አንዲት የውሃ ጠብታ መርከብ ታሰምጣለች

Wednesday, 03 December 2014 13:09

 

 

ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ

 

የዛሬ 15 ዓመት በአንዲት ጠባብ ጊቢ ውስጥ ጥቂት ተማሪዎችን በመዋዕለ ህፃናት ደረጃ ማስተማር የተጀመረው እንቅስቃሴ ዛሬ የበርካቶችን ህይወት መለወጥ ችሏል። ጅማሬው በህጻናት ላይ ቢሆንም ዛሬ ግን ግቢው ውስጥ የሚታዩት እንቅስቃሴዎች በአንድ መንደር ውስጥ ያለን ያህል ያስመስለዋል። በጊቢው ውስጥ የተለያዩ የባልትና ውጤቶች፣ የእጅ ሞያዎች እንዲሁም የመማር ማስተማር ተግባራት ይከናወናሉ። ከመገናኛ ወደ ኮተቤ በሚወስደው መንገድ ኮተቤ የመምህራን ኮሌጅ አጠገብ የሚገኘው ሙዳይ የበጎ አድራጎት ማህበር በዚህ አካባቢ ለዓመታት እነዚህን ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል። አሁን ላይ ግን የማህበሩ አባላት መጨመር እና የኑሮ መወደድ እየተፈታተነው ይገኛል።

የማህበሩ መስራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙዳይ ምትኩ ስለማህበሩ ማብራሪያ ሰጥተውናል። “ስጀምረው በትምህርት ቤት ነበር። ከእናቴ ጓደኛ ጋር በአክሲዮን ነበር ትምህርት ቤት የከፈትነው። እኔ ገና 18 አመቴ ነው፤ እርሷ ደግሞ ቤተሰብ ስለነበራት አብዛኛውን ኃላፊነት የምወስደው እኔ ነበርኩ። በዚህ ታዲያ አንዳንድ ሰዎች ምግብ ስለሚያበሏቸው ብቻ ልጆችን ያልክፍያ ሲያሰሯቸው አያለሁ። ደግሞ የቤት ሰራተኞች ልጆቻቸው ቤት ውስጥ እንደሚሰሩ እሰማለሁ። ይሄንን ስሰማ በጣም ይሰማኝ ነበር። በዚህም አንድ ጊዜ አንድ ሰራተኛ ቤት ቀጥ ብዬ ሄጄ ልጅሽን አምጪ በነፃ ላስተምርልሽ ብዬ ትምህርት አስጀመርኩት” ሲሉ አነሳሱን ገልጸውልናል።

በዚህ መልኩ በችግር ውስጥ ያሉ እና በነፃ ትምህርት መከታተል የሚፈልጉ ህጻናት ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ት/ቤቱን በከፈቱት ባለድርሻዎች መካከል አለመግባባት እየተፈጠረ መጣ። “እርሷ እንደቢዝነስ ስላሰበችው በነጻ እናስተምር የሚለውን ልትቀበል አልቻለችም። በዚህም እቃ ተካፍለን እኔ በነፃ ማስተማር ስጀምር እንደልቤ መወሰን ስለምችል ነፃነቴን አወጅኩ” ይላሉ ወይዘሮ ሙዳይ። በእዚህ ነፃነትም የተወሰኑ ከፍለው የሚማሩ እና የማይከፍሉ ህጻናትን ደባልቀው ማስተማር ቢጀምሩም ችግሩ በዚህ ሊፈታ አልቻለም። የደንብ ልብስ ለብሰው ቀን በትምህርት ቤት የሚውሉ ችግረኛ ህጻናት ከት/ቤት መልስ በልመና ላይ ወደተሰማሩት ወላጆቻቸው ያመራሉ። ከነደንብ ልብሳቸው በዚህ ቦታ የሚያዩዋቸው ከፍለው የሚያስተምሩ ወላጆችም ጥያቄ ይዘው ወደ ትምህርት ቤቱ መጡ።

“ከፋዩ ህብረተሰብ ልጆችን ሲያዩ ኮሚቴ አቋቁመው መጡ። ምርጫም ሰጡኝ። ልጆቻችን በልመና ከሚተዳደሩ ልጆች ጋር ሲማሩ በሽታ ይይዛቸዋል። ተባይ እና ሌሎች ነገሮችም ይይዟቸዋል። እነርሱን ከፈለግሽ እኛን አስናብቺን፣ እኛን ከፈለግሽ ደግሞ በነበረው ስርዓት እንሂድ አሉኝ። እኔም ንፅህናቸውን ጠብቄያለሁ፣ ዩኒፎርም አልብሻለሁ ብዬ ብከራከርም እምቢ ብለው ሲሄዱ የችግረኛ ልጆች እና ጥቂት ከፍለው መማር የሚችሉ ፈቃደኞች ብቻ ቀሩ” ሲሉ ያስረዳሉ። በዚህም ሳቢያ ቢያንስ ዓመቱን ለማጠናቀቅ የሚያስችላቸውን እርዳታ ከሚያውቋቸው ሰዎች እየለመኑ ማስተማር ጀመሩ።

