“የተነሱት ችግሮች ሃይማኖታዊ ችግሮች ናቸው የሚል ግምት የለኝም”

Wednesday, 09 April 2014 12:30

ኃ/ማርያም ታመነ የቅ/ስ/መ/ኮ ደቀመዛሙርት ሰብሳቢ

ሰሞኑን በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ውስጥ በሃይማኖት ሽፋን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ ነው የሚል ውዝግብ ሲነሳ ሰንብቷል። በዚህ ጉዳይ ላይ በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀመዛሙርት ሰብሳቢ ከሆኑት ኃይለማርያም ታመነ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ሰንደቅ፡- ሰሞኑን በመንፈሳዊ ኮሌጅ ውስጥ አንዳንድ ውዝግቦች ተፈጥረዋል። እነዚህ ውዝግቦች ምንድን ናቸው?

አቶ ኃ/ማርያም፡- የተነሳው ውዝግብ እንግዲህ በሃይማኖት ሽፋን ጉዳይ ነው። በሃይማኖት ምክንያት የተለያዩ ኀሳቦች እየተንፀባረቁ በተማሪው መካከል መለያየቶች ተፈጥረዋል። በዚህም ተማሪው በተለያዩ ሶስት ቡድኖች ተከፋፍሏል። የተወሰኑት አካላት ሃይማኖታዊ ችግር ስላለ ችግሩን መፍታት አለብን። ችግሩ ጊዜ የሚሰጠው አይደለም፤ ይህንን መግለፅ አለብን የሚሉ ናቸው። በዚህም እነዚህ አካላት ይህን ሃሳብ አውጥተው ክስ መስርተዋል።

ሰንደቅ፡- ክሱ ምንድነው?

አቶ ኃ/ማርያም፡- እነዚህ ተማሪዎች በክስ መልክ ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች ስናያቸው በክፍል ውስጥ በመማር ማስተማር ሂደት ሊመለሱ የሚችሉ ናቸው። ኮሌጁ ነገረ መለኮታዊ ትምህርት፣ የቤተክርስቲያን ቀኖና እና ዶግማ ተከብሮ በቤተክርስቲኒቱ ሊቃውንት የሚሰጥበት ታላቅ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንደመሆኑ፤ ጥያቄዎቹ እዚያ የሚመለሱ ናቸው። ደቀመዛሙቱም መፅሐፍ ቅዱስን መሰረት አድርገው ወቅቱንና ጊዜውን የዋጀ ደቀመዝመርት የማፍራት ዓላማ ያላትን ቤተክርስቲን አላማ የሚያስፈፅሙ ናቸው። ክሱም ሲታይ ተማሪዎቹ መምህራኖችን ጠይቀው ሊረዷቸው የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው በክስ ደብዳቤ የቀረቡት።

ይህ ለክስ የቀረበው ሃሳብ መምህራኑ ሊመልሱት እና ሊያቃኑት የሚችል ሲሆን በክስ መቅረቡ ተገቢ አይመስለኝም።

ሰንደቅ፡- በጥያቄዎቹ ሃይማኖታዊነት ላይስ ያለው ሃሳብ ምን ይመስላል?

አቶ ኃ/ማርያም፡- የተጠየቁት ጥያቄዎች ሃይማኖታዊ ችግሮች ናቸው የሚል ግምት የለንም። ምክንያቱም ጥያቄው ቀርቦ መምህራኑ የሚያቃኑት፣ የሚመልሱት መሆን ሲገባው ክስ ሆኖ መቅረቡ ለኮሌጁም ሆነ ለቤተክርስቲያኒቱ ጥሩ አይደለም። እነዚህ ከሳሽ የተባሉት አካላት ጥያቄያቸውን አስተዳደሩ እያየው ባለበት ሁኔታ ጉዳዩን በተለያዩ ጋዜጦችና መፅሔቶች እያራገቡት ነው። ምናልባት እነዚህ አካላት የራሳቸው ዓላማ ሊኖራቸው ይችላል። ነገር ግን ቤተክርስቲያኒቱንም፣ ኮሌጁንም ደቀመዛሙርቱንም በጣም ይጎዳል።

