“በሕይወት ያሉ ሰዎችን የማመስገን ልማድ የለንም”

Wednesday, 04 June 2014 12:36

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

 

ተመራማሪ እና ፀሐፊ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ-ገጾች እና የህትመት ውጤቶች ላይ በሚፅፋቸው ፅሁፎች እና በምርምር ስራዎቹ እናውቀዋለን። ለረጅም ዓመታት በእነዚህ ተነባቢ ፅሁፎቹ የምናውቀው ዲያቆን ዳንኤል በቅርብ ጊዜ ደግሞ በሀገራችን ምናልባትም የመጀመሪያ የሆነውን እና በጐ ስራ የሰሩ ሰዎችን በማስመረጥ ለመሸለም ሰፊ ራዕይ የሰነቀ መርሃ ግብር ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ሁለተኛው መርሃ ግብርም የፊታችን ግንቦት 30 ቀን 2006 ዓ.ም ይካሄዳል። በዚህ መርሃ ግብር ተሸላሚ ለሚሆኑ ሰዎች የተለያዩ መስፈርቶች የተቀመጡ ሲሆን፤ እነዚህ፤ በሰላም፣ በሀገራዊ እርቅና ማኅበራዊ አገልግሎት፣ በእርዳታና ሰብአዊ ስራ፣ በኪነ-ጥበብ፣ በግብርና እና ኢንዱስትሪ፣ በመንግስታዊ ስራ ተቋማት ኃላፊነት፣ በቅርስ፣ ባህልና ቱሪዝም እንዲሁም በጥናትና ምርምር የላቀ ስራ የሰሩ ናቸው። ለዚህ መርሃ ግብር እንደመነሻ የሆነውም በ2005 ዓ.ም “በዳንኤል እይታዎች” ጦማር ሦስተኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ አምስት ሀገራዊ በጐ ሰሪዎች መሸለማቸው በኅብረተሰቡ ላይ የፈጠረው መነቃቃት መሆኑ ተገልጿል። በጉዳዩ ላይ ከዲያቆን ዳንኤል ጋር ቆይታ አድርገናል።

ሰንደቅ፡- የበጐ ሰው ምርጫ መርሃ ግብር ዓላማ ምንድን ነው?

ዲያቆን ዳንኤል፡- የምርጫው ዓላማ በዚህች ሀገር አዲስ ትውልድ ውስጥ የመመሰጋገን፣ የመከባበር እና የመሸላለምን ልማድ ለማስረፅ፣ መወቃቀስ እና መካሰስ ብቻውን ስለማይገነባ ለሀገር በጐ የሰሩትን ሰዎች መልካም ሰርታችኋል ብሎ ለማመስገን ነው። እነዚህ በጐ የሰሩ ሰዎች ተሸልመው ሌላው ሰውም ከእነሱ ምሳሌነትን የሚወርስበትን ስርዓት መዘርጋት አለብን በማለት ነው የተጀመረው።

ሰንደቅ፡- ለተመራጮች ሰባት ያህል መስፈርቶች ተቀምጠዋል። ከእነዚህ መስፈርቶች መካከል ደግሞ በሀገራዊ እርቅ ላይ የሰሩ መሆን እንዳለበት ተቀምጧል። በሀገራችን ይሄን መስፈርት የሚያሟሉ እና ውጤታማ እጩዎች ይኖራሉ?

ዲያቆን ዳንኤል፡- ብዙ ጊዜ እኛ ፖለቲካዊ እርቅ ላይ ስለምናተኩር ውጤታማ አይደለም እንላለን። ነገር ግን እዚህ ሀገር ውስጥ እርቅ የሚያስፈልጋቸው ሌሎች ጉዳዮችም አሉ። ለምሳሌ በብሔረሰቦች፣ በትላልቅ ተቋማት፣ በቤተሰቦች መካከል፣ በድርጅቶች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች አሉ። እነዚህን ችግሮች ከየመንደሩ ጀምሮ በመፍታት ነው ሀገራዊ የሚሆነው። በአንዴ ሀገራዊ አይሆንም። ችግሮች እንዳይፈጠሩ በማስተማርና በመምከር እንዲሁም ከተፈጠሩ በኋላ በቀላሉ እንዲፈቱ ያደረጉ በርካታ ሰዎች አሉ። እኛ ሁልጊዜ ከፍታ ቦታ ላይ ያለውን የፖለቲካ እርቅ ስለምናስብ እንጂ በርካታ ሰዎች አሉ። እንዲያውም እነዚህን ሰዎች ባለማሳደጋችን ነው ፖለቲካው ላይ ጠሩ ሚና የሚጫወት ሰው ያጣነው። እነዚህን ሰዎች እውቅና እየሰጠን እያከበርን እና እያመሰገንን ወደ ላይ ብናወጣቸው ኖሮ በእርቅ ሊፈቱ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮችን የሚፈቱ ሰዎችን እናገኝ ነበር።

