ያልተመጣጠነው የግል ሆስፒታሎች ዋጋና የህመምተኞች አቅም

Wednesday, 31 December 2014 12:45

“መክፈል አልቻልንም” - ሕሙማን

በመላኩ ብርሃኑ

የሕክምና ወጪ ለመሸፈን ለልመና ከተሰማሩት አንዷ

 

ከቀዝቃዛው የህዳር ወር ምሽቶች በአንዱ። ወደየጉዳያቸው ከሚጣደፉት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል ስቃይ በሚነበብበት አይኗ አላፊ አግዳሚውን የምትማጸን አንዲት ታዳጊ መኪና ተደግፋ ቆማለች። ሰዎች አጠገቧ ሲደርሱ በእጇ የያዘችውን በአዳፋ ላስቲክ የተሸፈነ ወረቀት ወጣ አድርጋ ለማሳየት ትሞክራለች። ወረቀቱ ባህርዳር ከሚገኘው ፈገለገህይወት ሆስፒታል የተጻፈ የከፍተኛ ህክምና ማዘዣ (Referal slip) ነው።

የ16 ዓመቷ እናና ቢሻው የምትኖረው ጎጃም ዞን አዴት ከተማ ይልማዴንሳ በተባለ ወረዳ ውስጥ ነው። ይህንን ወረቀት ይዛ አዲስ አበባ የገባችው ለብዙ ዓመታት ሲያሰቃያት ከኖረው ህመም የመዳን ተስፋ ሰንቃ ነበር ። ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንደደረሰች ማዘዣውን የተቀበላት ሃኪም ከመረመራት በኋላ በሽታዋን አውቆ ተገቢውን ህክምና ለማድረግ በኤም.አር.አይ እንድትታይና ውጤቱን ይዛ እንድትመጣ አዘዛት። መሳሪያው የሚገኝበት የግል ሆስፒታል የጠየቃት 3ሺህ 500 ብር ክፍያ ግን ከአቅሟ በላይ መሆኑን ነው የምትገልጸው።

“አባቴ እስካሁን ያሳከመኝ የእርሻ በሬዎቹን ሸጦ ነበር። የያዝኩትን ጥቂት ብር ለመድሃኒት መግዣ፣ ለትራንስፖርት፣ ለምግብና ለማደሪያ አውዬው አልቋል። ከነበሽታዬ ወደሃገሬ ከመመለስ ውጪ የመዳን ተስፋ የለኝም። አሁን የትራንስፖርት ገንዘብ ለማግኘት ብዬ እየለመንኩ ነው” ትላለች-በዚያ ቀዝቃዛ ምሽት መንገድ ላይ ያቆማትን ምክንያት ስትናገር።

ከሁለት ወራት በፊት በኩላሊት ህመም የሚሰቃዩ ባለቤታቸውን ይዘው ከ500 ኪሎሜትር በላይ ከሚርቀው ሰሜን ወሎ ዞን ወደ አዲስ አበባ የመጡት ወይዘሮ የንጉስ በላይነው ደግሞ ከደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የተሰጣቸውን የኤክስሬይ ውጤት እያሳዩ እርዳታ መለመን ከጀመሩ አንድ ወር አልፏቸዋል።

“ባለቤቴ ህመሙ ከጀመረውና በየሃኪም ቤቱ መንከራተት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። በመጨረሻ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ስንሄድ ከባድ የኩላሊት በሽታ እንዳለበት ነገሩትና አዲስ አበባ ሄዶ እንዲታከም ጻፉለት። አዲስ አበባ መጥተን ሶስት የግል ሆስፒታሎችን ጠየቅን። በሃኪም የታዘዘለትን ህክምና [ጊዜያዊ የኩላሊት እጥበት] ለማግኘት በሳምንት ከስድስት ሺህ ብር ያላነሰ መክፈል እንዳለብን ነገሩን ። እኛ ጥሪታችንን አሟጠን ጨርሰናል። አምስት ልጆቻችንን ትተን ወደመጣንበት ቀዬ ለመመለስ የትራንስፖርት ገንዘብ ስላጣን እሱን በረንዳ ላይ አስተኝቼ እኔ እየለመንኩ ነው።” ብለዋል።

