ተፈጥሮ ፊቷን ስታዞር

Thursday, 16 October 2014 14:31

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ለተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት አንዷ ናት። ከእነዚህም አደጋዎች መካከል ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ረሀብ፣ የመሬት መንሸራተት እና የመሳሰሉት ይገኙበታል። እነዚህ አደጋዎች ታዲያ ባለፉት በርካታ ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ቀጥፈዋል። ያም ሆኖ ግን ለእነዚህ አደጋዎች ብዙም ትኩረት ሳይሰጥ ቆይቷል። ይህ አለም አቀፉ አደጋ ቅነሳ ቀን በየዓመቱ ጥቅምት 3 ቀን ይከበራል። ይህ ቀን ከትናንት በስቲያ ለ5ኛ ጊዜ “ለአደጋ አይበገሬነት በህይወት ዘመን (Resilience is for life) በሚል መሪ ቃል በሂልተን ሆቴል ተከብሯል።

በሀገራችንም ሆነ በዓለም ሀገራት ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች የሚከሰቱ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ ግን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱት ሁለቱ ተፃራሪዎች ድርቅ እና ጎርፍ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። እነዚህ አደጋዎችም በተደጋጋሚ በመከሰት በህዝብ እና በሀብት ንብረት ላይ ሰፊ ጉዳት በማድረስ ይታወቃሉ። አደጋዎች ታዳጊ እና ያደጉ ሀገራት ሳይሉ የሁሉንም ሀገራት ህዝብ የመጉዳት እድላቸው ከፍተኛ ቢሆንም፣ በተለይ ታዳጊ ሀገራት እነዚህን አደጋዎች ለመቋቋም በቂ የሆነ አቅም ስለሌላቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሀብታቸውን እና የብዙ ህዝባቸውን ህይወት በቀላሉ ያጣሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በአለማችን ላይ እነዚህ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ዓይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በአሁኑ ወቅት አለምን በአብዛኛው እያስጨነቋት የሚገኙት የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጎርፍ፣ ድርቅ፣ ጦርነት፣ የበሽታዎች ወረርሽኝ፣ የመሬት መንሸራተት፣ የእሳት ቃጠሎ፣ ውርጭ፣ በረዶ፣ የሰብል እና የእንሳሰት በሽታዎች፣ የእርስ በእርስ ግጭት እና የትራፊክ አደጋዎች ናቸው።

እነዚህ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች አይነታቸው ብቻም ሳይሆን፤ በሰው ልጅ ህይወት እና በሀገር ሀብት ላይ የሚያደርሱት ጥፋትም የዚያኑ ያህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው የመጣው። የተባበሩት መንግስታት የአደጋ ቅነሳ ስትራቴጂ በ2001 ይፋ ያደረገ መረጃ እንደሚያመለክተው እ.ኤ.አ ከ2000 እስከ 2006 ዓ.ም ባሉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ብቻ በአለም አቀፍ ደረጃ 130ሺ ሰዎች በአደጋ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በአደጋ ምክንያት የወደመው ሀብት መጠንም 235 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት መሆኑ ተገልጿል። በተጨማሪም በ2007 (እ.ኤ.አ) ብቻ በአለም አቀፍ ደረጃ 10ሺ ሰዎች በአደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ በዚሁ አመት 54 ቢሊዮን ዶላር ንብረት በአደጋ ምክንያት ሊወድም ችሏል ሲል መረጃው ጨምሮ ገልጿል።

በኢትዮጵያ ያለውን መረጃ ስንመለከት ደግሞ የዓለም አቀፉ የአደጋ መቆጣጣሪያ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1980 እስከ 2010 ዓ.ም በሰው ልጅ እና በኢኮኖሚ ላይ በአደጋ ምክንያት የደረሰ ጥፋትን አስመልክቶ ያወጣውን መረጃ መመልከት ይቻላል። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ በሀገራችን 86 ያህል የተለያዩ አደጋዎች የተከሰቱ ሲሆን፣ በእነዚህ አደጋዎች ምክንያትም 313 ሺ 486 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ይህ ማለትም በአማካይ 10ሺ 112 ሰዎች በዓመት በአደጋ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል። በአደጋ ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪም በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በአደጋዎቹ ምክንያት በ57 ሚሊዮን 382ሺ 354 ሰዎች ላይ የተለያዩ ችግሮች ደርሰውባቸዋል። ይህም ሲሰላ በአማካይ በዓመት 1 ሚሊዮን 851ሺ 44 ሰዎች በእነዚህ አደጋዎች ሳቢያ ችግር ደርሶባቸዋል።

እ.ኤ.አ. በ2006 ዓ.ም 364 ሰዎች የተፈጥሮ አደጋ በሆነው ጎርፍ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ በዚሁ ዓመት በጎርፍ ምክንያት 361ሺ 600 ሰዎች በተለያየ መልኩ በጎርፍ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፤ በድርቅ ምክንያትም በ2008 ዓ.ም 6 ሚሊዮን 400ሺ ሰዎች የተለያዩ ጉዳቶች የደረሱባቸው ሲሆን፣ በ2007 ዓ.ም ደግሞ 6 ሚሊዮን 200 ሺ ሰዎች በዚሁ በድርቅ ተጎድተዋል።

