“Under the Shade of a Gaashe” የክቡር ፕ/ት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ አጭር ቅኝት

Wednesday, 10 February 2016 13:44

 

 

በተረፈ ወርቁ

እንደ መንደርደሪያ

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበራቸው፣ በከፍተኛ የመንግሥት ሓላፊነትና በሥልጣን ቦታ ላይ የነበሩ ሰዎች እያወጧቸው ያሉት መጽሐፎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸው ነገር መልካም ዜና ነው። በተጨማሪም የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ አገራት የታሪክ ምሁራንና ተመራማሪዎች፣ ደራሲያን በአገራችን ታሪክ ጉልህ ድርሻና ስፍራ ያላቸውን የአገር ባለውለታ የሆኑ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ፣ ታሪካቸውን በግላቸው በማጥናት፣ መዛግብትንና ከታሪክ ድርሳናት በመፈተሽና፤ እንዲሁም የሥራ ባልደረቦቻቸውና ጓደኞቻቸውን ምስክርነት በማካተት እየተዉልን ያለው ሕያው የታሪክ ቅርስ ሊበረታታ የሚገባው እንደሆነ አያጠያይቅም።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ የትናንትናውን ታሪካችንን ሰንዶ በማቆየት ረገድ በቅርቡ የቀድሞ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፕሬዝዳንት የነበሩትን የክቡር ዶ/ር ግርማ ወ/ጊዮርጊስን የሕይወት ታሪክ በተመለከተ ዶ/ር ሲቫር ኩማር የተባለ ህንዳዊው ፕ/ር ‹‹Under the Shade of a Gaashe›› በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ አንድ መጽሐፍ አበርክቶልናል። በዛሬው መጣጥፌም በዚህ መጽሐፍ ላይ አጭር ቅኝት/የወፍ በረር ዳሰሳ ለማድረግ ወደድኹ። 

‘ጋሼ’ እንዴት የመጽሐፉ ርዕስ ሊሆን በቃ?!

በአገራችን ‹ጋሼ› የክብርና ልባዊ ፍቅርን መግለጫ የሆነ መጠሪያ ወይም ስያሜ ነው። ዛሬም ድረስ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያሉ ልጆች ታላላቆቻቸውንና የቀለም አባቶቻቸውን ‹ጋሼ› በሚል ስያሜ ነው የሚጠሩት። ይህ የፕ/ት ግርማ የሕይወት ታሪክ በተመለከተ በህንዳዊው ፕ/ር የተጻፈው መጽሐፍ ርዕስ ‹ጋሼ› የሚል ስያሜ ያገኘበትን አጋጣሚ የመጽሐፉ አሳታሚ የሆኑት የአምቦ ማይክሮ ቢዝነስ ኮሌጅ ባለቤትና ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ አበራ በመጽሐፉ ምረቃ ወቅት እንዲህ ገልጸውት ነበር።

1984 ዓ.ም. ገደማ የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አቶ አበራ ጥላሁን አጎዋ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በተጠራ ስብሰባ ላይ ተሳታፊ ነበሩ። በዚህ በአገር አቀፍ ደረጃ በሰሜን ሆቴል ላይ በተደረገ ስብሰባ ላይም የዛን ጊዜው መ/አ ግርማ በክብር እንግድነት ተጋብዘው ተገኝተው ነበር። ታዲያ በዚህ ስብሰባ ላሻይ እረፍት በመውጣት ላይ ሳሉ መ/አ ግርማን ደረጃው ያደናቅፋቸውና ሊወድቁ ሲንደረደሩ አቶ አበራ ‹ጋሼ!› እኔን ብለው በአየር ላይ እንዳሉ አቅፈውና ደግፈው ከመውደቅ ይታደጓቸዋል። ይሄ ገጠመኝ ነበር ‹ጋሼ› ከዓመታት በኋላ የዚህ የፕ/ት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ርዕስ ይሆን ዘንድ ያበቃው።

