በቀሲስ ምንዳዬ በ‹ኑ…!› የመዝሙር ‹አልበም› መነሻነት የተቃኘው የኢትዮጵያ ቤ/ን የመዝሙር አገልግሎት ዕድገትና ተግዳሮት አጭር ቅኝት

Wednesday, 03 February 2016 15:12

 

በዲ/ን ኒቆዲሞስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንጋፋ ዘማሪያን መካከል የኾነው ቀሲስ ምንዳዬ ብርሃኑ ባለፈው ሰሞን ‹‹ኑ…!›› በሚል ያወጣውን ቁጥር ፯ የመዝሙር አልበሙን በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አዳራሽ፣ ብፁዓን አባቶች፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንትና ካህናት፣ የታሪክ ምሁራን እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ እንግዶች በተገኙበት አስመርቋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዘማሪያን የመዝሙር አልበማቸውን ባስመረቁበት ጥቂት ዝግጅቶች ላይ ለመገኘት ዕድሉን አግኝቼያለኹ። ይሁን እንጂ ለዚህ ለዛሬው ጽሑፌ መነሻ የኾነኝ በቀሲስ ምንዳዬ የመዝሙር አልበም ምረቃ መንፈሳዊ ዝግጅት ላይ እምብዛም ያልተለመዱና ግና መኾን የሚገባቸው፣ የዚህ መዝሙር አልበሙ ምረቃው አካል የኾኑ ለየት ያሉና ሊበረታቱ የሚገባቸው ቅድመ ዝግጅቶቹ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ኾኖውኛል።

ከእነዚህም መነሻ ምክንያቶቼም ዛሬ ዛሬ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዘማሪያን እየወጡ የሚገኙ መዝሙራት በርካታ ትችቶችንና ወቀሳዎችን እያስተናገዱ በሚገኙበት በዚህ ወቅት ቀሲስ ምንዳዬ ብርሃኑ የመዝሙሩን ግጥምና ዜማ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ግምገማና ዳሰሳ እንዲደረግበት ያደረገበት ቅድመ ዝግጅት ሊጠቀስና ሊበረታታ የሚገባው ነው። ሌላኛው ምክንያቴ ደግሞ ቀደምት የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንትና አባቶች ለመንፈሳዊ መዝሙር አገልግሎት ዕድገት ያበረከቱት በጎ አስተዋጽኦ እንዲዘከርና ዕውቅና እንዲቸራቸው የተደረገበት፣ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ከመንፈሳዊ ልጆቻቸው አድናቆትና ምስጋና እንዲቸራቸው የተደረገበት ልዩ ዝግጅት ነው።

በዚህ የቀደምት የቤተ ክርስቲያቱን አባቶችንና ሊቃውንትን ሥራ ከመዘከርና ምስጋና የማቅረብ ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዜማ መሠረት ከኾነውና ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ከተቸረው ከማሕሌታዊው ቅዱስ ያሬድ ጀምሮ ከዕውቁ ኢትዮጵያዊ፣ የቋንቋ፣ የታሪክና የሥነ-መለኮት ምሁር ከሆኑት ከዶ/ር ዓለሜ እሸቴ እስከ ቅድመና ድኅረ አብዮት ድረስ የነበሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት አባቶች፣ አገልጋዮችና ዘማርያን ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መዝሙር ዕድገት ብቻ ሣይሆን ለአገራችን ዘመናዊ ሙዚቃ ጅማሮና ዕድገት ባበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦቸው ጭምር የተዘከሩበትና ዕውቅና የተቸሩበት መንፈሳዊ ዝግጅት ነበር የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቀሲስ ምንዳዬ ብርሃኑ፣ የ‹ኑ…!› የመዝሙር አልበም ምርቃት ደማቅ ዝግጅት።

 በቀሲስ ምንዳዬ የመዝሙር አልበም ላይ በቀረቡት ጥናታዊ ዳሰሳዎች ላይ ጥቂት ነገሮችን ከማለቴ በፊት ግን ላለፉት ፲ እና ፲፭ ዓመታት በኢትዮጵያ ቤ/ን ዘማሪያን እየወጡ በሚገኙ የመዝሙር አልበሞች ላይ በሚነሡ ክርክሮች፣ እየቀረቡ ባሉ ትችቶችና ወቀሳዎች ዙርያ ጥቂት ነገሮችን ለማለት እወዳለኹ። ዛሬ ዛሬ በኢትዮጵያ ቤ/ን ዘማሪያን እየወጡ ያሉ መዘሙራት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንትም ኾነ ምእመናን ዘንድ በርካታ ትችትና ወቀሳ እየተሰጠባቸው እንደኾነ እየታዘብን ነው። በተለይ ደግሞ ገበያና ዝና ተኮር የኾኑ ዘማሪያንና መዝሙራት በአገልጋዮችና በምእመናን መካከል ለክርክር፣ ለመለያያየት፣ ለጥላቻና እንዲያም ሲል ለጠብ እየጋበዙ ነው።

