የትምህርት ዘርፉ የቱ ጋር ነው?

Wednesday, 26 March 2014 12:34

ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርትና ስልጠና ዙሪያ ምን እየሰራ ነው? ምን ውጤት አስመዘገበ? ምን ጉድለትስ ተስተዋለበት? በሚለው ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ባለፈው ሳምንት ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርገው ነበር። እኛም የትምህርት መስኩ አካሄድ ምን ይመስላል የሚለውን ቃኝተናል።

በ2006 አጠቃላይ የሀገሪቱን የተማሪዎች ተሳትፎ 107 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ አፈፃፀሙ ግን 109 በመቶ ደርሷል። ይህ አፈፃፀምም የሚያመለክተው በርካታ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ነገር ግን የትምህርት እድል ሳያገኙ በየቤታቸው የተቀመጡ ህፃናት መኖራቸውን እንደሆነ ትምህርት ሚኒስቴሩ ገልፀዋል። የ1ኛ ክፍል ተማሪዎች ቅበላን በተመለከተም 3 ሚሊዮን 510ሺ ህፃናትን ለመቀበል ተችሏል። ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በተመለከተ 20 ሚሊዮን 660ሺ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ማስገባት ተችሏል።

በሚሊኒየሙ የልማት ግብ መሠረት “ትምህርት ለሁሉም” ወይም “Education for all” በሚለው መርህ እ.ኤ.አ በ2015 ሁሉም ህፃናት ትምህርት ያገኛሉ። ሀገራትም ይህን ግብ ለመምታት የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ላይ ናቸው። የተቀመጠው ጊዜ ወደ መገባደዱ በመሆኑም ብዙዎቹ ሀገራት ያቀዱትን መፈፀም ይችሉ ዘንድ በጥድፊያ ላይ ያሉ ይመስላሉ።

ኢትዮጵያም ይህን የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ተግባራዊ ለማድረግ በያዘችው እቅድ መሠረት እየሰራች መሆኑን ነው የትምህርት ሚኒስትሩ የገለፁት። ይህን እቅድ ለማሳካት በየዓመቱ የተከፋፈለ እቅድ የተዘጋጀ በመሆኑ አፈፃፀሙ እየገመገመ ይገኛል። በየመስኮቹ የሚመዘገበው አፈፃፀም የተለያየ ቢሆንም፤ በአንዳንዶቹ ግን ጥሩ አፈፃፀም እየተመዘገበ ይገኛል። ለአብነት ያህልም በቅድመ መደበኛ ትምህርት (መዋዕለ ህፃናት) ቅበላ በ2007 ዓ.ም 20 በመቶ ለመድረስ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፤ እስከ 2006 አጋማሽ ድረስ ያለው አፈፃፀም 31 በመቶ ነው። በመሆኑም እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ይህን ቁጥር 35 በመቶ ለማድረስ እቅድ ተይዟል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በ1999 (እ.ኤ.አ.) 33 በመቶ የነበረው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተሳትፎ በ2015 ዓ.ም 50 በመቶ ደርሷል። ሆኖም ግን በታዳጊ ሀገራት በተለይም ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ተሳትፎው 18 በመቶ ብቻ ነው። በዚሁ ዓመት 57 ሚሊዮን ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ የነበሩ ሲሆን፤ ይህም ለትምህርት ትኩረት የተነፈገው መሆኑን ያመለክታል።

ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ጋር በተያያዘ የዩኔስኮ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ከሚገኙ የዝቅተኛ ቤተሰብ ሴት ልጆች ውስጥ 23 በመቶዎቹ ብቻ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቅቃሉ። በዚህ ረገድ ወንድ ህፃናትም በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ማየት ይቻላል። በ2011 ዓ.ም 69 ሚሊዮን ታዳጊ ወንዶች ከትምህረት ገበታ ውጪ እንደነበሩም መረጃው ያመለክታል። በዚህ ዓመት አጠቃላይ 774 ሚሊዮን የሚሆኑ ምንም ትምህርት የሌላቸው ወጣቶች በዓለማችን ላይ ይገኙ እንደነበረ የሚገልፀው ሪፖርቱ፤ በ2015 ይህን ቁጥር ወደ 743 ሚሊዮን ዝቅ ለማድረግ መታቀዱንም ጨምሮ ገልጿል።

