ከሃና ጥቃት ጀርባ

Wednesday, 26 November 2014 13:07

ምናልባትም በሀገራችን ታሪክ ውስጥ እጅግ አስደንጋጭ ሊሆን የሚችል አደጋን ነው ከሰሞኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ስንከታተል የሰነበትነው። የ16 ዓመቷ ታዳጊ ሃና ላላንጎ ተሰምቶና ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በአምስት ወንዶች ተገዳ በመደፈሯ ህይወቷን ማጣቷን ተከታትለናል። ታዳጊዋ ራሷን መከላከል በማትችልበት ሁኔታ በደረሰባት ተገዳ መደፈር ህይወቷን ማጣቷን ተከትሎ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ግን እርግጠኛ የሆነ መረጃን ማግኘት አልተቻለም። ይህም ሆነ ያ ሃና በዚህ አስደንጋጭ መንገድ ህይወቷን ሰውታለች።

ታዳጊ ሃና ለቤተሰቦቿ የመጨረሻ ልጅ ስትሆን፤ በተለይ በአባቷ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ እና ከአይናቸው ሊያጧት የማይፈለጓት ልጅ እንደነበረች ታላቅ ወንድሟ ለመገናኛ ብዙሃን ገልፆ ነበር።

ይህ በሃና ላይ የደረሰ ክስተት በወንጀሉ ግዝፈት አሊያም በተደረገው ከፍተኛ የህዝብ ርብርብ ይፋ ይደረግ እንጂ በርካታ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በየቀኑ በተመሳሳይ መልኩ ህይወታቸው ያልፋል። ብዙዎችም ተሰናክለው ቀርተዋል። ተገዶ መደፈር በማህበረሰባችን ከደፋሪው (ከወንዱ) ይልቅ የሴቷ ስህተት ተደርጎ የሚወሰድበት ጊዜም አለ። ወንዱ ከሴቷ በላይ ነው ተብሎ በመታሰቡ ሴቷ ለዚህ አይነቱ ድርጊት እንደገፋፋችው በማሰብም የችግሩ ምክንያት ሴቷ ተደርጋ ትወሰዳለች። ይህን ወንጀላ በመፍራትም በርካቶች የደረሰባቸውን የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ለቤተሰባቸው እንኳ አይነግሩም።

በታዳጊ ሃና ላይ የተፈፀመው ወንጀል የሃናን ህይወት ይዞ ያለፈ ቢሆንም፤ ዛሬም ግን በርካታ ሃናዎች ነገ ምን ሊደርስባቸው እንደሚችል በማያውቁት ስሜት ውስጥ እንዲኖሩ እያደረጋቸው ይገኛል። ክስተቱን የሰሙ በርካታ ሃናዎችም ከድንጋጤ እና ከመሪር ሀዘናቸው በስተጀርባ ያለው የራሳቸው እጣ ፈንታ አሳስቧቸዋል። የታዳጊዋ ጉዳይ በህግ የተያዘ እና ጉዳዩ ከተጣራ በኋላ ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድበት ቢሆንም፣ ለጠቅላላ ግንዛቤ ያህል አስገድዶ መድፈር በሀገራችን፣ አህጉራችን እና በአለማችን ላይ ምን አይነት ገፅታ እንዳለው እንዲህ አቅርበነዋል።

ወንዶች ሴቶችን ለምን አስገድደው እንደሚደፍሩ ከተደረገ ጥናት ማረጋገጥ የተቻለው፣ ለዚህ ወንጀል የሚገፋፏቸው ምክንያቶች መኖራቸው ነው። ከእነዚህ ምክንያቶች መካከልም የሴቶች አለባበስ፣ የወንዶች አደንዛዥ እፅ እና ሌሎች ነገሮችን መጠቀም ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም የሀገራቱ ሕግ በአስገድዶ መደፈር ላይ የሚጥለው ቅጣት አነስተኛ መሆኑ እንደ ምክንያት ተቀምጠዋል። ሌላው ምክንያት ደግሞ ወንዱ ራሱ በሴቶች ተቀባይነት ላላገኝ እችል ይሆናል በሚል ስጋት ሴት ልጅን አስገድደው ይደፍራሉ። ከሁሉም በላይ ግን ወንዶች በድፍረት ድርጊቱን እንዲፈፅሙ የሚያደርጋቸው ወሲብን በተመለከተ ሴቶች ግልጽ አውጥተው ስለማይናገሩ፣ ቢናገሩም ተደማጭነት ስለማያገኙ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ።

በኢትዮጵያ ወንዶች በሴቶች ላይ ያላቸው የበላይነት በበርካታ ሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር እንዲፈፀም ሁኔታዎችን ያመቻቻል። በኢትዮጵያ አስገድዶ መድፈርን አስመልክቶ በቂ የሆነ መረጃ ባይኖርም ይህ ድርጊት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመር ላይ እንዳለ ከተለያዩ ሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። አስገድዶ መድፈር የደረሰባት ሴት የተፈፀመባትን ወንጀል ለሌላ ሰው ብትገልፅ ከማህበረሰቡ የሚደርስባትን መሸማቀቅ እና ሌሎች ተፅዕኖዎች በመፍራት ጉዳዩን የራሷ ምስጢር ብቻ ማድረግን ትመርጣለች።