ከሰሞኑን እንኳን ጥምቀትን በዓል ምክንያት በማድረግ ‹ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን የማይወክሉ መዝሙር መሰል ዘፈኖችን ባለመዘመር እንተባበር› የሚል የሶሻል ሚዲያ ዘመቻውን እንዲቀላቀሉ የሚጠይቁ ፖስቶችን አስተውያለሁ። እነዚህ ገበያንና ዝናን ተኮር ኾነው እየወጡ ያሉ የመዝሙር አልበሞች ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማና ቀኖና፣ ታሪክና ትውፊት አንፃር ሲገመገሙ በርካታ ግድፈቶች ያሉባቸው እንደኾኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንቶችና አባቶች መናገር ከጀመሩ ውለው አድረዋል፤ የሚሰማቸው አላገኙም እንጂ። እነዚህ ምድራዊ ምቾትን፣ ዓለማዊ ምኞትንና ‹‹ስኬትን›› የሙጥኝ ያሉ የሚመስሉ እነዚህ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የሚወጡ አንዳንድ መዝሙር ተብዬዎች፣ በአጭር ቃል የዘማሪያኑን የግል ‹‹ስኬታቸውን›› እና ምቾታቸውን የሚያውጁ፣ በምድራዊ ሀብትና ቅጥ በሌለው በዓለማዊ ምኞት የነኾለለ ሥጋዊና ዓለማዊ ስሜታቸውንና እኩይ ምኞታቸውን የሚያጋልጥ እንደሆነ ገሃድ እየወጡ ነው።

እነዚህ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ፣ ታሪክና ባህል፣ ወግና ትውፊት በእጅጉ እየራቁ እየሔዱ ያሉ ዘማሪዎቻችን ዛሬም የቤተ ክርስቲያኒቱን አባቶችና ሊቃውንቶች ምክርና ተግሣጽ ከቁብ የቆጠሩት አይመስሉም። በዘመናዊነት ስም ከራስ ባህልና ታሪክ፣ ሥርዓትና ትውፊት እያፈነገጡ የምዕራባውያኑ የረቀቀ የባህል ወረራ ጥገኛ የመሆን ሕልሙ፣ ሩጫውና ግሥጋሤው ተባብሶ የቀጠለ ይመስላል። እንደውም ከሰሞኑን ራሱን ‹‹ሕጋዊው ሲኖዶስ›› ብሎ የሚጠራው፣ በአሜሪካ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ፣ ዕውቅ ምሁርና አንጋፋ የሆኑ አንድ አባት፣ ‹‹በኦርጋን መዘመር እንችላለን፣ የቤተ ክርስቲያናችን ካህናትም በኦርጋን መዘመርን መማር አለባቸው።›› የሚል ይዘት ያለው መልእክትን አስተላልፈዋል። ይህን መልእክታቸውን ተከትሎም በበርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ምእመናን ዘንድ ያስነሳውን ሙግትና ክርክር በሶሻል ሚዲያውና በተለያዩ ድረ ገጾች ላይም እየታዘብን ነው።

ለመሆኑ ይህ በቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ ሣይሆን ለአገራችን ኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካና ለዓለም ሁሉ መደነቂያ የሆነ የዜማ ሥርዓትና በርካታ የራሳችን የሙዚቃ መሣሪያ ያለን ሕዝቦች በምን ምክንያት ይሆን የሌሎችን የሙዚቃ መሳሪያ መጠቀም ያስፈለገን?! በመሠረቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዓለም ገና ስለ ሙዚቃና የዜማ ምሥጢር ማወቅና መነጋገር ከመጀመሩ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ጥልቅና ሰማያዊ  የሆነ መንፈሳዊ ዜማ ድርሰትና ምልክቶች ምን መሆኑን ሳይደርስበት በፊት በታላቁ ሊቅና ማሕሌታይ በቅዱስ ያሬድ አማካይነት የሰማያዊ ድርሰትና ዜማ ባለቤት ለመሆን የበቃች ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ናት።

