የአውዳመት ገበያው ምን ይመስላል

Wednesday, 16 April 2014 13:44

 

ልክ እንደ ልማዱ የአውዳመትን መዳረስ ምክንያት አድርጎ ከተማው ደመቅመቅ ማለት ጀምሯል። በተለይ የትንሳኤ በዓል ለሁለት ወራት ገደማ በጉጉት የሚጠበቅ በዓል በመሆኑ ለእለቱ የሚደረገው ዝግጅት ገና ከሳምንታት በፊት ይጀመራል። የበረቱት ከሰሞነ-ህማማት ቀደም ብለው ዝግጅታቸውን ሲያጠናቅቁ ያልሞላላቸው ደግሞ ይህችን የህማማት ሳምንት ለቅመማ ቅመም ማዘጋጃ፣ ለጠላ ማቀነባበሪያ እና ለመሳሰሉት ዝግጅቶች ያውሏታል። በዚህ ሳምንት ታዲያ ገበያው እንዴት ዋለ የሚለውን መቃኘቱ አስፈላጊ ነው።

በሳምንቱ መጀመሪያ በእለተ ሰኞ በከተማዋ ታላቁ እና ዋናው ወደሆነው የፒያሳ አትክልት ተራ አመራን። ከወትሮው በተለየ ለአውዳመት የሚጠቅሙ በርካታ ሸቀጦች ወደገበያ እየገቡ መሆናቸውን ነው ማስተዋል የቻልነው። በተለይ የቀይ ሽንኩርት አቅርቦት አስደሳች ይመስላል። ዋጋው ግን ከአቅርቦቱ ጋር ብዙም የሚጣጣም አይደለም። አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት (የፈረንጅ) እንደደረቅነቱ እና እርጥበቱ ከ12 እስከ 14 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል። የሀበሻ የሚባለው እና ትናንሽ መጠን ያለው ሽንኩርት በኪሎ ከ20 እስከ 23 ብር ዋጋ አለው። ይህኛው የሽንኩርት አይነት ከፈረንጁ ሽንኩርት በተሻለ መልኩ የማስማት አቅም ስላለው ከፈረንጁ ሽንኩርት በላይ ዋጋ እንዳለው ተገልፆልናል።

እኛ እንደተመለከትነው በሾላ ገበያም ሆነ በአትክልት ተራ ያለው የቀይ ሽንኩት አቅርቦት ከፍተኛ ቢሆንም፣ ዋጋው ግን እንደአቅርቦቱ አይደለም። ሽንኩርት ሲሸምቱ ያገኘናቸው ሸማቾችም የገለፁልን ይህንኑ ነው። በፒያሳ አትክልት ተራ ሽንኩርት ሲገዙ ያገኘናቸው አንዲት እናትም እንዲህ ብለዋል። “እንደምታዩት ሁሉም ነጋዴዎች በቂ ሽንኩርት ይዘዋል። ዋጋቸው ግን አይቀመስም። የተመካከሩ ይመስል ሁሉም አንድ ዓይነት ዋጋ ነው የሚናገሩት” ብለዋል። እኛም ተዘዋውረን እንደተመለክትነው በርካታ ሸማቾች ነጋዴዎቹ በሚጠሩት ዋጋ ግራ በመጋባት ከመግዛት ይልቅ ያንንም ይህንንም መጠየቅን ይመርጣሉ።

ይህን የቀይ ሽንኩርት ዋጋ መናር አስመልክቶ ነጋዴዎችም አቅርቦቱ አስደሳች ቢሆንም ዋጋው ግን ከአምራቾቹ ከራሳቸው የጨመረ መሆኑን ይገልፃሉ። በሾላ ገበያ በአትክልት ንግድ ላይ ተሰማርተው ያገኘናቸው ወይዘሮ ሙሽሪትም የሚናገሩት ይሄንኔ ነው። “እኛ ብቻችንን በገዢው ላይ የፈጠርነው ችግር አይደለም። ገበሬው ራሱ ዋጋውን ከፍ አድርጎታል። ገበሬዎቹ ተመካክረው ነው የሚመጡት። ኩንታሉን እስከ አንድ ሺህ ብር ነው የምንገዛው። ገዝተን ደግሞ ትራንስፖርት አለብን። የእኛ ጉልበት አለ። ይሄንን አስበን ስንሸጥ ገዢው ደስተኛ አይደለም። እኛም እጃችን ላይ እንዳይበላሽ እያልን በዋናው የምንሸጥበት ጊዜ አለ” ሲሉ ያለውን ሁኔታ ያስረዳሉ።

