የቅን አስተሳሰብ ፍሬዎች

Wednesday, 14 May 2014 13:44

ቪዥን ኢትዮጵያን ኮንግረስ ፎር ዴሞክራሲ (ቪኢኮድ) የዛሬ 11 ዓመት ነበር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተቋቋመው። ያቋቋሙት ደግሞ በኢትዮጵያ መልካም ዜጋ፣ መልካም አስተዳደር እና መልካም መንግስት እንዲፈጠር ምኞት የነበራቸው አምስት ምሁራን ነበሩ። ይህ ጅምር ታዲያ እየተስፋፋ በመምጣት በአሁኑ ወቅት ምኒልክ እና ለገሀር ማዕከሎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎችን ማብቃት ችሏል። እስከ አሁን ድረስ በ41 ዙሮች ስልጠና የሰጠ ሲሆን፣ እስከ አሁን ድረስም 5 ሚሊዮን 209ሺ 85 ሰዎች ተለያዩ ስልጠናዎችን፣ አውደ ጥናቶች እና ውይይቶች አሳትፏል። ለ41ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 424 ተማሪዎች ባለፈው ቅዳሜ በሀገር ፍቅር አዳራሽ አስመርቋል።

በምረቃ ስነ ሥርዓቱ ላይ ለሶስት ወራት (ለ168 ሰዓታት) በምኒልክ እና ለገሀር የስልጠና ማዕከላት ትምህርታቸውን በአስተዳደርና ስራ አመራር ሙያ ማሻሻያ ዘርፍ ያጠናቀቁ ሰልጣኞችና አሰመራቂዎች እንዲሁም ዶ/ር ወረታው በዛብህ እና ዶ/ር ኢንጂነር ሳሙኤል ዘሚካኤልን የመሳሰሉ ምሁራን ተገኝተዋል። ምሁራኑም ሳቢ በሆነ መልኩ ለታዳሚያኑ አጫጭር ስልጠናዎችን ሰጥተዋል።

የ41ኛው ዙር ተመራቂዎች ከዚህ ቀደም ከነበሩት ተመራቂዎች በተለየ መልኩ ከስልጠናቸው ጎን ለጎን በርካታ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን አከናውነዋል። በእነዚህ ተግባራት መካከልም በፈቃደኛነት ላይ የተመሰረተ የደም ልገሳ አንዱ ነው። በተጨማሪም ተመራቂዎቹ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች አልባሳትና ቁሳቁስ በማሰባሰብ ለአእምሮ ህሙማን፣ ለአቅመ ደካሞች እና ወላጅ አልባ ለሆኑ ህፃናት ለግሰዋል።

እነዚህ ሰልጣኞች በማዕከሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ አትክልት የመትከል እንዲሁም በማዕከሉ ውስጥ ያለውን የወንበር እጥረት ለመቅረፍ 28 ወንበሮችን በመግዛት ለማዕከሉ አስረክበዋል። በዚህኛው ዙር ከዚህ ቀደም ከነበሩት በተለየ በለገሀር ማዕከሉ በርካታ የሶማሊያ ዜጎች ስልጠናውን ወስደዋል። እነዚህ ሶማሊያውያን ከኢትዮጵያውያኑ ሰልጣኞች ጋር የበለጠ እንዲተዋወቁ እና ወዳጅነታቸው እንዲጠነክር የወዳጅነት እግርኳስ ግጥሚያ በሁለቱም ፆታ ተካሂዷል።

ወጣት ሞሀመድ አሊ የሶማሊያ ዜግነት ያለው ሲሆን፣ በአለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ድግሪውን ይዟል። በራሱ ስራ ላይ ተሰማርቶ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን የአስተዳደርና ስራ አመራር ሙያ ማሻሻያ ስልጠና ለመውሰድ ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረው ወደዚህ ማዕከል መጥቶ እንደሰለጠነ ገልጿል። በስልጠናውም መስክ በርካታ እውቀት እንደቀሰመ እና በህይወቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣም ገልጿል። ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ በመሰልጠኑም ከትምህርቱ በተጨማሪ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞች እና እህቶቹ ጋር በማሳለፉ በጣም መደሰቱን ገልጿል። መሀመድ ከለገሀር ማዕከል በአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀ ሲሆን፤ በበጎ አድራጎት ስራዎች ውስጥም ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበረው ገልጿል።

