“ገና የፕላቲኒየም ሽልማት እንጠብቃለን”

Wednesday, 07 May 2014 14:01

ዘላለም መራዊ- የኬር ኤዥ እና

የዘላለም መኪና ኪራይና አስጎብኚ ስራ አስኪያጅ

 

ዘላለም መራዊ ትውልዱ በምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ በምትገኘው አምቦ ከተማ ሲሆን፤ እድገቱ ደግሞ በከፊል አዲስ ዓለም ከተማ፣ ከዚያም አዲስ አበባ ነው። ከሀገራችን በአፄ ምኒልክ የተቆረቆች የመጀመሪያዋ ከተማ እንዲሁም የመጀመሪያው አስፋልት የተሰራበት በሚላት አዲስ ዓለም ከተማ እስከ 6ኛ ክፍል ተምሯል። ቀሪውን ትምህርቱን በአዲስ አበባ ያጠናቀቀ ሲሆን፣ በቱሪዝም ዘርፍም የኮሌጅ ትምህርቱን ተከታትሏል። በአሁኑ ወቅት የዘላለም መኪና ኪራይ እና አስጎብኚ ዋና ስራ አስኪያጅ እና የኬር ኤዥ ኢትዮጵያ ማርኬቲንግ ኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጅ ነው። ዘላለም በተለይ የቱሪስት ጋይድ መፅሔትን በማዘጋጀት ይታወቃል። ይህ የቱሪስት ጋይድ መፅሔትም ዓለም አቀፍ ሽልማት ለማግኘት በቅቷል። ከወጣት ዘላለም ጋር ቆይታ አድርገናል።

ሰንደቅ፡- ወደ ቱሪዝም መስክ እንዴት ልትገባ ቻልክ?

ዘላለም፡- መጀመሪያ የተቀጠርኩት የአጎቴን መኪና ይዤ በሱማሌ ክልል በሚገኝ የመንገድ ስራ ድርጅት ውስጥ ነበር። በዚያ ድርጅት ውስጥ ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ በሹፍርና ሰርቻለሁ። በጣም በረሃ በሆኑት ጎዴ እና ኢሜ አካባቢዎች ነው የሰራሁት። ያንን ከባድ ጊዜ አልፌ ከመጣሁ በኋላ ግን ድሮ እሰራበት የነበረው የአጎቴ ጋራዥ ውስጥ ከሚያሰሩ የአስጎብኚ ድርጅቶች ውስጥ በአንዱ በሹፌርነት ተቀጠርኩ፡ ከዚህ በኋላ እንግዲህ የተማርኩትን ትምህርትም ተጠቅሜ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ውስጥ አንቱ ሊያሰኘኝ የሚችል አንድ ስራ ልሰራ ይገባል ብዬ ማቀድ ጀመርኩ።

በአስጎብኚ ድርጅት ውስጥ በሹፌርነት ወደ ስምንት ዓመት ስሰራ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ሰዎች ጋር ትውውቅ መፍጠር ችያለሁ። ከትምህርት ቤት ላገኘው ከምችለው በተሻለም ልምድ አግኝቻለሁ። ሹፌር ሆኜ ስሰራ በምግብ ዝግጅት እና መጠለያ በማዘጋጀት (camping management) በመሳሰሉት ስራዎች ላይ እሳተፍ ነበር።

ሰንደቅ፡- ሞያውን ወደኸው ነው ወይስ እንደመኖሪያ ቆጥረኸው ነው የምትሰራው?

ዘላለም፡- ቱሪዝም ማለት ለሰዎች ደስታን መፍጠር ማለት ነው። ቱሪዝም ማለት የሰዎችን ፍላጎት ማሟላት ማለት ነው። ሰው ደግሞ በተፈጥሮው ፍላጎቱ አይሟላም። ምንም ነገር ቢደረግለት ተጨማሪ ነገር የሚፈልግ በመሆኑ ለሰው ደስታን መፍጠር በጣም ከባድ ነገር ነው። ነገር ግን ሞያዊ በሆነ መንገድ ሲሰራ ለሰዎች ደስታን መፍጠር ይቻላል። ያም ሆኖ አንድ ሰው ሞያው ስለሆነ ብቻ በስራው ውጤታማ ይሆናል ማለት አይደለም። ፍቅርም ይጠይቃል። እኔም በጣም ስለምወደው ነው የምሰራው። ስራዎችን ደርቤ የምሰራው ለተጨማሪ ገቢ ብቻ አይደለም። ማንም ሰው ተጨማሪ ገቢ እንዲኖው ይፈልጋል። እኔ ግን ተጨማሪ ክፍያም ሳይከፈለኝ ልምድ ለማግኘት ስል እነዚህን ስራዎች እሰራ ነበር።

ሰንደቅ፡- ያደግህበት አካባቢ በስራ ዝንባሌህ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮብህ ይሆን?

