You are here:መነሻ ገፅ»ምልከታ
ምልከታ

ምልከታ (168)

 

 

ድንጋይና ቅዝምዝም የሚወረወረው ጣፋጭ ፍሬ ያፈራ ዛፍ ላይ ስለሆነ በሊቀ መንበራችን ላይ እየሆነ ያለው አያስበረግገንም!

አብዱራህማን አህመዲን፤ ከሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ - በግል

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋን የተሰጠው የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት “የፀረ-ሙስና ዘመቻ” ነው። አንዳንዶቻችሁ “ታዲያ በሳዑዲ ዓረቢያ ጉዳይ ምን አገባህና ነው ብዕር ያነሳኸው?” የሚል ጥያቄ ታነሱ ይሆናል። በርግጥ ከዜግነት አኳያ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ጉዳይ አይመለከተኝም፤ አያገባኝም። ለዓመታት አፎቱ ውስጥ ከትቼው የነበረውን መንጎለ-ብዕር ጥቀርሻውን አራግፌ በሳዑዲ ዓረቢያ ጉዳይ ላይ እንዳነሳ ግድ ያለኝ ግን ነገሩ ወዲህ ነው።  

እኔ ብቻ ሳልሆን በርካታ ኢትዮጵያውያን ሳዑዲ ዓረቢያን አስመልክቶ ሃሳብ እንድንሰጥ ግድ የሚሉን በርካታ ጉዳዮች አሉ። በዋናነት ከአምስት መቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎቻችን በሳዑዲ ዓረቢያ ምድር መኖራቸው የሳዑዲ ዓረቢያን መንግስት ለመክሰስም ለመውቀስም እንድንነሳ ግድ ይለናል። እኔንም በብእሬ “ላሌ ጉማ”ን እንዳቀነቅን ያደረገኝ፤ “አንድ” ግን ደግሞ “እንደ ሺ የሚቆጠር” የኢትዮጵያ “ልጅ” በሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት “ታገተ” መባሉን ሰምቼ ነው። ይህም “የአንድ ሺ” የሆነ “የኢትዮጵያ ልጅ” ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ይባላሉ። ከአናቱ እስከ እግር ጥፍሩ በሙስና እንደነተበ ዓለም የሚያውቀው የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት የእኛውን ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲንን በሙስና የመወንጀል የሞራል ልዕልና የሌለው መሆኑ ነው ንዴቴን ያባሰው።

ወደ ጽሑፌ ዋና ፍሬ ነገር ከመግባቴ በፊት ለአንባቢዎቼ ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ሁለት ማሳሰቢያዎችን ማስቀደም ወደድሁ። የመጀመሪያው ማሳሰቢያዬ፤ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የማሰፍረው ሃሳብ የእኔ የግል አስተያየት እንጂ ከምሰራበት መስሪያ ቤት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው መሆኑ ይታወቅልኝ የሚል ነው። ሁለተኛው ማሳሰቢያዬ ደግሞ፤ ይህንን ጽሁፍ ያሰናዳሁት ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ውስጥ ካሉት ኩባንያዎች በአንዱ ውስጥ ሠራተኛ ስለሆንኩ ሳይሆን፣ ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት ስለ ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ የሚናፈሰው አሉባልታ ትክክል ስላልሆነ ትንሽም ብትሆን የማውቃትን ሀቅ በመናገር ከሊቀ መንበራች ጎን እንድቆም ህሊናዬ ስለጎተጎተኝ ነው።  

የጽሑፌን ይዘት በተመለከተ፤ በቅድሚያ ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በኢትዮጵያ ያላቸውን ኢንቨስትመንት አጀማመርና ተዛማጅ ጉዳዮችን በአጭሩ አነሳለሁ። በመቀጠል ስለ ሼህ ሙሐመድ በኢንተርኔትና በማህበራዊ ሜዲያዎች ተደጋግመው የሚነሱ አሉባልታና ጭፍን ወቀሳዎችን እያጣቀስኩ አቀርባለሁ። የፖለቲካ ሣይንስና የኢኮኖሚክስ ባለሙያ እንደመሆኔ ሰሞኑን የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ሼህ ሙሐመድ አል-አሙዲንን ያገተበትን ምክንያት በተመለከተ አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳት እሞክራለሁ።

እንደሚታወቀው ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት የጀመሩት ከደርግ ውድቀት በኋላ ነው። “ሚድሮክ ኢትዮጵያ” የተባለው የሼህ ሙሐመድ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት ሼህ ሙሐመድ ከአቶ ታደለ ይድነቃቸው ተሰማ ጋር “አል-ታድ” የሚል ኩባንያ አቋቁመው በኮንትራክሽን ዘርፍ ነበር የተሰማሩት። ሸራተን ሆቴል የተገነባውም በዚሁ በ“አል-ታድ” ይመስለኛል።

ከዚያ በኋላ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ተቋቁሞ በደርግ መንግስት ይዞታ ስር የነበሩ የልማት ድርጅቶችን መሸጥ ሲጀምር ሼህ ሙሐመድ አክሳሪና ሊዘጉ የተቃረቡ ተቋማትን በመግዛት በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከስራ አጥነትና ከበረንዳ አዳሪነት አድነዋል። ተጨማሪ አዳዲስ ኩባንያዎችንም በማቋቋም ኢንቨስትመንታቸውን አስፋፍተዋል። የሥራ እድል ፈጥረዋል።

ከኢንቨስትመንቱ በተጨማሪ በበጎ አድራጎት ስራቸው የሚታወቁት ሼህ ሙሐመድ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ 75 ኩባንያዎች አሏቸው። እነዚህም ኩባንያዎች በኮንስትራክሽን፣ በሆቴል፣ በፋይናንስና አገልግሎት፣ በእርሻና በመሳሰሉት የሥራ መስኮች የተሰማሩ ናቸው። በእነዚህ ኩባንያዎችም በአጠቃላይ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ ቋሚ፣ ጊዜአዊና የኮንትራት ቅጥር ሠራተኞች የሥራ እድል አግኝተዋል ተብሎ ይታመናል። ይህም የሰው ኃይል ሼህ ሙሐመድን ከመንግስት ቀጥሎ ብዙ የሥራ እድል የፈጠሩ ባለሃብት ያደርጋቸዋል።

በኢትዮጵያ በሚያደርጉት የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በርካታ ኢትዮጵያውን የንግድ ሸሪኮችን በማፍራትም ይታወቃሉ ሼህ ሙሐመድ። ሼህ ሙሐመድ በተለያዩ ሀገራት ያካበቱትን የንግድ ድርጅት የአሰራርና የአስተዳደር ስልት ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት በርካታ የሰው ኃብት ልማትና የቴክኖሎጂ ሽግግርም አድርገዋል።

ከላይ እንደተገለጸው በኢትዮጵያ ያሉት የሼህ ሙሐመድ ኩባንያዎች ብዛት 75 ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ሃያ አምስቱ ኩባንያዎች “ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ” በሚል ጃንጥላ ስር የተደራጁና በእውቁ መሐንዲስ በዶ/ር ኢንጅኔር አረጋ ይርዳው CEO/ፕሬዝዳንትነት የሚመሩ ናቸው። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢም በቴክኖሎጂ ግሩፑ ውስጥ ከተራ ኦፊሰርነት እስከ ማናጀርነት በማገልገል ላይ ይገኛል።

ወደ ሚድሮክ ከመምጣቴ በፊትም ሆነ አሁን ድረስ ሚድሮክን በተመለከተ በርካታ አሉባልታዎች ሲናፈሱ ሰምቻለሁ። ከአራት ዓመታት በላይ በድርጅቱ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ በሹክሹክታ ሲራገቡ የነበሩት አሉባልታዎች ሁሉ መሰረተ ቢስ መሆናቸውን በቅርብ ርቀት የተመለከትኩ በመሆኑ አንዳንዶቹን እያነሳሁ መሰረተ-ቢስነታቸውን ለማመላከት እሞክራለሁ።

የዛሬ 17 ዓመት ገደማ ጀምረው ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕን በማቋቋም በCEO/ፕሬዝዳንትነት እየመሩ ያሉት ዶ/ር ኢንጅኔር አረጋ ይርዳው ናቸው። ዶ/ር ኢንጅኔር አረጋ ይርዳው ይህንን ኃላፊነት ሲረከቡ በቴክኖሎጂ ግሩፑ ውስጥ የነበሩት አምስት ደካማ ኩባንያዎች ብቻ ነበሩ። ከአምስቱ ውስጥ የተሻለ ሕይወት አለው ሊባል የሚችለው ሚድሮክ ጎልድ ኃ. የተ. የግል ኩባንያ ብቻ ነበር። እሱም ቢሆን በ35 ፈረንጆች “የተወረረ” እና ከገቢው ወጪው የሚያመዝን ኩባንያ ነበር።

ዛሬ በቴክኖሎጂ ግሩፑ ስር ያሉት ኩባንያዎች ብዛት 25 ደርሷል። እንደ ትረስት፣ ኩዊንስ ማርኬት፣ አውቶ ሜይንቴናንስ፣… ወዘተ. የመሳሰሉት ኩባንያዎች ዶ/ር ኢንጅኔር አረጋ ራሳቸው “ሀ” ብለው ያቋቋሟቸው ናቸው። አንዳንዶቹ ለምሣሌ፤ ኢትዮ-ድሪም፣ ጂቱ እና አንሊሚትድ ፓኬጂንግ፣… የመሳሰሉት ደግሞ በአሰራር ድክመት ከስረው ሊዘጉ ሲያጣጥሩ ሼህ ሙሐመድ ለዶ/ር አረጋ እየሰጧቸው የአሰራር ስርዓታቸው እንዲሻሻልና እንዲያገግሙ የተደረጉ ናቸው።

ይህንን ሁሉ ለማንሳት የተገደድኩት በመቀጠል የማነሳቸውን አሉባልታዎች በጥልቀት ለማየት እንዲረዳኝ በማሰብ ነው። አሉባልታ ከሼህ ሙሐመድ ተለይቶ አያውቅም። ገና ወደ ኢትዮጵያ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የአሉባልታ ዝናብ ይዘንባል። የሀሜት ጎርፍ ይጎርፋል። የበሬ ወለደ ጅረት ይፈሳል። ሼህ ሙሐመድ ሼራተን ሆቴልን መገንባት እንደጀመሩ “ሰውየው ይህንን መሬት የወሰዱት ምኒልክ ቤተ-መንግስት አጠገብ ጣሊያን የቀበረውን ማርትሬዛ ብር በዘዴ ቆፍረው ለመውሰድ ነው…” ተብሎ መወራቱን አስታውሳለሁ። ሼህ ሙሐመድ ራሳቸው ይቆፍሩት ይመስል እንዲህ ያለ አሉባልታ መፈብረክ ትርጉም የለውም። የሆነ ሆኖ በቁፋሮው ሂደት እንኳን የማርትሬዛ ብር የኃ/ስላሴን ምስል የያዘ ሣንቲም ስለመገኘቱ አላህ ይወቅ! በሼህ ሙሐመድ በኩል ግን ሸራተን በተሰራበት አካባቢ ለነበሩ 500 ገደማ ተነሺዎች ወደ ሲኤምሲ በሚወስደው መንገድ በተለምዶ “አል-ታድ ሚካኤል” በሚባለው አካባቢ ቤት ሰርተው በነፃ መስጠታቸው እውነት ነው።

ሌላ መሰረተቢስ አሉባልታ እናንሳ። በቴክኖሎጂ ግሩፑ ስር ካሉ ኩባንያዎች ሼህ ሙሐመድ የሀገሪቱን ሀብት እየበዘበዘ ነው እንዲባሉ ያደረጋቸው ሚድሮክ ጎልድ ነው። ሼህ ሙሐመድ ከፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ አንዳንድ ሙትቻ ኩባንያዎችን እየገዙ ስማቸው እየገነነ ሲመጣ አሉባልታውም ተጠናክሮ ቀጠለ። ሚድሮክ ጎልድን እንደገዙ “ሼህ ሙሐመድ የሀገሪቱን ወርቅ እያወጡ ቀጥታ ውጪ ሀገር እየወሰዱ ቸበቸቡት…” የሚል ሀሜት በሰፊው መወራት ጀመረ። እውነታው ግን እንደዚያ አልነበረም።

ሚድሮክ ጎልድ ለጨረታ ሲቀርብ ከሚድሮክ ሌላ የፈረንሳይና የሌሎች ሀገሮች ተጫራቾች ተሳትፈው ነበር። ሼህ ሙሐመድ በ170 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ለመግዛት ባቀረቡት ዋጋ አሸነፉ። የሚገርመው ነገር ሼህ ሙሐመድ ካሸነፉ በኋላ ተጨማሪ 50 ሚሊዮን ዶላር ከፍለው ሚድሮክ ጎልድን በ220 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነበር የገዙት።

በነገራችን ላይ ሼህ ሙሐመድ ሚድሮክ ጎልድን ሙሉ ለሙሉ አይደለም የገዙት። የኢትዮጵያ መንግስትም ባለ ድርሻ ነው። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያን መንግስት በመወከል የስራውን ሂደት የሚከታተለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሳያውቀው አንዲት ግራም ወርቅ አትሸጥም። የመሸጫ ዋጋውም የሚወሰነው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነው።

መንግስት ከወርቅ ሽያጩ የሚገኘውን የትርፍ ድርሻውን (dividend) በሂሳብ ባለሙያ እየተሰላ፣ በኦዲተር እየተረጋገጠ በየዓመቱ ይወስዳል። የትርፍ ግብርም ይወስዳል። የሮያልቲ ክፍያም ይወስዳል። ከዚህ በተጨማሪ ሼህ ሙሐመድ ከራሳቸው የትርፍ ድርሻ ላይ ለክልሉ መንግስት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በችሮታ ይሰጣሉ። አሁንም ከዚህ በተጨማሪ ሼህ ሙሐመድ ከራሳቸው ድርሻ ላይ ለአካባቢው ህብረተሰብ ት/ቤት፣ የጤና ተቋማትና ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮችን ገንብተዋል። መንገድ ሰርተዋል። ይህንን ሀቅ የአካባቢው ህብረተሰብና አባ ገዳዎች ጭምር ጠንቅቀው ያውቁታል። መላው የድርጅቱ ሰራተኛም ያውቀዋል። ሼህ ሙሐመድ እየዘረፉት ነው የሚባለው ሚድሮክ ጎልድ ይህንን የሚመስል አሰራር ያለው መሆኑን እኔም አይቻለሁ።   

ሌላው በየኢንተርኔቱና በማህበራዊ ሜዲያ ሼህ ሙሐመድን በተመለከተ ሲናፈስ ያየሁት አሉባልታ “ሼህ ሙሐመድ ሀሉንም የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በርካሽ ዋጋ እንዲገዙ ተመቻችቶላቸዋል…” የሚል ነው። ይህ የወሬ ቱማታ ተራ ስም ማጥፋት መሆኑን ለማሳየት አንዳንድ እውነታዎችን ልጥቀስ።

ከ1987 እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜአት ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ 260 የሚሆኑ የቀድሞ መንግስት የልማት ድርጅቶቸን በሽያጭ ለግለሰቦች አስተላልፏል። ከነዚህ ውስጥ ሼህ ሙሐመድ የገዟቸው 23 ብቻ ናቸው። (ቀሪዎቹ 237 ኩባንያዎች ለሌሎች ለውጭ ሀገርና ለኢትዮጵያውያን ባለ ሀብቶች ነው የተሸጡት) በመቶኛ ሲሰላ ሼህ ሙሐመድ የገዟቸው ዘጠኝ በመቶ (9%) ያህሉን ብቻ ነው ማለት ነው። ይህንኑም ከሌሎች ጋር ተጫርተው እየተሸነፉም እያሸነፉም ያገኙት ውጤት ነው። ሼህ ሙሐመድ ከመንግስት “ልዩ ድጋፍ” ቢረግላቸው ኖሮ ቢያንስ ቢያንስ ሃምሳ በመቶ የሚሆኑትን ኩባንያዎች በገዙ ነበር።