ሰማኒያ በመቶ የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀመዛሙርት የፕሮቴስታንት ተሃድሶ ተከታይ ሆኖ ተገኙ የሚለው በጋዜጦች፣ መፅሔቶች እና ድረገፆች ላይ እየተናፈሰ ነው ያለው። ጉዳዩ ሃይማኖታዊ ችግር ከሆነ ሁሉንም ደቀመዛሙርት ይመለከታል። ይህን ጉዳይ የያዙት ግን በቁጥር የተወሰኑት ናቸው። በኮሌጁ ውስጥ ደግሞ ከ150 በላይ ደቀመዛሙርት አሉ። ጉዳዩ የሃይማኖት ከሆነ እነዚህ ሁሉ ደቀመዛሙርት ሊያውቁት፣ ሊከታተሉት ሊሳተፉበት የሚገባ ሆኖ ሳለ የተወሰኑ ምናልባትም የተለየ ዓላማ ያላቸውና ማህበር ሳይወክላቸው ተወካይ ነን ያሉ ሰዎች ናቸው ሃሳቡን ያነሱት።

ሰንደቅ፡- አሁን ባለው ውዝግብ ምክንያት በኮሌጁ ተማሪዎች ዘንድ የተፈጠረ የተለየ ችግር ምንድን ነው?

አቶ ኃ/ማርያም፡- በአሁኑ ወቅት በኮሌጅ ውስጥ ያለው የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊ አይደለም። በኮሌጁ ውስጥ የተለያዩ መቅረጫዎችን የተለያዩ ደቀመዛሙት ይዘው ይንቀሳቀሳሉ። የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘትም አንዱ ሌላውን እየቀዳ ነው። ተማሪው ከክፍል ውስጥ ጥያቄ እንዳያቀርብና ዝም ብሎ የተነገረውን ብቻ ሰምቶ እንዲሄድ እየተደረገ ነው። በተማሪው መካከልም መተማመን የለም። ተማሪው አእምሮው ነፃ ሆኖ ትምህርቱን እንዳይከታተል እያደረገ ነው። ይሄንን ለመፍታት ጥረት ብናደርግም በካውንስሉም ዘንድ መከፋፈል እየተፈጠረ ነው።

እንዲያውም ትምህርት እናቆማለን ወደሚለው ድምዳሜ እየተሄደ ስለነበረ ይህን ችግር ለመቅረፍ እና ተማሪውንም ለማረጋጋት ኮሚቴው ስራዎችን ሰርቷል። ኮሌጁ መንፈሳዊ እንደመሆኑ ተማሪው ችግሩ እስኪፈታ ድረስ መንፈሳዊ እንጂ ስሜታዊ መሆን እንደሌለበት ለማስረዳት ሞክረናል። ጉዳዩንም ወደሚመለከተው አካል አቀርበን ተማሪው በሰከነ መንፈስ ትምህርቱን የሚከታተለበትን ሁኔታ እያመቻቸን ነው።

ሰንደቅ፡- ክሱን ያቀረቡት እነማን ናቸው?

አቶ ኃ/ማርያም፡- ከሳሾቹ ከካውንስል አባላት ተለይተው የወጡ ጭምር ናቸው። የሃይማኖት ችግር አለ፤ በሃይማኖችን ላይ ችግሮች እየደረሱብን ስለሆነ እነዚህን ሰዎች ማውጣት አለብን ብለው ጥያቄ ያቀረቡት 45 ተማሪዎች ከካውንስሉ በተውጣጡ ተማሪዎች የሚመሩ ናቸው። ከዚህ ውጭ የሆነው ተማሪ ግን የእምነት ጉዳይ ከሆነ ሁላችንንም ይመለከተናል። እናንተ ከካውንስሉ ተለይታችሁ መውጣታችሁ አግባብ አይደለም። ችግር ካለ ሁሉም ተማሪ አብሮ መታገል አለበት። ሂደቱ ትክክል አይደለም ብሏቸዋል።

ተማሪው ችግሩ የእምነት ችግር አይደለም። ክፍል ውስጥ የሚነሱ ጥያቄዎችን ይዛችሁ ወንድሞቻችንን የምትከሱ ከሆነ፤ እኛንም እየቀረፃችሁ ሰላማችንን የምትነሱን ከሆነ ጥያቄው አግበብ አይደለም ብለዋል። የቤተክርስቲያን ህጉ የሚፈቅደው አስተምህሮቱ እንዲመረመር ነው። ከተጠየቀ በኋላ ምናልባት ያ ሰው ተሳስቻለሁ ካለ ቀኖና ተሰጥቶት እንዲማር ይደረጋል። ነገር ግን ይህ ባልተደረገበት ሁኔታ አንድን ሰው መናፈቅ ነው፤ እንዲህ ነው እያሉ ማራገብ የቤተክርስቲያኑ ህግም አይፈቅደውም። ስለዚህ ተማሪው በዚህ መልኩ እየተቃወመው ነው።

ሰንደቅ፡- ካውንስል የተቋቋመው ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ነው። ይህ ችግር እዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ውይይት አላደረጋችሁም?

