ድህነት ገንዘብ ማጣት ብቻ አለመሆኑን ያመላከተ ተግባር

Wednesday, 01 October 2014 14:35

ወይዘሮ አበበች አልማው ነዋሪነታቸው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ነው። ህይወታቸውን የሚመሩት እና ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት ቅጠል ለቅመው በቤታቸው ውስጥ የሚያዘጋጁትን አረቄ፣ ጠላ እና እንጀራ በመሸጥ ነበር። በቀን ሥራ ላይ የተሰማሩት ባለቤታቸው እና እርሳቸው ሰርተው የሚያገኙት ገንዘብ ቤተሰቡን ለማስተዳደር እና ልጆቻቸውን ለማስተማርም በቂ አልነበረም። ነገር ግን የዛሬ ሁለት ዓመት ተኩል አካባቢ በተገኘ አንድ እድል የራሳቸውም ሆነ የቤተሰባቸው ህይወት መለወጥ ችሏል። ፒፕል ኢን ኒድ በኢትዮጵያ የከተሞች ማህበራዊ ልማት ላይ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ሲጀምር በአዲስ አበባ በጣም በከፋ ድህነት ውስጥ ያሉ ሴቶችን በማሰባሰብ ነበር። በዚህም ከተሰበሰቡት ችግረኛ ሴቶች መካከል ወይዘሮ አበበች አንዷ ነበሩ። በዚህም አጋጣሚ ወይዘሮ አበበች በፒፕል ኢን ኒድ ስር በሚንቀሳቀሰው ፕሮፕራይድ ፕሮጀክት ስር ተካተቱ።

ፒፕል ኢን ኒድ በአዲስ አበባ ከተማ እያካሄደ ባለው የከተማ ማህበራዊ ልማት ፕሮግራም ከባድ ድህነት ውስጥ ያሉ ሴቶች ተሰባስበው በገቢ ራሳቸውን የሚችሉበት ሁኔታ የማመቻቸት ሥራ ይሰራል። ለዚህም ሴቶቹን የንግድ ክህሎትን፣ በቤተሰብ ጤንነት አጠባበቅን፣ ፅዳትን፣ ትምህርትን፣ የጡረታ (ማህበራዊ ዋስትና) እንዲሁም ቁጠባን በተመለከተ ስልጠና ይሰጣቸዋል። በመቀጠልም ሴቶቹ ካላቸው ነገር ላይ ቁጠባ እንዲቆጥቡ ተደርጓል። በቀጣዩ ዓመትም ሴቶቹ ሊሰሩ የሚችሉትን የሥራ አይነት በመምረጥ ይወዳደሩ እና ወደ ሥራ ይገባሉ።

ፒፕል ኢን ኒድ መሠረቱን አውሮፓ ያደረገ እና በሀገራት ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተመስርቶ በከባድ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን የሚረዳ ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት በሀገራችን ከ12 ዓመታት በላይ የተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ በሶማሊያ፣ በኦሮሚያ፣ በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልሎች ይንቀሳቀሳል። በእነዚህ ክልሎች ውስጥ ድርጅቱ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አስመልክቶ የፒፕል ኢን ኒድ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ በረከት ወልደጊዮርጊስ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

እንደ አቶ በረከት ገለፃ ፒፕል ኢን ኒድ በሀገራችን በትምህርት ዘርፍ በትምህርት ቤት ግንባታ፣ ጥራት ያለው ትምህርት መስጠት የሚችሉ መምህራንን ለማፍራት በመምህራን ስልጠና እንዲሁም በውሃ እና ከአከባቢ ንፅህና ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ይሰራል። በሀገሪቱ በከባድ ድህነት ውስጥ ያሉ ሰዎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥም በገጠር አካባቢ ለገበሬዎች ምርጥ ዘርን በማቅረብ፣ የተሻሻለ የአስተራረስ ዘዴዎች በማስተማር፣ አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎች ፈጥኖ በመድረስ እርዳታን ያደርጋል። ከዚህ ጎን ለጎንም በአካባቢ ጥበቃ ላይ ሰፊ ሥራ በመስራት ላይ ይገኛል።