“እንግዲህ ቢሞትም ዘመድ መሃል ይሙት ብዬ ነው ወደመጣንበት ይዤው የምመለሰው” ይላሉ ወይዘሮ የንጉስ- አይናቸው እንባ እያቀረረ።

በጤንነት ላይ የተጋረጠ ሥጋት

ጥናቶች በኢትዮጵያ አንድን ዜጋ ከሚያሳስቡት መሰረታዊ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ውስጥ ከምግብና መጠለያ እንዲሁም መተዳደሪያ ስራ ከማግኘት ቀጥሎ የህክምና ወጪን በሶስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጡታል። የህክምና አገልግሎት ክፍያ በየጊዜው እየጨመረ መሄድ ባደጉም ይሁን በማደግ ላይ በሚገኙ ብዙ የዓለማችን ሃገራት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊም ይዘት ያለው አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል። በተለይ እንደኢትዮጵያ ባሉ ሲሶ ህዝባቸው በድህነት ወለል ስር በሚገኝባቸው ሃገራት ይህ ችግር የጎላ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገሪቱ የግል ሆስፒታሎች እየጨመረ የመጣው የህክምና ዋጋ “ኢትዮጵያ ውስጥ በከባድ ህመም ከመያዝ ይልቅ መሞት ይሻላል” የሚል አስተያየት ያላቸውን ዜጎች ቁጥር አበራክቶታል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የበርካታ የግል ሆስፒታሎች የአገልግሎት ዋጋ ከብዙሃኑ የሃገሪቱ ህዝብ የመክፈል አቅም ጋር ሲነጻጸር የማይሞከር ሆኖ መገኘቱ ነው።

“የሆስፒታሎች ቁጥር በቂ አይደለም”

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፖሊሲ ጥናት ዳይሬክቶሬት የተሰበሰቡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሃገሪቱ ላላት 85 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ መንግስት መገንባት የቻለው 125 ሆስፒታሎችን ብቻ ነው። በአምስት ክልሎች በመሰራት ላይ ያሉ 129 ሆስፒታሎች ግንባታ ሲጠናቀቅ ይህ የሆስፒታሎች ቁጥር ወደ 254 ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል። በአንጻሩ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤናና ጤና ነክ መረጃዎች አመላካች ጥናት እንደሚያሳየው በሃገሪቱ የሚገኙት የግል ሆስፒታሎች ቁጥር 56 ብቻ ነው።ከነዚህም መካከል 34 ቱ የሚገኙት በአዲስ አበባ ውስጥ ሲሆን የቀሩትም በጥቂት የክልል ከተሞች ውስጥ የተወሰኑ ናቸው። እንደቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሶማሊ እና ጋምቤላ ባሉ የሃገሪቱ ክልሎች ደግሞ ምንም አይነት የግል ሆስፒታል የለም።

እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ የተሰበሰቡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አንድ የመንግስት ሆስፒታል ከ680 ሺህ በላይ ለሆነ ህዝብ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በአንጻሩ በግል ሆስፒታል ተገልጋይ ምጣኔ መሰረት አንድ የግል ሆስፒታል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች አገልግሎት እንደሚሰጥ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

አንድ ዶክተር ለ28ሺህ 847 ዜጎች በሚዳረስባትና ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ እጥረት ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግስት የሚደጎሙ ሆስፒታሎች ቁጥር አነስተኝነት ሲታከልበት በሃገሪቱ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከባድ የጥራት ችግር እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል። ይህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ከህመማቸው ለመዳን ወደግል ሆስፒታሎች የሚያደርጉትን ምልልስ እንዲጨምሩ አስገድዷቸዋል። በዚህም ሳቢያ ሆስፒታሎቹ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታካሚ ያስተናግዳሉ። ያም ሆኖ የአገልግሎት ዋጋቸው ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የኢኮኖሚ አቅም ጋር ሲተያይ የማይሞከር ሆኗል።

