ስለስጋ ደዌ በሽታ ያለው ብዥታ አሁንም አልጠራም

Wednesday, 05 February 2014 15:21

የዓለም ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ቀን መከበር የጀመረው እ.ኤ.አ. በ1995 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ቀኑ በየዓመቱ ጥቅምት 18 ቀን (January 30) የሚከበር ሲሆን ይህ ቀን የተመረጠበትም ምክንያት እለቱ ለስጋ ደዌ በሽታ በከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ የነበሩት የህንዱ ማህተመ ጋንዲ የሞቱበት እለት በመሆኑ ነው። ይህ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ቀን የሚከበርበት ዋናው ምክንያት ስለ በሽታው ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ማድረግ ነው። ይህ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ቀን ዘንድሮም በመላው ዓለም ለ58ኛ ጊዜ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ15ኛ ጊዜ ተከብሯል።

የስጋ ደዌ በሽታ ከበሽታዎች ሁሉ ረጅም እድሜ ያስቆጠረ በሽታ መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። ማይክሮ ባክቴሪየም ሊፕሬ በተባለ ባክቴሪያ የሚመጣው የስጋ ደዌ በሽታ ቀዝቃዛ የሆኑ በተለይ በፊት፣ በእጅ እና በእግር አካባቢ ያሉ ነርቮችን የሚያጠቃ በሽታ ሲሆን፤ ወቅቱን የጠበቀ ህክምና ከተደረገ ከበሽታው መዳን እንዲሁም ወደሌላ ሰው እንዳይተላለፍ ማድረግ እንደሚቻል ነው ባለሞያዎች የሚናገሩት። ጊዜውን የጠበቀ ህክምና ካልተደረገ ግን ለአይነ ስውርነት እንዲሁም በእጅ እና በእግር ላይ ምንም አይነት ስሜት ማጣትን ሊያስከትል ይችላል።

ይህን የስጋ ደዌ የሚያመጣው ማይክሮ ባክቴሪየም በጣም በዝግታ ራሱን የሚያበዛ ሲሆን፤ የመፈልፈያ ጊዜውም አምስት ዓመት ነው። አንድ ሰው በስጋ ደዌ በሽታ ከተያዘ በሀያ ዓመታት ውስጥ ምልክቶቹን ማሳየት ይችላል። የስጋ ደዌ በሽታ በአፍ እና ከአፍንጫ በሚወጡ ፈሳሾች እንዲሁም ከበሽታው ተጠቂዎች ጋር ተደጋጋሚ ንክኪ በሚፈጠርበት ወቅት የሚተላለፍ በሽታ ነው።

በአለማችን ላይ ከስልሳ ዓመታት በላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የስጋ ደዌ በሽታን ልብ ሳይሉት ኖረዋል የሚሉት ዘገባዎች፤ በአሁኑ ጊዜም ይህ ችግር ከአንድ መቶ በላይ በሚሆኑ ሀገራት ላይ እየተስተዋለ መሆኑን ገልጸዋል። በ2008 (እ.ኤ.አ.) የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተውም ከ213ሺ በላይ ሰዎች የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ናቸው። ይህ ቁጥር ታዲያ በአፍሪካ እና በእስያ ያሉትን ብቻ ሲሆን የሚገልፀው፤ ከዚህ በተጨማሪም 249ሺ አዳዲስ ተጠቂዎች እንዳሉ ተዘግቧል። በ2012 (እ.ኤ.አ.) የተደረገው ጥናት እንደሚያመለክተውም በ31 የአፍሪካ፣ እስያ እና ኢንዶኔዥያ ሀገር ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በስጋ ደዌ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ይኖራሉ።

የስጋ ደዌ በሽታ ከመቀነስ ይልቅ አሳሳቢ በሆነ መልኩ ጭማሪ እያሳየ እንዳለ ነው የተገለፀው። በዚሁ ልክ ደግሞ በበሽታው ተጠቂዎች ላይ እየደረሱ ያሉት መገለሎችም ያንኑ ያህል እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል።

በስጋ ደዌ ተጠቂዎች ላይ ማህበረሰቡ እያደረሰ ያለው መድሎ በሽተኞቹ ራሳቸው እውነታውን እንዳይገልጹ ያደርጋቸዋል ይላሉ መረጃዎች።

