በዓይን የመጣ. . .

Wednesday, 29 October 2014 14:50

          

የአለም እይታ ቀን በአለም ለዘጠነኛ ጊዜ፤ በሀገራችን ደግሞ ለስምንተኛ ጊዜ «በቀላሉ ልናስወግደው በምንችለው ትራኮማ የሚመጣ አይነ ስውርነት ይብቃ» በሚል መሪ ቃል በአማራ ክልል ግህምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ ተከብሮ ውሎ ነበር። በእለቱ ለ800ሺ ሰዎች ዚትራኮማክስ የተባለው የትራኮማ መድሐኒት እደላ ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪም በጤና ጣቢያዎች ችግሩ ላለባቸው ሰዎች የአይን ቀዶ ህክምና ተደርጎላቸዋል።

ወጣት እንወይ ደሳለኝ በ2007 ዓ.ም የ11ኛ ክፍል ትምህርቷን ለመከታተል በትምህርት ገበታዋ ላይ ብትገኝም በአይኗ ላይ በገጠማት ችግር ምክንያት ክፍል ውስጥ ተቀምጣ ጥቁር ሰሌዳው ላይ የሚፃፈውንም ሆነ በመፅሐፍ እና ደብተሯ ላይ ያሉትን ፊደሎች ማንበብ አልቻለችም። በዚህም ሳቢያ ከትምህርት ገበታዋ ርቃለች። በዚህ ዘመቻ ላይ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ሊያገኙ ከመጡ ሰዎች መካከል ታዲያ ወጣቷ እንወይ ትገኛለች።

የወጣት እንወይ ወላጅ እናት እንደገለጹልን ከሆነ እንወይ ይህን የአይን ቀዶ ህክምና ስታደርግ ይሄ ሁለተኛዋ ነው። ባለፈው ዓመት እንደዚሁ ዘመቻ ሲደረግ በቀኝ አይኗ ላይ ቀዶ ህክምና ተደርጎላት ነበር። ህክምና የተሰጠው የቀኝ አይኗ ድኖላት ትምህርት መቀጠል ችላ ነበር። ዘንድሮ ደግሞ ሁለተኛውን አይኗን እንደታመመች የሚናገሩት የእንወይ እናት፤ በአይኗ ላይ የተፈጠረው ችግርም ማሳከክ፤ አንዳንድ ጊዜ ማቃጠል፣ እንባ መፍሰስ፤ ወረቀትም ሆነ ኮምፒውተር በምታይበት ወቅት ማንፀባርቅ እንዲሁም ፊደሎቹንም መመልከት አለመቻል መሆናቸውን ነግረውናል። በዚህ መልኩ ለተወሰነ ጊዜ ትምህርቷን ለመቀጠል ብትሞክርም ህመሙ እየባሰባት እና ችግሯም እየከፋ በመምጣቱ ወደ ህክምናው መምጣትን ብቸኛው አማራጭ አድርጋዋለች።

እንደሚታወቀው የትራኮማ በሽታ ትኩረት የሚሹ የትሮፒካል በሽታዎች (Neglected Tropical Disease) ተብለው በተቀመጡ በሽታዎች ተርታ የሚመደብ በሽታ ነው። ይህ በሽታ በአብዛኛው በግል እና አካባቢ ንፅህና ጉድለት የሚከሰት ሲሆን፣ በከፍተኛ ደረጃ የተፈጥሮ የአይን ብርሃንን የማሳጣት ጉዳት ያደርሳል። ሆኖም ግን በአግባቡ ህክምና ከተደረገ 80 በመቶ ያህል የአይነ ስውርነት መንስኤዎችን በማከም ማስወገድ ይቻላል ይላሉ የጤና ባለሞያዎች። የአለም ጤና ድርጅት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በአለማችን ላይ 31 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ማስወገድ በምንችላቸው የጤና ችግሮች ምክንያት ለአይነ ስውርነት ተጋልጠዋል። የሚያስቆጨው ነገር ደግሞ በእያንዳንዱ 5 ሰዎች ላይ ከተከሰተው አይነስውርነት የ4ቱን ቀድሞ በመከላከል ወይም በማከም ማስቀረት እየተቻለ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ሰዎች የአይናቸውን ብርሃን ማጣታቸው ነው። ከዚህ በተጨማሪም በአለማችን ላይ 285 ሚሊዮን ሰዎች በእይታ መቀነስ የሚቸገሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 90 በመቶዎቹ በታዳጊ ሀገራት ያሉ ሰዎች ናቸው። ከእነዚህ ሰዎችም መካከል 65 በመቶዎች እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ ነው።

