እሾህን በእሾህ

Wednesday, 12 November 2014 15:30

 

በኢትዮጵያ የሚገኙ እያንዳንዳቸው ሴቶች ስራ ከመጀመራቸው በፊት ትምህርታቸውን ቢያጠናቅቁ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ አራት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መጨመር ይችላሉ። “በ2013 ሴቶች እና ገቢ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ጥናት ያካሄደው ገርል ሃብ ኢትዮጵያ የተባለው ግብረሰናይ ድርጅት ይህ ገቢ ደግሞ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከእርዳታ ከምታገኘው ገንዘብ ይበልጣል ይላል።

ሴቶች ያሉባቸው እንቅፋቶች ተወግደው እውቅናና ማበረታቻ ቢደረግላቸው የራሳቸውን ህይወት ከማሻሻል አልፈውም በቤተሰባቸው፣ በማኅበረሰቡ፣ በሀገራቸው እና በመላው ዓለም ላይ አዎንታዊ የሆነ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ያመጣሉ።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ሴቶች በዕለት ተዕለት ህይወታቸው የሚገጥሟቸውን ችግሮች እና ተግዳሮቶች ነቅሶ በማውጣት፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች የተሳተፉበት ጥናት በማድረግ ወደ ስራ የገባው “የኛ የሬዲዮ ድራማ እና ቶክ ሾው”ም የተነሳው እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ነው። “የኛ የሬዲዮ ድራማ እና ቶክሾው” በተለያዩ ሦስት ምዕራፎች ከአንድ ዓመት በላይ በሬዲዮ ሲተላለፍ ቆይቷል። በየኛ ፕሮግራም እስከ አሁን ድረስ በተለይ ወጣት ሴቶች በስነ-ተዋልዶ፣ በማኅበራዊ እና ቤተሰብ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም በትምህርት ላይ የሚገጥሟቸውን ችግሮች እያነሳ ወጣት ሴቶች እንዴት ችግሮቻቸውን ተቋቁመው ማለፍ እንደሚችሉ እያስገነዘበ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን ሲያካሂድ ቆይቷል። በተጨማሪም ወጣቶች ሊማሩባቸው ይችላሉ የተባሉ ታዋቂ ግለሰቦችን በመጋበዝ ለወጣቶች ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉ መደረጉ ወጣት ሴቶች ብዙ ነገር ተምረው ለነገው ሕይወታቸው ተስፋን እንዲሰንቁ እንዳደረጋቸው ተገልጿል።

በፕሮግራሙ ላይ የሚቀርቡት ድራማዎች አንዲት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የምትኖር ሴት ሊገጥሟት የሚችሉትን ተግዳሮቶች እና ከተግዳሮቶቹ የምታመልጥባቸውን መንገዶች በማሳየት ሴቶች በራሳቸው ህይወት እንዲተረጉሙት ያደርጋል። በእያንዳንዷ ሴት ላይ የሚደርሰው ችግር መንስኤው የአመለካከት ችግር መሆኑን የሚገልፁት የፕሮግራሙ አዘጋጆች፤ እነዚህን የአመለካከት ችግሮች ለመቅረፍ ደግሞ በኪነ-ጥበብ ማስተማር ዘዴ የሌለው አማራጭ ሆኖ ተገኝቷል።

“የኛ” የሬዲዮ ድራማ እና ቶክሾው ሲቋቋም የራሱ የሆኑ ዓላማዎችን ሰንቆ እንደነበረ ነው የተገለፀው። ከእነዚህ ዓላማዎች መካከልም ሁሉም የሀገራችን ልጃገረዶች የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ ማድረግ፣ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሴቶች የራሳቸው የሆነ ገቢ ኖሯቸው ገበያቸውንም መቆጣጠር እንዲችሉ ማድረግ እንዲሁም ሁሉም ሴቶች በግብረሥጋ ግንኙነት እና በስነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር ማድረግ እንዲችሉ እና መወሰን እንዲችሉ ማድረግ ነው።

