ጣምራ ተግባር

Wednesday, 05 March 2014 14:08

እለተ ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን ጠዋት ላይ ነው። በርካታ በከዘራ እየተመሩ የሚንቀሳቀሱ አዛውንቶች ከተለምዶ አፍንጮ በር ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች ማህበር ግቢ ይጓዛሉ። አዛውንቶቹ አብዛኞቻቸው በራሳቸው ላይ ኮፍያ የደፉ ቢሆኑም ከኮፍያቸው አምልጦ የወጣው ነጭ ፀጉራቸው ግን የዕድሜያቸውን መግፋት ያሳብቃል። ሆኖም ግን ከዚህ ከነጭ ፀጉራቸው በስተጀርባ ጠንካራ ወኔ እንዳላቸው አሁንም ድረስ ያልዛለው ጉልበታቸው ይመሰክራል።

በእለቱ የኢትዮጵያ ጀግኖች ከራሳቸው ሀገር አልፈው ለሌላው አለም ያበረከቱትን አስተዋፅኦ የሚዘከር ዶኩመንተሪ ፊልም ለእይታ የሚበቃበት እለት በመሆኑ በርካታ የዚህ ታሪክ ተሳታፊ የነበሩ በተለይ ደግሞ በኮሪያ ዘመቻ የተሳተፉ ጀግኖች ነበሩ ወደ ዝግጅቱ ያመሩት። በታሪኩ ውስጥ የተካተቱት ተግባራቸውን በምልሰት ለመመልከት ሌሎች ደግሞ ይሄም ሆኖ ነበር ለካ ለማለት።

የኮሪያ ጦርነት በተካሄደበት ከ1951 እስከ 1953 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ጦር ዓለም አቀፉን ጥሪ በማክበር በአምስት ዙሮች ወደ ኮሪያ በመዝመት ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጎ ተመልሷል። በእነዚህ ዙሮች የተደረጉ ውጊያዎች ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ወታደሮች ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ሴቶችም ጭምር እንደነበሩ ታሪክ ቢነግረንም፤ በአሁኑ ጊዜ ግን በህይወት ያሉት ወንዶች ብቻ ናቸው። ለዚህ ደግሞ ምስክሮቹ ራሳቸው አባት ጀግኖች ናቸው።

በዚህ የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት በሚዘክረው በዶክመንተሪ ፊልም ላይ እንደተገለፀው እነዚህ ከቃኘው ጦር የተመለመሉ እና በብቃታቸው የተመረጡ ጀግኖች በኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ይሄንን ግዳጃቸውን ከተወጡ በኋላ በደርግ ዘመን ግን ከፍተኛ ግፍ ደርሶባቸዋል። “እነዚህ ነጥብ ከምታክል ሀገር ተነስተው በኮሪያ ምድር ላበረከቱት ከፍተኛ ተጋድሎ ከፍተኛውን ሽልማት የተሸለሙ ጀግኖች በስተርጅና በየግንባሩ ተሰልፈው ሕይወታቸው እንዲያልፍ ተደርጓል” ይላል ፊልሙ። በርካታ ጀግኖች አባቶች በመጦሪያ ጊዜያቸው ከባድ ኃላፊነት ተጥሎባቸው የትም ወድቀው የቀሩ ሲሆን፤ የተቀሩት ደግሞ በየደጀሰላሙ እጃቸውን ለምፅዋት ለመዘርጋት ተገደው እንደነበረ ፊልሙ ይተርካል።

በእርግጥ በፊልሙ ላይ የቀረበው እውነታ የሚያመለክተው ሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት ገጥመዋት በነበሩ ጦርነቶች አባት ጀግኖች ያደረጉትን ያህል ተጋድሎ ታሪካቸው የሚታወቀው በጥቂት ሰዎች ዘንድ ብቻ መሆኑን ነው። በፊልሙ ላይ የቀረቡት እውነታዎች በወቅቱ የነበረውን ትውልድ ወኔም የሚያንፀባርቅ ነበር። ፊልሙ በአጠቃላይ ያጠነጠነው ከቃኘው ሻለቃ ጦር አመሰራረት እስከ ኮሪያ ጦርነት ቢሆንም በመሀከል በርካታ አስደናቂ እውነታዎች ነበሩ።

