በሴቶች እና ህፃናት ላይ ያነጣጠረው ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች

Thursday, 03 October 2013 20:25

 

በሀገራችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አሉ። እነዚህ ድርጊቶች ታዲያ በሚያስገርም ሁኔታ በአሁኑ ጊዜም እየተተገበሩ ናቸው። የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒሰቴር በቅርቡ ባካሄደው ጥናት በሀገራችን ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ናቸው የተባሉትን ይፋ አድርጓል። አንድ ድርጊት ጐጂ ልማዳዊ ድርጊት የሚባለው በዘልማድ የሚደረግ ሆኖ፤ ድርጊቱም በሰው ልጅ ላይ አካላዊ፣ ስነ-ልቦናዊ፣ ጾታዊ ኢኮኖሚያዊ እና፣ ማኅበራዊ ተፅዕኖዎችን የሚፈጥር ድርጊት ሲሆን ነው።

የኢትዮጵያ ባህላዊ ድርጊቶች አስወጋጅ ኮሚቴ ይፋ እንዳደረገው በሀገራችን ከአንድ መቶ አርባ በላይ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አሉ። እነዚህ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችም ሴቶች ተኮር፣ ህፃናት ተኮር እና ሁለቱንም ጾታዎች ተኮር ተብለው ተለይተዋል። ከእነዚህ ድርጊቶችም ዋና ዋናዎቹ የሴት ልጅ ግርዛት፣ እንጥል መቁረጥ፣ የወተት ጥርስን መንቀል፣ ያለ እድሜ ጋብቻ እና የጠለፋ ጋብቻ ይገኙበታል። በኢትዮጵያ እነዚህ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሴቶች እና ህፃናት ጫንቃ ላይ የወደቁ መሆናቸውን ጥናቱ ያመለክታል። ይህም የሆነበት ምክንያት ሴቶች እና ህፃናት በማኅበራዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊው ጥገኛ በመሆናቸው ነው ይላል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዳስቀመጠውም እነዚህ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ ገፅታ አላቸው። በዚህም መሠረት በሴት ልጅ ግርዛት ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የአፋር ክልል ነው። በዚህ ክልል 87 በመቶ ድርጊቱ ይፈፀማል። ከአፋር ክልል በመቀጠል ሶማሌ ክልል የሚገኝ ሲሆን፤ ይኸውም 70.7 የመቶ ነው። እንዲሁም የሐረሪ ክልል 67.2 በመቶ፣ የአማራ ክልል 62.9 በመቶ ሲሆን በትግራይ ክልል ደግሞ 21.2 በመቶ መሆኑን ያመለክታል። በክልል ደረጃ ያለው ንፅፅር እንደሚያመለክተውም ከፍተኛውን ደረጃ የያዘው አፋር ክልል ሲሆን ዝቅተኛው ደግሞ በጋምቤላ ይገኛል።

በ2011 (እ.ኤ.አ.) የተደረገው ዌልፈር ምኒተሪንግ ሰርቬይ ሪፖርት እንደሚያመለከተው እድሜያቸው እስከ 14 ዓመት ከሆናቸው ኢትዮጵያውያን ሴት ህፃናት መካከል 23 በመቶዎቹ ተገርዘዋል። ከግርዛቱ ውስጥም 24 በመቶው በገጠር አካባቢ የሚፈፀም ሲሆን 15 በመቶው ደግሞ በከተሞች የሚፈፀም ነው።

የህፃናት ጋብቻ ወይም ያለ እድሜ ጋብቻን በተመለከተ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘው የአማራ ክልል ነው። በዚህም መሠረት ክልሉ 44.8 በመቶ ሲይዝ፣ ትግራይ 34.1 በመቶ፣ ቤንሻንጉል 31.9 በመቶ እንዲሁም አዲስ አበባ 32.3 በመቶ ይከተላሉ። ይህ ያለ እድሜ ጋብቻ በሰለጠኑት እና በከተሞች አካባቢም ጭምር ይተገበራል።

ጠለፋን በተመለከተም የጥናቱ ውጤት የሚያመለክተው በደቡብ ክልል እና ኦሮሚያ ክልሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ተጠልፈው ጋብቻ እንደሚፈፅሙ ነው። በዚህም መሠረት በደቡብ ክልል 17.5 በመቶ፣ ኦሮሚያ ክልል ደግሞ 13.2 በመቶ ይይዛሉ። በተጨማሪም ጋምቤላ 11.5 በመቶ፣ ትግራይ 5.9 በመቶ ሲይዙ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አማራ ክልል ደግሞ 5.5 በመቶ ነው።

