ሆኖ መገኘት

Wednesday, 23 April 2014 11:59

 

ወይዘሮ ሰብለ ኃይለልዑል የኢንተርናሽናል ፈንድ ፎር አፍሪካ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ናቸው። ተወልደው ያደጉት እዚህ አዲስ አበባ ሲሆን፤ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁትም በናዝሬት ስኩል ነው። ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላም ወደ አሜሪካ በማምራት በጤና ዘርፍ በኬንታኪ ዩኒቨርስቲ፣ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሜሪላንድ እና ፊሎሺፕ እንዲሁም ጆንሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ አጠናቀዋል። በአሁኑ ወቅትም በኢንተርናሽናል ፈንድ ፎር አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሲሆኑ እንዲሁም በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ የአይቲ ቴክኖሎጂ ኩባንያቸውንም ያስተዳድራሉ።

ኢንተርናሽናል ፈንድ ፎር አፍሪካ የተቋቋመው በወይዘሮ ሰብለ እና በአክስታቸው ልጅ ሲሆን የሚተዳደረውም ከመስራቾቹ በሚገኝ ገንዘብ ነው። ይህ ድርጅት ከሌሎች የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚለዩትም ዋና እንቅስቃሴውን የሚያደርገው በገጠር አካባቢ ባለው ህብረተሰብ ላይ መሆኑ ነው። ይህን ጉዳይም ወይዘሮ ሰብለ እንዲህ ይገልፁታል። “ብዙ ጊዜ የምንሰራቸው ስራዎች በጨቅላ ህፃናት ላይ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በገጠር አካባቢ በአይነስውርነት፣ በትራኮማ እንዲሁም ሞራ መገፈፍ በሚችሉ ከአይን ጋር በተያያዙ የጤና ጉዳዮች ላይ እንሰራለን” ያሉን ወይዘሮ ሰብለ፤ ከጤናው ባሻገርም በደሃ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ምሳ የማብላት ስራ ይሰራሉ።

በአይነስውራን ዙሪያ በሚሰሩት ስራ በተለይ በሰሜን ሸዋ አካባቢ በርካታ በአይናቸው ላይ በደረሰባቸው ችግር ምክንያት ቤት ውስጥ የቀሩ ሰዎች ሞራ ተገፎላቸው ብርሃናቸውን እንዲያገኙ ማድረጋቸውን ነው ወይዘሮ ሰብለ የገለፁልን። እንደ ወይዘሮ ሰብለ ገለፃ ከሆነ በእንቅስቃሴያቸው ወቅት እንደተገነዘቡት በኢትዮጵያ ውስጥ ወደህክምና ተቋም ሄደው ታክመው መዳን የሚችሉ በርካቶች በቤታቸው ውስጥ ከበሽታቸው ጋር ሲኖሩ መመልከታቸውን ገልፀውልናል።

በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ ለረጅም ዓመታት በጤና አጠባበቅ ዘርፍ በስራ ላይ የነበሩት ወይዘሮ ሰብለ፤ ይኖሩበት የነበረው ማህበረሰብ ባህል እርሳቸውም ወደዚህ ኃላፊነት እንዲገቡ ያደረጋቸው ይመስላል። “በሌላ ሀገር አንድ ሰው ተምሮ ሲጨርስ ለማህበረሰቡ አንድ ነገር ማድረግ አለበት። ያን ነገር ማንም ነገሮት አይደለም የሚያደርገው። የሁሉም ሰው ኃላፊነት እንደሆነ እያንዳንዱ ሰው ያውቃል” የሚሉት ወይዘሮ ሰብለ እርሳቸውም ወደዚህ ስራ እንዲገቡ የተፈጠረውን አጋጣሚ ችላ ብለው ማለፍ አልፈለጉም።

“የአክስቴ ልጅ ዶክተር ነው። እንደ አጋጣሚ ለቀዶ ህክምና ኢትዮጵያ ሲመጣ በርካታ ነፍሰጡር ሴቶች በተወሳሰበ ችግር ምክንያት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲቆዩ፤ በእግራቸው ወዲያ ወዲህ ሲሉ እና ሲቸገሩ ሲያይ ደውሎ በጨቅላ ህጻናት ላይ እንድንሰራ ጠየቀኝ። እኔም እንዲያውም ለዚህ ችግር ምክንያት በሆነው ነገር ላይ ብንሰራ ይሻላል የሚል ኀሳብ በማቅረብ ተሰማምተን ስራውን ጀመርን” ይላሉ ወይዘሮ ሰብለ። በዚህ መልኩ የተጠነሰሰው እንቅስቃሴ ሁለቱም በሚያውቋቸው አማካይነት ባሰባሰቧቸው መሳሪያዎች ስራቸውን ጀመሩ።