በማዕከሉ ስልጠናዎችን ለመውሰድ ያስቀመጣቸው መስፈርቶች አሉ። ከእነዚህ ውስም ሰልጣኞች በእድሜ ዝቅተኛው 18 ዓመት ሲሆን፤ ከፍተኛው ደግሞ 77 ዓመት ነው። በትምህርት ደረጃ ደግሞ ዝቅተኛው በቀድሞ 12ኛ ክፍል በአሁኑ ደግሞ 10ኛ ክፍል፤ ከፍተኛው ደግሞ ዶክትሬት ዲግሪ ነው። በዚህኛው ዙር ታዲያ አንዲት የከፍተኛ እድሜ ተመራቂ ተብለው የተሸለሙ እናት ነበሩ። እኚህ ሴት ወይዘሮ ምህረት ተፈሪ ይባላሉ። ወይዘሮ ምህረት በአሁኑ ጊዜ የ65 ዓመት እድሜ ባለፀጋ ናቸው። ከዚህ ቀደም በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት (በተለይ በሳይንስ ትምህርት) ለ11 ዓመታት አገልግለዋል። በመቀጠልም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቤተመፅሀፍት አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማግኘት በኮከበ ፅባህ ትምህርት ቤት በቤተመፅሀፍ ኃላፊነት ሰርተዋል።

ወይዘሮ ምህረት በዚህ ስራ ላይ እያሉ ዲቪ ደርሷቸው ወደ አሜሪካ ያቀኑ ሲሆን፣ ከ8 ዓመታት ቆይታ በኋላም በቃኝ ብለው ወደሀገራቸው ተመልሰዋል። በአሁኑ ወቅት በራሳቸው ህይወት ላይ የሚያጠነጥን መፅሐፍን በማዘጋጀት ላይ ይገኛሉ። ጎን ለጎንም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሚሰጡ ማዕከላት እየተዘዋወሩ ያገለግላሉ። ይህን ስልጠና ለመውሰድ የነተሳሱትም ማህበራዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሆነ ይናገራሉ። “በፊት ማህበራዊ ተሳትፎዬ ጥሩ ነበር። ከሀገር ወጥቼ ከተመለስኩ በኋላ ግን ክፍተት አለ። ስልጠናው ከሰዎች ጋር እንዴት ተግባብቼ መኖር እንደምችል፣ እንዴት እንደምቻቻል ለመገንዘብ ስለሚያግዘኝ ነው መሰልጠን የፈለኩት” የሚሉት ወይዘሮ ምህረት፤ በዚህ እድሜያቸው ስልጠናውን መውሰዳቸው ከቤታቸው ጀምሮ አብረዋቸው ከሚኖሩ ሰዎች ጋር እንዴት መኖር እንደሚችሉ መንገድ ከፋች መሆኑን ገልፀዋል።

አውሮፓን ፣ ኢየሩሳሌምን እና አሜሪካን ጎብኝተው መመለሳቸውን የሚገልፁት ወይዘሮ ምህረት፤ በሄዱበት ሀገር ሁሉ የተመለከቷቸው ነገሮች እየተለወጡ እና ዘመናዊ ገፅታን እየተላበሱ በመሆናቸው ራሳቸውን ከጊዜው ጋር ለማጣጣም ይህን ስልጠና መውሰዳቸው ወሰኝ መሆኑን ገልፀዋል። “ራሴን ስመለከተው ማስተካከል ያለብኝ ነገር እንዳለ ተገነዘብኩ። ስለዚህ ከዘመናዊው አስተሳሰብ ጋር ለመዋሃድ ስልጠናው ጥሩ አጋጣሚ ሆኖኛል። አንዲት ቤተሰባችን ሰልጥና ስታበቃ እኔም መሰልጠን እንዳለብኝ ወሰንኩኝ” የሚሉት ወይዘሮ ምህረት፤ እርሳቸው ያሉበት ዙር ሰልጣኞች ያደረጉት የበጎ ፈቃደኝነት ስራም ወትሮውንም የሚወዱት በመሆኑ አብረው እንደሰሩ ገልፀዋል።

ወጣት ዮናስ ኃይሉ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ የፕሮጀክት ኦፊሰር ነው። በዚህ ማዕከል ውስጥ ስልጠናውን ከወሰዱ ተመራቂዎችም አንዱ ነው። ወጣት ዮናስ በማዕከሉ ቆይታው ከስራው ጋር ተያያዥነት ያላቸው ኮርሶችን በመውሰዱ ራሱን እንዲፈትሽ እና አካባቢውም እንዲያይ እንዳደረጉት ይናጋል። “በርካታ የሚረዱኝን ነገሮች አግኝቻለሁ። የአስተዳደር ብቃት (Management Skills) ኮርሶችን መውሰዴ ቀደም ሲል ከነበረኝ ነገር ጋር አያይዤ እንድሰራ እና ለውጥ እንዳመጣ ጠቅሞኛል” ይላል።

