ስለ በጎ ፈቃደኝነት - ከበጎ ፈቃደኞች ጋር

Wednesday, 02 April 2014 12:51

በርካታ በራሳቸው ስራ ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ እና በትምህርት አለም ያሉ ወጣቶች የየድርሻቸውን ለመወጣት ለአንድ ዓላማ ተነስተዋል። ለበጎ አድራጎታቸው መዳረሻ ያደረጉት ደግሞ ሴቶችን እና ህፃናትን ነው። በተለያዩ ምክንያቶች ተገደው በለጋ እድሜ በመደፈር የልጅ እናት የሆኑ፣ በተለይ ከኤች አይ ቪ ኤድስ የተጋለጡ ሴቶችን እና ህፃናትን ለመርዳት ባላቸው ተመሳሳይ አላማ የተገናኙት እነዚህ በጎ ፈቃደኞች በመሰረት በጎ አድራጎት ደርጅት ስር ተሰባስበዋል። በድርጅት ስር ከተማሪ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ባለሙያዎች የሚደርሱ 70 ያህል በጎ ፈቃደኞች ተሰባስበዋል።

እነዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች በዚህ ድርጅት ስር የሚረዱ ሴቶችና ህጻናትን ገቢ ለማሻሻል በቆይታቸው የተለያዩ ተግባራትን ያከናወኑ ሲሆን፤ ባለፈው እሁድ መጋቢት 21 ቀንም በሀርመኒ ሆቴል የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አዘጋጅተው ነበር። ከእነዚህ በጎ ፈቃደኞች መካከል ወጣት ማናዬ እውነቱ እና ሄኖክ ያሬድ ይገኙበታል።

ወጣት ሄኖክ ወደዚህ ድርጅት ከገባ ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል። ድርጅቱ ዝግጅት በሚያቀርብበት ወቅት ነበር ወደ ድርጅቱ የመግባት ሃሳቡ የመጣለት። “ዝግጅቶችን በምሰራበት ወቅት ነበር ድርጅቱን ያገኘሁት። በትልቅ ዝግጅት ላይ ድርጅቱ የሚሰራቸውን ስራዎች በሚያስተዋውቅበት ወቅት ነው፤ እኔም የድርሻዬን ለመወጣት ያሰብኩት” ይላል ወጣቱ ማናዬ።

ቀደም ብሎም በበጎ አድራጎት ስራ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንደነበረው የሚናገረው እና ወደዚህ ድርጅት ከገባ ከአንድ ዓመት በላይ እንዳስቆጠረ የሚናገረው ሄኖክ ግን አማርጬ ነው የገባሁት ይላል። “ከዚያ በፊት የቢዝነስ አማካሪ ነበርኩኝ። ይህን ድርጅት ከጎበኘሁት በኋላ ግን የራሴን ድርሻ ማበርከት እንዳለብኝ ወሰንኩኝ። ቀደም ብዬ ሌሎች ሶስት ድርጅቶችን ጎብኝቼ የነበር ቢሆንም የኔ አገልግሎት በይበልጥ የሚያስፈልገው በዚህ ድርጅት ውስጥ ነው ብዬ ገብቼያለሁ” ይላል።

ወጣት ማናዬ ቀደም ሲል የፕሮግራም ዝግጅት እና ማስተዋወቅ ላይ ይሰራ ስለነበር፤ በድርጅቱ ውስጥም ያለው ድርሻ ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። በተለይ በድርጅቱ የሚረዱ ሴቶና ህፃናት ገቢያቸው እንዲጨምር ለማድረግ የተለያዩ ዝግጅቶችን የማዘጋጀት ስራ ይሰራል። ይህን ድርጊት የሚያከናውነው ከሌሎች ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ቢሆንም እርሱ ግን ስራውን የሚሰራው ለተረጂዎቹ ካለው የተለየ ስሜት የተነሳ መሆኑን ይናገራል።

“እነዚህ በድርጅቱ ውስጥ የሚረዱት ሴቶችና ህጻናት ለተለያዩ ጥቃቶች የተጋለጡ ናቸው። ሲረዱም ሙሉ ለሙሉ ከአንድ ህይወት ወደ ሌላ ህይወት እንዲዛወሩ ነው የሚደረገው” የሚለው ወጣት ማናዬ፤ እነዚህ ሴቶችና ወጣቶች መርዳት ብቻም ሳይሆን ድህነትን አሜን ብለው እንዳይቀበሉ የማድረግ አላማ እንዳለው ይናገራል። ሴቶቹ ወደ ድርጅቱ እንደመጡ ዝም ብሎ እርዳታ እንዲያገኙ ከማድረግ ይልቅ የተለያዩ ለህይወታቸው ጠቃሚ የሆኑ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ መደረጉ ሴቶቹ ከተረጂነት ስሜት ወጥተው ራሳቸውን እንደ አባል እንዲቆጥሩ ያደረጋቸዋል ባይ ነው።

