ትኩረት የተነፈጋቸው ባለውለታዎች

Thursday, 06 November 2014 09:16

 

የአለም የአረጋውያን ቀን በየአመቱ በፈረንጆቹ ህዳር አንድ ቀን በእኛ ደግሞ ጥቅምት 22 ቀን ይከበራል። ዘንድሮም ቀኑ በአለም ለ24ኛ ጊዜ በሃገራችን ደግሞ ለ23 ኛ ጊዜ “ማንንም ወደሁዋላ ሳንተው ሁሉንም ማህበረሰብ እናበረታታ (Leaving No one Behind; promoting a society for all)” በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ውሏል። እኛም ቀኑን በማሰመልከት የሃገራችን አረጋውያን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ የሚለውን መቃኘት ወደድን።

“አረጋዊ” የሚባለው ግለሰብ ከሀገር ሀገር የተለያዩ ፍቺዎች እና የእድሜ ደረጃዎች አሉት። ነገር ግን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አንድ ሰው አረጋዊ የሚባለው እድሜው 60 ዓመት እና ከዚያ በላይ ሲሆን ነው በማለት ደንግጓል። ይህ የአረጋዊነት እድሜ ደግሞ በሀገራችን ካለው የጡረታ መውጫ እድሜ ጋር በመገጣጠሙ በአገልግሎት ላይ እየዋለ ይገኛል።

የአረጋውያን ቁጥር በዓለማችን ላይ ባልተገመተ ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ። በመላው ዓለም ላይ እየተስፋፋ በሚገኘው የከተሜነትን ባህሪ፣ የኢንዱስትሪዎች መበራከት፣ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መስፋፋት እንዲሁም ዘመናዊነትን መሠረት ያደረገ የሰው ልጆች የአኗኗር ዘይቤ በርካታ ሰዎች ረጅም እድሜ እንዲኖሩ እያደረጋቸው እንደሆነ ነው የተጠቆመው።

ለእነዚህ ለአረጋውያን ረጅም እድሜ መኖር አዎንታዊ ተፅዕኖ በፈጠሩ ምክንያቶች በመታገዝም የዓለማችን አረጋውያን ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ ጭማሪ እያሳየ መጥቷል። እ.ኤ.አ. በ1950 ዓ.ም በዓለማችን ላይ እድሜያቸው 60 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆናቸው አረጋውያን ቁጥር 200 ሚሊዮን ነበር። ይህ ቁጥር በ50 ዓመታት ውስጥ ከእጥፍ በላይ በመጨመር በ2000 ዓ.ም 590 ሚሊዮን መድረስ ችሏል። በአሁኑ ወቅት በአለማችን ላይ 600 ሚሊዮን አረጋውያን ይገኛሉ። አሁን ባለው አካሄድ ከቀጠለ ደግሞ እ.ኤ.አ በ2030 ቁጥሩ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን እንዲሁም በ2050 የዓለማችን አረጋውያን ቁጥር 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ በባለሙያዎች ተገምቷል።

በኢትዮጵያ ልክ እንደሌሎቹ ጉዳዮች ሁሉ በአረጋውያን ቁጥር ላይም ሰፊ እና ተጨባጭ የሆኑ መረጃዎች ተደራጅተው አይገኙም። ያም ሆኖ ግን ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው እ.ኤ.አ በ1984 ዓ.ም በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ አረጋውያን ቁጥር 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ነበር። ከዚህ በተጨማሪ እ.ኤ.አ በ2006 ይፋ በተደረገ ሪፖርት እንደተቀመጠው ከኢትዮጵያ 75 ሚሊየን ሕዝብ ውስጥ 3 ነጥብ 3 በመቶዎቹ እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ ነው። ይህን ቁጥር በከተማ እና በገጠር የሀገሪቱ ክፍሎች ለይተን ስናስቀምጠውም በከተማ ከሚኖሩ 12 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 532 ሺህ 800ዎቹ አረጋውያን ነበሩ። በገጠር የሀገሪቱ ክፍል ከሚኖሩ 62 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሰዎች መካከል ደግሞ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚሆኑት እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆናቸው አረጋውያን እንደነበሩ የኤጀንሲው ሪፖርት ያመለክታል። በቅርቡ /እ ኤ አ በ 2010/ በሄልፕኤጅ ኢንተርናሽናል የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው በኢትዮጵያ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን እድሜያቸው ከ 60 አመት በላይ የሆናቸው አረጋውያን አሉ። ይህ ሁኔታ አሁን ባለበት አካሄድ ከቀጠለም በኢትዮጵያ በ2020 / እ ኤ አ/ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን አረጋውያን ይኖራሉ ተብሎ ተገምቷል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ከመጣው የአረጋውያን ቁጥር ጋር ተያይዞም በአንድ ሀገር ውስጥ የበርካታ አረጋውያን መኖር ራሱን የቻለ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። ነገር ግን እነዚህን አረጋውያን በሀገር ግንባታ እና በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ውስጥ የመጠቀሙ ሁኔታ እንዲሁም ለአረጋውያን አስፈላጊውን እንክብካቤ እና ድጋፍ የማድረጉ ጉዳይ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ቤተሰብ እርስ በእርስ የመረዳዳት እና አንዱ ሌላውን የመጦር ባህላችን ከፍተኛ በመሆኑ እነዚህ አረጋውያን በዚህ እድሜያቸው ሙሉ ለሙሉ በቤተሰቦቻቸው ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። አብዛኛው ቤተሰብም እነዚህ አረጋውያን የመጦር ግዴታው እና ኃላፊነቱ የእርሱ እንደሆነ አምኖ ስለሚቀበለው አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ያደርግላቸዋል። ነገር ግን በዚህ ቤተሰብ ላይ ችግር ሲፈጠር የመጀመሪያዎቹ የችግሩ ገፈት ቀማሾች እነዚህ አረጋውያን ይሆናሉ።

ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ በሀገራችን ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለልመና እጃቸውን ለምፅዋት የሚዘረጉ አረጋውያንን በእለት ተእለት ህይወታችን ውስጥ መገንዘባችን ነው። በርካታ ከፍተኛ እውቀት ያላቸው እና ከራሳቸው አልፈው ሌሎችንም ሊያስተዳድሩ የሚችሉ አረጋውያን በየመንገድ ዳር እና በየሀይማኖት ተቋማቱ ለምፅዋት እጃቸውን ሲዘረጉ ይስተዋላሉ። በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየተስፋፋ ባለው ከተሜነት እና በቤተሰብ መካከል ያለው ትስስር መላላት የተነሳ በርካታ አረጋውያን ለችግር እየተጋለጡ ይገኛሉ። እነዚህ አረጋውያን ከእድሜያቸው መግፋት እና ካለው ሁኔታ ጋር ተላምደው ለመኖር ከመቸገራቸው ጋር በተያያዘ አንድ ጊዜ ችግር ውስጥ ከገቡ በኋላ ተመልሰው ከችግሩ ውስጥ ለመውጣት እንደሚቸገሩ ነው ባለሙያዎቹ የሚገልፁት።

አረጋውያን በቂ የሆነ የጤና አገልግሎት ችግር፣ ቋሚ የሆነ መጠለያ እና የተመጣጠነ ምግብ ችግር እንዲሁም ከቤተሰብ እና ከማኅበረሰብ በሚደረግ እገዛ እጦት ችግር ውስጥ መሆናቸው ነው የሚገለፀው። በተጨማሪም በዚህ እድሜያቸው ሊተዳደሩበት የሚችሉት ማኅበራዊ ዋስትና እና ሌሎች አገልግሎቶች ችግር፣ ከእድሜያቸው ጋር የሚሄዱ ስልጠናዎች እና ትምህርት ማጣት ድህነት በእነዚህ አረጋውያን ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲያደርስባቸው የራሳቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ኤች አይ ቪ ኤድስ የእነዚህን የአረጋውያን ድህነት ከሚያባብሱ ነገሮች አንዱ እንደሆነ ይገለፃል። አረጋውያን ለኤች አይ ቪ የተጋለጡ ልጆቻቸውን እና የልጅ ልጆቻቸውን ለመንከባከብ በሌለ አቅም አና በሌላቸው ገቢ ሙሉ ኃላፊነት ወስደው ይኖራሉ። የሰራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው ጥናት እንደተረጋገጠው እ.ኤ.አ በ2011 ብቻ በኢትዮጵያ 1 ነጥብ 2 ሚለዮን የሚሆኑ ወላጆቻቸውን በኤች አይ ቪ ምክንያት ያጡ ህፃናት በአያቶቻቸው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛሉ።

ከአራት ዓመታት በፊት ሄልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት እና ሌሎች አምስት ሀገር አቀፍ አገሮች በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አስተባባሪነት በአዲስ አበባ ጥናት አካሂደው ነበር። ጥናቱ የተደረገው በአዲስ አበባ በሚኖሩ እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ በሆኑ አረጋውያን ላይ ነበር። በወቅቱ በአዲስ አበባ ብቻ 145ሺ አረጋውያን የነበሩ ሲሆን፤ በዚህ ጥናትም ከአንድ ሺህ በላይ የሆኑት በቃለ መጠይቁ ተዳሰው ነበር። በዚህ ጥናት የተደረሰበት ግኝትም እጅግ አስደንጋጭ ተብሏል።

በጥናቱ መሠረት ከተሳታፊዎቹ መካከል ከ88 በመቶዎቹ በላይ የሚሆኑት አረጋውያን ቤት አልባዎች ናቸው። 66 በመቶዎቹ ቤት ያላቸው ቢሆንም ምንም የሚበሉት ነገር የሌላቸው ሆነው ተገኝተዋል። ከጥናቱ ተሳታፊዎች 79 በመቶ የሚሆኑት አረጋውያን በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ቢበዛ ደግሞ ሁለት ጊዜ ብቻ የሚመገቡ ሲሆኑ፤ 79 በመቶዎቹ ቤት የሌላቸው አረጋውያን ደግሞ ውሃ የሚያገኙት በልመና ነው። ከጥናቱ ውስጥ ከተሳተፉት አረጋውያን መካከልም 93 በመቶዎቹ መፀዳጃ ቤትም ሆነ ሻወር ቤት የላቸውም። በዚህም ሳቢያ 71 በመቶ የሚሆኑት አረጋውያን በወንዝ ውሃ የሚታጠቡ ሲሆን 22 በመቶዎቹ ጭራሹኑ አይታጠቡም። ከዚህ በተጨማሪም 78 በመቶዎቹ ተሳታፊዎቹ ከባድ የጤና ችግር ያለባቸው ናቸው። ከሦስት አረጋውያን መካከል አንድ በመንግስት በኩል ለድሃ ሰዎች የሚሰጥ ነፃ የጤና አገልግሎት መኖሩንም አያውቅም ሲል ጥናቱ አመልክቱዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1433 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 853 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us