እዚህ ላይ “ሼህ ሙሐመድ የገዟቸው ኩባንያዎች የተሻለ ይዞታ ያላቸውንና አትራፊዎቹን ነው” የሚል ተጫሪ አሉባልታ ይነሳ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሼህ ሙሐመድ የገዟቸው ኩባንያዎች ከስረው በመዘጋት ሂደት ላይ የነበሩ ወይም ሊዘጉ አንድ ሀሙስ የቀራቸው አሊያም ሊሸጡ ባለመቻላቸው መንግስት መጣያ አጥቶ የተቸገረባቸው ድርጅቶች ናቸው። ለምሳሌ በዓይኔ ያየሁትን ልንገራችሁ። ሼህ ሙሐመድ ከገዟቸው ውስጥ አንዱ መልጌ ወንዶ የሚገኘው እርሻና የቲማቲም ድልህ ማምረቻ ፋብሪካ ነው። ይህ ፋብሪካ በ1930ዎቹ በጣሊያን ቅኝ ገዢዎች የተቋቋመ፣ መለዋወጫ የማይገኝለት፣ በሞዲፊክ መከራውን ያየ ሙት ፋብሪካ ነው። ያንን ፋብሪካ ያመረተው ፋብሪካ በምድር ላይ የሚኖር አይመስለኝም።

ማገናዘብ የሚችል ህሊና ላለው ሰው እነዚህን ሞት አፋፍ ላይ የነበሩና አክሳሪ ስመ ኩባንያዎችን ሼህ ሙሐመድ መግዛታቸው ያስመሰግናቸው እንደሆነ እንጂ ከቶም የሚያስወቅሳቸው ሊሆን አይችልም። እንኳን እጅ መንሻ ሰጥተውና ከባለስልጣት ጋር ተሞዳሙደው ሊገዟቸው ይቅርና ከገዟቸው በኋላ አስፈላጊውን ማሻሻያ እንዳያደርጉ እንኳ መንግስት “የንግድ ዘርፉን መለወጥ አትችሉም” የሚል አስገዳጅ ድንጋጌ በማስቀመጡ ሁኔታው ተጨማሪ ኪሳራን የሚያስከትል መሆኑ ይታያል። እንደ ዶ/ር ኢንጅኔር አረጋ ያለ ሌት ተቀን እንቅልፍ አጥቶ የሚሰራ ጥበበኛ የንግድ ሥራ መሪ ባይዛቸው ኖሮ ለሼህ ሙሐመድ እንኳን ትርፍ ሊያስገኙ ከስረው ይዘጉ ነበር። ይህ ሁኔታ ደግሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችና ቤተሰባቸውን ጎዳና ላይ እንዲወጡ ያደርግ ነበር።

እነዚህ ሁኔታዎች የሚያሳዩት ሼህ ሙሐመድ አላግባብ ሀብት ማግበስበሳቸውንና በሙስና መዘፈቃቸውን ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያዊ ለሀገራቸውና ለወገናቸው የቁርጥ ቀን ደራሽ መሆናቸውን ነው። እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ እወዳለሁ። ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ሼህ ሙሐመድ በኢትዮጵያ ውስጥ በሙስና የተዘፈቁበት ሁኔታም ሆነ በሙስና ያፈሩት ሀብት የለም አልኩ እንጂ “በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት 75 የሼህ ሙሐመድ ኩባንያዎች ውስጥ ሙስና የሚባል ነገር የለም፣ የሼህ ሙሐመድ ሀብትና ንብረት በነቀዙ ሰራተኞቻቸውና የኩባንያ መሪዎች አልተመዘበሩም ወይም አይመዘበሩም” እያልኩ እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ አደራ እላለሁ።

በኢትዮጵያ ያለውን የሼህ ሙሐመድን የኢንቨስትመንት ሁኔታ ካየን በኋላ ውጪ ወዳለው ሁኔታ ማምራት ተገቢ መሆኑን አምናለሁ። እንደሚታወቀው ሼህ ሙሐመድ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ከመጀመራቸው በፊትም ሆነ በኋላ በአሜሪካ፣ በአውሮፓም ሆነ በአፍሪካ፤ እንዲሁም በሳዑዲ ዓረቢያ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች እንዳላቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ በእነዚህ ሀገራት ያላቸው የንግድ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ስለማላውቅ ምንም ነገር ማለት አልችልም። በመሆኑም ከዚህ በመቀጠል ማንሳት የምፈልገው ሰሞኑን በሼህ ሙሐመድ ላይ በሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት የተፈጸመቀውን እገታና የእገታውን ምክንያት በተመለከተ ይሆናል።

ሰሞኑን ሼህ ሙሐመድ የታገቱበትን ምክንያት በተመለከተ በመገናኛ ብዙሃን፣ በኢትዮጵያውያን ማህበራዊ ሜዲያዎችና በህብረተሰቡ ዘንድ ብዙ ብዙ ነገር እየተወራ ነው። የሼህ ሙሐመድ ነገር ይህን ያህል መወያያ የሆነው ሼህ ሙሐመድ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው እንደ ዜጋ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ካላቸው ወደር የማይገኝለት ሚና በመነሳት ስለሆነ የሚያስገርም ጉዳይ ሆኖ አይታየኝም። ስለሆነም የሼህ ሙሐመድ ጉዳይ መታየት ያለበት ከአንድ ተራ ዜጋ ጉዳይ አንጻር ሳይሆን እኚህ ትልቅ ባለሀብት ካላቸው ጉልህ ሚና አኳያ መሆን ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ።

ቀደም ሲል መግቢያየ ላይ እንደጠቀስኩት በሙያየ ፖለቲካል ኢኮኖሚስት ነኝ። እናም የሼህ ሙሐመድን የእስር ምክንያት ከፖለቲካም ከኢኮኖሚም አኳያ ለመዳሰስ እሞክራለሁ። በዚህ መሰረት ሦስት አመላካች ነጥቦችን ለማንሳት እወዳለሁ። የመጀመሪያው ነጥብ፤ ሼህ ሙሐመድ የአሜሪካ መንግስት የትኩረት ዒላማ መሆናቸውን በተመለከተ ነው።

ብዙዎቻችን እንደምናውቀው እ.ኤ.አ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ አሜሪካ “አል-አሙዲ የአሸባሪዎች ደጋፊ ሊሆን ይችላል” በሚል ጥርጣሬ በሼህ ሙሐመድ ላይ ክትትል ታደርግ እንደነበር ይነገራል። በተለይም ቦስኒያ ውስጥ በሚንቀሳቀስና ለአል-ቃዒዳ ድጋፍ ያሰባስባል ተብሎ በሚጠረጠር አንድ የእርዳታ ድርጅት ሰነድ ውስጥ ስሙ ተገኝቷል በሚል ሰበብ በሼህ ሙሐመድ ላይ ክትትል እንደሚደረግ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ይሁን እንጂ፤ ቦስኒያ ውስጥ በሚንቀሳቀሰው የእርዳታ ድርጅት ሰነድ ውስጥ የሼህ ሙሐመድ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ታዋቂ ሰዎችና ባለሃብቶች ስም ተገኝቶ ስለነበርና እነሱም ተጠይቀው ለድርጅቱ እርዳታ መስጠታቸውን አምነው፤ ነገር ግን ድርጅቱ ለአል-ቃዒዳ መስራቱን እንደማያውቁ ገልጸው ስለነበር አሜሪካም በወቅቱ አላሰረቻቸውም ነበር። ስውር ክትትሉ ግን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አልተቋረጠም። አሁን ትራምፕ ወደ ስልጣን ሲመጡና የሳዑዲ አዲሶቹ ልዑላን “ለአልጋየ ያሰጋል ወይም አድርግ ያልነውን አላደረገም” የሚል ስጋት ሲያድርባቸው ይህቺን ካርድ መዘው እያስፈራሩባት እንደሆነ አስተያየት የሚሰጡት የፖለቲካ ተንታኞች ብዙዎች ናቸው።

ሁለተኛው ነጥብ፤ ሼህ ሙሐመድ ኢትዮጵያዊ ቁንጮ ባለ ሀብት በመሆናቸው የታሰሩበት ምክንያት ከህዳሴው ግድብ ጋር ሊያያዝ ይችላል የሚል ነው። እንደሚታወቀው የህዳሴ ግድብ በመሰራቱ የግብፅ መንግስት “ጥቅሜ ይነካል” በሚል መንፈስ ሳይሆን “በምቀኝነት መንፈስ” የግድቡን ሥራ ለማደናቀፍ እንቅልፍ አጥቶ ይዋትታል። አንዴ የኤርትራን መንግስት በመደገፍና በማስተባበር፣ ሌላ ጊዜ በውጪ ሀገራት ያሉ ተቃዋሚዎችን በማሰባሰብና መድረክ በመስጠት፣ ቆየት ብሎ ሶማሊያ ውስጥ ያለውን አልሸባብን በማንቀሳቀስ፣… ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የግብፅና የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስታት በፍቅር ክንፍ ማለታቸው ይስተዋላል። ግብፃዊ ሹማምንት ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ገባ ወጣ ማለት አብዝተዋል። በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት በመጠናከሩ ለ50 ዓመታት በግብፅ እጅ የነበረች ደሴትን ለሳዑዲ ዓረቢያ እስከ መስጠት ደርሷል። አዲሲቷ ደሴት ደግሞ ለሳዑዲ ንጉሳውያን ቤተሰቦች ተጨማሪ የመዝናኛ መንደር ለመመስረት ታስፈልግ ይሆናል።

ግብፅም ብትሆን ያልተረጋጋ ህዝቧ ጋር እየተነታረከች ደሴትን ያህል ነገር “በብላሽ ትሰጣለች” ብሎ ማሰብ፤ ማሰብ አለመቻል ነው። የሳዑዲ መንግስት ደሴት ካገኘ በኋላ ግብፅ “አድርግ” ያለቺውን “አያደርግም” ብሎ ማሰብም፤ ማስተንተን አለመቻል ነው እንጂ ሌላ ሊባል አይቻልም።

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚሆን ገንዘብ ማሰባሰብ እንደተጀመረ ሼህ ሙሐመድ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል። እዚህ ላይ መታየት ያለበት ሼህ ሙሐመድ ያበረከቱትን 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ብቻ ሳይሆን፤ የእርሳቸውን አርአያነት ተከትለው ሌሎች የሀገሪቱ ባለሀብቶች ያደረጉት መጠነ ሰፊ ተሳትፎ ያስገኘውን ውጤት ነው። እንዲህ ያለው የኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የትብብር መንፈስ ደግሞ በግብፆች ዘንድ በስጋት የሚታይ “መጥፎ ተግባር” ነው። እናም እንዲህ ያለውን ሁኔታ በተገኘው አጋጣሚ እንዲቋረጥ ለማደረግ “ይህንን ሰው አስደንግጡልን” የሚል መልእክት ከግብፅ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ “አይተላለፍም” ብሎ ማሰብ ቂልነት ነው።

ሦስተኛው ነጥብ፤ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የተደረገ ዳሰሳ ነው። ከርቀት ስናየው በዚህ ወቅት በሳዑዲ ዓረቢያ ያለው “አልጋ” የረጋ አይመስልም። ወጣቱ ልዑል የለውጥ ኃይል (ሪፎርሚስት) ናቸው ይባላል። አዘማኝ (ሞደርኒስት) ናቸውም እየተባለ ነው። በቅርቡ ካከናወኗቸው አውሮፓ አስተኔ ተግባራት ውስጥ ሴቶች መኪና እንዲነዱ ፈቅደዋል። የመናፍስት ቀን (Halloween Day) በሳዑዲ ዓረቢያ እንዲከበር ፈቅደዋል። ለአንድ ሮቦት ዜግነት ሰጥተዋል… እንዲህ ያለው ተግባራቸው ግን በሳዑዲ ዓረቢያ “ጎምቱዎች” የተወደደላቸው እንዳልሆነና ውስጥ ውስጡን “የመፈንቅለ ስልጣን” ሴራ እየተውጠነጠነ እንደነበርም ይወራል። ተጽእኖ ፈጣሪና ተሰሚነት ካላቸው የሳዑዲ ዓረቢያ “ጎምቱዎች” ውስጥ ደግሞ ሼህ ሙሐመድ አንዱ መሆናቸውን ታሳቢ ማድረግ ይቻላል። እናም የአሁኑ የመንግስት እርምጃ ጠንካራ የፖለቲካ ክንድን ተጠቅሞ እነዚህን “ጎምቱዎች” ዝም ለማስባል የተለቀቀ “shock therapy” ይመስላል።

ከዚህ በተጨማሪ ከሼህ ሙሐመድ ጋር የተያያዘ ሌላ ዓቢይ ጉዳይ ማንሳት ይቻላል። ይኸውም የሳዑዲ መንግስት በቀይ ባህር ዳርቻ ከጂዳ ከተማ ትንሽ ራቅ ብሎ “አብደላ” የተባለ አዲስ ከተማ (Abdela City) ለመቆርቆር አስቧል ይባላል። ይህም ከተማ ለሳዑዲ ዓረቢያ ዜጎች የተከለከለ (የማይገቡበት)፣ የውጪ ሀገር ዜጎች የሚኖሩበትና እንደልባቸው የሚሆኑበት፣ መጠጥም ጭፈራም… የተፈቀደበት ከተማ እንደሚሆን ይወራል።

በአሜሪካ በኩል፤ ይህንን ከተማ የአሜሪካ (የእነ ትራምፕ) የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች እንዲሰሩት ይፈለጋል። በሳዑዲ ዓረቢያ በኮንስትራክሽን ሥራ ታዋቂ የሆኑት የቢላደን ቤተሰብ እና የእነ ሼህ ሙሐመድ ድርጅቶችም “አገር በቀሎቹ እኛ እያለን የውጪ ኩባንያ ሊመጣ አይገባም” የሚል አቋም መያዛቸውና ንትርክ መነሳቱ ይነገራል።

በሌላ በኩል የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ይህንን ከተማ ለመገንባት በቂ በጀት የሌለው በመሆኑ ቁንጮ ቱጃሮቹ ገንዘብ እንዲሰጡት ካለበለዚያ ትልቁን የነዳጅ ሀብት ድርሻ (ሼር) ለህዝብ እንደሚሸጥ ያስጠነቅቃል። ከወደ ቱጃሮ በኩል ደግሞ፤ “የነዳጅ ሀብት ድርሻችን ተቀንሶ ለህዝብ አይሸጥም። ለከተማው መገንቢያ ገንዘብ እንሰጣለን። ገንዘቡን የምንሰጠው ግን የግንባታ ስራው ለእኛ ከተሰጠን ነው…” የሚል ወጣሪ ቅድመ-ሁኔታ ሲነሳ የሳዑዲ መንግስት በበኩሉ “እምቢ ካላችሁ በሙስና ሰበብ እናንተን አስሬ ሀብታችሁን እወርሳለሁ…” የሚል አቅጣጫን በመከተል ዋና ዋናዎቹን ሰዎች ማገቱ በአረብ ሀገራት በስፋት እየተወራ ነው።

ለእነ ሼህ ሙሐመድ መታሰር ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎችንም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መላምቶችን (Hypothesis) መዘርዘር ይቻላል። ይሁን እንጂ፤ የፈለግነውን ያህል መላምት ስንደረድር ብንውል እነ ሼህ ሙሐመድ የታሰሩበትን ምክንያት እቅጯን መናገር አይቻልም። እውነቱን የሚያውቀው አንድዬ የሆነው ፈጣሪ አምላክ - አላህ ብቻ ነው።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ እነዚህን ሰዎች ያሳሰራቸው ከጀርባ እየተውጠነጠነ ያለ ፖለቲካዊ ሴራ (Political Framing) ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ይቻላል። ፖለቲካዊ ሴራ (Political Framing) ማለት “አንድን ንፁህ ግለሰብ፣ ድርጅት ወይም ማህበረሰብ… ባልዋለበትና ባልሰራው ኃጢያት አቅዶና ሆን ብሎ፣ ሴራ በመጎንጎንና ሰነዶችን በማቀነባበር በህዝብና በፍትህ አካላት ተጠያቂ ለማድረግ የሚሸረብ ፖለቲካዊ ሴራ” ማለት ነው ይላሉ በመስኩ ጥናት ያደረጉ ተንታኞች።

እንዲህ ያለው የሴራ ፖለቲካ አሜሪካንን ጨምሮ በአውሮፓና በሌሎችም በርካታ ሀገሮች ይፈጸማል። በእኛም በገር (የሩቁን ዘመን ትተን) ከአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የስልጣን ተቀናቃኝን፣ አልታዘዝም ባይን፣ አፈንጋጭን፣… ለማንበርከክ መንግስታት የሚጠቀሙበት የሸርና የተንኮል መንገድ ነው። (ወንድማችንን ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲንን ከእንዲህ ያለው ሸፍጥ አላህ ይጠብቃቸው!!!)