ከጊዜ ወደጊዜ የጤና አገልግሎት ፍላጎት እየጨመረ በመጣባት ኢትዮጵያ የህክምና ዋጋ እየናረ መሄድ በጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳረፈ ስለመሆኑ ባለሙያዎች ይስማሙበታል።

የኢትዮጵያ የጤና ዋስትና ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዶክተር መንግስቱ በቀለ እንደሚናገሩት የኢትዮጵያ ህዝብ ለህክምና የመክፈል አቅምን በተመለከተ የተካሄዱ ጥናቶች እንዳረጋገጡት አንድ ዜጋ ከሚያገኘው ገቢ ለጤና አገልግሎት የመክፈል አቅሙ በሬሽዮ 0.33 በመቶ ብቻ መሆኑን አረጋግጠዋል። በርካታ የሃገሪቱ ዜጎች ዝቅተኛ ክፍያ በሚጠይቀው የመንግስት ሆስፒታል እንኳን ለመታከም የሚያስችል አቅም የላቸውም ያሉት ዳይሬክተሩ ይህም እውነታ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁትን የግል ሆስፒታሎች ለመጎብኘት እንደማይችል አመላካች ነው ይላሉ። ለህክምና የመክፈል አቅም ደካማ መሆን በጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ማነቆ ከፈጠሩት ችግሮች አንዱ መሆኑንም ዶክተር መንግስቱ ይናገራሉ።

የጤና መድህን ኤጀንሲ በቅርቡ ባካሄደው ጥናት እንዳረጋገጠው ለተመሳሳይ የህክምና አገልግሎት በግል ሆስፒታሎች የሚጠየቀው ዋጋ ከመንግስት ሆስፒታሎች ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ከ20 እጥፍ በላይ ይደርሳል። በተጨባጭ ምሳሌ ሲታይም አንድ የመንግስት ሆስፒታል ቀላል የሚባለውን የትርፍ አንጀት ቀዶ ህክምና ለመስራት 120 ብር ሲያስከፍል የግል ሆስፒታሎች ግን ከ3 እስከ 5 ሺህ ብር ድረስ ይጠይቃሉ። ይህ አሃዝም የአገልግሎት ክፍያውን ልዩነት ከ41 እጥፍ በላይ ያደርሰዋል።

ይህ ዘጋቢ መረጃ ለማሰባሰብ በተዘዋወረባቸው አዲስ አበባ፣ ባህርዳር፣ ደሴ፣ሃዋሳና አዳማ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ የግል ሆስፒታሎች የሚያስከፍሉት ዋጋ ከህብረተሰቡ የመክፈል አቅም ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑን ለመገንዘብ ችሏል። ለህክምና ወደሆስፒታሎቹ መጥተው ያገኛቸው አንዳንድ ሰዎችም “መክፈል አልቻልንም፣ ህክምና ማግኘትም አንችልም፣ሌላ ምርጫ የለንም” ብለውታል። አንዳንድ አስተየየት ሰጪዎች ደግሞ የከፈሉት ዋጋ ውድ መሆኑን ነገር ግን የተጠየቁትን ከፍለው ከህመማቸው ከመፈወስ ውጪ አማራጭ እንደሌላቸው ነው የተናገሩት።

“ሕይወቴን ለማትረፍ ቤቴን ሸጫለሁ”

የ64 ዓመቱ ጡረተኛ የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ ዘመነ መንግስቱ በልብ የደም ስር መጥበብ ሳቢያ ህይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁ የተነገራቸው ለአንድ ዓመት በፊት ነበር። በመንግስት ሆስፒታል ውስጥ ያክማቸው የነበረው ዶክተርም ይህ ህክምና በሆስፒታሉ እንደማይሰጥ በማስረዳት ህይወታቸውን ለማትረፍ ገንዘብ ከየትም ፈልገው እሱ በትርፍ ጊዜው ወደሚሰራበት የግል ሆስፒታል መምጣት ከቻሉ መፍትሄ እንደሚሰጣቸው ይነግራቸዋል።