ይህን እውነታ በኖርዌይ ትሮንድሄም እ.ኤ.አ በ2007 ዓ.ም. በተካሄደው በ፲፮ኛው ዓለም አቀፍ ኢትዮጵያ ጥናት ኮንፈረንስ ላይ ‹‹The Significance of St. Yared’s Music in the Age of Globalization›› በሚል ርእስ ጥናታዊ ወረቀት ያቀረበው በአሜሪካ ኮሎምቢያ የኦሃዮ ዩኒቨርስቲ ምሁሩ ሊቀ ዲያቆን ክፍሌ አሰፋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን ዜማ ያለውን መንፈሳዊ ምስጢር፣ ረቂቅነትንና ልዩ ውበቱን ሲገልጽ፡-

‹‹የቅዱስ ያሬድ የኢትዮጵያ ቤ/ን ዜማ እጅግ ጥንታዊ፣ ጥልቅ፣ ከመንፈስና ከነፍስ በሚመነጭ ፍሰትና ልዩ ጥበብ- የተፈጥሮን የለሆሳስ ድምፅና የፍቅርን ልዩና ረቂቅ ዜማ የሚያስቃኝ ሰማያዊና ሕያው መንፈሳዊ ዜማ ነው።›› በተጨማሪም ሊቀ ዲያቆን ክፍሌ በዚሁ የጥናት ሥራው ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን ጥንታዊ ዜማ ከእግዚአብሔር ፍጥረታት/ከተፈጥሮ ጋር በእጅጉ የጠበቀ ምሥጢርና ትስስር እንዳለው የሚከተለውን ሐሳብ ያክላል፡- ‹‹Ethiopian liturgical music is quite unique; those who listen carefully will recognize the haunting sounds of mother nature.››

ይሁን እንጂ ይህ ሰማያዊ ነው የተባለውና ለሺሕ ዓመታት የዘለቀው የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ዜማና የአምልኮተ ሥርዓት ዛሬ ዛሬ በእጅጉ እየተበረዘ ነው የሚሉ ታዛቢዎችን በብዛት እያስተናገደ ነው። በተለይ በዘመናችን ወጣት ዘማሪያን እያወጧቸው ያሉ መዝሙሮች፡- በአብዛኛው ምድራዊ ምኞቶችና ፍላጎቶች ላይ የሙጥኝ ያሉ፣ የጌታችንና መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የመስቀሉን ውለታና ፍቅር ኃላፊና ጠፊ በኾነ ምድራዊ ሀብትና ክብር የሚያነጻጽርና የሚለካ፣ በአብዛኛው ገበያ ተኮር የሆኑ፣ በእጅጉ ዓለማዊነት ያየለባቸው፣ ለጸሎት፣ ለንስሓና ለተመስጦ እንዲሁም ልዩ ምሥጢር ላለው ሰማያዊና ዘላለማዊ ሕይወት መንፈስንና ነፍስን ወደወዲያኛው ዓለም ለማሻገር አቅም የሚያነሳቸው፣ ደካማና ልፍስፍስ ናቸው…ወዘተ የሚሉና ተመሳሳይ የኾኑ ብርቱ ትችቶችንና ወቀሳዎችን እያሰተናገዱ ይገኛል።

መዝሙሮቻችን መዘመን አለባቸው፣ በዘመናዊ መሳሪያ ካልዘመርን ምናች ነው ታዲያ ክርስቲያን?!፣ መፈታት አለብን የምን መታሰር ነው- ታሪክና ባህል፣ ትውፊትና ወግ እያሉ በሰለጠነ ዘመን የምን ኋላ ቀርነት ነው ያሉ፣ የኢትዮጵያን ቤ/ን እናድሳልን በማለት የተነሡ ‹የተሐድሶ አራማጆች› እና የ‹መዝሙር አብዮተኞች› ነን ባዮች ዛሬ ምን ላይ እንዳሉ የምናውቅ እናውቃለን። መንፈሳዊ ክስረታቸውንና ውርደታቸውን በሙዚቃ መሳሪያ ጋጋታ፣ በተዋበ መድረክና ውድ ቁሳቁስ ለማካካስ እየተጉ ያሉ የእምነት ተቋማት በዘመናዊነት ስም ውስጣቸው ነትቦ፣ ተበልተው፣ ተራቁተውና ፈራርሰው ወዴት አቅጣጫ እየተጓዙ እንዳለም እያየን፣ እየታዘብን ነው።

