ስለ አዕምሮ ሕሙማን የኢትዮጵያ ሕግ ምን ይላል?

Wednesday, 23 March 2016 12:14

 

ታደሰ ካሳ

(ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ኮሙኒኬሽን ማስተባበሪያ)

ሰላም ጤና ይስጥልን ውድ የዚህ ፅሁፍ አንባቢያን፤ ስለ ሀገራችን ህግ ብዙ ታውቁ ይሆናል የሚል እምነት አለን። የምታውቁት እንዳለ ሆኖ በዛሬው ፅሁፋችን ግን የህግ ባለሙያ በመጋበዝ አንድ ሰው የአዕምሮ ህመምተኛ ነው የሚባለው መቼ ነው? ስለ አዕምሮ ህሙማን የኢትዮጵያ ህግ ምን ይላል? የሚሉ እና ሌሎች ጥያቄዎችን ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ዐቃቢ ህግ ባለሙያ ለሆኑት አቶ ዮናስ ዋሲሁን አቅርበን ዝርዝር ምላሾችን አግኝተናል፤ በዚህም ብዙ ቁም-ነገሮችን እንደምትጨብጡበት እንተማመናለን። የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የህግ ባለሙያው ላደረጉልን ቀና ትብብር በእናንተ በአንባቢያን ስም ከልብ እያመሰገን ወደ ዋናው ጉዳያችን ልንገባ ነው ተከታተሉን።

አንድ ሰው የአዕምሮ ህመምተኛ ነው የሚባለው መቼ ነው? በዋናነት ከአዕምሮ ጤና ጉድለት ጋር በተያያዘ በሕመም ምክንያት አንድ ሰው ችሎታውን አጣ የሚባለው ከመቼ ጀምሮ ነው? ምን ይመስላል? ችሎታ ማጣቱ የሚያበቃው መቼ ነው? በዚህ ሰው የተሰሩ ሥራዎች ከፍትሐብሔርና ከወንጀል ሕግ አንጻር ያላቸው ውጤት ምንድን ነው? የሚለውን ከህግ አንፃር እንዲያብራሩልን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የህግ ጥናትና ማርቀቅ እንዲሁም ማስረፅ ዳይሬክቶሬት ዐቃቢ ህግ የሆኑትን አቶ ዮናስ ዋሲሁንን ጠይቀናቸዋል። ታዲያ እሳቸው እንደሚሉት በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ በአንቀጽ 192 እና 196 (1) ላይ አንደተገለጸው ማንኛውም የተፈጥሮ ሰው ችሎታ ያለው መሆኑ በሕጉ ማዕቀፍ ውስጥ በመርህ ደረጃ የተቀመጠ ሲሆን በህግ የተለየ ክልከላ የተደረገበት ሰው ካልሆነ በስተቀር በመብቱ የመጠቀም ግዴታውን በመወጣት ማንኛውንም የማሕበራዊ ኑሮውን ተግባር ለመፈጸም ችሎታ እንዳለው ተደንግጓል። ችሎታ ማለት በሕግ ፊት ዋጋ የሚያወጣ ተግባር ለማከናወን ያለውን ብቃት የሚያመለክት አነጋገር ነው። በሕግ ፊት ዋጋ የሚያወጣ ተግባር ማለት ደግሞ ውል መዋዋል፣ጋብቻ መመስረት፣ ከሞግዚት አስተዳደር ነጻ ወጥቶ የራስን ንብረት በራስ ማስተዳደር መቻል፣ ኑዛዜ መናዘዝንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ማከናወንን ያጠቃልላል። የችሎታ ማጣትም ከእድሜ፣ ከሕመምና ከፍርድ ይመነጫል ዐቃቢ ህግ ዮናስ ዋሲሁን እንዳሉት።