“በድርጅቱ ውስጥ የሚረዱት ገና በ6 እና 10 ዓመታቸው ተደፍረው የልጅ እናት የሆኑ ናቸው። እንዲህ አይነቶቹን ነገሮች ምናልባት በሚዲያ ነው የምንሰማው። ወደዚህ ስራ ሲገባ ግን በአይን ይታያል። የተለያዩ ታሪኮችን መስማት ይቻላል። አንዳንዶቹ በአጎታቸው፣ ሌሎቹ በወንድሞቻቸው ተደፍረው ገና በህፃንነታቸው የልጅ እናት ሆነው ነው የሚመጡት። ይህ ነገር በጣም ልብን የሚነካ ነው” ይላል።

በበጎ አድራጎት ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በጣም ለክፉ ችግር የተጋለጡ እና ከሴትነታቸው ጋር ተያይዞ በደረሰባቸው ስቃይ ህይወታቸው የተመሰቃቀለ 125 ሴቶች እና 280 ህጻናት ይረዳሉ። ሴቶቹ ሰልጥነው የራሳቸውን ስራ እንዲሰራ የመነሻ ገንዘብ ተሰጥቷቸው ስራቸውን ይሰራሉ። ሰርተው ከሚያገኙት ላይም በስማቸው ባንክ ገንዘብ ያስቀምጣሉ። ህፃናቱ በበኩላቸው የትምህርት ቤት ክፍያቸው፤ ደብተርና እስክሪብቶ፣ እዲሁም ዩኒፎርማቸው ይሟላላቸዋል። ተረጂዎች የህክምና አገልግሎት ሲያስፈልጋቸውም ነፃ ህክምና ያገኛሉ።

ይህ ሁሉ ስራ ታዲያ የሚሰራው ምንም አይነት ክፍያ በማይከፈላቸውና በበጎ ፈቃደኝነት በሚሰሩ በጎ ፈቃደኞች ነው። የጤና ባለሙያዎች በህክምናው ስራ፤ መምህራን ስልጠናን በመስጠት ተግባር ተሰማርተው የየበኩላቸውን ይወጣሉ።

ወደዚህ በጎ አድራጎት ድርጅት የገባው ሀብታም ስለሆነ ሳይሆን ባለው ነገር ሁሉ የበኩሉን ለመወጣት እንደሆነ የሚነገራው ወጣት ሄኖክ በበኩሉ፣ በድርጅቱ የሚረዱት ሴቶች እና ህጻናት በመሆናቸው የበለጠ የመስራት ስሜቱን እንደጨመረው ይገልጻል። “እርዱኝ ብሎ የሚጠይቁ ሁሉ ተረጂ እንዳልሆኑ ሁሉ፤ ያልጠየቀም ሀብታም ነው ማለት አይደለም። ስለዚህ እኔ ያለኝ አቅም ችሎዬን ተጠቅሜ ለእነዚህ ሰዎች ገቢ ማሰባሰብ ስለሆነ ያንን ለመወጣት በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀስኩ ነው፤ ለወደፊትም በዚህ መልኩ ለመቀጠል እና የብዙዎችን ህይወት ለመቀየር አላማ አለኝ” ይላል።

