ራስን በሌሎች ውስጥ ፍለጋ

Wednesday, 19 November 2014 11:31

ወይዘሮ ገነት ለማ

ወይዘሮ ገነት ለማ የቤዛ ኦርጋናይዚንግ አሶሲየሽን ኦፍ ውሜን ኢን ኒድ መስራች እና ስራ አስኪያጅ ናቸው። አላማውን በተለያዩ ምክንያቶች ከማይወጡት የችግር አረንቋ ውስጥ የገቡ ሴቶችን መደገፍ አድርጎ የተመሰረተውን ይህን ማህበር በ1987 ዓ.ም ያቋቋሙ ሲሆን፣ ማህበሩም በቆይታው የበርካቶችን ህይወት መቀየር የቻለ ነው። ወይዘሮ ገነት ለዚህ ማህበር መመስረት ምክንያት የሆኗቸውን እናታቸውን፣ ሌሎች ወንድሞቻቸውን እና የሙት ልጆችን በመርዳት ላይ በመሆናቸው ራሳቸውን የማሻሻል ህልም ቢኖራቸውም ከአቅም እጥረት የተነሳ ግን ሊያሳኩት አልቻሉም። ነገር ግን እርሳቸው ያላገኙትን እድል ለብዙዎች እያስገኙ እና በእነዚህ ሴቶች ውስጥም እራሳቸውን እያገኙ ናቸው። ትምህርታቸውን በዲፕሎማ ደረጃ ያቆሙ ሲሆን፤ “ጊዜው ቢረዝምም ዲግሪዬን ሳልይዝ አልቀርም” ይላሉ። ከወይዘሮ ገነት ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንዲህ ይዘን ቀርበናል።  

ሰንደቅ፡- ወደኋላ ልመልስዎትና፤ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ይህን ማህበር ሲያቋቁሙ እንደመነሻ ያገለገልዎት ምን ነበር?

ወ/ሮ ገነት፡-እኔ በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን የስነፅሁፍ ኢቫንጀሊስት አገልግሎት ስር ሆኖ ሆም ኸልዝ ኢዱኬሽን ሰርቪስ ውስጥ አገለግላለሁ። በዚህም ስራ ቤት ለቤት እየዞርን ስለ ልጅ አስተዳደግ፣ የቤት አመራር እና ስለመሳሰሉት ጤና ሞግዚት ስለሚለው መፅሐፍ እናስተምር ነበር። በዚህ ስራ ታዲያ አንድ ጊዜ ከምሽቱ ስድስት ሰዓት ገደማ ይሆናል በዱከም ላይ ጭር ያለበት ቡና ቤት ውስጥ ስገባ በጠባብ ግድግዳ መካከል ለመታነቅ የምትታገል ልጅ አገኘሁ። ያቺን ልጅ አዳንኳትና እስከምትረጋጋ ድረስ ሶስት ቀን ያህል አብሬያት ቆየሁ። መፅሀፍ ሸጬ የነበረውን ገንዘብም ሰጥቻት ወደ ቤቷ እንድትሄድ አደረኳት። ይህ እንደ አንድ መነሻ ሆኖኛል።

ሌላው ደግሞ የእናቴ ታሪክ ነው። እኛ ትንንሾች ሆነን አባታችን ሲሞት እናታችን ዘጠኝ ልጆችን ብቻዋን ነው ያሳደገችን። እርሷም ወጣት ስለነበረች በተለይ በሴትነቷ የሚመጡባትን አደጋዎች ለመቋቋም እና እኔ ላይ የሚደርሱ ጠለፋን የመሳሰሉ የሴት ጥቃቶችን ለመከላከል ብዙ ለፍታለች። እኔን ሊወስዱ በር እስከመስበር የደረሰ ጥረት ሲያደርጉ ስመለከት የሴት ልጅ ጥቃት ያን ጊዜ ነው ውስጤ ሊገባ የቻለው። ሴቶችን በምን መልኩ ነው ከጥቃት ማዳን የምችለው? የሚለውን ጥያቄም በተደጋጋሚ ራሴን መጠየቅ የጀመርኩት በዚህ ሳቢያ ነው።

