የሴቷን ህይወት ያመረረው ሌላው ችግር

Wednesday, 28 May 2014 13:39

የአለም የፊስቱላ ቀን ባለፈው አርብ በአለም አቀፍ ደረጃ ተከብሯል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ታዲያ የፊስቱላ ችግር አሁንም ድረስ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን ገልጿል።

የፊስቱላ ችግር አንዲት ሴት በወሊድ ወቅት ለረጅም ጊዜ በማማጧ ምክንያት የሚከሰት ችግር ነው። ይህ ችግር የሚፈጠረው ሴቷ ከስድስት እስከ ሰባት ቀናት የሚፈጅ ከባድ ምጥ ሲያጋጥማት ነው። በዚህ በከባድ ምጥ ወቅት የህፃኑ ጭንቅላት ወደ እናትየዋ የወገብ አጥንት በመገፋት በህፃኑ ጭንቅላትና በእናትየዋ የወገብ አጥንት መካከል ያሉ የአካል ቁራጮች (Tissue) በቂ የሆነ ደም እንዳያገኝ ያደርጋል። በዚህ ሳቢያም እነዚህ የአካል ቁራጮች በመሞት በሴቷ ብልት እና በፊኛዋ አሊያም በብልቷና በወገብ አጥንቷ መካከል ቀዳዳ እንዲፈጠር ያደርጋል። በዚህም ሳቢያ ያቺ ሴት በተለይ ውሃ ሽንቷን የመቆጣጠር አቅም እንዳይኖራት ያደርጋታል።

በዚህ የፊስቱላ ችግር በአብዛኛው የሚጠቁት በታዳጊ ሀገራት ያሉ እናቶችና ሴቶች ናቸው። ለፊስቱላ ችግር ለሚያጋልጠው የረጅም ጊዜ ምጥ እንዲዳረጉ የሚያደርጋቸው ደግሞ በልጅነት እድሜ ማግባትና መውለድ፣ ልጅ የመውለጃ ጊዜን ለመወሰን አለመቻል፣ በጋብቻ እንዲሁም በወሊድ ጊዜ እና ከወሊድ በኋላ የሚደረጉ ባህላዊ ድርጊቶች፣ ስለወሊድ እና ተያያዥ ጉዳዮች እውቀት ማነስ፣ ሴቶች ያላቸው ገቢ ዝቅተኛ መሆን ወይም በወንዶች ላይ ጥገኛ መሆን እና የጤና ተቋማት እጥረት እንደሆኑ ነው የተገለፀው።

በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ቁጥራቸው ከሁለት እስከ ሶስት ሚሊዮን የሚሆን ሴቶች እና እናቶች በዚህ የፊስቱላ ችግር እየተሰቃዩ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት ያመለክታል። በአለማችን ላይም በአንድ አመት ብቻ ከሃምሳ ሺህ እስከ መቶ ሺህ የሚደርሱ ሴቶች በወሊድ ወቅት ለሚከሰት ፊስቱላ ችግር ተጋላጮች ናቸው። ይህ ችግር በአብዛኛው እየከፋ ያለው በእስያ እና ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ሲሆን፤ በርካታ በችግሩ ውስጥ ያሉ ሴቶችም ህክምናውን አያገኙም። በዚህም መሰረት ህክምና ከሚያስፈልጋቸው 50 የፊስቱላ ተጠቂዎች መካከል ህክምናውን የምታገኘው አንዲት ሴት ብቻ መሆኗን የአለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

በኢትዮጵያ ያለውን የፊስቱላ ችግር ስርጭት ስንመለከት የችግሩን ስፋት በግልፅ መገንዘብ ይቻላል። በኢትዮጵያ 142ሺ 387 ገደማ ሴቶች በፊስቱላ ችግር ውስጥ እንዳሉ ነው ባለፈው አመት (2013 እ.ኤ.አ.) የወጣ ሪፖርት ያመለከተው። በዚሁ ዓመት (2013) በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መጠይቆችን በመበተን በ14ሺ 70 በወሊድ ጊዜ ውስጥ ባሉ ሴቶች ላይ ጥናት ተደርጓል። በዚህም መሰረት በጥናቱ ከተሳተፉት ሴቶች መካከል 23 ነጥብ 2 በመቶዎች ስለፊስቱላ ጭራሽም ሰምተው የማያውቁ ናቸው። ከዚህ ቀደም ከወለዱ ሴቶች መካከል ደግሞ 103 ያህሉ የፊስቱላ ችግር አጋጥሟቸዋል። ይህ ማለት ደግሞ ልጅ ከወለዱ አንድ ሺህ ሴቶች መካከል ከ10 በላይ የሚሆኑት የፊስቱላ ችግር አለባቸው።