ሳር ቤት አካባቢ ወደሚገኘው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ (መቻሬ ሜዳ) በሄድኩ ቁጥር ከሼህ ሙሐመድ ትልቅ ፎቶግራፍ ስር የተጻፈ ሁሌም ቀልቤን የሚስብ ጥቅስ አለ። እንዲህ ይላል፤ “ፈረሱም ሜዳውም እነሆ። አንድና አንድን በማቀናጀት አስር ለማድረግ በርትታችሁ ስሩ” ይላል። ይህ ጥቅስ ከሼህ ሙሐመድ ንግግር ላይ የተወሰደ ነው። መቼና የት እንደተናገሩት ባላውቅም ሼህ ሙሐመድ ይህንን “ሚሽን” (ተልእኮ) የሰጡት በኩባንያዎቻቸው ለሚሰሩ ሠራተኞቻቸው መሆኑ ነው።

መጀመሪያ ላይ አንድ እና አንድ ተቀናጅቶ እንዴት አስር ሊሆን እንደሚችል አልገባኝም ነበር። በኩባንያዎቹ ያለውን ሥራና የአሰራር ስርዓት እንዲሁም በየዓመቱ የሚመዘገበውን ውጤት ሳይ ይህ ሼህ ሙሐመድ ለሠራተኞቻቸው የሰጡት ሚሽን ግልጽ ሆኖልኛል።

“ድንጋይና ቅዝምዝም የሚወረወረው ጣፋጭ ፍሬ ያፈራ ዛፍ ላይ ነው” እንዲሉ ሼህ ሙሐመድ የታሰሩት ታላቅ የስራ ሰው በመሆናቸው ነው እንጂ በነውረኛ ነገር ውስጥ ተገኝተው እንዳልሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ስራቸው ህያው ምስክር ነው። እንዲህ ያለው ውንጀላ እና የሊቀ መንበራችን መታሰርና መንገላታት አያስበረግገንም! እርሳቸው ታሰሩም ተፈቱ፣ በሀገር ውስጥ ኖሩም አልኖሩ… እርሳቸው የሰጡንን አንድ እና አንድን በማቀናጀት አስር የማድረግ ተልእኮ ለማሳካት መላው ሰራተኛ በበለጠ ትጋትና ጥንካሬ የምንሰራ መሆኑን ወዳጅም ጠላትም ሊያውቀው ይገባል።

በመጨረሻም፤ የሳዑዲ ዓረቢያን የሙስና ዘመቻ በተመለከተ አንዲት ነገር ለማንሳት ወደድሁ። በቅርቡ የሳዑዲ ንጉሳዊ ቤተሰቦች ወደ ፈረንሣይ ፓሪስ ለመዝናናት ሄደው ነበር። መሄዳቸው የሚገርም ነገር አይደለም። የሚገርመው ነገር ከንጉሳዊ ቤተሰቡ ጋር ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ፈረንሳይ ተጭኖ የሄደው “ጓዝ” ብዛት ነው። ክብደቱ 25 ቶን (2,500 ኩንታል) ነበር። ይህንን “ጓዝ” ከአውሮፕላን ማረፊያ ወደ አረፉበት ሆቴል ለማጓጓዝ፣ ለመጫንና ለማውረድ የነበረውን ውጣ ውረድ አስቡት። ሆቴሉ ውስጥ ወደ ፎቅ ለማውጣት የሆቴሉ አሳንሳር አልችል ብሎ እንደነበርም ዘገባዎች ያመለክታሉ።

ለመሆኑ ይህ ሁሉ “ጓዝ” ምንድነው? ልብስ ከሆነ አንድ ሁለት ሻንጣ ይበቃል። ቤትና አገር የለቀቁ ይመስል ዐረቢያን መጅሊስ፣ መኪናና ምግብ ጭምር ጭኖ ሽርሽር ከመሄድ በላይ ብክነትና ሙስና አለ? የሳዑዲ መንግስት ሙስናን እዋጋለሁ ማለቱ ከልቡ ከሆነ መጀመሪያ በንጉሳዊ ቤተሰብ የሚፈጸመውን ልቅ ኑሮና መረን የለሽ ብክነት እንዲቀር በማድረግ ቢጀምር መልካም ነው። በርግጥ ሙስናን ከልብ እንዋጋ ካሉና ዘመቻውንም ከቤት ከጀመሩ የንጉሳዊ ቤተሰቡ መኖሪያ ማረሚያ ቤት መሆኑ ጥርጥር የለውም። ይህንን ሳያደርጉ በሌሎች ላይ ጣት መቀሰሩ ግን የአንድ ሰሞን ሆይ ሆይታን ከመፍጠር የዘለለ ትርጉም አይኖረውም።

ሰሞኑን ሼህ ሙሐመድ መታሰራቸው እንደተሰማ “የድርጅቱ ባለቤት የሉም፣ ታስረዋል፣ አይመጡም…” በሚል አስተሳሰብ አንዳንድ ወገኖች በአንዳንድ ኩባንያዎች ላይ ያሳዩትን አሉታዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ እና ከሼህ ሙሐመድ መታገት ጋር የተያያዙ ተጨማሪ ሃሳቦችን ይዤ ሳምንት እመለስበታለሁ። እስከዚያው ድረስ ሊቀ መንበራችን እንደሚፈቱም ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ - ኢንሻ-አላህ!!!

 

በነብዩ ምክሩ ወ/አረጋይ
(በማናቸውም ፍ/ቤቶች ጠበቃና የህግ አማካሪ)

ለዚህ ጹህፍ መነሻ የሆነው የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ.20938 በቅጽ 4 በሰጠው ውሳኔ መሰረት በተዋረድ የፌደራል ፍ/ቤቶች የበታች የቤተሰብ ችሎቶች "በሁኔታ ፍቺ" ተፈጽሟል በሚል በሚሰጧቸው ውሳኔዎች ላይ የግሌን አስተያየት ለማቅረብ እና ለውይይት መነሻ ይሆን ዘንድ ለተጓዥ አንባቢ እንዲሆን በአጭሩ የተሰናዳ ነው።


ስለ ጋብቻ በቤተሰብ ህጎቻችን ለውይይት የሚበቃ ትርጓሜ የለም። ጋብቻ የተለያዩ ፀሐፋት የሰጡት ትርጓሜ ሀገራዊና ውጤት በሚያወጣ መልኩ ስንተረጉመው በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል መንፈሳዊና ቁሳዊ ጥምረት በመፍጠር ዘላቂ ቤተሰብ ለመመስረት የሚደረግ ጥምረት ነው። ይህ ጥምረት በተሸሻለው የቤተሰብ ህግ ቁጥር 213/1992 አንቀጽ 1 መሰረት ጋብቻው በክብር መዝገብ ሹም (በተለምዶ ማዘጋጃ ቤታዊ ጋብቻ)፤ ከተጋቢዎቹ በሁለቱም አልያም በአንዳቸው ሃይማኖት ወይም በሚኖሩበት አካባቢ ባህል መሰረት የሚፀና ጋብቻ ሊቋቋም እንደሚቻል የተደነገገ ሲሆን ከሶስቱ በአንዱ የጋብቻ አፈፃፀም ሥርዓት የተፈፀመ ጋብቻ በእኩል ደረጃ ህጋዊ ዕውቅና ያለው፤ ህጋዊ ውጤቱም ጋብቻ ከተፈፀመ ቀን የሚጀምር ሆኖ በሶስቱም የጋብቻ አፈፃፀም ሥርዓቶች የተፈፀሙ ጋብቻዎች በክብር መዝገብ ላይ መመዝገብ ያለባቸው መሆኑ የህጉ ተጨማሪ ድንጋጌዎች ናቸው።


ጋብቻ በሶስት አይነት የአፈፃፀም ሥርዓቶች ቢፈፀሙም ፍቺ ግን ሊፈፀም የሚገባው በፍርድ ቤት ብቻ መሆኑን የቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 76፤ 82 እና 75 የጋራ ንባብ ያሳያል። በዚሁም በማናቸውም አይነት የጋብቻ አፈፃፀም ሥርዓቶች የተቋቋሙ ጋብቻዎች በማፍረስና በውጤቱ ረገድ አንድ ዓይነት መሆናቸውን ልብ ይሏል።


ጋብቻ በሶስት አይነት የአፈፃፀም ሥርአቶች ቢቋቋምም ፍቺ ሊፈፀም የሚገባው በፍ/ቤት የፍቺ ውሳኔ ሲሰጥ ብቻ መሆኑ ተደንግጎ ሳለ "በሁኔታ ፍቺ" ከየት መጣ? ፍርድ ቤቶቻችንስ እንዴት እየተረጎሙት ነው?


የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2/1/የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ የፌደራል ወይም የክልል ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅነት ያለው የሕግ ትርጉም በመሆኑ፤ እነዚህ ትርጉሞቹን በተለያዩ ቅጾች ሲያወጣ ቆይቷል። ከነዚህ ውሳኔዎች ውስጥ በቅጽ 4 ላይ ታትሞ የወጣው በሰ/መ/ቁ20938 በወ/ሮ ሸዋዬ ተሰማ እና ወ/ሮ ሳራ ልነጋነ ሙግት የተሰጠው የህግ ትርጉም ውሳኔው በጥቅሉ ሲታይ ጋብቻ በፍ/ቤት ፍቺ ሳይፈፀም መፍረስን ያስተዋወቀ ሲሆን ይኽውም ጋብቻው በፍ/ቤት ባይፈርስም ጋብቻው (ግንኙነቱ) ማንም ሌላ ማስረጃ ሊያስረዳው ከሚችለው በላይ የጋብቻ ግንኙነቱ መፍረሱን ማስረዳት ከተቻለ ጋብቻው በፍ/ቤት ባይፈርስም ጋብቻው "በሁኔታ እንደፈረሰ" ይቆጠራል የሚል ይዘት ያለው ውሳኔ ሰጥቷል። በዚሁ ውሳኔ አስገዳጅ የህግ ትርጓሜ መሰረት የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔዎችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።


ከዚህ በላይ በተጠቀሰው ውሳኔ መሰረት በሁኔታ የጋብቻ ግንኙነት መፍጠር የህጉን ዓላማ ያሳካ የህግ ትርጓሜ ነው ወይ? ይህ ትርጓሜ በምን ደረጃ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል? የሚሉ ጥያቄዎችን ለማየት ስንሞክር፡-


የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ ሌላ (ሁለተኛ) የፍቺ መንገድ (ከፍርድ ቤት ውጪ) በማስተዋወቅ ዓላማ ሳይሆን ተጋቢዎቹ በሚያሳዩት ሁኔታ በሁለቱ ተጋቢዎች መካከል ያለው የጋብቻ ሁኔታ በሁለቱም መካከል ጋብቻ መኖርን ዕሳቤ ያላቸው መሆኑን የማያሳይና ይህንኑ ዕሳቤ መሰረት አድርገው የሚፈፅሟቸው ተግባራትም በትዳር አብሮ የመቆየትን ሳይሆን በተቃራኒው ትዳሩ እንደሌለ የሚያሳይ በመሆኑና በዚሁ መነሻ ቀድሞም የሚፈርስ ትዳር የለም (በተጋቢዎቹ ሁኔታ ትዳሩ ፈርሷል) የሚል የህግ ግምት የተያዘበት ሁኔታን የተተረጎመበት እንጂ እንደ ሁለተኛ የትዳር ማፍረሻ መንገድ (ከፍርድ ቤት ውጪ) እንደተዋወቀበት መቁጠር የህብረተሰብ መሰረት፤ የቤተሰብ ምሶሶ ለሆነው ጋብቻ ህጉ የሰጠውን ጉልህ ደረጃ እና ጥበቃ በማውረድ ህጉ በማናቸውም የጋብቻ አፈፃፀም ስርዓተ ጋብቻ ይፈፀም ፍቺው እና ውጤቱ በፍርድ ቤት እንዲመራ ያስቀመጠውን አቅጣጫ የሚያፋልስና ፍ/ቤቶች ከተሰጣቸው የህግ ተርጓሚነት ሚና ወደ ህግ አሻሻይ/አውጪ የሚቀይር የመንግስት ስልጣን ክፍፍል መርህን ጭምር የሚጋጭ በመሆኑ የህግ ተርጓሚው ከህግ አውጪው ሐሳብ አንፃር የሰጠው ትርጓሜ በዚህ ደረጃ የሚገልጽ ነው የሚል አስተያየት አለኝ።


በጋብቻ ውስጥ ያሉ ተጋቢዎች በትዳር ውስጥ ያሉ ተጋቢዎች መፈፀም የሚገባቸውን ግዴታዎች በመወጣት በጋብቻው የመቀጠል ሐሳብ እያላቸው እና ይህንኑ በመፈፀም ላይ ሳሉ ፍቺ ከፍ/ቤት በመለስ ሊደረግ እንደሚችል ተራ ግንኙነት በመቁጠር የጋብቻን ክቡርነትና ጥበቃ በሚቃረን መልኩ በበርካታ የፍርድ ቤት ጉዳዮች "ጋብቻው በሁኔታ ፈርሷል" የሚሉ ውሳኔዎች እየተስተዋሉ ይገኛሉ። ይህም በተለያዩ ፍርድ ቤቶች በተለያዩ መዝገቦች የጋብቻ ፍቺ ጥያቄ ሊቀርብ በተለይም የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመቅረፍ በስምምነት በተለያዩ ሀገሮች የሚኖሩ ዜጎችን የጋራ ንብረትና ክፍፍልን መሰል የፍቺ ውጤቶችን የተጋቢዎቹን መብት በሚጎዳ መልኩ በዘፈቀደ "ጋብቻው ቀድሞም በተጋቢዎች ሁኔታ ፈርሷል፤ፍ/ቤቱ የሚያፈርሰው ጋብቻ የለም" በሚል የሚሰጡ ውሳኔዎች የህጉንና የሰበሩን ፍ/ቤት ውሳኔ ዓላማ ያላገናዘበ ነው።


የሰበሩ ውሳኔ ጋብቻው "በተጋቢዎቹ ሁኔታ" ለመፍረሱ በርካታ ግብዓቶችን የተጠቀመ ሲሆን እንደዚሁም የተጋቢዎቹ ግንኙነት (ጋብቻ) ለረዥም ጊዜ የተቋረጠ፣ በዚሁ ግንኙነት መቋረጥ ምክኒያት ሌላ ጋብቻ መፈፀሙንና የዚሁ ግንኙነት መቋረጥ በተጋቢዎቹ መካከል በእርግጥ የሚታወቅ ‹‹ሌላ ማስረጃ ሊያስረዳው ከሚችለው በላይ ነጥቦችን የያዘ ሲሆን በተለይም የሰበር ሰሚ ችሎቱ በሶስተኛነት ያስቀመጠው የማስረዳት ደረጃ የተጋቢዎቹ ትዳራቸው የፈረሰና ይህንኑ ትዳር ለማቆየት በማሰብ ህጋዊ ተግባራትን ያልፈፀሙ፣ ትዳሩ መፍረሱን የሚያውቁ መሆኑን፣ የጋብቻ ኃላፊነቶችን መተጋገዝ፤ ቤተሰብን በጋራ መምራት፣ መተማመን፣ አብሮ መኖር ወዘተ በተቻላቸው ያልፈፀሙ መሆኑን በእጅጉ ጥብቅና ለፍፁማዊነት በቀረበ ደረጃ የማስረዳትን ኃላፊነት/ግዴታ ጋብቻው በሁኔታ ፈርሷል ብሎ ለሚከራከር ተከራካሪ ላይ የጣለ በመሆኑ ይህንን መሰል ጭብጥ በዚህ ደረጃ በጥብቅ የማስረጃ ምዘና መርህ ሊመዘን ይገባዋል።


በጥቅሉ ጋብቻ በዘፈቀደ ከፍ/ቤት በመለስ በታዩ ጥቃቅን የትዳር ጉድለቶች መነሻነት "በሁኔታ ፈርሷል" ሊባል የማይገባ በመሆኑ ይህንኑ መሰረት አድርጎ የሰበር ችሎቱ የሰጠው አስገዳጅ ትርጓሜ በጥንቃቄ ሊጤን የሚገባው ነው እንጂ በተለያዩ መዝገቦች እንደተስተዋለው በቀላሉ ተጋቢዎቹ ትዳራቸውን በሁኔታቸው ከፍርድ ቤት ውጪ አፍርሰውታል የሚል አቋም የጋብቻን ክብርና ጥበቃ የሚያወርድ፤የህግ ትርጓሚውን ሚናም ከህግ አውጪው ጋር የሚያቃርን መስመሩንም የሚያጣብብ ነው እላለሁ። እስኪ እንወያይበት። ፈጣሪን ኢትዮጵያን ይባርክ!!

