“ዲሞክራሲ ለአፍሪካ ቅንጦት ነው”

Wednesday, 24 February 2016 14:34

 

 

ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ

“ዝና ነጃሳ ናት!”

ደራሲ በአሉ ግርማ

በድንበሩ ስዩም

 

ታላቁ ደራሲ ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ ዝና ነጃሳ ናት የሚል አባባል አለው። ዝነኛ ሰው ነፃ አይደለም። ዝነኛ ሰው በሰው አእምሮ ውስጥ ገብቶ የተዋሃደ ነው። ሰዎች ስለ እሱ በቀላሉ ያወራሉ፤ ይወያዩበታል፤ ወደ ዝነኝነት መድረክ የሚያመጣ ደግሞ ተግባር ነው። በአንድ በተወሰነ ጉዳይ ላይ ታዋቂ መሆን ተወዳጅ መሆን ወደ ዝነኝነት ያመጣል። በዚህ ረገድ ፖለቲከኞች' ስፖርተኞች' የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለዝነኝነት ተጋላጮች ናቸው። ዝነኛ በመሆናቸው ተከታይ ያፈራሉ። የእነሱን ቃል እና ድርጊት አምነው የሚፈፅሙ ተከታዮች ይኖሯቸዋል። በዚህ የተነሣ ዝነኞች ጠንቃቃ ይሆናሉ። እንደ ልባቸው አፋቸው ላይ ያለውን ሁሉ አይናገሩም። የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም የሚባለው የሀገራችን አባባል በተለይ ዝነኞች ላይ ሲሆን ገናና ይሆናል። በቅቤ አለመታሸቱ ብቻ አይደለም። ሕመሙን ማዳን ከባድ ነው። ስር ሰዶ ዝነኛውን ሰው ከተራ ሠዎች ጐራ ውስጥ ይከተዋል። ለዚህም ነው በዓሉ ግርማ ዝና ነጃሳ ናት ያለው።

 

ዝና ሲመጣብን የምንጠነቀቃቸው ጉዳዮች ብዙ ናቸው። ለምሣሌ ከአፍ የወጣ አፋፍ ነውና፤ ከአፍ የወጣ መልሶ አይላመጥምና በተለይ ንግግር ላይ ከባድ ጥንቃቄ ይጠይቃሉ። ዝነኛ ሰው በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ወዳጆች እና ተከታዮች አሉት። ንግግሩ ውስጥ ሁሉ እነዚህ ወዳጆቹ እና ተከታዮቹ ከግምት ውስጥ መግባት አለባቸው። ዝነኛ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የነዚህ ወዳጆቹ የፍቅር አንቀልባ ላይ ታዝሎ የሚኖር ሰው ነው። ያዘሉት ደግሞ ለፍቅራቸው መግለጫ ነው። ለማዘል አልመቻቸው ካለ፤ ታዝሎ የሚያበሣጭ ከሆነ፤ ለአዛዩም ሆነ ለአቃፊው የማይመች ከሆነ፤ አውርደው ይተውታል። በቃ ከኛ እኩል ተጓዝ፤ እንደኛው ሂድ፤ እንደኛው ሁን ብለው ይለቁታል። ዝና ነጃሳ ናት።

 

ከሰሞኑ የማሕበራዊ ድረ-ገፅ ውስጥ ሰፊ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆነው ከቆዩት መካከል ዋነኛው ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ ነው። ኃይሌ ከBBC ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ስለ አፍሪካ ዲሞክራሲ የሰጠው አስተያየት ክፉኛ እየተነቀፈ ነው። ኃይሌ ለቢቢሲ በሰጠው መግለጫ ዲሞክራሲ ለአፍሪካ ቅንጦት (Luxury) ነው ብሏል። ከዲሞክራሲ ይልቅ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን መጣር እንዳለብን ተናግሯል። ሁል ጊዜ ዲሞክራሲ ዲሞክራሲ እየተባለ እንደሚወራ ነገር ግን ዋናው ጉዳይ ጥሩ መንግሥት መመስረት እንዳለበት እና እሱ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ኃይሌ ገልጽዋል። በሚቀጥለው የ2012 ዓ.ም ምርጫም ወቅት ወደ ፖለቲካው መድረክ ብቅ ብሎ በሀገሩ የመሪነት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሣተፍ እቅድ እንዳለውም በቃለ-ምልልሱ ወቅት ተገልፆአል። በኢትዮጵያ ውስጥ በሆቴል' በእርሻ' በሪዞርት' በመኪና አስመጪነትና ሻጭነት' በሲኒማ ቤት' በሕንፃ ወዘተ ከፍተኛ የሆነ ኢንቨስትመንት የሚያካሒደው ኃይሌ ገብረስሳሴ ዲሞክራሲ ለአፍሪካ ቅንጦት ነው ማለቱ ከባድ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።

