የለጋው ድርጅት በሳል አፈፃፀም

Wednesday, 26 February 2014 13:01

የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ከተቋቋመ ከሁለት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። ኤጀንሲው የተቋቋመበት ዓላማ በግል ድርጅቶች ውስጥ ሲያገለግሉ የቆዩ ዜጐች ከስራው ዓለም ሲገለሉ ቀጣይ ህይወታቸውን ሊመሩበት የሚችሉበትን ገቢ እንዲያገኙ ለማድረግ ነው። ኤጀንሲው ይህን የተሰጠውን ኃላፊነት በምን መልኩ እየተወጣ እንደሆነ የሚያሳይ የ2006 ዓ.ም የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈፃፀምን በማቅረብ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅዳሜ፣ የካቲት 8 ቀን 2006 ዓ.ም በጁፒተር ሆቴል የምክክር መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር።

በውይይት መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን፣ ከአሰሪዎች ፌዴሬሽን፣ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን እንዲሁም ከጡረተኞች ማኅበር እና ከሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የተውጣጡ ተወካዮች ተገኝተው ነበር። በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ገብረሚካኤል ነበሩ። አቶ ፀጋዬ እንደገለፁትም፤ ኤጀንሲውን ማቋቋም ያስፈለገው የግል ድርጅት ሰራተኛውን ለመደገፍ ብቻ ሳይሆን የግል ድርጅት አሰሪዎችንም ጭንቀት ለማቃለል ነው።

“በእርግጥ ለሰራተኛው እድሜው ሲደክምና መስራት ሲያቅተው የት እወድቅ ይሆን የሚለውን ስጋት ይቀንስለታል። ይሄ አጠያያቂ አይደለም። ከዚህ ቀደም [ኤጀንሲው ሳይቋቋም] በርካታ የግል ድርጅት ሠራተኞች ጉልበት ባላቸው ጊዜ ሠርተው ጉልበታቸው ሲያልቅ ሜዳ ላይ ይቀራሉ። በርካቶቹ የጐዳና ተዳዳሪዎች ሆነዋል። አሁን ግን እንዲህ አይነት ነገር የለም። ሁሉም በተስፋ ሰርቶ መጦሪያውን ያስቀምጣል” ብለዋል አቶ ፀጋዬ። አያይዘውም፤ “ብዙ የግል ድርጅት አሰሪዎችም በዚህ ጉዳይ ይጨነቁ ነበር። በጣም ጐበዝና ታታሪ ሰራተኞቻቸው በስተርጅና የጐዳና ተዳዳሪ ሲሆኑ እና ለልመና እጃቸውን ሲዘረጉ ማየት አይፈልጉም። ብዙ ነገር አብረው አሳልፈው፣ ለድርጅታቸው ብዙ ለፍተው ሲያበቁ ለእንግልት ሲዳረጉ በጣም ያዝናሉ። ይህ ኤጀንሲ መቋቋሙ ግን ከዚህ ዓይነቱ ስሜት አላቋቸዋል” ብለዋል።

በዋና ዳይሬክተሩ ንግግር በመቀጠልም የኤጀንሲው የመጀመሪያ ስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት የእቅድ አፈፃፀም እና የለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ አማረ ታደሰ ቀርቧል። የኤጀንሲው አጠቃላይ የስድስት ወራት አፈፃፀም ሲታይ፤ 97 በመቶ መሆኑን ያመለከተው ሪፖርቱ፣ ኤጀንሲው ጀማሪ ከመሆኑ አንፃር አፈፃፀሙ ለሌሎች አርአያ የሚሆን አፈፃፀም ሆኖ ተገኝቷል። ኤጀንሲው በ6 ወራት ውስጥ ለማከናወን ያስቀመጣቸው እቅዶች የምዝገባ፣ የጡረታ መዋጮ ገቢ፣ የጡረታ ፈንድ አስተዳደር፣ የጡረታ አበል ውሳኔና ክፍያ እንዲሁም የድጋፍ ስራዎች ናቸው።

ከኤጀንሲው አፈፃፀም ውስጥም ቀዳሚው የጡረታ መዋጮ ገቢ ሲሆን፤ የጡረታ መዋጮን አሟጦ ለመሰብሰብ በተደረገ ጥረት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ሰባት መቶ ሃምሳ ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 978 ሚሊዮን 241ሺ 523 ብር ለመሰብሰብ ተችሏል። ይህም አፈፃፀሙ 130 በመቶ መሆኑን ያመለክታል።