ፒፕል ኢን ኒድ በአዲስ አበባ በተለይ በማህበራዊ ልማት ላይ ሰፊ ሥራ እየሰራ ይገኛል። ይህ ፕሮግራም ላለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ በርካታ ሥራዎችን በመስራት የበርካታ ሰዎችን ህይወት መለወጥ እንደቻለም አቶ በረከት ገልፀዋል። ይህ ፕሮጀክት የተያዘለትን እቅድ አጠናቆ መዝጊያውን ባለፈው ሳምንት አድርጓል። ለመሆኑ ይህ የከተማ ልማት ፕሮጀክት ምን የተለየ ነገር ይዞ መጣ? አቶ በረከት ያብራሩታል። ፕሮጀክቱ የሚንቀሳቀሰው ሙሉ ለሙሉ በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ነው። ፕሮጀክቱ እየተንቀሳቀሰ ያለውም ከሶስት ሀገር በቀል ድርጅቶች ጋር ነው። እነዚህም ሚሽን ፎር ሶሻል ዴቨሎፕመንት (MSD)፣ ሶሳይቲ ፎር ውመን ኤድስ ኢን አፍሪካ ኢትዮጵያ እንዲሁም ፕሮፕራይድ ናቸው።

ይህ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ በጉለሌ፣ አራዳ፣ አዲስ ከተማ እና ቦሌ ክፍለ ከተማዎች ያሉ በከባድ ድህነት ውስጥ ያሉ ሴቶችን አቅም የማሳደግ ሥራ ይሰራል። ፕሮጀክቱ ማህበራዊ አገልግሎቶችን አሟልቶ የሚያቀርብ ሳይሆን የሰዎችን አእምሮ እና አመለካከት በመቀየር ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣትን እንደ ግብ ያስቀመጠ ነው። በተለይ ሴቶች ራሳቸውን ለውጠው ህይወታቸውን እንዲያሻሽሉ ያበረታታል። ይሄን የሚያደርገው ደግሞ በራስ አገዝ ቡድን እንዲደራጁ በማድረግ ነው። የፕሮጀክቱ አላማ በነፃ እንካችሁ ማለት እንዳልሆነ አቶ በረከት ይገልጻሉ።

“የፕሮጀክቱን ፅንሰሃሳብ ተጠቃሚዎች ምን አላቸው? የሚል እንጂ ምን የላቸውም የሚል አይደለም። ህብረተሰቡ ውስጥ ያለው ነገር አለ፤ ያንን ካፒታላይዝ እናደርገው ብለን ነው የጀመርነው። ከዜሮ ለመጀመር ሳይሆን ህብረተሰቡ ያለውን እውቀት፣ ሀብት እና አቅም የማሳደግ አላማ ነው ፕሮጀክቱ ያለው። እንደ ፕሮጀክቱ እምነት ድህነት ገንዘብ ማጣት ብቻ ሳይሆን የሰዎችን አለመቀበል ባህሪይ፣ ድምፅን ካለማሰማት እና ያለውን ነገር ካለመጠቀም ጋር የተያያዙ ምክንያቶች ውጤት ነው” ይላሉ አቶ በረከት።

ይህ ሰፊ ፅንሰ ሃሳብ ያለውን ድህነት ለመቅረፍ ታዲያ ሴቶቹ በማህበራዊ እና ተቋማዊ መዋቅር ስር ታቅፈው እንዲንቀሳቀስ ተደርጓል። በእነዚህ መዋቅሮች ውስጥም ራስ አገዝ ቡድን አንድ ነው። ራስ አገዝ ቡድን የተወሰነ ቁጥር ያላቸው እና በአንድ ጉዳይ ላይ አንድ አቋም ያላቸው ሴቶች የሚሰባሰቡበት ቡድን ነው። ቡድኑም ሴቶችን በመለወጥ፣ የተሻለ ደረጃ ለማድረስ እና ድምፅ ለማሰማት ያግዛል። በተጨማሪም ሴቶቹ ለነገ ሕይወታቸው እና ለቀጣይ አኗኗራቸው በማሰብ ሰርተው ከሚያገኙት ነገር ላይ ቆጥበው እንዲያስቀምጡ የሚያግዛቸውን ቁጠባ ያከናውናሉ። በመሆኑም በዚህ ፕሮጀክት 461 ራስ አገዝ ቡድኖች ማቋቋም ተችሏል።

ፕሮጀክቱ በተንቀሳቀሰባቸው ጊዜያት ውስጥ መደበኛ ባልሆኑ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ሴቶች ዋና አላማዎቹ ናቸው። እነዚህ ሴቶች ጠላ እና አረቄ በማዘጋጀት፣ ጉሊት ላይ በመሸጥ፣ በሸክላ ሥራ ላይ የተሰማሩ፣ በሰው ቤት እየተመላለሱ የሚሰሩ፣ እንጀራ በመጋገር የሚተዳደሩ እና ቤተሰባቸውን የማስተዳደር አቅም የሌላቸው ሴቶች ናቸው። በፕሮጀክቱ እንቅስቃሴም 8ሺ 146 ሴቶች የዚህ አገልግሎት ቀጥተኛ ተጠቃሚ ሆነዋል። በተጨማሪም 60ሺ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ ተጠቃሚ ሰዎችን እንዲሁም 52ሺ የቤተሰብ አባላትን መድረስ ተችሏል። እነዚህ ችግረኛ ስቶችም ብዙ ለውጥ አግኝተውበታል። እነ ወይዘሮ አበበችም የሚናገርት ይሄንኑ ነው።