 

ኃይሌ የኘላኔቷ ብርቅዬ አትሌት ነው። የአለም ሰው ነው። ፊልም በሕይወት ዙሪያው የተሰራለት። ታላላቅ ድምፃዊያን ያቀነቀኑለት፤ የተቀኙለት፤ ቀይ ምንጣፍ ተዘርግቶ በክብር የሚሔድበት፤ የአለም የስልጣኔ ምንጮች የት እንደሆኑ በክብር ሔዶ የጐበኘበት፤ የሰውን ልጅ ስልጣኔ የተመለከተበት ነገረ አለም ሁሉ የት ገባ ተብሎም እየተጠየቀ ነው።

 

ኃይሌ ሲናገር የተሻለው ነገር መልካም አስተዳደር መመስረት እንደሆነ አፅንኦት ሰጥቶ ገልጥዋል። ጉዳዩ መልካም አስተዳደር ራሱ ምንድን ነው? የመልካም አስተዳደር መገለጫዎች ምንድን ናቸው? መልካም አስተዳደርን ለመመስረት ለማስፈን ምን ያስፈልገናል? የሚሉት ነገሮች ለውይይት መቅረብ አለባቸው።

 

ዛሬ ዛሬ በባሕል ትምህርቶች ውስጥ አስተዳደር የሚለው ጽንሰ ሐሣብ ሁሉ እየተካተተ ነው። በማሕበረሰቡ እሴት ውስጥ ማስተዳደር እንዴት ይገለፃል? እንዴትስ ተግባራዊ ይደረጋል? ወደ ዘመናዊው የአስተዳደር ስርአትስ እንዴት መለወጥ ይቻላል የሚሉ ውይይቶችና ርዕሰ ጉዳዮች እየተካተቱ ነው። ለዚህ ምሣሌ የሚሆነን የሐገራችን የገዳ ስርአት ነው። የገዳ ስርአት በየ 8 አመቱ የሚደረግ የምርጫ ስርአት ነው። እንዲህ አይነት ነገሮችን ወደ ዘመናዊ አስተዳደር ውስጥ ቢገቡ የተሻለ ሐገርና ማሕበረሰብ ይገነባል በሚል ትምህርታዊ ውይይቶቸ ይደረጋሉ። ውይይቶቹ ያተኮሩበት ሃሣብ ዲሞክራሲ ውስጣቸው ስላለ ነው። የዲሞክራሲ መገለጫ የሆኑ ፅንሰ ሃሣቦች በውስጡ ስለሚገኙ እነርሱን የማወፈርና የማፋፋት ስራ በባህል ውስጥ ሁሉ እየተሰራ ነው። እናም ዲሞክራሲ ቅንጦት አይደለም።

 

መልካም አስተዳደርን (Good Governance)ን ካለ ዲሞክራሲ መመስረት ይቻላል ወይ? ዲሞክራሲ የሌለበት መልካም አስተዳደርስ አለ? የሚሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው። ኃይሌ ከዲሞክራሲ በላይ መልካም አስተዳደርን መርጧል። ዲሞክራሲ የሌለበት መልካም አስተዳደርስ እንዴት ይምጣ እያሉት ፀሐፊያን እየሞገቱት ነው።

 

መልካም አስተዳደር ከሚገነባባቸው መንገዶች አንዱ ነፃ ምርጫ ማካሔድ ነው። በሕዝብ ድምፅ ሣያጭበረብሩ ወደ ስልጣን መምጣት ነው። በሕዝብ ድምፅም መውረድ ነው። መንግስትን' ሥርአትን የሚመሰርተው የሕዝብ ድምፅ ነው። ይሔ አንደኛው የመልካም አስተዳደር መመስረቻ መንገድ ነው።

 

ሁለተኛው ነፃ ኘሬስ ነው። ለመልካም አስተዳደር ግንባታ ከሚጠቀሱ ቁልፍ ጉዳዮች መካከል ኘሬስ አንዱ ነው። ሰዎች ሃሳባቸውን የሚገልፁባቸው የኘሬስ ውጤቶች ካለ ማዋከብ እና ቅጥ ያጣ የገደብ ጫና ካለማድረግ ነፃ የሆኑ ኘሬሶች በአንዲት የመልካም አስተዳደር ስርአት አሰፍናለው በምትል ምድር ላይ መኖር አለባቸው። ቴሌቪዥኖች ሬዲዮኖች ጋዜጦች መጽሔቶች እንደ ልብ መኖርና መስራት አለባቸው። እነሱ በማይኖሩበት ሁኔታ ውስጥ መልካም አስተዳደርን ማሰብ ፈፅሞ አይቻልም። ነፃ ኘሬሶች የዲሞክራሲ መገለጫዎች ናቸው።