እኔም በራሴ ብዙ ጥቃቶች ይደርሱብኛል። በአድቬንቲስት ቤተክርስቲያን የመጀመሪያዋ ሴት የወንጌል አገልጋይ ነኝ። ብዙ ተፅዕኖዎች እየደረሱብኝ እያሉ በጉልበት ነው ሳገለግል የነበረው። አገልግሎቴን እና ሁኔታዬን እያዩ ያልፉኛል እንጂ ሴት ሆኜ በማገልገሌ ብዙም ፈቃደኛ አልነበሩም። በዚህም ሳቢያ ነው እንግዲህ የቃል ትምህርት ብቻ ሳይሆን፤ ሰጥቻት ራሷን እንደኔ ማቆም የምትችል ሴት መፍጠር አለብኝ ብዬ የወሰንኩት። በመቀጠል የብዙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ዶክመንቶች አጥንቼ በውስጤ የነበረውን ይዤ ይህን ማህበር አቋቋምኩ።

ሰንደቅ፡- ማህበሩ ድጋፍ እያደረገ ያለው የድሃ ድሃ ለሆኑ ሴቶች እንደሆነ ነው የተገለፀው። በእኛ ሀገር ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የድሃ ድሃ የሚባሉት የትኞቹ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው?

ወ/ሮ ገነት፡-በመፅሐፍ ቅዱስ ስንመለከት ድሃ የሚባሉት ባል የሌላት ሴት እና ወላጅ የሌላቸው ህጻናት ናቸው። በእኛ ደግሞ የድሃ ድሃ የምንላቸው ምንም መንገድ የሌላቸው ናቸው። በዚህም ቢሉ በዚያም ቢሉ ምንም የመለወጫ መንገድ የሌላቸው ናቸው። እነዚህን ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች አይቻለሁ። በመልሶ ማልማት በልደታ ቤቶች ሲፈርሱ ስመለከት የሽንት ቤት ፈሳሽ በአናታቸው እየሄደ እዚያ ውስጥ ነው የሚያድሩት። ራሳቸውን ለደህና ቤት የተመኙበት ጊዜ ባለመኖሩ ያ እንኳን ሲፈርስባቸው በጣም ነው ያለቀሱት። አንድ ነገር ልንገርሽ አንዲት እናት “ልጄ! እድሜዬን ሙሉ በሴተኛ አዳሪነት ነው ያሳለፍኩት። እጀራዬ ከወንድ የሚተርፈው ነው። አሁንም በዚሁ እድሜዬ ይህንኑ ነው ይዤ ያለሁት። በማልፈልገው ህይወት ውስጥ ነው ያለሁትና ከዚህ ህይወት አውጪኝ” ነው ያሉኝ። ያለው ነገር በጣም ያሳዝናል። እንግዲህ እኛ የድሃ ድሃ የምንላቸው እነዚህ መሰሎቹ ናቸው።

ሰንደቅ፡- በማህበሩ የሚረዱ ሴቶች በምን መልኩ ነው ህይወታቸው እንዲለወጥ የሚደረገው? ተረጂዎችስ የጥገኝነት ስሜት እንዳያድርባቸው ምን ይደረጋል?