ዘላለም፡- አዎ! ያደኩት አዲስ ዓለም እንደመሆኑ ልክ እንደ ሌሎች ልጆች አዲስ አለም ማሪያም ቤተክርስቲያን ሙዚየም አካባቢ አልጠፋም ነበር። ቤተክርስቲያኑ ከቤተክርስቲያንነቱ በዘለለ ትላልቅ ሀብቶች፣ የሚጎበኙ ቅርሶች ያሉበት ቦታ ነው። እዚህ ቦታ ላይ ማደግ እና መኖር በራሱ የሚሰጠው ስሜት አለ። ቱሪስቶች መጥተው ሲጎበኙ አይ ነበር። ልጅ ሆኜ ቱሪስቶች የሚመጡበት ምክንያት አይገባኝም ነበር። ሙዚየም ሲገቡ በጣም ተጠግቼ፣ አብሬ ገብቼም አይ ነበር። ስለዚህ የቱሪዝም ጽንስ ሀሳብ በውስጤ መቀመጥ የጀመረው ከዚያን ጊዜ አንስቶ ነው።

በነገራችን ላይ ሊጎበኙ ከሚገባቸው ቦታዎች አዲስ ዓለም አንዱ ነው። የምኒልክ ቤተ መንግስት የነበረና ትላልቅ የወርቅ መስቀሎች የሚገኙበት ቦታ ነው።

ሰንደቅ፡- ለሀገራችን ቅርሶች ያለውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዴት ታየዋለህ?

ዘላለም፡- በእኛ ሀገር ለቅርሶች የሚደረገው ጥበቃ ጉድለት አለበት። የአጠባበቅ ሁኔታው የተጠናከረ አይደለም። በርካታ ሀገራትን ማየት ችያለሁ። በዞርኩባቸው የአለም ሀገራት ትናንሽ የቱሪዝም ቅርሶች የሚደርግላቸው ጥበቃ በጣም ያስደንቃል።የማስታውሰው አንድ ሀገር ላይ አንዲት ትንሽ በእንጨት የተሰራች አንድ ሜትር የማትሞላ ድልድይ አለች። በስሯ ትንሽ ውሃ ታልፋለች። ያቺ ድልድይ በሰንሰለት ታጥራ ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግላታል፤ ትጎበኛለችም። ይሄ ነገር ምንድን ነው ብዬ ስጠይቅ ከዛሬ ሰባ እና ሰማንያ ዓመት በፊት ንጉስ እከሌ በዚህ በኩል ስላለፉ ነው። ንጉስ በዚህች ድልድይ ላይ ስለተሻገሩ እንደ ቱሪዝም ቦታ ይጠቀሙበታል ነው የተባልኩት። እኛ በርካታ መቶ ዓመታት ያስቆጠሩ ቅርሶች አሉን፤ ነገር ግን ብዙም ጥበቃ አይደረግላቸውም።

ለምሳሌ የጥያ ትክል ድንጋይ በዩኔስኮ የተመዘገበ ትልቅ ቅርስ ነው። ነገር ግን መፈራረስ እየደረሰበት ነው። እንዲህ አይነት ቅርሶችን እያጣን ከሄድን ታሪካችን እየተበላሸ ስለሚሄድ ጥበቃ ሊደርገላቸው ይገባል። ስለዚህ ቅርሶቻችን በተፈጥሮ ከሚደርስባቸው ጉዳት፣ ከስርቆት እና ከመሳሰሉቱ አደጋዎች መጠበቅ አለባቸው የሚል እምነት አለኝ።

ሰንደቅ፡- የሀገራችንን ገፅታ እና ለቱሪስቶች መረጃ የሚሰጥ መፅሔት ያዘጋጀኸው ምናልባት በስራ ዓለም ከገጠመህ ችግር በመነሳት ይሆን?

