ዛሬም ሚሊዮኖች በመጠጥ ውሃ ጥም ይሰቃያሉ

Wednesday, 21 May 2014 12:55

 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሰሞኑ በአለማችን ላይ ያለውን ንፁህ የመጠጥ ውሃ ስርጭት አስመልክቶ አንድ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። በሪፖርቱ እንደተመለከተው ዛሬም ድረስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር ይሰቃያሉ።

በዓለማችን ላይ ሁለት ቢሊዮን ያህል ሰዎች የተጣራ ውሃ የሚያገኙ ሲሆን 2ነጥብ3 ቢሊዮኖች ደግሞ ደህንነቱ የተጠበቀ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚዎች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥም 1ነጥብ6 ቢሊዮን የሚሆኑት በግቢያቸው ውስጥ የውሃ መስመር የተዘረጋላቸው ናቸው። በተቃራኒው ደግሞ በዓለም ላይ 700 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ጥሩ የመጠጥ ውሃ ማግኘት አይችሉም። ከእነዚህ 700 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ውስጥም ግማሾቹ በሰሀራ ከታች ባሉ ሀገራት የሚኖሩ ሰዎች ናቸው። ይህን እውነታ ይፋ ያደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአለም ጤና ደርጅት ከሰሞኑ ባወጡት ሪፖርት ነው። የዓለም ጤና ድርጅት የስነ ህዝብ ጤና፣ ኢንቫይሮመንት እና ማህበራዊ ጤና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ማሪያ ኔይሩ እንደገለፁትም ከዓለማችን ህዝብ አንድ ሶተኛው (25 ቢሊዮን ያህሉ) የተጣራ ውሃ የማያገኙ ሲሆን አንድ ቢሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከማንኛውም ስፍራ የተገኘውን ውሃ ይጠቀማሉ።

ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው በ2015 ለህዝባቸው ግማሽ ያህል ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለማቅረብ ካቀዱ ሀገራት መካከል 116 ሀገራት ዓላማቸውን አሳክተዋል። 77 ሀገራት ደግሞ በፍሳሽ በኩል ያለውን ችግር ለመቅረፍ ያስቀመጡትን ዓላማ አሳክተዋል።

የ2014 ሪፖርት እንዳመለከተውም በከተማ አካባቢ ከሚኖሩ ሰዎች መካከል እንኳ ግማሽ ያህሉ ብቻ የተጣራ የመጠጥ ውሃ ያገኛሉ። ይህ አሀዝ ከገጠሩ ህዝብ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ልዩነት ያለው ቢሆንም ከአመት ወደ አመት ያለው ለውጥ ግን ክፍተቱን እያጠበበው እንደመጣ ተገልጿል።

ከዓለም ጤና ድርጅት እና ዩኒሴፍ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው እ.ኤ.አ በ1990 በከተማ ከሚኖረው ህዝብ 95 በመቶ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ሲያገኝ፤ በገጠር ከሚኖረው ውስጥ ግን 62 በመቶው ብቻ ነበር ይህን ንፁህ የመጠጥ ውሃ የሚያገኘው። ይህ ስርጭት በመሻሻለም በ2012 ከከተማ ነዋሪው 96 በመቶው እንዲሁም ከገጠር ነዋሪው 82 በመቶዎቹ የተጣራ የመጠጥ ውሃ ያገኙ ነበር።

“አብዛኞቹ ንፁህ የመጠጥ ውሃ የማያገኙት በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ደሃ ሰዎች ናቸው። እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች እየጠቀሙ ያሉት ሀብታሞችን በመሆኑ ልዩነቱ እየሰፋ ነው የመጣው ሲሉ ዳይሬክተሯ ዶ/ር ኔይሩ ተናግረዋል። ዳይሬክተሯ አያይዘውም “አሁንም ድረስ በርካታ ሰዎች መሰረታዊ የሆነ የመጠጥ ውሃ አያገኙም። ትልቁ ተግዳሮትም ለእነዚህ ለችግሩ ተጠቂዎች ንፁህ የመጠጥ ውሃን በአፋጣኝ ተደራሽ ማድረጉ ላይ ነው። የመጀመሪያ እንቅስቃሴ ሊሆን የሚገባው ሊሰራለት የሚገባ ማነው? መቼ እና እንዴት የሚለውን መለየት ነው የሚሆነው። ስለዚህ በእነዘህ በችግሩ ውስጥ ባሉ አካላት ላይ ትኩረት አድርገን መስራት ያስፈልጋል” ብለዋል።