እንግዲህ ህንዳዊው ፕ/ር ሲቫ ኩማር ‹‹Under the Shade of a Gaashe›› ብሎ ርዕስ ለሰጠው የፕ/ት ግርማ የሕይወት ታሪክ መነሻው- በእርግጥም ይኼ ለዘመናት በኢትዮጵያዊነት ማንነት ውስጥ በክብር ጸንቶ የቆመው ‹አለኹልህ ወገኔ!› የሚል በዘመናት የተፈተነ ትሕትናን የተላበሰ፣ በፍቅርና በአንድንት አስተሳስሮን የቆየው አኩሪ ባህላችንና የኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴታችን ነው።

“Under the Shade of a Gaashe” አጭር ዳሰሳ

የቀድሞ ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በቅርቡ ለሕዝብ አገልግሎት ይውል ዘንድ በቤታቸው ያስገነቡትን የሰላምና የአረንጓዴ ልማት አዳራሽና የዲጂታል ቤተ መጻሕፍት ምረቃ ዝግጅት ሰበብ ነበር ይህ መጽሐፍ ለማገኘት የቻልኩት። ይህ በፕሬዝዳንት ግርማ ሕይወት ዙርያ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈው መጽሐፍ መግቢያውንና መቅድሙን ሳይጨምር ከመዘርዝሩ/ከኢንዴክሱ ጋር 194 ገጾች ተቀንብቦ የቀረበ የሕይወት ታሪክ /Autobiography ነው።

ህንዳዊው ፕ/ር ኩማር የዛሬውን የ92 ዓመቱ የዕድሜ ባለ ጠጋ ክቡር ፕሬዝዳንት ግርማ ውልደትና ዕድገት በአዲስ አበባ፣ አሁን ቅዱስ ራጉኤል ቤ/ን ያለበት ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ሰፈር እንደነበር ይተርካል። አባታቸው ወ/ጊዮርጊስ የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ሎሌ ስለነበሩ የፕሬዝዳንት ግርማ ውልደታቸውና ዕድገታቸውም ከዚሁ ሰፈር ይጀምራል። ጋሼ ከፊደል ዘር ጋርም የተዋወቁት በአቅራቢያቸው ከሚገኘው ከአማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ ከሚገኙት የኔታ ዘንድ ነበር።

ከሁለት ዓመት የቄስ ትምህርት ቤት ቆይታቸው በኋላ ጋሽ ግርማ ወደ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ነበር ያመሩት። በትምህርት ላይ እያሉ ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በመውረሩ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደቤተሰዎቻቸው ወደ ሰዶ ሊበን ተጓዙ። ፕ/ት ግርማ የአምስቱን ዓመት የኢትዮጵያውያን አርበኞች ተጋድሎና ጀግንነት በማስታወስ ፋሽስት ኢጣሊያን እንዴት በመጣበት እግሩ ውርደትና እፍረት ተከናንቦ እንደተመለሰ ይተርካሉ። ጋሼ ግርማ በዚህ ትረካቸው የቅርብ ዘመዳቸው የሆኑትን ታዋቂዋን የሴት አርበኛ ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌን ጀግንነትና ወኔ በክብር ያነሣሉ።

ታናሹ ወታደርና የልጅነት በአየር ላይ የመብረር ሕልም

ጣሊያን ተሸንፎ ከኢትዮጵያ ሲወጣ የ16 ዓመቱ ወጣት ግርማ በእንግሊዞች ስር ሆኖ በወታደርነት ሙያ አገሩን ለማገልገል ተቀጠረ። ሚያዚያ 10 ቀን 1933 ዓ.ም. የሲግናል ክፍል አባል ሆነው የተቀጠሩት ጋሽ ግርማ፣ በሲግናል ክፍል የሚሰጠውን ትምህርት ካጠናቀቁ በኋላ በአስተማሪነት ወደ ታንከኛ ከፍል ተዘዋወሩ። ከዛም ደግሞ ወደ አንደኛ ክፍለ ጦር ተዘዋውረው የ፶ አለቅነት ማዕረግ አገኙ። በ1936 ዓ.ም. ከሆለታ ገነት የጦር ትምህርት ቤት በምክትል ፻/አለቃነት ተመርቀው ወጡ።