 

 

ኢዛና ዘ መንፈስ

 

ሀገራችን የምትመራበት ፌደራላዊ ስርዓት ዋነኛ ዓላማ ካለፈው ታሪካችን በወረስናቸው የተዛቡ የዕርስ በርስ ግንኙነቶች ምክንያት ተፈጥሮ የቆየ የህዝቦቻችንን አሉታዊ ዝምድናን በጤናማ ወንድማማችነት እንዲተካ ማድረግ ነው ማለት ይቻላል። የሀገራችን ሕገ መንግስታዊ ስርዓት ምሰሶዎች ተደርግው ከሚወሰዱት መሰረታዊ በህሪያት መካከል ቀዳሚ ስፍራ የሚሰጠው የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዕርስ በርስ ተፈቃቅደው፤ ተፈቃቅረውና ተከባብረው እንዲኖሩ ማድረግ የሚለው ነጥብ እንደሆነ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም። ይሁን እንጂ ይህን ቁልፍ ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ እንደተራ ነገር ቆጥረው ሲጥሱት የሚስተዋሉ የአካባቢ መስተዳደር አካላትም ጭምር መኖራቸው አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ ይገኛል።


ለዚህ ደግሞ በቅርቡ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልሎችን በሚያዋስኗቸው አንዳንድ ተጎራባች አካባቢዎች የተስተዋለው ግጭት እንዲከሰት አድርገዋል ተብለው የሚጠረጠሩ የመስተዳድር አካላት መኖራቸውን ብቻ ማስታወስ ይበቃል። ይህ ዓይነቱ ከሕገ መንግስታችን መሰረታዊ ዓላማ ጋር ፈጽሞ በሚቃረን መልኩ ወንድማማች ህዝቦችን አቃቅሮ ደም እንዲቃቡ የማድረግ የአንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢ የመስተዳደር አካላት አስነዋሪነት ተግባር ዛሬ የተጀመረ ጉዳይ እንዳልሆነም ይታወቃል። ስለዚህም የችግሩ በተመሳሳይ መንገድ ሲደጋገም መስተዋል፤ ስለጉዳዩ የሚያውቀው ነገር የሌለውን ሰላም ወዳድ ህዝብ ላላአስፈላጊ የህይወትና የንብረት ኪሳራ ከመዳረግም ባሻገር፤ የፌደራል ስርዓቱን ጠቀሜታ የጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚያስገባ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ እንደማይቀር መገመት አይከብድም። በሰላማዊ መንገድ ተወያይቶ መተማመንና የጋራ ችግሮችን የሚፈታ ሕገ መንግስታዊ አግባብ መከተል እየተቻለ፤ ክቡሩን የሰው ልጅ ህይወት ወደሚቀጥፍ መሰል ግጭት ማምራትን እንደፈሊጥ የያዙት የመስተዳደር አካላቱ ራሳቸው እንደሆኑ ሲነገር ከመስማት በላይ አስደንጋጭ ዜና ሊኖር አይችልምና ነው እኔ በበኩሌ ስለጉዳዩ የሚሰማኝን ስጋት ለመግለጽ መገደዴ።


ስለሆነም ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት በተጣለባቸው አንዳንድ ምግባረ ብልሹ የመስተዳደር አካላት ምክንያት ህብረተሰባችን ለፈርጀ ብዙ ጉዳት ሲዳረግ የሚስተዋልበትን መሰል ግጭትና ቅራኔ በመቀስቀስ ረገድ እጃቸው አለበት የሚባሉ ፖለቲከኞች ላይ ለፈፀሙት ወንጀል የሚመጥን የእርምት እርምጃ መውሰድ ለነገ የማይባል አንገብጋቢ ጥያቄ ነው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። እናም ከዚህ አኳያ፤ የኢፌድሪ መንግስት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስቴሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ሰኞች መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ወቅታዊ መግለጫ ላይ፤ የኦሮሚያ ክልልን ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጋር በሚያዋስኑት ዞኖችና ወረዳዎች የተከሰተውን ሰሞነኛ ግጭት ቀስቅሰዋል በተባሉ የመስተዳደሮቹ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ስለመወሰኑ ሲናገሩ መደመጣቸውን እንደ ተስፋ ሰጭ ዜና ወስጀዋለሁ።


ይህን ስል ግን እንደሀገር እንቅልፍ የሚነሳ አሳሳቢ የፀጥታ ችግር እያስከተለብን ያለውን መሰል የመብት ጥሰት ማስቀረት የሚቻለው ከመናገር ያለፈ ተግባራዊ የእርምት እርምጃ በመውሰድና ትርጉም ካለው የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚመነጭ ተጠያቂነትን ማስፈን ሲቻል ብቻ መሆኑን አጥቸው አይደለም። ይልቅስ የሁለቱን ተጎራባች ክልሎች ወንድማማች ህዝብ ፈርጀ ብዙ ጉዳት ወዳስከተለ ትርጉም የለሽ ግጭት እንዲገባ አድርገዋል የተባሉት የመስተዳደር አካላት ሕግ ፊት ቀርበው እንዲጠየቁ የፌደራሉ መንግስት ውሳኔ ላይ ስለመድረሱ መስማታችንም በራሱ እንደ አንድ ጠቃሚ እርምጃ ሊወሰድ የሚችል ሆኖ ስላገኘሁት ነው እንደበጎ ጅምር ማድነቄ።


እንጂማ ይህ አሁን አገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት ወቅት ከመቸውን ጊዜ በላይ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አክብሮ የማስከበር ተግባራዊ እርምጃ መውሰድን ግድ የሚል ስለመሆኑ በጽሑፌ ርዕስ ጭምር ጠቁሜ የለ እንዴ? እንዲያውም እውነቱን እንነጋገር ከተባለማ፤ ለዚህ ዓይነቱ ቅጥ ያጣ የሕገ መንግስታዊ መብት ጥሰት የሚያወላዳ መፍትሔ አለመፈለግና እንደተለመደው በቸልታ ለማለፍ መሞከር፤ አጠቃላይ ሀገራዊ ደህንነታችንን ለማናጋት ያለመ ስትራቴጂ ነድፈው በግልጽና ግልጽ ባለሆነ መልኩ እየተንቀሳቀሱ ያሉት የሻዕቢያው መንግስት ጉዳይ አስፈፃሚዎች የልብ ልብ እንዲሰማቸው ዕድል እንደመስጠት ሊቆጠርም ይችላል። ይህን ያህል ሰላማዊ ህዝብ ከመኖሪያ ቀየው እስኪፈናቀል ድረስ ትርምስ ሲፈጠር አላየሁም አልሰማሁም ሊል የሚችል የክልላዊ መንግስት አካል ሊኖር ይገባልን ወገኖቼ!? እንደኔ እንደኔ ግን አይገባም ባይ ነኝ።
ስለዚህ የፌደራል ስርዓታችን የማዕዘን ድንጋይ ተደርጎ የሚወሰደውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት አደጋ ላይ የመጣል ዕኩይ ፍላጎት ያላቸውን ኪራይ ሰብሳቢ የፖለቲካ ቡድኖች ከጥፋት ተግባራቸው እንዲታቀቡ ሊያደርግ የሚችል ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ረገድ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ አመራር የተለየ ቁርጠኝነትን እንጠብቃለን። ደግሞስ በአስመራው የማፊያዎች መንግስት ጸረ ኢትዮጵያ አጀንዳ ዙሪያ ተሰባስበው የሚንቀሳቀሱት ሽብርተኛው ኦ.ነ.ግ እና የጥፋት አጋሮቹ ምን እስከሚያደርጉን ነው የምንጠብቀው!? እንደኔም እምነት ግን ፌደራላዊ ስርዓታችን ፈጽሞ ሊቀለበስ በማይችል የሕግ የበላይነት የሚመራና የሚዳኝ እንጂ በጥቂት አኩራፊ ፖለቲከኞች ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ ልናረጋግጥላቸው የሚገባ ይመስለኛል።


ስለዚህም ከሕገ መንግስታችን መሰረታዊ ዓላማዎች ጋር ፈጽሞ በሚቃረን መልኩ ህዝቦችን ወደለየለት የዕርስ በርስ እልቂት እንዲገቡ የሚጋብዝ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር ይዘት ያለውን ጠባብ ብሔርተኛ ክልል አቀፍ እንቅስቃሴ በማባባስ ረገድ የመሪ ተዋናይነቱን ሚና ተጫውተዋል በሚባሉ የየአካባቢው መስተዳደር አካላት ላይ ለጥፋታቸው የሚመጥን ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ግድ ይላል። ምናልባትም ከዚህ ቀደም የተከሰቱትንና ይህንኑ የፈረደበት የመከራው ገፈት ቀማሽ እየሆነ ያለውን ህዝባችንን ለተመሳሳይ የሕይወትና የንብረት ኪሳራ ዳርገውት ያለፉትን ተደጋጋሚ አካባቢያዊ ግጭቶች የቀሰቀሱ የመስተዳደር አካላት ላይ ትርጉም ያለው የተጠያቂነት እርምጃ መውሰድ ቢቻል ኖሮ፤ ቢያንስ የአሁኑን ፈርጀ ብዙ ጉዳት ማስቀረት ይቻል ነበር የሚል እምነት ነው ያለኝ እኔ በግሌ። ስለሆነም የእርምት እርምጃ መውሰድ የሚጠበቅበት ሕጋዊ አካል የመልፈስፈስ አዝማሚያን ባሳየ ቁጥር እቺን ሀገር ለማተራመስ ያለመ የጥፋት ተግባር በመፈፀም የሚታወቁት ኃይሎች ያሻቸውን ቢያደርጉ እንብዛም የሚያሰጋ ተጠያቂነት ሊያስከትልባቸው እንደማይችል ስለሚሰማቸው የበለጠ ሊፈነጩብን መነሳሳታቸው የሚያከራክር ጉዳይ አይሆንም የሚለውን ቁልፍ ነጥብ ልናሰምርበት ይገባል እያልኩኝ እነሆ እዚህ ላይ አበቃሁ።

(አለማየሁ ገበየሁ፤ ከሀገረ እንግሊዝ)

 

የሊቢያው መሪ ሙአመር ጋዳፊ ፖለቲከኛ ፣ ሃሳብ አመንጪ እና ደራሲ ነው ። በረጅም የስልጣን ዘመን ቆይታው Escape to hell and others , My vision እና The Green Book የተሰኙ ሶስት ተጠቃሽ መጻህፍትን ለዓለም አበርክቷል ።

አዲስ የፖለቲካ ፍልስፍናውን በመጽሐፍ መልክ ማሳተም የጀመረው በ1975 ነበር ። የዴሞክራሲ ችግር መፍትሄ ፣ የኢኮኖሚ ችግር መፍትሄ እና የሶስተኛው ዓለማቀፍ ቲዎሪ ማህበራዊ መሰረቶች የሚሉ ሶስት ጥራዞችን በተለያዩ ግዜ ጽፏል ። ኋላ ላይ እነዚህን ጥራዞች አንድ ላይ በመሰብሰብ አረንጓዴው መጽሐፍ በሚል ለንባብ አብቅቷቸዋል ።

አረንጓዴው መጽሐፍ ዓለምን ብዙ ያነጋገረና ያከራከረ ስራ ነው ። ይህን መጽሐፍ የተማሩበት የሊቢያ ወጣቶች ብቻ አልነበሩም ። በፈረንሳይ ፣ ምስራቅ አውሮፓ፣ ኮሎምቢያ እና ቬንዚውላ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች ተወያይተውበታል ፤ አውደጥናት ተካፍለውበታል ።

ጋዳፊ የፍልስፍና ውሃ ልኩን በአረንጓዴው መጽሐፍ ለማሳየት ሞክሯል ። በተለይ የምእራቡ ዓለም የዴሞክራሲ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ አስተምህሮ ጠማማ መሆኑን መነሻ በማድረግ የችግሮቹን መፍትሄ በአማራጭ አተያይ / ሶስተኛው አለማቀፍ ቲዎሪ / ለመተንተን ሞክሯል ።

ጋዳፊ በዚህ ጥራዝ ብዙ ርእሰ ጉዳዮችን ነው የመዘዘው ። በመጀመሪያ ክፍል ምርጫን ፣ የተወካዮች ም/ቤትንና ህዝበ ውሳኔን በእጅጉ ይኮንናል ። እንደርሱ እምነት ዴሞክራሲ የህዝቦች ስልጣን እንጂ የጥቂት እንደራሴዎች ሃብት አይደለም ። ህዝብን እንወክላለን ብለው በፓርላማ በሚሰበሰቡ አባላት ዴሞክራሲ እውን ሊሆን አይችልም ምክንያቱም እነሱ ከተመረጡ በኋላ ለራሳቸው ጥቅም ነው የሚንቀሳቀሱት ። በተለይ ፓርላማው በአንድ ፓርቲ የተዋቀረ ከሆነ የአሸናፊ ፓርቲ ፓርላማ እንጂ የህዝብ ፓርላማ መባሉ አግባብ አይደለም ። ጋዳፊ የወቅቱን የእኛ ሀገርን ፓርላማ ቀድሞ ነው የተቸው ማለት ነው ። እውነተኛው ዴሞክራሲ የሚገኘው በቀጥተኛው የህብረተሰብ ተሳትፎ ነው ። እውነተኛ ዴሞክራሲ ተግባራዊ የሚሆነው ብዙሃኑ በህብረት ወጥቶ ህዝባዊ ኮሚቴ እና ታላቅ የመማክርት ጉባኤ ሲዋቀሩ ነው ። ህዝበ ውሳኔም ቢሆን / Referendum / ዴሞክራሲን የማጭበርበሪያ ዘዴ እንደሆነ ጽፎታል ። ‹ አዎ › ወይም ‹ አይ › ብለው እንዲመርጡ የሚገደዱ ዜጎች ነጻ ሃሳባቸውን እንዲገልጹ አይደረግም ። በመሆኑም ይህ አይነቱ አሰራር ጨቋኝና አምባገነናዊ ነው ሊባል የሚገባው ።

ፕሬስንና ሃሳብን በነጻነት መግለጽን አስመልክቶም የግለሰቦችና የቡድኖች ያልተገደበ መብት እንደሆነ ይዘረዝራል « ፕሬስ ማለት ማንኛውም ሰው ራሱንና አስተሳሰቡን የሚገልጽበት ነው ፣ ሌላው ቀርቶ እብደቱን ጭምር ። የዚህ ሰውየ እብደት የሌላ ሰው ወይም ሰዎች እብደት ነው ተብሎ መቆጠር የለበትም ። በመሆኑም በጋዜጦች የሚወጡ አስተያየቶችን የህዝብን ሃሳብ አደርጎ ጥያቄ ማንሳት መሰረተ ቢስ ነው ፣ ምክንያቱም ጋዜጦች ያተሙት የዚያን ሰውየ አስተያየት ነውና »

በሁለተኛው ክፍል ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተዳሰዋል ። እንደ ጋዳፊ ሃሳብ ደመወዝተኞች ለቀጠራቸው ግለሰብ ግዜያዊ ባሪያዎች ናቸው ። መሰረታዊ ፍላጎቶች/ ቤት ፣ ትራንስፖርት ወዘተ / በግለሰቦች ቁጥጥር ስር መዋል የለባቸውም ምክንያቱም ብዝበዛንና ባርነትን ያመጣሉና ። በሶሻሊስት ማህበረሰብ ውስጥ ሰዎች የሚሰሩት በሽርካነት እንጂ ለደመወዝ ብለው አይደለም ። በሌላ ሠው ቤት የሚኖሩ ሰዎች ማለትም ኪራይ የሚከፍሉም ሆነ የማይከፍሉት ነጻነት አላቸው ማለት አይቻልም ። መሬት የማንም ሃብት አይደለም ነገር ግን ማንኛውም ሰው በመሬት ላይ ማንንም ሳይቀጥር የተለያዩ ስራዎችን ማከናወን ይችላል ። የቤት ሰራተኝነት የዘመናዊው ዓለም ባርነት ነው ። እናም የቤት ስራ መከናወን ያለበት በነዋሪዎቹ ነው ።