 

የነፃ ፍርድ ቤቶች መቋቋም'፣ የመሰብሰብ'፣ ሃሣብን በነፃነት የመግለፅ'፣ የመደራጀት' ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ'፣ የመቃወም'፣ ሃብት የማፍራት'፣ የሰብአዊ መብት ጥበቃዎች ወዘተ ሁሉ የዲሞክራሲ መገለጫዎች ናቸው። ካለ እነሱ መልካም አስተዳደርን መገንባት ፈፅሞ አይቻልም።

 

በዚህ ባለንበት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ ዲሞክራሲ ቅንጦት ነው ብሎ ማሰብ በራሱ ከባድ ነው። የማሰብ ነፃነት'፣ የመፃፍ ነፃነት'፣ የመናገር ነፃነት ወዘተ በሰፈነባቸው ግዛቶች ውስጥ ስልጣኔም ሆነ መዘመን አብሮ ይመጣል። መልካም አስተዳደሩም እዚያ ውስጥ ይወለዳል። ዲሞክራሲ የመልካም አስተዳደሩም እዚያ ውስጥ ይወለዳሉ። ዲሞክራሲ የመልካም አስተዳደር ዘር ነው። መልካም አስተዳደር እንዲረገዝ እና እንዲወለድ  የዲሞክራሲ ዘር ያስፈልጋል

 

የአንድ ስርአተ ማሕበርም አስተማማኝነት የሚገለፀው ለዲሞክራሲያዊ መንግስት ምሰረታ የሚያደርገውን ልፋትና ትግል በማየት ነው። ዲሞክራሲ ሂደት ቢሆንም ሂደቱ ላይ የሚደረግ ማናቸውም ገደብ ወንጀል ይሆናል። አፈናም ሊሆን ይችላል። ሂደቱን የሚያሰናክሉ ድርጊቶችን መከላከል መቻል በራሱ ለዲሞክራሲያዊ መንግስት ምስረታ የሚደረገውን ርብርብ ያሣያል።

 

ኃይሌ ገብረስላሴ እጅግ ብዙ የሚባሉ የኢንቨስትመንት ስራዎች በዚህች ሀገር ላይ እያካሄደ ነው። ይህ ሀብትና ንብረቱ ተጠብቆ የሚቆይለት ዲሞክራሲያዊ መንግስት (ስርአት) ሲኖር ነው። ስርአቱ ደግሞ አስተማማኝ መሆን አለበት። አንድ ስርአት ተቀይሮ ሌላ ስርአት የሚመጣበት መንገድ በዲሞክራሲያዊ መሠረቶች ላይ እንዲሆን ያስፈልጋል። የአስተማማኝ ስርአት ግንባታ በሕዝብ ድምፅ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። ሕዝብን የሚፈራ ስርአት መገንባት አለበት። ሕዝብ በምርጫ የሚያነግሰውና የሚያወርደው ስርአት መኖር አለበት። ያንን ስርአት ለመመስረት የሚደረገው ርብርብ ሁሉ የዲሞክራሲያዊ መንግስት ካስማ እና ማገር ናቸው።

 

ዛሬ ከአለም ስልጣኔ እና መዘመን ጋር የተወለዱ ልጆቻችን  ዲሞክራሲ ለአፍሪካ ቅንጦት ነው እያልን ስንነግራቸው ምን ይሰማቸዋል? እኛስ ልጆቻችንን ዲሞክራሲ ቅንጦት ነው እያልን ማሣደግስ ይገባል? ልጆቻችን ዲሞክራሲን እንደ ባሕል አድርገው እነዲለማመዱት ግፊት ማድረግ ማስተማር ሌት ተቀንም መወትወት ይገባልና። ዲሞክራሲ ባይኖር እንዲኖር መናገር አለብን። ዲሞክራሲ ቢረገጥም ቀና እንዲል መናገር አለብን። ደራሲ በዓሉ ግርማ ተስፋ በሌለበት ሁኔታ ውሰጥም ተስፋ አትቁረጥ ይላል። ተስፋ ማድረግ የሕይወት ስንቅ ነው።  ዲሞክራሲም ልክ እንደ ተስፋ ዘወትር ከአእምሯችን መውጣት የሌለበት ጉዳይ ነው።

