ሴቶችን የሚጎዱ ልማዳዊ ድርጊቶ

Wednesday, 08 October 2014 13:02

 

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትን የአፍሪካ የሴቶች መብት ፕሮቶኮል “በሴቶች ሰብዓዊ መብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጣቸውን ድርጊቶች የሚፃረሩ” ሲል ያስቀምጣቸዋል። እነዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ታዲያ በዓለማችን በተለያዩ ሀገራት አሁንም ድረስ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ሲሆን፤ ዋንኛ የድርጊቶቹ ተጠቂዎች ደግሞ ሴቶች እና ህጻናት ናቸው። ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ታዲያ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ስርጭቱም ሆነ ስፋቱ ይጨምራል።

የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ይፋ ያደረገው እና በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ የሚያጠነጥን ጥናታዊ ፅሁፍ እንደሚያመለክተው በተለያየ መንገድ በሀገራችን የሚተገበሩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶችን እና ህጻናትን እየጎዱ ይገኛሉ።

ጥናቱ እንዳመለከተው በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በሴቶች እና ህጻናት ላይ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች 140 ደርሰዋል። ይህ ቁጥር ከዛሬ 15 ዓመት በፊት እ.ኤ.አ. 1998 ዓ.ም 88 ብቻ ነበር። ይህ የሚያመለክተው ታዲያ በሴቶች እና በህፃናት ላይ እየተተገበሩ ያሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ቁጥር እና አይነት ስልጣኔ በተስፋፋበት በአሁኑ ወቅትም እያሻቀበ መምጣቱን ነው። በሚገርም ሁኔታ ደግሞ ከእነዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መካከል 90 በመቶዎቹ በሴቶች እና ህጻናት ላይ አሉታዊ አካላዊ እና አእምሯዊ ተፅዕኖ መፍጠራቸው ነው።

በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚተገበሩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሀገራችን የተለያየ አይነት ያላቸው ቢሆንም እነዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ከሴቶች ፣ ከህፃናት እንዲሁም ከፆታ እና እድሜ ጋር ተያያዥነት ያላቸው በሚለው ተከፍለው ተቀምጠዋል። እነዚህ ክፍፍሎችም የየራሳቸው የሆነ ጎጂ ልማዳዊ ተግባራት በስራቸው ተደልድለዋል። እነዚህም የሴት ልጅ ግርዛት፣ እንጥል መቧጠጥ የወተት ጥርስን መንቀል፣ ጠለፋ እና ያለ እድሜ ጋብቻ በሚለው ይዘረዘራሉ።

የሴት ልጅ ግርዛት በሀገራችን ረጅም እድሜን ያስቆጠረ እና ከጥንት ጀምሮ ሲተገበር የቆየ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እንደሆነ መዛግብት ያመለክታሉ። ይህ የሴት ልጅ ግርዛት በሀገራችን ባሉ ክልሎች እንኳን የሚከናወነው በተለያየ መልኩ ነው። ያም ሆነ ይህ ታዲያ ለዚህ ለሴት ልጅ ግርዛት የሚነሳው ምክንያት ሁሉንም የሚያግባባ ይመስላል። ለዚህ ለሴት ልጅ ግርዛት እንደምክንያት የሚነሱት አንደኛው የሴቷን የወሲብ ፍላጎት ለመቆጣጠር የሚለው ሲሆን፣ በዚህም ያልተገረዘች ሴት ከፍተኛ ወሲባዊ ፍላጎት ስለሚኖራት ከባሏ ጋር ላትረጋ ትችላለች የሚል ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘም ሴት ልጅ ከተገረዘች በወሲብም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ለባሏ ተገዢ ትሆናለች የሚል አመለካከት እንደምክንያት ይቀመጣል።

ሌላው ለሴት ልጅ ግርዛት እንደ ምክንያት የሚቀመጡት ነገሮች በአብዛኛው ባህላዊነት ያደላባቸው ናቸው። እነዚህም ያልተገረዘች ሴት እቃ ትሰብራለች፣ አይነ አውጣ ትሆናለች፣ ዝርክርክነት ይታይባታል፣ ቁጥብ እና አይነ አፋር አትሆንም የሚሉት አመለካከቶች እንደ ምክንያት ይቀመጣሉ። ከዚህ በተጨማሪም የሴት ልጅ ግርዛት ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ በመሆኑ ያልተገረዘች ሴት ባል አታገኝም፣ መሳቂያ፣ መሳለቂያ ትሆናለች የሚል እምነት አለ። እምነት ነክ የሆኑ ምክንያቶችን የሚጠቅሱ አካላት ደግሞ የሚያስቀምጡት ፈጣሪ ያልተገረዘችን ሴት ፀሎት አይሰማም፣ ስትሞትም የቀብር ስነስርዓቷ ስርዓቱ በሚያዘው ደንብና ልማድ መሰረት አይፈፀምም እንዲሁም ሴት ልጅን አለማስገረዝ ከፈጣሪ ዘንድ ቁጣን ያመጣል የሚል አመለካከት እንዳለ የሃይማኖት አባቶችን ዋቢ ያደረጉ መረጃዎች ያመለክታሉ።