ሶስተኛው ክፍል ማለትም የሶስተኛው ዓለማቀፍ ቲዎሪ ቤተሰብን ፣ ጎሳን ፣ ብሄርን ፣ ሃገርን ፣ አናሳ ብሄርን ፣ ሙዚቃን ፣ ስፖርትና ሴቶችን ይዳስሣል ። ሌላው ቀርቶ ጥቁር ህዝቦች ወደፊት አለምን / ቀደም ብሎ ቢጫዎች ፣ አሁን ደግሞ ነጮቹ እየገዙ ነው / ይመራሉ ይላል ። ስፖርት ልክ እንደ ጸሎት ግላዊ ጉዳይ መሆኑን ይገነዘባል ። ቦክስ እና ነጻ ትግል ግን የሰው ልጅ ገና ከአረመኔነቱ አለመላቀቁን የሚያሳዩ ድርጊቶች ናቸው ::

ጋዳፊ ቤተሰብ ከመንግስት የበለጠ አስፈላጊ ተቋም እንደሆነ በሚከተለው መልኩ ያምናል  « ቤተሰብ እንደ እጽዋት ነው ። ቅርንጫፍ ፣ ግንድ ፣ ፍሬና ቅጠል ያለው ። እጽዋት የመነቀል ፣ የመድረቅ እና የእሳት አደጋ እንደሚያጋጥማቸው ሁሉ ቤተሰብም ህልውናው በብዙ ነገሮች ይፈተናል ። ያበበ ማህበረሰብ ማለት ግለሰቦች በቤተሰብ ውስጥ ቤተሰቦች ደግሞ በማህበረሰብ ውስጥ ማደግ ሲችሉ ነው ። ቅጠል ለቅርንጫፍ ፣ ቅርንጫፍ ለዛፍ እንዲሉ ግለሰብም በቤተሰብ ውስጥ የጠነከረ ትስሥር አለው ። ግለሰብ ያለ ቤተሰብ ትርጉም የለውም ። የሰው ልጅ እንደዚህ አይነቱን ትስስር ከጣለ ስር የሌለው ሰው ሰራሽ አበባ ነው የሚሆነው »

ጋዳፊ ለጎሳ መራሹ የአፍሪካ ህዝብም ጠቃሚ ስንቅ ያቀበለ ይመስላል ። ማህበራዊ ትስስር ፣ አንድነት ፣ ቅርበትና ፍቅር ከጎሳ ይልቅ በቤተሰብ ይጠነክራል ፤ ከሀገር ይልቅ በጎሳ ይጠነክራል ። ከዓለማቀፍነት ይልቅ በሀገር ይጠነክራል ። ጎሳ ትልቅ ቤተሰብ ነው ... ለጎሳ ትልቁ መሰረት ደም ነው ... ጎሳ አባላቱን የሚከላከለው በመበቀል ነው ። ጎሰኝነት ናሽናሊዝምን ያጠፋል ፤ ምክንያቱም የጎሳ ታማኝነት ከሀገር ታማኝነት የላቀ ነው ። በሀገር ውሰጥ የሚገኙ ጎሳዎች የሚጋጩ ከሆነ ሀገር ችግር ውሰጥ ይወድቃል ። ብሄርተኞች ፍላጎታቸውን በሃይል የሚገልጹ ከሆነና የራሳቸውን ፍላጎት የሚያሰቀድሙ ከሆነ ሰብዓዊነት ላይ አደጋ ይፈጠራል በማለት ስጋቱን ክፍላጎቱ ጋር አዛምዶ መርሁ ላይ አስፍሮታል ።

የአንድ ሀገር ህዝቦች የሚበየኑት በቦታው ላይ በመፈጠራቸው ብቻ አይደለም ። ይህ መሰረታዊ ነገር ሊሆን ይችላል ። ከዚህ በተጨማሪ ግን ለረጅም ግዜ በአንድ ላይ በመኖር የጋራ ታሪክ ፣ ቅርስ እና ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ሲኖራቸው ነው ። ህዝቦች ከደም ትስስር ይልቅ ሀገራዊ አንድነትና የኔነትን በጋራ ይዛመዳሉ ።

ሴቶች ከወንዶች እኩል አይደሉም በሚባለው ብሂል ጋዳፊ አይስማማም ። ሴቶች እኩል መስለው የማይታዩበትንም ሳይንሳዊ ምክንያት በዝርዝር አስቀምጧል ። ሴቶች አንስታይ ወንዶች ተባእታይ ናቸው ። ባለሙያዎች እንዳረጋገጡት ሴቶች በየወሩ ደም ሲያዩ ወንዶች አይኖራቸውም ። ሴት ደም ካላየች ነፍሰጡር ናት ። ነፍሰ ጡር ስትሆን ለአመት ያህል ንቁ ተሳታፊ አትሆንም ። ልጅ ስትወልድ ወይም ሲያስወርዳት ደግሞ በ ፒዩፐሪየም / Puerperium / ትሰቃያለች ። ወንድ ይህ ሁሉ ስቃይ አይደርስበትም ። ከወለደችም በኋላ ለሁለት አመታት ታጠባለች ። ጡት ማጥባት ማለት ሴት ከልጅዋ የማትለያይበት በመሆኑ አሁንም ሌሎች እንቅስቃሴዎቿ ይቀንሳል ። በመሆኑም ሌላን ሰው ለመርዳት ቀጥተኛ ሃላፊነት መውሰድ በእሷ ላይ ይወድቃል። ያለ እርሷ ብርቱ ድጋፍ ያ ፍጡር ይሞታል ። ወንድ በሌላ በኩል አያረግዝም ፣ አያጠባም ::

ጋዳፊ በአረንጓዴው መጽሐፍ ታላላቅ ሀሳቦችን አንስቷል ። በክፍል አንድ ስልጣን የህዝብ መሆኑን እንመለከታለን ። ግለሰቦች ሊያብዱ ይችላሉ ይህ ማለት ግን ማህበረሰቡ አብዷል ማለት አይደለም በሚለው ነጥብ ዙሪያ ፕሬስ ሃሳብን መግለጫ ነጻ መሳሪያ መሆኑ ተሰምሮበታል ። በሁለተኛው ክፍል ለኢኮኖሚው ችግር መፍትሄው ሶሻሊዝም መሆኑ ተቀምጧል - በእያንዳንዱ ቤት ወስጥ የሚኖር ዜጋ የቤቱ ባለቤት እንጂ ጭሰኛ መሆን የለበትም የሚል የሚደላ አቋም ይታያል ። የአስቂኝም አስደናቂም ስብስብ በሆነው ሶስተኛ ክፍልም ሴት ከወንድ ታንሳለች ማለት የተፈጥሮ ህግን መካድ ነው የሚል ጠንካራ አቋም ይገኛል ።

ደራሲው ጋዳፊ ከፖለቲከኛው ጋዳፊ ጋር ተጣጥሞ ቢዘልቅ መልካም ነበር ። በተለይ በዙሪያህ የተኮለኮሉ ሰዎች / የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው / የስብእና አምልኮ እየገነቡልህ ሲሄዱ ዝም ካልክ መቀበሪያህ እየተማሰ መሆኑ ማወቅ ይገባል ። ። ጋዳፊ መርሁ እንዲዘመር እንጂ እንዲሰራበት ለማድረግ ያልቻለበት አንደኛው ምክንያትም ይሄው ነው ። ጹሑፍህን ደጋግመህ በፍቅር ታነበዋለህ እንጂ ደፍረህ አርትኦት አታደርገውም ። በዚያ ላይ ፍልስፍናን ለማሰብና ለመራቀቅ እንጂ ሆኖ ለመኖር ይከብዳል ።

በኤፍሬም

 

ኦፕራይድ (www.opride.com) የተባለ ድረ ገጽ በኦገስት 2017 ባቀረበው አንድ ቃለ ምልልስ በጀርመን አገር በታተተመ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ አንድ ፓስተር አቅርቧል። በንቲ ኡጁሉ ቴሶ (Rev. Benti Ujulu Tesso) የተባሉት ፓስተር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለው “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም ቆዳቸው የጠቆሩ ሰዎች ሁሉ ስም በመሆኑና አነጋገሩና ትርጉሙም አዎንታዊ ሳይሆን አሉታዊ በመሆኑ “ኩሽ” ወደሚለው ትርጉም መመለሱን ጠቅሰዋል። ሙሉውን ቃለ ምልልስ ለማንበብ ከዚህ (ሊንክ https://goo.gl/UKkf3G ) መመልከት ይቻላል።


እ.አ.አ በ1976 የታተመ “ጉድ ኒውስ ባይብል” ኢትዮጵያ የሚለው ስም የዛሬዋን መልክዐ ምድራዊቷን ኢትዮጵያን ሳይሆን የዛሬዋን ሱዳንን የሚመለከት በመሆኑ ማስተካከያ ማድረግ አለብኝ በሚል መነሻ ገሚሱን ክፍል ሱዳን ብሎ ተክቶ አሳትሞ ነበር። ይህንን ጉዳይ የተረዳው ቅዱስ ሲኖዶስም ስለነገሩ ማብራሪያ በመጠየቅ ብዙ ከቆየ በኋላ ትርጉሙ ስሕተት መሆኑን ከአሳታሚዎቹ ጋር በመተማመን እና ድጋሚም በዚህ መልክ እንደማያሳትሙ በመወሰን ጉዳዩን ሊቋጭ ችሏል። ወረቀትና ምን የያዘውን አይለቅም አንደሚባለው በወቅቱ የታተሙት “ጉድ ኒውስ” ባይብሎች ግን በተገቢው መንገድ ከአንባቢያቸው እጅ (አብዛኛውም በታዳጊው ዓለም) በመግባት ሱዳን ሱዳን ሲሉ ኖረዋል።


ይህ ጉዳይ በቀላሉ መታለፍ እንደሌለበት የተረዳው ቅዱስ ሲኖዶስ ለአማንያኑ ባወጣም መግለጫ ላይ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ በመስጠት ዋና ዋና ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ሰጥቷል። የፓስተር በንቲ ጥያቄም የከረመ ጥያቄ በአዲስ ጠያቂ ከመጠየቁ ውጪ ጥያቄውም መልሱም የከረመ ነው።


ይሁንና የፓስተር በንቲ ጥያቄ “ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል እና ኢትዮጵያዊነት የሚለው መለያ የጥቃት ዓላማ በሆነበት በዚህ ዘመን የነሣ ጥያቄ በመሆኑ የተለየ ትኩረት ማግኘቱ የግድ ነው። ምላሸችን ግን ያው ነው። ከዚህ ቀደም ተደጋግሞ የተባለው ነው። ዝርዝሩን ከዚህ ላይ ተመልከት (https://goo.gl/NiEEAx)።

 

የጀርመን ኢቫንጄሊካል ቸርች ለምን ይህንን አደረገች? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ጥያቄ ነው። ወደ ትልቅ ሴራ ትንተና ውስጥ ሳንገባ የጀርመን ቤተ ክርስቲያን በተለይም በኦሮሞ የቆየ አክራሪ የመገንጠል እንቅስቃሴ ውስጥ በቄሶቿ አማካይነት የነበራትን ሥፍራ በቅጡ የሚተነትን ጥናት ያስፈልገናል (ኖሮም እንደኹ አላውቅም)። የኦሮሞ ምሁር ናቸው የተባሉት ፓስተር በንቲ ስለ ጥናታቸው ያብራሩበት ድርጊት በርግጥ ሳይንሳዊ ጥናት ነው ወይስ ፖለቲካዊ ትንታኔ የሚለው በቅጡ መታየት አለበት።


ለማንኛውም ስለ ኢትዮጵያዊነት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥብቅና መቆሟ የሚገባ ቢሆንም ሌላውም ኢትዮጵያዊ እና ነገሩ የሚያገባው ማንኛውም ተቋም፣ ምሁር እና የእምነት አካል ስለ ጉዳዩ የራሱን የቤት ሥራ መሥራት ይኖርበታል። በዚህ ጉዳይ ከነገረ ሃይማኖት ምሁራን (ቲዮሎጂያን) ጋር “በአደባባይ” የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት እንሞክራለን። እዝከዚያው ግን ቅዱስ ሲኖዶስ ከሁለት አሥርት በፊት ለ“ጉድ ኒውስ ባይብል” አሳታሚ የሰጠውን ምላሽ እንድታነቡ በመጋበዝ ላብቃ። (ሊንኩን ከዚህ ታገኛላችሁ - https://goo.gl/yk9uMM)


ይቆየን 

 

በመሠረት አስማረ

ደብረ ብርሃን

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው ደብረብርሃን ከአዲስ አበባ 130 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች። የተቆረቆረችውና ስያሜዋን ያገኘችው ደግሞ ከ500 አመት በፊት በ1446 ዓ.ም አካባቢ በአፄ ዘርአያእቆብ /1426-1460ዓ.ም/ ነበር።

ከተማዋ ድሮ ደብረኢባ በመባል የምትታወቅ ሲሆን የንጉሱ የግራ በአልቴሃት /ግራ በአልቴሃት ከንጉሱ ሶስት ሚስቶች የአንደኛዋ የክብር ስም ነው/ ርስት ነበረች። በ1440ዎቹ መጀመሪያ ንጉሱ ጐብኝተዋት ደስ ስለተሰኙባት ተጉለት የነበረውን መናገሻ ወደዚያ አዙረው የድንኳን ከተማቸውን ከተሙባት። በኋላም ቤተመንግስት አሳንፀውና ባለወርቅ ጉልላት የነበረውን የስላሴ ቤተክርስቲያን አሰርተው ቆረቆሯት።

"ተአምረ ማርያም" የተሰኘ የጥንት ድርሳን የከተማዋን ስያሜ ከአንድ ተአምራዊ ሁነት ጋር አያይዞ ይገልፀዋል። በ1446 ዓ.ም በክርስትና ሃይማኖት ካህናትና በጥቂት የሃይማኖቱ ተከራካሪዎች መካከል ክርክር ይነሳል። ንጉሱና የካህናቱ አለቆች በተገኙበት አንድ እለት በጉባኤ ክርክሩ ተካሄደ። በመጨረሻም "እስጢፋኖሳውያን" በሚል መጠሪያ የሚታወቁት ተከራካሪዎች አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ ተጠይቀው አሻፈረን በማለታቸው ከፍተኛ ቅጣት ይደርስባቸዋል።

ይህ በሆነ በ38ኛው ቀን መጋቢት 10/1446 ዓ.ም ረዘም ላለ ጊዜ / ምናልባትም ለቀናት/ የቆየ ቦግ ያለ ብርሃን ከሰማይ ይወርዳል። የብርሃኑ መውረድ ለእስጢፋኖሳውያን ስህተተኛነት ለካህናቱ ደግሞ ትክክለኛነት ምስክር ነው በሚል ተተርጉሟል። ስለዚህ ብርሃን መውረድ የንጉሱ ዜና መዋእልም ያትታል። በዚህ ሳቢያ ንጉሱ የስፍራውን ስም ደብረብርሃን /የብርሃን አምባ/ በማለት ሰይመውታል።

አፄ ዘርአ ያእቆብ ከንግስና ዘመናቸው 14 አመት የሚሆነውን በደብረብርሃን ከተማ እንዳሳለፉና አብዛኛዎቹን የሃይማኖትና የፍልስፍና ድርሰቶቻቸውን የፃፉት በዚሁ ከተማ መሆኑ ይነገራል። በዘመኑም ደብረብርሃን ከፍተኛ የትምህርት ማእከል የነበረች ሲሆን በንጉሱ ትእዛዝ በርካታ የሃይማኖት መፃህፍት የትርጉም ሥራ ተከናውኖባታል።

 

አንጎለላ ከተማ

አንጎለላ ኪዳነ ምህረት አንጎለላ ከተማ የምትገኘው ከደብረብርሃን ከተማ በስተምእራብ 10 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ነው። በንጉስ ሳህለ ስላሴ /1805-1840/ ዓ.ም እንደተመሠረተች የሚነገርላት ሲሆን በሸዋም ሁለተኛዋ ከተማ ነበረች።