 ስለ አዕምሮ ሕሙማን የኢትዮጵያ ሕግ ምን ይላል? ስንልም ጠይቀናቸው ዐቃቢ ሕግ አቶ ዮናስ እንዲህ ብለዋል በፍ/ሕ/ቁ 341 እና 347 ላይ የአዕምሮ ሕመሙ በግልጽ የታወቀ እና ያልታወቀ ብሎ በሁለት ከፍሎ የሚያያቸው ሲሆን በግልጽ የታወቀ የአዕምሮ ህመም ሆኖ በሕግ የሚቆጠረው የአዕምሮ ጉድለት ያለበት ሰው በሆስፒታል ውስጥ ወይም በአንድ የአዕምሮ ህመምተኞች መኖሪ ቦታ አለያም በአንድ የጤና ጥበቃ ተቋም ውስጥ ተዘግቶበት በዚህ በተዘጋበት ቦታ እስከሚቆይበት ጊዜ ነው። ከሁለት  ሺህ ነዋሪች በላይ በሚኖሩበት በገጠር ቀበሌ ደግሞ አንድ ሰው በቤተ ዘመድ ወይም አብሯቸው በሚኖሩ ሰዎች በኩል በአዕምሮው ሁኔታ ምክንያት የግድ የሚያስፈልግ ተጠባባቂነት የሚደረግለት ሆኖ ሲገኝና ከእርሱ ጋር የሚኖሩት ሰዎች በተባለው ሁኔታ ምክንያት ለመዛወሩ የፈቃድ ወሰን ሰጥተውት ሲገኙ ይህ ሰው ህመሙ በግልጽ እንደታወቀ ሆኖ ይቆጠራል። ህመሙ ግልጽ በሆነበት ጊዜና ቦታ የሠራቸውን ሥራዎች እርሱ ወይም ወኪሎቹ  ወይም ወራሾቹ ሊቃወሟቸው ይችላሉ። ተቃራኒ ማስረጃ ካልቀረበ በስተቀር የእነዚሕ ሰዎች ሥራና ፈቃድ የውለታ ፈራሽነትን የሚያስከትል ጉድለት ያለበት ነው ተብሎ ይገመታል። ስለሆነም ይላሉ ዐቃቢ-ህግ ዮናስ በስህተት ምክንያት ስራዎችንና የውሎችን መፍረስ የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በግልጽ ለታወቀ የአዕምሮ ህመምተኛ በተጨማሪነት ያገለግላሉ። የአዕምሮ ህመምተኛ ከሆነ ሰው ጋር የተደረጉ ውሎች በመፍረሳቸው ምክንያት በቅን ልቦና ሦስተኛ ወገኖች ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ኃላፊ ይሆናሉ። ነገር ግን የሦስተኛ ወገኖች ቅን ልቦና አለመኖር ከተረጋገጠ ወይም የአዕምሮ ህመምተኛ የሆነው ሰው ባለበት አንድ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ወይም አዋሳኝ ቀበሌ ውስጥ የሚኖሩ መሆናቸው የተገለጸ ከሆነ በቅን ልቦና ያላደረጉት ለመሆናቸው በቂ ማስረጃ ይሆናል እንደ ዐቃቢ ህግ ዮናስ ገለፃ።

እንደ ዐቃቢ ህግ ባለሙያው ንግግር የአዕምሮ ህመምተኛ መሆኑ በግልጽ ያልታወቀ ሰው የፈፀማቸው ማናቸውም በሕግ ፊት ዋጋ የሚያወጡ ተግባሮች የአዕምሮ ጉድለቱን ብቻ መሰረት በማድረግ ሊሻሩ አይችሉም። ነገር ግን የውል አድራጊው የአዕምሮ ጉድለት ከተደረገው የውል ቃል የተነሳ የሚታወቅ ከሆነ ግን ህመሙ በግልጽ እንደታወቀ ሰው ተቆጥሮ ውሉ በእርሱም ሆነ በሌሎቹ እንዲፈርስ መጠየቅ በሚችሉ አካላት አመልካችነት ፈራሽ  ሊሆን ችላል። የአዕምሮ ህመምተኛነቱ በግልጽ ለታወቀም ሆነ ላልታወቀ ሰው ከውል ውጭ ኃለፊነትና ያለአግባብ የመበልፀግ ሕግ ድንጋጌዎች ለጤናማ ሰው እንዳለው ኃላፊነት ነው ።

በፍርድ የሚደረግ ክልከላ በተመለከተ እንዲያብራሩልን ዐቃቢ ህግ ዮናስን ጠይቀናቸው እንዲህ ሲሉ ነግረውናል።በፍርድሂደት ለጤናውና ለጥቅሙ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የእምሮ ታማሚው ሰው እንዲከለከል (እንዲጠበቅ) ዳኞች ፍርድ ሊሰጡ ይችላሉ ። እንደዚሁም በግልጽ ለታወቁ  የአዕምሮ ህመምተኞች የመከልከል ፍርድ ሊሰጥ ይችላል። ዳኞች ስለ አንድ ሰው መከልከል ፍርዳቸውን ሲሰጡ በሚሰጡት ውሳኔ የአዕምሮ ህመሙ የጀመረው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው በማለት ውሳኔ ሊሰጡ ይችላሉ። ነገር ግን በዳኞች ፍርድ የተቆረጠው ቀን ስለ ክልከላው ከቀረበው ጥያቄ በፊት ከሁለት ዓመት የበለጠ ጊዜ ሊሆን አይችልም። ስለ ክልከላው ውሳኔ እንዲሰጥ የአዕምሮ ህመምተኛ በሆነው ሰው በራሱ፣ ከባልና ሚስት ጤነኛው ወይም ጤነኛዋ፣ ከጋብቻ ወይም ከሥጋ ዘመዶች አንዱ ወይም ዐቃቤ ሕግ  ሊጠይቅ ይችላል። ዳኞች በሰጡት ፍርድ ላይ አቤቱታ የማቅረብ መብት የአላቸውም እነዚሁ ሰዎች ናቸው። በፍርድ የተከለከለ ሰው አካለ መጠን እንደአላደረሰ ልጅ ሰውነቱና ንብረቱ ይጠበቃል፣ ሞግዚትና አሳዳሪ የሚሾሙለትም ዳኞች ናቸው የፍትህ ሚኒስቴር ዐቃቢ ህግ ዮናስ ዋሲሁን እንደነገሩን። 