“ልቤ በማንኛውም ጊዜ ስራውን እንደሚያቆም ነግሮ ተስፋ አስቆርጦኛል። ለሕክምናውን የተጠየቅኩትን 280 ሺህ ብር ለመሸፈን ያለኝ አንድ አማራጭ መኖሪያ ቤቴን መሸጥ ነበር።ነገር ግን ልጆቼ ማደሪያ እንዳያጡ ብዬ ሞትን መረጥኩ። ሆኖም ልጆቼ እያለቀሱ ስለለመኑኝ ቤቴን ሸጬ ታከምኩ። ህክምናው ከአንድ ቀን በላይ ባይፈጅም እኔና ልጆቼን ግን ሙሉ እድሜያችንን የሰው ቤት ተከራይተን እንድንኖር አስገድዶናል” ብለዋል።

ከ288ሺህ በላይ ነዋሪ ባላት ባህርዳር ከተማ ውስጥ ከሚገኙት ሁለት ሆስፒታሎች አንዱ ጋምቢ አጠቃላይ ቲቺንግ ሆስፒታል ነው። ይህ የግል ሆስፒታል በመንግስት ባለቤትነት ከሚተዳደረው ፈለገ ህይወት ሆስፒታል ጋር በድምሩ ከ5 ሚሊዮን በላይ ለሚገመቱ የአማራ ክልል እና አጎራባች ክልሎች ነዋሪዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ጋምቢ ሆስፒታል እንደ ኩላሊት እጥበት ህክምና፣ ሲቲ ስካን፣ ኢኮ ካርዲዮግራፊ፣ ታይሮይድ እና የካንሰር ምርመራዎች ያሉ በፈለገ ህይወት ሆስፒታል የሌሉ አገልግሎቶችን ይሰጣል። እነዚህ ምርመራዎች የታዘዙላቸው ብዙ የገጠርና የከተማ ሰዎች ወደዚህ ሆስፒታል ይሄዳሉ።

ይህ ዘጋቢ ሊቦ ከምከም ከተባለች የገጠር ወረዳ መጥተው በሆስፒታሉ ሲታከሙ ያገኛቸው ወይዘሮ አዘንጌ ዋልተንጉስ የታዘዘላቸው የልብ ምርመራ መሳሪያ ጋምቢ ሆስፒታል ብቻ የሚገኝ በመሆኑ ክፍያው ቢበዛባቸውም ከወዳጅ ዘመድ ተበዳድረው በመክፈል በአገልግሎቱን እየተጠቀሙ መሆኑን ይናገራሉ። “አሁን አሁን ግን ብሩ እያለቀ መድሃኒት መግዣም እያጣሁ ነው።ህክምናው ከቀጠለ በአቅም ማነስ ማቋረጤ አይቀርም ” ብለዋል።

ከአዊ ዞን የመጡት ወይዘሮ በርነሽ አባኔ በበኩላቸው የታይፎይድ እና የታይፈስ ምርመራ ለማድረግ ጋምቢ ሆስፒታል 120 ብር መክፈላቸውን ይናገራሉ። “በርግጥ ክፍያው ከፈለገ ህይወት ጋር ሲነጻጸር በ90 ብር እንደሚበልጥ ባውቅም እዚህ መጠቀም የፈለግኩት ግን ወረፋ ሳልጠብቅ ህክምናዬን አግኝቼ ቶሎ ወደመጣሁበት ለመመለስ በመፈለጌ ነው” ብለዋል።

የእብናት ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሙላት ፈንቴ በበኩላቸው “የአይን ሞራ ቀዶ ህክምና ለማካሄድ ወደጋምቤ ሆስፒታል ስመጣ 1 ሺህ 500 ብር ክፈል ተባልኩ።ወረፋውን ፈርቼ የተውኩት ፈለገ ህይወት የመንግስት ሆስፒታል 100 ብር ብቻ ነው የሚያስከፍለው። ይህን ያህል የተጋነነ ልዩነት መኖር አልነበረበትም” ነው ያሉት።