ወ/ሮ ገነት፡-ለተለዩ ተዛማጅ በሽታዎች የተጋለጡ ሴቶችን፣ እንዲሁም አካል ጉዳተኛ የሆኑ ችግረኛ ሴቶችን ህክምና እንዲያገኙ እናደርጋለን። ከዚህ በተረፈ ወንዶች ያለ አግባብ ተጠቅመው የጣሏቸውን፣ ትምህርታቸውን ያቋረጡ ሴቶን በመሰብሰብ ከቀበሌ አዳራሽ እየለመንኩ ስልጠና እንዲወስዱ አደርጋለሁ። ከዩኒቨርስቲ መምህራንን በማምጣት፣ የዶክተሮች እና ነርሶችን እገዛ በመጠየቅ ሴቶችን እንዲያሰለጥሉልኝ አደርጋለሁ። ሴቶቹ በሞግዚትነት፣ በብሎኬት ስራ፣ በዳቦ መጋገር እና ምግብ ስራ እንዲሁም የልብስ እጥበት ዘርፍ ይሰለጥናሉ። በተጨማሪም በኮምፒውተር እና በሲልክ እስክሪን ህትመት ሙያ ይሰለጥናሉ። እነዚህ የሰለጠኑትም በሀገር ውስጥ ተቀጥረው እንዲሰሩ፣ ካልሆነም ሰርተፍኬት ተሰጥቷቸው ሰርተው ምርታቸውን እንዲሸጡ እና ገቢ እንዲያገኙ ይደረጋል።

በተረፈ ግን ስልጠናው የሚሰጠው ለችግር ጥገኛ መሆን እንደሌለባቸው በማስገንዘብ ነው። ችግርን ተቋቁመው እንዴት ራሳቸውን ነፃ ማውጣት እንዳለባቸው ይማራሉ። አስተሳሰባቸውን እና ስነልቦናቸውን የመቀየር ስራ ነው የምንሰራው። ደግሞም የራሴን ሕይወት ነው የማስተምራቸው። ብዙዎቹ በማደርግላቸው ነገር ደስተኞች ናቸው። ቀደም ብሎ ባወቅነው ኖሮ ነው የሚሉት።

ይህን ስራ ስጀምረውም ማንም ጥገኛ እንዲሆን አልፈለኩም። ምክንያቱም ደግሞ እኔ በምንም ጥገኛ ሆኜ ስለማላውቅ ነው። እነዚህ እናቶች በራሳቸው እንዲተማመኑ በመጀመሪያው በአእምሯቸው ላይ ነው የምንሰራው። ተማሩም አልተማሩም ዋናው ነገር አእምሮው ነው። አእምሮው ከተገነባ እና ራሱ ሰብሮ እንዲወጣ ተደርጎ አእምሮው ከተሰራ ችግረኛ ሰው ወደ ኋላ አይመለስም። መንገዱን በዚያው ይቀጥላል እንጂ ወደኋላ አይመለከትም። የራበው ሰው ከርሃቡ የሚያወጣውን ምግብ እንጂ ምግቡ የቀረበበትን እቃ አያይም። የእኔ ህይወት ብዙዎችን ያስተምራል። እኔ በድሃዋ ፊት መኪና ይዤ መታየት አልፈልግም። ኑሮዬን እያዩ በሶ ሁሉ አምጥተው የሚመግቡኝ ነበሩ።

መጀመሪያ ላይ የኔ ኑሮ መመስከር አለበት። ቤቴ ድረስ መጥተው ኑሮዬን እንዲያዩ አደርጋለሁ። ኮሚቴዎቹን ተራ በተራ ቡና አፍልቼ ቤቴ በመጥራት ኑሮዬን እንዲያዩ አደርጋለሁ። በእኔ ህይወትም እራሳቸውን እንዲቀይሩ አደርጋለሁ።

ሰንደቅ፡- ማህበሩ ከእድሜ አንጻርስራውን እያከናወናችሁ ያላችሁት በተወሰኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ብቻ ነው። ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? ወደ ሌላ ለማስፋፋት ስምን ታስቧል?

