ላይ ይገኛል።

ወደ ዘይት ገበያ ስናልፍ ደግሞ፤ የዘይትን ዋጋ በሁለት ከፍለን ተመልክተነዋል። ይኸውም በአብዛኛው በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት ለህዝቡ የሚከፋፈለው የአትክልት ወይም የሚረጋው ዘይት በቀበሌ ባለ ሦስት ሊትሩ ዘይት በ71 ብር ከ 25 ሣንቲም በመሸጥ ላይ ሲሆን፤ በችርቻሮ ሱቆች ደግሞ እስከ 72 ብር ይሸጣል። ባለአምስት ሊትሩ የሚረጋ ዘይት ደግሞ በ115 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ እና በተለያየ ዓይነት ወደገበያው የቀረቡ ፈሳሽ ዘይቶች ይገኛሉ። እነዚህ ዘይቶች በአመዛኙ ዋጋቸው ተቀራራቢ ሆኖ አግኝተናቸዋል። በመሆኑም አንዱ ሊትር የታሸገ የሀገር ውስጥ ዘይት ከ50 ብር እስከ 53 ብር ዋጋ ያለው ሲሆን፤ ባለ ሁለት ሊትሩ ደግሞ ከ100 እስከ 110 ብር ዋጋ አለው። ባለ አምስት ሊትሩ ዘይትም ከ263 ብር እስከ 265 ብር በሆነ ዋጋ በመሸጥ ላይ ይገኛል።

በአብዛኛው የባህላችን መገለጫ የሆነው እና ዓውድዓመት ሲባል የማይቀረው ደግሞ የዶሮ ወጣችን ነው። የዶሮ ወጥ ሲነሳ አብረው የሚነሱ በርካታ ነገሮች ቢኖሩም ከእነዚህ መካከል አይቀሬው ግን እንቁላል ነው። የዘንድሮውን የእንቁላል ዋጋ ስንመለከትም አንዱ የአበሻ እንቁላል ከ2 ብር ከ80 ሣንቲም እስከ ሦስት ብር ዋጋ አለው። አንዱ የፈረንጅ እንቁላልም እስከ ሦስት ብር ዋጋ አለው። በሌላ በኩል ደግሞ ኤልፎራን በመሳሰሉ አንዳንድ እንቁላል አቅራቢዎች ዘንድ አንዱ የፈረንጅ እንቁላል በ2 ብር ከ50 ሣንቲም ዋጋ ይሸጣል። የዶሮን ዋጋ ስንመለከት፤ በሾላ ገበያ ተዘዋውረን እንዳየነው አንድ ወንድ ዶሮ ከ160 ብር ጀምሮ በመሸጥ ላይ ይገኛል። ከአዲስ አበባ ዙሪያ አምጥተው ከሚሸጡ ግለሰቦች ላይ ደግሞ አንድ ወንድ ዶሮ ከ130 ብር እስከ 150 ብር ይገኛል።

ለአውድ ዓመት ከሚያስፈልጉ ነገሮች ሌላው ደግሞ ዳቦ ነው። ለዳቦ የሚሆነው ዱቄት ዋጋንም ለመመልከት ሞክረን ነበር። በዚህም መሠረት አንድ ኪሎ የፍርኖ ዱቄት በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሱቆች በ8 ብር ከ50 ሣንቲም በመሸጥ ላይ ይገኛል። ይህ ፍርኖ ዱቄት በቸርቻሪ ሱቆች ደግሞ ከ14 ብር እስከ 16 ብር ዋጋ ይገኛል።

ከዚህ የዱቄት ዋጋ ጋር በተያያዘ ሸማቾች በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና በቸርቻሪዎች ሱቅ ያለው ዋጋ ከፍተኛ ልዩነት በማምጣቱ፤ሸማቾች በአብዛኛው ከሸማች ማኅበራት እና ከቀበሌ ለመግዛት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ሆኖም ግን በቀበሌ ያለው ወረፋ ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን ይገልፃሉ። በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ይህንኑ የፍርኖ ዱቄት ለመግዛት ሞክረው እንዳልተሳካላቸው የሚናገሩት አንዲት እናት እንደገለፁልንም፤ ዱቄቱን ለማግኘት ቀናትን የፈጀ ትዕግስት ይጠይቃል። ዱቄቱን ለመግዛት ወደ ቀበሌ ከሚመጣው ሰው ብዛት የተነሳ ለገዢዎች የወረፋ ቁጥር እየተሰጠ ተራ እንዲይዙ እና በቁጥራቸው መሠረት እንዲገዙ ይደረጋል። በርካታ ሰዎች በመሰለፋቸው ምክንያትም በአንድ ቀን ተራ ሳይደርሳቸው እየቀረ በቀጣዩ ቀን መጥተው ለመግዛት መገደዳቸውን እኚሁ ሴት ገልፀውልናል።