የነዋሪዋ ቁጥር ከ200 ሺህ የሚበልጠው ደሴ ከተማ ከባህርዳር ጋር ሲነጻጸር የተሻለ የህክምና ተቋማት አሏት። ሁለት የመንግስትና ሶስት የግል ሆስፒታሎች ይዛለች። ያም ሆኖ የደሴ ሪፈራል እና የቦሩ የመንግስት ሆስፒታሎች ግቢ ሁልጊዜም በታካሚዎች እንደተጨናነቀ ነው። ይህ ዘጋቢ በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ወለል ላይ ተኝተው ካገኛቸው ህመምተኞች መካከል ሸህ ሰዒድ አሊን አናግሯቸው ነበር። ሃርቡ ከተባለ አካባቢ መምጣታቸውን የሚናገሩት እኚህ ታማሚ ላለፉት አራት ቀናት ህክምና ለማግኘት ወረፋ እየጠበቁ መሆኑን ነበር የተናገሩት። የግል ሆስፒታል ሄደው እንደሁ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልሳቸው ምሬት የተሞላበት ነበር። “ከዚህ ቀደም ደሴ ውስጥ በሚገኙት ሶስቱም ሆስፒታሎች ተመላልሼ በተለያዩ ዶክተሮች ታይቻለሁ። 12 ሺህ ብር ከፍዬ ገንዘቤን ጨረስኩ እንጂ አንዳቸውም በሽታዬን አላወቁልኝም። አሁን ባዶዬን ስቀር ነው ወደዚህ የመጣሁት።” ነበር ያሉት።

በደሴ ከተማ የሚገኙት የግል ሆስፒታሎች በመሳሪያ ዓይነትም ይሁን በባለሙያ ስብጥር ከመንግስት ሆስፒታሎች የተሻለ አቅም ባይኖራቸውም የሚያስከፍሉት ዋጋ ከፍተኛነት ግን 80 በመቶ የሚሆነው ነዋሪዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ደሴ የማይሞከር መሆኑን ነው የተሰበሰቡ የህዝብ አስተያየቶች የሚጠቁሙት።

በመንግስት ሆስፒታሎች በነጻ የሚሰጠው የወሊድ አገልግሎት በነዚህ ሆስፒታሎች ከ 3ሺህ እስከ 7 ሺህ ብር ያስከፍላል። በተመሳሳይ በ8 ብር የሚሰጠውን የደም፣ የሽንትና የሰገራ ምርመራ በ45 ብር፣ 82 ብር የሚከፈልበትን የጉበትና ኩላሊት ምርመራ በ700 ብር ይሰራል።

ከአዲስ አበባ በ100 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው አዳማ ከተማ ደግሞ በሃገሪቱ ግዙፍ ተብለው ከሚጠሩ ሆስፒታሎች ውስጥ አዳማ ጄኔራል ሆስፒታልና የከተመባት ናት። የሆስፒታሉ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ከቢር ሁሴን ለግንባታና ለህክምና መሳሪያዎች ግዢ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ ያወጡት የሃገሪቱን ዘመናዊ የህክምና ደረጃ ከፍ በማድረግ የውጭ ሃገር ህክምና ጉዞን ለማስቀረት መሆኑን ይናገራሉ።

በከተማዋ የሚገኘው አዳማ አጠቃላይ ሆስፒታል (በቀድሞ ስሙ ሃይለማርያም ማሞ) በከፍተኛ ሁኔታ በታካሚ ከመጨናነቁ የተነሳ በየበረንዳው ተኝተው ህክምና የሚጠብቁ ነዋሪዎች ቁጥር በርካታ ነው። በአንጻሩ በ86 ሺህ ስኩዌር ካሬ ላይ ያረፈውና ባለ250 አልጋ የሆነው አዳማ ጄኔራል ሆስፒታል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተደራጀ የህክምናና ምርመራ አቅሙ ማስተድናገድ ከሚችለው ታካሚ በታች እያስተናገደ መሆኑን ነው ይህ ዘጋቢ የታዘበው። ዘጋቢው ለዚህ ምላሽ ለማግኘት ለ20 የአዳማ ነዋሪዎች “ቢታመሙ ወደአዳማ ጀኔራል ሆስፒታል ይሄዳሉ ወይ?” የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር። ሁሉም የሰጡት ምላሽ “ብንፈልግም የመክፈል አቅማችን አይፈቅድም” የሚል ነበር ።

የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ ህሩይ ሰንበቶ የስኳርና የደም ግፊት ህመማቸውን ለመከታተል ሁልጊዜም ሆስፒታል እንደሚመላለሱ ይናገራሉ። “እዚህ ሆስፒታል ብቅ ብዬ በሃኪም መታየት የቻልኩት ለአንድ ቀን ብቻ ነው” የሚሉት አቶ ህሩይ “አዳማ ጄኔራል የሚያስደስት ህንጻ ያለውና አዳዲስ መሳሪያዎች የተገጠሙለት ሆስፒታል ቢሆንም ዋጋው ግን አቅም የሚጠይቅ ነው” ይላሉ።

የሆስፒታሉ ማርኬቲንግ ሃላፊና ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶከማል ከቢር ግን “አገልግሎታችን የህብረተሰቡን አቅም ያገናዘበ እንዲሆን ለማድረግ ብዙ ቅናሽ አድርገናል” ነው የሚሉት። “በኛ ግምት ሆስፒታላችን በኢትዮጵያ ከሚገኙት ሆስፒታሎች ሁሉ ግዙፉና ዘመናዊው ነው። በዚያው መጠን ደሃው ህብረተሰብ እንዳይጎዳ ክፍያችንም ፍትሃዊ እንዲሆን ጥረናል። ኤም. አር. አይ እንደደረጃው ከ 1 ሺህ 500 ብር ጀምሮ፣ ሲቲ ስካን ከ900 ብር ጀምሮ፣ ኢንዶስኮፒ 700 ብር፣ኢኮካርዲዮግራፊ 240 ብር ነው የምናስከፍለው። የካርድ ክፍያችን 59 ብር ብቻ ነው።ለአንድ ሃኪም እስከ70 ሺህ ብር ደሞዝ እየከፈልን በዚህ ዋጋ አገልግሎት መስጠታችን አገልግሎታችን ትርፍን ሳይሆን ህብረተሰብን ያማከለ መሆኑን ያረጋግጣል” የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ።

ከ350ሺህ በላይ ነዋሪ ያላት ውቧ ሃዋሳ ደግሞ አሴር፣ ቤተ አብረሃም እና ክብሩ የተባሉ ሶስት የግል ሆስፒታሎች ሲኖሯት ሃዋሳ ሪፈራል እና አዳሬ የተባሉ ሁለት የመንግስት ሆስፒታሎችንም ይዛለች። የከተማዋ ጤና ሽፋን 97 በመቶ መድረሱን የሚናገሩት የከተማዋ ጤና መምሪያ ጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች የጥራት ቁጥጥር አስተባባሪ አቶ ዘመን ለገሰ የሆስፒታሉ ቁጥር ለነዋሪው በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ መንግስት አንድ ተጨማሪ ሆስፒታልም እየገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

በመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ አገልግሎት በማግኘት ላይ ሳሉ ይህ ዘጋቢ ያነጋገራቸው የነገሌ ቦረና ነዋሪው አቶ ድሪባ በዳዳ እና ከባሌ ሮቤ የመጡት አቶ በርከሌ ጉዲና “በመንግስት ሆስፒታሎች የሚሰጠው አገልግሎት ከታካሚው ብዛትና ፍላጎት ጋር የተጣጣመ አይደለም” የሚል ቅሬታ ያቀርባሉ።