አቶ ኃ/ማርያም፡- እንደ ካውንስል የሰራናቸው ስራዎች አሉ። ከዚህ ቀደምም የሚነሱ የሃሳብ ልዩነቶች አሉ። በዘንድሮው አመት ሁለተኛ ሴምስተር ላይ የተነሳው ግን ትንሽ ለየት ያለ ነው። ጠዋት ጠዋት ፀሎት ቤት ኪዳን አድርሰን የአራተኛ አመት ደቀመዛሙርት ተመርጠው ትምህርተ ወንጌል በሚሰጡበት ጊዜ እንዲህ ነው አይደለም የሚሉ ሃሳቦች እየተንፀባረቁ ያስቸግሩናል። በዚህ ጊዜ ካውንስሉ ችግሮቹ ጊዜ ሊሰጣቸው አይገባም፤ከመስፋታቸው በፊት መወያየት አለብን ብለን ለአስተዳደር አቅርበናል። አስተዳደሩ ጉዳዩን እየሄደበት ባለበት ሁኔታ ነው ይህ ነገር የተፈጠረው። አስተዳደሩ መልስ ለመስጠት የራሱን ሂደት በመሄድ ላይ ነው። ካውንስሉም አስተዳደሩም የራሱን ሂደት እየሄደ ነበር።

ሰንደቅ፡- ክሱ አግባብነት የለውም እያሉ ነው እርስዎ?

አቶ ኃ/ማርያም፡- ጉዳዩ ለክስ የሚያበቃም አይደለም። ተማሪ ይጠይቃል። ተማሪው የነገረ መለኮት ተማሪ እንደመሆኑ መፅሐፍ ቅዱስን ያነባል፤ ይመራመራል። የቤተክርስቲያኒቱን ዶግማ እና ቀኖና ለይቶ ያውቃል። እነዚህ ነገሮች ላይም ጥያቄ ይጠይቃል። ተማሪው በሚጠይቅበት መምህሩም መልስ በሚሰጥበት ወቅት የረሳቸው ሃሳብ ያላቸው፤ ይሄ ልክ ነው፣ ይሄ ልክ አይደለም የሚሉ ሃሳቦች ተንፀባርቀዋል። የትኛውም ተቋም ላይ ደግሞ ምርምሮች አሉ። ተማሪ እንደተማሪነቱ መጠየቅ ካልቻለ፤ መመራመር ካልቻለ እና የተነገረውን ብቻ ይዞ ከወጣ ወረቀት ብቻ ይዞ ይወጣል እንጂ ብቁነት አይደለም። ተምሮ ተመራምሮ እና አውቆ ነው መውጣት ያለበት።

ቤተክርስቲያኒቱም የምትፈልገው ዶግማዋን እና ቀኖናዋን ጠንቅቀው የሚያውቁ ደቀ መዛሙርትን ነው። ለዚህ ደረጃ ለመድረስ ደግሞ መጠየቅ፣ መመራመር ያስፈልጋል። ይሄ ደግሞ ተቋማዊ መብት ነው። ኮሌጁ ሲመሰረት የትምህርት ነፃነቱን ይዞ ስለተመሰረተ ተማሪ ይህን መብቱን ተጠቅሞ ሊጠይቅ ይችላል። የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ግን ወደ ሌላ ሊቀየሩበት አይገቡም። የእውቀት ጥያቄ እንጂ የእምነት ጥያቄ አይደለም። ስለዚህ ችግር አለ የሚሉ አካላት ቆም ብለው በተረጋጋ መንፈስ የሚመለከታቸውን አካለት ማነጋገር ይችላሉ። መንፈሳዊ ቤት ውስጥ በስሜት የሚሆን ነገር የለም። ችግሩን ከማራገብ እና ከማዋከብ ይልቅ ችግሮችን ያዝ አድርጎ በመወያየት ነው መፍታት የሚቻለው።

ሰንደቅ፡- ይህ አሁን የተነሳው ችግር በተማሪዎችና በማህበረሰቡ ዘንድ አለመተማመንን ይፈጥራል የሚሉ አካላት አሉ። ይሄን እንዴት ያዩታል?