“መጀመሪያ ፕሮፕራይድ ችግረኛ ሴቶችን ሲመለምል እኔም አንዷ ነበርኩ። ገና ወሬውን ስሰማው ትልቅ ተስፋ ነበር የጣልኩበት። ከችግር እንደሚያላቅቀኝ ስለተሰማኝ እየዞርኩ ሴቶቹን ማስተባበር ጀመርኩ” የሚሉት ወይዘሮ አበበች፤ በዚህ ጊዜ ታዲያ በርካታ ውጣ ውረዶችን ማለፋቸውን ይናገራሉ። “እኔ ስለጓጓሁ እየዞርኩኝ ስቀሰቅስ አንዳንዶቹ ሲሰድቡኝ፣ ሌሎች አርፈሽ ጠላሽን ብትጠምቂ እና አረቄሽን ብታወጪ ይሻልሻል ይሉኛል። ግማሾቹም ይስቁብኝ ነበር” ሲሉ የገጠማቸውን ፈተና የገለፁት ወይዘሮ አበበች፤ በዚህ ውጣ ውረድ መካከል ሆነውም 20 ያህል ሴቶችን በማሰባሰብ ቡድን መፍጠር ችለዋል።

ወይዘሮ አበበችም ስልጠናውን ወስደው በወር ሶስት ብር ከቆጠቡ በኋላ በምግብ ዝግጅት ነበር የተወዳደሩት። “ውድድሩ ሲመጣ እኔ ጠላ እና አረቄ ከመሸጥ ይልቅ ምግብ አዘጋጅቼ መሸጥ እችላለሁ ብዬ ተወዳደርኩ። በፊትም ይሄንን የምግብ ዝግጅት ጀምሬው ነበር። ነገር ግን ልጆች ስለማስተምር እና ገንዘብ ስለማጠፋ እከስር ነበር። በውድድሩ ወቅት ግን 300 ብር ተበድሬ የምግብ ዝግጅቱን በጥሩ ሁኔታ ማስኬድ ችያለሁ” ይላሉ ወይዘሮ አበበች።

በዚህ ብድር ተጠቅመው ስራቸውን ከጀመሩ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያመጡትን ለውጥም እንዲሁ ያስቀምጡታል። “ሁለት ልጆቼ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ነበሩ። መስከረም በመጣ ቁጥር እኔም ልጆቼም ለቅሶ ነበር። አልብሼ እና አስይዤ የምሸኛቸው ስላልነበረኝ ሁላችንም ለቅሶ እና ጭንቀት ነበር። ያቺን 300 ብር ተበድሬ ከሰራሁ በኋላ ግን ልጆቼን አልብሼ ለመጀመሪያ ጊዜ ደስ ብሎኝ ሸኘኋቸው” ይላሉ። በዚህ መልኩ ሥራ የጀመሩት ወይዘሮ አበበች፣ በየጊዜው ብድር እየወሰዱ እና ሥራቸውን እያሻሻሉ በመሄዳቸው ተወዳድረው እስከመሸለም ደርሰዋል። የአረቄ እና የጠላ ሥራን ሙሉ በሙሉ በመተው እና በሽሮ የተጀመረውን የምግብ ዝግጅትም ከፍ በማድረግ የመለስተኛ ምግብ ቤት ባለቤት ሆነዋል።

“ተወዳድሬ ሳሸንፍ ፕሮፕራይድ ግምቱ አስር ሺህ ብር የሚሆን የምግብ ቤት እቃ ነው ገዝቶ የሰጠኝ። እኔም ያንን ተጠቅሜ ስራዬን አሻሽያለሁ። በአሁኑ ወቅት 36ሺ ብር ካፒታል አስመዝግቤያለሁ። በፊት እሰው ቤት በተመላላሽ እሰራ ነበር። አሁን ግን ሁለት ሰራተኞችን ቀጥሬ እያሰራሁ ነው” ያሉት ወይዘሮ አበበች በአሁኑ ወቅት ለሚፈልጉት ነገር እንደልባቸው ገንዘብ ማውጣት መጀመራቸውንም ይናገራሉ። “በጣም ከባድ ሥራዎችን እሰራ ስለነበረ በመካከል ታምሜ ነበር። በፊት ክሊኒክ እንኳን የመሄድ አቅም አልነበረኝም። አሁን ሲያመኝ ግን 8ሺ 8 መቶ ብር ከፍዬ መታከም ችያለሁ። በመስራቴ ነው ይሄን ያህል ገንዘብ አውጥቼ መታከም የቻልኩት እንጂ ልጆቼ እያዩኝ ሟች ነበርኩ” ሲሉ ያገኙትን ለውጥ ይናገራሉ።

