በኢትዮጵያ የስኳር ሕመምተኞች ቁጥር እስከ ሶስት በመቶ ይደርሳል

Wednesday, 22 October 2014 12:40

 

በኢትዮጵያ በስኳር ህመም ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር በ2003 እ.ኤ.አ. 21ሺ መድረሱን ዲያቤቲስ አትላስ ሶስተኛው እትም ባወጣው መረጃ ይፋ አደርጎ ነበር። የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ በ2000 ዓ.ም እ.ኤ.አ የስኳር ህመም ያለባቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥር 800ሺ እንደነበር ይፋ አድርጎ ነበር። ይህ አካሄድ አሁን ባለበት ሁኔታ ከቀጠለ ቁጥሩ እ.ኤ.አ. በ2030 ወደ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ያሻቅባል ሲልም ግምቱን አስቀምጧል። ከኢትዮጵያ ህዝብ ከ2 በመቶ እስከ 3 በመቶ የሚሆነውም የስኳር ህመምተኛ ነው።

የፊታችን ህዳር ወር የሚከበረውን የዓለም የስኳር ህመም ቀን አስመልክቶ ባለፈው ሐሙስ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን፤ በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ስኳር ህሙማን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር አህመድ ረጃ በሀገራችን ለስኳር ህመም የሚጋለጡ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱን ገልጸው ነበር።

የስኳር ህመም በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት አየተስፋፋ እና የብዙዎችን ህይወትም እየቀጠፈ ያለ አሳሳቢ ህመም እየሆነ መምጣቱም እየተገለፀ ነው። ከዓለም አቀፉ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ከዓለም ህዝብ 5 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆነው (246 ሚሊዮን) ሰዎች ከስኳር ህመም ጋር የሚኖሩ ናቸው። ከእነዚህ ከስኳር ህመም ጋር ከሚኖሩ ሰዎች ውስጥ ደግሞ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት በታዳጊ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው የጉዳዩን አሳሳቢነት ከፍ አድርጎታል። በተያያዘም እስከ 2025 ዓ.ም የዓለም ስኳር ህመምተኞች ቁጥር 380 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። ይህ ማለት ደግሞ ከአለም ወጣቶች መካከል 7 ነጥብ 1 በመቶዎቹ በስኳር ህመም ይጠቃሉ ማለት ነው። ይህ ቁጥርም ታዲያ በሚያሳዝን መልኩ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የሚስተዋል መሆኑ ነው።

የስኳር ህመም በአሁኑ ሰዓት ሰዎችን ለዓይነስውርነት፣ ለስትሮክ እና ከኩላሊት ጋር ለተያያዘ በሽታ ከሚያጋልጡ ህመሞች ቀዳሚው ሆኖ ተቀምጧል። በየጊዜው የሚመዘገቡ አዳዲስ የህመሙ ተጠቂዎች ቁጥርም እያሻቀበ መጥቷል። በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ የአዳዲስ የህመሞቹ ተጠቂዎች ቁጥር በማደግ ላይ ባሉ ሀገራተ በ200 በመቶ የሚጨምር ሲሆን፤ በአደጉት ሀገራት ደግሞ በ45 በመቶ የመጨመር ሁኔታ ይኖረዋል ተብሏል።

የስኳር ህመም በማንኛውም የእድሜ ክልል እና ሁኔታ ውስጥ ያለን ሰው የሚያጠቃ ህመም ነው። በተለይ ግን ነፍሰ ጡር ሴቶችን በሁለት መልኩ ያጠቃል። ይኽውም በቅድመ እርግዝና እና በእርግዝና ወቅት ናቸው። ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከ2 እስከ 5 በመቶ የሚሆኑ ነፍሰጡር እናቶች የስኳር ህመም ይታይባቸዋል። ከዚህ ውስጥም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ በእርግዝናው ወቅት የሚከሰት የስኳር ህመም ነው። ይህ አይነቱ በእርግዝና የመጀመሪያ ወቅት የሚከሰት የስኳር ሀመም በብዛት የሚስተዋለው በተወሰኑ የስኳር ህመም ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ በሆኑ ዝርያ ውስጥ የተካተቱ እናቶችን ነው። ይህ ማለት ደግሞ አፍሪካዊ የዘር ግንድ ያላቸው፤ የፓስፊክ ደሴቶች ነዋሪዎች፣ መሠረተ አሜሪካውያን (Native Americans)፣ የእስያ ዝርያ ያላቸው ህዝቦች፣ የላቲን አሜሪካ ዝርያ ያላቸው ህዝቦች ላይ ህመሙ በብዛት ሊከሰት ይችላል።

ከእርግዝና ጋር በተያያዘ የሚከሰተው የስኳር ህመም በፅንሱና እናትየዋ ላይ የተለያዩ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። ከእነዚህ ችግሮች መካከልም የፅንስ ውርጃ፣ በማህፀን ውስጥ የፅንስ ድንገተኛ ሞት፣ የፅንስ አካል ክፍሎች ላይ የሚከሰቱ የአካል ጉዳቶች ይጠቀሳሉ። ከዚህ በተጨማሪም በእናትየዋ ላይ በማህጸን የመውለድ ችግር፣ በእናትየዋ ላይ የደም ግፊት መጨመር፣ በስኳር ህመም ምክንያት የተከሰቱ የአይን ችግሮች መባባስ፣ የሽርት ውሃ መብዛት እና የመሳሰሉት ችግሮች ይከሰታሉ።

