ለተፈጥሮ ጥበቃ ጀግናው በባሌ የቆመ መታሰቢያ

Wednesday, 16 March 2016 13:27

 

ከሄኖክ ስዩም

ብዙዎች ሰብዕናውን ከተፈጥሮ ፍቅሩ ነጥለው ማየት ይሳናቸዋል። ቢኒያም አድማሱ በአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች፣ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ቤተሰብና በጥብቅ የማህበረሰብ ስፍራዎችና በብሔራዊ ፓርኮቻችን ማህበረሰብ ዘንድ በእጅጉ ይታወቃል።

በዚህ ምድር ላይ መኖር የቻለው 33 ዓመታትን ነው። ከአስር ያላነሱትን ደግሞ ስለተፈጥሮ ሲጮህ፣ ሲታመም፣ ሲጎዳ ኖሯል። በ1974 ዓ.ም. በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በራፍ በዶዶላ ከተማ ተወለደ። ለተፈጥሮ ቅርብ ሆኖ የማደጉ ምስጢርም አስደናቂውን ስነ ምህዳር ከልጅነቱ እያየ መምጣቱና የስነ ምህዳርን ለውጥና የተፈጥሮ ጥፋትን በቅርበት መመልከት መቻሉ ይመስለኛል።

ቢኒያም ወጣትነቱ ለተፈጥሮ ጥበቃ አሳልፎ የሰጠ ጀግና ነው። ከምንም በላይ ጉዳዩ የአካባቢ ጥበቃ ነው። በጎሳና በዘር ስላልተደራጁ፣ በእምነት በድንበር ስላልተከለሉ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ይወግናል። እጽዋትን በስስት እየተመለከተ ስለ ህልውናቸው ይጨነቃል።

የዛሬ ዓመት በተፈጥሮ ፍቅር ሞተ።

ነገሩ እንዲህ ነው። ቢኒያም በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ በአቡነ ዬሴፍ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ፣ በመንዝ ጓሳ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራና በአርሲ ተራሮች እንደሰራው የዘላቂ ቱሪዝም ልማትና የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ ሁሉ በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክም ተመሳሳይ ስራ እየሰራ የነበረበት ወቅት ነበር።

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በእሳት ሲወድም ቀድሞ ጮኽ፣ ጮኽቱ እንደያሪኮ ግንብ በተአምር የሚያፈርሰው ነገር ባይኖር እያየሁ ባሌ ከሚወድም እየሞትኩ የቻልኩትን ማድረግ ብሎ ጸና። የዱር እንስሳቱን መክሰምና መንደድ፣ በመዓዛቸው የሚፈወስባቸውን እጽዋት ከሰል መሆን መቀበል አልቻለም።

ቀኑ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም ነበር፤ እሳቱ የበረታው ቱሉቄ በሚባለው ቦታ ነው። ድንገት ጋብ አለ ተብሎ ያገረሸው እሳት በቱሉቄ ተፈጥሮን ማውደም ጀመረ። አምስት የፓርክ ሠራተኞችና ቢኒያም ወደ ስፍራው አቀኑ። ቢኒያም ስፍራው ጋር ሲደርስ መግባትና ማጥፋት አለብን ብሎ ወደ እሳቱ ለመግባት ተገለገለ። ጓዶቹ የቦታው አቀማመጥ የእሳቱ ጉልበትና አካባቢው የነብር መኖሪያ በመሆኑ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ አጢነው እሳቱን ማጥፋት ላንችል መስዕዋት መሆን ነው በሚል አግባብተውት መንገድ ጀመሩ። ይህ ታሪክ ለመታሰቢያው ከታተመው በራሪ ወረቀት የተገኘ ነው።

በመመለስ ላይ እያሉ ይላል ይህ ኩነቱን የሚተርከው ሰነድ፤ በመመለስ ላይ እያሉ ጥቂት ተጉዘው ያ ሰደድ እሳት ያንን ቢኒ የምኖረው ለዚህ ነው የሚልለትን ተፈጥሮ ዶግ አመድ እያደረገው ነበር። ምንም ሳያመነታ 400 ሜትር ወደሚሆነው ገደላማ ስፍራ ወረደ፤ አብረውት የነበሩት የስራ ባልደረቦቹም ተከተሉት። እሳቱን ለማቆም መራወጥ ጀመረ። በንፋስ የታገዘው አስታ ቤኒዚን እንደተርከፈከፈበት ደረቅ የባህር ዛፍ ቅጠል ሲከንፍ መጣ። ከፊሉ ሸሸ፤ ከፊሉ በድንጋይ ቋጥኝ ስር ተሸሸገ። ያ ፈጣን እሳት ወደየትም ሳይሸሽ አለበት ከተፍ ብሎ እንደሚወደው አስታ፣ እንደሚሳሳላቸው ዱር እንስሳት፣ እኔ ለአንቺ ነው የምሞተው እንደሚላት ቀይ ቀበሮ በሰደዱ አቶን ተቃጠለ።

ቢኒያም አድማሱ ለተፈጥሮ ፍቅር ሲል መስዕዋት ከሆነ አንድ ዓመት ተቆጥሯል። በርግጥም ዛሬ ከጥላቻ፣ ከጎሰኝነት፣ ከሌብነትና ከራስ ወዳድነት ፈቅ ያለ ይህንን መሳይ የትውልድ ጌጥ ማጣት ምንም ተደርጎ ሊታሰብ ይችል ይሆናል። ቢኒ ለተፈጥሮ ፍቅር ባልተሰጡ ስልጡኖች መካከል የሚኖር በመሆኑ ያጣው ነገር ቢኖርም ስራው ግን ህያው ነው። ለአካባቢ ጥበቃ መቆርቆር እስከምን ድረስ ለሚሉ መልስ የሆነ ተግባር ያከናወነ ብሔራዊ ጀግና፤

ለዚህ ጀግና መታሰቢያ ይሆን ዘንድ መስዕዋት በሆነበት በቱሉቄ አካባቢ በፍራንክፈርት ዞሎጂካል ሶሳይቲ አማካኝነት ታሪኩን የሚገልጽ መታሰቢያ ቆሞለታል። ወዳጆቹና ቤተሰቦቹ ደግሞ በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መግቢያ በዲንሾ የመታሰቢያ ሐውልት አሰርተው ያቆሙለት ሲሆን ሐውልቱ ህይወቱን መስዕዋት ባደረገበት ዓመቱ ማለትም መጋቢት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በድምቀት ተመርቋል።

የአካባቢው ህዝብ፣ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች፣ ጓደኞቹና ቤተሰቦቹ በተገኙበት፤ የባሌ ብሔራዊ ፓርክ ሰራተኞች ባደመቁት ሥነ-ሥርዓት የተመረቀው ይህ የመታሰቢያ ሐውልት ቢኒያም አድማሱ በስራ ላይ እያለ የነበረውን ገጽታ የሚያሳይ የራሱ ምስልና የሚወዳት ቀይ ቀበሮ የተካተቱበት ነው።

የቢኒያም አድማሱን ስም ለማኖር እንደእሱ ለተፈጥሮ ዋጋ የሚሰጡ ወገኖችን ለመዘከር በስሙ ሽልማትን የሚሰጥ የመታሰቢያ ማህበርና ፋውንዴሽን ለማቋቋም እንቅስቀሴ መደረጉን በመታሰቢያ ሐውልት ምረቃው ወቅት የዝግጅቱ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ቤዛ አበበሸዋ ገልጸዋል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
672 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us