ህፃናት ነክ ወንጀል ፍትህ እያገኘ አይደለም

Wednesday, 11 June 2014 13:40

በአዲስ አበባ በተደረገ ጥናት እ.ኤ.አ. ከሰኔ 2005 እስከ ታህሳስ 2006 ዓ.ም ብቻ 1ሺ 666 የተለያዩ ወንጀሎች በህጻናት ላይ ተፈፅመዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 23 በመቶዎቹ ወይም 383 ያህሉ ህፃናት ፆታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ለጥናቱ ምላሽ ከሰጡት ህጻናት መካከልም 21 ነጥብ 3 በመቶዎቹ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ነው ጥቃቱ የተፈፀመባቸው። ከእነዚህ ህጻናት ውስጥ 70 ነጥብ 3 በመቶዎቹ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ 28 ነጥብ 1 በመቶዎቹ ደግሞ እድሜያቸው በ11 እና በ14 አመት መካከል ነው።

ተገዶ መደፈርን በተመለከተ አንድ በ2005 የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው በጎዳና ላይ ከሚኖሩ ሴት ህፃናት መካከል 15 በመቶዎቹ ተገደው ተደፍረዋል። እነዚህ ሴት ህፃናት ደግሞ እድሜያቸው ከ10 እስከ 24 ዓመት ነው። ኢትዮጵያ በዓለማችን ላይ በከፍተኛ ደረጃ በሴቶች ላይ በሚደርስ ጥቃት የምትታወቅ ሀገር ከመሆኗ የተነሳ በተለይ በሴት ህፃናት ላይ ከከፍተኛ አስገድዶ መደፈር ጋር የተያያዙ ፆታዊ ጥቃቶች ይደርሳሉ። አንድ የተባበሩት መንግስታት ያወጣው ሪፖርት እንደሚጠቁመው ከሆነ በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ሴቶች መካከል 60 በመቶዎቹ ፆታዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል።

ባለፈው ሳምንት በፌዴራልና በክልል ጠቅላይ ፍ/ቤቶች መካከል የህጻናት ፍትህ አስተዳደር መግባቢያ ሰነድ በተፈረመበት ወይይት መድረክ ላይ ጥንታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት በፌ/ጠ/ፍ/ቤት የህጻናት ፍትህ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊዋ ወይዘሮ ሰላማዊት ግርማይ እንደገለፁት፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ መካከል 53 በመቶዎቹ በህፃናት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። እነዚህ ህጻናት ደግሞ በእድሜያቸው ለጋነት እና ለጥቃት ተጋላጭ በመሆናቸው በቤት ውስጥ፣ በአካባቢያቸው፣ በትምህርት ቤት እና በተለያዩ አካባቢዎች ለተለያዩ ጥቃቶች ይጋለጣሉ።

ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሴቶችና ህፃናት ምርመራ ቡድን በበኩሉ ባወጣው መረጃ በዚህ በያዝነው 2006 ዓ.ም በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ በህፃናት ላይ የደረሱ ዘጠኝ ከባድ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ 8ቱ በመምሪያው ታይተዋል። በተጨማሪም ክስ ከቀረበባቸው 130 መካከለኛ ወንጀሎች መካከል 122ቱ በታቀደው ጊዜ ውስጥ የታዩ ሲሆን 8ቱ ወደ ቀጣይ እቅድ ተላልፈዋል።

ከዚህ በህፃናት ላይ ከሚፈፀሙት ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ወደ ኋላ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት በ2005 ዓ.ም 95 የአስገድዶ መድፈር፣ 12 የግብረሰዶም፣ 62 አካላዊ ጥቃት እንዲሁም 82 የአጥፊ ህጻናት ወንጀሎች ተፈፅመዋል።

እነዚህን በህጻናት ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ወንጀሎችን ለመከላከል ብሎም ከተፈፀሙ በኋላ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ተቋማት ተቋቁመዋል። ለህፃናት የሚደረገውን ጥበቃና ከለላ ለማጠናከር፣ ህጻናትን በጦርነት ውስጥ እንዳይሳተፉ እንዲሁም ወሲብ ነክ በሆኑ ፊልሞች ውስጥ ተሳታፊ እንዳይሆኑ የሚደረጉ የተለያዩ ኮንቬንሽኖችን ሀገራችን በተለያየ ጊዜ ፊርማ አፅድቃለች።