ከጡረታ መዋጮ በመቀጠልም ጥሩ አፈፃፀም ያሳየው ምዝገባ ነው። ምዝገባው የሰራተኞች ምዝገባ እና የድርጅቶች ምዝገባ ተብሎ ለሁለት የተከፈለ ሲሆን፤ በተለይ የሰራተኞች ምዝገባ አፈፃፀም አበረታች ሆኖ ተገኝቷል። ይኸውም በስድስት ወራት ውስጥ 92ሺ 36 ሠራተኞች የጡረታ መዋጮ ለመቁረጥ የተመዘገቡ ሲሆን፤ ይህም አፈፃፀሙ 108 በመቶ ሆኗል። ከእነዚህ ውስጥም በዋናው 1ሺ 328 ድርጅቶችና 33ሺ 252 ሠራተኞች የአባልነት ካርድ ያገኙ ሲሆን፤ በሪጅን ደግሞ ለ4ሺ 944 ድርጅቶችና ለ52ሺ 50 ሠራተኞች የአባልነት ካርድ ተሰጥቷል። የድርጅት ምዝገባን በተመለከተ ግን 10ሺ 161 ድርጅቶች ብቻ የተመዘገቡ በመሆኑ አፈፃፀሙ 55 በመቶ ብቻ እንዲሆን አድርጐታል። በአፈፃፀም ረገድ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ሊቀመጡ የሚችሉት የጡረታ ፈንድ አስተዳደር እና የጡረታ አበል ውሳኔና ክፍያ ናቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች በእድሜ፣ በስራ ላይ ጉዳትና ህመም እንዲሁም ለተተኪዎች የአበል ውሣኔ በመስጠት ረገድ አፈፃፀሙ 100 በመቶ ያሳያል። በዚህም መሠረት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 1ሺ 243 ተገልጋዮች የጡረታ መብት ጥያቄ አቅርበው 1ሺ 183ቱ ተገልጋዮች የተሟላ መረጃ በማቅረባቸው ተጠቃሚ ሆነዋል። በሪጅንም የተሟላ መረጃ ላቀረቡ 624 ባለጉዳዮች የጡረታ አበል ተወስኖላቸዋል።

በድጋፍ ስራዎች ስር የተካተቱት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች፣ የአመለካከትና ክህሎት ማሳደጊያ እንዲሁም የበጀት አጠቃቀምን በተመለከተም በኤጀንሲው አበረታች ውጤት ተመዝግቧል። ኤጀንሲው ማኅበረሰቡ ስለ የግል ድርጅቶች የማህበራዊ ዋስትና በቂ የሆነ መረጃ እንዲኖረው ለማድረግ በተለያዩ መድረኮች እና የመገናኛ ብዙሃን አማካይነት ሰፊ ስራ መስራቱ ታውቋል። ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በዋናው መ/ቤት በ11 መድረኮች ለ603 ተሳታፊዎች እንዲሁም በሪጅን ጸ/ቤቶች በተዘጋጁ 21 መድረኮች ለ1ሺ 284 ተሳታፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ተደርጓል። በተጨማሪም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና አሰሪዎች ባዘጋጁዋቸው 18 መድረኮች ለ2ሺ 503 ተሳታፊዎች በአጠቃላይ በ50 መድረኮች ለ4ሺ 390 ተሳታፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል።

ኤጀንሲው በአሁኑ ሰዓት በዋናው መስሪያ ቤት እና በሪጅን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች 685 ወንዶች እና 465 ሴቶች በድምሩ 1ሺ 150 ሠራተኞች በስራ ላይ ያሉት ሲሆን፤ በስራ ላይ ያሉትን ሠራተኞች አመለካከትና ክህሎት ለማሳደግም ስልጠና ይሰጣል። በዚህ መሠረት ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር 19 ሠራተኞች የማስተርስ ዲግሪያቸውን እንዲማሩ ተደርጓል። የበጀት አጠቃቀምን በተመለከተም በስድስት ወራት ውስጥ 33 ሚሊዮን 9ሺ 447 ብር በስራ ላይ ለማዋል ታቅዶ 28 ሚሊዮን 606 ሺህ 837.07 ብር ወጪ ተደርጓል። ይህም የበጀት አፈፃፀሙን 87 በመቶ ያደርገዋል።