ምንም እንኳን እነዚህ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተመሣሣይነት ቢኖራቸውም አንዱ ክልል ውስጥ በተደጋጋሚ የሚፈፀሙ ድርጊቶች ሌላው ክልል ውስጥ ግን እምብዛም ሆነው ተገኝተዋል። ለአብነት ያህልም በአማራ ክልል ያለ እድሜ ጋብቻ፣ የህፃናት ጋብቻ፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ የወተት ጥርስ መንቀል፣ እንዲሁም እንጥል መቁረጥ፣ በስፋት የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው። በሶማሌ ክልል ደግሞ የህፃናት ጋብቻ፣ እና የውርስ ጋብቻ ይጠቀሳሉ። በኦሮሚያ ክልል በስፋት የሚከናወኑት ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የህፃናት ጋብቻ፣ ጠለፋ እና ከፍተኛ ጥሎሽ ናቸው። በአፋር ክልልም እንዲሁ “አብሱማ” የተባለው በአክስት ልጆች መካከል የሚደረግ ጋብቻ፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ የወተት ጥርስ መንቀል፣ እንጥል መቁረጥ፣ የህፃናት እና ያለ እድሜ ጋብቻ፣ የውርስ ጋብቻ እንዲሁም የግዳጅ ጋብቻ ይገኙበታል።

በሀገራችን የሚከናወኑ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እነዚህ ብቻ አይደሉም። የኢትዮጵያ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አስወጋጅ ማኅበር በ2008 (እ.ኤ.አ.) ይፋ ባደረገው ጥናት እንደገለፀው፤ በሀገራችን ሰዎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የሚፈፅሟቸው በርካታ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አሉ። ጋብቻን በተመለከተ ከጠለፋ በተጨማሪ የልዋጭ ጋበቻ፣ የውርስ ጋብቻ እና የግዳጅ ጋብቻ ይጠቀሳሉ። ከስነ ተዋልዶ ጋር በተያያዘም በእርግዝና ወቅት ሆድን ማሸት፣ ሴቷን በኃይል ማንሳት እና ማነቃነቅ፣ በወር አበባ ወቅት ሴቶችን ከማኅበረሰቡ ማግለል እንዲሁም በጫካ ውስጥ እንዲወልዱ ማስገደድ ይገኙበታል። አመጋገብን በተመለከተም ሴቶች እንዲበሏቸው የማይፈቀዱ የምግብ አይነቶች እንዳሉ በመጥቀስ ሴቶችን መከልከሉ ከጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተርታ ይመደባል።

እነዚህ የተጠቀሱት ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንደየአካባቢው የየራሳቸው ምክንያት ቢኖራቸውም፤ በአጠቃላይ ግን ለሁሉም እንደምክንያት የሚነሱ ነጥቦች አሉ። እነዚህ ምክንያቶች ጥልቅ ምክንያት፣ አማካይ ምክንያት እና ፈጣን ምክንያት ተብለው ይከፈላሉ። ከአማካይ ምክንያቶቹም ሴቶች እና ህፃናት በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸው የኢኮኖሚ ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ ለዚህ ችግር ተጋላጭ እንዳደረጋቸው ተረጋግጧል።

ሌላው እንደ ምክንያት የተነሳው ነገር የትምህርት እና ስልጠና እጥረት ነው። ይህ ደግሞ ሁለት ዓይነት ተፅዕኖዎች አሉት። በመጀመሪያ ደረጃ ሴቶች እና ህፃናት የተሻለ ህይወት ለመምራት የሚያስችላቸው ትምህርት እና ስልጠና ስለማይኖራቸው የሚፈፀምባቸውን ድርጊት ለመቀበል ይገደዳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆች እና በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አባቶች ለእነዚህ ድርጊቶች ያላቸው አመለካከት ነው። ይኸውም እነዚህ አባቶች የተሻለ ትምህረት ስለሌላቸው ድርጊቱን እንደ ትክክለኛ ድርጊት ለመቁጠር ይተገበር ዘንድ ከፍተኛውን ሚና ይጫወታሉ።

የጤና አገልግሎት በስፋት አለመዳረስ እና ያለው ጥራት አስተማማኝ አለመሆንም ለእነዚህ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መስፋፋት ሌላው ምክንያት ነው። ሰዎች የሚፈልጓቸውን ከወሊድ በፊት እና በኋላ የሚደረጉ የጤና እንክብካቤዎች፣ ጥራቱን የጠበቀ ውርጃ እና የመሳሰሉትን የምክር አገልግሎቶች የሚሰጡ የጤና ተቋማት በየአካባቢያቸው ባለማግኘታቸው በእነዚህ ድርጊቶች እንደሚጠቀሙ እና ለጉዳትም እንደሚዳረጉ ጥናቱ አመልክቷል። በዚህም ምክንያት ሰዎች የራሳቸውን እውቀት ተጠቅመው እዚያው በአካባቢው ባህላዊ ድርጊቶችን ይፈፅማሉ።