ትምህርት ቤቱን ከባለድርሻው ጋር ማስተዳደር እንደቀረም ወይዘሮ ሙዳይ በመጀመሪያ የወሰዱት እርምጃ አስከፍሎ ማስተማርን ማቆም ነበር። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱን እንዲህ ይገልፁታል። “የመጀመሪያ ምክንያቴ ምግብ ነበር። አንዱ መኮሮኒ ወይም ፓስታ ይዞ ሊመጣ ይችላል። ሌላው ደግሞ ደረቅ ዳቦ ሊሆን ይችላል ያመጣው። ያቺው ደረቅ ዳቦ ጠፍታ ባዶ እጁን የሚመጣም ይኖራል። ልጆቹ አንድ አይነት ልብስ ለብሰውና በአንድ ገበታ እየበሉ ምግባቸው ሲለያይ ሥነልቦናቸው በጣም ይጎዳል። ስለዚህ ከፍለው ማስተማር የማይችሉ በልመና እና በሴተኛ አዳሪነት ህይወት የሚኖሩ እንዲሁም የተለያዩ ድርጅቶች እየከፈሉላቸው የሚማሩ የድሃ ልጆች ብቻ እንዲማሩ ነው ያደረኩት” የሚሉት ወይዘሮ ሙዳይ ለእነዚህ ልጆች ከገርጂ ኮተቤ ድረስ ምግብ እያመላለሱ ያበሉ እንደነበርም ገልጸውልናል። ይሄ አላዋጣ ሲላቸውም በት/ቤቱ ግቢ ውስጥ ወተት እና ዳቦ ለህፃናቱ መመገብ ጀመሩ።

ህጻናቱን ከወተት እና ዳቦ ተመጋቢነት ለማውጣት በማሰብም በግቢው ውስጥ ለህፃናቱ ምግብ እንዲያዘጋጁ፣ ለራሳቸው በልተው ልጆቻቸውንም እንዲያበሉ በማድረግ 21 ያህል የጎዳና ተዳዳሪዎች እንዲሰሩ ተደረገ። በዚህም ህፃናቱ በቀን አንድ ጊዜ እንዲበሉ ተደረገ። እነዚህ የጎዳና ተዳዳሪዎች እና ሴተኛ አዳሪዎች በሳምንት አንድ ጊዜ ምግብ እየሰሩ ጎን ለጎን ደግሞ እጅ ስራ ሰርተው ገቢ እንዲያገኙም ይደረጋል። በማህበሩ የሚረዱት ሴቶች ባል የሌላቸው በመሆናቸው ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ወላጆች ደግሞ ወደ ስራ እንዲሄዱ ተደርጓል። በዚህ መልኩ በጊቢው ውስጥ በሽመና ሞያ ላይ ያገኘናት ሰናይትም የገለፀችልን ይሄንኑ ነው።

ሰናይት በልጅነቷ ካገባችው ባሏ በተለያየችበት ወቅት አንድ ልጅ ወልዳ ሁለተኛዋን ነፍሰ ጡር ነበረች። ልጁን ለማሳደግ እና ኑሮዋን ለመኖርም በሰው ቤት በተመላላሽነት መስራትን ነበር አማራጭ ያደረገችው። ነገር ግን እርግዝናዋ እየገፋ ሲመጣ ስራውንም በመተው ውሎና አዳሯን ጎዳና ላይ አደረገች። ያረገዘቻት ልጇንም በጤና ጣቢያ ብትውልድም የኔ የምትለው ማረፊያ ግን አልነበራትም። “ልጄን የወለድኳት ጤና ጣቢያ ነው። ሌሎች ወልደው ልጃቸውን ይዘው ወደቤታቸው ሲገቡ እኔ ግን ልጄን ለድርጅት ልሰጥ ስንከራተት ነበር። ግማሾቹ ልጅ የሚወስድ ድርጅት መገናኛ አለ ይሉኛል። ሌሎች ደግሞ መሳለሚያ አለ ይሉኛል። ግን ተንከራትቼ ማንንም ባላገኘሁበት ጊዜ ነው ወደዚህ ማህበር የመጣሁት” ስትል እንባ እየተናነቃት ትናገራለች። “እኔ ሞቼ እንደገና እንደተነሳሁ ነው የሚሰማኝ። ሙዳይን ባላገኝ የሌሊት ጅብ ሳይሆን የቀን ጅብ ነበር የሚበላኝ። እንኳን ልጅ ይዞ ለአንድ ራስም ይከብዳል” ትላለች።