ወ/ሮ ገነት፡-እስከአሁን ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ በአስሩም ክፍለ ከተማዎች ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው። በእነዚህ ክፍለ ከተሞች ኮታ እየያዝን ፈቃደኛ የሆኑት እየመጡ ይማራሉ። በሀገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን ዓላማችን አፍሪካን እና አለምን ማዳረስ ነው። ነገር ግን የገንዘብ እጥረት አለብን። ከአዲስ አበባ ወጣ በማለትም ለገጣፎ አካባቢ እየሰራን እንገኛለን። በዚህች ከተማ ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ጋር በመተባበር 28 ሴቶችን አቋቁመናል።

ሰንደቅ፡- የእርዳታ ድርጅቶች ብዙ ጊዜ እንረዳዋለን ብለው ላቋቋሙት ህብረተሰብ አይሰሩም፤ መጠቀሚያ ነው የሚያደርጉት ይባላል። የእርስዎስ ድርጅት በዚህ በኩል እንቅስቃሴው ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ገነት፡-በስማችን ገንዘብ እያመጡ ይበላሉ ይባላል። ሊያደርጉ የሚችሉም ይኖራሉ። ፕሮፖዛሉ በቀረበው ባህሪይ ነው እንጂ የሚሄደው ሁሉም አንድ አይደለም። ገንዘብ ለሰጠው አካልም የሚቀርበው ሪፖርት የውሸት መሆን የለበትም። የመጣለት ድሃም በገንዘቡ መገልገል አለበት። እኔ በመጀመሪያ ይረዳኝ የነበረው የኢትዮጵ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ነበር። ጠአም ያለው ስራ የሰራሁትም ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር ነው። በአባኮራን ሰፈር ራስ እምሩ ግቢ ውስጥ በልብስ እጥበት 55 ሴቶችን አደራጅቻለሁ። በገንዘብ ረገድ ከሲዳ ጋር ነው የሰራሁት እንጂ ሌላ የውጭ ድጋፍ የለኝም። እኔም እንደሰራተኛነቴ ደሞዝ ይከፍሎኛል። ያም ሆኖ ከቴክኒክና ሞያ ፈቃድ ወስዶ ይሰራ የነበረው የአይሲቲ ማዕከሉ የቤት ኪራይ ይችል ነበር።

ሰንደቅ፡- ይህንን ስራ በሚያከናውኑበት ወቅት የገጠመዎት ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?

ወ/ሮ ገነት፡-ስራው በጣም ከባድ ነው። ሴቶቹ ዛሬ በደንብ አድርጌ ገንብቼ አጨብጭበው ደስ ብሏቸው ከሄዱ በኋላ እዚያ ቡና ሲጠጡ የተገነባውን ግንብ አፍርሰው ሌላ መልክ ይዘው ይመጣሉ። ብዙ ችግር አውርተው አልቅሰው፤ እንደተማሩ ሆነው ይሄዱና ተቀይረው ይመጣሉ። ያንኑ በየጊዜው መገንባት ይፈትናል። ስነ-ልቦናን መቀየር በጣም ከባድ ነው። ለምን ገባሁበት የምልበት ጊዜ አለ። እንደዚያም ሆኖ ከ50 ሴት 5 ሴት ማውጣት ከተቻለ ጥሩ ነው። በአራዳ ክፍለ ከተማ ለምሳሌ ከ150 ሴቶች ጠንክረው የተገኙት 50 ብቻ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ እስከ ዛሬ ያሉት 28 ሴቶች ብቻ ናቸው። ግን መታከት የለብንም። እስከመጨረሻው ድረስ መስራት ያስፈልጋል።

ሴቶቹ ጠንክረው ሆ ብለው ሲመጡ ቀበሌ ላይ ችግር አለ። ለመተባበር ፈቃደኛ ያለመሆን አለ። የሚተባበሩት ደግሞ ፍርሃት አላቸው። ከኤንጂኦ ጋር በመተባበር እየተባሉ መገምገም ይመጣል። ይሄንን ችግር ፈትቼ ስመለስ ደግሞ የገነባሁት የሴቶች ስብስብ ይፈርሳል። ሴቶችን ተናጥቄ ነው እያወጣሁ ያለሁት።