አንድን ሰው ለአይነ ስውርነት ሊያጋልጡት ከሚችሉ ችግሮች መካከል የአይን ሞራ ግርዶሽ (Cataract), የአይን ማዝ (ትራኮማ) እንዲሁም ግላኮማ ዋና ዋናዎች ናቸው። ከእነዚህ መንስኤዎች መካከል በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ለአይነ ስውርነት በመዳረግ የሚታወቁት ደግሞ የኤን ሞራ ግርዶሽ እና ትራኮማ ናቸው። በሀገራችን እ.ኤ.አ. በ2005 / 2006 የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው ከ600ሺህ የሚበልጡ ሰዎች በአይን ሞራ ግርዶሽ ምክንያት አይነ ስውር ሆነዋል። በተጨማሪም ከ132 ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በአይን ማዝ (በትራኮማ) ምክንያት የአይን ብርሃናቸውን አጥተዋል። በአይናቸው ግፊት መጨመርና (ግላኮማ) ሳቢያ የአይን ብርሃነቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥርም 50ሺ ገደማ እንደሆነ ጥናቱ ያመለክታል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ 989 ሺ የሚጠጉ ሰዎች በመነፅር መስተካከል በሚችል የማየት አቅም መቀነስ ችግር እየተሰቃዩ ናቸው። ይህ ቁጥር ሲጠቃለል ታዲያ በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ለአይነ ስውርነት የተዳረጉ ሰዎችን ቁጥር 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ይደርሰዋል።

በሀገራችን ያለውን የትራኮማ በሽታ ስርጭት ስንመለከት ከፍተኛው ስርጭት የሚስተዋለው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ነው። ከክልሉም የዋግኽምራ ዞን እስከ 54 በመቶ የሚገመት ከፍተኛ የሆነ የትራኮማ ስርጭት እንዳለው ተገልጿል። በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ 7 ወረዳዎች በ6ቱ ወረዳዎች ውስጥም ስርጭቱ ከ30 በመቶ በላይ መሆኑን ከክልሉ ጤና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ። ሰቆጣ ያለው የትራኮማ ስርጭት 61ነጥብ 5 በመቶ፣ ሰቆጣ ዙሪያ 55 በመቶ ሲሆን በከተማዋ ደግሞ 65 በመቶ መሆኑን መረጃው ያመለክታል። በአጠቃላይ በክልሉ ያለው የበሽታው ስርጭት ደግሞ 26 ነጥብ 3 በመቶ ነው። በዚህ በዋግኽምራ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል ከፍተኛው ስርጭት የተስተዋለውም በሰቆጣ ነው።

በአማራ ክልል ከፍተኛ የሆነ የትራኮማ በሽታ አለባቸው ተብለው ከተቀመጡ 167 ወረዳዎች መካከል ትራኮማን ለማጥፋት ስኬታማ ጥረት በማድረግ ውጤት ያስመዘገቡት 6 ወረዳዎች ብቻ ናቸው። በዚህም ሳቢያ በዋግኸምራ ዞን እየተካሄደ ያለውን የትራኮማ ህክምና እና መድሐኒት እደላ ዘመቻ በድጋሚ ማካሄድ አስፈላጊ ሆኗል። ከእነዚህ ውጤታማ ካልሆኑ ወረዳዎች ከተገኙት ታካሚዎች መካከል አንዱ አቶ ንጉሴ ለየ ናቸው።