ከዚህ በተጨማሪም በፍትህ ስርዓት ውስጥ በተለያዩ ጉዳዮች የሚያልፉ ህፃናትን መብት እና ጥቅም ለማስጠበቅ በጠቅላይ ፍ/ቤት ስር የሚንቀሳቀስ የህፃናት ፍትህ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ተቋቁሟል። ይህ ፕሮጀክት ጽ/ቤት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ የህፃናትን መብት ለማስጠበቅ ነፃ የህግ ምክር፣ የማህበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ድጋፎችን በመስጠት ህፃናቱ በህገ-መንግስት እና በአለም አቀፍ አህጉራዊ ሰነዶች የተቀመጠውን በህግ ፊት እንደ ማንኛውም ሰው ፍትህ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ይሰራል።

በተያያዘም በዚሁ ፕሮጀክት ስር የሚንቀሳቀሰው የህፃናት የህግ ከለላ ማዕከል በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ይህ ማዕከል በዋናነት ለህፃናት ምቹ የሆነ የፍትህ አገልግሎት በመስጠት ረገድ በርካታ ተግባራትን ያከናውናል። ከእነዚህ ውስጥም በሚሰጠው ነፃ የህግ ድጋፍ ከቃል ምክር ጀምሮ ለፍርድ ቤትና ለተለያዩ አካላት የሚገቡ ፅሁፎችን እንዲሁም እንደ ጉዳዩ ውስብስብነት ፍርድ ቤት ጠበቃ መድቦ የመከራከር ስራ ይሠራል። ወንጀል ውስጥ ገብተው ለተገኙ ህፃናት በጎ ፈቃደኛ ጠበቃ መድቦም መብታቸውን ያስከብራል።

ሌላው ማዕከሉ የሚያከናውነው ተግባር የህፃናቱን ቤተሰቦች የማስማማት ስራ መስራት መሆኑን ወይዘሮ ሰላማዊት አብራርተዋል። በማስማማት ስራው አገልግሎት ፈላጊው ፈቃደኛ ሆኖ ሲገኝ ከቤተሰብ ችሎቶች ጋር በመቀናጀት ይሰራል። በዚህ በማስማማት ስራ ባለፈው አመት ብቻ 140 ጉዳዮች በስምምነት ማለቅ ችለዋል። ያለፈውን ስድስት ወር አፈፃፀም ስንመለከት ደግሞ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 133 ጉዳዮች በስምምነት ታይተዋል። ከእነዚህ ጉዳዮች መካከልም 24ቱ በሂደት ላይ ይገኛሉ። ከተጠናቀቁት 109 ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ 87ቱ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የህፃናትን ጥቅም በሚያስከብር ሁኔታ ተጠናቀዋል። ቀሪዎቹ 22 ጉዳዮች ደግሞ ወደ ፍርድ ቤት ክርክር ተሸጋግረዋል።

ለህፃናት ምቹ የህግ አገልግሎት በመስጠቱ ረገድ ሌላው እንደ አማራጭ የተወሰደው ደግሞ በዘረመል ምርመራ የህፃናቱን አባት የማረጋገጥ አሠራር ነው። ይህ ተግባር የህፃናቱን አባታቸውን የማወቅ መብት ከማስከበር በተጨማሪም፤ ህፃናት ቀለብ፣ ውርስ፣ አሳዳሪነት እና የመሳሰሉትን ጥቅሞች ለመወሰን ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተገልጿል። ይሁንና ይህ አይነቱ የህፃናትን መብት ማስጠበቂያ ዘዴ ካለው የመረጃ እጥረት እንዲሁም ምርመራውን ለማድረግ የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ በርካታ ህፃናት ይህን መብታቸውን ሳያገኙ ቀርተዋል።

ይህን ችግር ግምት ውስጥ ያስገባው የህፃናት የህግ ከለላ ማዕከል ባለፈው ዓመት ብቻ 28 የዘረመል ምርመራዎችን ወጪ በመሸፈን ህፃናት አባታቸውን እንዲያውቁ አድርጓል። የዘረመል ምርመራ ካደረጉ 28 ህፃናት መካከልም 26ቱ ምርመራ የተደረገላቸው ወንዶች የህፃናቱ አባቶች ሆነው ተገኝተዋል። ባለፉት አራት ወራት ውስጥም በተመሳሳይ በህፃናቱ እና አባት ናቸው ለተባሉ 17 ወንዶች ምርመራው ተደርጎ ከእነዚህ ውስጥ 15ቱ አባት ሆነው በመገኘታቸው ህፃናቱ ተጠቃሚ ሆነዋል።