ለአህጉራችን አፍሪካ እ.ኤ.አ ከ1972 እስከ 1973 ዓ.ም ድረስ ያለው ጊዜ በጣም አሰቃቂው ጊዜ እንደነበረ ነው የተገለፀው። ይህም የሆነበት ምክንያት የአህጉሪቱ ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምስራቅ እና መካከለኛው ክፍል ክፉኛ በድርቅ እና በረሀብ የተጠቃ በመሆኑ ነበር። በእነዚህ የአህጉሪቱ ክፍሎች በተፈጥሮ አደጋዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩት ሀገራትም ቦትስዋና፣ ቡርኪናፋሶ፣ ቻድ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ፣ ሞሪታኒያ እና ሞዛምቢክ ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን የዓለም ምግብ ድርጅት በ2001 ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል። ከእነዚህ ሀገራት መካከልም ኢትዮጵያ በሀጉሪቱ ከ1972 እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ ባሉት አስከፊ ጊዜያት ውስጥ በተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ቀዳሚዋ ሆናለች።

በሀገሪቱ በ1972 በተከሰተ ረሀብ 600ሺ ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ በቀጣዩ 1973 ዓ.ም በተከሰተ ድርቅ 100ሺ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በ1974 ዓ.ም ደግሞ 200ሺ ሰዎች በድርቅ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ፣ ይህም በእነዚህ አመታት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚዋ የተፈጥሮ አደጋ ተጠቂ መሆኗን ያመለክታል።

በየዓመቱ የአደጋዎች አይነት እና የሚያደርሱት ጥፋት እያሻቀበ በመምጣቱ ታዲያ አደጋውን ማስቀረት ባይቻልም አስቀድሞ ለመከላከል እና ከተከሰተ በኋላም አደጋውን እና የአደጋውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚያስችሉ መንገዶችን ማመቻቸት አስፈላጊ ብቻም ሳይሆን አስገዳጅ ሆኗል። በዚህም መሰረት ሀገራት የየራሳቸውን ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው። አደጋዎች የሚፈጠሩበትን ጊዜ እና ሁኔታ ከመገመት የዘለለ ትክክለኛውን ማወቅ አዳጋች እንደመሆኑ ሀገራት አደጋዎችን ለመቋቋም የሚወስዷቸው እርምጃዎች ከአደጋው መከሰት አስቀድሞ የሚደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች፣ የአደጋ ጊዜ ዝግጅት እንዲሁም ድህረ አደጋ ዝግጅቶችን ያካተቱ ናቸው።

በኢትዮጵያ የአደጋ ሥራ አመራር (Disaster Management) እ.ኤ.አ ከ1973 ጀምሮ ነበር የተቋቋመው። በዚያ ጊዜም የእርዳታ እና ማገገሚያ ኮሚሽን በሚል ስያሜ የተቋቋመ ሲሆን፤ አላማውም ለአደጋዎች ምላሽ መስጠት ነበር ። ይህ ኮሚሽን በ1975 ዓ.ም የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽን በሚል የተቀየረ ሲሆን፣ ይህ አዲሱ ኮሚሽንም አላማው አድርጎት የነበረው ለልማታዊ እንቀስቃሴዎች እርዳታ ማድረግን ነበር። በመቀጠልም ይህ ኮሚሽን የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኤጀንሲ እና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ቢሮ ተብሎ እ.ኤ.አ. በ2004 ዓለም በሁለት ተከፈለ። በዚህን ጊዜ የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኤጀንሲ የአስቸኳይ ጉዳዮች ምላሽ እንዲሰጥ ሲደረግ የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ቢሮ ደግሞ ለከፍተኛ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ ምላሽ እንዲሰጥ ተወስኖ ነበር።

በሀገሪቱ በተደረገ የቢፒአር (Business process reengineering) መሠረት አደጋ መከላከልና ዝግጁነት እና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ተብሎ በአንድ ተቋም የተደራጀ ሲሆን፤ ዋና ትኩረቱ ያደረገውም ለአደጋዎች ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እና በአደጋ ምክንያት የሚከሰቱ ቀውሶችን መቆጣጠርን ነው። ይህ ተቋም በተለያየ መልኩ የተፈጥሮ አደጋዎች ከመከሰታቸው አስቀድሞ ቅድመ ማስጠንቀቂያዎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ተጎጂዎችን የማቋቋም ስራዎች እየተሰራ ይገኛሉ።

በ1998 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ተከስቶ የነበረውን የጎርፍ አደጋ ተከትሎ በ1999 ዓ.ም የሰው ህይወት ሊታደጉ የሚችሉ ባለሞያዎችን የማሰልጠን ተግባር የተከናወነ ሲሆን በዚህም 165 ነፍስ አድን ሰራተኞችን ማሰልጠን ተችሏል።

በሀገራችን በ2014 ዓ.ም ብቻ ለምግብ እና ምግብ ነክ ላልሆኑ ነገሮች የሚያስፈልገው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ 403 ሚሊዮን ዶላር እንደሚገመት ነው የተገለፀው። ከዚህ በተጨማሪም ከምግብ ውጪ ለሆኑ አስቸኳይ እርዳታ 68 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግም ነው የተገለፀው። እነዚህን የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ፈላጊ አካባቢዎች ባለፈው የመኸር ወቅት ለይቶ ማሰቀመጡንም የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት እና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ይፋ አድርጓል።

     ከዚህ በተጨማሪም ዘርፉ አደጋዎች ሊከሰቱ የሚችሉባቸውን ስፍራዎች፣ የአደጋዎች አይነቶች እና ሊያደርሱ የሚችሉትን ጥፋት በመለየት እና ለህብረተሰቡ የማሳወቅ ስራዎችን ይሰራል። በቅድመ ማስጠንቀቂያ ተግባሩም አደጋውን የማሳወቅ እና አስቀድሞ የመቆጣጠር ስራዎችን ይሰራል። ከዚህ በተጨማሪም አደጋዎች ከተከሰቱ በኋላ ህዝቡን መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልግ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እና የመሳሰሉትን ነገሮች የማሟላት ስራ ይሰራል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1657 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1034 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us