“የሆስፒታሎቹ ዋጋ ዝቅተኛ ቢሆንም ታመን ስንሄድ ግን በተገቢው መንገድ የሚያስተናግደን የለም። መሳሪያዎች ቢኖሩም ወረፋው አይዳረስም። በዚህ መሃል ታማሚ እርዳታ ሳያገኝ ይንገላታል። ሃኪሞቹም ‘ወረፋ ስለማይደርሳችሁ ወደሌላ ሆስፒታል ብትሄዱ ይሻላል’ እያሉ ህመምተኞችን ወደግል ሆስፒታል ይልካሉ። የግል ሆስፒታል መታከም ደግሞ ከፍተኛ ዋጋ ይጠይቃል። ብዙው ታማሚ ምርጫ በማጣት ግራ የተጋባ ነው” ብለዋል።

በተቃራኒው የሶስቱም የግል ሆስፒታሎች ሃላፊዎች ውድ ነው ለሚባለው የአገልግሎት ክፍያቸው ምክንያት ካደረጉት ችግር መካከል ዋናው የህክምና ባለሙያዎች የሚጠይቁት ደመወዝ መጠን ከፍተኛነት ነው። “የህክምና ባለሙያዎች መንግስት ጋር ከሚከፈላቸው ደሞዝ 400 እጥፍ ይጠይቃሉ። አማራጭ ስለሌለን እንቀጥራቸዋለን። ይህ ከመድሃኒትና ከመሳሪያ ግዢ ወጪ ጋር ተዳምሮ በአገልግሎት ዋጋችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል” ነው ያሉት።

“የግል ሆስፒታል አትራፊ ንግድ አይደለም”

የግል ሆስፒታሎች በታማሚዎች ላይ ከፍተኛ የአገልግሎት ክፍያ በመጫን ትርፍ ያጋብሳሉ የሚለውን የህብረተሰቡን ወቀሳ የሆስፒታሎቹ ባለቤቶችና ስራ አስኪያጆች አይቀበሉትም። ‘የአገልግሎት ክፍያው ውድነት ሆስፒታሉ ካለበት ወጪ ጋር ሲተያይ የተጋነነ አይደለም’ የሚሉት ሆስፒታሎቹ “መንግስት ለሆቴል የሚሰጠውን ማበረታቻ ያህል እንኳን ለግል ሆስፒታሎች አያደርግም” በማለት ቅሬታቸውን ያቀርባሉ።

የኢትዮጵያ የግል ሆስፒታሎች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙላቱ ሲሳይ እንደሚናገሩት የግል ሆስፒታሎች ካለባቸው ከፍተኛ ወጪ አንጻር አትራፊ ናቸው ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። “ባለሃብቶች በሆስፒታል ኢንቨስትመንት ላይ ሲሰማሩ በመንግስት የሚደረግላቸው ማበረታቻ አርኪ አይደለም። የህክምና መሳሪያዎች ከቀረጥ ነጻ ከማስገባታቸው በቀር ሆስፒታል ሲገነቡ እንኳን ከሊዝ ነጻ መሬት አይሰጣቸውም። ለህንጻ ኪራይ በወር እስከግማሽ ሚሊዮን ብር የሚከፍሉ አሉ። አንድ አልትራ ሳውንድ ማሽን መግዛት እስከ450ሺህ ብር ድረስ ያስወጣል። ከፍተኛ የትርፍ ግብር እና የአስተዳደራዊ ወጪዎች አሉባቸው። ከሁሉም በላይ ሆስፒታሎቹ በሃገሪቱ ባለው የባለሙያ እጥረት ሳቢያ ስፔሻሊስት ዶክተሮችን ለመቅጠር ከፍተኛ ደሞዝ መክፈል ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ አንድ የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት እስከ45 ሺህ ብር ደሞዝ ይጠይቃል። አንድ የቀዶ ህክምና ባለሙያ በኦፕሬሽን ወቅት ከሚገኘው ገቢ ከ65 በመቶ በላይ ይወስዳል። የመድሃኒት ቀረጥ ከፍተኛ ነው። ይህን ሁሉ ወጪ አካትቶ የሚሰራው የአገልግሎት ክፍያ ተመን በታካሚ ላይ ይወድቃል። በአዲስ አበባ ብቻ ወጪና ገቢያቸው አልመጣጠን ብሎ በኪሳራ የተዘጉ ሁለት ሆስፒታሎች አሉ። የግል ሆስፒታል ስራ ከውጪ እንደሚታሰበው ከልክ በላይ አትራፊ ተቋም አይደለም፣እንደውም መንግስት የባለሙያዎችን ችግር ተረድቶ ጣልቃ በመግባት ማስተካከል ይጠበቅበታል” በማለት ይሞግታሉ።