ይህ የዱቄት ገበያ ችግር በተለያዩ የከተማችን አካባቢዎች በስፋት እየተስተዋለ እንደሆነ የገለፁልን ሸማቾች፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ወጥተው ሰልፍ እንደሚይዙ፣ ድንጋይ አሰልፈው እንደሚገቡ እና ተራ እየገዙ የሚሸምቱ ሰዎች እንዳሉም ገልፀውልናል። ይሄን አይነቱ ትርምስ ሊፈጠር የቻለውም ቸርቻሪ ሱቆች የዱቄቱን ዋጋ በእጥፍ ስለሚጨምሩ ሕዝቡ ለዋጋው ብሎ ወደዚያ ስለሚሄድ እንደሆነ ገልፀውልናል።

የአዲስ ዓመት መምጣትን ተከትሎ ከዓውደዓመት አከባበሩ ጐን ለጐን ለወላጆች አሳሳቢው ነገር የልጆች ትምህርት ቤት እና ተያያዥ ወጪዎች ናቸው። ምንም እንኳን ወላጆች ለሦስት ወራት ያህል ከትምህርት ቤት ውጪ አርፈው ቢከርሙም፤ መስከረም ሲጠባ ግን የወጪው ጉዳይ ማሳሰቡ አይቀርም። በመሆኑም የደብተር፣ የእስክሪቢቶ እና የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) ዋጋ ጉዳይ የወላጆች ሃሳብ ነው። የእነዚህን የትምህርት መሣሪያዎች ዋጋ ለመቃኘትም ሞክረናል። በመሆኑም አንድ ደርዘን የተለበደ ባለ 50 ሉክ ደብተር ከ85 ብር እስከ 90 ብር፣ ያልተለበደው አንድ ደርዘን ደግሞ ከ80 ብር ጀምሮ ሲሸጥ፤ አንድ ደርዘን የተለበደ ባለ 32 ሉክ ደብተር ከ55 ብር እስከ 60 ብር እና ያልተለበደው ባለ 32 ሉክ ደብተር ደግሞ በደርዘን ከ54 ብር እስከ 57 ብር ዋጋ በመሸጥ ላይ ይገኛል።

እነዚህን ደብተሮች በችርቻሮ ለመግዛት ለሚፈልግም ዋጋቸውን ለመጠቆም ያህል፤ አንዱ የተለበደ ባለ 50 ሉክ ደብተር በ7 ብር ከ75 ሣንቲም፣ ያልተለበደው ደግሞ በአማካይ በ7 ብር ከ50 ሣንቲም፣ የተለበደው ባለ 32 ሉክ ደብተር ደግሞ በ5 ብር ከ75 ሣንቲም ዋጋ፣ ያልተለበደው በ5 ብር ከ50 ሣንቲም መበሸጥ ላይ ነው። የእነዚህ ደብተሮች አይነት የተለያየ ቢሆንም፤ የሁሉም ዋጋ ግን በዚህ የዋጋ ወሰን ውስጥ ይገኛል።

ሌላው ከትምህርት ጋር ተያይዞ የሚነሳው የተማሪዎች የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) ነው። ይህ የዩኒፎርም ዋጋ መርካቶ በሚገኙ የጣቃ ጨርቅ መሸጫ መደብሮች የተሻለ ዋጋ እንዳላቸው ለመገንዘብ ችለናል። እንደየጨርቁ አይነት አንድ ሜትር የዩኒፎርም ጨርቅ ከ28 ብር እስከ 32 ብር ዋጋ ይገኛል። የዩኒፎርም ማላበሻ ሹራቦች እንደየጥራት ደረጃቸው ከ50 ብር ጀምሮ በመሸጥ ላይ ናቸው። በተለያዩ ሹራብ መሸጫ መደብሮችም እስከ 150 ብር ዋጋ አላቸው። የዩኒፎርም ሸሚዞችም ከ40 ብር ጀምሮ በመሸጥ ላይ ይገኛል።

    የዘንድሮውን የአትክልቶችም ሆነ የትምህርት መሣሪያዎችን ዋጋ ከአለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ስናነፃፅረው ብዙም የዋጋ ልዩነት እየተስተዋለበት አይደለም። በተለይ በአትክልት ዋጋ ላይ መጠነኛ የሆነ ቅናሽ እንዳለ ከነጋዴዎችና ከሸማቾችም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። አንዳንድ ያለ አግባብ ጥቅም የሚፈልጉ ነጋዴዎች በሸቀጦች ላይ የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ ቢያደርጉም፤ በአመዛኙ ያለው ዋጋ ግን ብዙም ልዩነት እንደሌለው ይጠቁማሉ። ኅብረተሰቡም በበዓል ዋዜማ ገበያ መውጣት እና ለግዢ የመረባረብ ባህሉን በማስወገድ የማይበላሹ እቃዎችን አስቀድሞ ገዝቶ ማስቀመጥን እየለመደው የመጣ ይመስላል። ለዚህ ማሳያው ደግሞ ከነሐሴ ወር መገባደጀ እና የጳጉሜን ወር መጀመሪያ አንስቶ ገበያዎች እና መደብሮች በሸማቾች መጥለቅለቅ መጀመራቸው ነው። ሸማቾቹ እንደገለፁልንም ከበዓል ቀደም ብሎ መሸመት ከዋጋው በተጨማሪም ጥራት ያለው እቃ ለማግኘት ያግዛል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1331 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 890 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us