ምትሃታዊው መስኮት

Wednesday, 10 February 2016 13:42

 

 

በመኩሪያ መካሻ

 

‹‹ቴሌቪዥን መጣ!›› (TV is here to stay!)


ቴሌቪዥን ለአንድ ህብረተሰብ የዕድገትና የዕውቀት ሂደት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ባህላዊ ተፅዕኖም ያሳድራል። የመረጃና የመዝናኛ ምንጭ በመሆን ሰዎች ከአደባባይ ወደ ቤት ገብተው (Toolshade Home) እንዲመለከቱ ያደረገ የጊዜው ተፅዕኖ ፈጣሪ የኮሙኒኬሽን መሣሪያ ሆኗል። የአምስተኛው የኮሙኒኬሽን አብዮት ዘመን ግኝትም ነው። የቴሌቪዥንን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ለመግለጽ አንድ አነስተኛ ምሳሌ በቂ ይሆናል።


ጥናቱ ከ4 ዓመት እስከ 6 ዓመት የሆኑ ህፃናትን ‹‹ከቴሌቪዥንና ከአባባ ማንን የበለጠ ትወዳላችሁ?›› በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ 54 በመቶ የሚሆኑት የመለሱት - ቴሌቪዥን!›› በሚል ነበር። (Mingo,as qtd in Vivan, 1983)። በዓለም ላይ በተለይ በእንግሊዝ በ1936 (እኤአ)፣ በአሜሪካ ደግሞ በ1939 (እኤአ) ለመጀመሪያ ጊዜ ቴሌቪዥን በቀጥታ ለህዝብ ስርጭት መጀመሩ ይታወሳል። ይህ ማለት ቴሌቪዥን ወደ ኢትዮጵያ የገባው ከ28 ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው።


ቴሌቪዥን በኢትዮጵያውያን መኖሪያ ቤት ውስጥ ከገባ እነሆ 5ዐ ዓመት ሆነው። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለተመልካቾቹ ዝግጅቱን ለማቅረብ የቻለውና ጥቅምት 23 ቀን በ1957 ዓ.ም ሊቋቋም የበቃው አምስት የተለያዩ ሂደቶችን በማለፍ መሆኑን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የታሪክ ማህደር ያወሳል (ለይኩን፣ 1994 ዓ.ም)።


የመጀመሪያው ሙከራ አፄ ኃይለሥላሴ የብር ዕዮቤልዩ የንግሥና በዓላቸውን በሚያከብሩበት በ1948 ዓ.ም ሲሆን፣ ይህም አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን የኤግዚቢሽን ማዕከል (Pavilion) ነበር። ኤግዚቢሽኑ የተዘጋጀው በብሪትሽ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (BBC) አማካኝነት ሲሆን በኤግዚቢሽኑ ውስጥ ብቻ የሚሠራጭ የዝግ ሰርኪዮት (close-circuit) ዘዴ ዝግጅቱን ማስተላለፍ የቻለበት ወቅት እንደነበር ይጠቀሳል። ይህ ወቅት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለመመስረት የተደረገ የእርሾነት ዝግጅት ነበር ማለት ይቻላል። በበለፀገውም ዓለም ቢሆን ቴሌቪዥን ሲጀመር በቅድሚያ በዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖች ላይ ታይቶ እንደነበር ድርሳናት ይጠቁማሉ።


ሁለተኛው ከ1952-1953 ዓ.ም ያለው ጊዜ ይጠቀሳል። በወቅቱ ደጃዝማች ዳንኤል አበበ የተባሉ መኳንንት የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም ያደረጉት ጥረት ሳይወሳ አይታለፍም። በወቅቱ ለሚኒስትሮች ም/ቤት የግል ቴሌቪዥን ለማቋቋም የሚያስችላቸውን ፕሮፖዛል አቀረቡ። ደጃዝማቹ ያቀረቡትን የማቋቋሚያ ፕሮፖዛል ም/ቤቱ ከተነጋገረበት በኋላ ተቀባይነትን አጣ። ለደጃዝማቹም የተሰጠው መልስ በግለሰብ ደረጃ የቴሌቪዥን ጣቢያ ማቋቋም አይቻልም! የሚል ቁርጥ ያለ መልስ ነበር።


ሦስተኛው ሙከራ የተደረገው በ1955ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጽ/ቤት በአዲስ አበባ ሲቋቋም ነው። በወቅቱ በአፍሪካ አዳራሽ ብቻ የተወሰነ የበዓሉን ሥነ-ሥርዓት የሚያሳይ ስርጭት ተካሂዷል። ይህ ወቅት ገና ነፃነታቸውን ላገኙ ለአዳዲሶቹ የአፍሪካ መንግሥታት ትልቅ መነሻ እንደሆነ የሚያጠራጥር አልነበረም (Bourgeult, as qtd in Brhanu, 1995)።