በአሁኑ ጊዜ ምንም እንኳን በሽታውን ማጥፋት እና ወደ ቀድሞ ቦታው መመለስ ባይቻልም ባለበት ማቆም እና ሌላ ችግር እንዳይፈጥር ማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ዘዴዎች አሉ። ነገር ግን በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ይሄንን ከማድረግ በሽታውን ይዘው መቀመጥን እንደሚመርጡ ነው የተገለፀው። ከበሽታው ጋር መኖራቸው ቢታወቅ ከህብረተሰቡ ዘንድ የሚደርስባቸውን መገለል በማሰብም ብዙዎች ወደ ህክምና ቦታ አይሄዱም።

በሽታውን ለሌላ ሰው ከማሳወቅ ይልቅ ምንም እንዳልተፈጠረ በዝምታ በመኖራቸውም የተነሳ ብዙዎች ከንፈራቸው፣ አይናቸውን ወይም ደግሞ ሁለቱንም ያጣሉ። አንዳንዶቹም ህይወታቸው ያልፋል። ሌሎች ደግሞ በሽታውን ይዘው ወደ ከተማ አካባቢ በመምጣት ከመታከም ይልቅ ወደሌሎች እንደሚያስተላልፉ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

በኢትዮጵያ ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማህበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋዬ ታደሰ በኢትዮጵያ ስለ ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ያሉትን ሁኔታዎች አስመልክቶ አነጋግረናቸዋል። በተለይ በህብረተሰቡም ሆነ በራሳቸው የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ዘንድ ስለበሽታው ያለው አመለካከት አሁንም ድረስ እንዳልተቀረፈ ነው አቶ ተስፋዬ የሚገልጹት።

በስጋ ደዌ የተጠቁ ሰዎች ከሌላው ማህበረሰብ ጋር ተቀላቅሎ ለመኖር ከፍተኛ የሆነ ፍራቻ እንዳለባቸው የገለፁት አቶ ተስፋዬ፤ የኢትዮጵያ ስጋ ደዌ ብሄራዊ ማህበር በ1987 ዓ.ም ሲቋቋምም ይሄንን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ እንደነበር ይገልፃሉ። “ማህበሩ በሰራቸው ስራዎች በተወሰነ ደረጃ መሻሻል አለ ብንልም አሁንም ግን ችግሮች አሉ። ችግሮች ያሉት በበሽታው ተጠቂዎችም በሌላው ማህበረሰብም በኩል ነው። ተጠቂዎቹ በራሳቸው የመተማመን ችግር አለባቸው። በዚህም ሳቢያ ራሳቸውን አግልለው ብቻቸውን ይኖራሉ። በማህበራዊ ህይወትም አይሳተፉም። ሌላው ማህበረሰብ ደግሞ ደፍሮ ከእነዚህ አካላት ጋር ለመቀላቀል ስጋት አለው ከስጋ ደዌ ተጠቂዎች ጋር ከመቀራረብ ይልቅ ሲያገላቸው እና ሲጠየፋቸው ይታያል” የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ ማህበሩም እየሰራ ያለው በሁለቱም ወገኖች ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

በርካታ ሰዎች የስጋ ደዌ በሽታ በህክምና የሚድን መሆኑን ካለማወቃቸው የተነሳ ወደ ህክምና ከመሄድ ይልቅ ወደ ጠንቋይ፣ ወደ ፀበል እና ወደተለያዩ የአምልኮ ቦታዎች መሄድን በመምረጥ ለረጅም ጊዜ ሲጎዱ መቆየታቸውን ነው አቶ ተስፋዬ የገለፁት። አሁን ግን ከሞላ ጎደል ህብረተሰቡ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ እየተቀየረ በመምጣቱ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ከሌላው ማህበረሰብ ጋር አብሮ የመብላት እና እድር፣ ለቅሶና እቁብ ውስጥ ጭምር መሳተፍ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማህበር በሀገሪቱ ሰባት ክልሎች አገልግሎቱን የሚሰጥ ሲሆን ከ63 በላይ ቅርንጫፎች አሉት። በእነዚህ ቅርንጫፎችም የስጋ ደዌ ተጠቂዎች በመደራጀት መገለልን እንዲታገሉ፣ ራሳቸውን በደንብ ጠብቀው እንዲኖሩ እንዲሁም ተዛማጅ በሽታዎች ካሉ ወደ ህክምና ሄደው ዘላቂ ህክምና እንዲያደርጉ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ አቶ ተስፋዬ ገልፀውልናል። በተጨማሪም የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅሎ በመኖር የሚያስችሏቸውን ንጽህናን የመጠበቅ እና ራሳቸውን የመንከባከብ ስራ ላይ ጠንክረው እንዲሰሩ ሁኔታዎች ይመቻቹላቸዋል።