ይህ ዳይሬክተሯ የገለፁት ልዩነት ታዲያ የሚስተዋው በከተማ እና በገጠር ነዋሪው ህዝብ መካከል ብቻ አይደለም ይላል ሪፖርቱ። በትላልቅ ከተሞች እና ትናንሽ ከተሞች መካከልም ያለው ልዩነት አሳሳቢ እንደሆነ ተገልጿል። ዝቅተኛ ገቢ ኖሯቸው ኢ መደበኛ ወይን ሕገ ወጥ በሆነ አሰፋፈር በከተሞች ጠረፋማ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ለንፁህ የመጠጥ ውሃ ያላቸው ተደራሽነት በመሀል ከተማ ከሚገኙት ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ ነው።

“መፍትሄ የሆነ የመጠጥ ውሃ ስርጭትን ማዳረስ ሲያቅተን በርካታ ደሃ እና ተጋላጭ ህፃናትና ቤተሰብን ነው የምናመርተው” ያሉት በዩኒሴፍ የውሃ እና ሳኒቴሽን ኃላፊው ሳንጃይ ዊጄሴካራ፣ “ለወደፊቱ ጤናማ እና የተማሩ ህፃናትን ለማየት የምናልም ከሆነ ፍትሃዊ የሆነ የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ተደራሽነትን ልንፈጥር ይገባል” ብለዋል።

የመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ሀይል ጉዳይ በአሁኑ ወቀት ከፍተኞቹ የእድገት ተግዳሮቶች እንደሆኑ የገለፀው የተባበሩት መንግስታት በበኩሉ፤ አባል ሀገራት ይህን ችግር ለመቅረፍ ከምን ጊዜውም በላይ መረባረብ እንዳለባቸው አሳስቧል። “የመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ቀጣይነት ያለው ሃይል አገልግሎት እጥረቶች ተደማምረው ድህነትን የሚያጎሉ፣ በጤና እና በእናቶች ላይ እንዲሁም በፆታ እኩልነት ላይ የሚያስከትሉት አሉታዊ ተፅእኖ ከፍተኛ ነው” ሲሉ የምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጆን አሺ ገልጸዋል። “የመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ዘላቂ ሃይል ተደራሽነት የጀግንነት ጉዳይ ሳይሆን የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ሞራል ጉዳይ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ በአሁኑ ጊዜ 783 ሚሊዮን ህዝብ ንፁህ ውሃ እያገኘ እንዳልሆነም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን የመጠጥ ውሃ ስርጭት ስንመለከት የውሃ፣ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትር ያወጣው የ2012/13 ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከኢትዮጵያውያን መካከል 61ነጥብ6 በመቶዎቹ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚዎች ናቸው። በከተማ ከሚኖረው ህዝብ መካከል 80ነጥብ72 በመቶው ንፁህ የመጠጥ ውሃ ሲያገኝ በገጠር ከሚኖረው ህዝብ ግን 58ነጥብ71 በመቶው ብቻ ነው ንፁህ የመጠጥ ውሃ የሚያገኘው።