እ.ኤ.አ በ2011 በተባበሩት መንግስታት የተጠና ጥናት እንዳመለከተው ኢትዮጵያውያን ወንዶች በሴቶች ላይ የአሰገድዶ መድፈር አደጋ የሚያደርሱባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ ምክንያቶች መካከልም ወንዱ ወሲብ ለመፈጸም ያለው ፍርሃት እንዲሁም ወሲብ ለመፈጸም በቂ አቅም እና ችሎታ አለኝ ብሎ በራሱ አለመተማመን ይገኝበታል። የተወሰኑት ደግሞ ይህን የአስገድዶ መድፈር አደጋ ለምን እንደፈፀሙ ሲጠየቁ የሚሰጧቸው መልሶች እጅግ አሳዛኝ እና ሊታመኑ የማይችሉ መሆናቸውን ነው ጥናቱ ያመለከተው። ደፋሪዎቹ ከሰጧቸው ምላሾች መካከልም ብቻዋን ስላገኘኋት፣ እራሷ ይህን እንድፈፅም ስለገፋፋችኝ እንዲሁም አለባባሷ ለዚህ ድርጊት ስለጋበዘኝ እና የመሳሰሉት ምላሾች ይገኙበታል።

በሴቶች ላይ የሚደርሱ አስገድዶ መድፈሮች በታዳጊ ሀገራት ብቻም ሳይሆን በመላው አለም ላይ የብዙ ሴቶችን ህይወት እያጨናገፉ ይገኛል። የተባበሩት መንግስታት በ65 ሀገራት ላይ ባደረገው ጥናት መሰረት በየዓመቱ ከ150 ሺህ በላይ ሴቶች አስገድዶ መድፈር እንደሚፈጽምባቸው ከፖሊስ የተገኙ መዛግብትን ጠቅሶ ዘግቧል።

ልክ እንደሌሎች ችግሮች ሁሉ አፍሪካ በዚህም በአስገድዶ መድፈር በከፍተኛ ሁኔታ ከተጎዱ ሀጉራት አንዷ ናት። በአፍሪካዊቷ ሀገር ቦትስዋና በ2011 በተደረገ ጥናት ማረጋገጥ እንደተቻለው በሀገሪቱ ካሉ ሴቶች 4 ነጥብ 6 በመቶዎቹ አስገድዶ መድፈር ተፈፅሞባቸዋል።

በጦርነት እየታመሰች በምትገኘዋ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ያለው የሴቶች ተገዶ መደፈር እጅግ አሰቃቂ መሆኑንም ጥናቶች ያመለክታል። በዚህች ሀገር በየአመቱ ከ40 ሺህ በላይ ሴቶች ተገደው ይደፈራሉ። በዚህም ሳቢያ በሃገሪቱ ተገዶ መደፈር፣ ርካሽ፣ ቀላል እና ከቦንብ እና ከጥይት ይልቅ በቀላሉ ሊገኝ የሚችል መሳሪያ እስከመባል ደርሷል። በዚሁ በጦርነት ቀጠና ውስጥ በምትገኘው ሩዋንዳም ያለው አስገድዶ መድፈር ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል። በሀገሪቱ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ወቅትም ከ100ሺ እስከ 250ሺህ የሚደርሱ ሴቶች መደፈራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሌላዋ አስገድዶ መድፈር አሳሳቢ የሆነባት አፍሪካዊት ሀገር ግብፅ ናት። በግብፅ በየአመቱ 200 ሺህ ሴቶች ተገደው ይደፈራሉ። ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ በአራት ቀናት ውስጥ 91 ሴቶች በታህሪር አደባባይ ተገደው ተደፍረዋል።

ከአፍሪካ ሀገራት ዜጎች በአስገድዶ መድፈር ከፍተኛ ጥቃት እየተፈፀመባቸው የሚገኙት ደቡብ አፍሪካውያን እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህች ሀገር የወራት እድሜ ካላቸው ህጻናት አንስቶ እስከ ትላልቅ ሴቶች ተገደው ይደፈራሉ። ለአብነት ያህልም ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት የዘጠኝ ወር እድሜ ያላት ህጻን ተገዳ ተደፍራ ህይወቷ ያለፈ ሲሆን በዚያው ዓመት ሌላ የዘጠኝ ወር ህጻን በስድስት ወንዶች ተደፍራ ህይወቷ ማለፉ ተዘግቧል። ከዚህ በተጨማሪም የ4 ዓመት ታዳጊ በወላጅ አባቷ ተደፍራ ህይወቷ አልፏል። እንዲሁም የ14 ወራት እድሜ ያላት ህጻን በሁለት አጎቶቿ ተደፍራለች። ይህን አይነቱ አሰቃቂ ድርጊት በደቡብ አፍሪካ ከመቀነስ ይልቅ እምርታን እያሳየ ነው የመጣው። በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ. በ2002 የስምንት ወራት እድሜ ያላት ጨቅላ ህፃን በአራት ወንዶች መደፈሯ ተዘግቦ ነበር።