መ/አ ግርማ ከገነት ጦር ትምህርት ቤት ተመርቀው እንደወጡም ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ተልከው አላማጣና ኮረም ላለው ጦር የሲግናል ትራንስፖርት ክፍል ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል። ከጥቂት ዓመታት በኋላም ግዳጃቸውንም በትጋት በመወጣት ከምስጋና ጋር ወደ አዲስ አበባ ተሸኙ። መ/አ ግርማ ወደ አዲስ አበባ እንደመጡም በአራተኛ ክፍል ጦር ግቢ ውስጥ ከእነ ጄ/ል ድረሴ ዱባለና ካፒቴን ይልማ ዓለሙ ጋር በመሆን ሥልጠና መስጠት ጀመሩ። በዚህ ክፍል ውስጥ እያሉ ነበር ለፕ/ት ግርማ የልጅነት ጊዜ ምኞታቸው የሆነውን በአየር ላይ የመብረር ሕልማቸው ዕውን የሆነበትን ዕድል/አጋጣሚ ያገኙት።

‹ጋሼ› መጽሐፍ ደራሲ ፕ/ር ኩማር የኢትዮጵያ አየር ኃይል ፅንሰትና ውልደት ታሪኩ የሚጀምረው ከስዊድናዊው አብራሪ በኮ/ል ፎርዝን ነው በማለት እንዲህ ይተርክልናል። ይህ ሰው በአምስቱ ዓመት የኢጣሊያ ወረራ ጊዜ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር አብራሪ ሆኖ ለኢትዮጵያ ያገለገለ፣ የአገራችን ባለውለታ የሆነ ታላቅ ሰው ነው። በአንድ ሥራ አጋጣሚ ይህ ሰው የሲግናል ባለሙያው ወደሆኑት ወደ መ/አ ግርማ ወደነበሩበት ወደ አንደኛ ክፍል ጦር ግቢ ቢሮአቸው ድረስ ይመጣል።

ኮ/ል ፎርዝን ወደ መ/አ ግርማ የመጣበት ምክንያቱ ደግሞ በኢጣሊያ ወረራ ጊዜ በፋሽስት ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ለተገደሉት የስዊድን ቀይ መስቀል ሐኪሞች ሀውልት ለማቆም አብሮት የተጓዘው ጓደኛውን ካፒቴን ማንጉስን በመጥፋቱ ነበር። ከሚያበራት ሴስና አውሮፕላን ጋር የጠፋውን ጓደኛውን ለማፈላለግ የሚቻልበት የሲግናል ዘዴ ይኖር እንደሆነ ወደ መ/አ ግርማ ቢሮ የዘለቀው ይህ ሰው በመ/አ ግርማ መልካም መስተንግዶና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታቸው እጅጉን ተገርሞ፣ ‹‹እኛ እኮ እንዳንተ ዓይነት ሰው ነው የሚያስፈልገን ለምንድን ነው ወደ አየር ኃይል የማትገባው?!›› ሲል አነጋገራቸው። ይህ የኮ/ል ፎርዝን ግብዣ በመ/አ ግርማ ልብ ውስጥ ለዓመታት ተደብቆ የነበረው በአየር ላይ የመንሳፈፍ፣ የመብረር የልጅነት ዘመን ምኞታቸውን በብርቱ ቀሰቀሰባቸው።

እናም መ/አ ግርማ ነገ ዛሬ ሳይሉም አየር ኃይልን ለመቀላቀል ወሰኑ። ወደ ጃንሆይ ዘንድ በመሄድም ጥያቄያቸውን አቅርበው አየር ኃይልን ተቀላቀሉ። ዝውውራቸውን በተመለከተም ወደ መከላከያ፣ ለምክትል ሚ/ሩ ለጄ/ል ዐቢይ አበበ ደብዳቤ ተጻፈ። የመከላከያ ሚ/ሩ ራስ አበበም፣ ‹‹እንዴት ትከደናለህ?!›› የሚል ጥያቄ የቀረበባቸው መ/አ ግርማ፣ ‹‹ክቡር ሚ/ር አልከዳኋችሁም ይልቁንስ ከልጅነቴ ዘመን ጀምሮ ምኞቴ ወደነበረውና እናት አገሬን በሚገባ ወደማገልግልበት የዘወትር ምኞቴና ሕልሜ እየሄድኩ ነውና እገዛችሁና ማበረታታችሁ አይለየኝ።›› በማለት ወደ አየር ኃይል አቀኑ።