ዘላለም፡- የራሴን የመኪና ኪራይ እና አስጎብኚ ድርጅት ስከፍት እንዴት ማህበረሰቡን በቱሪዝም መስክ መጥቀም እንችላለን የሚለውን ነገር ማሰብ ጀመርኩ። ሳስበው ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ የተፃፈ ነገር ግን አያገኙም። ስለዚህ በምን አይነት መንገድ ነው ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ የቱሪዝም መረጃ መስጠት የሚችል ተቋም መገንባት የሚቻለው የሚለውን ማሰብ ጀመርኩ። ለዚህም ድረገፅ፣ መረጃ እና መፅሔት ለማዘጋጀት ወሰንኩኝ። ድረ-ገፁ መስራት ሲጀምር ደግሞ ይህን መረጃ በሀርድ ኮፒ (በመፅሔት) ለማዘጋጀት ታቅዶ ነው ስራው የተጀመረው። በዚህም አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እና ዳይሬክተሪ ጭምር ያለው እንዲሁም በውስጡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ጨምሮ ብዙ መረጃዎችን የሚሰጥ አንድ የቱሪስት ጋይድ መፅሔት አዘጋጅተን ያስመረቅን ሲሆ፤ በሁለት ዓመታት ውስጥ 60ሺ ያህል ኮፒዎች ታትመው በመላው አለም ተሰራጭተዋል። ይህ መፅሔት ለቱሪስቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸውን ቆይታ የሚያቀል መሳሪያ ነው።

ሰንደቅ፡- በዚህ መፅሔት ዓለም አቀፍ ሽልማት አግኝተሃል። ሽልማቱ ምን ይመስል ነበር? የፈጠረብህ ስሜትስ?

ዘላለም፡- መፅሔቱ የተሸለመው ስዊዘርላንድ ጄኔቫ ነው። ሽልማቱ ሴንቸሪ ኢንተርናሽናል ኳሊቲ ኤሩ አዋርድ ይባላል። ሽልማቱን ያገኘነው በአለም አቀፍ ደረጃ ከ3ሺ በላይ ድርጅቶች ጋር ተወዳድረን በቱሪዝም መስክ ላበረከትነው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነው።

ሽልማት በራሱ ከሚሊዮኖች በላይ ነው። ለሰራነው ነገር ክብር ሲሰጠን፣ ለሀገራችን እና ለአለም ባበረከትነው ነገር እውቅና እና አለም አቀፍ ሽልማት ሲሰጥ የሚሰማው ስሜት ለሀገር ሜዳሊያ እንደማምጣት ነው። ከ85 በላይ ሚዲያ እና ከ3ሺ በላይ ድርጅቶች ባሉበት ስለ ኢትዮጵያ ቱሪዝም ሀብት እና መልካም ገፅታ ከ15 ደቂቃ በላይ ገለፃ አድርጌያለሁ። በተለያዩ አለም አቀፍ ጋዜጦች እና መፅሔቶች ላይ ወጥቷል። ይሄ ለእኛ ትልቅ ሽልማት ከመሆኑም በላይ ወደፊት ትልቅ ስራ መስራት እንዳለብን የማንቂያ ደወል የሰማንበት ነው። ሽልማቱ የሚያኮራን ሳይሆን ትልቅ ነገር መስራት እንደምንችል መንገድ ያሳየን ነው። እየሰራን ባለነው ስራ ገና የፕላቲኒየም ሽልማት እንጠብቃለን። በቀጣይም ኬር ኤዥ አፍሪካ የሚል እና በአፍሪካ ቱሪዝም ላይ የሚሰራ ፕሮጀክት ይዘን እየተንቀሳቀስን ነው። በተጨማሪም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነ የቱሪዝም ፌስቲቫል ለማዘጋጀት አስበናል።

ሰንደቅ፡- በሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ላይ ምን እየሰራችሁ ነው?