ዐቃቢ ህግ ባለሙያው አክለውም ሞግዚት ያደረጋቸው የኪራይ ውሎች፣ በቤተዘመድ ምክር ጉባኤ ፈቃድ ካልተደረጉ በስተቀር የተከለከለው ሰው ችሎታ የማጣቱ ሁኔታ ከቀረ በኋላ የሚያስገድዱት እስከ 3 ዓመት ብቻ ነው። የተከለከለው ሰው ክልከላው በፍርድ ከተነገረ ኑዛዜ ማድረግ አይችልም። ከመከልከሉ በፊት ያደረገው  ኑዛዜ ይፀናል። ነገር ግን የኑዛዜው ድንጋጌዎች ለርትዕ ነገር ለዳኞቹ ተቃራኒ መስለው ከታዩአቸው፣ የተናዘዘው ሰው የጤና ሁኔታው እንዲናዘዝ ያስደረገው መስሎ የታያቸው ከሆነ ኑዛዜውን በሙሉ ወይም በከፊል ፈራሽ ሊያደርጉት ይችላሉ ይላሉ የህግ ባለሙያው።

በፍርድ የተከለከለ የአዕምሮ ህመምተኛ ሰው በፍርድ ቤት ካልተፈቀደለት በቀር የጋብቻ ውል መዋዋል አይችልም። ጥያቄውንም ራሱ አዕምሮ ህመምተኛው ወይም አሳዳሪው ሊያቀርብ ይችላል። ያለ ዳኞች ፈቃድ ግን ጋብቻው የተመሰረተ ከሆነ ግን ማንኛውም ያገባኛል የሚል ሰው ጋብቻው እንዲፈርስ  ሊጠይቅ ይችላል።

የተከለከለ ሰው የፈጸማቸውንና ከስልጣኑ በላይ የሆኑትን ሥራዎች አካለመጠን ያላደረሰ ልጅ ያደረጋቸውን ሥራዎች ለመቃወም በሚችልበት አኳኋን መቃወም ይችላል። አዕምሮው መለስ ባለበት (ወደ ጤነኝነት መንፈስ በመጣ) ጊዜ የፈጸማቸው ውሎች ናቸው በማለት የእነዚህን ውሎች ውጤት ማጽደቅ አይችሉም ።

የተከለከለ ሰው ችሎታ የሌለው መሆኑን ከማያውቅ ቅን ልቦና ካለው ሰው ጋር ውል ያደረገ እንደሆነ ውሉ በመፍረሱ ምክንያት በዚህ ሰው ላይ ለሚደርው ጉዳት ኃላፊ የሚሆነው አሳዳሪው ነው። ነገር ግን የፍርድ ቤት መዝገብ ሹም የተከለከለውን ሰው ለመመዝገብ በተዘጋጀው መዝገብ ላይ ሳይመዘግበው የቀረ እንደሆነ ወይም ተዋዋዩን የምዝገባ መዝገቡን እንዳያይ የከለከለ እንደሆነ ኃላፊነቱ ከአሳዳሪው ወደ ፍርድ ቤት መዝገብ ሹሙ ይዞራል ማለት ነው እንደ ፍትህ ሚኒስቴር ዐቃቢ ህግ ዮናስ ዋሲሁን አባባል።

ሌላው ጉዳይ ደግሞ በፍርድ መከልከል ቀሪ የሚሆነው ስለ ክልከላ የተሰጠው ፍርድ ሲሻር ነው ያሉት ዐቃ ህግ ዮናስ በማናቸውም ጊዜ ፍርዱ ይሻር በማለት መጠየቅ የሚችሉት የአዕምሮ ጉድለት ካለበት ሰው በቀር ፍርድ እንዲሰጥ ለመጠየቅ የሚችሉ ሰዎች ናቸው ። የተከለከለው ሰው ንብረቱን መምራትና ማስተዳደር የሚችል ከሆነ እና ያስከለከሉት ምክንያቶች የቀሩ ከሆኑ ፍርድ ቤቱ የክልከላውን ውሳኔ ቀሪ ማድረግ አለባቸው። የክልከላው ውሳኔ መቅረት ውጤቱ አካለ መጠን ያላደረሰ ልጅ ከሞግዚት አስተዳደር መውጣት ያለው ውጤት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን በንፅፅር ደረጃ አንድ መሆናቸውን አስቀምጠዋል።

