የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ችግር በንቅናቄ ይፈታ ይሆን?

Wednesday, 24 September 2014 11:56

 

እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም በኢትዮጵያ ከነበሩት 30 ሚሊዮን ሴቶች መካከል 16 ነጥብ 7 በመቶዎቹ ብቻ የተማሩ ናቸው ተብሎ እንደሚገመት የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። በዚህም የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ 40 በመቶ ነበር። ከ14 ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ. በ2014 ደግሞ የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ወደ 94 ነጥብ 2 በመቶ ከፍ ማለቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስቀምጧል። የሴቶችን በትምህርት ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ እና ለውጥ ለማምጣትም የአንድ ዓመት እድሜ ያለው ይፋዊ ዘመቻ እና የንቅናቄ ተግባራትን የማከናወን እንቅስቃሴ ባለፈው ሳምንት ተጀምሯል።

በኢትዮጵያ ያለውን የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ አስመልክቶ ዩኔስኮ እ.ኤ.አ. በ2012 ይፋ ያደረገው አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ላይ ያለው የወንዶች እና ሴት ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ ከመሆኑም በላይ፤ ከእነዚህ ሴት ተማሪዎች መካከልም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ የሚችሉት 41 በመቶዎቹ ሴቶች ብቻ ናቸው። በዚህም ሳቢያ በ2009 ዓ.ም 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ወጣት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንደነበሩ ተገልጿል። በዚህ ዓመት እድሜያቸው 15 ዓመት እና ከዚያ በላይ ከሆኑ ሴቶች መካከል 82 በመቶዎቹ ሴቶች ያልተማሩ ነበሩ። ይህ ደግሞ 58 በመቶ ድርሻ ካለው የወንዶች ድርሻ ጋር ሲነፃፀር በጣም ከፍተኛ ነው።

ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በ2010 እና በ2011 ብቻ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሚሆኑ እድሜያቸው ከ11 እስከ 14 ዓመት የሆኑ ሴቶች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው። ለዚህ ቁጥር ደግሞ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ሲሆኑ፤ ይኸውም ከዚህ ቁጥር 58 በመቶውን ይዘዋል።

በእነዚህ ሁለት ክልሎች ያለው የወንድ እና ሴት ተማሪዎች ተሳትፎም ክፍተቱ 10 በመቶ እንደሆነ ተጠቅሷል። በእነዚህ ሁለት ክልሎች የነበረው ትምህርታቸውን ከአንደኛ ክፍል የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥርም በሀገር አቀፍ ደረጃ ካለው መጠን በጣም ከፍተኛ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው ትምህርታቸውን ከአንደኛ ክፍል የሚያቋርጡ ተማሪዎች መጠን 19 ነጥብ 2 በመቶ ሲሆን፤ በእነዚህ ሁለት ክልሎች ያለው ግን 37 በመቶ ነው።

በ2012 በመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያለው የወንዶች እና ሴቶች ተማሪዎች ቁጥር ሲነፃፀር ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው የዓለም ባንክ ሪፖርት ያመለክታል። በሀገሪቱ ያለውን የሁለተኛ ሳይክል ትምህርት የሚከታተሉ ሴቶች ቁጥርን ስንመለከትም እ.ኤ.አ. ከ2008/09 እስከ 2012/13 የታየው ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ይኸውም በ2008/09 ከነበረበት 3 ነጥብ 5 በመቶ በ 2012/13 ወደ 8 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ እድገት አሳይቷል።

በሀገሪቱ ላለው የሴቶች ትምህርት ተሳትፎ እንደ ትልቅ እንቅፋት ተደርገው የተቀመጡትም ሴቶች ለቤት ውስጥ ስራ ያላቸው ከፍተኛ ተፈላጊነት፣ ወደ ትምህርት ቤት በመሄጃ እድሜ ጋብቻ መፈፀም፣ እንዲሁም ለሴት ልጅ ማኅበረሰቡ ያለው አነስተኛ ግምት እንደምክንያት ተቀምጠዋል።

በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው የአመለካከት ችግር እና ድህነት ለሴቶች ትምህርት ተሳትፎ መውረድ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ። አንዲት ሴት ተማሪ በተለይ እድሜዋ ለትምህርት በሚደርስበት ወቅት የቤት ውስጥ ኃላፊነትን ሙሉ ለሙሉ እንድትወስድ የሚደረግ ሲሆን፤በአንዳንድ አካባቢዎችም ይህ አስተሳሰብ አንዳንድ ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ እንደ ግዴታ የሚጣልበት ጊዜ እንዳለም ተገልጿል። ከትምህርት ቤት መልስ በኋላም በቤት ውስጥ የሚጠበቅባትን ኃላፊነት የመወጣት ግዴታ ስለሚኖርባት ሙሉ ጊዜዋን በቤት ስራ ላይ እንድታሳልፍ እና ቀን የተማረችውን እንድታጠና ትደረጋለች የሚለው የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ፤ የዚህ ደግሞ ውጤቱ በትምህርት ቤት በጣም ዝቅተኛ የሆነ ውጤት ማስመዝገብ ብሎም ከክፍል ወደ ክፍ መዘዋወር አለመቻል ይሆናል ይላል።