የጤና መድህን ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዶክተር መንግስቱ በቀለ መንግስት የሆስፒታሎቹ ወጪ በዝቶ በአገልግሎት ላይ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር የሚያስገቡትን መሳሪያ ከቀረጥ ነጻ ከማድረግ ባሻገር በመድሃኒቶች ላይም የተወሰነ ፐርሰንት የቀረጥ ቅናሽ ያደርግላቸዋል። ያም ሆኖ የህክምና ስነምግባርን በመጣስና ታማሚውን የመደራደሪያ ምርጫ በማሳጣት ትርፍ ለማጋበስ የሚሰሩና በዚያው መጠን ለህክምናው ከሚያስፈልገው በላይ ዋጋ የሚቆልሉ የግል ሆስፒታሎች መኖራቸው ግን አይካድም። ይህም ችግሩን አስከፊ አድርጎታል” ብለዋል።

“መንግስት ጣልቃ አይገባም”

የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ አንተነህ ምትኩ እንደሚናገሩት ህዝቡ በግል ህክምና ዋጋ መወደድ ላይ የሚያቀርበው ጥያቄ ትክክል ቢሆንም የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በነጻ ገበያ ስርዓት የሚመራ በመሆኑ መንግስት የህክምና አገልግሎት ጥራትን መቆጣጠር እንጂ በግል ጤና ተቋማት አሰራር ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ዋጋ መወሰን አይችልም። “ለዚህ መፍትሄው የመንግስትን የጤና ተቋማት በብዛት በማደራጀት የህክምና አገልግሎትን በጥራት ማዳረስ ብቻ ነው” ይላሉ።

መፍትሄው ምንድነው?

የኢትዮጵያ መንግስት የጤና አገልግሎት ማዳረስን ቀዳሚ የትኩረት መስክ አድርጎ እየሰራ ነው የሚሉት የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዶክተር መንግስቱ በቀለ በሃገሪቱ የግል ሆስፒታሎች ውስጥ ያለውን የህክምና ዋጋ መናር ለመቆጣጠርና ህብረተሰቡ በተገቢው መንገድ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ መንግስት የጤና ተቋማትን የማስፋፋት፣ የህክምና ባለሙያዎችን ቁጥር የመጨመር እና የዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችን ወደሃገር ውስጥ የማስገባት ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።

     “ችግሩን ለመፍታት በዋናነት መፍትሄ የሚሆነው ግን ማንኛውም ዜጋ ሲታመም ኪሱ ውስጥ ገንዘብ የመኖርና ያለመኖሩን ጉዳይ ሳይጠብቅ አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ማግኘት የሚችልበት የጤና መድህን ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ ነው። ይህንን ለማስፈጸም የተቋቋመው የጤና መድህን ኤጀንሲም ወደስራ ገብቷል። ወደፊት ማንኛውም ሰው ከገቢው ላይ በሚያዋጣው ጥቂት ገንዘብ የትኛውም ደረጃ ያለው ህመም ቢገጥመው ያለምንም ቅድመሁኔታ ወደህክምና ተቋማት መጥቶ ጥራት ያለው አገልግሎት ማግኘት የሚችልበት አሰራር እየተዘረጋ ነው። ምናልባት አሁን የሚነሱት የጤና አገልግሎት ዋጋ መናር ችግሮች ያኔ መፍትሄ ያገኙ ይሆናል” ነው ያሉት። ይህ ዘገባ በአፍሪካ ሚዲያ ኢኒሺየቲቭ ድጋፍ የአፍሪካ ስቶሪ ቻሌንጅ ለተባለ አህጉራዊ ውድድር የተዘጋጀ ነው፡፡

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1936 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 919 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us