ከአንድ ብርቱ. . .

Wednesday, 12 March 2014 12:24

የሴቶች ራስ አገዝ ማህበር (Women Support Association) ከተመሰረተ ከ15 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፤ በዚህ ቆይታውም ከ6 መቶ ሺህ በላይ ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሴቶች የራሳቸውን ገቢ ማግኛ እንዲፈጥሩ፣ ማህበራዊ ህይወታቸው የተቃና እንዲሆን እና ሴት ልጆች የትምህርት እድል እንዲያገኙ በርካታ ስራዎችን ሰርቷል። በማህበሩ የሚረዱ ሴቶች ከሬት ተክል ሳሙና እንዲሁም የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ (ሞዴሶችን) የማምረት አቅም ላይ ደርሰዋል። ማህበሩ ልክ እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ ባለፈው ቅዳሜ ከየአካባቢው የተውጣጡ የማህበር ተጠቃሚዎች በተገኙበት በበሻሌ ሆቴል ዓመታዊ ጉባኤውን አካሂዷል።

በጉባኤው ላይ ተሳታፊ ከነበሩት ሴቶች መካከል አንዷ ወይዘሮ ከድጃ መሀመድ ሲሆኑ፣ ወይዘሮ ከድጃ የመሰረት ራስ አገዝ ህብረት ዋና ፀሐፊ ናቸው። ወይዘሮ ከድጃ ወደ ራስ አገዝ ማህበር የገቡት በ2004 ዓ.ም ነው። ከዚያ በፊት ግን ሶስት ልጆቻቸውን ያሳድጉ የነበሩት ስፌት ሰፍተው እና ሽሩባ ሰርተው በመሸጥ ነበር። በተመሳሳይ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ እና የአንድ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ 200 ሴቶች በመሰባሰብ ነበር ማህበሩን የመሰረቱት። ቡድኑ በወር ሁለት ጊዜ ጠቅላላ ስብሰባ በማካሄድ የሰራውን ይገመግማል፤ የብድር አሰጣጥ እና አመላለስን በተመለከተ ውይይት እና ክትትል ያደርጋል። በተጨማሪም የትምህርት እና የልማት ቅስቀሳዎች ይካሄዳሉ። ወይዘሮ ከድጃም ከዚህ ማህበር ያገኙትን ጠቀሜታ እንዲህ ይገልፁታል።

“እኔ ቃላት ያጥረኛል። ራሴን ብወስድ ቁጠባ መቆጠቡን ስለማላውቅ አምስት ሳንቲም አልነበረኝም። ስልጠናውን ከወሰድን በኋላ ግን በፍላጎታችን ተደራጅተን በአምስት ብር ነው የጀመርነው። የእለት ጉርስ ከመያዝ በስተቀር የምቆጥበው ነገር አልነበረኝም። ዛሬ ግን ከዚያው ከቡድናችን ብድር በመውሰድ በንግድ ስራ ተሰማርተን በሳምንት እስከ 50 ብር በመቆጠብ ላይ እንገኛለን” የሚሉት ወይዘሮ ከድጃ፤ በቡድን በመደራጀታቸው በኢኮኖሚ ራሳቸውን ከመቻል በተጨማሪም በማህበራዊ ህይወታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣታቸውን ይናገራሉ። ቀድሞ በብቸኝነት ይኖሩ የነበሩ ሴቶች አሁን ግን በሀዘንም በደስታም በጋራ ለመኖር በቡድን መደራጀታቸው እንደጠቀማቸው ይናገራሉ።

“አሁን አንዲት ሴት ስትወልድ ዘመድ ኖራትም፣ አልኖራትም እስከ አርባ ቀን ድረስ ተራ በተራ እየገባን እያረስን፣ ሀዘንም ከደረሰባት ተራ በተራ ሁላችንም እናግዛታለን። ልጅ የምትድር ከሆነችም ሁላችንም ዩኒፎርማችንን ለብሰን ለሌሎች አርአያ እና ግንባር ቀደም ሆነን እንተጋገዛለን ይላሉ።