የእርዳታ ድርጅት ሲባል በብዙዎቻችን አእምሮ ውስጥ የሚመጣው በገንዘብ ወይም በቁስ መርዳት ነው። ነገር ግን በስራው ውስጥ ያሉ ሰዎች የራሳቸው አፈታት አላቸው። ወጣት ማናዬም እርዳታን እንዲህ ይገልፀዋል። “እርዳታ በገንዘብ መደገፍ ብቻ አይደለም። አቅም ያለው ቃል (Powerful word) ራሱ ትልቅ እርዳታ ነው” ይላል። ወጣት ሄኖክ ደግሞ መቆሸሽ እና በጥሩ አቀራረብ አለመቅረብ የእርዳታ ጠያቂዎች መገለጫ መሆንም የለበትም። “እኛ ተረጂዎቻችንን የምናሰለጥናቸው ፅዱ እና ጠንካራ እንዲሆኑ ነው። በመቆሸሽ እርዳታ ለማግኘት መሞከር የለባቸውም። የራሳቸውንም የልጆቻቸውም ንፅህና ጠብቀው ሲቀርቡ በራሳቸው ላይ ያላቸው እምነትም ጠንካራ ይሆናል” የሚለው ወጣት ሄኖክ፤ እርዳታ ማለት ሰዎች አቅም እንዲፈጥሩ ማድረግ መሆኑን ይገልፃል። “የእኛ ስራ በእርዳታ ብቻ የሚቆም አይደለም። ተረጂዎች በራሳቸው ላይ ለውጥ በማምጣት ከተረጂነት ለሀገርና ለወገን ጠቃሚ ወደሚያደርጋቸው ረጂነት መሸጋገር ያስፈልጋቸዋል። የተረጂነት ስሜት በራሱ ከባድ ነው” የሚለው ሄኖክ፣ እነርሱም እየሰሩ ያሉት ተረጂዎቹን ከዚህ ስሜት ለማላቀቅ መሆኑን ገልፆልናል።

በሀገራችን ባለው የእርዳታ ስርዓት ላይም እነዚህ የበጎ ፈቃደኞች ያላቸውን አስተያየት በተለያየ መልኩ ይገልፃሉ። በተለይ ወጣት ማናዬ እኛ ኢትዮጵያውያን እንረዳዳለን የምንለውን ነገር አያምንበትም። “ኢትዮጵያዊነት የመተጋገዝ ባህል ያለው ቢሆንም፤ አሁንም ግን ብዙ ሊሰራበት ይገባል። ስለእርዳታ ሀሳቡ ገና የገባን አይመስለኝም። የእርዳታ ሃሳብ ገና አልተለመደም” ሲል ይገልፃል። ሄኖክ በበኩሉ አካባቢያችንን ማዳመጥ የመጀመሪያው እርዳታ ነው ባይ ነው። “በአካባቢያችን ያሉትን ማዳመጥ ያስፈልጋል። መርዳት ማለት ድርጅት አቋቁሞ ብቻ አይደለም። የሰዎችን ሃሳብ ማዳመጥ እና መረዳት በራሱ ትልቅ እርዳታ ነው። እንዲህ አይነቱን ሀሳብ ማዳበር አለብን” ይላል።

በእነዚህ እና ሌሎች ጓደኞቻቸው ጥረት የተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅትም በደመቀ ሁኔታ ነበር የቀረበው። በዝግጅቱ ላይ የተለያዩ ባለስልጣናት፤ ባለሞያዎች እና ራሳቸው ተረጂዎቹ ጨምሮ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ እንግዶች ተገኝተዋል። ለዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ከታቀዱት ዝግጅቶች መካከልም በድርጅቱ የሚደገፉ ህፃናት አስደናቂ ኬሮግራፊ አቅርበዋል። በተጨማሪም በአዋቂዎች የተከናወነ የጫማ መጥረግ ውድድርን ጨምሮ በርካታ አዝናኝ ዝግጅቶች ቀርበው ነበር።

በዝግጅቱ ላይ የተገኙ በጎ ፈቃደኞችም ድርጅቱን በጎበኙበት ወቅት ሴቶቹ እና ህጻናቱ ባሳለፉት አሳዛኝ የህይወት ታሪክ ልባቸው በመነካቱ በራሳቸው ተነሳሽነት ወደዚህ እንቅስቃሴ እንደገቡ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት የወገኖቻችን ህመም ሊያመን ይገባል፤ ለወገኖቻችን አናንስም፣ እኛ በእኛው ለእኛው ፈጥነን ልንደርስ ይገባል በሚል መሪ ቃል በጎ አድራጊነትን በመተግበር ላይ ይገኛሉ።

     በዚህ በገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ለድርጅቱ ከ300 ሺህ ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ ቃል የተገባ ሲሆን፤ የተለያዩ የአይነት እርዳታዎችም ቃል ተገብተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በእለቱ ሁለት የተለያዩ ፎቶዎች ለጨረታ ቀርበው ነበር። የመጀመሪያውን ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ በ100ሺ ብር ያሸነፈ ሲሆን፤ ሁለተኛውን ደግሞ በተለያዩ ሰዎች ተሳትፎ 90ሺህ ብር ተሸጧል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
2823 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 781 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us