ሌላው እንደምክንያት የሚነሳው ሃይማኖት እና ባህል ነው። በሀገራችን እነዚህን ጐጂ ልማዳፂዋ ድርጊቶች አስመልክቶ ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ አመለካከት እንደሌለ ነው ጥናቱ የገለፀው። አንዳንዶቹ ድርጊቶች ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ሲሆን፤ ሌሎቹ ደግሞ የአካባቢው ባህል ስለሆነ ብቻ ይተገበራሉ። ለአብነት ያህልም የህፃናት ጋብቻ የሚፈፀመው ከጋብቻ በፊት የሚፈፀም ጾታዊ ግንኙነትን እና እርግዝናን ለመከላከል በማሰብ ነው። አክሱማዊ አክሱማ ተብሎ የሚጠራው እና በአፋር ክልል የሚደረገው የጋብቻ አይነት ደግሞ የቤተሰብን ሀብት ለሌላ ሰው አሳልፎ ላለመስጠት የሚደረግ ነው።

የእነዚህን ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጉዳት ስንመለከትም የአብዛኞቹን ችግሮች ገፈት ቀማሾች ሴቶች እና ህፃናት ናቸው። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህልም እነዚህ ድርጊቶች ለከፍተኛ ደም መፍሰስ፣ ለኢንፌክሽ፣ በወሊድ ወቅት ለሚከሰት ችግር፣ ለፊስቱላ እና ለኤች አይ ቪ ቫይረስ ያለውን ተጋላጭነት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል። እነዚህ ድርጊቶች በሚፈፅሙበት አካባቢ የማኖሩ ሴቶች የወሊድ መቆጣጠሪያዎች መጠቀምን እንደነውር ስለሚቆጥሩት በርካታ ቁጥር ያላቸው ልጆችን በመውለድ በወሊድ ወቅት ለሚከሰት ሞት ይጋለጣሉ።

ሌላው በእነዚህ ድርጊቶች የሚደርሰው ተፅዕኖ የስነ-ልቦና እና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ነው። እነዚህ ተፅዕኖዎችም ጭንቀት፣ ደስታን ማጣት፣ ከቤተሰብ ጋር የሚኖረው ግንኙነት ጤናማ ያለመሆን፣ በማኅበረሰቡ መገለል ይገኙበታል። በተጨማሪም ህፃናት ጋብቻ በሚፈፅሙበት ወቅት ትምህርታቸውን በማቋረጣቸው፣ በልጅነታቸው በማርገዛቸው እና ብዙ ልጆችን በመውለዳቸው የተሻለ ህይወት ለመምራት የሚኖራቸው ተስፋ እንዲመነምን ያደርጋቸዋል። በተጨማሪም ለእነዚህ ድርጊቶች የተጋለጡ ሴቶች ስራ ሰርተው የራሳቸውን ገቢ ከማግኘት ይልቅ በቤት ውስጥ ስራ ስለሚጠመዱ በሌላ ሰው ላይ ያላቸው ጥገኝነት ያሰፋዋል። ይህ ተፅዕኖ ደግሞ በአንድ ትውልድ የማያበቃ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ነው።

እነዚህን ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ እና ሴቶች እና ህፃናትን ለመታደግ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። በሀገር አቀፍ ደረጃ ኮሚቴ ተቋቁሞ ግንዛቤ የማስጨበጫ እና ጉዳቱን የሚያመለክቱ ትምህርቶችን የመስጫ ስራዎች ተሰርተዋል። በዚህም ምክንያት የተወሰኑ ለውጦች እየተመዘገቡ እንደሆነ እየተገለፀ ነው።

ለአብነት ያህልም የሴት ልጅ ግርዛት አሳሳቢ በነበረበት ትግራይ ክልል ድግግሞሹ ከ48.1 በመቶ ወደ 21.2 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፤ በደቡብ ክልል ደግሞ ከ36 በመቶ ወደ 30.8 በመቶ ወርዷል። የህፃናት ጋብቻን በተመለከተም ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው በደቡብ ክልል ከ18.7 በመቶ ወደ 9.9 በመቶ ሲወርድ በቤኒሻንጉል ክልል ደግሞ ከ50.1 በመቶ ወደ 31.9 በመቶ መቀነሱን ያመለክታል። የጠለፋ ጋብቻም ቢሆን በቤንሻንጉል ቀድሞ ከነበረበት 26 በመቶ ወደ 11 በመቶ እንዲሁም በትግራይ 13.9 ወደ 5.9 በመቶ ቀንሷል። ሆኖም ግን የችግሩ አሳሳቢነት አሁንም እንደቀጠለ ነው።

Last modified on Thursday, 03 October 2013 20:39
ይምረጡ
(8 ሰዎች መርጠዋል)
3542 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1079 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us