አቶ ንጉሴ ለየ በሰቆጣ ዙሪያ ነዋሪ ሲሆኑ በከተማዋ የትራኮማ በሽታ ላለባቸው ሰዎች ህክምና እንደሚሰጥ በመስማታቸው ወደ ጤና ጣቢያ መጥተዋል። በአይናቸው ላይ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ ችግር የተፈጠረባቸው መሆኑን የገለፁት አቶ ንጉሴ፤ ነገር ግን ከዛሬ ነገ ይሻለኛል በማለት ብዙም ትኩረት ሳይሰጡት መቆየታቸውን ገልጸውልናል። «መኸር መኸር ሲሆን እና ስራ ስሰራ በተለየ ነው የሚያመኝ። በጣም ሲብስብኝ አልፎ አልፎ ጠብታ አደርግበታለሁ። ግን ምንም አይነት መፍትሔ አላመጣልኝም” ይላሉ አቶ ንጉሴ። በጠብታው ብቻ ለውጥ ማምጣት ያልቻሉት አቶ ንጉሴ ህመሙ እየባሰባቸው እና የሽፋሽፍታቸው ፀጉር እየታጠፈ ወደ አይናቸው ውስጥ መግባት ሲጀምር ሌላ መፍትሄ ነው ያሉትን ነገር ማድረግ ጀመሩ።

“ይሄን ሁለት ዓመት እየባሰብኝ ሲመጣ ፀጉር መለቀም ጀመርኩ ። በተወሰነ ወራት በቤቴ ውስጥ በወረንጦ ፀጉሩን ከአይኔ ውስጥ ማስለቀም ጀመርኩ። ግን ሌላ እየተካ ይመጣል እንጂ ጨርሶ ሊድንልኝ አልቻለም» የሚሉት አቶ ንጉሴ አይናቸው ዙሪያ ማበጥ እና ህመም፣ የሽፋሽፍታቸው መነቃቀል እንዲሁም የአይናቸው መቅላት ብቻም ሳይሆን፣ ስራቸውን በአግባቡ እያዩ እንዳይሰሩ እንደዳረጋቸው ገልፀውልናል። በዚህም ምክንያት አዝመራ የመሰብሰብ ሃላፊነቱን በባለቤታቸው እና ልጆቻቸው ላይ ጥለዋል።

አቶ ንጉሴ ብቻም ሳይሆኑ ባለቤታቸው ጭምር በዚህ ችግር ውስጥ እንደሆኑ ነው የገለፁልን። ነገር ግን ባለቤታቸው ከእርሳቸው ሻል ስለሚሉ ወደ እርሻ ቦታ ሄደዋል። ህክምና ለማግኘትም አልሞከሩም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የበሽታውን ምንነት አለመረዳት ነው። አቶ ንጉሴም እንዲህ ይገልፁታል። “በፊት ህመሙን ቀለል አድርገን ነበር የምናየው። በምን እደሚመጣብንም አናውቅም ነበር። በመደዳው ስለሆነ የሚያውቀው ምንም ማድረግ አልቻልንም ነበር። አሁን ግን ካለመታጠብ እና ንፅህናችንን ካለመጠበቅ እንደሚመጣ ተረድተናል” ይላሉ አቶ ንጉሴ።

በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች አማካይነት በተሰጠው ትምህርት መሰረት መፀዳጃ ቤት መስራታቸውን እና በዚያም እየተጠቀሙ መሆኑን የገለፁት አቶ ንጉሴ፤ ይህ አይነቱ ትራኮማን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት እርሳቸውንና ባለቤታቸውን በትራኮማ ከመያዝ ባያድናቸውም ልጆቻቸውን ግን ሊታደግ እንደሚችል ተስፋ ሰንቀዋል።

የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች ማህበረሰቡ የራሱን እና የአካባቢውን ንጽህና በመጠበቅ፣ መፀዳጃ ቤቶችን በማዘጋጀት እና በአግባቡ በመጠቀም ትራኮማን እንዲካላከል ያስተምራሉ። ለትራኮማ እና ተያያዥ ለሆኑ በሽታዎች ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት ሴቶች ደግሞ ዋንኛዎች የስልጠናው አባላት ናቸው። እነዚህን ሴቶች አንድ ለሰላሳ፣ አንድ ለአምስት እና በመሳሰሉት በማደራጀት እርስ በእርሳቸው እንዲወያዩ እና ትምህርት እንዲወስዱ እየተደረገም ይገኛል። በዚህም ሴቶቹ መፀዳጃ ቤቶችን በማስገንባት እና በአግባቡ በመጠቀሙ ረገድ እንዲሁም የመኖሪያ ቤት እና አካባቢያቸውን በንጽህና በመያዙ ረገድ ውጤታማ ስራዎችን እንዳከናወኑ የመስክ ጉብኝት ባደረግንባቸው ወረዳዎች መረዳት ችለናል።

በጤና ጣቢያዎች ህክምና አገልግሎት ለመውሰድ ተሰልፈው የሚጠባበቁት የትራኮማ በሽታ ችግር ካለባቸው ታካሚዎች መረዳት እንደተቻለውም የትራኮማ መንስኤን ጨምሮ በሽታውን በምን መልኩ መከላከል እንደሚቻል በቂ የሆነ ግንዛቤ በህብረተሰቡ ዘንድ ሊሰርፅ አልቻለም። በሽታውን እንደ አንድ የተፈጥሮ ህመም ከመውሰድ ውጪ በህክምና ለማዳን እና አስፈላጊውን ክትትል ለማድረግ ብዙም ጥረት ሲደረግ አይስተዋልም። አብዛኞቹም የትራኮማ በሽታ በንፋስ አማካይነት በሚመጣ አቧራ እና ቆሻሻ ምክንያት እንደሚከሰት ነው የሚገልጹት።

በሌላ በኩል ደግሞ ድህነት በራሱ ህብረተሰቡን ለዚህ በሽታ እጅ እንዲሰጥ ያደረገው ይመስላል። በሽታው የግል ንጽህናን ባለመጠበቅ እንደሚመጣ ግንዛቤው ያላቸው ሰዎች በድህነታቸው ሳቢያ በሽታውን መከላከል ሲያቅታቸው ይስተዋላል። እኛም ከታካሚዎቸ እንደተረዳነው እጃቸውን እና ፊታቸውን ዘወትር በሳሙና መታጠብ እንዳለባቸው እያወቁ ነገር ግን ሳሙና ማግኘት ከፍተኛ ችግር ያለባቸው በርካቶች ናቸው። ለምን በሳሙና አትታጠቡም ተብለው ሲጠየቁም «በሳሙና መታጠብ ንፁህና መሆኑን እናውቃለን፡፤ ለማግኘት አቅማችን አይፈቅድም። ማግኘት አልቻልንም እንጂ ንጽህናን የሚጠላ የለም” ሲሉም ይመልሳሉ።

      በተለይ በዋግኸምራ አካባቢ ያለው ተፈጥሮ በራሱ ለዚህ የትራኮማ በሽታ መባባስ እንደ ትልቅ መንስኤ ሊወሰድ የሚችል ሌላው ምክንያት ነው። አካባቢው ውሃ አጠር በመሆኑ ምክንያት ንጽህናን ለመጠበቅ በቂ የሆነ ውሃ ማግኘት አዳጋች ነው። ከዚህ በተጨማሪም አካባቢው ደረቅ እና የተራቆተ በመሆኑ የትራኮማ በሽታ ያለባቸው ሰዎች በቀላሉ ለአቧራ እና ተያያዥ ለሆኑ ደረቅ ቆሻሻዎች በመጋለጥ ህመማቸው ይባባሳል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
2939 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 879 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us