በደቡብ አፍሪካ ከድንግል ሴት ጋር ወሲብ መፈፀም ኤች አይ ቪን ይፈውሳል በሚል አጉል እምነት የተነሳም በርካታ ሴቶች ተገደው ተደፍረዋል። በርካቶችም በዚህ ምክንያት ህይወታቸውን ሰውተዋል። ሀገራቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ የሴቶች ጥቃት ከሚፈፀምባቸው ሀገራትም አንዷ ናት። እስከ የካቲት 2012 መጨረሻ ድረስ እንኳን ከ65ሺህ በላይ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ጥቃቶች በሀገሪቱ ተፈፅመዋል።

ለአብነት ያህል እነዚህን ሀገራት አነሳን እንጂ ተገዶ መደፈር በሁሉም ሀገራት የሚፈፀም ወንጀል ነው። ሆኖም ግን በርካታ ሀገራት ምን ያህል ዜጎች የዚህ ወንጀል ሰለባ እንደሆኑ እንኳን በግልጽ የሚያስቀምጡት መረጃ የለም። በተለይ በኢትዮጵያ ወሲብን በተመለከተ ያሉ መረጃዎችን ይፋ ለማድረግ ከፍተኛ ችግር አለ። ወሲብ ነክ ነገሮች አይነኬ ከሚባሉት ጉዳዮችም አንዱ እና ዋናው ነው። ተጎጂዎችም ጉዳታቸውን እንዳይገልፁ ባህል፣ የማህበረሰብቡ አመለካከት እና ለሴቶች የሚሰጠው ዝቅተኛ ግምት ያግዳቸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስገድዶ መድፈርን በተመለከተ በየሀገራቱ ያሉት መረጃዎች አነስተኛ የሆኑባቸውን ምክንያቶቸ ለማስቀመጥ ሞክሯል። ከእነዚህ ውስጥ ጥቆማው የሚደርሳቸው ፖሊሶች ስለሴት ልጅ ተገዶ መደፈር ያላቸው አመለካከት አንዱ ነው። በቱርክ በተደረገ ጥናትም ከጥናቱ ተሣታፊ ፖሊሶች መካከል 33 በመቶዎቹ ሴት ልጅ ተገዳ መደፈር አለባት ብለው የሚያምኑ ሲሆን፤ 66 በመቶዎቹ ደግሞ ሴትን ልጅ ተገዳ እንድትደፈር የሚያደርጋት ውጫዊ ሁኔታዋ (አለባበሷ አረማመዷ እና የመሳሰሉት) ነው ብለው ያምናሉ።

ከዚህ በተጨማሪም እንደ ጥናቱ ከሆነ ጥቃቱ የሚደርስባቸው ሴቶች ጥቃቱን ይፋ ቢያደርጉ በማህበረሰቡ የሚደርስባቸውን መገለል መቋቋም ያቅታቸዋል። በቤተሰባቸው የሚጣልባቸው እምነትም ይነሳል። ከዚህ በተጨማሪም በአንዳንድ ሀገራት ማግጠዋል በሚል እስከ ስቅላት ለሚደርሱ ቅጣቶች ሊዳረጉ ይችላሉ። በቀጣይም የትዳር አጋር ማጣት፣ በማህበረሰቡ ውስጥ እንደማንኛውም ዜጋ ለመኖር አለመቻል እና ባስም ሲል ለሴተኛ አዳሪነት መጋለጥን ሊያስከትልባቸው ይችላል።

አስገድዶ መደፈር በተደፋሪዋ ላይ ብቻም ሳይሆን በቤሰቦቿ፣ በመላው ማህበረሰብ እና በሁሉም ዜጋ ላይ የሚያደርሰው ስነ-ልቦናዊም ሆነ ማህበራዊ ቀውስ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። ዛሬም ብዙዎች በሃና ጥቃት አንገታቸውን ደፍተዋል። በስሜትም የየራሳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል። ሆኖም ግን ከዚህ ክስተት በስተጀርባ ያለው ነገር ብዙ መስራትን ይጠይቃል። በርካቶችአቋም ይዘው ለሃና ፍትህን እያፈላለጉ ነው፤ ብዙዎችም ድርጊቱን እያወገዙ ነው። ነገር ግን ጉዳዩ ሰው በፆታው ሳይሆን በሰብዓዊነቱ ብቻ ከጥቃት ነፃ ሆኖ የሚኖርበትን አለም የመፍጠር ጥያቄ ነው። 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
2976 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 876 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us