ሴቶች በተለይ ልጃገረዶች በሀገራችን በተለያዩ ወጥመዶች እና ማነቆዎች ተተብትበው እንዳሉ በተለያየ ጊዜ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከእነዚህ መሰናክሎች ምክንያትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጃገረዶች በውስጣቸው ያለውን እምቅ ኃይል አውጥተው መጠቀም እንዳይችሉ እና በራሳቸው ህይወት ላይም ለውጥ እንዳያመጡ እያደረጋቸው ይገኛል። ለአብነት ያህል በሀገራችን እ.ኤ.አ በ2011 ከተካሄደው የስነህዝብ ጥናት መመልከት ይቻላል።

በዚህ ጥናት ይፋ እንደተደረገው በሀገራችን ካሉ ሦስት ልጃገረዶች መካከል አንዷ ወደ ትምህርት ቤት የማትሄድ ሲሆን፤ በሦስት ልጃገረዶች መካከልም አንዷ ማንበብ አትችልም። ከትምህርት ገበታ ከመራቅ ጐን ለጐንም ለሀገራችን ለሴቶች ከሚሰጠው የተሳሳተ ግምት የተነሳ ሴቶች አንድ ሰው በየትኛውም ዓለም ሊሰራበት ከሚገባው የስራ ሰዓት በላይ ለጉልበት ብዝበዛ የተጋለጡ ናቸው። ከጥናቱ መረዳት እንደሚቻለውም በኢትዮጵያ ያሉ ሴቶች በአማካይ በሳምንት 28 ሰዓታትን በቤት ሥራ ላይ ነው የሚያሳልፉት።

በሀገራችን ያሉ ሴቶች ኅብረተሰቡ ከሚሰጣቸው ግምት በተጨማሪም ራሳቸው ሴቶቹ ለራሳቸው የሚሰጡት ግምት በራሳቸው ላይ የሚደርሱ አላስፈላጊ በደሎችን እንደመደበኛ ድርጊት (Normal Act) በመውሰድ ላይ ናቸው። ይህ ችግር በሁሉም ላይ የሚደርስ በመሆኑም አንዷ ከሌላዋ ለመነጋገር እንኳን ስለማይደፈሩ እንዲሁም ካለባቸው የቤት ውስጥ የስራ ጫና አኳያ ከጓደኛ ጋር ተገናኝተው ለመወያየት ጊዜ አይኖራቸውም። በዚህም መሠረት ከሦስት ሴቶች ውስጥ ሁለቱ ሴት ልጅ በባሏ መደብደቧ ትክክለኛ ነው ብለው ያምናሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከአምስት ሴቶች መካከል አንዷ ችግሯን የምታካፍላት ጓደኛ እንደሌላት ትገልፃለች።

የኛ የሬዲዮ ፕሮግራም እና ቶክሾው ታዲያ እነዚህን የሀገራችንን ሴቶች አንቀው ያሰሯቸውን ችግሮች በአመለካከት ለውጥ ለመቅረፍ ነው ጥረት እያደረገ ያለው። ለዚህም እንደ ዋና መሳሪያ የሚጠቀመው ሰዎች ስለ ሴት ልጅ ያላቸውን አመለካከት በመለወጥ እና በራሳቸው በሴቶች ላይ በመስራት ለውጥ ለማምጣት ጥረት ማድረግ ነው። “የኛ” ፕሮግራም የተነሳበትን ዓላማ ለማሳካት በተለይ ከአማራ ሴቶች ማኅበር ጋር በመተባበር ፕሮግራሙ በመላው ሴቶች ዘንድ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። ለአብነት ያህልም ከማኅበሩ ጋር በመተባበር 10ሺ ያህል የአድማጭ ቡድኖች እንዲፈጠሩ አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪም ፕሮግራሞቹ በአማራ ክልል በሚገኙ 3ሺ 500 ትምህርት ቤቶች እንዲተላለፉ ተደርጓል።