ሁለተኛ ሳይክል (የመሰናዶ ትምህርት)ን በተመለከተም የታቀደው እቅድ እና የተገኘው ለውጥ ከፍተኛ ልዩነትን አምጥቷል። ይኸውም 290ሺ ተማሪዎችን ለመቀበል ታስቦ 456 ሺ ተማሪዎችን በ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ለማስተማር ተችሏል። ይህም ሊሆን የቻለው የ10ኛ ክፍል ተፈታኞች ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመምጣቱ ነው። በዚህም መሠረት በ2005 ዓ.ም ሁለት ነጥብና ከዚያ በላይ ያመጡ የነበሩ ተማሪዎች ቁጥር ወደ 73 በመቶ ማደጉን አቶ ሽፈራው ገለፀዋል። በተጨማሪም ወደ መስናዶ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር ባለፉት ሁለት ዓመታት እምርታን አስመዝግቧል።

ትምህርትን የማጠናቀቅ ምጣኔን በተመለከተም ያለው አፈፃፀም አበረታች ነው። ከአንደኛ እስከ 4ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን የትምህርት ማጠናቀቅ ምጣኔን እንኳ ብንመለከት 76 በመቶ ነው።

ከ5ኛ ክፍል እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች የትምህርት ማቋረጥ ደግሞ 42 በመቶ ደርሷል።

የቴክኒክና ሞያን በተመለከተ በ2006 393 ሙያዎችን ለመለየትና ደረጃ ለማውጣት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፤ አፈፃፀሙ 628 ነው። ምዘናውንም ከተፈታኞቹ 71 በመቶዎቹ እንደሚያልፉ ተገልጿል።

ከትምህርት ጋር በተያያዘ ሌላው የሚነሳው ትምህርትን ማቋረጥ ነው። ይህ ጉዳይ በሀገራችን ትልቅ ተግዳሮት ይወሰድ እንደነበረ የተገለፀ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም ለውጥ እያመጣ መሆኑ ተመልክቷል። ባለፈው ዓመት ከአንደኛ ክፍል ትምህርትን የማቋረጥ ችግር 16 በመቶ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን ከ3 በመቶ በታች መውረዱ ተገልጿል። በዚህ መሠረት ከቀጠለም በዓመቱ መጨረሻ ላይ ተግሩን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እንደሚቻል ተስፋ ተደርጓል።

ዝቅተኛ የትምህርት ጥራት ማለት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት መሠረታዊ እውቀቶችን አልገበዩም ማለት ነው ይላል ዩኔስኮ። አያይዞም 250 ሚሊዮን ያህል ህፃናት በዓለም ላይ ጥራት ያለው ትምህርት ማግኘት ባለመቻላቸው መሠረታዊ እውቀት እንደሌላቸው ይገልፃል። እነዚህ ህፃናት መሠረታዊ እውቀት ሳያገኙ ቢያንስ አራት ዓመታት በትምህርት ቤት በማሳለፋቸው ደግሞ 129 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኪሳራ ይደርሳል ይላል።

ኢትዮጵያም የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ ትገኛለች። ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች መካከል ደግሞ አንዱ ጥራት ያላቸው መምህራንን ማቅረብ ነው። በመሆኑም እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚያስተምሩ መምህራን 25 በመቶዎቹን የማስተርስ ዲግሪ ባለቤት ለማድረግ እየተሰራ ነው። ከዚህ በተጨማሪም እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ በተፈለገው ሙያ ብቃት ያላቸው መምህራንን ከተለያዩ ሀገራት በማስመጣት እንዲያስተምሩ በመደረግ ላይ ነው።

ከትምህርት እቅዱ አፈፃፀም ጋር በተያያዘ የታሰበውን ግብ ማስገኘት ያልቻለው የ9ኛ እና 10ኛ ክፍል ተማሪዎች (ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት) አፈፃፀም ነው። በዚህ ረገድ እስከ 2006 ድረስ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ቅበላ 58 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም የተገኘው ውጤት የሚያመለክተው ግን አፈፃፀሙ 40 በመቶ መሆኑን ነው። ይህ ፈፃፀም ደግሞ ሊጠናቀቅ አንድ ዓመት ብቻ የቀረውን የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ተገልጿል። በተቀመጠው ግብ መሠረት የሁለተኛ ደረጀ ተማሪዎችን ቅበላ ኢትዮጵያ 62 በመቶ ለማድረስ አቅዳ ነበር።

ይህ የአፈፃፀም ክፍተት ሊፈጠር የቻለውም በተለይ ከ8ኛ ክፍል ወደ 9ኛ ክፍል የሚሸጋገሩ ተማሪዎች መንጠባጠብ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በበቂ ሁኔታ አለማዳረስ እንደ ምክንያት የቀረቡ ናቸው።