እስከ 2007 (የምእተ አመቱ ማጠቃለያ) ድረስ በተያዘው እቅድ በከተማ ነዋሪዎች ዘንድ 1ነጥብ5 ኪሎ ሜትር የሚርቁ አባወራዎች እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በቀን 15 ሊትር ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ ይደረጋል። እንዲሁም በገጠር የሚኖረው ህዝብ ዘንድ በየ 0ነጥብ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ አባወራዎች በቀን ለአንድ ሰው 20 ሊትር የጉድጓድ ውሃ ለማቅረብ ታቅዶ ነበር። በዚህም በከተማ የሚኖረው 29 ሚሊዮን 678 ሺህ 725 እንዲሁም በገጠር ሚኖረው ህዝብ 3 ሚሊዮን 613ሺ 216 ሰዎች ደህንነቱ የተጠበቀ የመጠጥ ውሃ አቀርቦት ያገኛል።

ይህ እቅድ ሲከፋፍልም በሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ 16ነጥብ5 ሚሊዮን የከተማ እና 1ነጥብ7 ሚሊዮን የገጠር ህዝብ በድምሩ 18ነጥብ2 ሚሊዮን ሰዎች ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ያገኛሉ ተብሎ ታቅዶ ነበር። አፈፃፀሙ ሲታይ ደግሞ ለከተማው ህዝብ ከታቀደው እቅድ 68 በመቶው እንዲሁም ከገጠሩ 73ነጥብ5 በመቶው ብቻ ተሳክቷል።

ይህን የታቀደ እቅድ ለማሳካት የተለያዩ የውሃ ምንጮችን የማዳበር እና የመገንባት ስራዎች ተሰርተዋል። ለአብነት ያህልም ከ26ሺ በላይ በእጅ የሚሰሩ የውሃ ጉድጓዶች፣ ከ7ሺ በላይ የተፈጥሮ ምንጭ ማጎልበት እንዲሁም የተለያዩ የውሃ አቅርቦት ዘዴዎች ስራ ላይ ውለዋል። በአጠቃላይም ከ44ሺ በላይ የውሃ ቦታዎች ተጋጅተው ለ11ነጥብ1 ሚሊዮን የገጠር እና ለ1ነጥብ2 ሚሊዮን የከተማ ህዝብ አገልግሎት መስጠት ተችሏል።

በእነዚህ በተወሰዱ እርምጃዎች የተገኘው ውጤት አበረታች እና ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ነገር ግን በቀጣይ ብዙ ሊሰራ እንደሚገባ የሚያመለክት ነው። አሁን ያለው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ፍላጎት ያለመመጣጠን ችግር እንዳለ ያመለክታል። በተለይ ደግሞ በከተማው እና በገጠሩ ሀብረተሰብ መካከል ያለው ፍትሃዊ ያልሆነ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ስርጭት ሀገሪቱ ለመድረስ ባቀደችው እቅድ ጋር የሚፃረር መሆኑ ያሳሰበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሀገራት ይህን ክፍተት ለቻላቸው ለማጥፋት ባይቻላቸው ደግሞ ለማጥበብ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው በማስጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ።

በርካታ እናቶች እና ሴት ተማሪዎች ከስድስት ሰዓታት በላይ ከሚያስኬዱ ሩቅ ቦታዎች ላይ የመጠጥ ውሃ ለማምጣት እንደሚጓዙ ነው ሪፖርቶች የሚገልፁት። በዚህም ሳቢያ ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ፣ እናቶችም በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት ችግር እንዲገጥማቸው ምክንያት ሆኗል ይላሉ ሪፖርቶቹ።

ይህ የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት ካልተቀረፈ በእያንዳንዱ በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ህዝብ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የተባበሩት መንግስታት ስጋቱን ገልጿል። ለምሳሌ ያህልም ንፅህናውን ያልጠበቀ እና የተመረዘ የመጠጥ ውሃ ኮሌራ፣ ዲያሪያ (የተቅማጥ በሽታ)፣ ሂፒታይተስ ኤ እና የታይሮይድ በሽታን እንደሚያመጣ ነው የህክምና ባለሙያዎች የሚገልፁት። ይህ ደግሞ ከተሞክሮም የተገኘ ነው። ለአብነት ያህልም በአንድ ዓመት ውስጥ በተቅማጥ (ዲያሪያ) ምክንያት 842ሺ ያህል ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1364 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 909 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us