ዛሬም ብዙዎች ፋታ በማይሰጠው ረሃብ ውስጥ ናቸው

Wednesday, 17 September 2014 14:17

በምግብ ራስን መቻል የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ በ1996 እ.ኤ.አ. የተደረገው የዓለም ምግብ ጉባኤ እንዲህ ሲል ያስቀምጠዋል። “ሁሉም ሰው፣ ሁልጊዜም በቂ፣ የተመጣጠነ እና ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ጤናማና ንቁ የሆነ ህይወት እንዲኖር የሚያግዘውን ምግብ ሲያገኝ በምግብ ራሱን ቻለ ይባላል” ይላል። አፍሪካን የመሳሰሉ ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት ታዲያ ለዚህ አይነቱ በምግብ ራስን ያለመቻል ችግር የተጋለጡ ናቸው።

በየአመቱ የሚካሄደው እና የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ፎረም አካል የሆነው አፍሪካን የመመገብ ፖሊሲ ምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ከሰሞኑ ተካሂዶ ነበር። በምክክር መድረኩ እንደተገለፀውም በአፍሪካ አሁንም 200 ሚሊዮን ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አለባቸው። በተጨማሪም 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በየአመቱ በረሀብ ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ። በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ስንመለከትም ያለው መረጃ የሚፈለገውን ያህል ሰፊ ባይሆንም አሁንም ድረስ ይህ በምግብ ራስን የመቻል ችግር እንዳለ ያመለክታል።

እ.ኤ.አ. በ2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ከሚገኙ አስር ሰዎች አንዱ በቂ፣ የተመጣጠነ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ ለማግኘት ከባድ ትግል ያደርጋል። በፈረንጆቹ 2014 ደግሞ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የአለም ምግብ ፕሮግራም ይፋ አድርጓል። እ.ኤ.አ በ2010 የወጣ አንድ ሪፖርት እንዳመለከተው በኢትዮጵያ 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች በምግብ እጥረት ውስጥ ነበሩ። ለዚህ ደግሞ እንደ ዋና ምክንያት የተቀመጠው ቀደም ብሎ በነበረው አመት የነበረው ዝናብ በቂ አለመሆኑ ነበር።

በኢትዮጵያ ያለውን በምግብ ራስን የመቻል መጠን በሚወለዱ ህፃናት እድገት ላይ መሰረት አድርጎ መለካት እንደሚቻል ነው የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ያስቀመጠው። ይህም የሆነበት ምክንያት የእነዚህ የሚወለዱ ህፃናት የሰውነት ክብደት መጠን በአለም አቀፍ ደረጃ አንድ ህጻን ያለውን የተመጣጠነ ምግብ እና ጤና ለመለካት የሚያግዝ በመሆኑ ነው። ይህ ደግሞ አንድ ህጻን በሚወለድበት ወቅት የሚኖረውንም ክብደት ያካተተ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚወለዱ ህፃናት የሰውነት ክብደት ታዲያ የምግብ እጥረት በሀገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ መሆኑን የጠቆመ ነበር።

ለአብነት ያህልም እ.ኤ.አ. በ2005 ከተወለዱ ህጻናት መካከል 20 በመቶዎቹ ዝቅተኛ የተባለውን 2ሺ 500 ግራም ክብደት ይዘው ነው የተወለዱት። በዚህ ጎን ለጎንም እድሜያቸው ከ5 አመት በታች ከሆኑ ህጻናት መካከል 53 ነጥብ 5 በመቶዎቹ እንዲሁም ከነፍሰ ጡር እናቶች መካከል 30 ነጥብ 6 በመቶዎቹ ደካማ ወይም አቅመ ቢሶች ናቸው። በሃገሪቱ ካሉት ታዳጊዎች 34 ነጥብ 6 በመቶዎቹ ደግሞ አንድ ታዳጊ ሊያሟላ ከሚገባው ክብደት በታች ነው ያላቸው። ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ የህፃናት ሞትን ያባባሰ ሆኗል። በዚህም መሰረት 50 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆኑት ካለባቸው ምግብ እጥረት የተነሳ በአስተዳደጋቸው ላይ ዝግመት ይከሰትባቸዋል። 12 ነጥብ 3 በመቶዎች ደግሞ በሽታን የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ በመሆን በቀላሉ ለበሽታ እንዲጋለጡ እና ህይወታቸውንም እንዲያጡ እያደረጋቸው ነው።

ይህ በምግብ ራስን አለመቻል ወይም በቂ የሆነ ምግብ ማግኘት አለመቻል በግለሰብ ላይ ብቻም ሳይሆን በሀገር ኢኮኖሚ እና ምርታማነት ላይ ጭምር ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለው ነው የተገለፀው። ከተጠቀሱት ችግሮች መካከልም የአእምሮ እድገት መጫጨት፣ በትምህርት ገበታ ላይ ብቁ አለመሆንና እንዲሁም በሴቶች ላይ በወሊድ ወቅት ለውስብስብ ችግሮች መጋለጥን ያስከትላል። ይህ አይነቱ ችግር ደግሞ ዞሮ እናቶች በሚገጥማቸው የወሊድ ችግር ምክንያት ዝቅተኛ ክብደት ያላቸው ህጻናት እንዲወልዱ ያደርጋል።