የቀይ ሽንኩርት ዋጋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከታታይ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን ነው ነጋዴዎችም ሆነ ሸማቾች የሚናገሩት። ከዚህ በተጨማሪም በችርቻሮ ከትናንሽ መደብሮች ከሚሸጠው ይልቅ የአትልክት ተራዎቹ ዋጋ የሚሻል መሆኑን የሚገልፁት ሸማቾች፤ ነገር ግን በአትክልት ተራ ከአምስት ኪሎ በታች የማይሸጥ በመሆኑ ፊታቸውን ወደ ትናንሽ መደብሮች እንዲያዞሩ እና ለተጨማሪ ዋጋም እንዲዳረጉ እንዳደረጋቸው ገልጸውልናል።

ከዚህ ከሽንኩርት ዋጋ ሳንወጣ ሌላ የተመለከትነው የነጭ ሽንኩርት ዋጋ ነው። ጥሩ ጥሩ ራስ ያለው ነጭ ሽንኩርት በፒያሳ አትክልት ተራ ከ40 እስከ 45 ብር በኪሎ የሚሸጥ ሲሆን፣ በሾላ ገበያ ደግሞ ከ42 እስከ 45 ብር በኪሎ በመሸጥ ላይ ይገኛል። አንድ ኪሎ ድፍን ኮረሪማ ከ95 እስከ 110 ብር እየተሸጠ ሲሆን፤ የተፈለፈለው ደግሞ ከ200 ብር እስከ 220 ብር በኪሎ በመሸጥ ላይ ነው። ዝንጅብል በኪሎ ከ25 እስከ 27 ብር ይሸጣል። ወትሮውንም ዋጋው እያሻቀበ እንደመጣ የሚገለፀው ቲማቲም ከሰሞኑ መጠነኛ ቅናሽ በማሳየት ከ9 ብር እስከ 12 ብር ዋጋ አለው።

ሌላው በተለይ ለትንሳኤ በዓል አስፈላጊ ከሆነ ነገሮች ውስጥ ዋናው የባቄላ ክክ ነው። በሰሞኑን ህማማት የፀሎት ሐሙስ እለት ለሚዘጋጀው ጉልባን የሚያገለግለው የባቄላ ክክ በኪሎ ከ12 እስከ 14 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል።

ወደሌሎች ማጣፈጫዎች ገበያ ስናቀናም ዋጋቸውን እንደሚከተለው ቃኝተናል። በመርካቶ ቅቤ በረንዳ አንድ ኪሎ የሸኖ ለጋ ቅቤ ከ180 እስክ 190 ብር በመሸጥ ላይ ሲሆን፤ በመካከለኛ የመብሰል ደረጃ ላይ የሚገኝ አንድ ኪሎ ቅቤ ከ170 እስከ 180 ብር ዋጋ አለው። ብዙም ፈላጊ እንደሌለው የሚገለፀው በሳል ቅቤ ደግሞ በ160 እስከ 170 ብር በኪሎ በመሸጥ ላይ ይገኛል። አንድ በሳል የወለጋ ቅቤ በኪሎ ከ160 ብር እስከ 170 ብር ዋጋ ሲኖረው ለጋው ደግሞ በ180 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል። ትኩስ አይብ በኪሎ ከ25 እስከ 27 ብር ዋጋ ሲኖረው፤ ትንሽ ቆየት ያለው ደግሞ 23 እስከ 25 ብር በኪሎ ይሸጣል።

የዘይት ዋጋን ስንመለከት ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውጭ ሀገር ምርት የሆኑ በርታ የዘይት ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ በመግባታቸው በሀገር ውስጥ ዘይት ዋጋ ላይ ቅናሽ እንዲደረግ ግፊት ያደረገ ይመስላል። በዚህም መሰረት ያልታሸገው የኑግ ዘይት ከ48 እስከ 50 ብር በሊትር የሚሸጥ ሲሆን የታሸገው ከ50 ብር እስከ 53 ብር በሊትር ይሸጣል። ባለሶስት ሊትሩም እስከ 65 ብር ዋጋ አለው። ከውጭ ወደ ሀገርውስጥ የሚገባ የአኩሪ አተር ዘይት በሊትር ከ58 እስከ 60 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል። አንድ ሊትር የበቆሎ ዘይትም ከ65 እስከ 68 ብር ዋጋ አለው።