ከዚህ በተጨማሪም የትምህርት ፖሊሲው በራሱ በሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ላይ ተፅዕኖ እንዳለው ተቀምጧል። አንዳንድ በመማሪያ መፅሐፍት ውስጥ የሚካተቱ ርዕሶች እና ታሪኮች የተዛባ የማኅበረሰቡን አስተሳሰብ የሚያንፀባርቁ መሆናቸው የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ሊገድበው እንደቻለም ባለሙያዎች አስተያየት ሰጥተዋል።

በርካታ በሁለተኛ ደረጃ እና ዩኒቨርሲቲ ውሰጥ የሚማሩ ሴት ተማሪዎች ለተለያዩ ጾታዊ ጥቃቶች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ። ለአብነት ያህልም እ.ኤ.አ. በ2011 በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው 8 ነጥብ 7 በመቶዎቹ ሴት ተማሪዎች መደፈር የሚደርስባቸው ሲሆን፤ 23 ነጥብ 5 በመቶዎቹ ደግሞ የመደፈር ሙከራ ተደርጐባቸዋል። 24 ነጥብ 2 በመቶዎቹ አካላዊ ጥቃቶች የደረሰባቸው ሲሆን፣ 18 ነጥብ 7 በመቶዎቹ ቃላዊ ጥቃት እንዲሁም 11 ነጥብ 3 በመቶዎቹ ደግሞ አስገዳጅ ወሲብ ተፈፅሞባቸዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ሴቶች ትምህርት እንዳያገኙ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች ልላው ተጠቃሽ ጋብቻ ሲሆን ይህም በገጠር 23 ነጥብ 3 በመቶውን ሲይዝ በከተማ አካባቢ ደግሞ 16 በመቶውን እንደሚይዝ ተቀምጧል። ከዚህ በተጨማሪም ትምህርት ከጀመሩ ሴቶች መካከል በገጠር 38 ነጥብ 6 በመቶዎቹ እንዲሁም በከተማ 21 በመቶዎቹ በጋብቻ ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ።

ሌላው ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ከሄዱም በመሃል እንዲያቋርጡ የሚያደርጋቸው ጾታዊ ጥቃት ነው። ይህም ማለት ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ፤ እና ሲመለሱ በትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ፣ በስራ አጥ ወንዶች፣ ያላገቡ እና የትዳር አጋር በሚፈልጉ ወንዶች የተለያዩ ጾታዊ ጥቃቶች ይፈፀሙባቸዋል። እነዚህ ጾታዊ ጥቃቶች እስከ አስገድዶ መድፈር እንደሚደርሱም ጥናቶች ያመለክታሉ። በዚህም እድሜያቸው ከአስር እስከ 19 ዓመት የሆናቸው ሴቶች ይበልጥ ተጠቂዎች ናቸው። በእነዚህ በሚደርሱባቸው ጾታዊ ጥቃቶች ምክንያትም ሙሉ ትኩረታቸውን በትምህርታቸው ላይ ከማድረግ ይልቅ በቀጣይ ሊገጥሟቸው የሚችሉ ጥቃቶችን በማሰብ በትምህርታቸው ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘግባሉ።

ሌላው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጭምር የሚማሩት ተማሪዎች በሴት መምህራን እንዲማሩ አለመደረጉ ሴት ተማሪዎች በትምህርት ዘርፍ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች እንዳይወያዩ እና መፍትሄ እንዳያገኙ ያደርጋቸዋል ተብሏል። በዚህም ሳቢያ ሴቶች ተማሪዎች እንደልባቸው መጠየቅ እና መልስ ማግኘት አለመቻላቸው ከትምህርት ጐን ለጐን የሚመጡ ጫናዎችን መቋቋም ያቅታቸዋል።

በሀገርም ሆነ በዓለም ደረጃ ያለውን ድህነት ለማስቀረት ሴት ልጅን ማስተማር ዋነኛ አማራጭ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስቀምጣሉ። ሴት ልጅን የማስተማሩ ጥቅምም ከግለሰብ አልፎ ለቤተሰብ፣ ለማኅበረሰብ እና ለዓለም የሚበቃ ነው። ከጠቀሜታዎቹ መካከል ባለሙያዎቹ የሚስማሙባቸውን ለመጥቀስ ያህል አንዲት ሴት ሊኖሯት የሚችሉት ልጆችን ቁጥር መቀነስ ያስችላል፤ የጨቅላ ህፃናት እና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ያግዛል፣ የእናቶች ሞትን እና የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ይቀንሳል። ከዚህ በተጨማሪም በስራ ዓለም እና ከፍተኛ ገቢ በሚያስገኙ ሙያዎች ላይ የሚኖረውን የሴቶች ተሳትፎ ማሳደግ እና ለቀጣይ ትውለድ የሚተርፍ ጠቀሜታን ማስገኘት ይጠቀሳሉ።

    አንዲት የተማረች ሴት ጋብቻ የምትፈፅምበትን ወቅት በትምህርት ገበታ ላይ በማሳለፏ የምታገባውን ሰው የመምረጥ፣ ቤተሰብ ከመሰረተች በኋላም የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በመጠቀም፣ የቤተሰቧን ጤንነት በመጠበቅ እና ራሷን እና ቤተሰቧን ከበሽታዎች ለመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የሚገልፁት ባለሙያዎቹ፤ ይህም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ያስቀምጣሉ።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
1984 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1033 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us