በአራተኛው ሙከራ በግለሰብ ደረጃ ለማቋቋም የነበረው ፍላጐት ከመከነ በኋላ በድርጅት ደረጃ ለማቋቋም የተደረገ ጥረት ነበር ማለት ይቻላል። ይኸውም የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ድርጅት የንግድ ቴሌቪዥን ጣቢያ የማቋቋም ፍላጐት ያሳየበት ወቅት ነበር። ሆኖም ግን ድርጅቱ ያስቀመጠውን ዕቅድ ሊያሳካ አልቻለም። ይህም የሆነው በሁለት ምክንያቶች ሲሆን አንደኛው፣ ከመንግሥት ፈቃድ ባለማግኘቱና ሁለተኛው ምክንያት ተደርጐ የሚወሰደው ጣቢያው ቢቋቋም የሚኖረው የአትራፊነቱ አጠራጣሪነት ነው ማለት ይቻላል።


አምስተኛው ሙከራ የብሥራተ-ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ ከተቋቋመ በኋላ የቴሌቪዥንም ጣቢያ በተጓዳኝ ለማቋቋም ያሳየው ፍላጐት ነው። ጣቢያው ለሚኒስትሮች ም/ቤት የማቋቋሚያ ፍላጐቱን ያቀረበ ቢሆንም ም/ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ አድርጐታል። የዚህ የኃይማኖታዊ ድርጅት ጥያቄ እንደ ሌሎች የቀድሞ ጠያቂዎች ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። ይህ ሁኔታ የሚያመለክተው መንግሥት ፕሮግራሞቹን ለመቆጣጠር አያስችለኝ ይሆናል ከሚል ፍራቻ እንደሆነ ይገመታል።


በመጨረሻም መንግሥት አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ በአዲስ አበባ ለማቋቋም በማሰብ ለሁለት ተከታታይ ጊዜያት ከተለያዩ ዓለምአቀፍ የቴሌቪዥን ኩባንያዎች ጋር ተነጋግሯል። ከነዚህም ውስጥ ተጠቃሾቹ ቶምሶን ቴሌቪዥን ኢንተርናሽናል ሊሚትድና ፊሊፕስ ኢትዮጵያ ናቸው። (ለይኩን፣ 1994 ዓ.ም)። የቴሌቪዥን ጣቢያውን ሁለቱም ድርጅቶች በአንድነት ለማቋቋም ፈቃደኛ መሆናቸውን ለመንግስት ገልፀዋል።ቶምሰን ኩባንያ ደግሞ በቀን የአንድ ሰዓት ተኩል ፕሮግራም በሳምንት ስድስት ቀን ለማሳየት ለሠራተኞች ደሞዝ፣ ለሥራ ማስኬጃ፣ ለፊልም ኪራይና ለፕሮግራሞች ወጪ በዓመት ብር 247,ዐዐዐ በጀት እንደሚያስፈልግ ነበር አጥንቶ ያቀረበው። ምንም እንኳ የጣቢያው ሥራ ተጠናቆ ጥቅም 23 ቀን፣ 1956 ዓ.ም ሥራውን ለመጀመር ፍላጐት የነበረ ቢሆንም የጽህፈት ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት ዮሐንስ ኪዳነማርያም ነሐሴ 7ቀን 1956 ዓ.ም በጻፉት ማስታወሻ በንጉሠ ነገሥቱ መፈቀዱን በመግለጽ የጠቅላይ ሚኒስቴር ም/ሚኒስትር ለነበሩት ሥዩም ሐረጐት መፈቀዱን አስታወቁ። በዚህም መሠረት ከቶምሰን ቴሌቪዥን (ኢንተርናሽናል) ሊሚትድ ጋር በመንግሥት በኩል ስምምነት ተደርጐ ጣቢያውን የማቋቋም ሥራው ተጣደፈ። የቴሌቪዥን ጣቢያውም አዲስ በተገነባው የማዘጋጃ ቤት ህንፃ አራተኛ ፎቅ ውስጥ 21 የተለያዩ ክፍሎች ተደራጅተው ጥቅምት 23 ቀን በ1957 ዓ.ም (1964) ለመጀመሪያ ጊዜ ስርጭቱን ጀመረ። በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹ቴሌቪዥን መጣ!›› (TV is here to stay!) ተባለ።n

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
781 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us