በሀገሪቱ ያለውን የምግብ እጥረት ለማስወገድ በየጊዜው የተለያዩ ጥረቶች የተደረጉ ቢሆንም፣ ነገር ግን ይህን ችግር በቀላሉ መቅረፍ አልተቻለም። ለአብነት ያህልም በ1994 (እ.ኤ.አ.) እስከ 2003 ባሉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ተደርጓል። ሆኖም ግን የዚህ የአስቸኳይ ምግብ እርዳታ በተለይ በገጠር የሀገሪቱ ክፍል በሚኖሩ ሰዎች ዘንድ ጥያቄው እየጨመረ መጥቷል ይላሉ ዘገባዎች።

የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ሰዎች እርዳታን ከመስጠት ጎን ለጎንም በሀገሪቱ ያለውን የመሰረተ ልማት ጥራት ለማሻሻል፣ የትምህርት እና የስነ-ምግብ ክፍተቶችን ለማጥበብ የተደረጉ ጥረቶች መጠነኛ ለውጦች እንዳመጡ የአለም ባንክ ገልጿል። በዚህም መሰረት በ2000 (እ.ኤ.አ) በድህነት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ቁጥር ከህዝቡ 55 በመቶዎቹ እንደነበሩ ያመለከተው ባንኩ፣ ይህ ቁጥር በ2011 ወደ 29 ነጥብ 6 በመቶ ዝቅ ማለቱን አመልክቷል። በተጨማሪ በቀጣዮቹ 2012 ዓ.ም ከድህነት ወለል በታች የነበሩ ሰዎች ቁጥር 77 ነጥብ 6 በመቶ የነበረ ሲሆን በቀጣይ 2013 ዓ.ም ደግሞ ወደ 66 በመቶ መውረድ መቻሉን እንደ ጥሩ ተሞክሮ አስቀምጦታል።

ከላይ የተጠቀሰውን ለውጥ ለማምጣት የተቻለውም በተለይ የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት በሆነው የግብርና ዘርፍ ላይ ጥሩ ስራዎችን በመስራት እንደሆነ የገለፀው የባንኩ ዘገባ፣ ከእነዚህ ተግባራት መካከልም የግብርና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችን እያሰለጠኑ ወደ ስራ ማስገባቱ የበለጠ አዋጪ እንደሆነ ጠቁሟል። በዚህም መሰረት እስከ 2014 ድረስ ኢትዮጵያ 60ሺ ያህል የግብርና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችን አሰልጥና በመላው ሀገሪቱ ወደ ስራ አስገብታለች።

አፍሪካም ሆነች ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ የመጣውን የህዝብ ቁጥር እና የሚያስፈልገውን የምግብ መጠን ለማመጣጠን ከባድ ፈተና ውስጥ ናቸው። ለእዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች ተቀምጠዋል። ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የነፍስ ወከፍ ገቢ ፍላጎት መጨመር፣ እንዲሁም በፕሮቲን ለበለፀጉ ምግቦች ያለው ፍላጎት ማሻቀብ የሚሉት እንደ ዋና ዋና ምክንያቶች ተቀምጠዋል።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ህዝብን ለመመገብ ታዲያ በተለይ በግብርና ልማት ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣትን ይጠይቃል ይላል የአለም ምግብ ድርጅት። የኢትዮጵያ ህዝብ በአብዛኛው የሚተዳደረው በግብርና እንደመሆኑ እና ግብርናው ደግሞ በተፈጥሮው የክረምት ዝናብ ላይ መሰረት ያደረገ በመሆኑ ይህን አይነቱ መሰረታዊ ለውጥ የግድ እንደሆነ ነው የተለገፀው። የኢትዮጵያ ገበሬ ጥሩ የክረምት ዝናብ ባለበት ወቅት እንኳ ለፍጆታ በቂ የሆነ ምርት ለማምረት እየተቸገረ መሆኑም ተገልጿል። በዚህ በግብርናው ዘርፍ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ አለማድረግ በራስ ሌላው በምግብ ራስን ያለመቻል ፈተና እንደሆነ ተገልጿል።

     በሀገሪቱ ላለው የምግብ እጥረት ድርቅ፣ ጦርነት እና ወቅታዊ የሆነ የግብርና ስራ እንደዋና ምክንያት የተቀመጡ ናቸው። እነዚህ ምክንያቶች በሀገሪቱ ታሪክ ረጅም እድሜ ያስቆጠሩ ቢሆኑም እያደረሱ ያሉት ችግር ግን ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ነው የመጣው። በሀገሪቱ እ.ኤ.አ ከ1980 ጀምሮ የምግብ እጥረት እንደነበረ የተገለፀ ሲሆን በ1974/80 ዓ.ም የነበረው ህዝብን የመመገብ ክፍተት ዜሮ ነጥብ 75 ሚሊዮን ቶን እንደነበረ ተጠቅሷል። ይህ ቁጥር በ1993/94 ወደ 5 ሚሊዮን ቶን እንዳሻቀበ ገልጿል። በመቀጠልም በ1995/96 ደግሞ ወደ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን ዝቅ ብሎ እንደነበረ ዘገባዎች አመልክተዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1157 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 881 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us