ሌላው እንደ ችግር የተነሳው በትምህርቱ ዘርፍ ያለው የጾታ ተዋፅኦ ነው። ለአብነት ያህለም 356ሺ ተማሪዎች ባሉበት የከፍተኛ ትምህርት የጾታ ተዋፅኦን ስንመለከት በመጀመሪያ ዲግሪ 34 በመቶ፣ በማስተርስ ደረጃ 20 በመቶ እንዲሁም በዶክትሬት ደረጃ 11 በመቶ ነው። ይህም ራሱን የቻለ ምክንያት እንዳለው ነው የተገለፀው።

ይህ የጾታ ተዋፅኦ በሀገራችን ብቻም ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስተዋለ ይገኛል። በ2011 ዩኔስኮ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው በዓለማችን ላይ ካሉ 774 ሚሊዮን ያልተማሩ ወጣቶች መካከል ከሁለት ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። በሚያሳዝን መልኩ ደግሞ እነዚህ ወጣት ሴቶች ከድንቁርና ለመላቀቅ እስከ 2072 ሊፈጅባቸው ይችላል። እስከ 2005 (እ.ኤ.አ.) ሀገራት ይህን የጾታ ልዩነት ለመቅረፍ እቅድ ይዘው የነበረ ቢሆንም፤ 60 በመቶዎቹ በአንደኛ ደረጃ ያለውን ክፍተት ሲቀርፉ በሁለተኛ ደረጃ ያለውን የቀረፉት ደግሞ 38 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣም የልዩ ፍላጐት ተማሪዎች የትምህርት እድል ለማግኘት በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው ተገልጿል። ከሌላው ተማሪ በተጨማሪ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች በመኖራቸው እነዚያን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ ከችግሩ መጠነ-ሰፊነት የተነሳ በቀላሉ መቅረፍ አለመቻሉን ሚኒስትሩም ጨምረው ገልፀዋል።

እንደ አቶ ሽፈራው አገላለፅ ችግሩ የሚታይበት መጠን እና በተጨባጭ መሬት ላይ የሚታዩት ችግሮች የተለያዩ ናቸው። ችግሩ እና የችግሩ ባህሪይ ከሚደረገው ጥረት በላይ ከመሆኑም ባሻገር፣ የኅብረተሰቡ አመለካከትም ትልቅ ቅስቀሳ የሚፈልግ በመሆኑ እቅድ ተይዞ እየተሰራበት ነው። እነዚህን አካላት ማንኛውም ሰው ማስተማር ባለመቻሉ ሰብአዊነትን የተላበሱ እና በፍላጐት የሚያስተምሩ መምህራን እየተዘጋጁ እንደሆነም ተገልጿል።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ በሆኑባቸው ሀገራት ዘንድ ችግሩን ለመቅረፍ እየተደረገ ያለው ጥረት እና የሚመዘገበው ለውጥም አነስተኛ መሆኑ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ አድርጐታል፤ እንደ ዩኔሰኮ ሪፖርት። እነዚህ ሀገራት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ዜጐቻቸውን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት የአምስት ዓመት የጊዜ ገደብ አስቀምጠው የነበረ ቢሆንም፤ እስከ 2011 (እ.ኤ.አ) ድረስ የ14 ሀገራት ከ1 ሚሊዮን በላይ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው።

ከእነዚህ ከትምህርት ገበታ ውጪ ከሆኑ ህፃናት መካከል ደግሞ በአብዛኛው ተጐጂዎቹ የአካል ጉዳት ችግር ያለባቸው ህፃናት እንደሆኑ ተገልጿል። እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሌሎች ህፃናት በተለየ መልኩ ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ የሚደረጉት በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ብቻም ሳይሆን በኢኮኖሚ ባደጉ ሀገራትም ጭምር ነው።

     የተማሪ ቅበላን አስመልክቶ በተወሰነ ደረጃ እ.ኤ.አ ከ1999 እስከ 2011 ባለው ጊዜ ውስጥ መሻሻል እንዳለ ያመለከተው ሪፖርቱ ኢትዮጵያንም ትልቅ ለውጥ ካመጡ ሀገራት ተርታ መድቧታል። ይኸውም በሀገሪቱ በ1999 ዓ.ም 23 በመቶ የነበረው የተማሪዎች ቅበላ በ2011 94 በመቶ መድረሱን ሪፖርቱ ያመለክታል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
2214 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1087 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us