 

ኃይሌ ገብረስላሴ ዲሞክራሲ ለአፍሪካ ቅንጦት ነው አለ። ከባድ ንግግር ነው። 54 የአፍሪካ ሀገሮች በሙሉ የወከለ ነው። በተአምረኛ እግሮቹ በአለም የአትሌቲክስ መድረክ ላይ የአፍሪካን ስም ደጋግሞ ያስጠራ የነበረው አፍሪካዊው ጀግና ኃይሌ ገብረስላሴ ይህን ተናገረ ብሎ ማመንና መቀበል ይከብዳል ። ግን አለ። ተናገረ። ለዚያው ለአለም አቀፉ ተቋም ለBBC። ጋዜጠኛው እስኪገርመው ድረስ ሰማው።

 

ታዋቂው ፖለቲከኛ እና የሕግ ምሁር ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም ሰሞኑን የኛ ኘሬስ ተብሎ ለሚጠራው ጋዜጣ በሰጡት ቃለ-ምልልስ ኃይሌ የአፍሪካን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ አለበት ብለዋል። አፍሪካዊያኖች በርካታ የመከራ ዘመናትን አሣልፈዋል። መከራው የረዘመው ዲሞክራሲ ስለጠፋ ነው። የመከራ ሸክማቸውን የሚያራግፉት ዲሞክራሲያዊ መንግስት ሲመሰርቱ ነው። በመፈንቅለ መንግስት እና በጠመንጃ አፈ-ሙዝ ትንቅንቅ የሚመሰረት መንግስት እንዳይኖር ዲሞክራሲ ለመገንባት ሌት ተቀን እየጣሩ ነው። እንደ ኃይሌ ገብረሥላሴ ያሉ የምድሪቱ ብርቅ ሰዎች ድንገት ተነስተው ዲሞክራሲ ለአፍሪካ ቅንጦት ነው ብለው ሲናገሩ ግራ ያጋባል።

 

ጋና' ደቡብ አፍሪካ' ናይጄሪያ እና ኬኒያን የመሣሰሉ የአፍሪካ ሀገራት በተለያዩ አጋጣሚዎች ስማቸው የሚሞካሸው ለዲሞክራሲ ማበብ እየከፈሉ ያሉትን መስዋዕትነት በማሰብ ነው። በነዚህ ሀገራት በሕዝብ ድምፅ መንግሥታት እየተቀያየሩ ነው። ይህ ማለት ዲሞክራሲ ሰፍኖባቸዋል ማለት አይደለም። ግን የዲሞክራሲን አንዱን መንገድ ተያይዘውታል። ዲሞክራሲ ቅንጦት አይደለም። የሐገር እና የሕዝብ የሕልውና መሰረት ነው።

 

ኃይሌ ሲናገር ዋናው ጉዳይ መልካም አስተዳደር መልካም መንግስት የመመስረት ጉዳይ ላይ ነው። በርግጥ አንድ መንግስት ልማታዊ መንግስት (Developmental State) ሊሆን ይችላል። ይህ የዲሞክራሲ መገለጫ ነው ማለት ፈፅሞ አይቻልም። በልማት ስም ብዙ ጥፋቶች ሊሰሩ ይችላሉ። በልማት ስም ሙስና ሊስፋፋ ይችላል። ግን ዲሞክራሲ ሲኖር ተጠያቂነት አለ። መቆጣጠሪያ መንገዶች አሉ። ዲሞክራሲ የጥፋት ማስታገሻና ማስወገጃ ሲሆን ለሕግ የበላይነት እና ተጠያቂነት መስፈን ደግሞ ዋነኛው መሣሪያ ነው።

 