ከአየር ኃይል ጉዞ ወደ ሲቪል አቬዬሽን

ፕሬዝዳንት ግርማ ከአየር ኃይል ወደ ሲቪል አቬዬሽን የተቀየሩበትን አጋጣሚ ፕ/ር ኩማር እንዲህ ይተርከዋል። በሲቪል አቪዬሽን ውስጥ የሬዲዮኑም፣ የቴሌኮሚኒኬሽኑም ሓላፊ ሆኖ የሚሠራየነበረ አንድ ጀርመናዊ ሚ/ር ሆፍማን የሚባል ጀርመናዊ ነበር። በዚያን ጊዜ ሲቪል አቪዬሽንም ያደገ መስሪያ ቤት አልነበረም። የአየር መንገዱም ገና አዲስ መቋቋሙ ስለነበር ሌሎች አውሮፕላኖች ስላልነበሩና የነበረው ትልቅ ዲፓርትመንት የናቪጌሽን ክፍል፣ የመሬት መምሪያውና የመገናኛ ክፍሉ ብቻ ነበር። ይህን ሁሉ ጠቅልሎ የሚሠራው ሚ/ር ሆፍማን ለካስ የናዚ ወንጀለኛ ኖሮ ሌሎች የናዚ ወንጀለኞች መያዛቸውን ሲሰማ አንድ ቀን ጠዋት ተነሥቶ በጅቡቲ በኩል አድርጎ ጠፋ።

ያ እርሱ የሚመራው ቦታ ባዶ ሲሆን ለቦታው የሚመጥን ከውጭ ሀገር ተቀጥሮ እስኪመጣ ድረስ ከአየር ኃይል ሰው መገኘት አለበት ተባለ። አየር ኃይልን ሲጠይቁ ያን ችሎታ ይዘው የተገኙት መ/አ ግርማ ነበሩ። ያን ቦታ ለመምራት ሲባልም ወደሲቪል አቬዬሽን ተዛወሩ። በወቅቱ ሲቪል አቬዬሽን የግራውንድ ሰርቪስ ነበር የሚባለው ይለናል ፕ/ር ሲቫ ኩማር። የአየር መቆጣጠሪያ፣ የጠፋ አውሮፕላን መፈለጊያ መምሪያ ክፍል ሓላፊ ሆነው ነው የተዘዋወሩት መ/አ ግርማ ይህን መስሪያ ቤት እንደተቀላቀሉም የዓለም ሲቪል አቬዬሽን ትምህርት ቤት አዲስ አበባ ተከፈተ።

ትምህርት ቤቱ በናቪጌዬሸን፣ በሚትሮሎጂ፣ በኮሚኒኬሽን፣ ጄኔራል ኤር ክራፍት መካኒክና ኤሮናቲካል ኢንጂነሪንግ ሁሉ ጠቅልሎ የሚያስተምር፣ በእጅጉ ደረጃውን የጠበቀ ነው። ክቡርነታቸው ፕ/ት ግርማ በዚሁ ት/ቤት አማካኝነት ነበር በሙያቸው ወደተሻለ ደረጃ ለመድረስ መንግሥት ባመቻላቸው የከፍተኛ ትምህርት ወደ ካናዳ፣ ስዊድን፣ ሆላንድና አውስትራሊያ ተልከው በአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ዙርያ ከፍተኛ የሆነ ልምድ የቀሰሙት። ክቡርነታቸው ወደ አገራቸው ከተመለሡም በኋላ በቀሰሙት እውቀት ሲቪል አቬዬሽንን በታላቅ ትጋትና ፍቅር አገልግለዋል። በአቪዬሽን ሥራ ውስጥም ሆነ በበረራ ሙያ በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እንዲሳተፉም ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። 