ሰንደቅ፡- ሽልማት እየተሰጠ ያለው በግለሰብ ነው። ከግለሰብ ተላቆ በተቋም ደረጃ ለማድረግ ምን እየተደረገ ነው?

ዲያቆን ዳንኤል፡- ሀሳቡን ያነሳሁት እኔ ነኝ። ነገር ግን እየተሰራ ያለው ኮሚቴ ተዋቅሮ ነው። ኮሚቴው ብዙ ነገር እየሰራ ነው። በአንደኛው መርሃ ግብር ትንሽ ነው የሰራነው። ሁለተኛው ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሆኗል። በቀጣዩ ሦስተኛው ግን በተቋም ደረጃ ለማድረግ ታቅዷል። በቀጥታ ወደ ተቋም ያልገባነው ያለ እድገት የሚመጣ ማንኛውም እድል የመሰናከል ዕድል ስላለው ነው። ልምድና ተሞክሮ ተወስዶ ችግሮች አስቀድመው መፈታት አለባቸው። አንድ ልጅ እንዲወለድ ስለተፈለገ ብቻ በሦስት ወር አይወለድም። አቦርት ካልተደረገ በስተቀር የግድ ዘጠኝ ወሩን ጠብቆ ሲመለድ ጤነኛ ይሆናል። ተቋምም እድገቱን ጠብቆ ሲመጣ ነው ውጤታማ የሚሆነው።

ተቋሙን ከማቋቋማችን በፊት እነዚህን ልምዶች ስናገኝ የተሻለ ለመስራት ሌላው ቀርቶ ምርምር ለማድረግም ያግዘናል።

ሰንደቅ፡- ይህ የሽልማት ኮሚቴ በዘርፉ ልምድ እና ብቃት ያላቸው ሰዎች ስብስብ ነው?

ዲያቆን ዳንኤል፡- አዎ! የተለያዩ የሕግ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ በምህንድስና፣ በሳይንስና በመሳሰሉት ዘርፎች ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ስብስብ ነው።

ሰንደቅ፡- የተለያዩ የክብር ሽልማቶችን እና ማዕረጐችን የሚሰጡ ተቋማት እንዳሉ ይታወቃል። የእናንተ መርሃ ግብር ከመሸለም በተጨማሪ ምን የተለየ ነገር አለው?

ዲያቆን ዳንኤል፡- እስካሁን ድረስ እየሰራን ያለነው እውቅና መስጠት ነው። ወደፊት ግን ሰፊ እቅድ አለን። በሀገራችን ቀድሞ ይሰጡ የነበሩ አሁን ግን የጠፉ የማዕረግና የክብር ስሞች አሉ። በየብሔረሰቡ ለበጐ ሰዎች የሚሰጡ አሁን ጥቅም ላይ የማይውሉ ስሞችም አሉ። እነሱን ሁሉ መልሰን በየብሔረሰቡ ባህል አስደርገን ለመስጠት አስበናል።

ሰንደቅ፡- ተሸላሚው ወይም እጩው ግለሰብ በጐ ስራ እየሰራ ያለ መሆን እንዳለበት ተጠቅሷል። ከዚህ ቀደም በርካታ በጐ ስራዎችን ሰርተው ያለፉ ግለሰቦችንስ በምን መልኩ ለማስተናገድ ታቅዷል? ለምንስ በህይወት ያሉት ብቻ ሊመረጡ ቻሉ?