ስለ ልማት ሲነሣ አንድ ያነበብኩት ታሪክ ትዝ አለኝ። ጊዜው በፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ነው። በወረራው ምክንያት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የመንግሥታቸው ባለስልጣኖች ወደ እየሩሳሌም ይሰደደሉ። በስደትም ይቆያሉ። በዚህ ወቅት ጣሊያን አዲስ አበባ ላይ ስለሚያደርገው ሁኔታ መረጃ ይሰበስባሉ። ጣሊያን መንገድ እየሰራ መሆኑን' መኪና እተነዳ መሆኑን' የንግድ ቤቶች መከፈታቸውን' ት/ቤቶች መከፈታቸውን' ሀኪም ቤቶች መከፈታቸው ወዘተ ይሰማሉ። ባጠቃላይ ልማት አየተካሔደ መሆኑን ይሰማሉ። ከጃንሆይ ጋር ከተሰደዱት መካከል ደጃዝማች ወልደ አማኑኤል እና አንዳንድ ሹማምነት ልባቸው ወደ አዲስ አበባ ይከዳል። ጣሊያን ልማት እያካሔደ ነው፤ እኛም የምንፈልገው ልማት ነው፤ ሀገሪቷ እየለማች ከሆነች ለምን ታርቀን ወደ ሐገራችን አንገባም? ብለው አሰቡ። በምስጢር ከጣሊያኖች ጋር ተላላኩ። ከዚያም ወደ ጅቡቲ መጡ። ቀጥለውም ከልማታዊው ጣሊያን ጋር አብሮ ለመቀጠል አዲስ አበባ ገቡ። ነገር ግን ብዙ ሣይቆዩ ጣሊያን ገደላቸው። ማን ይጠይቀዋል? የሰው ሀገር የወረረ ቀኝ ገዢ፤ በዚያ ላይ ተጠያቂነት ያለው ስርአት ያልገነባ። ስለዚህ ልማት የመልካም አስተዳደር መገለጫም እነዳልሆነ ማሣየት ይቻላል። በነገራችን ላይ ጣሊያን በአምስት አመት ውስጥ ከዚህ አስመራ ድረስ መንገድ ከማሰራቱ በተጨማሪ ኢትዮጵያን በመንገድ ኔት ወርክ አስተሣስሯል። ልማታዊ ነው። ግን የመልካም አስተዳደር መገለጫ አይደለም።

 

ኃይሌ ገብረስላሴ ከአራት አመት በኋላ በሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ወደ ፖለቲካው አለም እንደሚገባም ለBBC ተናግሯል። በሐገሪቱ የፖለቲካ አመራር ውስጥ ከፊት የመሆን እቅድ እንዳለው አውስቷል። እንደ ኃይሌ ገብረስላሴ ያሉ ግዙፍ ስብዕናዎች ወደዚህ የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ሲመጡ የተሻለ ነገር ይዘው ብቅ ይላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ግን ገና ወጡ ሣይወጠወጥ ሆነና የኃይሌ ንግግር መነጋገሪያ ሆኖ አረፈው። አንድ ወደ ፖለቲካው አለም እመጣለሁ እያለ የሚንደረደር ታላቅ ሰው' ዲሞክራሲ ቅንጦት ነው ብሎ ከተናገረ ራሱን በራሱ ከፖለቲካው መድረክ እንደማግለል ይቆጠርበታል።

 

እቅዱ ተሣክቶለት ኃይሌ የፖለቲካው ቁንጮ ቢሆን ዲሞክራሲ ቅንጦት ነው ይለን ይሆን? ግን አይሣካለትም። ምክንያቱም ዋናውን የመልካም አስተዳደር መገንቢያ መሣሪያውን ሣይዝ ወደ ፖለቲካው ቁንጮነት አይመጣም። ኃይሌ ወደ ፖለቲካው አመራር እንዲመጣ መጀመሪያ የሚረማመድበት የዲሞክራሲ መንግድ ያስፈልገዋል። እንደ ልቡ ሚዲያውን ሊጠቀምበት ይገባል። እንደ ልቡ ደጋፊዎቹን ሰብስቦ መናገር መቃወም መቀስቀስ መቻል አለበት። ኃይሌ በሚመሰርተው በራሱ ፓርቲ ውስጥም ቢሆን ዲሞክራሲ ከሌለ እንዴት አድርጐ ነው እሱ ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ከነ ታላቅ ግርማ ሞገሱ ብቅ የሚለው?

 

የበርካታ የማሕበረሰብ ድረ-ገፆች ውስጥ በአብይ ጉዳይነት አነጋጋሪ የሆነው የኃይሌ ገለፃ ግዙፍ እንዲሆን ያደረገው የራሱ የኃይሌ ስብዕና ነው። የዚህች ሀገር ብርቅዬ (Icon)ኪሚባሉት ሠዎች መካከል በዋናነት የሚጠራ ስለሆነ ነው። ዝነኛ ነው። ዝና ደግሞ ነጃሳ ናት ብሏል በአሉ ግርማ። ዝነኛ ሰው ለቃሉ መጠንቀቅ አለበት። ለድርጊቱ መጠንቀቅ አለበት። ዝነኝነቱ የመነጋገሪያ አጀንዳ ያስከፍታልና ነው። ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም እንዳሉት ኃይሌ ይቅርታ መጠየቅ ያለበት ይመስለኛል። ይህ ንግግሩ ከዚህ ታላቅ ስብዕናው ጋር አብሮ መጓዝ የለበትም። መራገፍ አለበት።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
1054 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us