የኢትዮጵያ ንብረት የሆኑ አውሮፕላኖች ላይ ያለውን ምልክት ያስለወጡትና ET ተብሎ እንዲጠራ ያደረጉት የዛሬው የ92 ዕድሜ ባለጠጋው፣ የአቪዬሽን ባለ ሙያው ክቡር ፕሬዝዳንት መ/አ ግርማ ናቸው። እንዲሁም የሲቪል አቬዬሽን አማካሪ ቦርድ የሚባል እንዲቋቋም ያደረጉና የአቪዬሽን መስሪያ ቤት በሂደት ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እንዲመራ በማድረግ ረገድ የነበራቸው ሚናም ወሳኝና ታላቅ ነበር።   

የፍቅር ሕይወትና ሦስት ጉልቻ

ፕ/ት ግርማ በጋብቻ ከተሳሰሩ ዘንድሮ 68ኛ ዓመታቸውን አክብረዋል። ጋሼ ግርማ ወደ ትዳር የገቡት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባል በነበሩበት ጊዜ እንደነበር ፕ/ር ኩማር ይተርካል። የጋሼ ግርማ የትዳር ሕይወት በወቅቱ መስሪያ ቤታቸው አየር ኃይል የሚፈቅደው ጉዳይ አልነበረም። እናም የነበራቸው አማራጭ ባለቤታቸውን ይዘው ወደ አስመራ መኮብለል ነበር። ይሁን እንጂ በአለቆቻቸው ተጠርተው በከፍተኛ ወታደራዊ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደረገ። መ/አ ግርማ ግን ለጃንሆይ ይግባኝ በማለት ጉዳያቸው ዳግመኛ እንዲታይ አቤቱታቸውን አቀረቡ።

ንጉሡም አቤቱታቸውን ከመረመሩ በኋላ እንዲህ አሉ፣ ‹‹እንዴ ምን ማለታችሁ ነው ሰዎች?! እንደውም ይህ ሰው ማግባቱ ጥሩ ነው እንጂ በይበልጥ ሓላፊነት እንዲሰማውና ሥራውንም በትጋት እንዲያከናውን ጉልበት ይሰጣዋል።›› ሲሉ የመ/አ ግርማ ጋብቻ ውሳኔያቸው ትክክለኛ መሆኑን አሳወቁ። በዚህም ጋሼ ግርማ ከእስር ነጻ ሆኑ።

ፕ/ር ኩማር በዚህ መጽሐፉ እምብዛም ያልተለመደ አንድ የጋሼ ግርማን ከትዳራቸው ውጪ የተደረገ የፍቅር ገጠመኝ ይተርክልናል። መ/አ ግርማ ለአቪዬሽን ስልጠና በካናዳ ሞንትሪያል እያሉ ከአንዲት ቺኮዝላቪኪያዊት ስደተኛ ወጣት ሴት ጋር ድብቅ የፍቅር ግንኙነት ጀምረው ነበር። ከአገራቸውና ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ሳሌም ርቀው በውቧ የካናዳ ከተማ በሞንትሪያል የጀመሩት የፍቅር ግንኙነት የኋላ ኋላ ውስጣቸውን በኀዘንና በጸጸት እንደበላው ያስታውሳሉ ጋሼ ግርማ።

ሥልጠናቸውን ጨርሰው ወደ አገራቸው ለመጓዝ በዝግጅት ላይ በነበሩበት ወቅት ባለ ትዳር የመሆናቸውን መርዶ ከመ/አ ግርማ የሰማችው ወጣት ልቧ ተሰብሮ በእንባዋ የራሰና የወየበ የናፍቆት ትዝታ ደብዳቤዋን በአይሮፕላን ጉዞ ሣሉ ያነበቡት ጋሼ ግርማ በጊዜው የተሰማቸውን የጸጸት ስሜት እንዲህ ገልጸውታል።