ሰናይት በማህበሩ ውስጥ ከምግብ ሰራተኝነት እስከ ፅዳት ሰራተኝነት የሰራች ሲሆን፤ በገጠማት የአስም ህመም ምክንያት በአሁኑ ወቅት ወደ ሽመና ስራ ተዛውራለች። ይህን ስራ በመስራቷ በወር የ650 ብር ደሞዝ ተከፋይ ናት። ማህበሩ የ500 ብር ቤት የተከራየላት ሲሆን፣ ልጆቿን እዚያው አስተምራ፤ መግባ እና ለራሷም ተመግባ ወደ ቤቷ ትሄዳለች። በዚህም ህይወቷ መቀየሩን አጫውታናለች። “በጎዳና ህይወት ላይ መናገር የማልችለው ችግር ይገጥመኝ ነበር። ሰካራም አለ፣ ሴት እንደመሆኔ መደፈር አለ። አሁን ግን ቢያንስ የኔ የምለው ቤት አለኝ። እንደሰው ያማረኝነት ነገር ገዝቼ መመገብ እችላለሁ። የአሁኑን ካለፈው ህይወቴ ጋር ሳነፃፅረው ልዩነቱ የሰማይ እና የምድር ያህል ነው” ትላለች።

 

በሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር ውስጥ ራሳቸውን እያገዙ ከሚገኙት እናቶች መካከል ከ75 በመቶ በለይ የሚሆኑት ከኤች አይቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥም በርካታ አካል ጉዳተኞች አሉ። በአጠቃላይ በማህበሩ ውስጥ 430 የጎዳና ተዳዳሪዎች እና ሴተኛ አዳሪ የነበሩ ሴቶች ይገኛሉ። እነዚህ ሴቶች ልጆቻቸውን በብቸኝነት የሚያሳድጉ ናቸው። በመሆኑም በሚፈልጓቸው የእጅ ሞያዎች ላይ ተሰማርተው በመስራት ገቢያቸውን ይፈጥራሉ። ማህበሩ በኪራይ ባገኛቸው ሁለት ቤቶች ውስጥ የሸክላ ስራ፣ የጨሌ እና የተለያዩ ጌጣጌጥ ስራዎች፣ የሽመና እና የፈትል ስራ እንዲሁም የስፌት ስራዎች ይሰራሉ። እነዚህ ሴቶች እርስ በራሳቸው በመማማር የምታውቀው ለማታውቀው በማሳየት ነው ይሄንን ሞያ የለመዱት። ስልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ የገንዘብ አቅም ስለሚጠይቅ ስልጠናውን መስጠት አልተቻለም። እነዚህ ሴቶች ከሚያገኙት ገቢ ላይ እቁብ እንዲጥሉ አልፎም ደግሞ ገንዘባቸውን በባንክ እንዲያስቀምጡ ይደረጋሉ። ይሄንን ማድረግ ያስፈለገውም ነገ ማህበሩ ቢቆም የሴቶቹ ህይወት እንዲቀጥል በማሰብ መሆኑን ወ/ሮ ሙዳይ ይገልፃሉ።

“ሴቶቹ ሞያውንም ገንዘብም እንዲይዙ አደርጋለሁ። ነገ እኔ በሆነ ምክንያት ባልኖር እነዚህ ሴቶች ወደቀድሞ ህይወታቸው መመለስ የለባቸው። ካሉበት መቀጠል ነው ያለባቸው። ራሳቸውን ችለው ሰርተው ህይወታቸውን ወደተሻለ ደረጃ ማራመድ አለባቸው” የሚሉት ወይዘሮ ሙዳይ፤ ዋና የትኩረት አቅጣጫቸው ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን እንዲህ ይገልጻሉ።

“የመጀመሪዋ አስተማሪ እናት ናት። ሴት ደግሞ ባል ባይኖርም ሰርታ ራሷን መቻል እንደምትችል ማወቅ አለባት። ይሄ ደግሞ ራሷን ከመጠበቅ ይጀምራል። ንፁህ ልብስ ለብሳ፣ ራሷን ጠብቃ መገኘት አለባት። ከዚያ በመቀጠል ጥሩ በራስ መተማመን ይኖራታል” ይላሉ።