በምሰራበት ወቅትም የገጠሙኝ ነገሮች አሉ። ሴቶቹን በሲልክ ስክሪን ህትመት በሲኒ፣ በሳህን፣ በአልጋ ልብስ እና በመጋረጃ ላይ ማተምን በቀላሉ ይማራሉ። የሚማሩት በፍላጎት ነው። የሚገርመው ግን በከተማው ውስጥ ይሄንን ስራ የሚሰሩ ሰዎች ስልጠናውን በነፃ እየሰጠች ሞያውን አራከሰች ብለው አድመውብኛል። ልታስተምር የወጣች አንዲት ሴትም ሞያዬን ስለምሰጥ የተለየ ክፍያ ይከፈለኝ ያለችበት ጊዜ ነበር። አዶቤ ሾፕም ስናስተምር ፒያሳ አካባቢ ጠቅላላ አሳድመውብኝ ነበር። ግን የደረስኳቸውን አስተምሬያለሁ።

ሰንደቅ፡- ከዚህ ስራ አገኘሁት የሚሉት ነገር ምንድን ነው?

ወ/ሮ ገነት፡-እርካታ አለኝ። ምንም አላግኝ እርካታ ግን አግኝቼበታለሁ። መጀመሪያ የምንጀምረው በጋብቻ ነው። ሴት ምድራዊ መልአክ ናት ብለን ነው የምንጀምረው። ወንድን የምትገነባ ሴት አገልግሎቷ ቀላል አይደለም። ከቤቷ ጀምራ እስከ ሀገር የምትመራ ሴት ናት። ስለዚህ ይህቺ ምድራዊ መልአክ ራሷን መጣል የለባትም። ክብሯን ጠብቃ እና ችግሯን ተቋቁማ መውጣት አለባት ብዬ ነው የማስተምረው። በዚህም ራሴን በብዙ ሴቶች ውስጥ ፈጥሬዋለሁ። ይሄ በጣም ያስደስተኛል። ወንዶቻቸውም እየመጡ ያመሰግኑኛል።

አንዲት ሴት ልደታ ላይ ሳስተምር መጥተው ሰሙ። ሳስተምር “ባሎቻቸው ቢሰክሩም እንኳ መውቀስ እና ማስወቀስ እንደሌለባቸው፤ ነገር ግን መጥቶ ወድቆ መሶቧን ቢደፋባት፣ ቢያስመልስባት ዛሬ ወንድሜ ብላ ጠርታ እጥብጥብ አድርጋ ልታስተኛው ይገባል። መንከባከብ አለባት። ያንን የሚያደርገው አእምሮ ሳይሞት አውቆ ነው። እየሰደበችው ስትሄድ እየባሰበት ይመጣል። ነገር ግን ብትንከባከበው ያንን ነገር ይጥለዋል” እያልኩ ነበር። ያንን በመስማታቸው ያልኳቸውን አድርገው ምስክርነት ሰጥተዋል። “ገነት ያለችኝን ሳደርግ እንደህጻን ልጅ ገላዬን አጥቦ ነው አልጋ ላይ ያስተኛኝ። ለካ ራሴን የምጎዳው እኔው ነኝ ነው” ያሉት።

     ሴቶች ኃላፊነታችን ሰፊ በመሆኑ አስፍተን በማሰብ ምድራዊ መልአክነታችንን መመስከር አለብን። እኛ ስንፈጠርም ረዳት ተደርገን ነው የተፈጠርነው። የምንረዳው አቅመ ቢሱን ሰው፣ አቅም ስላለን ነው የምንረዳው። ስንረዳ ደግሞ አቅም ብቻ ሳይሆን የምንረዳበት አእምሮም ነው የተሰጠው። ዛሬ እነዚህ ሴቶች ይሄንን ምክርና ትምህርት ለራሳቸውም ሲጠቀሙበት በጣም ነው የሚያስደስተኝ። ከምንም በላይ እነዚህን ሴቶች በማፍራቴ እርካታዬ ታላቅ ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1580 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 925 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us