I really felt guilty of cheating an innocent girl who loved me from the bottom of my heart. Even now I feel the pain, the guilt of my action. በትዳር ሕይወት ውስጥ ፍቅር፣ ታማኝነትና ይቅር ባይነት አስፈላጊ መሆናቸውን ያሰመሩበት ጋሼ ግርማ በዚህ ከትዳራቸው ውጪ የፈጸሙት ይህ ድብቅ የፍቅር ግንኙነት ያሳደረባቸውን የሕሊና ወቀሳ በማስታወስ ግን ደግሞ ስህተትን አምኖና አርሞ በይቅርታ ልብ የትዳር ግንኙነትን ማደስ እንደሚቻል ለወጣቱ ትውልድ እንዲህ ሲሉ ምክርን ይለግሣሉ፣ ‹‹Confession is always good in one’s life.››

የአረንጓዴ ልማት አርበኛና የሰላም አምባሳደር

ፕ/ት ግርማ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ/ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ ሙግት የጀመሩት ገና በ36 ዓመታቸው የኢትዮጵያ ፓርላማ ሆነው በተመረጡበት ወቅት እንደነበር ፕ/ር ኩማር ይተረካል። ጋሼ ግርማ በንጉሡ ዘመን በፓርላማ ውስጥ ከቡዙ ሙግት በኋላ የደን ሕግ እንዲወጣ አድርገዋል። ይህ የክቡርነታቸው ለአረንጓዴ ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ ያላቸው ቁርጠኝነት ደግሞ እስካሁንም ድረስ የዘለቀ ነው። በዚህ በአረንጓዴ ልማትና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ባላቸው ቁርጠኝነትም ፕ/ት ግርማ ከአገር ውስጥ በርካታ ሽልማቶችንና ዕውቅናዎችን ተችረዋል። ክቡርነታቸው በቅርቡ በመኖሪያ ግቢያቸው ያስመረቁት የሰላምና አረንጓዴ ልማት አዳራሽም የዚህ ትጋታቸው አንድ ማሳያ ነው።

ፕ/ት ግርማ በሰላም ዙርያም ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ በሰላም ዙርያ ከሚሰሩ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ከተለያዩ የሰላም አምባሰደሮች ጋር በመሆን ዓለማችን ሰላም የሰፈነባት እንዲሆን የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ነው። ጋሼ ግርማ በመኖሪያ ቤታቸው ያስገነቡትን የሰላም አዳራሽም በሰላም ጉዳይ ላይ ለሚሠራው ‹ለዓለም የዕርቅና ሰላም ግብረሰናይ ድርጅት› በስጦታ አበርክተዋል። ክቡር ጋሼ ግርማ ገና ከ16 ዓመታቸው ጀምሮ በውትድርና፣ ከዛም በአየር ኃይልና በሲቪል አቬዬሽን፣ በፓርላማ፣ በግብርና፣ በኋላም ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ በፕሬዝዳትነት አገራቸውን ስላለገለገሉበት ቆይታቸው- ‹ጋሼ› በሚለው የሕይወት ታሪካቸው መጽሐፍ እንዲህ ይላሉ፣ 

‹‹አገርን መውደድ ማለት አገርህ የምትጠቀምበትንና ሕዝብ፣ ወገንህ የሚከበርበትን፣ የሚኮራበትን ሥራ መሥራት ነው።››እኔ በዘመኔ ሁሉ ይህን ለማድረግ አብዝቼ ስተጋ፣ ስለፋና ስደክም ቆይቻለሁ። አሁንም በሕይወት እስካለሁም ድረስ አገሬንና ሕዝቤን የሚጠቅም ሥራ ከመሥራት ፈጽሞ ወደኋላ አልልም። የአሜሪካን ፕሬዝዳንት የነበረው ጆኔፍ ኬኔዲን እንዲህ ይላል፣ ‹‹አገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ ሣይሆን እኔ ለአገሬ ምን አደረኩላት ስትል ራስህን ጠይቅ።››ይህ የኬኔዲ ንግግር አንድ የሚነግረን ታላቅ ቁም ነገር አለ። ይኸውም፣ አገርህ መነሻህና መድረሻህ፣ አገርህ ሀብትህ፣ ውበትህ፣ አገርህ ጌጥህ፣ ዝናህና መከበሪያህ፣ አገርህ መኩሪያህ፣ ዘውድህና መቃብርህ፣ አገርህ መኳያህ፣ መዳርያህ፣ ማዕረግህ፣ ወልደህ የምትሰምባት ዘርትህ የምትቅምባት የዘላለም ርስትህ ናት።