በአብዛኛው ጤናማ ባልሆነ አኗኗር የሚከሰተው የስኳር ህመም በሀገራችን ያለው ስርጭት በሀገር አቀፍ ደረጃ 2 በመቶ ይሆናል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፤ እድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ዘንድ ግን ስርጭቱ እስከ 5 በመቶ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። በኢትዮጵያ ያለው የስኳር ህመም ስርጭት በአብዛኛው የተመጣጠነ ምግብ ካለማግኘት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ከሚገኙ የስኳር ህሙማን መካከል አስፈላጊውን ህክምና የሚያገኙት ከግማሽ በታች እንደሆኑ በ2012 መጨረሻ ይፋ የሆነ ጥናት ውጤት ያመለክታል።

የስኳር ህመም ከጥንት ጀምሮ በዓለም ላይ ሲስተዋል የነበረ ቢሆንም፤ በተለይ ዓለም በቴክኖሎጂ በተለወጠችበት በአሁኑ ወቅት ከተጠበቀው በላይ ጭማሪ እያሳየ መሆኑን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጤና ተቋም ይፋ አድርጓል። ተቋሙ ይፋ ካደረጋቸው ምክንያቶችም ቀዳሚው በአሁኑ ወቅት ሰዎች በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ መሆናቸው፣ ህይወት በሩጫ እና በጥድፊያ የተሞላች በመሆኗ ሰዎች ስለሚመገቡት ምግብ እና አመጋገባቸው እንዲሁም ስለጤንነታቸው ብዙም የማይጨነቁ እና የማይጠነቀቁ መሆናቸው እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ለኬሚካሎች ያላቸው ተጋላጭነት እንደምክንያት ተቀምጠዋል። ከዚህ በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ ሰዎች የሚያከናውኗቸው ስራዎች በአብዛኛው አንድ ቦታ መቀመጥን የሚፈልጉ መሆናቸው እና ባለው የጊዜ ጥበት የተነሳ ሰዎች ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዝቅተኛ ግምት መስጠታቸው እንደምክንያት የተቀመጡ ናቸው።

ከላይ የጠቀስናቸው ለስኳር ህመም እንደምክንያት የተጠቀሱት ጉዳዮች በአጠቃላይ ለስኳር ህመም መንስኤዎቹ ናቸው። ነገር ግን በአብዛኛው ለስኳር ህመም ተጋላጭ ናቸው ተብለው ከተቀመጡ የሰው ዝርያዎች መካከል የሆኑት አፍሪካውያን ደግሞ የራሳቸው ምክንያት አላቸው። ከእነዚህ አፍሪካውያንን ለስኳር ህመም ከሚያጋልጡ ምክንያቶች መካከልም በቤተሰብ የሚተላለፍ ህመም፣ ዝቅተኛ ክብደትን ይዞ መወለድ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ ብዙ ተመግቦ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ እና የመሳሰሉት ተጠቅሰዋል። ከዚህ በተጨማሪም የከተሜነት መስፋፋት እና ከተለያዩ ንጥረ ነገሮች የሚመረቱ ምግቦች መስፋፋት እንደምክንያት ይነሳሉ።

በኢትዮጵያ ባለው ያለመማር ችግር አንጻር የስኳር ህመም በምን ደረጃ ላይ ይገኛል የሚለውን እርግጠኛ ሆኖ ለመመለስ አስቸጋሪ እንደሆነ ባለሞያዎች ይናገራሉ። ሌላው ቀርቶ ራሳቸው የስኳር ህመምተኞች የህመማቸው ሁኔታ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የማወቅ ችግር እንዳለባቸው ነው የተገለፀው።

በ2005 እ.ኤ.አ በኢትዮጵያ ጆርናል ኦፍ ሄልዝ ዴቪሎፕመንት በተደረገው ጥናት እንደተመለከተውም በሀገራችን ባሉ የስኳር ህመምተኞች ላይ ከስኳር ህመም ጋር በተያያዘ የሚከሰቱት በሽታዎች የደም ግፊት እና ከህመሙ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የአይን ህመም ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ምክንያቱ ምንም ይሁን ምንም አብዛኞቹ የህመሙ ተጠቂዎች ወደ ህክምና የመሄድ ባህላቸው አነስተኛ መሆኑ ተገልጿል። ጆርናሉ እንደሚያመለክተውም ጥናት ከተደረገባቸው ውስጥ 86 ነጥብ 9 በመቶዎቹ ብቻ ሁኔታቸውን በመደበኛነት ይከታተላሉ። ከእነዚህ ከሚከታተሉት ውስጥም 20 ነጥብ 6 በመቶዎቹ ብቻ በወር አንዴ ወደ ጤና ተቋም ይሄዳሉ። 61 ነጥብ 8 በመቶዎቹ ከአንድ እስከ ሶስት ወራት ውስጥ ወደ ጤና ተቋም የሚያመሩ ሲሆን፤ 13 ነጥብ 6 በመቶዎቹ ደግሞ በሶስት ወር እና ከዚያ በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ ወደ ጤና ጠቋም ያመራሉ።

     የስኳር ህመም በአብዛኛው የሚከሰተው የአኗኗር ዘይቤዎችን ምቹ ባለማድረግ ነው። የአመጋገብ ዘይቤን ጠብቆ አለመመገብ፣ የተመጣጠነ ምግብን አለመመገብ እና በየእለት ተዕለት ህይወት ውስጥ የአካል እንቅስቃሴን አለማካተት በአብዛኛው ለዚህ ህመም የሚያጋልጡ ናቸው። ብዙዎች ህመሙን እንደ ሀብታም በሽታ ቢቆጥሩትም፤ ህመሙ ግን በሁሉም የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችን ያጠቃል። በመሆኑም ሁሉም ሰው በያለበት የኑሮ ደረጃ ህመሙን በቀላሉ መቆጣጠር እንደሚችል ነው ባለሞያዎች የሚመክሩት።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1531 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 917 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us