ኤጀንሲው ከላይ የተጠቀሱትን መልካም ተግባራት እንዳከናወነው ሁሉ አንዳንድ እንከኖችም እንዳሉበት ተገልጿል። በተለይ ከምዝገባ ጋር በተያያዘ የድርጅቶች ምዝገባ አፈፃፀም አነስተኛ ሆኖ የተገኘበት ምክንያት ምን እንደሆነ ተጠይቋል። በሪፖርቱ እንደቀረበውም 1ሺ 253 ድርጅቶች በኤጀንሲው ባለመመዝገባቸው ምዝገባ እንዲያካሂዱ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥም 649 ያህሎቹ ተመዝግበዋል። ለዚሁ ደግሞ ምክንያቱ ምን እንደሆነ አቶ ፀጋዬ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

እንደ አቶ ፀጋዬ ገለፃ በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማራ ድርጅቶች ስራቸው በፕሮጀክት የሚንቀሳቀስ እና በጊዜ ገደብ ውስጥ የሚጠናቀቅ በመሆኑ ለዚህ የማኅበራዊ ዋስትና ለመመዝገብ ፈቃደኛ እንደማይሆኑ ገልፀዋል። ከዚሁ በተጨማሪም ስለ ማኅበራዊ ዋስትናው ያለው የአመለካከት ችግር በስራቸው ላይ እንቅፋት እንደፈጠረባቸው አቶ ፀጋዬ ገልፀዋል። ከቀርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቅጣቱ በራሱ በድርጅቱ ላይ ስለሚፈፀም ግዴታን የመወጣት ሁኔታ እየተስተዋለ እንደሆነ ገልፀዋል።

ሌላው በኤጀንሲው ላይ እንደ እንቅፋት የተነሳው አንዳንድ ድርጅቶች የራሳቸውን ድርሻ ከፍለው ሰራተኛውን የሚያስከፍሉ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ ጀምረው የሚያቋርጡ ወይም ደግሞ በአጠቃላይም ያልተመዘገቡ ድርጅቶችና ሰራተኞች መኖራቸው ነው። ለዚህም የተቀመጠው ምክንያት አብዛኛዎቹ ስለ ግል ድርጅቶች የሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ መሆኑ ነው። በዚህም መሠረት 29 በመቶ የሚሆኑት የኅብረተሰብ ክፍል ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህ የግንዛቤ ማነስ ጋር በተያያዘም በተለይ በአበባ አምራች ድርጅቶች አካባቢ ሰራተኞች ከደመወዛቸው ላይ የጡረታ መዋጮ ከማስቆረጥ ይልቅ ከአንዱ ወደ ሌላው መሸጋገርን እንደሚመርጡ ተሳታፊዎች ያነሱ ሲሆን፤ ኤጀንሲውም ይህን ችግር የተገነዘበው በመሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተገልጿል።

ሌላው ኤጀንሲው እንደችግር ያስቀመጠው ከፍተኛ የሆነ የሠራተኞች ፍልሰት መኖሩን ነው። ለዚህስ ምክንያቱ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ከተሳታፊዎች የተነሳ ሲሆን፤ አቶ ፀጋዬ በሰጡት ምላሽም፤ ለሠራተኛው የሚከፈለው ደመወዝ እና የሚሰራው ስራ አለመጣጣም መሆኑ ተገልጿል። “ሠራተኛው ሁሉ የሚከፈለው በሲቪል ሰርቪስ የደመወዝ ስኬል መሠረት ስለሆነ፤ የሠራተኛው ደመወዝ አነስተኛ ነው። በዚህ ላይ ደግሞ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሰርቪስ እንኳን ስላልነበረን ሠራተኛው ለሥራ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ለትራንስፖርት ከኪሱ አውጥቶ ለመክፈል ይገደዳል። ስራው እንደ ቤት ለቤት ስራ በየድርጅቱ መንቀሳቀስን ይጠይቃል። የድርጅቶችን በር እያንኳኳን ነው የምንመዘግበው። ስራው በጣም አድካሚ ነው” ብለዋል አቶ ፀጋዬ።

    ከዚህ በተጨማሪም በተለይ አነስተኛ የግል ድርጅቶች በቤተሰብ የሚያዙ እና የሚተዳደሩ በመሆናቸው ግልፅ የሆነ አሰራር እጦት እንዳለ ተገልጿል። ስራውን የሚሰሩት የአንድ ቤተሰብ አባላት ሆነው ገቢውም የጋራ በሚሆንበት ወቅት ምዝገባ ከማካሄድ ይልቅ ዝም ብሎ ስራውን መስራትን ስለሚመርጡ እንዲህ አይነቶቹን ድርጅቶች ቤት ለቤት እየሄዱ የመመዝገብ ጭምር ኃላፊነት እንዳለባቸው አቶ ፀጋዬ ጨምረው ገልፀዋል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1341 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1050 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us