ያለውጤት የቀረ ቢሆንም ንጉስ ሣህለ ስላሴ የውጭ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ከእግንሊዝ /1834/ እና ከፈረንሳይ /1835 ዓ.ም/ መንግስታት ዲፕሎማቶች ጋር የንግድና የወዳጅነት ውል የተፈራረሙት በዚሁ በአንጎለላ ከተማ ነው።የዳግማዊ ምኒሊክ የትውልድ ቦታ በሆነችው በዚችው በአንጎለላ ከተማ ታሪካዊቷ የአንጐለላ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ትገኛለች። በቤተክርስቲያኗ ዳግማዊ ምኒሊክ ክርስትና የተነሱባት ከመሆኗ በተጨማሪ በአድዋ ጦርነት ህይወታቸውን ለአገራቸው መስዋእት ያደረጉት የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ገበየሁ አጽም በክብር አርፎበት ይገኛል። የጀግናው አጽም ከተቀበረበት የአድዋ የጦር አውድማ ከሰባት አመታት በኋላ እንዲመጣ ተደርጎ በክብርእንዲቀመጥ የተደረገውም አጼ ምኒሊክ ራሳቸው ባሰሩት ሳጥን መሆኑ ይነገራል።

የአንጐለላ ከተማ ከፍተኛ የከተማነት እንቅስቃሴ የተካሄደባት ቦታ በመሆኗ ልዩ ዋጋ የሚሰጣቸው የስነ ህንፃ ቅርሶች ፍርስራሽ ይገኝባታል። ከ150 አመታት በላይ እድሜ እንዳስቆጠረ የሚገመተው የንጉስ ሣህለ ስላሰ ቤተመንግስት ፍርስራሽ በተለይም በስሩ የሚገኘው አስገራሚው የቤተመንግስቱ የምድር ቤት አሠራር ዓይንን የሚማርክና የጥንት አባቶቻችንን የፈጠራ ውጤት አጉልቶ የሚያሳይ ነው።

 

አንኮበር

በ1733 ዓ.ም በሸዋው ነጋሲ በመርዕድ አዝማችአ ምሀ እየሱስ /1733-1767 ዓ.ም/ የተመሰረተችው አንኮበር ከደብረብርሃን ምስራቃዊ አቅጣጫ 42 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች።

አንኮበር ከአጼ ይኩኖአምላክ /1262-1277 ዓ.ም/ ዘመን ጀምሮ ለኢትዮጰያ ነገስታት ማረፊያነት አገልግላለች። አፄ አምደጽዮን የድንኳን ከተማቸውን እንደተከሉባት ይነገራል። አፄ ልብነድንግል ደግሞ በተሻለ ሁኔታ የባለወልድ ቤተክርስቲያንን ለማነጽ ጀምረው እንደነበር የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ።

የከተማነት ታሪኳ የጐላው ግን የሸዋ ስርወ መንግስት በመንዝ በማንሰራራት /1665-1881 ዓ.ም/ የመስፋፋት እንቅስቃሴ በጀመረበት ወቅት ነው። የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ወደ እንጦጦ እስከዞረበትና በኋላም አዲስ አበባ እስከተቆረቆረችበት ጊዜ ድረስ በቀዝቃዛ አየሯ የምትታወቀው አንኮበር ለስድስት የሽዋ ነገሥታት በማዕከልነት አገልግላለች።አንኮበር የሸዋ ነገስታት ቋሚ መናኸሪያ ለመሆን የበቃችው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስልጣን በያዙት ንጉስ ሳህለ ስላሴ / 1806-1840 ዓ.ም/ ነበር።

ንጉሱ የእጅ ባለሙያዎችን በከፍተኛ ደረጃ የሚያበረታቱ በመሆኑ በርካታ የእደጥበብ ሥራዎች ይከናወኑባት ነበር። በቤተመንግስት የሚተዳደሩ ከ1000 በላይ አናጺዎችና ግንበኞች በተለይም ባሩድ ቀማሚዎች፣ የጦር መሣሪያ ሠራተኞችና አንጥረኞች በወቅቱ ነበሩባት።

የንጉስ ሳህለስላሴ ወራሽ ኃይለመለኮት ዘውድ በጫኑበት ዘመን አንኮበር በአጼ ቴዎድሮስ /1855-1868 ዓ.ም/ ሠራዊት ከመወረሯ በፊት ሹማምንቱ ቤተመንግስቱን አቃጥለውታል። አጼ ቴዎድሮስም በቦታው ድንኳን ጥለው ጥቂት ቀናት ቆይተዋል።በተካሄደው ጦርነትም አንኮበር ክፉኛ መጐዳቷን መረጃዎች ይገልፃሉ። በ1870ዎቹ ከሚኒሊክ መመለስ በኋላ አንኮበር እንደገና ተቋቁማ የጥንት ማዕረጓ ተመልሷል።

ዛሬ በአንኮበር ከአጼ ምኒሊክ ቤተመንግስት ፍርስራሽ በተጨማሪ በተለያየ ዘመን የተሰሩ አምስት አብያተ ክርስቲያናትና ዘመናዊ ሎጅ ይገኛሉ። እነሱም፡- አንኮበር ጊዮርጊስ በ1733 ዓ.ም በአምሃ እየሱስ፣ አንኮበር ማርያም በ1767 ዓ.ም በአስፋው ወሰን፣ አንኮበር ሚካኤል በ1817 ዓ.ም እና አፈር ባይኔ ተክለሃይማኖት በ1821 ዓ.ም በንጉስ ሳህለስላሴ፣ አጼ ምኒሊክና እቴጌ ጣይቱ በ1875 ዓ.ም የጋብቻ ሥነስርአታቸውን ሲፈጽሙ ቅዱስ ቁርባን የተቀበሉበት የመድሃኒአለም ቤተክርስቲያን በ1772ዓ.ም ሥራው ቢጀመርም በ1846 ዓ.ም በንጉስ ሃይለመለኮት የተሰሩ ናቸው።

ረጅሙን የዞኑን ተራራ ተንተርሳ የምትገኘው የቁንዲ ከተማ ሌላዋ ታሪካዊ ቦታ ናት። ከተማዋ የተመሰረተችው በመርእ ድ አዝማች ወሰን ሰገድ /1800-1805 ዓ.ም/ ነው። አንኮበር ለመድረስ 10 ኪሎ ሜትር ሲቀር በምትገኘው ቁንዲ የሚገኘው ቤተመንግስት በግንብ የተከበበ እንደነበረ በዙሪያው የሚታየው ፍርስራሽ ያረጋግጣል። የቁንዲ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንም የዚያን ዘመን የእደ ጥበብ ውጤት ያንፀባርቃል።

 

አልዩ አምባ

የአንኮበር ታሪክ ሲዘከር የስምጥ ሸለቆ Aካል የሆነችው የአልዩ አምባ ከተማና የአብዱል ረሱል የሙስሊም መቃብር ስፍራ አብረው የሚጠቀሱ ናቸው። ከአንኮበር ከተማ 12 ኪ/ሜ ያህል ቁልቁል ተወርዶ የምትገኘው አልዩ አምባ እንደ ሐረር በግንብ የተከበበች ስትሆን በምስራቅ፣ በደቡብና በምእራብ በሮች አሏት።

ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ በኢ ትዮጵያ ታሪክ ጥንታዊ ከሚባሉት የቀረጥ ኬላዎችና የንግድ ማእከል አንደኛዋ ነበረች። የፈረንሳይ ዲፕሎማት ሮቺ ሄሪኮርት እንደፃፈው ከ1500 እስከ 1700 የሚጠጉ ግመሎች የአገር ውስጥ ምርት ወደውጭ ያጓጉዙባት ነበር።

በ1834 እና 1835 ዓ.ም በአገራችን መጀመሪያ የሆነው የቀረጥ ውል የተፈረመው በአልዩ አምባ ገበያ መሠረት ነው። በከተማዋ ከፐርሽያ / ኢራን/ ፣ ከህንድና ከአረብ አገሮች የሚመጡ በርካታ የውጭ አገር ዜጎች ይኖሩባት እንደነበርም ጎብኝዎች ጽፈውላታል። በአጼ ምኒሊክ ዘመን የቀረጥ መስሪያ ቤት ሲከፈት በአልዩ አምባ የጉምሩክ ጽ/ቤት ስራውን እንዲጀምር ተደርጎ ነበር። ስልክም ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ ከእንጦጦ እስከ አልዩ አምባ ድረስ መስመር ተዘርግቶለት ነበር። አልዩአምባ የተዳከመችው የባቡር ሃዲድ በከተማዋ ማለፍ ባለመቻሉና ወደ ድሬዳዋ በመዛወሩ መሆኑ ይነገራል። ዛሬ የአልዩ አምባ ገበያ አብዛኛዎቹን አርጎባዎች ይዞ የአፋርንና አማራ ብሔረሰቦችን ያገናኛል።

 

ሳላይሽ የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት

የአጼ ምኒሊክ የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ሲሆን የሚገኘውም በሀገረ ማርያምና ከሰም ወረዳ ኮርማሽ ከተማ ነው። ከደብረብርሃን ወደ አዲስ አበባ ዋናውን መንገድ ተከትሎ 50 ኪ/ሜ ከተጓዙ በኋላ ወደግራ በመታጠፍ 13 ኪ/ሜ ርቀት ላይ የኮርማሽ ከተማ ይደረሳል። ግምጃ ቤቶቹ በቁጥር 14 ናቸው። አሰራራቸው ደግሞ በእንቁላል ቅርጽ ነው። በ1890 ዓ.ም ከአድዋ ድል ማግስት ለጦር መሣሪያ ማከማቻነት ተብለው የተሰሩ ሲሆን የቦታው ስትራቴጂያዊ /ስልታዊ/ የተፈጥሮ አቀማመጥ የጐብኝን ቀልብ ይስባል። የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቶቹ ቀደም ሲልም ለአፈንጋጭ ባለሥልጣናት እስር ቤት በመሆን አገልግለዋል። ከእስረኞቹ መካከልም ልጅ እያሱ ይጠቀሳሉ። በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ታሪካዊ ግንብ ቤቶች ለመንግስት መስሪያ ቤቶች በጽህፈት ቤትነት እያገለገሉ ይገኛሉ። ይዞታቸውን ሳይለቁ የጥገና እድሳት ሥራ ተሠርቶላቸዋል።

 

የአቡኑ ከተማ ሰላድንጋይ

የአቡኑ ከተማ ሰላድንጋይ ከደብረብርሃን በስተሰሜን 72 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች። ለ38 አመታት የኢትዮጵያ ፓትሪያርክ የነበሩት ግብፃዊው አቡነ ማቴዎስ መንበረ ጵጵስናቸው በዚችው በሰላ ድንጋይ ነበር። በ1875 ዓ.ም በአቡነ ማቴዎስ የተሰራው የሰላድንጋይ ማርቆስ ቤተክርስቲያን በ25 አመቱ በመብረቅ ቢፈርስም እንደገና በ1900 ዓ.ም በአጼ ምኒሊክ ልዩ ትእዛዝ ተሰርቶ ሚያዚያ 30 ንጉሱ ባሉበት በአቡኑ ተባርኳል። የቤተክርስቲያኑ ህንፃ የውስጥ አሰራር ውበት አይንን የሚማርክና የዘመኑን የህንፃ ሥራ ልዩ ችሎታ የሚመሰከር ነው። በውስጡም ከግብጽ ሀገር የመጣውን የአቡነ ማቴዎስ መቀመጫ ጨምሮ በርካታ የታሪክና የባህል ቅርሶች ይገኙበታል።

ሰላድንጋይ የንጉስ ሳህለ ስላሴ የትውልድ ሥፍራም ናት። በእናታቸው በወይዘሮ ዘነበወርቅ እንደተሰራችና በስማቸውም የምትጠራው ሰገነት ከተሰራች 150 አመት አስቆጥራለች። ስላድንጋይ የአብዛኛዎቹ የሸዋ ነገስታት ሚስቶችና እቁባቶች መቀመጫ ስለነበረች የወይዘሮዎች ከተማ በመባልም ትታወቃለች።

ከሰላድንጋይ አቅራቢያ ከ1433 /1434/ ዓ/ም በአጼ ዘርአያቆብ የተተከለችው ደብረምጥማቅ ቤተክርስቲያንና ብዙ መነኮሳት የሚገኙባት የፃድቃኔ ማረያም ከፊል ዋሻ ደብር ይገኛል።

 

ባልጭ አማኑኤል

ባልጭ አማኑኤል ቤተክርስቲያን የሚገኘው ከደብረብርሃን 260 ኪ/ሜ ርቆ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ባልጭ ከተማ ነው። ቤተክርስቲያኑ የተመሰረተው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጼ ገላውዲዎስ ሲሆን አጼ ምኒሊክ በ1870ዎቹ አሳድሰውታል።

በቅድስቱ ግድግዳ ላይ የተሳሉት ጥንታዊ የፈትል ስእሎች ከመንፈሳዊ መግለጫነት ባሻገር ደጃዝማች ምኒሊክ በልጅነታቸው በአጼ ቴዎድሮስ ሲማረኩ፣ በ1857 ዓ.ም ከመቅደላ ሲያመልጡና በኋላም በፍቼ ከተማ ከአጼ ዮሐንስ /1864-1881 ዓ.ም/ ጋር ያካሄዱትን ስምምነት የሚገልጹ ናቸው። በመካነ ፈውስነቱ በአገራችን ስሙ እየገነነ የመጣው የሸንኮራ ዮሐንስ ፀበልም የሚገኘው ከባልጭ ከተማ የ15 ደቂቃ የእግር ጉዞ በኋላ ነው። ፀበሉ ቀደም ሲል በሽተኞችን ያድን እንደነበር ይነገር እንጅ ቀሳውስትና የፀበሉ አስተዳዳሪዎች ግን ከ1957 ዓ.ም ጀምሮ ዝናው እንደታወቀ ይናገራሉ።

ፀበሉ የሚገኝበት አካባቢ ዳገታማና ቁልቁለት በመሆኑ ከአዲሱ ዩሐንስ ቤተክርስቲያን ህንፃ አጠገብ ሆኖ ሲመለከቱት የአካባቢውን አስደናቂ መልክአምድራዊ አቀማመጥና በተፈጥሮ ውበት የታደለውን የመስህብ ሥፍራ ማየት ያስደስታል።

 

ወፍ ዋሻ ደን

በሰሜን ሸዋ ከሚገኙ የተፈጥሮ መስህብ ስፍራዎች መካከል የወፍ ዋሻ ደን አንዱ ነው። ደኑ አምስት ወረዳዎችን፡- ጣርማበር፣ ቀወትን፣ አንኮበርን፣ ላሎማማንና ጌራቀያን የሚያካልል ሲሆን 16925.5 ሄክታር የቆዳ ስፋት አለው። ደኑ ጎሽ ሜዳ፣ ወፍ ዋሻና ጓሳ በተባሉ የጉብኝት ሥፍራዎች የተከፋፈለ ነው።

ጐሽ ሜዳ ከደብረብርሃን በ30 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ይገኛል። በቀወት በኩል 12 ኪ/ሜ ጥርጊያ መንገድ አለው። ከአራት የማያንሱ ብርቅዬ አዕዋፋት የሚገኙበት ጐሽሜዳ ከጭላዳ ዝንጀሮና ከምኒሊክ ድኩላ ከብርቅዬ እንስሳት በተጨማሪ አነር፣ ሚዳቋ፣ ጉሬዛና ሰስ ከመሳሰሉት ሌላ በአለም በየትኛውም ስፍራ የማትገኘው "አንኮበር ሴረን" ወፍ ብቸኛ መገኛም ነው። ከደብረብርሃን ወደ ደብረሲና 15 ኪ/ሜ በዋናው መንገድ ተሂዶና ወደ ምሥራቅ 14 ኪ/ሜ ገባ ብሎ እይታው የሚጀምረው ወፍ ዋሻ ደን በክረምት ወራት አዕዋፋት ስለሚበዙበት የወፎች መሸሸጊያ /ዋሻ/ ተብሎ ይጠራል።

ከጎሽ ሜዳ ባልተለየ መልኩ ማራኪ ሲሆን በደብረሲና በኩል 7 ኪ/ሜ የክረምት ከበጋ ጥርጊያ መንገድ አለው። ጓሳ የሚገኘው በመሀል ሜዳ መዳረሻ ላይ ነው። ስያሜውን ያገኘውም በአካባቢው በብዛት ከሚበቅለው የጓሳ ሳር ነው። ቦታውን ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ወርቃማው ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እፅዋትና ከአስራ አራት የማያንሱ በአገራችን ብቻ የሚገኙ አዕዋፋት ያሉበት መሆኑ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የአካባቢው የመሬት አቀማመጥ ማራኪ መሆኑ ነው።¾