ወደ አትክልት ተራዎች ጎራ ማለታችን ካልቀረ በአለፉት ሁለት ወራት ከፍተኛ ተፈላጊነት የነበራቸው አንዳንድ አትክልቶችን ዋጋ መቃኘት ችለናል። ፎሰሊያ በኪሎ ከ15 እስከ 18 ብር፤ ጥቅል ጎመን ከ5 ብር እስከ 7 ብር በኪሎ፤ ድንች ከ6 እስከ 7 ብር በኪሎ እንዲሁም ካሮት ከ18 እስከ 22 ብር በኪሎ በመሸጥ ላይ ይገኛል። ቃሪያ ከ25 እስከ 28 ብር በኪሎ ሲሸጥ ቀይ ስር በኪሎ ከ20 ብር ጀምሮ በመሸጥ ላይ ይገኛል። ጎመን እንደየዝርያው በአስር በአምስት ብር ሲሸጥ በኪሎ ከ12 ብር እስከ 15 ብር ዋጋ አለው።

ወደ እንቁላል ገበያ ስናልፍ ደግሞ እስከ ዛሬ ባለው ዋጋ የአንዱ የሀበሻ እንቁላል ዋጋ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በ2ብር ከ70 ሳንቲም የሚሸጥ ሲሆን፣ አንዳንድ ቦታዎች ደግሞ በ2ብር ከ80 ሳንቲም ይሸጣል። የፈረንጁ ደግሞ ከ2 ብር ከ80 ሳንቲም ጀምሮ እስከ 3ብር ዋጋ አለው። የእንቁላል ዋጋ በፆሙ ውስጥም ቅናሽ እንዳላሳየ ነው የተገለፀው። ባለፉት የፆም ወራት ውስጥም አንድ እንቁላል ሁለት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ጀምሮ እስከ 2 ብር ከ60 ሳንቲም ሲሸጥ እንደከረመ የገለፁልን አንዲት እናት፤ በአሉ ሲደርስ ያለው ዋጋም ይህን ያህል ጭማሪ እያሳየ እንዳልሆነ ገልፀዋል። ቀድሞ በፆም ወራት አንድ እንቁላል እስከ 1 ብር ከሃምሳ ሳንቲም ድረስ ይረክስ እንደነበረ የገለፁት እኚህ እናት የዘንድሮ የፆም ጊዜ ግን ከፍስኩ ብዙም ያልተለየ መሆኑን ጠቅሰዋል።

      የዶሮ ገበያን ስንመለከት ደግሞ ከአዲስ አበባ ዙሪያ ከተማዎች ዶሮ ይዘው ወደ ከተማዋ በሚገቡ ግለሰቦች ዘንድ አንድ ወንድ ዶሮ ከ150 እስከ 180 ብር ዋጋ አለው፤ አንዲት ሴት ዶሮ ደግሞ ከ120 እስከ 140 ብር ዋጋ አላት። በቅርጫት አድርገው በሚሸጡ አትራፊዎች ዘንድ ወንድ ዶሮ ከ160 እስከ 180 ብር ዋጋ አለው። ሙሉ ለሙሉ የፈረንጅ የሆነ እና ትልቁ ዶሮ እስከ 190 ብር ዋጋ ያለው ሲሆን፤ የሀበሻ የሚባለው ዶሮ ደግሞ እስከ 170 ብር የሚደርስ ዋጋ አለው።

በዓሉን የተዘጋጀ በርበሬ እና ሚጥሚጣ ገዝተው ለማሳለፍ ለሚፈልጉም በገበያ ላይ ያለውን የዋጋ ዝርዝር እናሳውቅ። አንድ ኪሎ የተዘጋጀ በርበሬ ከ75 እስከ 80 ብር ዋጋ ሲኖረው፤ ግማሽ ከ38 እስከ 40 ብር ዋጋ አለው። ሩብ ኪሎ ለሚፈልጉ ደግሞ በ20 ብር ይሸጣል። አንድ ኪሎ የተዘጋጀ ሚጥሚጣም ከ40 እስከ 45 ብር ዋጋ አለው።

የዘንድሮውን የትንሳኤ በዓል የሸቀጦች ዋጋ ባለፈው አመት በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነፃፀር በቀይ ሽንኩርት እና በቅቤ ዋጋ ላይ መጠነኛ ጭማሪ ተስተውሏል። በመሆኑም በቀይ ሽንኩርት ዋጋ ላይ ከ1ብር ከ50 ሳንቲም እስከ 2 ብር ጭማሪ የተስተዋለ ሲሆን፤ በቅቤ ዋጋ ላይም ከ5 ብር እስከ 10 ብር የዋጋ ጭማሪ ተስተውሏል። በኮረሪማ ዋጋ ላይም ከ3 እስከ 5 ብር ጭማሪ መስተዋሉን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

     በአንጻሩ ደግሞ በነጭ ሽንኩርት ዋጋ ላይ ከ20 እስከ 25 ብር የዋጋ ቅናሽ ተስተውሏል። በዘይት ምርት ዋጋ ላይም ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር ከ2 እስከ 8 ብር ቅናሽ ማሳየቱ ተስተውሏል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1718 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 783 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us