ከወረኢሉ ወረዳ የመጡትና በአሉ ቀበሌ አንድ የእንደግ በህብረት ማህበር ሰብሳቢ የሆኑት ወይዘሮ አፀደ ከተማ በበኩላቸው ወደ ማህበሩ የገቡት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ቢሆንም በርካታ ጠቀሜታዎችን እንዳገኙ ይናገራሉ። ማህበሩ ሲጀምር ቁጠባቸው ከአንድ ብር የተነሳ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን አንዲት ሴት በአማካይ ከ50 እስከ 100 ብር በሳምንት ትቆጥባለች።

ከዚህ በተጨማሪም በቤተሰብና በማህበረሰብ ወይይት ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ላይ መሆናቸውን ወይዘሮ አፀደ ይናገራሉ። “በማህበራዊ ችግሮች ላይ በየጊዜው ውይይት እናደርጋለን። የተጋጩ ባለትዳሮችን ከማስታረቅ አንስቶ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይካሄዳል። ወላጆች ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት እያስቀሩ ስራ ማስራት እንደሌለባቸውም እናወያያለን። በአሁኑ ጊዜ ልጁን ከትምህርት ቤት የሚያስቀርም ሆነ በትዳር ላይ መግባባትን በውይይት የማይፈታ ሰው አይኖርም” ይላሉ።  

እርሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ ይኖሩ የነበሩ በርካታ ሴቶች እንጀራ መጋገርን የመሳሰሉ የጉልበት ስራዎችን ከመስራት ውጪ ህይወታቸውን ለመለወጥ ብዙም ጥረት ያደርጉ እንዳልነበር የገለፁት ወይዘሮ አፀደ፤ አሁን ግን አብዛኞቹ የዚህ ማህበር ተጠቃሚዎች በመሆናቸው በህይወታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት መቻላቸውን ገልፀውልናል።

ሌላዋ በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ያገኘናቸው ሴት ከአርጎባ ቀበሌ የመጡት ወይዘሮ ሀዋ ፋሪስ ናቸው። ወይዘሮ ሀዋ በትዳር አለም ሶስት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን ትዳራቸው ባለመግባባት በመፍረሱ ልጆቻቸውን በብቸኝነት ያሳድጋሉ። ባለቤታቸው ጥለዋቸው ወደ ጅቡቲ በመሄዳቸው እርሳቸውም ለስደት ተዘጋጅተው ነበር። “እነዚህን ልጆች እንዴት አድርጌ ብቻዬን አሳድጋቸዋለሁ ብዬ እኔም ወደ ድኩቲ ለመሄድ በወሰንኩበት ወቅት ነው ወደዚህ ማህበር የመግባት እድል ያገኘሁት” የሚሉት ወይዘሮ ሀዋ ይህ አጋጣሚ በሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣ ይናገራሉ።

“ከራሴ ብነሳ በፊት ምንም ነገር የማላውቀውን አሁን ግን ሀዋ ብዬ ፅፌ ነው የምፈርመው። ሌሎች መሰሎቼም አሁን ስማቸውን ፅፈው ነው የሚፈርሙት” የሚሉት ወይዘሮ ሀዋ፤ በአካባቢው በሴቶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችንም በኮሚቴ ተዋቅረው መታገል መቻላቸውን ይናገራሉ።

ከውርጌሳ ራስ አገዝ ማህበር የመጡት ወይዘሮ እጅጋየሁ ዋኘው በበኩላቸው በማህበራቸው ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሴቶች ከራሳቸው አልፈው በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት መቻላቸውን ይናገራሉ። “የኛ ማህበር አባላት ከትንሽ ነገር ተነስተን ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ችለናል። በአሁኑ ጊዜ በንግድ ዙሪያ የምንንቀሳቀስ ሲሆን ቤተሰባችንን መምራት እና በማህበረሰቡ ዘንድም ተቀባይነት ማግኘት ችለናል” ይላሉ።