እነዚህን የተለያዩ ምክንያቶች በመደርደር በሴቶች ላይ ግርዛት ሲፈፀም ታዲያ ዋንኛ ተዋንያኑ ሴቶች ራሳቸው ናቸው። በዚህ ሂደት ውስጥ የችግሩን ፅዋ የተጎነጩ ሴቶች ነገም ተመልሰው ልጃቸውን፣ እህታቸውን አሊያም በዙሪያቸው ያለችን ሴት ለዚህ አስከፊ ድርጊት አሳልፈው ይሰጣሉ። ይህ የሴት ልጅ ግርዛት ታዲያ በሴቷ ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ነው የሚያደርሰው።

የሴት ልጅ ግርዛት በሚፈፀምበት ወቅት በሴቷ ላይ ከሚደርሰው ስነ-ልቦናዊ ቀውስ ጋር በተያያዘ በግርዛቱ ወቅትም ሆነ ከግርዛቱ በኋላ በሚሰማት ፍርሃት እና መሸማቀቅ ምክንያት ሴቷ ፈሪ፣ ሆደ ባሻ፣ ተጠራጣሪ እና በራሷ ለመተማመን የምትቸገር ትሆናለች። በተጨማሪም በግብረስጋ ግንኙነት ወቅት በሚሰማት ህመም ምክንያት ለባሏ መስጠት ያለባትን ወሲባዊ እርካታ መስጠት ባለመቻሏ፤ እርሷም እርካታን ማግኘት ባለመቻሏ ስሜቷ በጣም ይጎዳል።

ሌላው የዚህ የሴት ልጅ ግርዛት አሉታዊ ጎን ደግሞ ድርገቱ ከሚያስከትለው ተፅዕኖ የተነሳ የተገረዙ ሴቶች ከማህበረሰቡ ጋር ለመቀላቀል ድፍረት በማጣት ማህበራዊ ተሳትፏቸው በጣም የተወሰነ እንዲሆን ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪም ሴቷ በቤቷ ውስጥ ያላትን የአመራር ድርሻ በአግባቡ መወጣት ስለሚያቅታት ትዳሯን እና ቤተሰቧን በአግባቡ ለማስተዳደር አትችልም። በዚህም ሳቢያ ውሎ አድሮ የትዳር መፍረስ እና የቤተሰብ መበተን ያጋጥማታል።

እ.ኤ.አ በ2011 በሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ እና እድሜያቸው ከዜሮ ዓመት እስከ 14 ዓመት ከሆናቸው ህፃናት እና ታዳጊዎች መካከል 23 በመቶዎቹ ተገርዘዋል። በዚህ በሴት ልጅ ግርዛት ታዲያ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘው የአፋር ክልል ነው። ይኸውም 60 በመቶ የሚሆኑት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ህጻናት እና ታዳጊዎች ሴቶች ተገርዘዋል። ከአፋር ክልል በመቀጠል ደግሞ የአማራ እና ሶማሊያ ክልል የተቀመጡ ሲሆን፤ ይኸውም በአማራ ክልል ከሚገኙ ከ14 ዓመት በታች ያሉ ህፃናትና ታዳጊዎች መካከል 47 በመቶዎቹ ሲገረዙ በሶማሊያ ክልል ከሚገኙት ደግሞ 31 በመቶዎቹ ተገርዘዋል። ይህ ድርጊት በሀገሪቱ የከተማ እና ገጠር አካባቢዎች ከፍተኛ ልዩነት እንዳላቸው ተመልክቷል። ይኸውም በገጠር ከሚገኙ ህጻናትና ታዳጊዎች 24 በመቶዎቹ እና በከተማ ከሚገኙት 15 በመቶዎቹ የተገረዙ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከሴት ልጅ ግርዛት በተጨማሪም በተለይ በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ የአሳሳቢነቱ ደረጃ እያሻቀበ የመጣው ያለ እድሜ ጋብቻ ነው። በተለይ በገጠር የሀገሪቱ ክፍሎች ይህ ያለ እድሜ ጋብቻ በስፋት የሚተገበር መሆኑ ተገልጿል። ለአብነት ያህልም በአማራ ክልል ያለው ያለ እድሜ ጋብቻ 44 ነጥብ 8 በመቶ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል ደግሞ 34 ነጥብ 1 በመቶ ነው። ይህ ቁጥር በቤንሻንጉል ጉምዝ 31 ነጥብ 9 በመቶ ሲሆን፣ በመዲናችን አዲስ አበባም 32 ነጥብ 3 በመቶ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል።