ዘላለም፡- በመላው አለም የተለያዩ ቱሪስቶች እየሄዱ ሌላውን ሀገር ያያሉ። የሚገርመው ነገር 95 በመቶ አካባቢዎች ወደ ውጭ የሚሄዱ ጎብኚዎች መጀመሪያ ሀገራቸውን ጎብኝተው ነው። ብቁ ቱሪስት የሚባለው መጀመሪያ የራሱን ሀገር የሚያውቅ ነው። በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ ውጭ ሄደን ለመጎብኘት እንጓጓለን። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለንን የቱሪዝም ሀብት ሳናይ ሌላውን ለማየት ልንጓጓ አይገባም። አንድ ቦታ በሄድን ቁጥር ጭንቅላታችን በርካታ ነገሮች ይዞ ይመጣል። አንድ ቦታ ደርሰን ስንመጣ በርካታ ነገሮችን ተገንዝበን እንመጣን። ስንጎበኝ እንደሰታለን። ምን እንስራ የሚለውንም ጥያቄ መመለስ እንችላለን። በተለይ ወጣቱ መጎብኘት ከቻለ በርካታ የስራ ሀሳቦችን ማግኘት ይችላል። ይሄ ግን ሲሆን አይታም። አሁን ያለው ነገር ትንሽ መሻሻል እያሳየ ነው። ወደፊትም የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን በእጥፍ ለማሳደግ አስበናል።

ይህን ስራችንን በዚህ ሁለት ወር ውስጥ በጎንደር እና በባህርዳር አድርጎ የታላቁን ህዳሴ ግድብ ጉብኝት በማዘጋጀት እንጀምራለን

ሰንደቅ፡- በህይወትህ ፈታኝ ናቸው የምትላቸው ጊዜያት የትኞቹ ናቸው? ምንስ ተማረክባቸው?

ዘላለም፡- በርካታ የህይወት ውጣ ውረዶችን አሳልፌያለሁ። ከልጅነቴ ጀምሮ የቀን ስራ፣ የሊስትሮ ስራ እና የጋራዥ ስራን ሰርቻለሁ። እነዚህ ጊዜያት እንዴት በስራ ማደግ እንደሚቻል፣ ከማህበረሰቡ ጋር እንዴት እንደምኖር የተማርኩባቸው ጊዜያት ናቸው፡ በሹፍርና ስራ ላይ ሳለሁም ከሞት ያመለጥኩበት ጊዜ ነበር። ሽፍታ መኪናዬን በጥይት ደብድቦ እኔንም በሰደፍ አከርካሪዬ ላይ ጉዳት አድርሶብኛል። ያ ሁሉ ፈተና ሲደርስብኝ ታዲያ ጠንካራ አድረጎኛል። ፈተናውን ባለፍኩ ቁጥር አንድ ነገር ተምሬ ነው የማልፈው።

አንድ ሰው ውስጡ የተቀመጠ ድፍን ነገር አለው። ማንም ሰው ሲወለድ ውስጡ ፍላጎት፣ ራዕይ እና ግብ አለ። ያንን ግብ ወደ ተግባር መቀየሩ ነው ትልቁ ቁም ነገር። እኔ ውስጥ ስወለድ ጀምሮ የተቀመጠ ነገር አለ። ያንን የተቀመጠ ነገር ነው ያወጣሁት። እዚያ ደረጃ ላይ ስደርስ ደግሞ ሌላ ራዕይ ይመጣል። ስለዚህ ውስጤ የተቀመጠውን ፍላጎት አውጥቼ በመጠቀም ከእነዚህ ፈተናዎች ሁሉ አልፌ ውጤታማ መሆን ችያለሁ።

ሰንደቅ፡- ባሰብከው ጊዜ የተሳካልህ ይመስልሃል?

ዘላለም፡- እኔ እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር አድርጎልኛል። ሁሉን ነገር ተሳክቶልኛል። በዚህ በወጣትነት እድሜዬ የ7 ዓመት ልጅ ማድረስ ችያለሁ። ብዙዎች ያልኖራቸውን አግኝቻለሁ። እግዚአብሔር የሚያስፈልገኝን በሚያስፈልገው ጊዜ ሰጥቶኛል። ውጤታማ ለመሆን ጠይቀን ወደዘገየብን ነገር መሄድ እና ያን ለማግኘት መጣር እንዳለብን አይቻለሁ።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
1596 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 784 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us