ማህበሩ ከዚህ ጎን ለጎንም የስጋ ደዌ ተጠቂዎቹ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ራሳቸውን የሚችሉበትን ሁኔታም ያመቻቻል። በዚህም በፍፁም ድህነት ውስጥ የሚኖሩ የበሽታው ተጠቂዎች ሰርተው በሚያገኙት ገቢ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ይደረጋል። ከዚህ በተጨማሪም በየቦታው የሚገኙ አረጋውያን መጠለያ እንዲያገኙ ይደረጋል።

የስጋ ደዌ ተጠቂዎች በከብት ማደለብ ስራ እንዲሰማሩ፣ ባለ አምስት ቋት ወፍጮዎችን ተጠቅመው የራሳቸውን ገቢ እንዲያገኙ እንዲሁም የብድር እና ቁጠባ ተጠቃሚዎች በመሆን ስለነገ ህይወታቸው ማሰብ እንዲጀምሩ እንደሚደረግም አቶ ተስፋዬ ጨምረው ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በየቦታው ተበታትነው እና በአልባሌ ቦታዎች ላይ የሚገኙ የስጋ ደዌ ተጠቂዎችን አሰባስቦ መጠለያ የመስጠት ስራ ይሰራል። ለአብነት ያህልም በሀዋሳ 50 ያህል የስጋ ደዌ ተጠቂ አባወራዎች ከነበሩበት ቆሻሻ ስፍራ ተነስተው በራሳቸው ቤት ውስጥ በመኖር ላይ እንደሆኑ ነው አቶ ተስፋዬ አያይዘው የገለፁልን። ከዚህ በተጨማሪም የስጋ ደዌ ተጠቂዎቹ የጫማ እርዳታ እንዲያገኙ ከውጭ ድርጅት ጋር በመተባበር ሁኔታዎች ይመቻቻሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል የስጋ ደዌ ተጠቂዎች እንዳሉ በትክክል ለመግለፅ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዳሉ የገለፁት አቶ ተስፋዬ፣ በዚህም ሳቢያ ይሄን ያህል የስጋ ደዌ ተጠቂዎች አሉ ለማለት ያስቸግራል ባይ ናቸው። “ቁጥራቸው ይሄን ያህል ነው ብሎ አፍ ሞልቶ ለመናገር አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን በኢትዮጵያ በህክምና ላይ ያሉ እና ታክመው የዳኑ ከአንድ መቶ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሃያ ሺህ የሚደርሱ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች አሉ። ከዚህ ውጪ ግን ትክክለኛ ቁጥሩን መግለፅ አስቸጋሪ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንቅስቃሴ ስለማይደረግ የተሟላ መረጃ እጥረት ነው። ማህበራችን ራሱ ካለበት ያቅም ውስንነት የተነሳ እየሰራ ያለው በሰባት ክልሎች ብቻ በመሆኑ ትክክለኛ ሁኔታውን ለመናገር ያስቸግራል” ይላሉ አቶ ተስፋዬ።

     ቀደም ሲል በየአመቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ይመዘገቡ እንደነበር የገለፁት አቶ ተስፋዬ በአሁኑ ጊዜ ግን መድሃኒት የመስጠት ስራው በስፋት በመቀጠሉ ቁጥሩን መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል። በዚህም በአሁኑ ወቅት በአመት ከአራት እስከ አምስት ሺህ አዳዲስ ተጠቂዎች ብቻ መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
3464 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 686 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us