ይህ ሰፊ ፅንሰ ሃሳብ ያለውን ድህነት ለመቅረፍ ታዲያ ሴቶቹ በማህበራዊ እና ተቋማዊ መዋቅር ስር ታቅፈው እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል። በእነዚህ መዋቅሮች ውስጥም ራስ አገዝ ቡድን አንድ ነው። ራስ አገዝ ቡድን የተወሰነ ቁጥር ያላቸው እና በአንድ ጉዳይ ላይ አንድ አቋም ያላቸው ሴቶች የሚሰባሰቡበት ቡድን ነው። ቡድኑም ሴቶችን በመለወጥ፣ የተሻለ ደረጃ ለማድረስ እና ድምፅ ለማሰማት ያግዛል። በተጨማሪም ሴቶቹ ለነገ ሕይወታቸው እና ለቀጣይ አኗኗራቸው በማሰብ ሰርተው ከሚያገኙት ነገር ላይ ቆጥበው እንዲያስቀምጡ የሚያግዛቸውን ቁጠባ ያከናውናሉ። በመሆኑም በዚህ ፕሮጀክት 461 ራስ አገዝ ቡድኖች ማቋቋም ተችሏል።

ፕሮጀክቱ በተንቀሳቀሰባቸው ጊዜያት ውስጥ መደበኛ ባልሆኑ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ሴቶች ዋና አላማዎቹ ናቸው። እነዚህ ሴቶች ጠላ እና አረቄ በማዘጋጀት፣ ጉሊት ላይ በመሸጥ፣ በሸክላ ሥራ ላይ የተሰማሩ፣ በሰው ቤት እየተመላለሱ የሚሰሩ፣ እንጀራ በመጋገር የሚተዳደሩ እና ቤተሰባቸውን የማስተዳደር አቅም የሌላቸው ሴቶች ናቸው። በፕሮጀክቱ እንቅስቃሴም 8ሺ 146 ሴቶች የዚህ አገልግሎት ቀጥተኛ ተጠቃሚ ሆነዋል። በተጨማሪም 60ሺ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ ተጠቃሚ ሰዎችን እንዲሁም 52ሺ የቤተሰብ አባላትን መድረስ ተችሏል። እነዚህ ችግረኛ ስቶችም ብዙ ለውጥ አግኝተውበታል።

ሌላዋ የዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ የሆኑትን እናት አነጋግረን ነበር። እኚህ እናት የሶሳይቲ ፎር ውመን ኤድስ ኢን አፍሪካ ኢትዮጵያ ድርጅት ተጠቃሚ ናቸው። እኚህ እናት በሰው ጓሮ ውስጥ የሚኖሩ እና በላቀች ምድጃ እንጀራ መጋገር ሥራ ላይ የተሰማሩ ነበሩ። ይህ ፕሮጀክት መምጣቱን የሰሙ ሰዎች ባደረጉላቸው ጥሪ እድሉን ማግኘታቸውን ገልፀውልናል። ነገር ግን በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ይገልፁታል። “ራስ አገዝን ልናስፋፋ ነው ብለው 80 ያህል ችግረኛ ሴቶችን ሰበሰቡንና ካላችሁ ቡና መግዣ ላይ አስር ሳንቲም ቆጥቡ አሉን። የጠራችሁን ገንዘብ ልትሰጡን አይደለም እንዴ? ጭራሽ ቆጥቡ ትሉናላችሁ? ብለው ብዙዎቹ ጥለው ሄዱ። እኔ መጨረሻውን ለማየት ስጠብቅ 14 ሰዎች ቀረንና ቁጠባ ጀመርን። በላቀች ምጣድ የሰው ጓሮ ውስጥ እንጀራ እጋግር ስለነበር ባለቤቴም ይጠቅምሻል እንዳትተዪ አለኝ። ከዚያም ከስድስት ወር በኋላ 50 ብር የመጀመሪያዋ ተበዳሪ ሆኜ ተበደርኩ” ይላሉ እኚህ እናት።