ተመራቂዎቹ ትምህርቱን ከመከታተል ጎን ለጎን ያከናወኗቸው የበጎ ፈቃድ ተግባራት በቀጣይ ለሌላ ስራ እንዲዘጋጁ ኃላፊነት የጣለባቸው መሆኑን ይገልጻሉ። ወጣት ዮናስም እንዲህ ይላል። “ምናልባት እዚህ ቦታ ስለተገኘን ብቻ አይደለም፤ ባለንበት የስራም ሆነ ሌላ ሁኔታ በተቻለን መጠን እንደሰው ሰዎችን ልንረዳ ይገባናል። ለሰዎች እርዳታ ሲባል የገንዘብ እና የቁሳቁስ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን እርዳታ የጊዜ ሊሆነ ይችላል፣ የሞራልም ሊሆን ይችላል። በሀገራችን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ብዙም አልተለመደም። እኔ በዚህ ስራ በጣም ነው የተደሰትኩት። ለወደፊቱም የበለጠ እንድሰራ ነው ያደረገኝ” ይላል።

በማዕከሉ የሚሰጡት ስልጠናዎች ከእለት ተእለት ህይወት እና ተሞክሮ ጋር ተያያዥነት ያላቸው በመሆናቸው ሰልጣኙ በቀላሉ ሊገነዘበው እንደሚችል ነው ወጣት ዮናስ የገለፀልን። አሰልጣኞች ከተሞክሯቸው ተነስተው የሚሰጡት ስልጠና፤ ሰልጣኞች በራሳቸው ህይወት ውስጥ ከገጠማቸው ነገር ተነስተው የሚያቀርቧቸው ምሳሌዎች እና አጠቃላይ ተሳትፎው ራሱን እንዲያይ እንዳደረገውም ገልጿል።

ቪዥን ኢትዮጵያን ኮንግረስ ፎር ዴሞክራሲ ሲመሰረት የአስተዳደርና ስራ አመራር ሙያ መሻሻያ ስልጠናዎችን ለመስጠት ቢሆንም በቆይታው ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውኗል። በተለይ ደግሞ በስነ ዜጋ እና ሥነ-ምርጫ ትምህርት፣ የንግግር ነፃነት ማዳበር፣ በሴቶች እና ህፃናት ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች ላይ ግንዛቤ መፍጠር እንዲሁም በዴሞክራሲ እና በሰብዓዊ መብት ላይ ያጠነጠኑ በርካታ ስልጠናዎች ሰጥቷል።

በማዕከሉ ውስጥ ለሰልጣኞች ስልጠናውን የሚሰጡትም በዚያው በማዕከሉ ሰልጥነው የወጡ በጎ ፈቃደኞች ምህራን ናቸው። እነዚህ በጎ ፈቃደኛ መምህራን ከተማሩት መደበኛ ትምህርት ጋር የተያያዘ ስልጠናዎችን እንዲሰጡ ይደረጋል። እነዚህ መምህራንም በፈቃደኝነት ተመልሰው ስልጠናውን እንዲሰጡ ይደረጋል። ወጣት ዮናስም ለዚህ ዝግጁ መሆኑን ይናገራል። “እኔ በኮሙኒኬሽን ዘርፍ ነው ስልጠናውን ለመስጠት የተሰማማሁት። መቼ እንደሚደርሰኝ ባላውቅም የደረሰኝ ቀን ግን ልክ እኔን እንዳስተማሩኝ መምህራን ተመልሼ ለማስተማር ዝግጁ ነኝ” ብሏል።

በእለቱ በነበረው የምርቃት ስነ ስርዓት ላይ በበጎ ፈቃደኝነት ስልጠና ሲሰጡ ለቆዩ መምህራን፣ እንዲሁም ቤተሰብ ሆነው ለሰለጥኑ፣ በበጎ ፈቃደኝነት ደም ለለግሱ እና ከየማዕከላቱ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ለወጡ ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቷል። ከዚህ በተጨማሪም ለክቡር ዶ/ር አበበች ጎበና የክብር ሽልማት ተሰጥቷል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1979 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 686 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us