ይህ የፊስቱላ ችግር ስርጭት ከከተማ ሴቶች ይልቅ በገጠር ሴቶች ዘንድ ከፍተኛ እንደሆነ ነው የተገለፀው። ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ቁጥር ያላቸው ልጆችን የወለዱ ሴቶች ዝቅተኛ ቁጥር ያላቸው ልጆች ከወለዱት በበለጠ ለዚህ ችግር ተጋላጮች ሆነው ተገኝተዋል።

የፊስቱላ ችግር ያለባቸው ሴቶችን ቁጥር በቀላሉ ለማወቅ እጅግ ከባድ እንደሆነ ነው የሚገለፀው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ሴቶቹ ይህ ችግር ሲደርስባቸው ወደ ህዝብ ከመቅረብ ይልቅ ራሳቸውን ከህብረተሰቡ ጭምር ስለሚያገልሉ ነው። በአንድ ወቅት ስለዚህ ችግር የገለፁት የሃምሊን አዲስ አበባ ፌስቱላ ሆስፒታል መስራቿ ዶክተር ካትሪን ሃምሊን እንዲህ ብለው ነበር። “ወደዚህ ሆስፒታል የሚመጡ ሴቶች ለራሳቸው ምንም ግምት የሌላቸው እና ከማህበረሰቡም የተገለሉ ናቸው። የራሳቸው ባልሆነ ጥፋት ገና በለጋነት እድሜያቸው ከማህበረሰቡ ተገልለው በስቃይ ውስጥ ያሉ ናቸው። ይህን ችግራቸውን ራሳቸው ያመጡት እየመሰላቸው ይዘውት ሲሰቃዩ ይኖራሉ” ብለዋል።

የአለም ጤና ድርጅት እንደገለፀው ከሆነ በኢትዮጵያ በየአመቱ ቢያንስ ስምንት ሺህ ያህል ሴቶች ለፊስቱላ ችግር ይጋለጣሉ። በኢትዮጵያ ላለው የፊስቱላ ችግር እንደ ዋና ምክንያት የተቀመጠው ደግሞ ያለ እድሜ ጋብቻ ነው። እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም የተደረገ የስነ ህዝብ እና ጤና ጥናት እንዳመለከተው ይህ ያለ እድሜ ጋብቻ በተለይ በአማራ ክልል ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። በጥናቱ መሰረትም በክልሉ ያሉ ሴቶች ጋብቻ የሚፈፅሙበት አማካይ እድሜ 14 ነጥብ 5 ዓመት ነው።

በዚህም ሳቢያ በኢትዮጵያ በየአመቱ ከዚህ የፊስቱላ ችግር ጋር በተያያዘ ዘጠኝ ሺ ያህል እናቶች ሲሞቱ፤ ሌሎች ዘጠኝ ሺ ያህሉ ደግሞ ልጆቻቸውን አጥተው የእነርሱ ህይወት ይተርፋል። እነዚህ በህይወት የተረፉ እናቶች ታዲያ ቀሪውን ህይወታቸውን በከባድ ስቃይ ለማሳለፍ ይገደዳሉ። ከእነዚህ ዘጠኝ ሺህ ሴቶች መካከል ህክምና የሚያገኙት 1ሺ 200 ያህሉ ብቻ ናቸው።

ለዚህ ሁሉ አሰቃቂ አደጋ ሴቶችን የሚያጋልጣቸው ምክንያት ታዲያ በሀገሪቱ በቂ የሆነ የጤና አገልግሎት አለመኖር መሆኑ ይገለፃል። በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት መቶ እንኳን የማይሞሉ የዚህ የፊስቱላ ባለሞያዎች እንዳሉ ነው የአለም ጤና ድርጅት ከሰሞኑ ያወጣው መረጃ የሚያመለክተው። የአዋላጅ ነርሶችን ቁጥር ያየን እንደሆነ ደግሞ ለ14ሺ ነፍሰጡር ሴቶች አንዲት አዋላጅ ነርስ ታገለግላለች ብሏል ሪፖርቱ። በዚህም ሳቢያ ተገቢውን እርዳታ ባለማግኘት የበርካታ ነፍሰ ጡር ሴቶች ህይወት እያለፈ ይገኛል።