እነወይዘሮ ሰብለ ስራቸውን የጀመሩት ከምኒሊክ ሆስፒታል ጋር ሲሆን፤ እያደር ያዩት ለውጥ አበረታች በመሆኑ ወደሌሎችም ማስፋፋትን ጀመሩ። “እኛ ስራውን ስንጀምር በእርግዝና ወቅት ችግር ያለባቸው እናቶች ቀድሞ ልጁ ይሞታል ብለው ጥለው ይሄዱ የነበሩት ልጃቸውን መጠበቅ ጀመሩ። በዚህም ሳቢያ የጨቅላ ህጻናት ሞት ከ15 በመቶ ወደ 5 በመቶ ወረደ። ስለዚህ ይህንኑ አገልግሎታችንን በጋንዲ እና በየካቲት 12 ሆስፒታሎችም ማስፋፋት ጀመርን” የሚሉት ወይዘሮ ሰብለ፤ ይህን የጨቅላ ህፃናት ሞት ለማስቀረት አስቀድሞ ክትትል ማድረጉ ዋናው መፍትሄ በመሆኑ ትምህርት በመስጠት ላይ እንዳተኮሩም ገልፀውልናል።

ዋና አላማቸው በገጠር አካባቢ ለመስራት ስለነበረም ወደተመረጡ የገጠር አካባቢዎች የጤና ትምህርት ዘመቻን ጀመሩ። ነገር ግን ለበሽተኞች መድሃኒት በመስጠት ብቻ ችግሩን መቅረፍ እንደማይቻል መረዳታቸውን ወይዘሮ ሰብለ ይገልፃሉ። “ያሰው ታክሞ ተመልሶ እዚያው ቤት ውስጥ ከኖረ፣ ያንኑ ምግብ ከበላ ሊድን አይችልም” የሚሉት ወይዘሮ ሰብለ፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ የህብረተሰቡን የኢኮኖሚ አቅም መገንባትን እንደ አማራጭ እንደወሰዱት ገልፀውልናል። በመሆኑም ህብረተሰቡ ንፅህናውን እንዲጠብቅ፤ በዓመት አንዴ የሚያመርተው አመቱን ሙሉ እንዲያመርት እንዲሁም ኑሮን ቀለል ባለ መልኩ እንዲመራ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ሰርተዋል። ይህን ሁሉ ስራ ለመስራት ታዲያ ብዙ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ እንቀስቃሴውን ፈታኝ ቢያደርገውም መስራቾቹ አማራጮችን በመጠቀም ላይ ናቸው። ወይዘሮ ሰብለ በአሜሪካ ይንቀሳቀስ የነበረውን የአይቲ ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ ለማምጣት ሲወስኑ የአክስታቸው ልጅ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህን የጤና ችግር ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍል በህክምናም በኢኮኖሚም ለማገዝ ክሊኒክ ለመክፈት በዝግጅት ላይ ናቸው።

ህክምናው ዘርፍ ድርጅቱ ለየካቲት ሆስፒታል ባስገባው መሳሪያ በወር ከ600 እስከ አንድ ሺ ሰዎች ህክምናውን እንዲያገኙ ተደርጓል። ይህ የታሰበ ክሊኒክ ስራውን ሲጀምር እና ድርጅቱም በቂ የሆነ ገቢ ሲኖረው ደግሞ የተጠቃሚዎች ቁጥር ከዚህ በላይ ይሆናል የሚል ተስፋ ብቻም ሳይሆን ችግሩን ሙሉ ለሙሉ የመቅረፍ እቅድ አላቸው።

ሌላው የዚህ ድርጅት እንቅስቃሴ በትምህርት ቤቶች እየተንቀሳቀሰ ደሃ ህጻናትን ምሳ ማብላት ነው። በርካታ ህፃናት ከረሀብ የተነሳ በክፍል ውስጥ ራሳቸውን ስተው እንደሚወድቁ፣ በርካቶች በጎዳና እና በቪዲዮ ቤት በር ላይ እንደሚያድሩ የገለፁት ወይዘሮ ሰብለ አላማቸውም ይህን ችግር ለመቅረፍ ነው። እስከ አሁን ድረስም 150 ተማሪዎን ምሳ እያበሉ ይገኛሉ። የእነዚህ ተማሪዎች እርዳታ እንዳይቋረጥም በቋሚነት ገቢ የሚያስገኙ እንደ ዳቦ ቤት እና ወፍጮ ቤት ያሉ የገቢ ማስገኛ አማራጮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።

በእንስሳት ጥበቃ ላይ የሚደርገው እንቅስቃሴም ሌላው የድርጅቱ ተግባር ነው። በዚህ እንቅስቃሴያቸውም እንስሳትን ያለ አግባብ ከመግደል ይልቅ ጤናማ ሆነው ሊኖሩ የሚችሉበትን ሁኔታ የመፍጠር ስራ ይሰራሉ፡ ይህ እንቅሰቃሴ ደግሞ ቢቻል እንስሳትን መብላት ቢቆም የሚመከር ነው። “እንስሳትን የሚበሉትን አትብሉ ማለት አንችልም። ነገር ግን ለመኖር የግድ እንስሳትን መብላት አያስፈልግም” የሚሉት ወይዘሮ ሰብለ፤ ይህንንም እየሰራንበት እንደሆነ ገልፀውልናል። በአብዛኛው በተለይ ውሾችን ከመግደል ይልቅ አኮላሽቶ እርባታቸውን በማስቆም ጤነኛ ሆነው እንዲኖሩ ያደርጋሉ። ከዚህ ቀደም ከማዘጋጃ ቤት ጋር በመተባበር 800 ያህል ውሾችን በዚህ መልኩ ከሞት ማዳን መቻላቸውንም ገልጸውልናል።