የ“የኛ” ፕሮግራሞች የሚተላለፉት ተማሪዎች በትምህርት ቤት በማይገኙበት ቀን እሁድ ዕለት በመሆኑ ፕሮግራሙን በፍላሽ ጭምር እየቀዱ ለየትምህርት ቤቶች እንደሚያደርሱ የ“የኛ” ዋና ፀሐፊ ወይዘሮ ሰሎሜ ታደሰ ገልፀዋል። በተጨማሪም ፕሮግራሙን በቀላሉ ማግኘት የማይችሉ ጠረፍ አካባቢ ያሉ ትምህርት ቤቶችም ፕሮግራሞቹ በዚህ መልኩ እንደሚደርሷቸው ተገልጿል።

የኛ ፕሮግራም እየተንቀሳቀሰ ባለባቸው ጊዜያት ታዲያ በራሳቸው በሴቶች እና በማኅበረሰቡ ላይ ከሚታሰበው በላይ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ተገልጿል። ባለፈው መስከረም ላይ የተደረገው ቅድመ ጥናት እንዳመለከተውም አብዛኞቹ የድራማው ተከታታዮች ስለሴቶች መብት፣ ችግራቸውን ለጓደኛ ማካፈል አስፈላጊ መሆኑን፣ ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅተኛ እንደነበረ እና አሁን ድራማውን መከታታል ከጀመሩ ወዲህ ግን ግምታቸው እንደተስተካከለ እንዲሁም ፕሮግራሙን የሚከታተሉ ሴቶች ቁጥጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተረድተናል ብለዋል። በዚህም መሰረት ፕሮግራሙን ከሚከታተሉ ሰዎች መካከል 44 በመቶዎቹ ችግሮቻቸውን ከጓደኞቻቸው ጋር መነጋገር እና መወያየት ለችግራቸው መፍትሄ እንደሚያመጣ ተረድተዋል። 46 በመቶ የሚሆኑት አድማጮች ደግሞ ስለ ሴቶች መብት መረጃ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የሚቀርቡት ድራማዎች ባለፉት ሦስት ምዕራፎች በገፀ-ባህሪያት አማካይነት ለህዝቡ ይቀርቡ የነበረ ሲሆን፤ በዚህ በአራተኛው ምዕራፍ ግን እውነተኛ የአካባቢውን ሰዎች ጭምር ለማሳተፍ ታቅዷል። በዚህም ፕሮግራሙን የሚያደምጡ ሴቶች የድራማውን መልዕክት በቀጥታ ከራሳቸው ህይወት ጋር በቀላሉ ለማገናኘት ይችላሉም ተብሏል።

በእነዚህ ምዕራፎችም በሴቶች ላይ ከሚደርሱ ተግዳሮቶች መካከል ያለ እድሜ ጋብቻ፣ ያለ እድሜ እርግዝናን፣ የጾታ ጥቃትን፣ የትምህርት ማቋረጥን የመሳሰሉትን አስመልክቶ በድራማ እና በቶክሾው ወደ ኅብረተሰቡ ይደርሳሉ። ይህ ቶክሾው እና ድራማ ደግሞ ዋና አላማው ያደረገው ራቅ ባሉ እና ጠረፋማ የሀገሪቱ አካባቢ ድረስ ያሉ ሴቶችን ነው፡፡

እስከ አሁን ድረስ የተነሱት ጉዳዮች ፕሮግራሙ በሚተላለፍባቸው አካባቢዎች በህብረተሰቡም ሆነ በራሳቸው በሴቶቹ ተቀባይነት በማግኘታቸው ለቀጣዩ ፕሮግራምም አበረታች እንደሆነ ተገልጿል። ባለፈው ጥቅምት 3 ቀን የጀመረው አራተኛው ምዕራፍ “የኛ ሬዲዮ ድራማ እና ቶክሾው”ም ልክ እንዳለፉት ክፍሎች ሁሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶችን ህይወት ይቀይራል ተብሎ ይጠበቃል። ችግሩ በአንድ እና በሁለት ክልሎች ብቻ ተወስኖ የሚቀር ባለመሆኑም በመላው ሀገሪቱ ለመስራት እና ሁሉንም ሴቶች ከእነዚህ ማነቆዎች ነፃ ለማውጣት ሰፊ እቅድ ተይዟል።   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1706 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 928 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us