በአጠቃላይ ሲታይ የህክምናው ቴክኖሎጂ የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሷል ተብሎ በሚታሰብበት በአሁኑ ወቅት እንኳ በየደቂቃው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ከዚህ ከፌስቱላ ጋር በተያያዘ ምክንያት ህይወታቸው እያለፈ ነው። በአንድ አመት ብቻ 300ሺ ያህል ሴቶች ከእርግዝና እና ካለ እድሜያቸው ከመውለድ ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን ያጣሉ። ከአለማችን ነፍሰ ጡር ሴቶች ውስጥም አምስት በመቶዎቹ ለፊስቱላ ችግር ተጋላጭ ናቸው።

ምንም እንኳን የፊስቱላ ችግር በአመዛኙ የጤና ችግር ቢሆንም፤ የሚያስከትለው ማህበራዊ ቀውስም ያንኑ ያህል ነው። ችግሩ የተከሰተባት አንዲት ሴት ሽንቷን መቆጣጠር ባለመቻሏ ከማህበረሰቡ ጋር ለመቀላቀል ከፍተኛ ችግር ይፈጥርባታል። በዚህም ሳቢያ ምቶች አለመሰማት፣ ከጓደኛ እና ቤተሰብ እንዲሁም ከማህበረሰቡ መነጠል፣ ጋብቻ ማፍረስ እንዲሁም በፌስቱላ ምክንያት ነርቮች ሲሞቱ መንቀሳቀስ አለመቻል (paralyze) መሆን ይገኙበታል።

ከዚህ በተጨማሪም ተጨማሪ ልጆችን መውለድ አለመቻል፣ ሰርቶ መብላት አለመቻል፣ የወር አበባ ማየት አለመቻል፣ ለኩላሊት በሽታ መጋለጥ እና የመሳሰሉት ችግሮች አንዲት የፊስቱላ ችግር የገጠማት ሴት የምትሰቃይባቸው ችግሮች ናቸው። እነዚህ ችግሮች ታዲያ ሴቶችን ለጭንቀት፣ እራስን በራስ ለማጥፋት እና ለተለያዩ አደጋዎች ያጋልጧታል።

በሚያሳዝን መልኩ ደግሞ እነዚህ በችግሩ ውስጥ ያሉ ሴቶች ችግሩን ከፈጠሩባቸው ባለቤቶቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ጀምሮ ማንም የሚረዳቸው እና የሚያግዛቸው አይኖርም። ባሎቻቸው እነሱን በመፍታት ሌላ ሚስት ሲያገቡ ወላጆቻቸው ደግሞ ሰው በማያያቸው በሰዋራ ስፍራ ያስቀምጧቸዋል።

ከፊስቱላ ችግር ተጠቂዎች ውስጥ ዘጠና በመቶዎች በህክምና የሚድኑ ናቸው። ትልቁ ችግር ግን እነዚህ በችግሩ የተጠቁ ሴቶች ወደ ህክምና ለመምጣት ፈቃደኛ ሆነው አለመገኘታቸው ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ በርካቶች ህክምናው መኖሩንም ባለማወቃቸው ነው። ነገር ግን ለእነዚሁ የፊስቱላ ተጠቂዎች በቀዶ ህክምና ዘዴ በከባድ ምጥ ወቅት የተፈጠረውን ቀዳዳ የመድፈን ስራ ይሰራል።

      በኢትዮጵያ በፊስቱላ ላይ በብቸኝነት የሚንቀሳቀሰው እና በ1974 በአውስትራሊያዊቷ ዶ/ር ካትሪን ሀምሊን የተቋቋመው ሀምሊን ፌስቱላ ሆስፒታል በአመት ለ2ሺ 500 ዜጎች ቀዶ ጥገና ያደርጋል። ከእነዚህ ታካሚዎችም 90 በመቶዎቹ ይድናሉ። ይህን የፊስቱላ ቀዶ ጥገና ለማድረግ አንድ ሰው 600 ዶላር ያህል ያስፈልገዋል። ይህን ወጪ ለመሸፈን ደግሞ ሆስፒታሉ ከተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች ገንዘብ እያፈላለገ አገልግሎቱን በማዳረስ ላይ ይገኛል።

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
2225 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 773 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us