የተበደሯትን ብር ተሸቀዳድመው ወደ እቃ የቀየሯት እኚህ ሴት ሌላ አንድ ላቀች ምድጃ በመግዛት ስራቸውን በሰፊው የቀጠሉ ሲሆን፣ የተበደሯትን እየከፈሉ፤ ቀጣይ እየተበደሩ ልጆቻቸውንም እንደልብ ማስተማር ችለዋል። ይሄን ጥንካሬያቸውን ያየው ፕሮጀክቱም ሁለት ኩንታል ጤፍ እና ተጨማሪ ምጣድ ገዝቶ ሸልሟቸዋል። “ልጆቼን ትምህርት ቤት ለመላክም ሆነ ልብስ እና ጫማ ለመግዛት ምንም አይነት አቅም አልነበረኝም። አሁን ግን አንድ ሊጥ አቡኪ እና አንድ እንጀራ ጋጋሪ እስከመቅጠር ደርሻለሁ” ሲሉ ይገልጹታል። ከዚህ በተጨማሪም መንትያ የእህታቸውን ልጆች በቤታቸው ውስጥ በመርዳት እና በማስተማር ላይ ናቸው።

ሥራቸውን እንዲሰሩ ከተደረገላቸው እገዛ በተጨማሪም በማህበራዊ ዋስትና ፕሮግራም ውስጥ እንዲካተቱ መደረጋቸው ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው እኚህ እናት ከልምዳቸው ተነስተው ያስረዳሉ። “ለእኛ ጡረታ ማለት ትልቅ ተስፋ ሰጪ ነው። እኔ ራሴ ስቸገር የነበረው ባለቤቴ የግል ድርጅት ውስጥ ሲሰራ ቆይቶ ምንም ጡረታ ስላልነበረው ነው። ባለቤቴ ሲሞት ጡረታው ቢኖር ኖሮ ልጆቼም እኔም አንቸገርም ነበር። ከአሁን በኋላ እኔም ልጆቼ ነገ ምን ይሆኑ ይሆን ብዬ አልጨነቅም። ይህች ጡረታዬ ለነገ ለልጆቼ መተማመኛ ትሆናቸዋለች” ብለዋል።

እንደ ወይዘሮ አበበች ገለፃ ቀድሞ መስከረም በመጣ ቁጥር ልጆቼን ምን አልብሼ ወደ ዩኒቨርስቲ ልላካቸው የሚለው ጭንቀት አሁን ቀርቷል። እንዲያውም ልጃቸውን በግል እየከፈሉ ማስተማር እና ለልጆቻቸው ላፕቶፕ እስከመግዛት ደርሰዋል። ከጥቃቅን እና አነስተኛ 1ሺህ 500 ብር ተበድረው መክፈል ባለመቻላቸው 4ሺህ ብር እዳ እንደነበረባቸው የገለፁት ወይዘሮ አበበች፤ አሁን ግን እዳቸውን ከፍለው ከሃሳብም ሆነ ከእዳ ነፃ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከምግብ ጎን ለጎን ለስላሳ መጠጦችን የሚሸጡት ወይዘሮ አበበች ማቀዝቀዣ (ፍሪጅ) የሌላቸው በመሆኑ ለስራቸው በአሸዋ እና በባልዲ ውሃ ያቀዘቅዙ የነበረ ሲሆን፣ ፒፕል ኢን ኒድ ቅኝት በሚያደርግበት ወቅት ችግራቸውን ተመልክቶ ማቀዝቀዣ እንደሸለማቸው ገልጸውልናል።

በዚህ ፕሮጅክት ውስጥ የተካተቱት ሴቶች ንግዳቸውን ሊያስቀጥሉ የሚችሉ እገዛዎች በገንዘብ ሳይሆን በቁሳቁስ መልክ እንዲደርሳቸው እንደሚደረግም ከአቶ በረከት መረዳት ችለናል። ጤፍ ለሚያስፈልገው ጤፍ፣ እቃ ለሚያስፈልገው እቃ በሽልማት መልክ መስጠቱ ተጠቃሚዎቹ ገንዘቡን ከታቀደለት አላማ ውጪ እንዳያባክኑት ይረዳልም ተብሏል።

      እነዚህ ሴቶች በዚህ መልኩ በፕሮጀክት ውስጥ በነበራቸው እንቅስቃሴ በአጠቃላይ ሶስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር መቆጠብ የቻሉ ሲሆን ከሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታልም ማስመዝገብ ችለዋል። ከእነዚህ ሴቶች ለማህበራዊ ዋስትና ተቀማጭ የተደረገው ገንዘብም 742ሺ ብር መሆኑ ተገልጿል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1665 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 949 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us