ያለ እድሜ ጋብቻ በቤተሰብ ፍቃድ እንዲሁም በጠለፋ የሚካሄድ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ቢሆንም፣ ጠለፋ በራሱ ደግሞ ሌላው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እንደሆነ ተቀምጧል። ጠለፋም ልክ እንደሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ሁሉ ከከተማ ይልቅ በገጠር የሀገሪቱ ክፍሎች በስፋት የሚዘወተር ተግባር ነው። ይህ ድርጊት በተለይ በደቡብ የሀገራችን ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶችን እየጎዳ መሆኑ ነው የተገለፀው። ይህም 17 ነጥብ 5 በመቶ መሆኑ ተቀምጧል። በመቀጠልም የሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ሲሆን ይኸውም 11 ነጥብ 5 በመቶ ነው። ትግራይ ክልል በ5 ነጥብ 9 በመቶ እንዲሁም አማራ ክልል በ5 ነጥብ 5 በመቶ ተከታትለው ተቀምጠዋል።

ከላይ በተጠቀሱት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በተጨማሪም ሴት ልጅ ምጥ በሚይዛት ወቅት ሴቷን ማወዛወዝ፣ “ሴቶች የማይበሉት”ን ምግብ ለይቶ ማስቀመጥ፣ የምታምጥ ሴትን ቶሎ እንድትወልድ በማለት ማሸት እንዲሁም ሴት ልጅ በወር አበባ አልያም በወሊድ ምክንያት ደም ሲፈሳት ከሌላው ሰው ተገልላ እንድተቆይ ማድረግን የመሳሰሉ ተግባራትም በጎጂነታቸው የተቀመጡ ናቸው።

እነዚህ ተግባራት በሀገሪቱ ለረጅም ዓመታት ሲተገበሩ ከመቆየታቸው የተነሳ የተለመዱ የእለት ተእለት ተግባራት ተደርገው እየተወሰዱ እንደሆነ ነው ጥናቱ የሚያመለክተው። ሴቶቹም ቢሆኑ ተግባራቱ በእነርሱ ላይ ሲፈፀሙ ለምን ተፈፀሙብኝ ከማለት ይልቅ በሴትነታቸው ምክንያት ሊጋፈጧቸው የሚገቡ ተግባራት እንደሆኑ አድርገው ነው የሚቀበሉት።

እነዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲፈፀሙ የሚያደርጉት ምክንያቶችም በባለሞያዎች በተደረገ ጥናት ተለይተው ተቀምጠዋል። ምክንያቶቹ በአብዛኛው ስር የሰደዱ ሆነውም ተገኝተዋል። ከእነዚህ ስር ሰደድ ምክንያቶች መካከልም በማህበረሰቡ ውስጥ ስለሴቶች እና ህጻናት ያለው የተዛባ አመለካከት፣ ሰፊ የሆነ የሴቶች እና ወንዶች የስልጣን (ኃላፊነት) ክፍተት፣ እንዲሁም ሴቶች እና ህጻናት በኢኮኖሚ፣ በትምህርት እንዲሁም በስልጠና ብቁ ሆነው አለመገኘት የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ አመለካከቶች እነዚህ ጎጂ ልማዳዊ ተግባራት እንዲፈፀሙ እንደ ምክንያት ተቀምጠዋል።

ምክንያታቸው ያም ሆነ ይህ እነዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ታዲያ በተለያየ መልኩ በሴቶች እና ህጻናት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖን ያሳርፋሉ። ከእነዚህ ተፅዕኖዎች ውስጥ ቀዳሚው በጤናቸው ላይ የሚፈጥ ችግር ሲሆን፣ ይኸውም በወሊድ ወቅት ለሚፈጠር ህመም፣ ደም መፍሰስ፣ የምጥ መጠንከር እና ለመሳሰሉት ችግሮች መጋለጥ፣ ለፊስቱላ እና ለኤች አይቪ በሽታዎች መዳረግ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም የቤተሰባቸውን ቁጥር መመጠን አለመቻል፣ የጤና አገልግሎት አለማግኘት እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል።

    ሌላው ችግር ደግሞ የስነ-ልቦና መቃወስ ችግር ነው። ይኸውም ከላይ ከተጠቀሱት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አንዱ ወይም ከአንድ በላይ የደረሰባት ሴት ለከፍተኛ ጭንቀት፣ ከሌሎች ለመገለል፣ ከትምህርት ገበታ ለመነጠል እና ተስፋ ለመቁረጥ ትዳርጋለች። ከዚህ ጋር በተያያዘም ሴቷ ለወደፊት ሊኖራት የሚችለውን አኗኗር ለመወሰን እንዳትችል እና ሁልጊዜም የበታችነት ስሜት እንዲያድርባት ያደርጋታል።

ይምረጡ
(14 ሰዎች መርጠዋል)
3963 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 880 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us