እንደ ወይዘሮ ሰላማዊት ማዕከሉ ከሚያከናውናቸው ተግባራት ውስጥ በሶስተኛነት የተቀመጠው ደግሞ በፍትህ ስርዓት ውስጥ የሚያልፉ ህፃናት ማህበራዊ እና ስነልቦናዊ ድጋፍ እንዲያገኙ የማድረግ ስራ ነው። በዚህ ዘርፍ እነዚህ ህፃናት የመጠለያ እና የእንክብካቤ አገልግሎት እንዲያገኝ፣ ለህፃናት እና ወላጆች የገቢ ምንጭ መፍጠር፤ የተመጣጠነ ምግብ፣ የትምህርት እና የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያገኙ ማድረግ፤ እንዲሁም የስነ ልቦና ምክር፣ የፎስተር ኬር አገልግሎት፣ ህጻናትን ከቤተሰብ እና ከማህበረሰቡ ጋር የማቀላቀል ስራዎች ይሰራሉ። በዚህም በአጠቃላይ 523 አገልግሎቶች ተሰጥተዋል።

ጥቃት ደርሶብናል በማለት ወደ ፍርድ ቤት ለሚመጡ ህፃናትም የተለያዩ የፍትህ አገልግሎት ተሰጥቷል ሲል ሪፖርቱን ያቀረበው ደግሞ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሴቶችና ህፃናት ምርመራ ቡድን ነው። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሰራው ስራ ፍትህ የማሳጣት አፈፃፀሙን ከባድ ወንጀል 85 በመቶ፤ መካከለኛ ወንጀልን 90 በመቶ እንዲሁም ቀላል ወንጀልን 95 በመቶ ማስፈፀም ተችሏል። በተሰጠው ውሳኔም በህፃናት ላይ ወንጀል ፈፅመው የተገኙ እና ጥፋተኛ የተባሉ ግለሰቦች ከ6 ዓመት እስከ 19 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተደርጓል። በተጨማሪም የግብረሰዶም ወንጀል ፈፅመው ወደ ፍርድ ቤት የቀረቡ ከሁለት ዓመት ከስድስት ወር እስከ 19 ዓመት የሚደርስ ቅጣት እንዲያገኙ ተደርጓል።

በአብዛኛው በህፃናቱ ላይ እየተፈፀሙ የሚገኙት ወንጀሎች በግንዛቤ እጥረት የተነሳ በመሆኑ ይህን ችግር እስከ መጨረሻው ነቅሎ ለመጣል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተከናውነዋል። በዚህም ከህፃናት ጋር በቅርበት የሚሰሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እንዲሁም በፍትህ ስርዓት ውስጥ የሚያልፉ ህፃናትን ጥቅምና ደህንነት የበለጠ ማስከበር የሚያስችሉ ስልጠናዎች ይሰጣሉ።

ከዚሁ በተጨማሪም ህፃናት ተጠቂ ሆነው ወደ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ቃላቸውን የሚሰጡበት ምቹ የሲሲቲቪ ሲስተም እና ወንጀል ውስጥ ገብተው ለተገኙ ህጻናት ምቹ የሆነ ችሎት አደረጃጀት ስራም በ47 የክልል እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተሰርተዋል።

     በውይይት መድረኩ ላይ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ እና ከደቡብ ክልል የተጠናቀሩ ሪፖርቶች ይፋ ተደርገዋል። ከእነዚህ ሪፖርቶች በተለይ በደቡብ ክልል የሚገኙ አንዳንድ ፍርድ ቤቶች በህፃናት ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች በቂ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት የተሟላ ጽህፈት ቤት እና አስፈላጊ የሆኑ መሳሪያዎች እጥረት እንዲሁም የባለሞያ እጥረት እንዳለባቸው ነው የገለፁት። በለሎች ክልሎች ያለው በበጀት እና በሰው ኃይል እጥረት እንዲሁም በመሳሪያ እጥረት ችግር እንደልባቸው እያሰራቸው እንዳልሆነ ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ በማህበረሰቡ እና በህፃናቱ በራሳቸው ዘንድ ያለው የግንዛቤ እጥረት የተፈለገውን ያህል ስራ ከመስራት እንዳገዳቸው ገልፀዋል።


ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
1523 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 750 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us