 

1.  የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ /ኦብኮ/

2.  የኦሮሞ አንድነት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኦአዲፓ/

3.  ኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር /ኦአነግ/

4.  የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ /ገሥአፓ/

5.  የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር /ኦነአግ/

6.  የኦሮሞ ነፃነት ብሔራዊ ፓርቲ /አነብፓ/

እኛ እላይ ስማችን የተመለከተው ስድስቱ በአገሪቱ ውስጥ በሰላማዊ የትግል መስመር እየተንቀሳቀስን ያለን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የወቅቱ ትኩሳት በመሆን በሁለቱ አጎራባች ክልሎች ማለትም በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢ በወንድማማች ሕዝቦች መካከል ከረጅም ጊዜ ጀምሮና እስከ አሁንም ድረስ መፍትሔ ከማግኘት ይልቅ እየተባባሰ የመጣውን ግጭት በሚመለከት ከዚህ በፊትም ይህ ግጭት የኦሮሞን ሕዝብ ሰበብ አስባብ በመፈለግ ከማጥቃት ባለፈ ምንም መነሻ ምክንያት እንደሌለውና ችግሩ ተባብሶ ሌላ አቅጣጫ ከመያዙ በፊት ተገቢው መፍትሔ ተደርጎለት ወንድማማች በሆነው በሁለቱም ሕዝቦች መካከል ዘላቂ የሆነ ሰላም እንዲፈጠር በማለት ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ወገኖች አመቺ በሆኑ መንገዶች ሁሉ ስናሳስብ ቆይተናል። በተለይም የኦሮሚያ ክልል ገዥ ፓርቲ ከሆነው ከኦ.ህ.ዴ.ድ ጋር የጋራ ምክር ቤት ስለአለን ከግጭቱ አጀማመር ጀምሮ ሊመጣ የሚችለውን ውጤት ጭምር ስንገልጽ የቆየን ቢሆንም የክልሉ ገዢው ፓርቲ ግን እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ግጭቱን የተራ ሽፍታ እንቅስቃሴና ከሁለቱም ክልል መንግስታት እውቅና ውጪ እየተደረገ ያለና ሁኔታውን ግን በቅርበት እየተከታተልን ነው በማለት ሲያጣጥልና ሲያስተባብል ቆይቷል።

ይሁን እንጂ በወታደራዊ ፓትሮል ተሽከርካሪ ላይ በተጠመዱ መትረየሶች የሚታገዝ ወራሪ ኃይል ከዚህም በተጨማሪ ልዩ ድጋፍ እየተደረገለት በባህላዊ የጦር መሳሪያ በሚከላከል የኦሮሞ አርሶ አደርና ባዶ እጁን በሚንቀሳቀስ የኦሮሞ ሚሊሻዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳትና እልቂት እየደረሰ በመሆኑ ሰሚ ጆሮ ከተገኘ ብለን ይህን የስድስቱ ፓርቲዎች የጋራ አቋም የሆነውን መግለጫ ለመስጠት ተገደናል።

 

 

ዝርዝር ሁኔታዎች

1.  አሁን ግጭቱ እየተካሄደበት ያለው አካባቢ ማለትም ከጉርሱም እስከ ሞያሌ ባለውና ከ1200 ኪሎ ሜትር በላይ ወሰን የሚጋሩ የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦች የጋራ ባህል፣ የጋራ እምነት፣ ሁለቱንም ቋንቋዎችን በጋራ የሚነገሩ በሚያገናኙ የልማት ውጤቶችም የሚገናኙና ከሁሉም በላይ በጋብቻ የተሳሰሩና ምንም ዓይነት ለግጭት የሚያበቃቸው ጉዳይ እንደሌለና አሁንም የተፈጠረው ግጭት የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት አለመሆኑ የጋራ እምነታችን መሆኑ፤

2.  እላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ግጭቱ የሸፈነው የወሰን አካባቢዎች ከ 1200 ኪሎ ሜትር በላይ በመሆኑና በተለይም አጥቂ ወገን ለጥቃቱ የሚጠቀምበት እጅግ ዘመናዊ መሳሪያ በመሆኑ ግጭቱ በግጭት መልክ የሚገለጥ ሳይሆን በአከባቢው በአለው የኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተደረገ ያልታወጀ ጦርነት መባል እንደሚችል የጋራ አቋማችን መሆኑን በተጨማሪም ይህ ያልታወጀ ጦርነት ያልነው ድርጊት በህዝባችን ላይ ሲካሄድ የነበረው እንኳንስ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀ ቀርቶ ውሃ እንኳን ከኮማንድ ፖስቱ እይታ ውጪ መንቀሳቀስ በማይችልበት በአገሪቱ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት ወቅት በመሆኑ እልቂቱን እየፈፀመ ያለው የሶማሊያ ልዩ ኃይል ከኋላው አይዞህ ባይ አስተማማኝ ኃይል ያለው መሆኑ የጋራ እምነታችን በመሆኑ፣

3.  በአሁኑ ወቅት ከአካባቢ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ከሆነ ወራሪው ኃይል የወረራውን ቀጠና እያሰፋ ከጉርሱም እስከ ሞያሌ እያዳረሰ ሲሆን በሌላ በኩል የኦሮሞ ተጠቂ ሕዝብና ሚሊሽያው የያዘውን ኋላ ቀር የጦር መሳሪያ እንኳን በመከላከያ ሠራዊት አማካይነት እየፈታ እንደሚገኝ ነው።

ስለሆነም በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ወገኖ ስለግጭቱ ምክንያት ልዩ ልዩ ሃሳቦች ቢሰነዝሩም ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በየእለቱ በወራሪ ኃይል ጥይት እየረገፈ ያለው የኦሮሞ ሕዝብ ነው። በመሆኑም፡-

ሀ. የአገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል መንግስት ወደ አንድ ወገን ያጋደለውን ጣልቃ ገብነት በመተው ፍትሃዊና ሕገመንግስታዊ መሠረት ያለው ጣልቃ ገብነት በመፍጠር ወይም በቀጥታ በመግባት እልቂቱ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ በወራሪ ኃይሎች ላይ ተገቢ ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ወደመኖሪያቸው ተመልሰው በተገቢ መንገድ እንዲቋቋሙ፤ የንብረትና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውንና ለሞቱት ወገኖቻችን አጥፊ ወገን ተገቢ ካሳ እንዲከፍልና በሕዝቦች መካከል ዘላቂነት ያለው ሰላም እንዲወርድ እንዲደረግ ወገናዊ ጥሪአችንን በድጋሚ እናቀርባለን።

ለ. የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የኦሮሞ ህዝብ በጦርነትና በግድ በስደት በለቀቀው ቀበሌዎችና ወረዳዎች ሕዝብ በሌለበት ሁኔታ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሔድ እያደረገ ያለውን መፍትሄ አልባ እንቅስቃሴ በመተው በ1998 ሕዝበ ውሳኔ የተካሄደባቸው አካባቢዎች የሕዝብ ድምፅ እንዲከበር በዚህ ወቅት ህዝበ ውሳኔ ያልተካሄደባቸውን አካባቢዎች አሁን ከመኖሪያ ሰፈራቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደ መኖሪያ ሰፈራቸው በመመለስ ከተቋቋሙና ከተረጋጉ በኋላ በሕዝቡ ነፃ ፍላጎት እንዲሁም በሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር በመሆን በሕዝቡ እምነት ብቻ በተጣደፈ ሁኔታ ሳይሆን በተረጋጋ ሁኔታ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ በተጨማሪም የኦሮሚያ ብሔዊ ክልላዊ መንግስት ቆም ብሎ በማሰብ ለኦሮሞ ሕዝብ ከኛ በላይ ለአሳር ማለቱን ትቶ የኛንም ሃሰብ እንዲያዳምጥ በድጋሚ ወገናዊ ጥሪአችንን እናቀርባለን።

ሐ. ኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦችን የሁለቱን የጋራ ትስስርና አብሮነት በምንም መልኩ አሳጥሮ መግለጽ አይቻልም። በአጭሩ የረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ ያለው በመከራም ሆነ በደስታ በጋራ የምትኖር አሁንም እየኖርክ ያለህ ወደፊትም የምትኖር ማንም ጣልቃ ገብቶ ሊያለያይህ የማይችል፣ የአሁኑም ችግር ያንተ ችግር ወይም የህዝብ ለህዝብ ችግር ሳይሆን የፀረ ሰላም ኃይሎች ችግር ስለሆነ በጥቂት የፀረ ሰላም ኃይሎች እንቅስቃሴ ተጠልፈህ ወደ ግጭት እንዳትገባና የረጅም ጊዜ የጋራ ክብር ዓላማህን ይዘን የጋራ ሰላምህን በጋራ እንድትጠብቅ ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ድል የሕዝብ ነው!!!

የስድስቱ የኦሮሞ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች

መስከረም 2010

 

ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ የተሰጠ መግለጫ

መስከረም 22 ቀን 2009 የእሬቻን ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓል ለማክበር በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ በተሰባሰቡ የኦሮሞ ዜጎች ላይ ሆን ተብሎ በተወሰደ የመንግስት ያልተገባ እርምጃ የብዙ ዜጎች ሕይወት ተሰዉቷል። አስቀድሞ ሲደረጉ የነበሩ ዝግጅቶች አደጋ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ በመጠርጠር ፓርቲያችን፤ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ “የእሬቻ በዓል የሕዝብ ባህልና ሃይማኖት በጣምራ የሚከበርበት መሆኑ ታዉቆ ማናቸዉም የፖለቲካ ኃይሎች ከዋዜማዉ ጀምሮ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡ አበክረን እናሳስባለን” የሚል መግለጫ መስከረም 10 ቀን 2009 ማዉጣታችንን እናስታዉሳለን።

የሰጠነዉ ማሳሰቢያ የመንግስት ባለሥልጣን ሰሚ ጆሮ ባለማግኘቱና ቀደም ሲልም በሕዝብና በገዥዉ ፓርቲ መሀከል የነበረዉ መልካም ያልሆነዉ ግንኙነት ፈጦ ሊወጣ በመቻሉ በተለይም ወጣቱ የተቃዉሞ ድምፅ በማሰማቱ የመንግስት ኃይሎች በታዘዙት መሠረት የኃይል እርምጃ ወስደዋል። በዚህም የተነሳ ጥቂት በሚባሉ ወጣቶች የተቃዉሞ መፈክር ማንሳት የተነሳ፤ የመንግስት ኃይሎች ኃላፊነት በጎደለዉ ሁኔታ እጅግ ብዙ ሆኖ በተሰበሰበዉና ምንም ማምለጫ መንገድ በሌለዉ ንጹኃን ሕዝብ ላይ የኃይል እርምጃ ተወስዷል። በዚያ ዓይነት ሁኔታ በሕዝብ ላይ የበቀል እርምጃ መዉሰድ እጅጉን የሚከብድ መሆኑ ማመዛዘን ለሚችል ሰዉ የሚከብድ መሆኑ እየታወቀ፤ ከአቅም በላይ የሆነ እርምጃ በመወሰዱ የብዙ ዜጎቻችን ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ አልፏል።

የዚህ መግለጫ አስፈላጊነት ደግሞ እነዚያን በግፍ የተገደሉ ዜጎችን ለማስታወስ ሲባል የመታሰቢያ ፓርክ የሚባል ተገቢ ባልሆነ ቦታ ላይ ተገቢ ባልሆነ አካል መሰራቱ ነዉ። በወቅቱ የተገደሉ ዜጎች ተለይተዉ መላዉ ሕዝብ ባላወቀበትና በገለልተኛ አካል ተጣርቶ በኦሮሞ ሕዝብ ደንብ መሠረት ጉማ ወይም የደም ካሳ ባልተከፈበት ሁኔታ ዉስጥ ሆኖ፤ ገዳዮችና አዛዦቻቸዉ ለፍርድ ሳይቀርቡ ፓርክ ተሰራላቸዉ ሲባል የሟች ቤተሰቦችም ሆኑ መላዉ ሕብረተሰባችን የሚቀበሉት አይደለም። ምክንያቱ ቀላል ነዉ። የሰማዕታት ሐዉልትም ሆነ የመታሰቢያ ፓርክ በተጠያቂዎች አይገነባም። ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስትም ሆነ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሚጠበቅ ነገር ቢኖር የሟቾችን ማንነት በገለልተኛ አካል ይፋ ማድረግ፣ ጉማ ወይም የደም ካሳ መክፈልና ገዳዮችን ለፍርድ ማቅረብ ነዉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ተሰራ የተባለዉ የመታሰቢያ ፓርክም ዜጎቹ ከተገደሉበት ቦታ ርቆ መተከሉ የግብር ይዉጣ ሥራ ከመሆኑም በላይ የታሪክ ሽሚያ ለማካሄድ ካልሆነ በስተቀር የእሬቻ የሰማዕታት ሐዉልትም ሆነ ፓርክ በተጠያቂዎች ሊቆም አይገባም እንላለን። በሌላም በኩል ሕብረተሰቡ እነዚህ የተሰዉ ወገኖች በጥልቅ ሐዘን የሚያስታዉሳቸዉ ከመሆኑም በላይ ስማቸዉንና ምስላቸዉን በዝርዝር ማስቀመጥ ሲገባ እንዲሁ አንድ ቁም ድንጋይ ተክሎ ከጉዳዩ ጋር የማይመስለዉን ሀተታ በጽሑፍ ማስቀመጡ አሳዝኖናል።

ከዚህ ጋርም በፓርኩ የመግቢያ በር ላይ በአፋን ኦሮሞ ተጽፎ የሚገኘዉ “Paarkii Yaadannoo Namoota Ayyanaa Irreechaa Irratti Lubbuun Isaani Tasa Darbe Yaadachuuf Moggaafame” የሚለዉ ዜጎቹ የሞቱት በድንገተኛ ሁኔታ እንደሆነ በጽሑፍ ማስቀመጡ በኦሮሞ ዜጎች መስዋዕትነት ላይ የማፈዝ ያህል ስለሆነ ተጨማሪ የሕዝብና የመንግስት ግጭትን ሳይጋብዝ ከቦታዉ እንዲነሳ እንጠይቃለን።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከኦሮሚያ ክልል ላይ የድንበር ጥያቄ የሚያነሱና በድንበሮች አካባቢ በሚገኙ የኦሮሞ ዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ኃይሎች ጉዳይ ከአሳሳቢ ደረጃም ያለፈና የዜጎቻችንን ሕይወት እየቀጠፈ መሆኑን ተገንዝበናል። ይህ የመሬት ጥያቄ የድንበር አከባቢ ሕዝቦችን በማጋጨት ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት እያስከፈለ ይገኛል። የመሬት ጥያቄዉን አንዳንዴ ሲመለከቱት ኢትዮጵያዊያን በቀጣይ ጊዜያት ዉስጥ አብሮ የመኖር ዕጣ ፋንታቸዉ እያበቃ ያለ ያስመስላል። ምክንያቱም በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብና በምስራቅ ኦሮሚያ በኩል የሚገኙት የገዥዉ ፓርቲ ካድሬዎችና ካቢኔዎች የሕዝቦች አብሮነት እንዲያከትም ፍላጎት ያላቸዉ ይመስላሉ።

በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች በግጦሽ ሳር፣ በኩሬ ዉሃ፣ በጠፈ ከብትና በጥቃቅን ነገሮች ሊጋጩ እንደሚችሉና በአካባቢ ሽማግሌዎችና በጎሳ መሪዎች አማካይነት ሊታረቁ እንደሚችሉ፤ እነዚህ የአገር ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎች ችግሮችን ሲፈቱም እንደነበረ ይታወቃል። የመሬት ወረራዉና የሰዎች ግድያዉ የኦሮሞን ሕዝብ ቁጥርና የኦሮሚያን የቆዳ ስፋት ለማሳነስ ታቅዶ የተቀመጠዉን እስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ያለ ይመስላል። በተለይም በምስራቅ ኦሮሚያ በኩል በሱማሌ ልዩ ኃይል በኦሮሞ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለዉ ጥቃት እጅጉን ያሳስበናል።

ስለሆነም እንደዚህ ዓይነት የጥቃት እርምጃዎች ለወደፊቱ ኢትዮጵያዊያን አብሮነት የማይፈይድና ወቅትን እየጠበቀ የሚፈነዳ ፈንጂ እየሆነ ስለሚቀጥል የሚመለከታቸዉ የመንግስት አካላትና ሕብረተሰቡ አስፈላጊዉን የዕርምት እርምጃ እንዲወስዱ አበክረን እናሳስባለን።