በኢትዮጵያውያን ዘንድ ብቻም ሳይሆን በመላው አፍሪካ አልፎም በመላው አለም ሁልጊዜ ሲወሳ የኖረውና የሚኖረው የአድዋ ጦርነት እንኳ ብንወስድ በፊልሙ ላይ የቀረበው እውነታ አስደናቂ ነበር። ከዚህ ውጪም የማይጨው ጦርነትን የመሳሰሉ አስደናቂ ጦርነቶችን እነዚህ አባቶች መክተዋል። ለመሆኑ በማይጨው ጦርነት ወቅት ኢጣሊያ 42 ሚሊዮን ወታደሮችን ስታሰማራ ኢትዮጵያ ደግሞ 12 ሚሊዮን ሰራዊት ብቻ አሰማርታ እንደነበረ ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን?

እንግዲህ በዚህ ሁሉ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆነው ሀገርን አናስነካም ያሉ ጀግኖች አባቶች ናቸው እጃቸውን ለልመና የዘረጉት። እንደ እድል ሆኖ በህይወት ቆይተው ለዚህ ታላቅ ቀን የበቁ አባቶች ደግሞ በማህበሩ አዳራሽ ተገኝተው ያን ታሪካዊ ፊልም ለመመልከት ችለዋል። በእድሜ መግፋት ምክንያት ግማሾቹ አይናቸው፣ ሌሎቹ ጆሯቸው፣ አንዳንደቹ ደግሞ ሁለቱም የስሜት ህዋሳቶቻቸው በአግባቡ ስራቸውን ባይሰሩም፣ የሁሉም ልብ ግን አንድ ነገር ላይ አተኩሯል። ሁሉም በሙሉ ልብ ሸራ ላይ አይናቸውን ተክለዋል።

ከፊልሙ መሀከል ሲተኮስና ኢላማውን ሲመታ ከመቀመጫቸው በመነሳት ልክ አሁን የሆነ ያህል አድናቆታቸውን ይገልፃሉ። አንዳንዶች አሁንም ድረስ ያልዛለ ክንዳቸውን ወደ ላይ እየዘነዘሩ “እንዲህ ነው ጀግና! ሲሉ ሌሎች ደግሞ በስሜት ያጨበጭቡ ነበር። ሬሳ ወድቆ ሲያዩ እና የጓደኞቻቸው ስም ሲነሳ ደግሞ እንባ አንብተው ያለቅሳሉ። ብቻ ፊልሙ እስከሚጠናቀቅ ድረስ አዳራሹ በሀዘን እና በሲቃ ተሞልቶ ነበር። የዚህን በስድስት የተለያዩ ክፍሎች የቀረበው ፊልም መጠናቀቅን ተከትሎ ሁሉም ሰው ስሜቱን መሰብሰብ ሲጀምር በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ከአባቶች ጋር ለመነጋገር ጊዜ አገኘን። በተለይ በኮሪያ ዘመቻ ወቅት ኢትጵያውያን ወታደሮች ከውትድርና ተግባራቸው በተጨማሪ በርካታ ሰብዓዊ ተግባራትን ያከናውኑ እንደነበረ በፊልሙ ተጠቅሷል። ይሄንንም ባለታሪኮች ራሳቸው አጠናክረውልናል።

“ለሰራዊቱ ራሽን ሲታደል እኛ ከመብላት ይልቅ ይዘን የምንሮጠው በምግብ እጦት ወደሚሰቃዩ ኮሪያውያን ህጻናት እና ሴቶች ነበር። ያቺን ሳናከፋፍል እኛ አንበላም ነበር። እነሱም ያውቁ ስለነበር ሰዓቷን ጠብቀው የኛን መምጣት ይጠባበቁ ነበር” ሲሉ ሻምበል ይልማ ገልፀውልናል። “በወቅቱ በሀገሪቱ በነበረ ጦርነት በርካቶች ያለምግብ ረጅም ጊዜ ለመቆየት በመገደዳቸው እኛ ኢትዮጵያዊያን ወታደሮች ስለእውነት ከፍተኛ ድጋፍ አድርገንላቸዋል” ሲሉ ሌሎችም አጠናክረውታል።