በማህበረሰቡ ዘንድ ሴቶች ቀደም ሲል የነበራቸው ተቀባይነት አናሳ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግን የተለየ ክብር እና ቦታ እየተሰጣቸው መሆኑንም ወይዘሮ እጅጋየሁ ይገልፃሉ። “ዛሬ ላይ ሁላችንም ዩኒፎርማችንን ለብሰን ነው የምንሄደው። አንዲትም ሴት የተቀደደ ቀሚስ ለብሳ አትታይም። እውነቱን ለመናገር የትኛው ባል ነው ለሚስቱ ልብስ የሚገዛ? ወይም ግዢበት ብሎ ገንዘብ የሚሰጥ? ማንም የለም! የእኛ አባላት ግን ዩኒፎርማቸውን ለብሰው ከሰው እኩል ውለው ይገባሉ” ይላሉ። እንደ እርሳቸው ገለፃ በአሁኑ ወቅት በአኪሱ ቀበሌ ሴቶች ከእንጨት ምድጃ ወጥተው ወደ ኤሌክትሪክ ምድጃ ተሸጋግረዋል።

የውርጌሳ ራስ አገዝ ማህበር ከምንም በላይ ደግሞ ለፆታዊ ጥቃት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የገለፁልን ወይዘሮ እጅጋየሁ፤ የጥቃት ተከላካይ ስፖርት ኮሚቴ ተቋቁሞም በርካቶችን ከጥቃት በመከላከል ላይ እንደሆነ ገልፀውልናል።

ሌላው በዚህ በራስ አገዝ ማህበር የታቀፉ ሴቶች እያገኙት ያለው ጠቀሜታ የትምህርት እድል መሆኑን ነው ወይዘሮ ከድጃ የገለፁልን። በተለይ ጎልማሳ እና ያልተማሩ ሴቶች ትምህርት እንዲያገኙ ራሳቸው የህብረቱ አባላት አመቻቾችን በመምረጥ ትምህርት ይሰጣል። በዚህም ቀድሞ በጣታቸው ይፈርሙ የነበሩ በርካታ ሴቶች ዛሬ ላይ አንብበው በብእር ለመፈረም መብቃታቸውን ወይዘሮ ከድጃ አያይዘው ገልጸውልናል። ከትምህርት ጎን ለጎንም ቡድኖቹ የማህበረሰብ ወይይት ያካሂዳሉ። በጣም ከፍተኛ ችግር አለባቸው ተብለው የተለዩ ቦታዎች ላይም ጠንካራ ስራ ይሰራል፤ እንደ ወይዘሮ ከድጃ አባባል።

“በጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ከፍተኛ ችግር አለባቸው ተብለው የተመረጡ ሁለት ጎጦች አሉ። በእነዚህ ቦታዎች ላይ በየአስራ አምስት ቀኑ እየተገናኘን እንወያያለን። ቃለ ጉባኤ አያይዝን በችግሮቹ እና መፍትሄው ላይ እንወያያለን” ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪም በየሶስት ወሩ የቤተሰብ ውይይት ይካሄዳል። ይህ የቤተሰብ ውይይት በሁለት መልኩ እንደሚካሄድ ነው የተገለፀው። የመጀመሪያ በየሳምንቱ የሚከናውን ሲሆን ይህም በቤት ውስጥ በራስ ቤተሰብ ጋር ይሆናል። ሁለተኛው ግን እያንዳንዱ አባል ቤተሰቡን ይዞ በመሰብሰብ የሚካሄድ ነው። “በሶስት ወር በሚካሄደው ውይይት ላይ የእያንዳንዱ ቤተሰብ ውይይት ሪፖርት እና የመዝገብ ሪፖርት ይቀርባል። የቆጠብነው ገንዘብ ስንት እንደደረሰ እንዲሁም አዲስ ያወጣነው ህገ-ደንብ ካለ ለባለቤቶቻችን እናቀርባለን። ባለቤቶቻችን ደግሞ እኛ ያለብንን ጠንካራ እና ደካማ ጎናችንን ይነግሩናል” ብለዋል ወይዘሮ ከድጃ።