አቶ ኃ/ማርያም፡- እኛንም እያሳሰበን ያለው ትልቁ ነገር ይሄ ነው። ህዝባችን በሃይማኖት አይደራደርም። ይሄ የኢትዮጵያዊነት መገለጫችን ነው። ለእምነታችን እና ለሀገራችን ትልቅ ቦታ አለን። ይሄ እየታወቀ ግን 80 በመቶ የፕሮቴስታንት ተሀድሶ ተከታይ ነው ብሎ በህዝቡ ዘንድ ማሰራጨት ለተማሪው ትልቅ ጉዳት ነው። ወደየሀገር ስብከቶቻችን ስንሄድ ይሄንን መረጃ በመያዝ ማንም ሊቀበለን አይችልም። በጀት በጅታ የምታስተምራቸው ደቀመዛሙርት ካላገለገሏት ለቤተክርስቲያኒቱ ትልቅ ኪሳራ ነው። ደቀመዛሙርቱ ደግሞ በቤተክርስቲያኒቱ በጀት እየተማሩ ቆይተው ሊያገለግሏት ሲሰማሩ አላውቃችሁም ስትላቸው ለደቀመዛሙርቱ ትልክ ኪሳራ ነው። ስለዚህ ይህ ወጣት ደቀመዝሙር ስራ አጥ ብሎም ተስፋ የቆረጠ እና ቤተክርስቲንን የሚጠላ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ይህ ጉዳይ በደቀመዛሙርቱ ስነ ልቦና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው።

ሰንደቅ፡- አሁን በኮሌጁ ያለው የመማር ማስተማር ሂደት በምን ሁኔታ ላይ ነው?

አቶ ኃ/ማርያም፡- ለጊዜው ትምህርቱ ባይቆምም ስጋት የተሞላበት ነው። የተለያዩ መቀረፅ ድምፆች በየክፍሉ አሉ። የሚጠየቁ ጥያቄዎች በክስ ማስረጃነት ወደ አስተዳደር እየቀረቡ ነው ያሉት። ተማሪው ትምህርቱንም እየተከታተለ ነው፤ መምህሩም እያስተማረ ነው ለማለት ያስቸግራል። ባለፈው ሳምንት ትምህርት መቆም አለበት፤ ችግራችን ተፈቶ ሰላማችን ተመልሶ እና ተረጋግተን ወደ ትምህርት መግባት አለብን የሚል ሃሳብ ቀርቦ ነበር። ነገር ግን ካውንስሉ ነገሮች እንዲስተካከሉ ትምህርት መቋረጥ የለበትም። ትምህርታችንን እየተከታተልን ጉዳዩን እንከታተላለን በሚል ተማሪው ሃሳቡን ተቀብሎት ለጊዜው በትምህርት ላይ ይገኛል። ነገር ግን መጠየቅም ሆነ መጠየቅ የለም ዝም ብሎ መምህሩ ያስተላለፉትን መልዕክት ተቀብሎ የመሄድ ሁኔታ ብቻ ነው ያለው። ይህ ደግሞ መማር ማስተማር ሊባል አይችልም።

ሰንደቅ፡- የመማር ማስተማር ሂደቱ ሳይስተጓጎል ችግሩ እንዲፈታ ያደረጋችሁት ጥረትስ ምንድን ነው?

አቶ ኃ/ማርያም፡- እንደካውንስል ገለልተኛ አካላት ሰሞኑን ስብሰባ አድርገናል። በስብሰባችን የትምህርት ቤታችን ስም መመለስ አለበት፤ አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ ትምህርታችንን መቀጠል አንችልም፤ ለህይወታችንም ያሰጋናል የሚሉ ሃሳቦች ተንፀባርቀዋል። በማጠቃለያው ላይም ገለልተኛ ኮሚቴ አቋቁመናል።ይህ ኮሚቴ በመጀመሪያ የኮሌጁን ስም ማስመለስ እና ተማሪውን አረጋግቶ ጤናማ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ማድረግ ነው ኃላፊነቱ። በዚህም መሰረት ከኮሌጁ ዲን እና የበላይ ኃላፊ ጋር ችግሩ በአስቸኳይ እንዲፈታ ካልተፈታ ግን ትምህርት ልናቆም እንደምንችል ተወያይተናል። ትምህርቱ ያለበትን ሁኔታ በማስረዳትም አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጡን ጠይቀናል። በቅርቡም ፓትሪያሪኩ እና ቅዱስ ሲኖዶስም በጉዳዩ መካከል ተገኝተው ችግሩን እንዲፈቱልን ኮሚቴው ተወያይቶ በፅሁፍ ጥያቄ ሊያቀርብ ተዘጋጅቷል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1666 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 889 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us