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ

ፊንፊኔ፤ ጳጉሜን 2/2009

ከስናፍቅሽ አዲስ

በመጀመሪያ በጎ ሰውን የማመስገን መንፈስ በኢትዮጵያ ብዙም አይታይም ነበር። ስለ በጎ ሰዎች የማሰብ ስሜቱ በጎንደር ከተማም ነበር። ንስር የተባለ የሽልማት ድርጅትም በ2001 ዓ.ም. በጎ ሰዎችን ላመሰግን እሸልማለሁ ሲል በህግ የሽልማት ድርጅት ሆኖ ተቋቋመ። ከዚያ በኋላ ንሥር የሽልማት ድርጅት በተከታታይ በጎንደር ባህልና ወግ ለሀገር የሰሩ ታላላቆችን ሸለመ፤ በዚህ አግባብም ባለ ሀብቱ አቶ ታዬ በላይ፣ አፍሮ አሜሪካዊው ዶክተር በርናንድ፣ የልብ ህሙማን መርጃው ባለ ራዕይ ዶክተር በላይ አበጋዝ፣ የቱሪዝም አባቱ አቶ ሀብተ ስላሴ ታፈሰ፣ ተመራማሪው አቶ ታለጌታ እንደ ቅደም ተከተላቸው ለመሸለም በቁ።

ከዚህ ሽልማት ከዓመታት በኋላ በአዲስ አበባ በዲያቆን ዳንኤል ክብረት አሳሳቢነት እና ጀማሪነት የበጎ ሰው ሽልማት የሚል ሀሳብ ተጀመረ። በሀሳቡ መነሻ እንዲህ ያለ ነገር በሀገራችን ስላልተሰራ ጀመርነው በሚል ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ግን በጎንደር በጎ ሰው ሽልማት ላይ የታደሙ ጋዜጠኞች ሳይቀር የመጀመሪያው ሀሳብ ብለው ሳይሞግቱት አጮሁት፤ ተጀመረ ቀጠለ።

መቼም በጎ ሰውን እናመሰግናለን ለማለት ለምን እከሌን ተከትሎ እከሌ ቀጠለ አሊያም ጀመረ የሚለው ሙግት መልካም የሚመስልን ሀሳብ የሚያደናቅፍ ስለሚመስለኝ ያን ማንሳቱ ተገቢ አይደለም። በጎ ሰው አደረጃጀት እንዳለው ሰምቻለሁ። ዳኞችም አሉት የሚል ነገር ይደመጣል። ዳኞች ናቸው ተብለው ከቀረቡት ሰዎች መካከል እሱ እያለ እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ሆነ የምንለው አንድ ሰው አለ። ሰርጸ ፍሬ ስብሐት ነው። የሙዚቃ ባለሙያው ሰርጸ መልካም እና ብሩህ አእምሮ ያለው ነገሮችን በስል እና በሰከነ መንፈስ የሚያይ ሰው ነው። ይሄን አካሄድ ዝም ብሎ ለማየት ያልፈለግኩትም ለዚሁ ነው።

በኢትዮጵያ ምድር የኖህ ልጅ ምድሪቷን ከሚረግጥበት ቀን እስከ ዛሬ እንዲህ ያለ ቅጥ ያጣ እውቅና አሰጣጥ ሰምቼም፣ አንብቤም፣ በተረት አድምጬም አላውቅም። ስህተቱ የማይነካ ሰው ሀሳብ ሆኖ ሲብስ ቆመን ማየት ቀጥለናል።

በጎ ሰው አንድ በጎ ሰው ለመሸለም አስር በጎ ሰዎችን ቅስም የሚሰብር ከሆነ ይሄ እንደ ሙስናው፣ እንደ አፈናው፣ እንደ መብት ጥሰቱ ሁሉ በህዝቡ ላይ የመጣ መዐት ነው ብዬ አምናለሁ። መስራቹ ለቤተክርስቲያን ቅርብ ነው፤ ቤተክርስቲያን ለዘመናት የማታፍርበት አንድ የአበው ትውፊት አላት። በደቀ መዝሙር በአቻ እና በመምህር መካከል ያለውን ድንበር በአግባቡ የምታስጠብቅ ናት። ይሄንን የሚያፈርሰው የበጎ ሰው ሽልማት ተስፋዬ ገሰሰን ያክል ሰው ከተማሪው ከአለማየሁ ታደሰ ጋር አወዳድሮ አሸንፈሃል ብሎ ሲሸልመው እንደማየት ልብ የሚሰብር ነገር የለም።

ለዚህ ነው በቅኔ ጉባኤ እንኳን መምህር ተማሪው ተማሪ መምህሩ ላይ ቅኔ የማይሞላው። አለም የአቻዎች ናት። አሁን ጋዜጠኛ ንጉሤ አክሊሉ አሸነፈ፤ ተሸለመ። ንጉሤ የሚገባው ሰው ነው። የማይገባው የተወዳደረበት መድረክ ነው። የሸገሩ ጋዜጠኛ እሸቴ አሰፋ እና ሸገር ራዲዮን ተወዳድሮ ንጉሤ አሸነፈ ማለት መልዕክቱ እሸቴና ሸገር አንድ ላይ ሆነው የንጉሤን ያክል አልሰሩም ማለት ነው። እሸቴ በግሉ ቢወዳደርም የሸገርም ዋና አዘጋጅ ነውና።

ተቋም እና ሰውን አንድ ላይ ማን ይበልጣል ብሎ ለውድድር መቀመጥ ሀገሬ እንዴት ያሉ ምጡቅ ባለ አእምሮዎችን አፈራች የሚያሰኝ ስላቅ ውስጥ ይከተናል። ሰው ግለሰብ ነው። ተቋም ተቋም ነው። ለምሳሌ የዘንድሮውን ሽልማት አስቡት ሆስፒታል የመራ እና የኦዲት መስሪያ ቤት የመራ በአንድ ዘርፍ የላቀ ተቋማዊ መሪ ተብሎ ቀርቧል። ያ ጤና ያ ሂሳብ ይሄን ፊደል ማወቅ ሳያስፈልግ የማይሰራ ስህተት በስህተት ሆነ ብዬ ላልፈው ያልፈለኩትም ለዚሁ ነው። አምስት አመታት ሙሉ እንዲህ ያለው አሰራር የቀጠለው በርቱ ባይ አሽሙረኛ በዝቶ ከሆነ ለምን አንድ እድል የራሴን አልሞክርም አስብሎ ሰንደቅ ላይ ያመጣኝም ይሔው ነው።

ለምሳሌ አንድን የታሪክ ምሁር ከአንድ የጤና ምሁር ጋር አወዳድራችሁ ታሪክ አሸንፏል ማለት አንድ ሰው ለመሸለም ሌላ ሰው በሰራው እና ለሀገሩ በኖረው ስሜቱን መግደል እና ክብሩን መንካት ነው። አንድን ታላቅ ተቋም አስር ዳኞች ስለመረጡት ከአንድ ግለሰብ ጋር አወዳድሮ ግለሰቡን መሸለም ሽልማቱን ዋጋ እንዲያጣ ማድረግ ይመስለኛል። ከዚህ ቀደም እንደ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ያሉ ተቋማት ከግለሰብ ጋር ሲወዳደሩ አይተን ስህተት መስሎን ነበር ዘንድሮም ተደግሞ አየነው።

ይህ የበጎ ሰው ሽልማት በጎ ያልሆኑ ጉዞዎች ማሳያ ነው። ማንም መስራት የሚችለው ነገር ለምን እንዳቃታቸው ሊገባኝ አልቻለም። የቻሉት ማንም መስራት ያልቻለውን ጥቂቶች የሚደፍሩትን በጎ ሰው መሸለም ነው። ታዲያ ይሄን የመሰለ ታላቅ ሀሳብ ችሎ እንዴት ተራ ነገር በየዓመቱ ስህተት ሆኖ ይቀጥላል?¾ 

 

 

·        መስራቹ የዓመቱ የበጎ ሰው ተሸላሚ ሆኗል

“ጳጉሜን ለጤና” የተሰኘው ዓመታዊ ነፃ የምርመራ አገልግሎት እነሆ ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ ጳጉሜን ጠብቆ ከጳጉሜ 1 እስከ 5 ቀን 2009 ዓ.ም ሊካሄድ ነው። ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል እንደ አምና ካቻምናው ሁሉ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። እንደውም ዘንድሮ ካለፉት ዓመታት በላቀ መልኩ የሲቲ ስካን፣ የኤም አር አይ እና የአልትራሳውንድ ምርመራን በነፃ ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የማዕከሉ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ኃይሉ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

“ጳጉሜን ለጤና” የተሰኘው ዓመታዊ የነፃ ምርመራ በውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ይሰጥ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዳዊት፤ ማዕከሉ እስካሁን ከ7ሺህ በላይ ለሚደርሱ ህሙማን ነፃ የምርመራ አገልግሎት እንደሰጠም ባሳለፍነው ቅዳሜ (ነሐሴ 27 ቀን 2009 ዓ.ም) ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተወክለው ከመጡት ዶ/ር ይበልጣል መኮንን እና ከማዕከሉ ሲኒየር ራዲዮሎጂስት ዶ/ር አበበ መኮንን ጋር በጋራ ሲናገሩ ሰምተናል።

“በጤናው ዘርፍ ማህበራዊ ኃላፊነታችንን መወጣታችን ለእኛ ወጪ ሳይሆን ጥቅም ነው” ያሉት አቶ ዳዊት፤ በዚህ ዓመት “ጳጉሜ ለጤና” የምርመራ አገልግሎት ለማግኘት ከመንግስትና ከግል ሆስፒታሎች የሚመጡ ህሙማንን ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። ለዚህም በመጀመሪያ ወደማዕከሉ የሚመጡ አገልግሎት ፈላጊዎች የሲቲ ስካን፣ የኤም አር አይ እና የአልትራሳውንድ ምርመራ እንዲያደርጉ የሀኪም ትዕዛዝ ያረፈበት ወረቀት ማምጣት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ በተጨማሪም የምርመራውን ወጪ ለመሸፈን እንደማይችሉ ከሀኪም የተሰጠ የማረጋገጫ ወረቀት ካቀረቡ የምርመራ አገልግሎቱን በነጻ ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።

በመግለጫው ላይ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን ወክለው በመድረኩ ላይ የተገኙት ዶ/ር ይበልጣል በበኩላቸው፤ መሰል ተቋማት ማህበራዊ ኃላፊነትን በሚያስተዋውቁ ተግባራት ላይ ቢሰማሩ ማህበረሰባቸውን ከመጥቀምም ባለፈ ራሳቸውን በበጎ ያስተዋውቁበታል ብለዋል። አክለውም መንግስት በያዘው የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ውስጥ ጥረትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለሁሉም ማህበረሰብ መስጠት አንዱ መሆኑን አስታውሰዋል። ሌሎች በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት ይህንን መሰል ተግባራትን እንዲያከናውኑ ቢደረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቅዳሜው መግለጫ ወቅት ከውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ነፃ የምርመራ አገልግሎት ያገኙ ህሙማን ስለማዕከሉ የሰጡትን ምስክርነት የሚያሳይ የአስራአምስት ደቂቃ ፊልም የተመለከትን ሲሆን፤ በአገልግሎቱ ያገኙትን ጠቀሜታና ምስጋናቸውን እንባ እየተናነቃቸው ጭምር ሲገልጹም ለመታዘብ ችለናል።

“ጳጉሜን ለጤና” ዘንድሮ ከጳጉሜ 1 እስከ 5 የሚካሄድ ሲሆን፤ ከውዳሴ በተጨማሪ ሌሎችም የጤና ተቋማት አብረው የሚሰሩበት ዕድል መኖሩን አቶ ዳዊት ተናግረዋል። አብዛኞቹ የምርመራ አገልግሎት ፈላጊዎች በመገናኛ ብዙሃን መረጃ ላይ ተመስርተው ወደማዕከላቸው እንደሚመጡ ያስታወሱት አቶ ዳዊት፤ ባለፈው ዓመት ብቻ “ጳጌሜን ለጤና” የምርመራ አገልግሎት ለማግኘት ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መጥተዋልም ብለዋል። ይንንም የምርመራ አገልግሎት ለመስጠት የተመዘገቡትን አገልግሎት ፈላጊዎች እስከ ጥቅምት ወር ድረስ አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር አስታውሰዋል። አብዛኛዎቹ ከክልሎች የሚመጡ ህሙማን መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ዳዊት፤ አብዛኞቹ የመመርመሪያ ገንዘብ አጥተው ለስምንት ወራት የሀኪም ወረቀቶቻቸውን ይዘው በጭንቀት አንዳች መፍትሄ ይጠብቁ እንደነበር መናገራቸውን ያስታወሳሉ። በመጨረሻም “ውዳሴ ይህንን ማህበራዊ ኃላፊነት በመወጣቱ ሌሎች ተቋማትም እኔስ ምን ማድረግ እችላለሁ በሚል የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማሳሰብ ጭምር በየዓመቱ የሚካሄድ የምርመራ ፕሮግራም መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል። “ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት የቅንጦት ወይም የትርፍ ጉዳይ አይደለም። ትልቅ ገንዘብ ሳይሆን ትልቅ ልብ የሚያስፈልገው ተግባር ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።

የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ሲኒየር ራዲዮሎጂስት የሆኑት ዶ/ር አበበ መኮንን በሰጡት ሙያዊ ማብራሪያ፤ በማዕከሉ ከሚሰጡት የምርመራ አገልግሎቶች ውስጥ ትንሹ “ኤክስ-ሬ” ነው በማለት ያስረዳሉ። በሌላም በኩል የሲቲ ስካን፣ የአልትራ ሳውንድ፣ የኤምአርአይ መሆናቸውን ዘርዝረው “ሲቲ ስካን እና “ኤስክ-ሬ” በተወሰነ መልኩ የጨረር ምርመራ የሚሰጥባቸው በመሆናቸው ሙሉ በሙሉ በሀኪም ሲታዘዝና ለህመምተኛውም አስፈላጊነታቸው ከፍ ሲል ብቻ የምንጠቀማቸው ይሆናሉ ብለዋል። በምርመራ ሂደት ውስጥ ማለፍ ያለባቸውንና የሌለባቸውን ህሙማን ከሃኪሞቻቸው ጋር በመነጋገር የመለየት ስራን እንደሚሰሩ የተናገሩት ዶ/ር አበበ፤ ለምሳሌም ሲጠቅሱ በኤም.አር.አይ እንዳይታዩ ከሚከለክሉት መካከል የልብ ባትሪ ያላቸው ህሙማን፣ አርቴፊሻል የጆሮ ማዳመጫ የሚጠቀሙ ወይም በአንዳች አደጋ ምክንያት በሰውነት ክፍላቸው ውስጥ ጥቃቅን የብረት መሳሪያዎች የተገጠመላቸው ሰዎች ይህን ህክምና አይመከሩም ብለዋል።

የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዳዊት ኃይሉን፤ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ላለፉት ተከታታይ ዓመታት የሰሯቸውን መልካም ተግባራት ከግምት ውስጥ በማስገባት የዘንድሮው “የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት” ፕሮራም “በበጎ አድራጎት ዘርፍ” ዕጩ አድርጎ አቅርቧቸው ነበር። ይህም በመሆኑም በዘርፉ ለውድድር ከቀረቡት የተቀናጀ የቤተሰብ አገልግሎት ድርጅት መሥራችና መሪ ከሆኑት መቅደስ ዘለለው እና በደብረዘይት ከተማ ችግረኞችን በመርዳት ከሚታወቀው ውጣት ሰለሞን ይልማ ጋር ተፎካክረው ባሳለፍነው እሁድ (ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም) በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል በተካሄደው ደማቅ የሽልማት ሥነ-ስርዓትም “በበጎ አድራጎት” ዘርፍ የ2009 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ በመሆን ዋንጫና የምስክር ወረቀቱን አቶ ዳዊት ኃይሉ ተቀብለዋል። ይህ ተግባር የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከልን ማህበራዊ እንቅስቃሴ በጉልህ ከማሳየቱም ባለፈ ሌሎች መሰል ተቋማትም ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት የሚመለሰውን ብድራት ያሳየ ነው ማለት ይቻላል።

    

Page 1 of 12

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us