ሴቶቹ ከስራቸው ጎን ለጎን ትምህርትም እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። ቀድሞ ወ/ሮ ሙዳይ ማታ ማታ ለሴቶቹ ትምህርት ይሰጡ የነበሩ ሲሆን፤ አሁን ግን በጎልማሳ ትምህርት ፕሮግራም ተካተው በመማር ላይ ይገኛሉ። ይሄ ደግሞ በራሳቸው መተማመንን ይጨምርላቸዋል።

በማህበሩ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከመዋዕለ ህጻናት እስከ 7ኛ ክፍል ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል። ከ7ኛ ክፍል በላይ ያሉ ወደ 90 የሚደርሱ ተማሪዎች ደግሞ ማህበሩ ሙሉ ወጪያቸውን ሸፍኖላቸው ቤት ተከራይተው በመቀመጥ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ። በዚህ ማህበር እርዳታ እየተደረገላቸው ዩኒቨርስቲ እየተማሩ ያሉም አሉ። ከእነዚህ ልጆች በተጨማሪ ግን ወይዘሮ ሙዳይ የአብራካቸው ክፋይ ከሆኑ ሁለት ልጆች በተጨማሪ 18 ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን በቤታቸው ውስጥ ይረዳሉ። ልጆቻቸውም እርሳቸውም የሚኖሩት በዚያው በማህበሩ ግቢ ውስጥ በምትገኝ ባለሁለት ክፍል ቤት ውስጥ ነው። የሚመገቡትም ከማህበሩ አባላት ጋር ነው።

ወጣት ሮማን ተስፋዬ የተወለደችው ሀረር ሲሆን ወላጅ እናቷን በሞት በማጣቷ ዘመድ ተከትላ ወደ ዱከም ከተማ መጣች። እዚያው ከተዋወቀችው ሰው ስትፀንስ ከልጇ አባት ጋር በመጣላቷ ወደ አዲስ አበባ መጥታ በሰው ቤት ሰራተኛነት ተቀጠረች። ልጇን በምትወልድበት ጊዜም ነገሮች አስቸጋሪ ሆኑባት። “ወልጄ ከሶስተኛ ቀኔ ጀምሮ አሰሪዬ ውሃ እንድቀዳ ታደርገኝ ነበር። ምግብ እንኳን ሳትሰጠኝ እየቀረች በአራስ ቤት እራብ ነበር” የምትለው ወጣት ሮማን በመቀጠልም ያንን ቤት ጥላ በመውጣት መተዳደሪዋን በሰው ቤት ልብስ ማጠብ አደረገች። በወር 70 ብር እየተከፈላት ከዚያችው ላይ ደግሞ ቤት ኪራይ እየከፈለች ልጇን በማሳደግ ላይ ሳለች የዛሬ አራት አመት ገደማ ወደዚህ ማህበር በጥቆማ መጥታለች።

ወጣት ሮማን በማህበሩ ውስጥ በሳምንት አንድ ቀን ለህጻናት እና ሴቶቹ ምግብ የምታበስል ሲሆን፤ ቀሪውን ጊዜዋን ግን ከዘንባባ ስፌቶችን በመስፋት ታሳልፋለች። በወር 900 ብር ደሞዝ የሚከፈላት ሲሆን፣ ከዚህ ገንዘብ ላይም 300 ብር እቁብ ትጥላለች። የሰባት ዓመቱ ልጇ በዚያው የማህበሩ ትምህርት ቤት በመማር ላይ ይገኛል። “እዚህ አገር የማውቀው ሰው እንኳን በሌለበት በጣም ስቸገር ነበር። በጣም ከመቸገሬም የተነሳ የምበላውን ነገር ሁሉ እስከማጣት ደርሼ ነበር። እናቴ ብትኖር አስተምራኝ ጥሩ ደረጃ ላይ እደርስ ነበር” ትላለች ወጣት ሮማን። አሁን ግን በወር የምታገኘውን ገቢ በማብቃቃት የተሻለ ህይወት እየመራች ትገኛለች።

    ወ/ሮ ሙዳይ ይህን ስራ ሲሰራ ለማህበሩ መተዳደሪያ የሚሆኑ የተለያዩ ስራዎችን ከጎን ይሰራሉ። ላሞችን ማርባት እና ወተት ማከራየት አንዱ ሲሆን፤ በተጨማሪም አትክልቶችን ያለማሉ። ከዚህ ውጪ ግን የማህበሩን ወጪ የሚሸፍኑት ከራሳቸወ ኪስ እና ከአንዳንድ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን በሚገኙ ገንዘብ እንደሆነ ገልፀውልናል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1587 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 901 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us