ኢትዮጵያውያኑ አብሮ መብላት እና ያለውን የሚያካፍል ማህበረሰብ መካከል በመኖራቸው እንዲህ አይነቱን ተግባር መፈፀማቸውን ነው እነዚህ አባቶች በኩራት የሚገልጹት። በዚህም ሳቢያ ከሌሎች ሀገራት ሠራዊት በበለጠ ኢትዮጵያዊያን ሰራዊት ከኮሪያውያን ጋር የጠበቀ ቅርበት እንደነበራቸውም አባቶች አጫውተውናል። “የኮሪያ ሴቶች የሌላ ሀገር ወታደርን አትቀርብም። እኛ ግን ለእነሱ ያለንን ሀዘኔታ ስለሚያውቁ አይለዩንም። በዚህ ቅርርብ የተነሳ እስከ ፍቅር ደረጃ የደረሰ ኢትዮጵያዊ ወታደር እና የኮሪያ ሴቶች ነበሩ። ምን ያደርጋል ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ተለያይተዋል” ሲሉ ያዩትን መስክረዋል።

ሁሉም ሰራዊት ከሰኞ እስከ ቅዳሜ መደበኛ ግዳጅን ሲወጣ ይሰነብትና የእረፍት ጊዜው እለት ሰንበት ብቻ እንደሆነች የሚያስታውሱት ዘማቾቹ፤ ሌላው ሰራዊት ይህችን የእረፍት ቀን ራሱን በመንከባከብ እና በራሱ ዙሪያ የሚያሳልፍ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ሰራዊት ግን ቀኗን በጉጉት የሚጠብቁበት የራሳቸው የተለየ ምክንያት አላቸው። ባለታሪኮቹም ይሄንኑ በትውስታ ይገልፁታል። “እሁድን በጉጉት ነበር የምንጠብቃት። በዚያን ቀን በማለዳ ተነስተን በተለያዩ ምክንያት ወላጆቻቸውን አጥተው በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ወደሚኖሩ ህጻናት ነበር የምናመራው። እዚያ ሄደን ለህፃናቱ ራሽን እንሰጣለን። እያጠብን እና እየተንከባከብን ፍቅር እንሰጣቸዋለን። ቋንቋም ባናውቅ ስናጫውታቸው እና ሙሉ ጊዜያችንን ስንሰጣቸው ያሉበትን ሁኔታ እስከመርሳት የሚደርሱበት ጊዜ ነበር” ሲሉ የነበረውን ሁኔታ አካፍለውናል። “ምናልባትም እነዚያ ህጻናት በዚያን ሰዓት የሚሰማቸውን ነገር እናንተ ብታዩት ሁኔታውን በግልጽ ትረዱት ነበር” ሲሉም ስሜታቸውን ገልጸውልናል።

የኮሪያ ጦርነት ሲነሳ በአብዛኞቻችን አእምሮ ውስጥ የሚመላለስ አንድ ነገር አለ። ይኸውም ኢትዮጵያዊያን የኮሪያ ዘማቾች የሰው ስጋ በልተዋል ይባላል። ለመሆኑ ይሄ ነገር እንዴት ነው አልናቸው። ጥያቄያችንን የመለሱልን አባቶች በሳቅ በመታገዝ ነበር። “ነገሩ እንዲህ ነው፡ የሆነ ሳይሆን ሌሎች የፈጠሩት ታሪክ ነው” አሉን አንድ አባት። “ኢትዮጵያውያን የሰው ስጋ በልተው ሳይሆን ታሪኩ የተቀናበረ ነው። በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ጥሬ ስጋ በኪሳቸው ይዘው አስክሬን ላይ ተቀምጠው በልተዋል። ስጋውን ከኪሳቸው አውጥተው በሳንጃ ሲቆርጡ ያዩ ከአሜሪካ እና ኬሎች ሀገራት የመጡ ወታደሮች የተለየ ነገር ነበር የሆነባቸው” አሉን እኚህ አባት። በዚህም የተነሳ ነገሩ ያልገባቸው ኢትዮጵያውያን የሰው ስጋ ይበላሉ እያሉ እንዳስወሩባቸው ነው የገለፁልን።

     ከአመጋገብ ጋር የተያያዘ ጉዳዮችን ማንሳታችን ካልቀረ በወቅቱ ኢትዮጵያውያን ሰራዊት ከሌላው ሀገር ሰራዊት በተለየ መልኩ የአመጋገብ ዘዬው የተለየ እንደነበረ ተነግሮናል። “ሌላው ሰራዊት እኮ ህይወት ያለውን ነገር ሁሉ ይበላል። የበከተ ሁሉ ይበላል። እኛ ግን መርጠን ነው የምንበላው” ብለውናል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1619 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 634 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us