ዲያቆን ዳንኤል፡- አሁን ባለው ሁኔታ በምርጫው የምናካትተው በህይወት ያሉትን ብቻ ነው። ሲሞት የማይመሰገን የለም። በህይወት እያለ የማመስገን ልማድ ነው እኛ የሌለን። ሲሞቱ አከሌ ደግ ነበሩ፣ ቅን ነበሩ፣ ታታሪ ነበሩ፣ በጣም አዛኝ ነበሩ የሚባሉ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ይህን ምስጋና በህይወት እያሉ አይሰሙትም። እኛም በህይወት ያሉትን በመሸለም የጀመርነው ከህይወት መጀመር አለብን ከሚለው ተነስተን ነው።

ሰንደቅ፡- እንቅስቃሴያችሁ በብዙዎች ዘንድ የመታወቅ እና የህዝቡ ተሳትፎ ምን ይመስላል?

ዲያቆን ዳንኤል፡- እንዲያውም ከጠበቅነው በላይ እውቅና አግኝተናል። በሬዲዮም በቴሌቪዥንም እንዲሁም በሕትመትና ማኅበራዊ ሚዲያዎች በደንብ ታውቀናል።

ሰንደቅ፡- መራጮች በምን መልኩ ነው እየተሳተፉ ያሉት?

ዲያቆን ዳንኤል፡- ምርጫው የተለያዩ ሦስት ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው የጥቆማ ደረጃ ነው። በዚህ ደረጃ ብዙዎች ይሳተፋሉ። ሁለተኛው ደረጃ ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ምርጫ ነው። ይሄ ደግሞ በኮሚቴ የሚሰራ ስራ ነው። የመጨረሻውና ሦስተኛው ደረጃ የመጨረሻዎቹን ሰዎች መለየት ነው። ይሄ ደግሞ በዳኞች የሚሰራ ስራ ነው።

ሰንደቅ፡- ምርጫው ገለልተኛ ነው ብሎ ለመደምደም የሚያስደፍር ደረጃ ላይ ይገኝ ይሆን?

ዲያቆን ዳንኤል፡- በጣም ገለልተኛ ነው። አንደኛ ዳኞቹ እርስ በርሳቸው አይተዋወቁም። ባሉበት ሆነው ድምፅ ይሰጣሉ እንጂ አንዱ ዳኛ ከሌላኛው ጋር ቁጭ ብለው የሚነገጋገሩበት አጋጣሚ እንኳን የለም። በሁለተኛ ደረጃ እኛ ዳኞቹን ለህዝቡ ይፋ አናደርግም። ምክንያቱም እንዴት ሳትመርጠኝ ቀረህ መባል፤ እነሱም እገሌ ይቀየመኛል፣ አይቀየመኝም የሚል ነገር ውስጥ መግባት የለባቸውም። መራጮቹ ተመራጮቹን ያውቋቸዋል እንጂ ተመራጮቹ መራጮቹን አያውቋቸውም። እያንዳንዱ ዳኛም የየራሱን ነጥብ ነው የሚሰጠው። ስለዚህ ፈጣሪ ራሱ ከሚያውቀው ችግር በስተቀር እኛ ያን ያህል የገጠመን ችግር የለም።

ሰንደቅ፡- አንዳንዶች በሚሰሩት ስራ እውቅናን ለማግኘት እንደሚጥሩት ሁሉ አንተም ይህን ነገር ለእውቅና መፈለጊያ አስበኸው ይሆናል የሚል ስጋት የሚያነሱ ሰዎች ስላሉ ለእነዚህ ሰዎች መልስህ ምንድን ነው?

ዲያቆን ዳንኤል፡- እኔ እስከ አሁን ድረስ ያገኘሁትን እውቅናም የምቀንስበት መንገድ ባገኝ ነው ደስ የሚለኝ። እንኳን ተጨማሪ እውቅና ልፈልግ ያለኝንም መቀነስ እፈልጋለሁ። በእርግጥ እንዲህ አይነት ችግሮች ሊገጥሙ ይችላሉ። ስራ ሲሰራ እንዲህ ዓይነት ነገር ያጋጥማል። ውሾቹ ይጮሀሉ፤ ግመሎቹም ይሄዳሉ ስለሆነ መመሪያው ሊያጋጥም ይችላል። ነገር ግን ይሄንን እየተሻገርሽ መሄድ ነው። በስራ ማሳየት እንጂ ለተነገረብሽ ነገር ሁሉ መልስ ስትሰጪ መዋል አያስፈልግም። ስራው ራሱ ወደፊት መልስ ይሰጣል። እኔ ደግሞ ያን ያህል እውቅና የቸገረኝ አይደለሁም። እንኳን ተጨማሪ ልፈልግ ያለው እውቅናም በዝቶብኝ መቀነሻ አጥቻለሁ።

ሰንደቅ፡- የዘንድሮው መርሃ ግብር ከአምናው የተለየ ምን ይዟል?