እንግዲህ በዚህ በአጭሩ ለመዳስ በሞከርኩት በቤተ ክርስቲያናችን እየወጡ ባሉ መዝሙራትና ዘማሪያኖቻችንን በተመለከተ በሚነሳው ትችትና ወቀሳ አንጻር የቀሲስ ምንዳዬ የ‹ኑ…!› የመዝሙር አልበም በታሪክ ምሁሩ በዲ/ን ታደሰ ወርቁና በኢትዮጵያ ቤ/ን ታሪክ ተመራማሪውና በሰባኪ ወንጌል በዲ/ን ዳንኤል ክብረት አጠር ያለ ምሁራዊና መንፈሳዊ ዳሰሳ ተደርጎባቸው ነበር። ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ባቀረበው አጭር ዳሰሳው፣ የቀሲስ ምንዳዬ የ‹ኑ…! የመዝሙር አልበም ግጥሞች ኢትዮጵያ ቤ/ን አስተምህሮ- ዶግማና ቀኖና፣ ታሪክና ባህል፣ ወግና ትውፊት ከመጠበቅ አንጻር ግባቸውን የመቱ እንደሆኑ የመዝሙራትን ግጥሞች በማንሣት ምሁራዊ ትንታኔውን አቅርቦአል።

ዲ/ን ዳንኤል በዚህ ትንታኔውም የቀሲስ ምንዳዬ መዝሙራት ግጥሞች- የኢትዮጵያ ቤ/ንን መንፈሳዊ ተጋድሎ፣ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን፣ የአበው ሐዋርያዊትን፣ ቅዱሳን፣ የሰማዕታትንና የጻድቃንን እስከ ሞት ድረስ የዘለቀ የእምነታቸውን ተጋድሎ፣ የፍቅራቸውን ጽናት፣ ትዕግሥታቸውንና ሰማያዊ ተስፋቸውን- መጽሐፍ ቅዱስንና ከቤተ ክርስቲያኒቱን የአዋልድ መጻሕፍት አስተምህሮን መነሻና መሠረት ያደረገ እንደሆነ በዚህ ጥናታዊ ዳሰሳው አቅርቧል። በተመሳሳይም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሩቅ የኾነው ዲ/ን ታደሰ ወርቁ፣ የኑ…! መዝሙር ‹አልበም› በመዝሙራዊና ኦርቶዶክሳዊ ማንነት! በሚል ርዕስ በዘመናት ከፋፍለው /በPeriodization በቀሲስ ምንዳዬ መዝሙራት ግጥሞች ላይ ሰፋ ያለ ቅኝታዊ ዳሰሳቸውን አቅርበዋል።

ዲ/ን ታደሰ በዚህ ቅኝታዊ ዳሰሳቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን በአማርኛ የቀረቡ መዝሙራትን በድኅረ ኢጣሊያ ወረራ፣ በድኅረ አብዮት፣ በዘመነ ኢሕአዴግና አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ- በቤተ ክርስቲያኒቱ እየወጡ ያሉ መዝሙራትን የግጥም ይዘት በተመለከተ ሰፋ ያለ ትንታኔ አቅርበዋል። የታሪክ ምሁር በቅኝታዊ ዳሰሳቸውም የቀሲስ ምንዳዬ መዝሙራት ግጥሞች ቀላልና ሁሉም ሊረዳቸው የሚችሉ፣ ዘይቤያዊ /Alegorical፣ እቅበተ-ሃይማኖት/Apologist ተምሳሌታዊና በቃላት አመራረጣቸውም የኢትዮጵያን ቤ/ን ውበትና መዓዛ ያልተለያቸው፣ ምሁራዊና መንፈሳዊ ምስጢርና ጥልቀት ያልተለያቸው መሆናቸውን ገልጾአል።

ግጥሞቹ ጸሎታዊ ኾነው ምስጋናዊ ይዘት ያላቸው፣ ለዕንባ፣ ለለቅሶ፣ ለጸጸትና ለእውነተኛ ንስሓ የሚያበረታቱ መሆናቸውንም ጨምሮ አንሥቷል። በማጠቃለያውም ዲ/ን ታደሰ ወርቁ ዘማርያን የመዝሙሮቻቸው ዜማና ግጥም የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ- ዶግማና ቀኖና፣ ታሪክና ባህል፣ ትውፊት፣ ወግና ሥርዓት በጠበቀ መልኩ ለማቅረብ መትጋ እንዳለባቸው የአደራ መልእክቱን አስተላልፏል።

በጽሑፌ ማጠቃለያም ዘማሪዎቻችንና መዝሙሮቻቸው መንፈሳዊ መልእክታቸውና ይዘታቸው ላቅ ያለና የመጠቀ፣ ዓለማዊነትንና ዓለማዊ ምኞትን የተጸየፉ፣ ለሰው ልጆች ኹሉ ፍቅርን፣ ቅንነትንና በጎነት የሚሰብኩ፣ ከታሪካችን፣ ከባህላችንና ከማንነታችን ጋር የማይጣረሱ ይሆኑ ዘንድ ለማድረግ፣ ዘማሪዎቻችን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንትና ምሁራን ልብና ጆሮ ሊሰጧቸው ይገባል ወንድማዊ መልእክቴ ነው። አበቃሁ!!

ሰላም!

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
2066 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us