ከወንጀል ህግ አንጻር የአዕምሮ ጤና ችግር ያለበት ሰው ድርጊት በህግ ማዕቀፍ እንዴት ይስተናገዳል ስንልም ገለፃ እንዲያደርጉልን ባለሙያውን ጠይቀናቸው ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል።

በወንጀል ሕጋችን ውስጥ በግልጽ ርዕስ ይዞ የተቀመጠ ድንጋጌ ባይኖርም አንቀጽ 48 እና 49 በማየት መረዳት የሚቻለው እነዚህ ድንጋጌዎች የአእምሮ ጤና ችግር ያለበትን ሰው በተመለከተ የተደነገጉ መሆኑን ነው። እንደ ወንጀል ሕጉ አገላለጽ የአእምሮ ጤና ጉድለት አለበት ተብሎ የሚታሰበው ሰው በእድሜ፣ በሕመም፣ ባልተለመደ የእድገት መዘግየት ፣ጥልቅ በሆነ የአዕምሮ መገንዘብ ወይም የማመዛዘን ችሎታ መቃወስ ወይም በማናቸውም ሌላ ተመሳሳይ ሥነ ሕይወታዊ ምክንያቶች የወንጀል ድርጊት በሚፈፅምበት ጊዜ የድርጊቱን አይነት ወይም ውጤት ለመገንዘብ ካልቻለ አለያም በዚሁ ግንዛቤ መሰረት ራሱን ለመቆጣጠር በፍጹም ያልቻለ ከሆነ ፍጹም ኢ-ኃላፊ ስለሚሆን አይቀጣም። ነገር ግን ከላይ በተጠቀሰው የሥነ- ሕይወታዊ ችግር ምክንያት የወንጀል ድርጊት በሚፈፅምበት ጊዜ የድርጊቱን አይነት ወይም ውጤት በከፊል ለመገንዘብ ካልቻለ አለያም በዚሁ ግንዛቤ መሰረት ራሱን ለመቆጣጠር ያልቻለው በከፊል ከሆነ ከፊል ኃላፊነት ይኖርበታል። ከፊል ኃላፊነት አለበት ስንል ፍርድ ቤቱ ከፊል ኢ-ኃላፊ የሆነውን ሰው ቅጣት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 180 መሰረት ከመነሻ ቅጣቱ ዝቅ አድርጎ ወይም ሌላ ቀለል ያለ ቅጣት ይቀጣል ለማለት ያክል እንጂ ሙሉ ለሙሉ ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ ሊሆን አይችልም ። ከመነሻ ቅጣቱ ዝቅ አድርጎ ፍርድ ቤቱ ይህንን ተከሳሽ ይቀጣዋል ስንል ቅጣት ለመወሰን በቅጣት ፍቃድ ሥልጣኑ ውስጥ ያለውን መነሻ ቅጣት እንጅ በህጉ ላይ የተቀመጠውን የወንጀሉን መነሻ ቅጣት ማለት አይደለም። ፍርድ ቤቱም ከወንጀሉ መነሻ ቅጣት ዝቅ ሊል እንደማይችል የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 180 ያስረዳል ሲሉ ገልፀውልናል።

በሌላ በኩልም ይላሉ ዐቃ ህግ ዮናስ ዋሲሁን በአዕምሮ ጤና ምክንያት ነጻ የተባለ ሰው እንደማንኛውም ጤነኛ ሰው ሁሉ በነጻ ወደቤቱ አይመለስም። ይልቁንም በአንጻሩ ተስማሚ የሆኑ የሕክምና ወይም የጥበቃ ጥንቃቄዎች እንዲደረጉለት ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ጭምር ይሰጣል እንጂ። እነዚህ ጥንቃቄዎች ተስማሚ በሆነ ተቋም አንዲቀመጥ ማዘዝ ወይም ለሕክምና ወደ ሆስፒታል እንዲገባ የሚሰጥ ትዕዛዝ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም የአዕምሮ ህሙማን ትክክለኛ ህመምተኛ ስለመሆናቸው ለማረጋገጥ የሚቻለው አንድ በህክምና ተቋም ተመርምረው ማረጋገጫ ሲሰጥ መሆኑ አያተያይቅም። ታዲያ በሀገራችን ይህን ለማረጋገጥ የሚችለው እስካሁን ጊዜ ድረስ አንድ ሆስፒታል መሆኑ በሚኖረው የስራ መደራረብ ምክንያት ህመምተኞች ፈጣን አገልግሎት ማግኘት እንዳይችሉ ምክንያት ይሆናልና ለምን ተጨማሪ የህክምና ተቋማት ተከፍተው አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ሁኔታ አይፈጠርም? ሰላም

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
908 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us