“የኔ ኃላፊነት ውጪ ያለውን አምጥቼ ሀገሬ ላይ መተግበር ሳይሆን፤ አሁን ባለንበት ሁኔታ የጤናውን ሁኔታ በምን መልኩ ማሻሻል አለብን የሚለውን መመለስ ነው” የሚሉት ወይዘሮ ሰብለ፤ በአንድ ማህበረሰብ ጋር ለመስራት “እኔ የምፈልገውን አድርግ” ከማለት ይልቅ ስለዚያ ጉዳይ ህብረተሰቡ ያለውን አመለካከት እና አስተሳሰብ መገንዘብ ይቀድማል የሚል አስተሳሰብ አላቸው።

ለዚህም ይመስላል ለሌላው አርአያ ሆኖ መገኘትን የመረጡት። ለአብነት ያህልም ስለእንስሳት ሲያስተምሩ ራሳቸው እንስሳት በመንከባከብ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ወይዘሮ ሰብለ ከአለፉት 15 ዓመታት ጀምሮ እንስሳትን አይበሉም። “ድሮውንም እኔና የእንስሳት ተዋፅኦ ብዙም አንዋደድም ነበር። ለእንስሳቱ አስቤ ሳይሆን ብዙም የስጋ በላተኛ አልነበርኩም” የሚሉት ወይዘሮ ሰብለ ሀኪም ቤት ሲሄዱ ለጤንነታቸው የእንስሳት ተዋፅኦ እንዲመገቡ ተነግሯቸው ለተወሰነ ጊዜ መመገብ ጀምረው የነበረ ቢሆንም ተመልሰው ግን አትክልት መመገብን መርጠዋል። ለዚህም የአክስታቸውን ልጅ እንደ አርአያ ያነሳሉ። “የአክስቴ ልጅ የውሻዬን የልብ ትርታ ሰማዋለሁ፤ እነሱም ልክ እንደኛ ስለሆኑ ከዛሬ ጀምሮ እንስሳት አልበላም” ሲለኝ እኔም በዚያው ዳግም ላለመብላት ወሰንኩኝ” ይላሉ።

ወይዘሮ ሰብለ እንስሳትን አለመመገብ ብቻም ሳይሆን ወድቀው ሲያገኙ ሰብስበው ያስጠልላሉ። በአሁኑ ወቅት በርካታ ሴት ውሾችን በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ያስጠለሉ ሲሆን፤ ለወደፊትም የእንስሳት መጠለያ የመክፈት ሃሳብ እንዳላቸው ገልፀውልናል።

“አሜሪካ ሀገር የሆስፒታል ኃላፊ ሆኜ ነበር የምሰራው። በደሞዝ ከሆነ ጥሩ ደሞዝ እየተከፈለኝ መኖር እችል ነበር። ነገር ግን ወደሀገሬ ገብቼ የበኩሌን ማድረግ ስላለብኝ ነው የመጣሁት” የሚሉት ወይዘሮ ሰብለ፤ በሌሎች ሀገራት እያንዳንዱ ዜጋ ለወጣበት ህብረተሰብ የየራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ይገልፃሉ። በእኛ ሀገር ያለው አመለካከት ግን የተለየ ነው ባይ ናቸው። “እኔ እንደተገነዘብኩት ከሆነ እዚህ ሀገር አንድ ሰው ጥሩ ህይወት ከኖረ የበለጠ ነገር እየፈለገ ይሄዳል እንጂ ሌላውን አንስቶ ለጥሩ ደረጃ ላድርስ አይልም። በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው እንዲህ የሚያደርጉት” የሚሉት ወይዘሮ ሰብለ፤ ይህ ደግሞ ከመጣንበት ባህል ጋር የሚያያዝ መሆኑንም ይገልፃሉ።

በተለይ እንስሳትን መንከባከብ በህብረተሰባችን ዘንድ እምብዛም የተለመደ አለመሆኑን ወይዘሮ ሰብለም ያምኑበታል። ነገር ግን ለህብረተሰቡ ከማሳየት ይልቅ ማስተማር የበለጠ ውጤታማ የሚያደር መሆኑን ገልፀዋል። “የወደቀ ሰው እያለ እንዴት የወደቀ እንስሳ ታነሳላችሁ ሊባል ይችላል። ይሄ የመፈታተን ጉዳይ አይደለም። አንዱ የወደቀ ሰው ሲያነሳ ሌላው ደግሞ የወደቀ እንስሳ ቢያነሳ ምንም ችግር የለውም” ይላሉ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1661 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 679 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us