ከድርቡሽ ወራሪ ጦር ጋር በመተማ ግንባር ክቡር ሕይወታቸውን ለአገራቸውና ለሃይማኖታቸው የሠዉት ዐፄ ዮሐንስ 4ለእናት አገራቸው ኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅርና ክብር እንዲህ ነበር የገለጹት፣

ኢትዮጵያ አገርህ አንደኛ እናትህ፣ ሁለተኛ ክብርህ ናት፣ ሦስተኛ ሚስትህ ናት፣ አራተኛ ልጅህ ናት፣ አምስተኛ መቃብርህ ናት። እንግዲህ የእናትን ፍቅር፣ የዘውድን ክብር፣ የሚስትን ደግነት፣ የልጅን ደስታ፣ የመቃብርን ከባቲነትን እንደዚህ መሆኑን አውቀህ አገርህን ኢትዮጵያን ውደዳት፣ ከጠላትና ከወራሪም ጠብቃት።

የአገራችን ሰውም፣

እናት አባት ቢሞት በአገር ይለቀሳል፣

ወንድም እኅት ቢሞት በአገር ይለቀሳል፣

አገር የሞተ እንደው ወዴየት ይደረሳል።በማለት ለውድ እናት አገሩ ይህን ዘመን የማይሽረው ግሩም ቅኔ የተቀኘው የአገራችን ሰው ይህ የአገር ታላቅነትና ክቡርነት ምስጢር ገብቶት ነው።

በመጨረሻም በቅርቡ በሞት ከተለየንና የኢትዮጵያን ታሪክ በተመለከተ በርካታ መጻሕፍትን ካበረከተልን ከህንዳዊው የኢትዮጵያ ወዳጅ ከፍራንሲስ ጆሴፍ በመቀጠል ይህን የክቡር ፕ/ት ግርማን የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ያበረከተልን ፕ/ር ሲቫ ኩማር ምስጋና ሊቸረው ይገባል። በተረፈ ጥቂት አስተያየቶቼን ለመስጠት ያህል መጽሐፉ አንዳንድ የአማርኛ የሰዎችንና የቦታ ስሞችን በእንግሊዝኛ ያሰቀመጠበት /Transliterations ስህተት አለው። ይህ ደግሞ ምናልባትም መጽሐፉን የአገራችን የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ተገቢውን የአርትኦት ሥራ እንዳላደረጉበት አንድ ማሳያ ይመስለኛል።

በሌላ በኩል ደግሞ በአብዛኛው የውጭ አገር ሰዎች የሕዝባችንን የረጅም ዘመናት ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ባህል፣ ወግና የማኅበራዊ ሕይወት መስተጋብር በቅጡ ካለመረዳት የሚመነጨውና በባዕዳን ዘንድ የሚንጸባረቀው ታሪካችንን በትክክልና በሚገባው መንገድ ያለመተረክ ስልት በዚህ በህንዳዊው ፕ/ር ሲቫ ኩማር ‹‹Under the Shade of a Gaashe›› መጽሐፍ ላይም በጥቂቱም ቢሆን ተንጸባርቋል። በተረፈ ይህን መጽሐፍ ያሳተመው የአምቦ ማይክሮ ቢዝነስ ኮሌጅ ለእንግሊዝኛ አንባቢዎችና ለውጭ አገር ሰዎች መጽሐፉን የማንበብ ዕድል እንዲያገኙ እንደ ቡክ ወርልድ ያሉ የመጽሐፍ መደብሮች እንዲደርሳቸው ቢያደርግ መልካም ነው እላለኹ። አበቃሁ!!

ሰላም!n

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1028 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us