ይህ እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶም በርካታ ሴቶች በራሳቸው፤ በቤተሰባቸው እና በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጡ ተገልጿል። በርካታ ከቤት ወጥተው እንኳን የማያውቁ ሴቶች ዛሬ በራስ መተማመናቸውን በመጨመር በአነጋገርም ሆነ በአኗኗራቸው ከፍተኛ ለውጥ ማምጣታቸውን ወይዘሮ ከድጃ የገለፁልን ሲሆን፤ ቀድሞ ስብሰባ እንኳን ውጡ ሲባሉ ይቃወሙ የነበሩ ሴቶች አሁን ግን ግንባር ቀደም ሆነው እንደሚቀርቡ ነው የተናገሩት።

ወይዘሮ እጅጋየሁ በበኩላቸው በጎልማሶች ትምህርት ደረጃ በሚሰጡት ተግባር ተኮር ስልጠና በርካታ ሴቶች ዛሬ ላይ በጣት ከመፈረም አልፈው የተፃፈውን አንብበው በራሳቸው ፊርማ መፈረም እንደጀመሩ እንዲሁም የሰሩበትን ሂሳብ የማወራረድ ችሎታን እንዳዳበሩ ይናገራሉ።

ከቤተሰብ እና ማህበረሰብ ውይይት ጋር በተያያዘም ያለውን ለውጥ ወይዘሮ እጅጋየሁ እንዲህ ይገልፁታል። “እኛ ከባሎቻችን ጋር የምንገናኝበት ዘዴ የቤተሰብ ውይይት ነው። በቤተሰብ ውይይት ወቅት ባሎቻችንን ማሳመን እየቻልንበት ነው” ይላሉ።

በአርጎባ አካባቢ ሴቶች ቤት ውስጥ ተቀምጠው ልጆች ወልደው ማሳደግ እንጂ ሌላ ኃላፊነት የሚሰጣቸው እንዳልነበረ የሚናገሩት ወይዘሮ ሀዋም፤ በቤተሰብ እና በማህበረሰብ ውይይት ግን የማህበረሰቡን አመለካከት መቀየር መቻላቸውን ይናገራሉሉ። “አሁን ሴቶች መስራት እንደሚችሉ ሁሉም ሰው እያመነ ይመስለኛል። ሴቶቹ በመድረክ ላይ ወጥተው መናገር ጀምረዋል። በዚህም ህብረተሰቡም እየተቀበላቸው ይገኛል” ብለዋል።

እነዚህ ሴቶች የማህበረሰቡ አካል እንደመሆናቸው ወደዚህ እንቅስቃሴ ሲገቡ ተግዳሮቶች ሳይገጥሟቸው አላለፉም። ወይዘሮ እጅጋየሁ እንዲህ ይገልጹታል። “ባሎቻችን ስራውን ስንጀምር ደስተኛ አልነበሩም። ተሰባስበን ወሬ አውርተን የምንመለስ ይመስላቸው ነበር። ነገር ግን በወይይት ወቅት ውጤታችንን ሲመለከቱ እያመኑ እና እየደገፉን ይመጣሉ” ይላሉ።

ወይዘሮ ከድጃም ተመሳሳይ ሀሳብ አላቸው። “በፊት በፊት ባሎች ሚስቶቻቸውን እዚያ ሄደሽ ስራ ልትፈቺ ነው፤ ገንዘቡስ ከየት ይመጣል? እያሉ ይከለክሏቸው ነበር። ነገር ግን በየቤታችን በመወያየት እና የስራነውን በማሳየት ልንለውጣቸው ችለናል” ይላሉ።

በጉባኤው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የራስ አገዝ ሴቶች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ማርታ ነበሩ እንደገለፁት ሴቶች ከምንም ነገር በላይ በቅድሚያ በኢኮኖሚ ራሳቸውን መቻል ስላለባቸው በዚህ ረገድ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። “ዋናው ነገር የራሳቸው ገቢ እንደኖራቸው ማድረግ ነው። የራሳቸውን ገቢ መፍጠር ሲችሉ ውሳኔ መስጠትም፣ ተናግረው ማሳመንም ይችላሉ” ያሉት ወይዘሮ ማርታ፤ ማህበሩም በሴቶች ላይ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ሴቶቹ በተደረገላቸው ጥቂት ድጋፍ በፋብሪካ የሚሰራ ምርቶችን ጭምር በራሳቸው በመስራት ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
2068 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 772 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us