ዲያቆን ዳንኤል፡- አምና የሸለምነው አምስት ሰዎችን ነበር። ከሚዲያ መዓዛ ብሩ፣ ንባብ እና መፅሐፍትን በማስፋፋት ደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደ፣ አዳዲስ የንግድ አሰራሮችን በማምጣት ዶ/ር እሌኒ ገ/መድህን፣ የቅርስና ባህል ጥበቃ ላይ በመስራት ንቡረዕድ ተፈራ መልሴ እንዲሁም የበጐ አድራጐት ስራን በመስራት የመቄዶኒያ መስራች ቢኒያም በለጠ ነበር። ዘንድሮ ደግሞ በየዘርፉ ሰባት ሰዎች ተመርጠው ይሸለማሉ።

ሰንደቅ፡- እነዚህ ተሸላማሚዎች እውቅናውን ካገኙ በኋላ የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት ምንድን ነው?

ዲያቆን ዳንኤል፡- እነዚህ ሰዎች ማኅበረሰቡ እውቅና ሰጥቷቸው ማኅበረሰቡን እንዲያገለግሉ ነው የሚፈለገው። ንቡረዕድ በተለይ በሰሜን ሸዋ አካባቢ ብዙ የፈራረሱ የአብነት ትምህርት ቤቶችን እንደገና እያሰሩ እና ቅርሶቻችንን እየጠበቁ ነው ያሉት። የ94 ዓመት እድሜ ባለፀጋ ቢሆኑም፤ በእዚህ እድሜያቸው በርካታ ስራዎችን እየሰሩ ነው የሚገኙት። እንዳለ ጌታም በተለይ በጉራጌ አካባቢ ንባብን በማስፋፋት እና በአዲስ አበባ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሊስትሮዎች ጭምር በሳንቲም ደረጃ መፅሐፍትን እንዲያነቡ እያደረገ ነው። ሌሎቹም በተሰማራበት ዘርፍ ከፍተኛ ኃላፊነት እየተወጡ ነው የሚገኙት።

እነዚህን ሰዎች በማሳወቃችን ሰዎች ከእነሱ ጋር እንዲሰሩ አድርገናል። ሁለተኛ ደግሞ እነሱም እንዲበረቱ አድርገናል።

ሰንደቅ፡- እንደ አብዛኞቹ የሽልማት ምርጫዎች የእናንተም ምርጫ ጥሩ ስም ባላቸው ግለሰቦች ላይ ያተኮረ ነው። ምንም እውቅና ሳያገኙ ብዙ ስራ የሰሩ እና እየሰሩ ያሉ ግለሰቦችን ለማካተት ለምን አልሞከረም?

ዲያቆን ዳንኤል፡- እኛ ከክልሎች ጀምሮ ለማካተት ሞክረናል። መቶ በመቶ ተሳክቶልናል ማለት አንችልም። ምክንያቱም እዚህ ሀገር መረጃ ለማግኘት በጣም ከባድ ነው። አንቺም እንደ ጋዜጠኛ ታውቂዋለሽ። አይደለም የሌሎችን ሰዎች መረጃ፤ ሰዎች የራሳቸውንም መረጃ አያውቁትም። አንዳንዶቹ የሰሩትን ስራ አውቀን ሄደን ስንጠይቃቸው የተሰናሰለ ታሪክ እንኳ የላቸውም። እኛ ሀገር ታሪክን መዝግቦ መረጃ ማስቀመጥ አልተለመደም። ስለዚህ ይህ ጉዳይ ለወደፊትም ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖ የሚቀጥል ነገር ነው። እኛ ብቻችንን የምንፈታው አይደለም። ጠቅላላ የሀገሪቱ ችግር ስለሆነ በጋራ የሚፈታ ችግር ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1465 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 732 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us